ጥበብ በታሪክ ገፅ

የባላገሩ ደረጃዎች

ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎች በክፍል እየተሸነሸኑ ወይም በቀዳሚው ክፍል የተነሳው ሐሳብ በሌላኛው ክፍል እየተደገመ መቀጠሉ እንግዳ ነገር አይደለም። የተወደዱ እና በዛ ያለ ተመልካች ያገኙ የፊልም ሥራዎች በክፍል ሁለት ህልውናቸው ቀጥሏል። አንባቢ የበዛላቸው፣ ገዢ የተበራከተላቸው መጻሕፍት ቀጣይ ክፍል ተጽፎላቸው ለአንባቢ ደርሰዋል።

አብርሐም ወልዴ

አብዛኛውን ጊዜ ሳይሆን ሁል ጊዜ ለማለት በሚቻል ሁኔታ ተከታዮቹ ክፍሎች የሚሰሩት በግፊት ነው። ግፊቱ የተመልካች እና የገቢ ነው። የጥበቡ ታዳሚ የቀደመውን ሥራ አብዝቶ ሲወድ ቢቀጥልለት፣ አበቃ በተባለበት ምእራፍ ባይቋጭ ይመኛል። በዚህ ጊዜ የጥበብ ከዋኙ ተከታዩን ክፍል ለመስራት ይገደዳል ወይም ተገደድኩ ይላል። ሁለተኛው ግፊት የገንዘብ ነው። የቀዳሚው ስራ ገቢ ማሻቀብ ሲያጓጓ- ገቢውን ለማስቀጠል ክፍል ሁለት ይሰራለታል።

በዛሬው የዘመን እና ዘፈን ዝግጅታችን በአርቲስት አብርሃም ወልዴ የተሰሩትን “ባላገሩ” የሚሉ ዘፈኖች በጥቂቱ ለማንሳት እንሞክራለን። ከአቦነሽ አድነው እስከ ዳዊት ጽጌ የተሰሩት ባላገሩዎች ቁጥር 4 ላይ ደርሰዋል። 5 ድምጻዊያንም ተሳትፈውባቸዋል። ዘፈኖቹ ላይ የወፍ በረር ዳሰሳ እያደረግን ልንቆይ ነው። አብራችቡን ዝለቁእንደሌሎቹ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ሁሉ ክፍል የተሰራላቸው ወይም ከቀዳሚ ስራው የቀጠሉ አሉ። አቤል ሙሉጌታ “ገዳም ገባሽ አሉ” የተሰኘ ዘፈኑ በሕዝብ ዘንድ እንዲታወቅ ያስቻለው የበኩር ዘፈኑ ነው። ፍቅርን ሸሽታ ገዳም ለመግባት መንገድ የጀመረችን ፍቅረኛውን የሚሞግት ገጸ ባህርይን ታሪክ የሚያስቃኘው ዘፈኑ ቀጣይ ክፍል ተሰርቶለታል።

“ገዳም ገባሽ አሉ” የሚሉት ሁለቱ የአቤል ዘፈኖች በራሳቸው መቆም የማይችሉ አይደሉም። የቀደመውን ዘፈን ያልሰማ ተከታዩን ቢያደምጥ፣ ወይም የማድመጥ ቅደም ተከተሉን ከሁለተኛው ቢጀምር የሚቀርበት ነገር አይኖርም። ሁለቱም ጥሩ የሚባሉ ናቸው።

ከዘፈን ግጥሞች ጋር በተያያዘ የቀደመውን ተከትሎ የተሰራ ዘፈን ያለው ድምጻዊ ጌትሽ ማሞ ነው። “እንከባበር” በሚለው ነጠላ ዜማ ተቀባይነት ያገኘው ጌትሽ የመጀመሪያውን ይዘት ያልለቀቀ ተከታይ ዘፈን ዘፍኖለታል። ሁለቱም ዘፈኖች ላይ ለአዚያሚው ወይም ለዘፋኙ ግጥም የሚሰጥ ሰው (ተቀበል) ባይ አለ። ሁለቱም ዘፈኖች ወቅታዊውን የሐገራችንን ሁኔታ እንዲያሳዩ ተደርገው ተሰርተዋል። ጥሩ ተቀባይነትም አግኝተዋል። ከላይ እንዳነሳነው ለየብቻቸው ቢደመጡ ወይም ቅደምተከተላቸው ተዛብቶ ለጆሮ ቢደርሱ አያጎድሉም።

አብርሃም ወልዴ ከሁሉም ሙያዎቹ አስቀድሞ ከሕዝብ ጋር የተተዋወቀው በራዲዮ ድራማ ነው። ማኅበራዊ ሕጸጾችን የሚነቅሱ አዝናኝ ጭውውቶችን እየፃፈ ከሞክሼ የሰፈሩ ልጅ ጋር ይተውናቸው ነበር። ብዙዎች በአሳቂ (ኮሜዲያን) ነት ብቃቱ የተዋወቁት ብላቴና ሌሎች ክህሎቶቹንም ለሕዝብ ዕያሳየ ቀጠለ። የዘፈን ግጥም ይጽፋል፣ ዜማ ይሰራል፣ የዘፈን ቪድዮዎችን ያዘጋጃል (ዳይሬክት ያደርጋል)፣ ሁለገብ ነው።

ሁለቱ አብርሃሞች በሚል ከአብርሃም አስመላሽ ጋር ኢትዮጵያ ራዲዮ ላይ ስራውን የጀመረው አብርሃም አስመላሽ አብዛኛው ትኩረቱ ሙያውን ማሳደጉ ላይ ነበር። በስራው ውጤት እና ሂደት የሚያገኘውን የመንፈስ እርካታ እና ደስታ እንጂ ክፍያውን እምብዛም እንደማያስብ ያስታውሳል።

ባላገሩ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የመጣበትን አጋጣሚ ባስታወሰበት ቃለ መጠይቁ እንዲህ ይላል።

“ከተወለድኩበት ፍቼ ወደ አዲስ አበባ እየተጓዝን እያለ መንገድ ላይ መኪና ተበላሸ። በብልሽቱ ምክንያት መንገድ ላይ ተጉላላን። ጊዜው የበዓል ሰሞን ነው። 1982 ዓ.ም. አካባቢ፣ ሌላ መኪና ባለማግኘታችን እዚያው የብልሽቱ ቦታ ልናድር ሆነ። በወቅቱ ከሩቅ የተመለከቱን ባላገሮች ገስግሰው ያለንበት ቦታ ደረሱ። አመጣጣቸው ያስፈራ ነበር። አንዳች የሚፈልጉትን ነገር ሊጠይቁን ወይም ሊለምኑን መስሎኝ ነበር። ነገር ግን አልነበረም። እንደዛ ፈጥነው እኛ ጋር የደረሱት መንገድ ላይ እንዳናድር እኔ ቤት እደሩ ብለው ተሻምተው ሊወስዱን ነበር። ያንጊዜ ነው የባላገሩ ደግነት በውስጤ ያደረው። ወዲያው የትኬቱ ጀርባ ላይ ማስታወሻ ጻፍኩ”

በዚህ ሁኔታ የተጠነሰሰው የባለ ሐገር ስራ በአውቶብስ ትኬት ጀርባ እንደዋዛ ተጽፎ አልቀረም። እስካሁን 4 ዘፈን ወጥቶታል። ድርጅቶቹም፣ የዘፈን ተረሰጥኦ ውድድሩም፣ በአጠቃላይ አብርሃም ያለባቸው ቦታዎች ሁሉ ባለ ሐገሩ የሚሉ ናቸው። ባለ ርስትነትን ባለ ሐገርነትን የሚያስታውሱ ናቸው።

ባለ ሐገሩ ቁጥር አንድን የተጫወተችው ድምጻዊት አቦነሽ አድነው ነች። የመጀመሪያዋ እና ብቸኛዋ ሴት ድምጻዊት ላይ የሚገኙት የአብርሃም ስንኞች የባለ ሐገሩን ናፍቆት የሚያሳዩ እና አንዴትነቱን የሚጠይቁ ናቸው። አማን አይደለም ወይ? እያሉ ይጠይቃሉ። የደጉ ባላገር ናፋቆት የሚያስጮሃት፣ ብረሪ የሚያስብላት ገጸ ባህርይ ተስላለች። አትከልክሉኝ ልሂድ ባይ ታቀነቅናለች።

አቦነሽ አድነው

አንተ ባትሰጠው እሸቱን ወተቱን

አልቆ አልነበረም ወይ ከተሜማ እለቱን

በዚህ ዘፈን ውስጥ ያለችው ገጸ ባህርይ የገጠሩን ኑሮ አሳምራ ታውቃለች። የከተሜ ኑሮ ተደጋጋሚነት፣ አርቴፊሻልነት ሰልችቷታል። ያለ ወቅሮዋ የናፈቃት ባላገር ምነው ደህና አይደለም እንዴ እንዲህ የናፈቀኝ ቢያስብላትም መሄድን አጥብቃ ትሻለች።

ባገራችን ወግ በባህል ኑሪ

ከተሜ ሄደሽ ብር አትደምሪ

ባላገር ሄደሽ በእምነትሽ ኑሪ

ቤተስኪያን ስመሽ ወንጌል ተማሪ

ሰፌዱን ሰፍተሸ ገብስ አበጥሪ

ጎተራ ሞልተሸ እህል ስፈሪ

ትላለች። በአብዛኛዎቹ የዘፈኑ ስንኞች የባላገሩን የአኗኗር ዘይቤ ያነሳል። በተለምዶ ያልሰለጠነ የምንለውን የገጠር ኑሮ ናፈቀኝ እያለ ከከተሜነት የሚበልጥ መሆኑን ያስረግጣል።

ነፋሻው አየሩ – ክረምትና በጋው

ሕይወት እና ኑሮው – መንፈስ እና ጸጋው

ምንጭ እና ቄጠማው – አጋም እና ቀጋው

ሜዳ እና ተራራው – ቆለኛ እና ደጋው

እንዳልተኛ አረገኝ – እንዳልንተራሰው

ጩሂ ጩሂ ይለኛል – ሲናፍቀኝ ያ ሰው

የግጥም እና የዜማ ደራሲው አብርሃም ወልዴ በአቦነሽ አድነው አንድ ያለውን የባላገሩ ጉዞ ሁለት ያለው በደሳለኝ መልኩ ነው። ደሳለኝ በተጫወተው ባላገሩ እንደቀደመው ሁሉ የባላገሩ መወድስ አለበት። ዋናው ርዕሰ ጉዳይ ባላገር ይሁን እንጂ፣ የሐሳቡ ማጠንጠኛ ባላገር ይሁን እንጂ፣ የሐሳብ ልዩነት አለው።

በቀደመው የአቦነሽ ዘፈን ላይ እንዳየነው የባላገሩን ናፍቆት እና ደህንነት አይጠይቅም። የሀገሬ ልጆች መከራ አይዩብኝ፣ ደስታ አይራቃቸው፣ ችግር እንዳይጎበኛቸው፣… የሚል ገጸ ባህርይ ያንጎራጉራል።

ደሳለኝ መልኩ

ጤና ፍቅር ይሁን ሀገሩ

ባለ ዜናው ባለ ክብሩ

ባላገሩ ባለ ሐገሩ

ይሕ የኔ ባላገር የሰው የማይነካ

ጦሙን እንዳያፈርስ ነው የሞተው ለካ

የልጆቹን ወዳጅ ጥጆቹን ሳይነካ

ከእንስሶቹ በፊት ነው የሞተው ለካ

አብዛኛው ተማጽኖውን ለአምላክ የሚሰጠው በዘፈኑ ውስጥ ያለው ገጸ ባህርይ ጥጋብን፣ ሰላምን፣ ደስታን፣ ፍቅርን፣… ለባለ ሐገሩ ሁሉ የሚመኝ ነው።

ባላገሩ ቁጥር አንድ እና ሁለት በተለያየ ጊዜ “ባላገሩ” የሚለውን ስያሜ ይዘው የወጡ ናቸው። በመካከላቸው የዓመታት ልዩነት አለ። በዚሁ አካሄድ የቀጠለው ቁጥር 3 ከቀደሙት የተለየ መልክ አለው። የመጀመሪያው ልዩነት በሁለት ድምጻዊያን መሰራቱ ነው። ከፊት የተሰሩት ሁለቱ የተዘፈኑት በአንድ ድምጻዊ ነው። ሌላው ተጨማሪ ልዩነት ደግሞ በስመ ጥር ድምጻዊያን መሰራታቸው ነው። የቀደሙት ደሳለኝ መልኩ እና አቦነሽ አድነው በጅማሬ ስራዎቻቸው ላይ የነበሩ ሲሆኑ ሦስትን የተጫወቱት ኤፍሬም እና ጎሳዬ ግን ቀደም ብለው በሕዝብ ዘንድ እውቅና እና ተወዳጅነት አትርፈዋል።

ሁሉም የባላገሩ ዘፈኖች በህዝብ ዘንድ ተወዳጅነት እና ተደማጭነት ያገኙ ቢሆንም በንጽጽር ባላገሩ ቁጥር 3 የበለጠ አድማጭ አግኝቶ ነበር ማለት ይቻላል።

ባላገሩ ቁጥር 3 እንደቀደመው ሁሉ ባላገሩ የሚለውን ሐሳብ ይዞ ቢነሳም በዚህኛውም ላይ ልዩ መልክ ሊሰጠው ጥሯል። ተሳክቶለታልም።


ኤፍሬም ታምሩ እና ጎሳዬ ተስፋዬ በባላገሩ ዘፈን ላይ

እቤት ካሉት ይልቅ- የጠፉት በጎቿን

ኢትዮጵያም እንዳምላክ- ናፍቃለች ልጆቿን

በዚህ ዘፈን ውስጥ የእናት ጥሪ ይሰማል። በዓለማቱ የተበተኑ ልጆቿን የምትጣራ እናት ድምጽ ይሰማል።

እንደሰው በባህር- እንደ አሳ በምድር

ሆነን እንዳንቀር- አምላክ ስጠን ፍቅር

ጊዜው የኢትዮጵያ ሚሊንየም ሰሞን በመሆኑ የሰመረ መልእክት ነበር።

እስክሁን የተመለከትናቸው ዘፈኖች ውስጥ በሙሉ ባላገር አለ። ሐገር እና የሐገር ሰው ሐሳቦች አሉ። ተደጋጋሚነት ግን የላቸውም። ይህንን ተለያይነት እንደጠበቀ የዘለቀው ገጣሚ እና የዜማ ደራሲ አብርሃም ወልዴ የመጨረሻውን ባላገሩ ዘፈን የሰራው ከዳዊት ጽጌ ጋር ነው። ከወጣቱ ዳዊት ጋር ባለ ሐገሩን በተመለከቱበት ሌላ መነጽር ደግሞ ምን ልሁን ይሉናል።

ዳዊት ጽጌ

ቴዎድሮስ ቢጋደል ምኒልክ ቢቀላ

ምን ጉዳይ አላቸው ካገራቸው ሌላ

እምዬ ምኒልክ ደጃዝማች ገረሱ

ባንቺ ቀልድ አያውቁም ማን ሊነካሽ እሱ

ያ በላይ ዘለቀ ባልቻ አብዲሳ አጋ

ጀግኖችሽ እያሉ ማን ሊደርስ አንቺ ጋ

የሐገሪቱንም፣ የፖለቲካውንም መንፈስ በደምሳሳው ለተመለከተ የዜማ መፍትሔ የሚያቀርብ ዘፈን ነው። ጀግኖቹን ከየማእዘኑ ሲጠራ ምን ማለት እንደፈለገ መረዳት ከባድ አይደለም። የዘመኑን እና የግጥሙን መንፈስ ተንተርሰን

ተቃቃሩ ብለህ ደስ እንዳይልህ ጠላት

ያው ላመል ነው እንጂ ማን ቀልድ ያውቃል በናት

የሚለውን ስንኝ ስንጨምርበት መልእክቱ ግልጽ ይሆናል። አጭር ምልከታችንን በተከታዮቹ የዘፈኑ ስንኞች እንደምድም

ምን ችግር ቢገጥመው ባላገር

ተስፋ አይቆርጥም ከቶ ስላገር

ይማከር ሰክኖ ይነጋገር

ይጥፋልን ችግር ብሎ ነገር

አንድ ይሁን ይፋቀር ልባችን

ካፈሩ ሰው ነው ገንዘባችን

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top