ታዛ ስፖርት

የመጀመርያዋ

እንስቶች ብዙ ሰው በተሰበሰበበ ኳስ ለማጫወት ዳኛ ሆነው ወደ ሜዳ መግባታቸው ያልተለመደ ነበር። ተመልካቹም ሆነ ተጫዋቹ ውሳኔያቸው ላይ እምነት አልነበረውም። ዛሬ ሴቶች ወንዶችን ከማጫወት አልፈው በኢንተርናሽናል ውድድር ላይ ትላልቅ ጨዋታዎችን በመምራት የሀገር ስም ከማስጠራታቸውም በተጨማሪ ለሌሎች እንስቶች አርአያ እስከመሆን ደርሰዋል። በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ኢንተርናሽናል በመሆን በር ከፋቾች ከሆኑት ዳኞች ውስጥ ሊዲያ ታፈሰ ትጠቀሳለች። ሊዲያ በአፍሪካ መድረክ ግማሽ ፍጻሜ በማጫወት የመጀመርያዋ ናት፤ ከዚያም በላይ ሄዳለች፤ ሀገራችን በዓለም አቀፍ ዳኝነት ትልቁን እርከን የያዘው ስዩም ታረቀኝ ነው፤ ስዩም በዓለም ዋንጫ የመሀል ዳኛ በመሆን በ1970 በሜክሲኮው ውድድር ያጫወተ ነው። ይሄም እስካሁን በትልቁ ውድድር ዓለም ዋንጫ ላይ ያጫወተ ብቸኛው ሰው ያደርገዋል፤ ባለፈው ባምላክ ተሰማ በሩስያ ዓለም ዋንጫ ተመርጦ ቢሄድም የማጫወት ዕድል ስላላገኘ ስዩም ታረቀኝ ባለታሪክነቱን ይዞ ቀጥሏል፤ ይሄን ታሪክ መጋራት የቻለችው ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ሊዲያ ታፈሰ አበበ ናት፤ ከስድስት ወር  በፊት በፈረንሳይ በተካሄደው የሴቶች ዓለም ዋንጫ የመሀል ዳኛ ሆና ሰርታለች፤ ከስዩም ጋር ታሪኩን ብትጋራም ከከሴቶች ግን ብቸኛዋና የመጀመርያዋ ናት። ከሊዲያ ጋር ትንሽ ቆይታ አድርጉ

ከጨዋታ ውጭ

“..ጅማ ላይ ኮርስ ለመጀመሪያ ጊዜ እየወሰድን  በተጓዳኝ ህጻናትን እናጫውት ነበር። እኔ ረዳት ዳኛ ነበርኩ። የማዕዘን ምት ተሰጠ። በእኔ በኩል  ነው የተመታው። የመቺው ቡድን አጥቂ በቴስታ ነቅንቆ አገባ። ተጫዋቾቹ እየተደሰቱ ሳለ ባንዲራ አነሳሁ። ዋናዋ ምንድነው ስትለኝ ኦፍሳይድ ነው አልኳት። የአግቢው ቡድን ተጫዋቾች ከዬት “የመጣች ነች!! ይህቺ! አሉ በኮርና ላይ ኦፍሳይድ እንደሌለ ምንም ትዝ አላለኝም። ዋናዋ ዳኛ ባንድራ ሳነሳ ሌላ ነገር የተፈጠረ መስሏት ነው የሻረችው። ኦፍሳይድ ነው ስላት “ተይው ችግር የለውም” ብላ ወደ ልጆቹ ሄዳ ግቡ ይጸድቃል አለች። ጀማሪ ስትሆን አንዳንድ ነገሮች ይሳሳትሀል። አልጀርስ ላይ ረዳቴ በእጅ ውርወራ ኦፍሳይድ ብላ ባንዲራ አንስታ ነበር። እርሷ ልምድ አላት ግን አንዳንዴ ይዘነጋሀል”

ዝናብ ሽሽት

“..መቀሌ ላይ ረዳት ሆኜ ስሰራ ሀይለኛ ዝናብ መጣ። ያለማቋረጥ ስለሚዘንብ መሀል ዳኛው ጨዋታውን አንደሚያስቆመው ገምቼ ነበር። ኳስ ወደ ውጭ ወጣ። ዳኛው ፊሽካውን ከፍ አድርጎ ሲነፋ በዝናቡ የተነሳ ጨዋታውን ለማቆም እንደሆነ ስለገመትኩ እየሮጥኩኝ ወደ ትሪቡን ሄድኩኝ። እንደደረስኩ መጠለያ ፈልጌ ለመቀመጥ ረጅሙን ደረጃ በፍጥነት እየወጣሁ ሳለ ኮሚሽነሩ ኢንስትራክተር ሽፈራው ነበር። ቁጭ ብሎ ጨዋታውን እያየ ነው። ሮጬ ስመጣ “ሊዲያ ወዴት ነው?” ሲለኝ “ልጠለል ነዋ!!” አልኩት። “የስራ ባልደረቦችሽን ትተሸ ነው የምትጠለይው?” ሲለኝ “ይመጣሉ” ብዬው ዞር ስል ጨዋታው እየተካሄደ ነው። ለካ ዳኛው የነፋው ለእጅ ውርወራ ነበር። ደንግጨ ከተጠለልኩበት ትሪቡን ወርጄ ስሮጥ ህዝቡ እያየ በኔ ደርጊት ተገርሞ ይስቅ ነበር….”

የመጀመሪያ ጨዋታ

“‹…ኮርስ ከወሰድኩ በኋላ የመጀመሪያውን የነጥብ ጨዋታ እንድመራ የተመደብኩት መቀሌ ላይ በፕሮጀክት ውድድር ነው። የሚጫወቱት ሱማሌ ክልልና አዲስ አበባ ነበሩ። ፔናሊቲ ክልል ውስጥ አጥቂው ተጠለፈና ለአዲስ አበባ ሪጎሬ ሰጠሁ። እነዚያ በፍጹም አያሰጥም ብለው ተከራከሩ። እንደውም እንወጣለን ብለው ከሜዳ ለቀው ሄዱ። ነገሩ ግራ አጋባኝ። በመጀመሪያ ጨዋታዬ ተረብሾ በመቋረጡ ቅር አለኝ። በውሳኔዬ ግን አልተጸጸትኩም። ምክኒያቱም እርግጠኛ ነበርኩ። በኋላ ግን ቡድን መሪያቸው አግባብቷቸው ተመለሱ።…”

አንሸከመውም

“….ለመጀመሪ ጊዜ በፕሪመር ሊግ ጨዋታ ያገኘሁት በ1993 ዓ.ም ነበር። ክፍለ-ሀገር ነበር የምኖረው። በአስቸኳይ አዲስ አበባ ትፈለጊያለሽ ተብሎ በአውሮፕላን ነበር የመጣነው። የምንሰራው በረዳት ዳኝነት ነው። አቶ ጸሀዬ ዕድሉን እንድናገኝ ካደረጉ በኋላ እንዳትፈሩ የምታውቁትን፤ ያያችሁትንና ያመናችሁበትን ወስኑ። ብትሳሳቱም ችግር የለም ብሎ አበረታታን። እንደምናጫውት ስለተነገረ ስታዲየም አንድ ሰው አይቶን “እናንተ ልታጫውቱ ነው እንዴ? አይከብዳችሁም” ሲለን እኛም “ምን ይከብዳል። አንሸከመውም!!” ብለን መለስንለት። ሰውየውም “እነዚህ ከየት የመጡ ሙጢዎች ናቸው” ብሎ  ተናግሮ ሄደ። ብዙዎቹ በእኛ ላይ እምነት አልነበራቸውም። ይሄ ነገር የተፈጠረው ስናጫውት አይተውን ስለማያውቁ ነው። የተመደብነው ጊዮርጊስ ከወንጂ  ነበር።  ፋሲል ተካልኝ ረዳት ዳኛ ስር ተሸጉጦ ይሸውዳል ስላሉኝ በአብዛኛው እስርሱን ስከታተል ነበር…”

እዚህ ለመድረስ

“…እኔን ጨምሮ ሌሎች እንስት ዳኞች እዚህ ለመድረስ አቶ ጸሀዬ ገብረእግዚአብሄር ትልቅ ባለውለታችን ነው። ሴቶች እንኳን ሊጫወቱ ሊያጫውቱም ዕድሉ አይሰጣቸውም ነበር። የሴት እግር ኳስ ቡድን ክለቦች እንዳሁኑ ሳይስፋፉ ኢንተርናሽናል ውድድር አንዲያደርጉ የተመቻቸው ያኔ ነበር። ሴት ዳኞችም የወንዶችን ውድድር ጭምር እንድንመራ ሲያበረታታንና ኣይዟችሁ በማለት ዕድሉን እንዲሰጠን ያደረጉት እርሳቸው ነበሩ።

ኮርስ

“…ለመጀመሪያ ጊዜ የዳኝነት ኮርስ የሰጠኝ ኢንስትራክተር ሽፈራው እሸቱ ነበር።ቦታው ጅማ ነው። ከብዙ ወንዶች መሀል ኮርስ ስንወስድ “ለመማር ብቻ ሳይሆን ሜዳ ገብታችሁ እንድታጫውቱም ጭምር ነው። ወደ ኋለ እንዳትሉ” ብሎ አበረታታን። አሁን ድረስ ሽፌ እገዛው አልተለየኝም…”

ወይኔ ጉዴ!!

“…በኢኳቶሪያል ጊኒ የተዘጋጀው ስምንተኛው አፍሪካ ዋንጫ ለኔ የመጀመሪያ አፍሪካ ዋንጫ ነበር። በግማሽ ፍጻሜ ደቡብ አፍሪካና ናይጀሪያ ነበር የተጫወቱት። ይሄንን ጨዋታ እኔ ነበር የመራሁት። በዚህ ጨዋታ ናይጀሪያ አሸንፎ ለዋንጫ ያልፋል ተብሎ ነበር የተገመተው። ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ሻምፒዮና የሆኑት እነርሱ ስለነበሩ ነው። ነገር ግን ደቡብ አፍሪካ መሪነቱን ያዘና በዚያው ቀጠለ። ጸሐዩ ኃይለኛ ነው። በጣም አቃጠለኝ በፍጹም አልቻልኩም። ቶሎ አልቆ ከሜዳ በወጣሁ ብዬ ነበር የማስበው። ሰዓቱ ማለቂያ ላይ ደረሰ። ቶሎ ነፍቼ መገላገል ነበር የፈለግሁት። የባከነው ሰዓት ሁሉ ሊጠናቀቅ ነው። በዚህ ጊዜ ደቡብ አፍሪካ በር ላይ ጥፋት ተሰራና ቅጣት ምት ሰጠሁ። ወሳኝ ቦታ ነው። ይሄ ግብ ከተቆጠረ እኩል ስለሚሆኑ ሰላሳ ደቂቃ መጨመሩ ነው። እንዲህ ከሆነ ተዝለፍልፌ መውደቄ ነው። ረዳቴ ትርሀስ ነበረች። በዎኪ ቶኪ እንነጋገራለን። ይሄ ግብ ከተቆጠረ አለቀልን አልኳት። አርሷም ጸሀዩን አልቻለችም  እንደኔ ተጨንቃለች። ልክ እንደተመታ ወደ አንግሉ ስር ሲሄድ “ድንግል ድረሽ!!”› አልኩኝ ኳሱን እያየሁ ረዳቴ “ተርፈናል አይዞሽ “አለችኝ እርሷ በደምብ ስለሚታያት ኳሱ ወደውጭ መውጣቱን ቀድማ አረጋግጣለች። እኔ ግን የገባ መስሎኝ ደንግጬ ነበር..”›

ጠፋብኝ!!

“..ድሬዳዋ ከነማና መከላከያ ላመውረድ አዲስ አበባ ስታዲዬም ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋሉ። እነርሱ እንዳሉት “ዛሬ የሞት ሽረት ነው” ሁለቱም መሸነፍ የለባቸውም። የተሸነፈ አከተመለት። ማለቂያው አካባቢ ቅጣት ምት ተሰጥቶ ድሬዳዋ የግብ ሙከራ አደረገ። ኳሱ በአየር ላይ ነበር የሄደው። በረኛውን አይቼ ዞር ስል ኳሱ በአናት ወደ ውጭ ወጣ። እኔ ያየሁት በአናት መውጣቱን ነው።ረዳቴ ባንዲራውን ወደ ላይ ሲያወጣ ነፋሁና እየሮጥኩ ስሄድ ከኔ ቀድመው የመከላከያ ተጫዋቾች ወደ ረዳቴ እየበረሩ ደረሱና ሰፈሩበት። ከበውት አዋከቡት ።ብዛት ስለነበራቸው አደናገሩት። እኔ ከደረስኩ በኋላ ገለል እንዲሉ ነገርኳቸው።ረዳቴ በእጅ መነካቱን ነገረኝ። እነርሱም ይሄን ስላወቁ ነው ግር ብለው የመጡት። እኔም ሪጎሬ ሰጠሁ። እንደገና ከበው ይናገሩት ጀመር። እንግዲህ የሚገባ ኳስ በእጅ ተነክቶ ስለወጣ ነው ሪጎሬ   የተሰጠው። የሚገባ ኳስ እንደበረኛ ሆኖ ነው የመለሰው። የነካው ልጅ በቀይ መውጣት ስላለበት ረዳቴን ማነው የነካው? ንገረኝ አልኩት። ከበው ሲያዋክቡት ስለነበር “ልጁ ጠፋብኝ” አለ። ተከላካዮቹ ረጃጅምና ተመሳሳይ ስለሆኑበት ሁሉም ሲመጡበት የነካው ጠፋበት። ድሬዎች ዋናው የሚፈልጉት ጎሉን ስለሆነ ሌላ ጥያቄ ትተው ቅጣቱን መቱ። ሪጎሬው ተሳተ።በኋላ ሲያስቡት ለመሸነፋቸው ምክኒያት ለማበጀት በዳኛ ማሳበብ ስለነበረባቸው ከውጭ አምበሉን ጠርተው ክስ አስይዝ አሉት። አምበሉ መጥቶ ሁኔታውን  በማዘን ነገረኝ።”

መብራት ፍለጋ

“…ለመጀመሪያ ጊዜ ለማጫወት የሄድኩት አልጀሪያ ነበር። ብዙ ተጉዤ ደረስኩ። ክፍል ተሰጠኝ። ሆቴሉ ዘመናዊ ነበር። በኤለክትሮኒክስ ነበር የሚሰራው። በሩን በካርድ ከፈትኩና ገባሁ። መብራት በርቶ ጠፋ። በሩን ከፍቼ ተመለስኩ እንደገና በራና ጠፋ። ግራ ተጋባሁ። ጭለማ ውስጥ ቁጭ አልኩ። ስልኩም አይሰራም። ለእራት ሌሎች ዳኞች ስቀርባቸው አንኳኩተው ጠሩኝ። እራት በልቼ ስመለስ ጨለማ ቤት ማደሬ ነው። ሌሎች ዳኞችን መጠየቅ ፈራሁ። ከእራት መልስ አንዲት ሴኔጋላዊ ዳኛ ክፍል ሄጄ አብረን እናውራ አልኳትና ተቀመጥን። እርሷ ሰትገለገልበት አየሁ። ሁሉንም ነገር ካርዱን ሰክታው ነው የምትጠቀመው። ነገሩ ገባኝና ወሬውን አቋርጬ ቶሎ ሄጄ ካርዱን ሰካሁና ተጠቀምኩ። ያንን ባላደርግ ጨለማ ውስጥ አድሬ ነበር”

ያልገባ ኳስ

“…. በውሳኔ አንዳድንድ ጊዜ ያልታሰበ ነገር ይገጥምሃል። ሀረር ላይ በተደረገ ጨዋታ ከርቀት የተመታ ጠንካራ ኳስ የሀረር ግብ ጠባቂ አምባዬ ይዞት  አመለጠው። ርቀት ስለነበረኝ ግብ እንደሆነ ገምቻለሁ። መረቡ ተቀዶ በዚያ ወደ ውጭ ስለወጣ ግብ መሆኑ በመረዳት አፀደቅሁ። ወዲያውኑ አምባዬ እየሮጠ መጥቶ” አልገባም “ሲለኝ ክርክር ተነሳ። በረኛው ሊዱ በእኔ ይሁንብሽ ግብ አይደለም። እኔ ላንቺ ብዬ ነው። ከፈለግሽ አጽድቂው። ግን ሊያስቀጣሽ ይችላል አለኝ። ረዳቴን ስጠይቀው ግብ  አላየሁም አለ። ለማንኛውም መረቡን ማጣራት ስላለብኝ ሄጄ ስመለከተው ምንም ቀዳዳ የለውም። ካረጋገጥኩ በኋላ ግቡን ሻርኩት። እነዚያ ደግሞ “እንዴት የፀደቀ ኳስ ትሽሪያለሽ“ ብለው ተሟገቱ። ‹ዞር በል!! መሻርም ማፅደቅም የኔ መብት ነው› ብዬ ሄድኩ…

አዲስ ጸባይ

“…በጥር 2005 ማርገዜን አወቅሁ። ሁለት ወር ያህል አጫወትኩ። ግን ያነጫንጨኝ ጀመር። ከዚህ በፊት ሴቶችን ሳጫውት እየተቃለድን እየተነጋገርን ነበር። ካረገዝኩ በኋላ ግን በትንሹ ጥፋት እየተቆጣሁ እየተነጫነጭኩ በማጫወቴ ልጆቹ “ሊዱ ምን ሆነች? ምን ነካት? ፀባዩዋ ተቀየረ” እያሉ ሲናገሩና ሲጠቋቆሙብኝ  ነበር። ሰውነቴም እየከበደኝ ሄደ። ዶክተር አያሌው እስከ 3 ወር ችግር እንደሌለው ነገረኝ። ከዚያ ማጫወቱን  አቆምኩ። አሁን የሴት ልጅ እናት ሆኛለሁ። 

ሞራል ግንባታ

 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ የሰራሁት በ1997 ነበር።መከላከያ ከወንጂ ነበር። በፕሪማች ሚቲንግ ላይ እኛ እንደምናጫውት ሲነገር ተቃውሞና ትችት ነበር የጠበቅሁት። የመከላከያ አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ “በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሴት ዳኛ እንድንጫወት በመደረጉ ደስተኛ ነኝ” ብሎ በመናገሩ ለኔም ሞራል ስለሰጠኝ ሳልቸገር ለማጫወት ችያለሁ። የመጀመሪያው ላይ ቢያደናግሩኝ ኖሮ ችግር ነበር…”

ዩንቨርስቲ

“..በብሄራዊ ሊግ ውድድር  በአለማያ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ሲጫወቱ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ቡድን ደጋፊዎች ሲሳደቡ፤ ሲያወግዙ ቆይተው በዛቻ በማስፈራራት “ስትወጪ እንገልሻለን” በሚል አስቸገሩ። በእረፍት ስንወጣ ወደ ውስጥ ገብቼ ጠረጴዛ ላይ ሄጄ ቁጭ አልኩና ለረዳቶቼ ማጫወት የሚፈልግ ገብቶ ይምራ እኔ በቅቶኛል አልኩ። ምክኒያቱም እየዛቱ ነው። ዩንቨርስቲ ደግሞ ፖሊስ አይገባም ስለተባለ አንድ ነገር ቢነሳ መቅለጥ ነው ብዬ ልብሴን ቀይሬ  በተማሪው መሀል እያፈፏጨሁ ሄድኩ። ኮፍያ ስላደረግሁ አላወቁኝም። ጨዋታው በሌላ ጊዜ በዝግ ሜዳ አበበ ቢቂላ ተደገመ።”

ዛቻ

  “..መተሀራ ላይ ሳጫውት ሙቀቱን ስላልቻልኩ በእረፍት በቃኝ ብዬ ረዳቴን ገብተሽ አጫውቺ ብዬ ነበር። ቆይቶ ግን እንደገና ሀሳቤን ቀይሬ ገባሁ። አንድ ተጫዋች በውሳኔዬ ተናዶ መጥቶ “እገልሻለሁ” አለ። በጣም ስላናደደኝ ‹በል ጎበዝ ከሆንክ ግደለኝ። አንተ ደግሞ ሳትገለኝ አትወጣትም ብዬ ቢጫም ቀይም ሳልሰጠው አቆየሁት። ልጁ ደክሞታል ለመውጣት ብሎ ቀይ ፈልጓል። እንዲህ ሲናገር ጓደኞቹ ሰምተው “ሴት ስለሆነች ነው የምታስፈራራት?” ብለው ወቀሱት። በኋላ ነገሩ ተሰምቶት  በሌላ ጊዜ ሲያገኘን እየተሸማቀቀ መጫወት ጀመረ።”

ቀይ

 “በአንድ ጊዜ ብዙ ቀይ የሰጠሁት ጊዮርጊስና ሜታ ሲጫወቱ ነበር። ተከላካዮቹ ሳላሃዲንን ሲጠልፉት እኔ ስስጥ። እንደገና እነርሱ ሲጠልፉት እኔ ስሰጥ ሦስት ቀይ ደረሰ። በሶስተኛው የወጣው ልጅ ሊመታኝ ሲመጣ ሳላ አንገቱን ይዞ አስቀረው። እርሱ ከሳላ ጋር ሊጣላ ተያያዘ። ሳላ ግን አተረፈው እንጂ  ዳኛ ቢማታ ኖሮ ቅጣቱ ከባድ ይሆንበት ነበር..”

.አር.ኤስ

“…አንድቀን አርባ ምንጭ ለጨዋታ ስሄድ መንገድ ላይ የበላሁት ምግብ ስላልተስማማኝ ሆዴ ታመመ። ወደ ሜዳ ኦ. አር. ኤስ. ይዤ እስከመሄድ ደረስኩ። መሯሯጥ እንኳን አልቻልኩም። መሀል ሜዳ እየተሸከረከርኩ ቆየሁ። በእረፍት ፎጣ ውሃ አስነክቼ ፊቴ ላይ አድርጌ ጠረጴዛ ላይ ተኛሁ። አንዳንድ ተመልካቾች እኛ ወዳለንበት በመምጣት “ጎበዝ ዳኛ ነች በጣም ትሯሯጣለች” ብለው በአድናቆት ሲናገሩ ስሙን የማልነግርህ አሰልጣኝ በጨዋታው ቅር ተሰኝቶ ኖሮ “ምን ትሯሯጣለች እንደተሸነፈ ቦክሰኛ ፎጣ ተጥሎባት ተዘርራለች” ሲል ሰማሁት..”።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top