ጥበብ በታሪክ ገፅ

ዘመን የማይሻገር የጥበብ ሽመና

የስነ-ጽሑፍ ፈር ቀዳጅ ታላላቆች፤ ፈለግ ተከታይ ታናናሾችም ስለዝምታ ውበት፣ አስፈላጊነት ከዛም አልፎ ገዢ ኃይልነት ጽፈዋል። ከተነገሩበት ዘመን አልፈን ዛሬም ድረስ ለእኛ ተብሎ የተጻፈልን እስኪመስለን ድረስ፤ ስማቸውን እያጣቀስን በየመድረኩ ዘመን ባስቆጠረው ነጭ ወረቀትም ይሁን ዘመን ባመጣው ልዩ ልዩ ቴክኖሎጂ ከእጃችን በጣለው ሰሌዳ ላይ ቃላቸውን ደግመን ደጋግመን እንጽፋለን። እውነት ነው ስንል እየተጋራንም ያልሰማ ስማ እያልን እናስተጋባለን።

የስነ-ጽሁፍ ሰው ለምን ዝምታን ይመርጣታል? ምክንያቱም ቃል ኃይል ነው። ዓለምን ይገዛል። ዓለማውያንንም ይዘውራል። ማንም ሰው ያለ ቃል ምንም ማድረግ አይቻለውም። በቀላሉ ለማየት “ና” ወይም “ሂድ”፤ “እወድሃለው” ወይም “እጠላሃለው”፤ “አከብርሃለው” ወይም “እንቅሃለው” እነዚህ ቃላት በሰው ድርጊት፣ እሳቤ፣ እምነት፣ ልቦና ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ የሚፈጥሩትን ለውጥ መገንዘብ በቂ ነው። እናም የስነ-ጽሑፍ ሰዎች ዝምታን የሚመርጡት የቃላቸውን ኃይል ስለሚያውቁት ነው። ያዩትን ሁሉ ሳይሆን የተገነዘቡትን ቃል መደረግ እንዳለበት ሲነግሩን ነው።

ደራሲ ይሰማዕከ ወርቁ “ክቡር ድንጋይ” በሚል መጽሐፉ ለክብሩ መታሰቢያ ያቆመለትን “ቃል” ጉዳይ ዛሬ ያነሳሁባችሁ እንዲያው ደሞ ምን እናውራ? በሚል መነሻ አይደለም። ዘመን የተሻገሩ መልዕክቶች “ስነ-ጽሑፍ ‘እውነት’ ምስጢሯን ሹክ የምትላት ወዳጇ ናት” የሚል ድምዳሜ ያሰጡ፤ ትውልድ ያላየውን ዘመን የኖረበት ያክል እንዲሰማው በሚያደርጉ ቃላት የተጻፉ ግጥሞች፣ ወጎች፣ ቲያትሮች፣… እና ልዩ ልዩ ዘርፍ ውስጥ የሚመደቡ መጻሕፍት የጻፉ ኪነጥበባውያን ስራን ተቀበልን።

የፊታችንን የስነ-ጽሑፋውያን ስራዎች የትውልድ ገመድ የተቀበልን ‘እኛ’ የጥበብ ሽመናውን እንዴት ቀጠልንበት? ስለ ቃላት ኃይል እናውራ ያልኩት፣ አይደለም የቀጣዩን ትውልድ የመጪውን ወር ብርሃን የማያይ ስራ በስነ-ጽሑፍ ስም በመሰናዘሪያ ቃላት ተቀንብቦ ሲቀርብ ባይ ጊዜ ነው።

የቀደሙት ቀድመውናል እና ከእኛ በፊት ጥቂት ስለእነሱ

ባለንበት ዘመን መጽሐፍ አንባቢው ማኅበረሰብ ያለሙግት ታላላቅ ስራዎች ሰርተዋል ብሎ የሚያነሳቸውን ደራሲያን ስራ እናጣቅስ።

በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የታተመው እና “እውነት በሌለበት ዓለም አልወለድም” ሲል ገና በእናቱ ማህጸን በጽንስነት ከነበረበት ተወልዶም ያለውን የህይወት መራርነት አጥንት ሰብረው ዘልቀው በሚገቡ ቃላት እያብራራ የሚናገር ህጻን ታሪክ ዙሪያ የሚያጠነጥነው የደራሲ አቤ ጉበኛ “አልወለድም” መጽሀፍን ለአብነት እንመልከት።

በመጽሐፉ ገጽ 49 ላይ እንዲህ ተጽፏል። “ይህን በመሰለ ጭቅጭቅ አደገኛ የሆንሁት ጽንስ እና ደሀዋ እናቴ ስንሟገት ብዙ ጊዜ ካጠፋን በኋላ የምችል ብሆን በዓለም የሚገኘውን ነገር ሁሉ አድርግልኝ ብትይኝ አደርግልሽ ነበር። ባርነትን ተቀበል ለባርነት ተወለድ ብለሽ የምታቀርቢውን ልመና ግን እንኳን አንድ ጊዜ መቶ ጊዜ ብትሞቺ እሺ አልልሽም፤ አልኳት።” ይላል።  

አልወለድም እስከዛሬም ድረስ በስነጽሑፋዊ ይዘቱም ሆነ በዘመን ተሻጋሪ መልዕክት ታጭቆ አንባቢን እውነት እና ፍትሕ በሌለበት ዓለም መወለድ ህመሙን በግልጽ የሚያስረዳ ውስጠት ባለቤትነቱ በብዙሀን ዘንድ ተወዳጅ መጽሐፍ አድርጎታል።

አቤ ጉበኛ በዘመኑ የነበረውን የገሀዱን ዓለም በወቅታዊ ሁኔታ ብቻ የተጠመደ ምላሽ መስጫ፤ ለእዛ ዘመን ህዝብ ብቻ የተጻፈ ያ ትውልድ ብቻም የሚረዳው ገሀዳዊ እውነትን በማብራራት ውስጥ አልሰመጠም። ይልቁንስ በየትኛውም ዓለም ያለ አንባቢ አንብቦ ራሱንም ዙሪያውን የከበበው እውነቱንም የሚመዝንበት ህሊናውን የሚሞግትበት እሳቤ አበርክቷል። እናም ቃል ኃይል ነው፤ ትውልድ አልፎ ትውልድ ሲተካ ያለፈውን እና የአሁኑን ማጣመሪያ፣ ማጋመጃ፣ መገምገሚያ፣ እምነትን በውሳጤ ፈተና ነበልባል የሚያጸናበት የእውነት ዥረት በህሊና የሚፈስበት በር መክፈቻ ቁልፍነቱ በአልወለድም የፊደላት ቀመር ለሰሚው ሁሉ ይጮሀል። እኔነትን ይፈትናል፣ ያጸናል አልያም ይቀይራል።

ደሞ ሌላ ታላቃችን፣ የሌላ ድንቅ ደራሲ ስራን እንመልከት። የደራሲ ስብሃት ለአብ ገብረእግዚአብሔር “ትኩሳት”። ትኩሳትን ያነበቡ ብዙሀን የሚጋሯት የመጽሐፉ መጀመሪያ ገጻት ላይ የሰፈረች፤ ወጣት መሆንን የደረሰበት፤ ያጣጣመው፤ የታገለው፤ የኖረው ሁሉ በስምምነት “እውነት እውነት” ብሎ ቃላቶቹን ደጋግሞ ያነበባት፣ ለሌሎችም እኔ ያየሁትን እውነት ዕዩ ብሎ በቻለው መንገድ ሁሉ ሲያጋራት የምንመለከታት ጽሑፍ እንዲህ ትናገራለች።

“ጥሩ ነው ወጣት መሆን። ገንዘብ ባይኖርህም ጤና ይኖርሀል፣ መልክ ባይኖርህም አንጎል ይኖርሃል፣ ፍቅር ባይኖርህም ተስፋ ይኖርሃል፣ ደስታ ባይኖርህም ንዴት ይኖርሃል፣ መጨቆን ቢበዛብህ ሪቮሊውሽን ታነሳለህ፣ መኖር ቢያስጠላህ ወይም ቢያቅትህ ራስህን ትገድላለህ… ሰው ባያውቀውም ቅሉ ታሪክ ይኖርሃል፤ ወጣት ነህና…”

የእኔ፣ የአንተ፣ ወጣት የሆነው፣ ወጣት የነበረው፣… የዓለም ህዝብ ሁሉ የህይወቱ ምዕራፍ ክፋይ እንደየራሱ እውነት እንዲሰማው በጥቂት ፊደላት ስምም ስክኪ ራሳችንን እንድንፈትን፤ እንድናውቅ አልፈን እንድንሆነው ሆኖ ተተይቧል፤ ወጣትነት።

እውነት በትኩሳት ውስጥ ሳትሸራረፍ ሳትጎሳቆል በምሉእ ማንነቷ ነብራለች። በሙሉ ግርማዋ ተገልጣለች። ህይወት ከእነ ሽሙንሙን ቁንጅናዋ፤ ከእነምስጢራዊ ፈገግታዋ፣ ከእነእንቆቅልሿ ምን አቅልህ አሸንፈኝ ወይ ልርታህ በልሀ ልበልሃዋ በደራሲ ስብሃት ቃላቶች ከማንነቷ ከምን መሆኗ አንዱም ሳይጎልባት ተገልጻለች።

እናም አዎ ቃል ኃይል ነው። ገዥ መንፈስ ነው። የአስተርዕዮ መድረክ ነው። አንድ ታላቅ ደራሲ አንድ መጽሐፍ ምሳሌ ብቻ ልጨምር።

የሚያቃትተው እውነት ህሊና ሞጋችነት ወደ ትውልድ ነቅናቂ አዋጅነት ሲቀይረው ቃል ለህይወት መስዋዕትነት ምክንያት እንደሚሆነው እያወቀ “ኦሮማይ” ብሎ ሰይሞ ጻፈው። ደራሲ በዓሉ ግርማ።

በኦሮማይ “አስመራ ያን ቀን በዘምባባዎች ጥላ ስር ንግሆ ወጋሕታ” የሚል አርዕስት ካለው ምዕራፉ ስር ቀጣዩ ተከትቧል።

“ናይ ሰሜናዊት ጽብቕቲ አስመሪና። የቀይ ባህር እንቁ ሸብእረብ፣ ክንብል ዝንፍል፣… ብለው በየመንገዱ ዳር የሚታዩት ዘንባባዎች እና የሰሜናዊ ቆነጃጅት ሹሩባዎች አንጻራዊ ውበት ባለቅኔም ባይሆኑ ስሜት ይቀሰቅሳሉ። ከዘንባባ እና ከሰሜናዊት ቆንጆዎች ሹርባ ጥላ ስር ላንዳፍታ አረፍ፣ ጋደም፣ በማለት እንደ ኩል ከጠራ ሰማይ ላይ የምታበራውን ሰሜናዊ ኮከብ በጠፍ ጨረቃ በእፎይታ መመልከት ምንኛ ደስ ይል ይሆን? ሰላም ናፈቀኝ! ጦርነት በሕይወት እና በቁስ ላይ የሚያስከትለው ጥፋት የበለጠ የሚያስጠላኝ ነገር በዚህ ዓለም ያለ አይመስለኝም። የሰው ልጅ በመካከሉ የሚፈጠሩትን ልዩነቶች በውይይት እና በሰላም የሚፈታበት ቀን መች ይመጣ ይሆን? ያ ቀን ናፈቀኝ። ለምንድነው የሰው ልጅ በሰላም የማይኖረው? ያለጦርነትም ሕይወት ራሷ አጭር ናት።”

ዐየሃቸው ቃላቶቹን? ውበታቸውን? ጥልቀታቸውን? እያንዳንዱ ቃል ከባህር እንደተገኘ ልዩ እንቁ አምሳያ አልባ ሆኖ የገለጸውን ሃሳብ፣ ያወጀውን እውነት፣… እያንዳንዱ ቃል ከእርሱ ውጭ ተክቶት በእሱ ኃይል ሊገልጸው የሚችለው እኩያ ቃልቢስ ሆኖ መከሰቱን? አንዱ ቃል ለብቻው የሚገልጸው ጎረቤቱ ያለውን ቃል ሳያዝለው፣ ሳይገፋው፣ ሳይናጠቀው፣… በስምም የሚናገረውን?

ይህን አንብበህ አስመራን አይተሃት ባታውቅ እንኳን ውበቷ አልገነነብህም? የደራሲ በዓሉን ዐይኖች በውበት ነጸብራቅ ያጥበረበረችው፣ ለልቡ የከበደችው፣ ባለቅኔ ቢሆኑ እንዴት በገለጿት ነበር ያስባለችው፣… ከተማን ለቅጽበት ተመልክተህ ምነው ባየኋት? በሚል ምኞት ከምናብ ዕይታ ተመስጦህ ወደ ማውጠንጠንህ አልተመለስክም?

የከተማ ውበት፣ የቁንጅና ልዕልታት መልክ፣ የሰላም ጥም፣ የጦርነት ክፋት፣.. ሁሉም እኩል ዐይነት፤ ደግሞ እንደገና ለየብቻ በየትርጓሜያቸው ጸንተው ገንነው እንዲሰሙን፤ በንግርታቸው ውስጠት ድብልቅልቅ የእውነት እና የስሜት ማዕበል የፈጠሩ ፊደላት ኅብረት ኃይል በኦሮማይ እንዲሰማን ግድ ሆኗል።

ወደራሳችን…

3 ወይም 4 እንሆንና የጥበብ ምሽት እናዘጋጃለን፡፡ ባለፈው ሳምንት ላበሳጨን ጸሐፊ እሳቤ መሰናዘሪያ እንከትባለን። የቀደሙት የተጠቀሟቸውን የፊደል ገበታ ዘርግተን መርጠን የምናጣምራቸው በህብር የሚናገሩት የሚፈጥሩት ቃል ምንድነው?

“ለቃል ኃይል የማያስገዙ” ማለት መቻል ቀሊል እንዳይሆንበት፣ ነፍሱን እንዲቆረቁረው የማያደርጉ፣ ከፍጥረተ ዓለም እኩል በዝንተዓለም ነባሪነት ውሳጤ ውስጥ ያሉ፣ የቀደሙት ከገለጧቸው ብርሃናዊ እውነቶች እኩል ቀርቶ ለዝምድና ያልቀረቡ፣… ግን ደግሞ ከመኖር ወደ አለመኖር የሚያመጣቸው ነጻ አውጪ ጸሐፊን ፈጣሪያዊ ቃል ፍለጋ ባለመታየት ጽልመት ተጋርደው የሚቃትቱ እውነታዎችን አካል ለሆንለት ትውልዳችን የማያበረክቱ፤ “አንቺ እዛ ማዶ… እኔ እዚ ማዶ” መጯጯሂያዎችንን በነጭ ወረቀት አግተልትለን ጽፈን የሚፈልግ ብቻ የሚሰማው፣ አይደለም ዘመን ሳምንት የማይሻገር የቃላት ጥርቅም ከመድረክ ቆመን እናነበንባለን።

ጩኸት ብቻ! ጩኸት! ከዛስ? የፈጣሪነትን ማዕረግ ኒሻን ለራሱ “ደራሲ”፣ “ገጣሚ” ሌላም ሌላም ሸልሞ ከባዶነት ገደላማ ማንነት የሚንከላወሰው ሌላኛው ጯሂ ይነሳል። ጩኸቱ በጭንቅላቱ እንደገደል ማሚቶ እየተቀባበለ ያደነቁረዋል። ብዕሩን አሹሎ ያልወደደውን ጩኸት ማስተጋባት ለመቅበር ለመሸፈን መሳዮቹን ሰብስቦ የራሱን ጩኸት እሪሪሪታ ይቀኛል።

የእሪ በከንቱ ቃላት ባለቤት ሆነናል። የገሀዱን ዓለም እውነታ ማንጸሪያ ሽሽግን ሊገልጡ ያልፈቀዱ ይሉኝታ የሸበባቸው፣ የጋረዳቸውን የመሳይ ጽልመት የማይገፉ በመፈክርነት ኖረው በሌላ መፈክር የሚዋጡ ምንም የሆኑ ምንሞች እንለፈልፋለን።

“እስከአፉ ድረስ ጢም ተደርጎ በተሞላ ብርጭቆ ላይ ተጨማሪ ቢቀዱበት ወደውጭ ፈሶ ለተመልካች መባከኑ ያሳዝነዋል እንጂ ሌላ ምንም አይፈጥርም፤ ምንም አይቀይርም” የራስ ውዳሴ ከንቱነት ላይ ተኩኖ የቃል ወዳጅ ለመሆን የመባከን ቀንበር ከእውነታችን ላይ ጭነናል። መሽቶብናል። ለእኛ ብቻ ግን አይደለም ጽልመቱ መጋረጃችን የትውልዱንም ዐይነ-ህሊና እያጨለመው ነው።

መፍትሄ?

ሰዓሊ እና ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታ በአንዲት ግጥም እንዲህ ነግሮናል።

“አለ በውስጣቸን…

እውነት ፍጹም ሆና እምታበራበት

ደግሞም ማወቅ ማለት

ከውጭ ያለውን ሄዶ ከመፈለግ

ከውስጥ ያበራውን እንዲወጣ ማድረግ።”

እኔም እላለሁ ከውስጥ እስክናንጸባርቅ ዝምታን እንወቅ። ውደውጭ በመጮህ የውስጡን ከማፈን ከራሳችን እስክንተዋወቅ በባዶ ጩኸታም የጅራፍ ቃላት መሰናዘሩ ይቆየን። ሰላም!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top