አጭር ልብወለድ

ክቡር ውርስ!!

ጨረቃ-አልባ ለሊት ነው። ክዋክብቶቹ ጨለማ በዋጠው የምሽቱ ሰፊ ጥቁር ሰማይ ላይ የተዘሩ የብርሃን ፍንጥርጣሪዎች ይመስላሉ። ጨለማ ከዋጠው ሰማይ ስር፤ ብርሃን የተሞላች ከተማ ትታያለች። በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ ቤቶች ውስጥ፤ የሳቅ ሁካታ እና የደስታ ስካር አለ።

በከተማዋ ከሚገኙ ቤቶች ሁሉ በተለየ ግን፤ ሁለት ቤቶች ደስታና ሳቅ ርቋቸዋል። የሁለቱም ቤት አባወራዎች የመጨረሻ እስትንፋሳቸውን ተንፍሰው፤ ሞትን ሊያስተናግዱ ከተዘጋጁበት የመሞቻ አልጋዎቻቸው ላይ ተኝተዋል።

የመጀመሪያው ቤት አባወራ የከተማዋ ከንቲባ ነው። በከተማዋ ከሚገኙ ፖለቲከኞች ሁሉ ስኬታማ የሚባል ሰው ነው። ከተማዋን ለአስር ዓመታት በከንቲባነት መርቷታል። በእነዚህ አስር ዓመታት ውስጥ በከተማዋ የተሰሩ አብዛኞቹን ተቋማት፤ በስሙ እንዲጠሩ አድርጓቸዋል። እርሱ ገናና ስም እንዲኖረው ሲል፤ በከተማዋ የሚገኝ ሁሉም ትልልቅ ነገር፤ በእሱ ስም እንዲሰየም አስደርጓል። ከንቲባው በስም እና በዝና ማንም እንዳይበልጠው በማለት ለስልጣን የማይፎካከሩትን በሌላ ዘርፍ ያሉ ሰዎችን ጭምር አሉታዊ ተፅእኖ በማሳደር ስማቸው እንዲጠለሽ በማድረግ ተሳክቶለታል።

የሁለተኛው ቤት አባወራ በከተማዋ በበጎ ስራው የሚታወቅ መምህር ነው። በከተማዋ የሚገኙ ምሁሮች፣ ደራሲዎች፣ ባለሃብቶች፣ ሐኪሞች፣ እንዲሁም ፖለቲከኞች፤ ክቡር ከንቲባዋንም ጨምሮ አብዛኞቹን ይሄ መምህር አስተምሯቸዋል። በከተማዋ የተሰሩ ትልልቅ ተቋማት እንዲገነቡ አነሳስቷል።

በመሰራት ላይ ሳሉም፤ በፈቃዱ የነፃ አገልግሎት በመስጠትና፤ ሌሎች በጎ ፈቃደኞችም የበኩላቸውን እንዲወጡ፤ የተቻለውን ሁሉ አድርጓል። በከተማዋ ያሉ ወላጅ አልባ ህፃናት ፣ ጧሪ የሌላቸው አዛውንቶች፣ እና ዘመድ የሌላቸው አስታማሚ ያጡ ህሙማን፤ በመምህሩ አስተባባሪነት ብዙ እርዳታ እንዲያገኙ ሆኗል።

የመጀመሪያው ቤት በብዙ ወዳጅ ነን ባዮች ተሞልቷል። አብዛኛዎቹ ሰዎች ከንቲባውን የሚወድዱ ይመስላሉ፤ ነገር ግን ከቅርብ ዘመዶቹ እና ጓደኞቹ በስተቀር፤ ሁሉም አስመሳዮች ናቸው።

እነዚህ አስመሳይ የሰው እስስቶች፤ አእምሯቸውን የተቆጣጠረው ሃሳብ፤ ከከንቲባው ሞት በኋላ፤ እንዴት አድርገው ስልጣኑን እና ሃብቱን እንደሚቀራመቱ እቅድ የማውጣት ሴራ ነው። ከቤተሰቡ እና ከእውነተኛ ጓደኞቹም ውጪ፤ በአብዛኞቹ ሰዎች ፊት ላይ የሐዘን ስሜት አይነበብም። የሰው እስስት የሆኑት እነዚህ ሰዎች፤ ሐዘንተኛ መስለው መተወን ቢከብዳቸውም እንኳ፤ የልቦናቸውን ፈቃድ ልክ እንደጎበዝ የካርታ ቁማርተኛ ፊታቸው ላይ ምንም አይነት ስሜት ባለማስነበብ ሸፋፍነውታል።

ከንቲባው ስሙ በመልካም ይጠራ ዘንድ ያላደረገው ነገር አልነበረም። ተፅዕኖ ፈጣሪነቱን ተጠቅሞ፤ በከተማዋ የሚገኝ ትልልቅ ነገር በሙሉ፤ በስሙ እንዲጠራ አስደርጓል። የከተማዋ ጋዜጦች፣ መፅሔቶች፣ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች፤ ስለሱ መልካም የሆነውን ብቻ እንዲያወሩ አስደርጓል።

ከንቲባው ለማይቀረው ሞት ተዘጋጅቶ በሚገኝበት በመጨረሻው ሰዓት፤ በአስመሳይ እና አድርባይ ሰዎች መከበቡ ፤ በጣም አበሳጭቶታል። ራሱን በአድርባዮች አስከብቦ በመኖሩም ተናድዷል። ስሙን ከፍ ከፍ እያደረጉ በማታለል ፤ እሱን እና ቤተሰቡን እንደተጫወቱባቸው የገባው ዘግይቶ ነው። ለከተማዋ ጥሩ በማሰብ ፤ ከሱ ጋር ሳይግባቡ የቀሩትን የሐቅ ሰዎች በማስቀየሙም፤ በታላቅ ፀፀት ነፍሱን አስጨንቋታል። ከሱ በኋላ ፤ የቤተሰቡ ዕጣፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል፤ እጅግ በጣም አሳስቦታል።

ሁለተኛው ቤት ውስጥ ግን ብዙ ሰው የለም። መልካም ሰው የሆነው መምህር፤ በሶስት ልጆቹ እና በሚወዳት ሚስቱ ብቻ ተከብቧል። የመምህሩ ቤት ውስጥ የሚያስመስል ሰው የለም። ሁሉም ሰው ፊት ላይ የሐዘን ስሜት ይነበባል። እውነተኛ የሐዘን ስሜት በሁሉም ልቦና ውስጥ ሰፍኗል። ማስመሰል የሚባለው ቀፋፊ ነገር ፤ እዚህ ቤት ውስጥ ቦታ የለውም።

መምህሩ ለከተማዋ እድሜ-ልኩን በመድከሙ ያገኘው ልዩ ጥቅም የለም። ስለሰራቸው በጎ ስራዎች ግን ህሊናው ሁልጊዜ እንደረካ ነው። ከንቲባው እና በከንቲባው ዙሪያ ያሉ ፖለቲከኞች በክፉ ዓይን እያዩት፤ ያሰበውን እንዳይፈፅም ብዙ ጊዜ አስቸግረውታል። ከነሱ ጋር እየታገለ፤ እንደምንም ብሎ እንዲታነፁ ያስደረጋቸውን ተቋማት፤ ራሳቸው እንደሰሩት እያስመሰሉ መልካም ስሙን ቀምተውታል። መምህሩ ግን ከስሙ በላይ ለከተማዋ ስለሚቆረቆር፤ እስካሁኗ የመጨረሻ ለሊት ድረስ ለከተማዋ እና ለህዝቦቿ ያለውን ሁሉ ሰጥቷል።

መምህሩ፤ ህይወቱን በሚያጣባት በመጨረሻዋ ለሊት በብዙ ሰዎች ባለመከበቡ ሆድ ብሶታል። ነገርግን በሚወዳቸው ቤተሰቡ መሃል የመጨረሻዋን ለሊት በማሳለፉ፤ ራሱን እንደ ዕድለኛ አድርጎ በማሰብ፤ ልቦናው ፍሰሃ ተሞልቷል። ያሳለፈውን ህይወትና የሰራቸውን ስራዎች ሲያስብም፤ ስለ ነፍሱና ስለ ስሙ ኩራት ተሰምቶታል። ለቤተሰቡ ትልቅ ሃብት ሊያወርሳቸው ባይቻለውም፤ ምንም ዓይነት ዕዳ ስላልጫነባቸው የእፎይታ ስሜት ውስጥ ነው።

ከሞት በላይ ፤ ሁሉንም ሰው በእኩል ሊያይ የሚችል፤ ምንም ነገር የለም። በሞት ፊት፤ ሁሉም ሰውና ሁሉም ህይወት ያለው ነገር እኩል ነው። ሰዎችን እኩል እናያለን የሚሉ ሃይማኖቶች ሳይቀሩ፤ ፃድቃንን (መልካም ሰዎች) ከኃጥአን (አጥፊ ሰዎች) ያስበልጣሉ። በሞት ፊት ግን ሌባ እና ፖሊስ፣ ዳኛ እና ወንጀለኛ፣ ፖለቲከኛ እና ሃይማኖተኛ፣ ጥሩ ሰሪ እና አሸባሪ፤ ሁሉም ሰው እኩል ነው። አያ ሞት ለማንም አያዳላም፤ ሁሉንም ባሻው ጊዜ ይወስዳል ከፈለገም ይተዋል።

የመጀመሪያው ቤት ውስጥ በመሞት ላይ የሚገኘው ከንቲባ፤ ሞቱ እንደማይቀርለት እያወቀ ሲመጣ፤ ዙሪያውን ለከበቡት ሰዎች በግል ጠበቃው ፊት፤ ኑዛዜውን መናገር ጀመረ። ጠበቃው፤ የከንቲባውን ንግግር እየተከተለ፤ ኑዛዜውን በፅሁፍ እየሰነደ ነው።

ከንቲባው፤ የሚንቀሳቀስ እና የማይንቀሳቀስ ሃብቱን ለሚስቱ እና ለልጆቹ አስተላልፎ ሲያበቃ፤ ከሱ በኋላ በከተማዋ ፖለቲካ ላይ ማድረግ ስለሚገባቸው ነገሮች፤ ፊት ለፊቱ ለተኮለኮሉት ፖለቲከኞች ማስረዳት ጀመረ። ፖለቲከኞቹም በሙት አልጋው ላይ ስላለ አሳዝኗቸው፤ በአንደኛው ጆሯቸው የገባውን በሌላኛው እያፈሰሱ፤ ከንቲባውን የሚሰሙት መስለው፤ እያዳመጠ እንዳለ ሰው ጭንቅላታቸውን ቀና ደፋ ያደርጋሉ።

በሁለተኛው ቤት ውስጥ ያለው መምህር ደግሞ፤ ለልጆቹ የመጨረሻ ቃሉን በአሳዛኝ ሁኔታ እየተናዘዘ ነው።

“ልጆቼ ሆይ!! በደንብ አድርጋችሁ አድምጡኝ። መልካም የሆነውን ብቻ ስሩ… ንግግራችሁ መልካም፣ ድርጊታችሁ መልካም፣ ሃሳባችሁም መልካም ይሁን። እኔ የማወርሳችሁ ትልቅ ሃብት ፤ መልካም የሆነውን ስሜን ብቻ ነው። ከማንም እና ከምንም ነገር አብልጬ የምወዳችሁ ልጆቼ ሆይ… በእኔ ከእናንተ መለየት አትከፉ። በእኔ የተነሳ ‹የሌባ ልጅ› የሚላችሁ ማንም ስለሌለ ኩሩ። በእኔ ክፉ ድርጊት የተነሳ… እናንተን የሚያሳድድ ባለመኖሩ ደስ ይበላችሁ። እኔ ከእናንተ ጋር በማልኖርበት ጊዜ… በነፃነት መኖር እንድትችሉ… የቃል፣ የቁስና የገንዘብ ዕዳ    ትልቅ ሸክም በእናንተ ትከሻ ላይ ባለማኖሬ… እፎይታ ይሰማችሁ።

ልጆቼ ሆይ!!… በዚህች የስንብት ሰዓት እና… በአሁኗ የመጨረሻ እስትንፋስ መተንፈሻ ጊዜዬ… ለእናንተ የማወርሰው… በብዙ መከራዎች መሃል ፀንቼ… በሚያማልሉ ነገሮች በተሞሉ ጊዜያት ቁጥብ ሆኜ  የግል ፍላጎቴን ገትቼ… በታታሪነት ያቆየሁት… በመልካም ስራ ያፈራሁትን… መልካሙ ስሜን ብቻ ነው። ልጆቼ ሆይ!!! ስለዕድላችሁ አትከፉ፤ ደስ ይበላችሁ እንጂ።… ከከበሩ ውርሶች ሁሉ የከበረ ፣… ከተወደዱ ቁሶች ሁሉ የተወደደ…፣ ከሁሉም የከበረ ውርስ… መልካም የሆነ ስም ብቻ ነውና።… መልካሙን ስሜ ውረሱኝ!!!… እናንተም መልካሞች ሁኑ… አደራ… አደራ…!!!!”

ይላል ድምፁ እየተቆራረጠና የቀረችውን እንጥፍጣፊ ጉልበት ለንግግሩ እየተጠቀመ።

በሁለቱም ቤቶች ውስጥ ያሉ እነዚህ አሳዛኝ ሰዎች፤ ህይወታቸውን ሊነጥቅ ሲታገላቸው ለነበረው ሞት ለሚባለው ክፉ ጠላት፤ የለሊቱ አጋማሽ ሊደርስ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ እጅ ሰጡ።

በሁለቱም ቤት የነበሩ ወዳጆቻቸውም፤ ስለሚወድዷቸው ስለእነዚህ ምስኪን ሰዎች እንባቸውን አፈሰሱ አለቀሱም። የእነዚህ ሁለት ሰዎች ቀብርም በቀጣዩ ቀን ተፈፀመ። በሚኖሩበት ጊዜ ‹አሉ› የተባሉ ህይወታቸው ባለፈ ሰዓት ‹ነበሩ› ተባለ።

የእነዚህ ሰዎች ህይወት ካለፈ ከብዙ ዓመታት በኋላ፤ በከንቲባው ስም ተሰይመው የነበሩ ብዙ ተቋማት ስማቸውን ቀየሩ። የፖለቲከኞች ፀባይም የተበላሸ በመሆኑ፤ ከንቲባው በህይወት ባለ ጊዜ ለከንቲባው አጎብዳጆች የነበሩ ሁሉ የከንቲባው ዋነኛ ወቃሾች ሆኑ።

የከንቲባው ልጆችም ቢሆኑ ከአባታቸው ብዙ ሃብት እና ንብረት ቢወርሱም ፤ የአባታቸው ስም በክፉ ሲነሳ እየሰሙ ፤ ደስታ የራቃቸው አሳዛኝ ሰዎች ሆኑ። የእነሱ እጅ በሌለበት ነገር ሁሉ፤ ከንቲባው አባታቸው ስለነበረ ብቻ ፤ በአሉባልታ እና መሰረተ-ቢስ ወሬዎች ስማቸው ተብጠለጠለ። ደስታ የራቃቸው ሰዎችም በመሆናቸው ኑሯቸው ተቃወሰ።

***

የመምህሩ ልጆች ደግሞ አባታቸው ህይወቱ ካለፈ በኋላ፤ ስለአባታቸው መልካም ስራ እና በጎ አስተዋፅኦ ፤ በከተማዋ ሰዎች የሚከበሩ እና የተወደዱ ሊሆኑ ቻሉ።

አባታቸው መልካም ሰው ስለነበረ ብቻ ፤ ልጆቹ በሰሩትም ይሁን ባልሰሩትም ስራ በከተማዋ ሰዎች ስማቸው ዘወትር በበጎ ይነሳል። የሰው ልጅም ውዳሴን የሚወድ በመሆኑ ፤ እነዚህም ልጆች ስማቸው በደግ በደጉ በመነሳቱ፤ ደስታ የማይለያቸው ሰዎች ለመሆን በቁ። ደስተኛ ሰዎች ከሌላው ሰው በበለጠ በህይወታቸው ስኬታማ የመሆን ጥሩ ዕድል አላቸው። እነዚህም ልጆች ደስተኛ ሰዎች በመሆናቸው ምክንያት የሚኖሩት ኑሮ የደመቀ፣ የሚሰሩት ስራ የሰመረ፣ እንዲሁም በስኬት ላይ ስኬት መጨመር ልማዳቸው የሆነ ጠንካራ ስብእናን የገነቡ በራሳቸው የሚተማመኑ እና የሚኮሩ ሰዎች ለመሆን በቁ።

***

ከሁለቱ ቤተሰቦች ታሪክ ለመረዳት እንደቻልነውም፤ ወላጆች ለልጆቻቸው ሊያወርሱት የሚችሉት ክቡር ውርስ፤ ትልቅ ሃብት እና ንብረት ሳይሆን፤ በመልካም ስራ የተገነባ መልካም ስም እንደሆነ ነው።

በእርግጥም አንድ ወላጅ ለልጁ ከሚያወርሳቸው ነገሮች ሁሉ፤ በሰዎች የተከበረ፣ የተወደደ እና የታፈረን መልካም ስም የሚያህል ምንም የለም። መልካምነት መልሶ መላልሶ ራስንም እንዲሁም ወዳጅን እና ቤተሰብንም ጭምር ይከፍላል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top