ጥበብ በታሪክ ገፅ

“ከራስ በላይ ምን ይሰጣል?”

(252ኛው ንጉሥ)

የንጉሠ ነገሥት ዘውዳቸውን አክሱም ጽዮን ከአቡነ አትናቴዎስ እጅ ተቀብተው ስለተቀበሉት፣ የዘር ሐረጋቸው ከንግሥት ሳባ እና ከንጉሥ ሰሎሞን ስለሚመዘዘው፣ 3ሺሕ ዓመታትን በተሻገረው ሰለሞናዊ አገዛዝ ስሌት መሰረት 252ኛ ንጉሥ ስለሆኑት፣ ግብጽ የዓባይ ወንዝን ለመቆጣጠር ያደረገችውን ጥረት በተደጋጋሚ ጦርነቶች ስላሸነፉት፣… ኢትዮጵያዊ ንጉሥ ካሳ ምርጫ ጥቂት ልንባባል ነው። ንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ ፬ኛ መተማ ላይ የተሰውበትን 131ኛ መታሰቢያ ዕለት ሰበብ አድርገን አበርክቶዎቿቸውን አንቃኛለን። አብራችሁን ዝለቁ!

የሁሉም ብሔሮች ደም

የዘርሃረጋቸው ወደኋላ ሲቆጠር የማይገባበት የኢትዮጵያ ክፍል የለም ማለት ይቻላል። ትግራይን ጨምሮ የሸዋ፣ የጎንደር፣ የኦሮሞ፣ የአፋር (አዳል) እና የሐረር ነገሥታት ይዛመዷቸዋል። የካሳ የቅርብ ቤተሰቦች የእንደርታ፣ የአጋመ እና የተምቤን ገዢዎች ነበሩ። አባታቸው፣ አያታቸው፣ ቅድመ አያታቸው የተምቤን ሹሞች ነበሩ። ቅም አያታቸው ደግሞ የአርሲ ግዛት ሹም የነበረው ሰላታባ ልጅ ናቸው። የንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ አእላፍ ሰገድ (ጻድቁ ዮሐንስ ቀዳማዊ) ልጅ የሆነችው ልእልት አምላካዊት፤ የማሞ አርሲ ባለቤት የሆነችው ሰብለ ወንጌል እናት ነች። የአምላካዊት አባት ደግሞ ባሻ ወልደ ጊዮርጊስ ናቸው።  

ከላይ ያነሳነውን እውነት “YOHANNES IV OF ETHIOPIA” በሚለው ማለፊያ መጽሐፋቸው የተነተኑት ደጃዝማች ዘውዴ ገብረሥላሴ፤ የካሳ ምርጫ ውልደት ‘ማይ በሃ’ የተባለ ቦታ እንደሆነ ጽፈዋል። ተምቤን አካባቢ የምትገኘው ማይ በሃ ውስጥ የተምቤን አካባቢ ገዢ ከነበሩት ደጃዝማች ምርጫ ወልደኪዳን እና የትልቁ አርአያ እህት ከሆኑት ወ/ሮ ሥላስ ድምጹ ነው ካሳ ምርጫ የተገኙት። የካሳ እናት ወይዘሮ ሥላስ የትልቁ ራስ አርአያ እህት ብቻ ሳይሆኑ የእንደርታው ባልጋዳ ድምጹ እና የአጋሜዋ ወ/ሮ ታቦቱ ወልዱ ልጅ ናቸው።

በወጣትነት ዘመኑ ብርቱ ተዋጊ የሆነው ካሳ በልጅነቱ ታማሚ ነበር። ልጅነቱን የሐይማኖት ትምህርት በመማር፣ የቋንቋ፣ የተኩስ እና የአደን ልምምዶችን እና ስልጠናዎችን በመውሰድ አሳልፏል። የራስ ሚካኤል ስሁል፣ የራስ ወልደሥላሴና ደጃዝማች ስባጋድስ ዘመድ በመሆኑ ራሱን ለንግሥና እያዘጋጀ አድጓል።

ከጠቢቡ ሰሎሞን እና ንግሥት ሳባ ተነስቶ ኢትዮጵያን ያዳረሰውን የቀደምት ትውልዶቻቸውን የታሪክ እውነት ያስተዋሉ ከሁነቱ ተነስተው አጼ ዮሐንስ ፬ኛን የመላው ኢትዮጵያ ነገሥታት ልጅ የሚል ስያሜ የሰጧቸው በርካታ ናቸው። የጎንደር ዘመነ-መንግስትን በመመስረት ላይ የነበረው የሃዲያ፣ የወላይታ፣ የየጁ ኦሮሞዎች፣ የከፋ፣… ሚናን ከታሪክ ስናስተውል፤ የአፄ ዮሃንስ የንግሥና መሰረት በመላው ኢትዮጵያ ያሉ ነገሥታት እና ሥልጣኔዎች እንደሆነ እንገነዘባለን።

ንግሥና፣ ሹመት፣ ሥልጣን

የካሳ ምርጫ የመጀመሪያው ሹመት ባላምባራስነት ነው። የምርጫ ልጅ ካሳ፤ የኃይሉ ልጅ ካሳ (አጼ ቴዎድሮስ) በሰጠው ሹመት ደስተኛ አልነበረም። እ.አ.አ. 1864-1865 ካሳ ምርጫ ከታላቅ ወንድሞቹ ከጉግሳ እና ከማሩ ጋር በመሆን ወደዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የሄደው በሁለት ምክንያቶች ነው። የመጀመሪያው ሹመት ለመቀበል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የታሰሩ ዘመዶቹን ነጻ ለማውጣት ነበር። ባላምባራስ ካሳ እናቱን እና አጎቱን በምህረት ሳያስፈታ ወደ ትግራይ በመመለሱ ብቻ ሳይሆን በእድሜው ለጋነት ምክንያት የተሰጠው አነስተኛ ሹመትም አበሳጭቶታል። እንደቀድሞው ልማድ በእድሜ ተዋረድ የተሰጠውን ትንሽ ሥልጣን በትውልድ ሐረግ ማድረግ እና ከፍ ያለውን ሥልጣን ሊሰጠኝ ይገባ ነበር በሚል ቂም ያዘ። የእናቴን ይፍቱልኝ ልመናም ለማቄሙ ተጨማሪ ምክንያት ነው። ከዚህ በኋላ ካሳ ምርጫን የሾመው የለም። ራሱን እየሾመ ቀጠለ።  

ካሳ ምርጫ “ዮሐንስ ፬ኛ” የሚለውን ስመ-መንግሥት ይዘው ንጉሠነገሥት የሆኑት ጥር 13፣ 1864 ዓ.ም. ነው። ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ “አጼ ዮሐንስ እና የኢትዮጽያ አንድነት” በሚለው መጽፋቸው እንደዘገቡት ከ1932 ዓ.ም. የፋሲለደስ ንግሥና በኋላ በአክሱም ጽዮን ንግሥናቸውን የተቀበሉ የመጀመሪያው ንጉሥ ናቸው። የንግሥና ዘመናቸውም እ.ኤ.አ ከ1872-1889 ለአስራ ስምንት ዓመታት ነው።

ካሳ እና ካሳ

ባላምባራስ ካሳ ምርጫ በአጼ ቴዎድሮስ ላይ ለማመጽ ተሰናዳ። አቡነ ሰላማ በመቅደላ ላይ ሲታሰሩ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የተላከው የውግዘት ደብዳቤ ለካሳ ምርጫ ምቹ ሰበብን ፈጠረ። በአጼ ቴዎድሮስ ጳጳሱን ማሰር ምክንያት ሁሉንም የኢትዮጵያ መስፍኖች ያወገዘው ደብዳቤ ለኢትዮጵያ አንድነት የጣረውን ቴዎድሮስን ተቃውሞ እንዲበዛበት ያደረገ ቢሆንም ከሁሉም የከፋው የካሳ ምርጫ አመጽ ነበር።

በ1865 ካሳ ምርጫ የሰራዬ ገዢ የነበረውን ደጃዝማች ገብረሚካኤልን ገጥሞ አሸነፈው። በአፄ ቴዎድረስ ትዕዛዝ ዋግሹም ጎበዜ ለጥቂት ጊዜያት በትግራይ እንዲቆይ ተደረገ። ጊዜው አብቅቶ ወደላስታ ሲመለስ ግን፤ ካሳ ምርጫ ያለቴዎድሮስ ፈቃድ ራሱን የትግራይ ገዢ አደረገ። ርዕሰ-መኳንንት ዘኢትዮጵያ ደጃዝማች ካሳ የሚል ማህተምም አስቀረፀ። ድርጊቱ ለቴዎድሮስ ከንቀትም በላይ ነበር። ካሳ፣ ካሳን ለማጥፋት ቆርጦ ተነሳ። የካሳ ማመፅ ትልቅ ችግር የሆነበት አፄ ቴዎድሮስ በሦስት ታላላቅ ደጃዝማቾች የሚመራ ጦር ወደትግራይ ላከ። እነሱም ደጃዝማች ተክለጊዮርጊስ፣ ደጃዝማች ድረስ፣ እና ደጃዝማች ሳሀሉ ናቸው። መልእክተኛው ሠራዊት የወረርሽኝ ሰለባ ሆነ። ደጃዝማች ተክለጊዮርጊስም በወረርሽኙ ምክንያት ህይወታቸው አለፈ።

በድጋሚም ቴዎድሮስ ለሁለተኛ ጊዜ ወደዮሃንስ ጦር አዘመተ። አሁንም ግን በወረርሽኙ ሳቢያ ሰራዊቱ ተመናመነበት። በግንቦት 1867 እ.አ.አ ደጃዝማች ድረስ ከካሳ ምርጫ ጋር ‹ክልተ አውላዕሎ› ላይ ጦርነት አደረጉ፤ አሸናፊውም ኋላ ላይ ዮሃንስ ፬ኛ ተብሎ የሚነግሰው ደጃዝማች ካሳ ምርጫ ሆነ። ደጃች ድረስ ለጥቂት ጊዜ በምርኮ ቢቆዩም፤ ኋላ ላይ ካሳ ይቅር ብሏቸው በነበሩበት ርስት እንዲፀኑ ሆነዋል። ራስ ኃይሉም የነገሮችን አዝማሚያ ተመልክተው በደጃዝማች ካሳ ለመገዛት ተስማሙ።

የደጃች ካሳ እና የዋግሹም ጎበዜ ስምምነት

ከነሐሴው የ1867 እ.አ.አ ድላቸው በኋላ የደጃዝማች ካሳ ስም በመላው ሃገሪቱ የሚታወቅ ሆነ። ዋግሹም ጎበዜም ወደትግራይ ሄደው ከካሳ ጋር በጦርነት እንዳይፈላለጉ ተማምለው፤ የካሳ ምርጫን እህት ድንቅነሽን አገቡ። ወዳጅነታቸውም ከስምምነት ባለፈ በስጋ ዝምድናም ፀና።

ከዚህ ሰምምነት በኋላ፤ ለኢትዮጵያ አንድነት ቀናኢ የነበረው ንጉስ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ አብዛኛው የሃገሪቱ ክፍል ከእጁ ወጣ። ሸዋ በምንሊክ እጅ፣ የአገው ምድር እና የትግራይ ምድር በዋግሹም ጎበዜና በደጃዝማች ካሳ እጅ ወደቁ። ቴዎድሮስ ከምዕራብ አቅጣጫ በስተቀር፤ በሁሉም ማእዘን ያሉ የንግድ መስመሮችና ግዛቶችን ተነጠቀ። በኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛ ንጉስ የመሆኑ ምክንያትም በጳጳስ እጅ የተቀባ እሱ ብቸኛ በመሆኑ ነበር።  

ንጉሥ ምኒልክ እና ንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ

አፄ ተክለጊዮርጊስ እና አጼ ቴዎድሮስ ህይወታቸው ካለፈ በኋላ ደግሞ የተቀሩት ሁለቱ ኃያላን ምኒልክና ዮሃንስ ሆኑ። ሁለቱም በየበኩላቸው ንጉሠ ነገሥት የሚል ማህተም ያስቀረፁ ቢሆንም፤ በዘመኑ ልማድ በጳጳስ የተቀባው ዮሐንስ እንደህጋዊ ንጉሥ ይቆጠር ነበር። በተክለፃዲቅ መኩሪያ መጽሐፍ ላይ የቀረበው ሌላኛው ምክንያት አንኮበር ከመንገስ በአክሱም መንገስ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ትልቅ ክብር ያለው በመሆኑ ነው።

በተክለፃድቅ መኩሪያ መጽሐፍ ላይ እንደተገለፀው በመጋቢት 14፣ 1970 ዓ.ም. ንጉሥ ምኒልክ እና ንጉሠ ነገሥት ዮሃንስ የእርቅ ስምምነት አድረጉ።

በተገናኙበት ሰዓት ዮሐንስና ምኒልክ መሳሳማቸውንና፤ በዮሐንስ ዙፋን ቀኝ ለምኒልክ ከዙፋኑ ዝቅ ያለ ዙፋን ተዘጋጅቶላቸው ነበር። ኢትዮጵያም ከዚያ ዕለት ጀምሮ አንድነቷ ተጠብቆ በአንድ ኃያል ንጉሠ ነገሥት መመራት ጀመረች።

ዋና ዋና ጦርነቶች

ግብፅ በከዲቭ ኢስማኤል ፓሻ እየተመራች በርካታ ጦርነቶችን ከአጼ ዮሀንስ ጋር አድርጋለች። የዓባይ ተፋሰስን የግሏ ለማድረግ በማለም ጉንደት እና ጉራዕ የዘመተችው ግብጽ በአጼ ዮሐንስ ጦር በሚመራው ሰራዊት ድልን ተነፍጋለች። ኢትዮጵያን የመውረር ዝግጅቷ በተደጋጋሚ ከሽፏል።

አንድ ለ ዜሮ

አራኪል ቤይ እና ዴንማርካዊው ኮሎኔል አህሬንድረፕ በባህር ወሰን ከሚገኙ ግዛቶች እየተነሱ ወረራ ፈፀሙ። ጥቂት ተቃውሞ ብቻ እየገጠማቸው ወደደቡብ አቅጣጫ ገሰገሱ። በኖቬምበር 16፣ 1876 ዓ.ም. ጠዋት ላይ ግን ከአፄ ዮሐንስ ጦር ጋር ተገናኙ። የኢትዮጵያ ጦር በተራሮች ጀርባ መመሸጉን ያልጠረጠሩት ግብፆች በተራሮች መካከል በሚጓዙበት ጊዜ የኢትዮጵያው ጦር ከሁሉም አቅጣጫዎች ከቦ ጉንደት ላይ ሽንፈትን አቅምሷቸዋል። ሙሉ ጦሩ የወደመበት የግብጽ ሕዝብ በከዲቭ ኢስማኤል ላይ ታላቅ ቁጣውን አሰማ።

አፄ ዮሃንስም በድሉ ሳይኩራራ የሰላምና እርቅ ጥያቄውን ለግብፁ ከዲቭ ኢስማኤል አቀረበ። ከዲቭ ኢስማኤል ግን ለሰላም ጥሪው አሻፈረኝ አለ። ከጉንደት በፊት እንዳስተላለፉት መልእክት ሁሉ “አንተም ከአባቶችህ አትበልጥም እኔም ከአባቶቼ አላንስምና፤ ባገርህ ረግተህ የያዝከውን አገሬን ልቀቅ”  ብለው በድጋሚ ለከዲቭ መልእክት ላኩበት። ነገር ግን አሁንም በምፅዋ ያሉ የግብፅ ባለሥልጣናት መልእክተኛውን 6ወር አስረው አስቀመጡት። በመጨረሻም በሕመምና በችግር ለመሞት በቃ።

ሁለት ለ ዜሮ

በተለያዩ መጻሕፍት ላይ እንደተጠቀሰው ወደጉራዕ የዘመተው የግብፅ ሰራዊት በአሜሪካዊው ጄነራል ሎሪንግ እና ሌሎች ሁለት አሜሪካዊ ኮለኔሎች ያሉበት፤ በረጢብ ፓሻ ኤታማዦርነት የሚመራ በአግባቡ የሰለጠነ 25 ሺህ ሠራዊት ነው። በጉራዕ ጦርነት ላይ ኢትዮጵያ የገጠመችው ጦር በ19ኛው ክፍለዘመን ከመጡባት ጠላቶች ሁሉ (የዓድዋው ጣሊያንን ጨምሮ) በጦሩ ስፋት ግዙፉ ነው። አንድ የቱርክ ፓሻ፣ አንድ ስዊዘርላንዳዊ አድሚራል ፓሻ (ሙዚንገር)፣ አንድ አሜሪካዊ ጄነራል (ሎሪንግ) እና ወደ 6 አሜሪካዊ ኮለኔሎች የነበሩበት ነው። የኢትዮጵያ ጦር በአንፃሩ በራስ አሉላ እና በአፄ ዮሐንስ የሚመራ ሲሆን፤ የጠላት ጦር ከምሽጉ እንዲወጣ በማድረግ ከፍተኛ ጥፋት እንዲደርስበት አድርጓል። የግብፅ ሠራዊት ውጊያው ሲበረታበት የሸሸ ሲሆን፤ ለማምለጥ ባለመቻላቸው 3500 የሚያህል ሠራዊት ሊማረክ ችሏል። ከእነዚህም በተጨማሪ 20 መድፍ፣ 13 ሺህ ሬሚንግተን ጠመንጃዎች እና፤ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የጥይት ቀለሃዎች ሊማረኩ ችለዋል። ከመጀመሪያው ጥፋቱ ያልተማረው የግብፅ ጦር በዚህ የጥቂት ቀናት ውጊያ የቀደመ ሽንፈቱን ደገመ።

ኩፊት

ኩፊት ላይ በተደረገው ጦርነት የማህዲስቱ የኦስማን ዲግና ሠራዊት ሙሉ በሙሉ ተደመሰሰ። ምንም እንኳ ኢትዮጵያውያን ድል ቢያደርጉም በጦርነቱ ብዙ ሰው አጡ። ብላታ ገብሩ እና አሰላፊ ሐጎስ ተሰውተዋል። አሉላ አባነጋ ሳይቀር በኩፊቱ ውጊያ ላይ ቆስሏል።

ራስ አሉላ አባነጋ እና አጼ ዮሃንስ ፬ኛ በሂወት ስምምነት ላይ የገቡትን ቃል አክብረው ኃላፊነታቸውን ቢወጡም፤ ግብፅና እንግሊዝ ግን የምፅዋን ወደብ ለጣሊያን ለቅቀው በመውጣት በኢትዮጵያውያን ላይ ታላቅ ክህደትን ፈፀሙ።

ሰሐጢ

ከወሎው ዘመቻቸው በኋላ የጣሊያን በሰሜን በኩል የሚደረግ መስፋፋት እንደተሰማ፤ ንጉሠ ነገስት አፄ ዮሐንስ ወደ ‹ሰሐጢ› ምሽግ ዘመቱ። ወደሰሐጢ የበዛ ቁጥር ያለውን ጦራቸውን ይዘው የተጓዙት ንጉሡ፤ ጣሊያን ከጠንካራው ምሽግ አልወጣም ብሎ አስቸገራቸው። ድርብርብ መርዶ ዜናዎችም ደረሷቸው። የመጀመሪያው የልጃቸው የአልጋወራሹ የራስ አርአያ ሥላሴ ታሞ መሞት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የንጉስ ተክለሃይማኖት በደርቡሾች የመሸነፋቸው ዜና ነው። ንጉሠ ነገሥቱ የሰሐጢውን ምሽግ ሳይሰብሩ ወደመናገሻቸው መቐሌ ተጉዘው ሐዘን ከተቀመጡ በኋላ፤ ሌላ የመርዶ ዜና ደግሞ ተሰማ ሁለቱ ንጉሦች ተክለሃይማኖት እና ምኒልክ በዮሃንስ ላይ ማመፃቸው ተወራ።

ምንሊክ እና ተክለሃይማኖት አንዱ ቢወረር ሌላኛው ለማገዝ የተስማሙ ቢሆንም፤ የዮሃንስ ሠራዊት ወደጎጃም በዘመተ ጊዜ ምኒልክ ተክለሃይማኖትን ባለመርዳታቸው የጎጃም ሠራዊት በዮሃንስ እጅ አለቀ። ከጦርነቱ ድል በኋላም ዮሃንስ የወንድሞቻቸውን የኢትዮጵያውያን ደም ስላፈሰሱ እጅጉን አዘኑ።

መተማ

ደርቡሽ በጎንደር ገብቶ ህዝቡን እና ካህናቱን ማረዱ፤ እንዲሁም አብያተ-ክርስቲያናትን ማቃጠል እንደተሰማ፤ ከዮሐንስ ጋር ጦርነት መደረጉ አይቀሬ እንደሆነ ታወቀ። በኢትዮጵያውያን ላይ ከፍተኛ የሆነ የበቀል ስሜት ይነበብ ነበር። ዮሐንስም የሃገራቸውን ሰው ምኒልክን ከመውጋት፤ ደርቡሽን መውጋት መረጡ።

አፄ ዮሐንስ ወደመተማ ሲዘምቱ “መጣሁብህ፤ እንደሌባ በድንገት መጣብኝ እንዳትል ተዘጋጅተህ ጠብቀኝ” ብለው ወደደርቡሽ መልእክት ላኩ። ደርቡሽም ኢትዮጵያውያንን በሜዳ ላይ ከመግጠም በአጥር ውስጥ ሆኖ መግጠም የተሻለ መሆኑን ስላወቀ፤ ከግንብ ኋላ መሽጎ ለመዋጋት ተዘጋጀ።

ኢትዮጵያውያን ከውጊያው ቦታ እንደደረሱ የደርቡሽን ግንብ እንደደረመሱና ወታደር ከህፃን፣ ወንዱን ከሴት ሳይለዩ እንደፈጁ፤ በተክለፃዲቅ መኩሪያ መጽሐፍ ላይ ሰፍሯል። ድሉ የኢትዮጵያውያን እንደሚሆን በደርቡሽም በዮሃንስም ሠራዊት ዘንድ የታወቀ ሆኖ ሳለ ግን፤ ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት ዮሐንስ ሰሩ። እሱም ንጉሥ ሆነው ሳለ እንደተራ ወታደር ከሠራዊቱ ጋር ወርደው መጋጠማቸው ነው። እንደ ሐበሻ ስርዓት ንጉሥ ያዋጋል እንጂ አይዋጋም።

ቀጥሎ ያለውን ታሪክ ብላቴን ጌታ ኅሩይ እና ቴዎባልድ አፄ ዮሐንስ በተባራሪ ጥይት መመታታቸውን ያብራራሉ። የኢትዮጵያ ጦር ውስጥ የንጉሡ መመታት እንደተሰማ ሠራዊቱ በእጁ ላይ የገባውን ምርኮ እየያዘ በየአቅጣጫው ወደእየአገሩ ተመለሰ። ቴዎባልድ እንደሚነግረን ደርቡሾች ካሁን አሁን ኢትዮጵያውያን ተመልሰው መጡብን እያሉ ሙሉ ቀን ሲጠባበቁ ቆይተዋል። የመጋቢት ፩ አመሻሽ ላይ ግን የንጉሡ መሰዋት ተሰማ። የኢትዮጵያውያን ነገር፤ ግራ ያጋባቸው ደርቡሾች ነገሩን በመጠራጠር ሰላይ ላኩ። ወደየአቅጣጫው የሚሸሽ እንጂ የሚዋጋ ኢትዮጵያዊ እንደሌለም ተረዱ። የንጉሡን ሬሳ የተሸከሙ መኳንንትም ወደ አትባራ ወንዝ አቅጣጫ እየተመለሱ እንደሆኑ ሰሙ። ከአንድ ቀን ድካም በኋላም መጋቢት ፪ ላይ የአትባራ ወንዝ መሻገሪያ ላይ ደርሰውባቸው፤ የንጉሱን ሬሳና የመኳንንቱን አንገት ቆርጠው በደስታና በሽለላ ወደሃገራቸው ተመለሱ።

አበርክቶ

ንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሃንስ ፬ኛ ለኢትዮጵያ ሃገራቸው ብዙ የደከሙ መሪ ነበሩ። ደሴና አዲስ አበባ በአፄ ዮሐንስ ዘመነ-መንግሥት የተከተሙ ናቸው። አፄ ዮሐንስ ፬ኛ ደሴን በ1882 እ.አ.አ. ከትመዋታል። ንጉሥ ምኒልክ ደግሞ አዲስ አበባን እ.አ.አ በ1886 የመሰረቱት በአጼ ዮሃንስ ፬ኛ ዘመነ-መንግሥት ነው። ደሴ የተከተመችው፤ በዚያው ዓመት ለታየችው ኮሜት ማስታወሻ ሲባል የተመሰረተች ከተማ ናት።

ዋይልድ እንደፃፈው ንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ የባሪያ ንግድ እንዲቀር አዋጅ አስነግረው ነበር። ሲነግዱ የተገኙም እንዲቀጡ ሆኗል። ቀይ፣ ቢጫ እና አረንጓዴ የሆነ ባንዲራ ለኢትዮጵያ ያስተዋወቁት አፄ ዮሐንስ ናቸው። በአፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ የዚህ ባንዲራ ከላይ ወደታች ተርታ እስኪቀየር ድረስም፤ የሃገሪቱ ባንዲራ በመሆን አገልግሏል።

የመጀመሪያዎቹ ክሊኒኮች በዓድዋ እና በጎንደር እንዲሰሩ አድርጓል፡፡ ሮልፍ የተባለ ሃገር ጎብኚ እንደገለጸው ዮሃንስ በ1886 የኩፍኝ ክትባት ከመኳንንቱ ጋር ወስዷል፡፡ ዘመናዊ ህክምና እንዲጀመርም ከውጭ ሃገር ሃኪሞች አስመጥቷል። ዋይልድ እንደሚለው ከአፄ ዮሐንስ በፊትና በኋላ ኢትዮጵያን ጎብኝቶ ትልቅ የኑሮ ለውጥ በህዝቧ ዘንድ አይቷል። ከዮሃንስ በኋላ የመጡ መሪዎችም የተሻለ ንቃት ያላቸው እንደነበሩም ዋይልድ ምስክርነቱን ሰጥቷል።

ስለአፄ ዮሐንስ ብዙ መፃህፍት ተፅፈዋል። ብዙ የመድረክ ላይ መወድሶችም ቀርበዋል። በኢትዮጵያውያን ዘንድም እንደተከበሩ የሚኖሩ ንጉስ ናቸው። ለኢትዮጵያ በነበራቸው ፍቅር ላይ ጥያቄ ለሚያነሱ ወገኖች ግን “ከራስ በላይ ምን ይሰጣል?” ብዬ ለመሞገት እወዳለሁ። ህይወትን አሳልፎ ከመስጠት የሚበልጥ የሃገር ፍቅር የለምና!!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top