ማዕደ ስንኝ

እውነትም እኛ… ልዩ ነን!

ላለመስማማት ተዋደን

ላለመዋደድ ተስማምተን

ላለመኗኗር ተቧድነን

ላለመፋቀር ተቃቅፈን

ላለመጋባት ተጫጭተን

ይሄው ዙረን ዙረን… እዚያው ነን!

አጀብ ዘመናችንን ቸብችበን

በኪሳራችን ቶጅረን

የመጠላለፍ ጽዋችንን፤

ተራ በተራ…. ጨልጠን

ይሄው… ሃቻምና‘ምና… ተነበርንበት

እዚያው ዞረን ዞረን… ግጥም አልንበት፤

እንግዲህ ማን አለ እንደኛ

ዞሮ ዞሮ ተነበረበት የተኛ

ማተብ ጠባቂ ሀቀኛ

ብርቅም አይዶለን እኛ?…

እንደ ዋሊያ እንደ ኒያላ

እንደጭላዳ እንደምንሊክ ድኩላ

በሌላው ዓለም የሌለን

እኛኑ ታግለን የጣልን

ቀይ ቀበሮን ተመስለን

ልዩነታችንን ያሳየን…

እውነትም እኛ ልዩ ነን

ማንም ማንም ያልበለጠን

ሃቻምና‘ምና… ተነበርንበት

ፈጥነን ሮጠን በመገኘት

ወደር አቻ ያልተቸረን

እውነትም እኛ አንደኞች ነን።

እውነትም እኛ ልዩ ነን።

ይሄው ዙረን ዙረን… ተገጣጠምን

አንድ ላንሆን ተማምለን

ለባለጊዜ ተመቻችተን

ጉሮሮ ለጉሮሮ ተያይዘን

እልካችንን ውጠን…

ማን አባቱ ሊደፍረን ብለን…

አንድ ራሳችንን አሸንፈን

አንድ ራሳችንን ጥለን

አንድ ራሳችንን ገለን

ይሄው… ባሸናፊነት እንስቃለን

“እኛ ልዩ ነን…” እንላለን።

በራሳችን እንመጽታለን።

በኪሳራችን እንከብራለን።

በሽንፈታችን እንኮራለን።

አዎን… ልዩ ነን እንላለን።

አጀብ ጊዜያችንን ፈጅተን

ወገናችንን ነውረን

እራሳችንን አጰጵሰን

ሌላ ሌላውን ኮንነን

ይሄው ዞረን ዞረን…. እዚያው ነን፤

የእዝን ንፍሮ እየቃምን

ስውር ሠርግ እየበላን

ለብቻችን እየሞትን

ለብቻችን እየሳቅን

ይሄው እኛነታችንን አልረሳንም

ሃቻምና‘ምና… ተነበርነበት ዞር አላልንም

አንደኝነታችንን አለቀቅንም፤

ይሄው…

ላለመስማማት ተዋደን

ላለመዋደድ ተስማምተን

ላለመኗኗር ተቧድነን

ላለመፋቀር ተቃቅፈን

ላለመጋባት ተጫጭተን

ይሄው ዙረን ዙረን… እዚያው ነን

ሃቻምና‘ምና… ተነበርንበት

ፈጥነን ሩጠን… ግጥም አልንበት፤

እውነትም አኛ ልዩ ነን

እውነትም እኛ ጀግኖች ነን

ወደር አቻ ያልተቸረን

አቻዮ ዲፌሮ የተሰኘን

ማንም ምንም ያልበገረን፤

እውነትም እኛ ልዩ ነን…

ወገን ወገኑን ሲበላ ዕያየን

የምንስቅ፥ የምንፈግግ ጉዶች ነን

ይሉኝታ ላይ ተኝተን

እንደር ብለን ተሸጠን

እየሞትን እኖራለን…

ሳንኖር እንሞታለን

እውነትም ልዩ ፍጡር ነን!

ዋልያ ነን የምንል

ጭላዳ ሆንን የምንል

ቀይ ቀብሮን የምንወክል

እውነትም እኛ ልዩ ነን

ማንም ምንም ያልታከለን

አጀብኛ የታደለን…

እውነትም እኛ ልዩ ነን!!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top