ከቀንዱም ከሸሆናውም

እውቅ ምሳሌዎች

ታላቅ፣ ተራ እና የማይረባ ከንቱ ሰው

ታላቁ የቻይና ፈላስፋ እና መምህር ኮንፊሽየስ፤ በተራራ ተቀምጦ ድንኳን ዘርግቶ እያስተማረ በነበረበት አንድ ቀን፤ ደቀመዝሙሩን ትዙ ሉን ውሃ እንዲያመጣለት አዘዘው፡፡

       ትዙ ሉም ውሃ ሊያመጣ ወደ ወንዝ ሲወርድ ነብር ያጋጥመውና፤ ነብሩን በጭራው ይዞ ይገድለዋል፡፡ በሰራው ጀብድም ኩራት ስለተሰማው፤ የነብሩን ጅራት ቆርጦ በኪሱ ከትቶ፤ አምጣ የተባለውን ውሃም ቀድቶ፤ ወደ ኮንፊሽየስ ድንኳን ይመለሳል፡፡

    ኮንፊሽየስንም እንዲህ ሲል ይጠይቀዋል፦

“አንድ ታላቅ ሰው፤ እንዴት አድርጎ ነብርን ይገድለዋል?”

ኮንፊሽየስም “አንድ ታላቅ ሰው፤ ነብር የሚገድለው ጭንቅላቱን ይዞ ነው”

“ተራ ሰውስ?”

“አንድ ተራ ሰው፤ ነብር የሚገድለው ጆሮውን ይዞ ነው”

“የማይረባ ከንቱ ሰውስ ?”

“የማይረባ ከንቱ ሰው ነብርን የሚገድለው ጭራውን ይዞ ነው”

     ትዙ ሉ የኮንፊሽየስን መልሶች በሰማ ጊዜ፤ ከድንኳኑ ርቆ በመሄድ፤ የነብሩን ጭራ ከኪሱ በማውጣት ወረወረው፡፡

      በንዴት ውስጥ ሆኖም፦

      “መምህሬ ከወንዝ አጠገብ ነብር እንዳለ እያወቀ የላከኝ፤ በነብር ተበልቼ እንድሞት እና እንድገደል ስለሚፈልግ ነው” አለና፤ ኮንፊሽየስን ለመግደል በኪሱ ድንጋይ ይዞ ሄደ፡፡

    ኮንፊሽየስ ጋር በደረሰም ጊዜ፤ በድጋሚ እንዲህ ሲል ጠየቀ፦

“አንድ ታላቅ ሰው፤ ሰው ሊገድል የሚችለው እንዴት ነው?”

“ታላቅ ሰው ሊገድል የሚችለው የሚፅፍበትን ብዕር ተጠቅሞ ነው”

“አንድ ተራ ሰው፤ ሰው ሊገድል የሚችለው እንዴት ነው ?”

“ተራ ሰው፤ ሰውን ሊገድል የሚችለው፤ ምላሱን ተጠቅሞ ነው”

“የማይረባ ከንቱ ሰውስ እንዴት አድርጎ ሰው ሊገድል ይችላል?”

“የማይረባ ሰው ከሆነ ሰውን ሊገድል የሚችለው ድንከጋይ በመጠቀም ነው”

ትዙ ሉ የኮንፊሽየስን መልስ በሰማ ጊዜ፤ አሁንም እንደቅድሙ ከድንኳኑ ርቆ በመሄድ፤ መምህሩን ሊገድልበት የነበረውን ድንጋይ ወረወረው፡፡

    ትዙ ሉም ከዛ ጊዜ በኋላ፤ የኮንፊሽየስን የእውነት ታላቅ ሰው መሆን፤ አምኖ ተቀበለ፡፡ መምህሩን የሚያከብር ተማሪም ሆነ፡፡

አንድ ታላቅ ሰው፤ በነብር የተመሰለውን የሱ በሃሳብ ተቃራኒ የሆነ ጠላት፤ በጭንቅላቱ ይዞ (በሃሳብ በልጦት) ያሸንፈዋል፡፡ ተራ ሰው ግን፤ በነብር የተመሰለውን የሱ ተቃራኒ የሆነ ጠላት፤ በጆሮው ይዞ (በጣፋጭ ቃላት ደልሎ) ያሸንፈዋል፡፡ የማይረባ ከንቱ ሰው ደግሞ፤ በነብር የተመሰለውን የሱ ተቃራኒ የሆነ ጠላት፤ በጭራው በመያዝ (ከጀርባው ሆኖ በሐሜት እና ስሙን በማጥፋት) ያሸንፈዋል፡፡

ጀግና ማን ነው

ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ አንድ ጊዜ ከጠንካራ ውጊያ በኋላ፤ ድሉ የቴዎድሮስ ይሆንና፤ ተደግሶ እየተበላ እያለ፤ ሁሉም ይስቃል፤ ካሳ ግን ተክዞ ነበረ፡፡ ለምን እንደተከዘ ሰዎች በጠየቁት ጊዜ፤ ጥያቄያቸውን በጥያቄ መለሰላቸው፤ እንዲህም ሲል

“ለመሆኑ፤ ለናንተ ጀግና ማን ነው ?”

ሰዎቹም “ጀግናማ አንተ ነህ መሪያችን” ሲሉ መለሱለት፡፡ ልክ እንዳልሆኑ ነገራቸው፡፡ ከዚያም የብዙ ሰው ስም ጠሩ፤ ሁሉንም ተሳስታችኋል ሲል መለሰ፡፡ በመጨረሻም፤ መልሱን ለማግኘት ሲቸገሩ ጊዜ፤ መልሱን እንዲነግራቸው ጠየቁት፡፡

ካሳም እንዲህ አለ “ዛሬ ያሸነፍናቸው ሰዎች፤ በብርታታቸው ወቅት ጀግና አልነበሩምን? አሁን ግን ጊዜ የኛ እጅ ላይ ጣላቸው፡፡ በውጊያው የሞቱ ጓደኞቻችንስ፤ በጀግንነት ከኛ የሚያንሱ ነበርን? አልነበሩም፤ ጊዜ ግን እነሱን ሟች፤ እኛን ደግሞ ህያው አደረገ፡፡ ጊዜ እኛን ዛሬ አሸናፊዎች እንዳደረገን፤ ነገ በኛ ላይ ፊቱን ሊያዞር ይችላል፡፡ የነገን ስለማናውቅ፤ ምንም ማለት አንችልም፡፡ ጊዜ ያነሳል፤ ጊዜ ይጥላል፡፡ ስለዚህ በአንድ ወቅት ጀግና የነበረ፤ በሌላ ወቅት ተሸናፊ ይሆናል፡፡ ጊዜ ግን ሁልጊዜ አሸናፊ ነው፡፡ ጀግና ሊባል የሚገባው ጊዜ ብቻ ነው፡፡ የሰው ጀግና የለውም፤ የጊዜ እንጂ” ሲል መለሰላቸው፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top