ሌሎች አምዶች

እናትና ሴት ልጅ ምን መሰል ፍቅር አላቸው?

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በጎርጎሪዮሳዊው ቀመር “ማርች 8” በእኛ አቆጣጠር ደግሞ ዘንድሮ እንደ ሁልጊዜው በየካቲት መደምደሚያ ዕለት ተከብሮ ይውላል።

በዚህም መሰረት በተቋማት ደረጃ የተቆረቆሩና በግለሰብም በቡድን በቡድን የተደራጁ ማኅበራት፣ እንዲሁም ሌሎች ድርጅቶች ይህን ታላቅ ቀን በተለያየ መሰናዶ ያከብሩታል። ቤተ-እምነቶች ሳይቀሩ “የእናቶች ቀን፣ የእህቶች ቀን፣…” ብለው ለዝክር ያበቁታል። ውይይቶችና የመድረክ ትዕይንቶች ይካሄዳሉ።

እንዲህም ሲሆን ከውይይቶቹ መሐከል ቤተሰባዊው ጉዳይ ይጠቀሳል። የዚህ ጽሑፍም የሚያተኩረው ወደ እርሱ ስለሆነ በጥያቄው እንጀምረው ዘንድ የአንባቢን ትዕግሥት እንጠይቃለን።  

“በእናቶችና በሴት ልጆቻቸው መሐከል ያለው ግንኙነት እንደ ማር የጣፈጠ ነው? ወይስ እንደ ኮሽም የኮመጠጠ? ፍቅር ወይስ ጥላቻ?”

ይህ ጥያቄ ምናልባት ለአያሌዎቻችን ግራ ሊሆንብን ይችላል። እናትን ያህል ርኅሩኅ እንዴት በጥላቻ ትጠረጠራለች? የማሕጸኗ ፍሬ የሆነችው ልጅስ ስለምን እናቷን ትጠላለች? የምንል አንታጣም። በልጅቷ ላይ ፈርደን ጥፋተኛ እርሷኑ ብቻ አድርገን ወላዲቱን አወድሰን ተወላዲቱን ወቅሰን የምንገኝም አንጠፋም። እናቲቱን በርኅራኄ ልጅን በጭካኔ ተራ አሰልፈን በጭፍን የምንበይንም እንኖራለን። በዚያው ልክ ደግሞ አረጋዊቷን   “ጎታች” ወጣቷን “ተራማጅ” አድርገን በዕድሜ የላቀቸው እናት የልጅዋን እርምጃ የገታች በሞራል ያደቀቀች፣ በመንፈስ ያደኸየች አድርገን ለልጅቷ ቀኝ እንሰጣለን። እናትን እንኮንናለን። አለመግባባት ተፈጠረ ሲባል ሁሉም የግሉን ፍርድ ይሰጣል።

ይህ እንግዲህ በዕለት ግምት፣ በሰሞን ኩርፊያ ላይ ያተኮረ በሚሆንበት ጊዜ ነው። ብያኔውም ምስክርነቱም ያኔ ነው። በተረፈ እናትና ሴት ልጅ የሚያባብሳቸው፣ የሚያመካኝባቸው ሥር የሰደደ ምክንያት አለ ብሎ የሚያስብ ከስንት አንድ ቢሆን ነው። “አዬ የእናንተ ነገር”  ብሎ ጉዳዩን ከማንኳሰስ፤ ከረር አድርጎ ያጤነ ያውጠነጠነ ሰው በኅብረተሰባችን ፍጹም የለም ለማለት ያስደፍራል። እናት ርኅርኅት፣ አዛኝ፣ ልጅ ደግሞ አፍቃሪ፣ ጧሪ ከመሆን አልፈው ወደ ጥላቻ ይራመዳሉ አይባልም። በሸበተ እሳቤ ላይ የተመረኮዘ አመለካከት ሆኖ ለዘመኑ አልጠቀመም ማለት ነው እንጂ የሚከፋ አልነበረም።

ፈረንሳያዊው የሥነ ልቡና ተንታኝ ቤርትራን “እናቶችና ሴት ልጆቻቸው ጠበኞች ናቸው” ማለት አይቻልም። “ፍቅረኞች ናቸው” ለማለትም አያስደፍርም። ፍቅርና ጥላቻን በአንድነት የተላበሱ ናቸውና” ያሉት ልዩ ትርጓሜ የሚቸረው አነጋገር ነው።

የሥነ ልቡና ተጠባቢዎችና ተንታኞች የሥነ ባሕርይ ተመራማሪዎችና የማኅበራዊ ጉዳይ ፈታሾች በዚያው በእናቶችና በሴት ልጆች መሐከል ዘወትር ስለሚከሰተው ያለመጣጣም እንደመከሩበት፣ ትውልድን በትውልድ እየተኩ፣ አልፈዋል። ጊዜ ያዘመናቸው ጥበብ ያበለጸጋቸው ሊቃውንት ዛሬም በነገሩ ከመጥለቅ በምርምር ከመርቀቅና መፍትሔ ለመሻት ከመጨነቅ የቦዘኑበት ወቅት የለም። ጭጋጋማው የእናቶችና የሴቶች ልጆች ግንኙነት ፈክቶ ሊገኝ የሚችልበትን መንገድ ለመቀየስ ጥረት ያደርጋሉ። መንሥኤውን ለማወቅ የበቃ ባይኖርም ጥቂት መፍትሔውን ሊጠቁም ያስቻለ የፍተሻ ውጤትም እስካሁን አልተገኘም።

“ሁለት መሰል ጾታዎች በአንድ ቤት ውስጥ ተቀምጠው፤ የአንድ ቤተሰብ አባል ሆነው መቅረባቸው ራሱ የውድድሩን መድረክ ያሰፋል። የቅናትንና የምቀኝነትን በር ይከፍታል። በቁመና በመልክና በተሰጥኦ ረገድ ያለውን ፉክክር ያጠነክራል። የሚለው የሸበተ ሰነድ ትረካ አሁንም ቢሆን ሞቶ ወደ መቃብር አልወረደም። ይልቁንም በዘመኑ ጠበብት “እኔ ነኝ” ያለ ሥፍራ ተችሮት በማስረጃነት እየቀረበ ለምርምር መጎልበቻ፣ ለውጥን ቅር መፍቻ ሊሆን በቅቷል።

የእናትና የሴት ልጅ ግንኙነት ፍቅርም ጥላቻም ሳይሆን የጥላቻ ፍቅር ነው ብለው በአንድነት ያመኑበት የሥነ-ልቡና ሊቃውንት የምርምር ወረቀቶቻቸውን ያቀለሙበት ፍተሻ ወደ አብያተ ተዋንያቱ ጎራም ጥቂት ወልከፍ ሳይል አልቀረም። እናቶችና ሴት ልጆቻቸው ከጥላቻ ፍቅር ተጨምደው፣ ተቀናንተው፣ ተመቀኛኝተው የሚኖሩት ዘወትርና አብዛኛውን ቦታ ላይ ነው ቢባልም እንደ ተውኔቱ ሙያ በዚህ ረገድ በብርቱ ሊጎንጥ የቻለ የለም ሲሉ አስምረውበታል።

እናትም ሴት ልጅም ተዋናይት የሆኑበት ቤተሰብ ግዙፍ የጥላቻ ፍቅር የነገሠበት ሁኔታ ውስጥ ያሉበትና ቅናትና ምቀኝነት ያየሉበት፣ ፉክክርና ውድድር የተጎራበቱበት መሆኑን ሳይዘረዝሩ አላለፉም። በፌዴራዊት ጀርመን የተጠናቀቀው አንድ ሰነድ አክሎ እንዳመለከተው ለአያሌ ዓመታት “ኮከብ” ተብላ እንደፈርጥ ስትንቆጠቆጥ የኖረችውን እናት ቦታ እያስለቀቀ አስከፊ ገጽታውን ይዞ ይቀርባል። ቅናት ሲበረክት ወደ ምቀኝነት ሄዶ ቀዬ ማተራመሱ ኅብረተሰብ ማመሱ እንዲያ ሲልም ሀገር ማበጣበጡ መቼም የማይቀር ነውና ይህ በሚሆንበት ጊዜ እነዚህ ሁኔታዎች ተከስተዋል።

“ተውኔት” ስንል በኪነ ጥበብነቱ ወስደን ተጓዳኞቹን ዜማና ውዝዋዜንም መጨመር ይኖርብናልና እናትና ሴት ልጅ በዘፋኝነት ወይም በዳንኪረኝነት የተሰማሩ ከሆነ ያው ተብሎ ያለቀለት የጥላቻ ፍቅር ሕልውናውን አስመስክሮ ሆድ ለሆድ ያሻከረበትን፣ ያቃቃረበትን ሁኔታ የዘመናችን ፈታሾች ሳይጠቃቅሱ አልተውትም።

ውስጥ ውስጡን ባይዋደዱ ከውስጥ ባይፋቀሩ እንኳ ወላዲቷና ተወላዲቷ በአንድነት የዘፈኑበት ጊዜ ጥቂት አይደለም። አውራጅና ተቀባይ መሪና ተመሪ እየሆኑ ዜማ ያንቆረቆሩበት ቅኝት ያሳመሩበት ወቅት ሞልቷል። ብሎም ቢሆን የተመልካች ዓይን ተሰክቶ የሚቀረው የአድማጭ መወደስ የሚጎርፈው በወረት ለአዲሲቷ፣ ለጉብሊቷ ዘፋኝ ነውና በዚሁ ሳቢያ እናት ኩርፊያ ታመጣለች። ዳግም አብሮ በመድረክ ላይ ላለመገኘት ይምላሉ። ይገዘታሉ። በማግስቱ ግን “ለምን እሷ ብቻ ትታወቅ” በማለት በአልሞት ባይ ተጋዳይነት እንደገና አብረው ይቆማሉ፣ ይወዛወዛሉ፣ ዳንኪራውን ይረግጣሉ።

“እኔ የእርሷ ነገር አይገባኝም አብረን ስንዘፍን ትስቃለች ፣ በኃላ ታኮርፋለች። በአንድ መድረክ መውጣታችን ይቅር ስል ደግሞ ትቆጣለች ተመልካች ስሜን እየጠራ ሲያጨበጭብልኝ ደግሞ ትገላምጠኛለች። ለእርሷ ሲጨበጨብ የሳቅሁ እንደሆነ ደግሞ ለምን ታላግጭብኛለሽ ትልና የጎሪጥ ታየኛለች” ያለችው ጀርመናዊቷ ጉብል ተዋናይትና ዘፋኝ ሱዛን ዑላንስ የእናቷን ነገር ስታነሳ እንደ እሬት ይመራታል።

        በእጅጉ የሚገርመው ደግሞ አመዛኙ እናቶች ሴቶች ልጆቻቸው እንደ እነርሱ በተውኔቱ፤ በኪነቱ እንዲሠለጥኑላቸው በመሻት፣ በሙያው እንዲታወቁላቸው በመመኘት፣ ብዙ ገንዘብ ከፍለው የማስተማራቸውንና ለዕድገት የመጓጓታቸው ነገር ነው። ፍቅሩ በጥላቻ ፍቅር ተለውጦ የሚበልጠውና የሚደበዝዘው በኃላ ነው። “ኮከብ” እናት ድንገት በደመና ሲሸፈኑ፣ በትኩስ ጉም ሲጀቦኑ ነው። ኩርፊያውና ፊት ማንጠልጠሉ፣ ለምቦጭ መጣሉ ያኔ ነው። ግልምጫውና ፍጥጫው ያኔ ነው።

በለማጅነታቸውና በሠልጣኝነታቸው፣በኋላም በጀማሪነታቸው ጊዜ ሴቶችም ልጆችም  ቢሆን ለተዋናይት እናታቸው ፍቅር የላቸውም አይባልም። በተወላዲነታቸው ወላዲቱን ይወዳሉ። ይሁንና በወረተኝነት ሰሚ ጆሮውን ሲከፍትላቸው፣ ተመልካች ዓይኑን ሲጥልባቸው፣ በጥበብ ቃል ሲሞሽራቸውና “ኮከብ” ሲላቸው ወይም ከንዑሳት ከዋከብት አንደ አንዷ ሲያያቸው መተቤት ይጀምራሉ። “እናቷማ አርጅታ ሲባል ልጅቱ በልጣ አምጥቃ እርቃ ሂዳ” ሲባል ትዕቢትና ተድላ በአንድነት ተደባልቀው፣ አሸዋና ኖራ ሆነው ጎጆ ያዋቅሩባቸዋል። እናትን መናቅ ይመጣል። የሻጉራ ማየት ይበዛል። አትንኩኝ ይበረክታል። እንዲህም ሲሆን ነገር ወዲያና ወዲህ እያሉ መውደድ ይጠነፍፋል። ቤተሰባዊ ጣዕም ይጠፋል። ሥነ-ሕይወታዊ ዝምድና ስላላቸው ብቻ ይጠያየቁ ይሆናል። በተረፈ ከልብ የመነጨ መተሳሰብና መተዛዘን የታከለበት ግንኙነት አይኖራቸውም። “የጥላቻ ፍቅር” እውን ይሆናል።

እናት በቅናት እንዲያም ሲል በምቀኝነት ይታመማሉ። እያገገሙ ይነሳሉ። እያገረሸባቸውም ይቸገራሉ። ልጅ ደግሞ በኩራት፣ ውሎ እያደረም በትዕቢት ትወጠራለች። ልበ ድፍን ትሆናለች። እንዲህና እንዲህ እያሉም የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው በኪነ-ጥበብ ጎዳና ይጓዛሉ። ተጽናንተው ያዝናናሉ ወይም አዝናንተው አዝነው ይጽናናሉ። ጊዜም አርጅቶ ይገረጅፋሉ።  ዓመቱም ያፈጃል። ከዚያስ? ከዚያማ ምኑ ይጠየቃል? አሮጌው ይሞታል። ጉብሉ ያረጃል። ወይም አሮጌው ይኖራል። ጉብሉም ይሞታል። አቆራራጩ የጥላቻ ፍቅር ግን በወጣትነት እንደከበረ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ ሌጊዜ አዛውንትነትም ምስክር እንደሆነ ይቀራል። መንሥኤውን መመርመር የቻሉ ሊቃውንት፣ መፍትሔውን  ለማግኘት የሚያበቁት ጊዜም እንደማይኖር ጥናታዊ ሰነዶች በየጊዜው ሲወጡና እንዲሁም ታዛቢን ሲያመካክሩ መኖራቸውን እናያለን።

“ሴት ልጅ እንደ እናቷ ተዋናይት ወይም ከያኒት ሆና ባትገኝስ?” የሚሉ አንዳንድ ተመራማሪዎች አልጠፉም። በእርግጥም አሉ። ዳሩ ግን ይህ መፍትሔ ሊሆን አልቻለም። “እንዲያው ከያኒ፣ ተዋናይ፣…” ተባለ እንጂ ዝምድናው የከሰመው በተውኔት አዳራሹ ብቻ አይደለም። በባልትና ውድድር ይጀምራል። የውበት ፉክክር በገበያ ቀን ይደራል። ከማጀት እስከ አደባባይ ይቀጥላል። ብርቱ ጠብ እጅግም ጎልቶ አይታይም። ይጠያየቃሉ፣ ይነጋገራሉ፣ ይሳሳማሉ፣ አይጨካከኑም። ሌላው ቀርቶ አንዱ የሌላውን እናት የልጅቷ፣ ልጅቱ የእናቷን ክፉ የተመኘችበት ጊዜ እውን ሆኖ የተደመጠበት ወቅት አልተዘገበም። ግን አይፋቀሩም። ፍጹም ጠበኞችም አይደሉም። ታድያ ምን ሊባሉ ይበቁ ይሆን? የዚህ ምላሽ በየወቅቱ በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ አማካይነት ተነግሯል። ምላሹ ዛሬም እንደትናንቱ ያው ስለሆነ አሁንም ይደገማል። “የጥላቻ ፍቅር” የሚባለው ነው። ይኸው ብቻ ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top