የጉዞ ማስታወሻ

አሰብን አየኋት

በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1869 ዓ.ም. በ6000 ዶላር በሁለት ወንድማማቾች ለጣሊያን ተሸጠች። ስምምነቱ ያስደንቃል፣ በዛሬ ዘመን 185,933 ዶላር ይተመናል፣ ምንዛሪው አምስት ሚልዮን ሠባት መቶ ሺህ ስልሳ ሦስት ይሆናል…

በአሣ ምርቶቿ ትታወቃለች። በቅይጥ ማንነት ገናና የአፋር ወንድማማች ሱልጣኖቹ ከሸጧት ወዲህ፤ ከተማዋ ለተለያዩ ቅኝ ገዥዎች ጡንቻ ማሳያ ነበረች። የመጀመሪያዋ ጣሊያን የገዛት ከተማም ነበረች። የደቡብ ኤርትራ ፈርጥ አሰብ።

የዛሬው ጽሑፌ ጥንስስ ብዙዎች የይለፍ ወረቀት ይዘው ይገቡባት የነበረች፣ ኅብረ ቀለማቷ ሲቆጠር ሰማያዊና ነጭ ከለር የሚያይልባት፣ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ በተቀሰቀሰው ጦርነት ያጣናት፣ ብዙ ኢትዮጵያውያን እትብታቸውን ለእሷው ትተው ስለተሰደዱባት፣… የወደብ ከተማ ቀደምት ነዋሪዎች (እኔን ጨምሮ) የኢትዮ ኤርትራን ድንበር መከፈትና እርቅ ተከትሎ በድጋሚ ስለጎበኘናት ከተማ ይሆናል።

ሐጎስ ጊላይ

ቁመተ መለሎ ጠይም ደልዳላ ሠውነት ያለው ሲሆን፤ የኪሮስ ዓለማየሁን ዘፈን ከነክራሩ ሲጫወት ቁጭ ብድግ ያሰብላል። መድረክ ሲመራ ቋንቋችንን የማያውቅ ፈረንጅ እንኳ ቢገኝ ሳያፍር ያጨበጭብለታል። መድረኩ ላይ በአረብኛ፣ በትግርኛ፣ በጣሊያንኛ፣… በጉራማይሌ ቃላት በመደስኮር ስሜትን ይገዛል። የሀበሻ ልብስ ለብሶ መድረኩ ላይ ሐጎስ ጊላይ ነኝ፤ አዲ ጉዶም”  ሲል የቀይ ባህር ንፋስ ከባህሩ ጋር በስልት ይደንሳል። ኦሮሞው ያፏጫል፣ አማራው ሐጎስ ጀግናው፣ ትግሬው ከበሮውን ይደልቅለታል፣ ኤርትራውያን ማማሚያ ሐጎስ ይሉለታል።

ከተማዋ እንደ ልዕልት የጫጉላ ሸርሸር የደመቀች ጊዜ፣ ከ20 ዓመት በኋላ ከተማዋና ህዝቦቿ እንዴት እንደጠበቋቸው ይናገራል። አሁን በዚህ ጊዜ እንኳ የጠርጣራውን አይበልናንዶሲያቀነቅን ባድመ ያለህ ይመስልሀል።

ጉዞ ወደ አሰብ ፩

(የኢትዮጵያውያን)

በህይወቴ ያስለቀሰኝ ሁነት የተከሰተው በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ምክንያት ድንበሩ ሲዘጋ ነው። ድንበሩ ሲከፈት የተደሰትኩትንም ያህል ተደስቼ አላውቅም። አሰብ ብዙ ያየሁባት፣ ክፉና ደጉን የለየሁባት፣ ወልጄ የከበድኩባት ከተማ ነች። እናቴን በተባራሪ ጥይት በእኩለ ሌሊት ያጣሁት እዚሁ ነው። የሚደንቅ የሙዚቃ ትርዒት ሀሌ ብን ጨምሮ ሠርቻለሁ፣ ከኪነጥበብ ባሻገር የወደብ ማሽኒስት ነበርኩ፤ ዋነኛ መዝናኛዬ ነበር። ድንበሩ መከፈቱን ተከትሎ በመላው ዓለም የሚገኙ የከተማዋ ተወላጆች ጥምቀትን ወደ ከተማዋ ሄዶ ለማሳለፍ የገንዘብ መዋጮ ተለመነ። በመላው ኢትዮጲያ የሚገኙ የተለያዩ ቀደምት የአሰብ ነዋሪዎች ጥር 9 ዲቼኤቶ ለመገናኘት ቀጠሮ ያዝን። ጥር 9. 2011 ዓ.ም. ከአዲስ አበባም፣ ከደሴም፣ ከኮምቦልቻም፣ ከወልደያም የመጡ 5 የህዝብ አውቶብሶች ዲቼኤቶን አጨናነቋት፣ በአባዱላና በተለያየ የቤት መኪና የመጡም ነበሩ። የዲጄኤቶ የቀድሞ ነዋሪ ልጆች ታዲያ በተለይም ‘አልማዝ ደሳለኝ’ ሻወር፣ ምግብ እና መኝታ አዘጋጅታ የጉዞ መሰናድኦችንን አሳመረችው። በማግስቱ እየተጨፈረ፣ እልል እየተባለ፣ ዘፈን እየተቀባበልን በረሀውን ‘ሀ’ ብለን ጀመርነው::

ወደ አሰብ እየሄድን እንደሆነ ማመን አልቻልኩም። የተማርኩበትን አንድነት፣ የታሰርኩበትን፣ በተደጋጋሚ ስሳለመው ብሶቴን የምነግርበት ሚካኤል ቤ/ክርሰትያን፣ ሜሎቲ ቢራ የተጎነጨሁበትና የቀሩ ወዳጆቼን በነበሩበት አገኛቸው ይሆን? የሚል ጥያቄ ለራሴ እያቀረብኩ በምናብ በረሀውን እያጋመስኩ ነው…

ኤሊዳርን አልፈን ማለዳ ከቡሬ እንደገባን ጭፈራው፣ መዝሙሩ፣ ፉጨቱ እየቀነሰ ሄዶ ለጥልቅ ዝምታ ቦታቸውን ለቀቁ፡፡ ጉዳዩ ህልምን የመጨበጥ ያህል ነበር፡፡ ልጅነታችንን እያስታመምን ወደ እትብታችን ቋጠሮ እየዳኽን አለማልቀስና አለመረበሽ እንደምን ይቻለናል?

መልካም አቀባበል ተደረገልን

ቡሬን እንዳለፍን አሰብ ልንገባ ጥቂት ኪሎሜትር እንደቀረን የሠው ጎርፍ ጠበቀን። በውስጤ የተቀበረው እምቅ ናፍቆት እምባ አስተፋኝ፡፡ የከተማዋ ወጣቶች በ5 አውቶብስ ተሞልተው እግር ለማጠብ ነው የመጡት። ድንኳን ሠርተዋል፣ ለቅሶው፣ መሬት መሳሙ፣ ከማቀፍ ማነቅ የበዛበት ፍቅር ተቀባበልን፣ እግራችንን ካጠቡን በኋላ አብረን ወደ ከተማዋ በጩኸት፣ በፌሽታ፣ በእሪታ የተመላለስንበትን ጎዳና ቋጨን።

አሰብ ሰቂር፣ አሰብ ከቢር፣ ነጋዴ ሠፈር፣ ካምቦ ሱዳን፣ አዲሱና አሮጌው ራሻን ካምፕ ዞርን፣ በሄድንበት ሁሉ ጭብጨባ፣ እልልታ፣ ሰላምታና ፈንዲሻ ጭምር በመርጨት አሰባውያን መድረሳችንን አሣመሩት። አሠብ ደመቀች፣ ለቤተ-ክርስትያን የገዛነውን ስጦታ ይዘን ምሣ ወደተዘጋጀልንና ብዙ እንግዶችን ለመያዝ ሰፊ ወደ ሆነው ሚካኤል ቤ/ክርስትያን ሄድን፣ ወደ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ያመራው ኦርቶዶክሱ ብቻ አልነበረም፡፡ ፕሮቴስታንቶችም ሙስሊሞችም አብረው ተጉዘዋል፡፡ አሰባሳቢው ማንነት አሰብ ምድር ላይ መወለድ ብቻ ነበር፡፡

ዝማሬው፣ ስብከቱ፣ ርህራሄውና ያሳዩን ፍቅር ለአንድ ንጉስ የተደረገ አቀባበል ይመስላል። ከመምጣታችን በፊት ለሁለት ቤተ ክርስትያንና (ለቤተክርስትያን የሚገቡ) መስጊድ (ለእስልምና የሚገቡ) ያመጣነውን ስጦታ ለሚካኤል አሰረከብን። ለካምቦሱዳን መስጊድ እና ለማርያም ቤ/ክርሰትያን ስጦታ ከሰጠን በኋላ ቀጥታ ወደ አሰብ ሰቂር መስጊድ ሄድን። ሚካኤል ከተቀበለን ሰው የማያንስ ህዝብ ተቀበለን፣ ጥቂት ቆይታ በኋላ ለማደሪያ ወደ ተዘጋጀልን ሚካኤል ብንመለስም ሁሉም ወደየፍላጎቱ ተበተነ፡፡

የአሰብ ቆይታ

በበነጋው ሁሉም ሐይማኖት ተከታዮች ያለ ልዩነት የማርያምን ታቦት ወደ ጥምቀተ ባህሩ ሸኘ። ከተማዋ ሁለት የተጠፋፉ ልጆቿን አገናኝታ የተኮፈሰች መሠለች፣ እሷው እንዳልገፋች በአዲሱ መንገድ እርቅም ሠላምም እኔ ነኝ ማለቷ ትዝብት ላይ ጥሏታል።

ጥር 12፣ 2011 ለመጀመሪያ ጊዜ የከተማዋ ታቦት በምንጣፍ ተከበረ። ቀይ ባህር ተሽሞነሞነች። ፀአዳ የለበሱ እንስቶች ወደቡ ስራ እንዲጀምር ሊቀ መልአኩን ጠየቁ። ፀበላችንን ተረጨን፣ አንድ ብር ሳናወጣ ሦሰተኛ ቀናችንን ይዘናል፡፡

በመጀመሪያ ዕይታችሁ የኳስ አቋም እንዳለው እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ። በኳስ ችሎታው የተጨበጨለት ሲሆን ለወደብ ክበብ ተጫውቷል፣ በኳስ መዝናናት፣ በሎጬ ተከላካይ ማለፍ ይወዳል፣ እኔ አሰብ ሰመለስ ብቻ ሳይሆን ስወጣም በድግስ ተሸኝቼ ነው የወጣሁት ይለናል፡፡ የዚያን ጊዜው የወደብ ክበብ ፈርጥ ‹‘ጌታነህ’›። እርሱም ስለ አሰብና ስለ ህዝቡ አቀባበል የሚከተለውን ይነግረናል፡፡

ዲችኤቶ እንደገባን ወደ ከተማችን እንደቀረብን አወቅን፣ የጥንት ወዳጆቼን ለ20 ዓመታት ዐይቼያቸው የማላውቅ አብሮ አደግ የዲችኤቶ ጓደኞቻችንን ሳገኝ በቃ አሰብ ገባን አልኩኝ። ሞቅ ያለ ግብዣ ተደረገልን፣ ትዝታ ያወቀው ኃያል ጉልበት ለሣቅም፣ ለወሬም፣ ለዘፈንም ይመነጭቃል። ቢራው ተጠጣ፣ ድካም ያዘለው ሠውነታችን እረፍት ቢያሰኘውም፣ በተጨማሪ በወሬ እንደተጠመደ ወደ አሰብ ለጉዞ ተነስ የተባለው ብዙ ነበር።

ከሌሊቱ 9፡00 ሠዓት ቀድሞ የተነሳው እንቅልፍ የጣለውን እየቀሰቀሰ ጉዞው ተጀመረ። ሲያወሩ ያደሩት መኪናው ውሰጥ እንቅልፍ ያዳፋቸው ጀመር። የቀኑ ወበቅ ሌሊት አልነበረም፣ መኪናው እየሄደ እረፍት የወሰደው ህዝብ ሲነጋጋ መንጫጫት ጀመረ። ውሃ መዋዋስ፣ ብርቱካን መመገብ፣ ደግሞ ጭፈራ፣ ሙቀቱ ሲበረታ ከላይ የደረብነውን መቀነስ ጀመርን፡፡ ……..

የቋጠርነውን እየበላን፣ በውሃ ጥም የተቃጠለውን አንጀታችንን እያረሰረሰን፣ በረሀውን እየቃኘን፣ መስኮታችንን ከፍተን ግመሎቻችንንና ጠባቂዎቹን ስንቃኝ፣ ያ የአፋር ጎልማሳ ስንት ዓመት ከወንድሞቹ የኤርትራ አፋሮች ጋር በጥቂት ኪ.ሜ መለያየቱ እየገረመን ኬላ ልንደርስ ጥቂት ሲቀረን ከርቀት የሰዎች ስብስብ ተመለከትን ። ሰንጠጋ ነጫጭ የለበሱ የአሰብ ልጆች ዐየን። በጩኸት ተቀበሉን። እኔ ራሴን መቆጣጠር አቃተኝ። እያለቀሡ መደንዘዝ፣ እየደነዘዙ ማልቀስ፣ ከክንውኖቻችን አንዱ ነበር። በተለይ የመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃ ቃላት ለማውጣት አቅም የነበረው አልነበረም። ቀስ በቀስ አቅም ያገኙት አንዳንድ ነገር አወሩ። ቀስ በቀስ ማውራት ጀመርን። ከከተማዋ 25 ኪ.ሜ ወጥተዉ የተቀበሉን እግራችንን ለማጠብ ነበር። እግራችንን ይዘውት የመጡትን ውሃ ከእንባችንና ከእንባቸው ለውሰው እጠቡን። አጠባው አልቆ ተያይዘን ወደ ኬላው፣ ወታደሮቹ በደስታ መታወቂያችንን መዝግበው አስገቡን።

መዝሙሩ እየተዘመረ፣ እልልታው እየቀለጠ፣ ጭብጨባው እየደራ፣ ክላክስ እየተነፋ ከተማው አበደ። ህፃናት፣ ወጣቶች፣ ጎልማሶችና ሽማግሌዎች ጎዳናው ላይ ተደረደሩ። ኡኡታ ነበረበት፣ ለቅሶው ቀጥሏል። አበባ የያዙ አንዳንድ እንስቶች ይታያሉ። የመንገድ ላይ ዳንስ(ስዕስዒት) በርክቷል። እንደ ታቦት አሰብን እየዞርን ሰላም ለኪ አልናት። በመጨረሻም ወደ ተያዘልን ባህሩ አጠገብ ወደሚገኘው ሚካኤል ቤ/ክርስትያን ገባን።

በሚቀጥለው ቀን ታቦት ስንሸኝ፣ ትዝታችን ወደተቸነከረበትና ማየት ወደ ጓጓንለት እየሄድን ጠፋን። ሁሉም ይጠራሃል፣ ሁሉም ደግሷል። በጊዜ የሚዘጉ ዳንስ ቤቶች ‹ወጋሕ ትበል ለይቲ› አሉ።  ምግብ ቤቶች ደመቁ። ባህሩ ግን ዝም እንዳለ ነው።

ጥምቀቱን እንደ ዳግም ጥምቀት ቆጠርነው። ለቆጠብነው ፍቅር እንደ ቅጣት ማቅለያ፣ ለተኮራረፍንበት ጊዜ ማካካሻ፣ ለመዘጋጋታችን ንሰሃ፣ አብሮነታችንን ዘመርን። የትግርኛና አማርኛ  ት/ቤት ብለን ሳይሆን አንድ ላይ ለተማርንባቸው ጊዜያት አመሠገንን።  እንጀራ የተቀባበልንባቸው የእጥረት ዘመናት……`

ኤርትራዊያን

ሃሳበ-ብዙ ነው። ረዥም ፂሙን ያንዠረገገ በአዲሳባ ውበትና ስፋት የተመሰጠ ይመስላል። ገራገር ነው። ሀገሩ እያለ የክ/ ጦር መሪ ፀሀፊ ነበር ፣ አማርኛም አይቸግረውም፤ ኢትዮጵያዊያን የአሰብ ቀደምቶች ድንበሩ ተከፍቶ አሰብ ሲገቡ ድባቡን እንዲህ ያስቃኘናል።

“ኢትዮጵያዊያኑ እንዳሚመጡ ከታወቀ በኋላእንዴት እንቀበላቸው?” የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ነበር። ስለሚያድሩበት ቦታ፣ ስለሚበሉት ነገር፣ ስለ ደህንነታቸው አጥብቀን ተነጋግረናል። ስለሚተኙበት ቦታ አንሶላ ያለው አንሶላ፣ ምንጣፍ ያለው ምንጣፍ  ኣዋጥተናል። ከውጭ ሀገር ዘመድ ቢመጣ እንኳን እንዲህ አይጠበቅም፣ ጠራራ ፀሀይ እየለበለበን ይመጣሉ ከተባሉበት ሠዐት ጀምሮ አራት ወይም አምስት ሠዐት ጠብቀናቸዋል። ከከተማዋ 25 . ወጣ ብለን የናፈቀን ሁሉ ለማየትና የእንግዶችን አመጣጥ ለማሳመር  ነበር አወጣጣችን፣

በጥሩንባ የታጀቡ በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ የተጥለቀለቁ መኪኖች ወዳለንበት ስፍራ ሲግተለተሉ አየን፣ እልልታው ቀለጠ፣ የምስጋና መዝሙር ቀረበ፣ ሲወርዱ አንጀታችን ተበላ፣ ረዥም ሠዐት ተቃቅፈን አለቀስን፤ ጥቂት ከቆየን ቦሀላ እግር ማጠብ ጀመርን፣ እግራቸውን ሰናጥብ እየዘመርን ነበር። አጠባውን እንዳገባደድን ወደ ከተማዋ ዘለቅን።ያስደንቅ ነበር፤ ከተማዋን በመኪናዋ ዞረው እሰኪጨርሱ የከተማዋ ህዝብ አቀባበል ህዝቡ በሙሉ ያበደ ይመስላል በእውነት አሰብ የዛን ቀን ቀውሳ ነበር። ከዘረቱ መልስ ሚካኤል ቤተክርስትያን የምሳ ግብዣ ተደረገ። ትዝታቸውን እንዲያጣጥሙ የተለያዮ የመዝናኛ መርሀ ግብሮች ተከናወኑ፣ 4 ቀናት ቆይታቸው ማለትም ገብተው እሰከወጡባት እለት በስስት ያዝናቸው እንዳይቀሩ ለመናቸው አንቀርምብለው ማሉልን።”

እኔ

የጠፋሁኝ በጓ ነኝ። ጥያት እልም ካልኩኝ እነሆ ሀያ አራት ዓመት አደረግኩኝ። ለኔ ይህች ከተማ በህልምም ይሁን በእውን እንድጎበኛት ነፍሴን የሚያንኳኳ እጅ አላት። ተወልጄባታለሁና ኢትዮጵያ ውስጥአሰብ የሚል ፅሁፍ ካነበብኩም ይሁን ድምፅ ከሰማሁ የአእምሮዬ ሴሎች ይነቃቃሉ። ስለሷ ማሰብም ይሁን ማለም መብቴ ቢሆንም፤ እሷን መርገጥ ግን ሐራም ነበር። አንቺን ማየት አልችልም በሚል ቁልፍ ልቤን ባልቆልፈውም አንድ ቀን የሚል ድምፅ ይሰማኝ ነበር። ሆኖም ኢትዮጵያ  አዲስ መሪ ስትቀይር ሐራሙ ተነሳላት፤ ድንበሩ ክፍት ሆነ፤ አንድ ቀን ግን ድንበሩ ቢከፈትም ቀላል አልነበረችም፤ በግል ችግር ምክንያት ያች አንድ ቀን ተራዝማ ድንበሩ ተዘጋብኝ። አዘንኩኝ ሆኖም አንድ እድል አለኝ፦ በአውሮፕላን ወደ አስመራ መጓዝ ከዛ ረዥም በረሀውን አልፎ አሰብ መድረስ። አደረግኩት!!

ከሌሊቱ 11፡00 ሠዐት ጓዜን ጠቅልዬ በየብስ ድንበር መግባት የተከለከልኩባትን ከተማ እነሆ ግማሹን በአውሮፕላን ግማሹን በህዝብ አውቶብስ ለመሄድ ባሷ ቁልቁል በበረሀው ሰርጥ ዉስጥ ገጭ እንጓ እያለች ጉዞዋን ቀጥላለች አብሮኝ ወንድሜ (ረዳት አብራሪ ሱራፌል)ና ወዳጁ እሱም ረዳት አብራሪ ነው፣ በረሀውን አሰብን ሊመለከቱ ሊጨብጡ ሲሆን ለወንድሜ ጓደኛ አንድ ጥያቄ አነሳሁለት ወንድሜስ አሰብን ሊያይ በዚህ በረሀ የጓጓላት ስለተወለደባት ነው አንተስ?” አልኩት። ብዙ ጊዜ ሲያወራና ሲያጋንንላት የሰማሁትን ከተማ ማየት አለብኝ ብዬ ነው” አለኝ።

ጉዞ ወደአሰብ ፪

(የእኔ እና የወንድሜ)

ምፅዋን አልፈን ወደ ‹ፎሮ› እያዘገምን ነው። ተጓዦቹ አሰቤዎች ሲሆኑ እንደአማርኛ ተናጋሪነታችን የባሷን ሠዎች ቀልብ ይዘናል። አብዛኞቹ ተጓዞች ነጋዴዎች ሲሆኑ መጫን ካለባቸው በላይና የተከለከሉ ዕቃዎችን ይዘዋል። ብዙ ዕቃዎች በምስራቅ አፍሪካ ተፅእኖዋ እየጨመረ የመጣውና እቃዋን ወደምትቆጣጠራቸው ሀገራት በማራገፍ የምትታወቀው የተባበሩት አረብ ኤሚሬት ስትሆን፤ እልፎ አልፎ የየመንም ነበረበት። ድንበሩ ተከፍቶ የነበረ ጊዜ በኢትዮጵያ ምርት ኤርትራ ተጥለቅልቃ ነበር። እዛው የተዋወቅነው ተጓዥ ዕድሜው በሀያዎቹ መጨረሻ የሚገኘው ሀጎስ ወታደርመሆኑን ነገረኝ። በጣም ቀጭን ሲሆን ቅጥንቱ ከጠላት ጥይት ለማምለጥ የሚጠቀምበት ይመስላል። ድንበሩ ክፍት የነበረ ጊዜ ምን ያህል ኑሮ ረክሶላቸው እንደነበር አጫወተን። ውሃ፣ ቲማቲም፣አቮካዶ፣ ሽንኩርትና የመሣሠሉት በጣም ረክሶ ነበር ብሎኝ እጁን አወራጨ።  አሳዘነኝ።

ፎሮ ደረስን። በጀብደኝነት ጊዜዋ የኮንትሮባንድ ከተማ የነበረች ሲሆን፤ ከከተማዋ ጥቂት ኪሜ ወደ ትግራይና አፋር እንዲሁም ወደ ሳኡዲ አረቢያ ለመሄድ እንደ ቅርብ መሸጋገሪያ ነበረች። መስቀለኛ መንገድ ነች። ሀገርም፣ በረሃም ባህርም ለማቋረጥ፤ ከፎሮ በጀልባ ተጉዞ ሳውዲ ለመግባት አንድ ቀን ይፈጃል።

ድካምና ረሀቡ ጠንቶብን ወዳጅ ያደረግነውን ወታደር በተደጋጋሚ እንደተመላለሰበት ሰው ካሉት ምግብ ቤቶች የሚሻለውን እንዲያሳየን ጠይቀን ወሰደን። የተሻለውን መርጬላችኋለሁ አለን። ጥብስ አዘን ‘የለም’ ስለተባልን እንደነገሩ ፍሪታታውን፣ ካፕሬቶውን፣ ምስሩን በማሽላ እንጀራ አዘዝን። እየተመገብን የጥብስ ሽታ ሸው አለብን። ሳናንኳኳ ጥብሱ ወዳለበት አቅጣጫ ተመለከትን። እንዴ ተባባልን፣ መገረማችንን ያየው ሀጎስ ጥብስ ለማን ብቻ እንደሚሰራ ነገረን፤ አውታንቲ ጥራይ ኣለን(ለሾፌር ብቻ ለማለት ነው)። ሾፌሩን ገርምመን የተፈረደልንን ማላመጣችን ቀጠልን። ቶሎ ምግብ ያገባደድኩት እኔ ነበርኩ፣ ቡና መኖሩን ለመጠየቅ፣ የትም አልነበረም። ወደ መኪናችን ገባን፣ ጉዞ ወደ ገለዐሎ።

ላባችን ይንቆረቆራል። በሽርጥ ካልተሸፈኑ በህይወትህ ገጥሞህ የማያውቅ ኣሸዋ ፀጉርህ ውስጥ ይሠገሠጋል። አቧራው ሽበት ላይም ይታያል። ሙቀቱ ትንፋሽ ያሣጣል ብቻ ሳይሆን ላለመደው ሠው መኖር አያሰመኝም። ልብስህን አውልቅ አውልቅ ቢልህም አመዱን ፈርተን አላደረግነውም።  እንደከበደን ያወቁ ተጓዦች አስር ጊዜ ደርሰናል ይሉናል። ከ2:30 ጉዞ በኋላ ገለዐሎ ደረሰን። እንደወረድን ጥማችንን ለመቁረጥ ወደ ግሮሰሪዋች ሄድን። ፍሪጅ ስለሌለ ለስላሳም ይሁን ቢራ የሚቀዘቅዝው ውሃ በሞላ ባልዲ ሲሆን፤ በሙቀት የተቃጠለውን ውስጣችንን በቻልነው ለስላሳ አዛልነው። ሁለት ዛኒጋባዋች ውስጥ የሁለት ባስ ተሳፋሪዎች ፀሀዩን ለማምለጥ ተኮልኩለናል። ጥቂት እንዳረፍን የግቡ ክላክስ በመነፋቱ አቅጣጫችንን ወዳ ታዋቂዋ ‹ጢዖ› አደረግን።

ለብዙ ሠዓት በመጓዛችን ደክመናል። የተኛም አለ። በራሱ ጊዜ የሚከፈተው ሁሉም የመኪናው መስኮት አመድ አሸዋ እያለበሰን እሰልቺውን መንገድ ጀመርን። እንዲህ አይነት አስከፊ ጉዞ በሊማሊሞ ከጎንደር ወደ ትግራይ ስሄድ ቀምሼዋለሁ። ሊያውም ከነ ጠመዝማዛነቱ። ይሄኛው ግን ለጥ ባለ ሜዳ የሚኬድ ጉዞ ሆኖ አይወጣበትም አይወረድበትም።  አንድ አብሮን የሚጓዘውን ስለባሱ ጠየቅኩት፣ “የነዳጅ ማጣሪያ ሰርቪስ ነበር” አለኝ። ከጣራ በላይ አይነት ሳቅ አስተጋባሁ፣ ከ40 ዓመት በፊት አባቴም ሄዶበታል፣ በጉዞአችን ብቸኛው አዝናኝ ነገር እሱ ነበር። ከ2፡30 ጉዞ በኋላ ወደ ታዋቂዋ ወደብ ጢዖ ደረስን።

ጢዖ ከአሱበ አውራጃ አንዷ የነበረች ሲሆን በቀዥቃዣው ሹፌር ምክንያት እምብዛም አላየኋትም ፣  ውሃ ለመግዛት እንደወረድን ክላክስ  ጲጵ …..

ጉዞ ወደ ኢዲ

ኢዲ አሰብ ከመግባታችን በፊት የምናድርባት ከተማ ነች። ቶሎ ለመድረስ እንኳን እኛ የለመዱትም ቸኩለዋል። ይህ አድካሚ ጉዞ እሰከ ፎሮ መናጥ አለው። ከፎሮ እሰከ ገለዐሎ መንገዱ ሲፈልግ ይሳባል ሲሻው ይናጣል። ከሁሉም የሚከብደው ግን ከገለዐሎ ጢዖ የሚወሰደው ሲሆን መፋቅ ይበዛበታል። በአሸዋው ምክንያት ጢርርር የሚለው መኪና ወደ ኢዲ ሲያዘግምም እየተንፏቀቀ ነበር። ከምሽቱ 2፡0ዐ ሠዐት ኢዲ ደረስን። የዛሬው የ12 ሰዐታት ጉዞ ተጠናቀቀ።

ፀሀይ ሞሀመድ ሆቴል(ባለቤቷ ኢትዮጲያዊት ነች) ውጪ ላይ ታጣፊ የሽቦ አልጋ ላይ የተቀመጠ ፍራሽ አለ። ፍራሹ ከታጠፈ ተይዟል ካልታጠፈ አልተያዘም ማለት ነው። ወንድሜን ጨምሮ አሰብን ለማየት አብሮን የመጣው ወዳጃችን አብርሀም በተከታታይ ሶስት ረድፍ ያዝን። እነሡ ለሻወር ሲሄዱ ቀኑን ሙሉ ያልጠጣሁትን ቡና ፍለጋ ተንጠራወዝኩ። 40 ናቅፋ ከከፈልኩ እንደሚያፈሉልኝ ተነገረኝ፣ ተስማማሁ። ኢዲ ስመለስ በቀን እንዳኋት በረሀማና ሻይ ቤት የመሠሉ ወደ ሶስት የሚጠጉ ሆቴሎች ሲኖራት ከመጣንባቸው ከተሞች ይልቅ ትደምቃለች። ቡናው እስኪፈላ በማንችስተር ሲቲና በአርሰናል መካከል ያለውን ጨዋታ ማየት ጀመረኩ። ጥቂት እንዳየሁ ቡናው መድረሱ ተነግሮኝ ወዳሚፈላልኝ ቦታ ሄድኩ። ብዙ ነበር፣ ወጣ ብዬ በትግርኛም በአማርኛም የሚያጣጣኝን ሠው ፍለጋ ኳተንኩ። አራት ሆንን አሰብ በዚህ ሰዓ እንደርሳለንምናምን እያሉ አወሩኝ። አብረውኝ ከሚጠጡ ሰዎች መካከል አንደኛው በ50ዎቹ መጀመሪያ ላይ ያለ ጎልማሳ አሰር ጊዜ መንግስቱን ይማል። አብሬው እንዳላማ አንጎሌ አሰብ ገብቷል። ቡናውን ሰጠጣ ተነቃቃሁ። ሆኖም የነቃሁት ወደ ራሴ ምናብ እንጂ ለአጣጪዎቼ አልነበረም። አብሬያቸው ነበርኩም አልነበርኩም፤ መሰስ ብለው እያመሠገኑኝ ወደ መኝታቸው ሄዱ። ሂሳብ ከፍዬ እኔም በጀርባዬ ተንጋለልኩ። ወንድሜም ሆነ ወዳጃችን ተኝተዋል። እኔ ግን ቡናውና ወደ ትውልድ ከተማዬ መመለስን ስለማስብ ይሁን አላውቅም እንቅልፍ እምቢ አለኝ። ከዋክብት በበረሃዉ ምሽት ኢዲ ሠማይ ላይ ፈክተዋል። እንኳን ደህና መጣህ የሚል መስተንግዶ፣ እኔም በፈገግታ መለስኩኝ። ነፍሴ በጥያቄ ወጥራኛለች።

የኖርንባት ራሻን ካምፕ እንዴት ሆኖ ይሆን? አቡነ ዘበሰማያት የተማርኩበት ቅ/ሚካኤል ቤ/ክርስትያንስ? ወደቡስ? የነርኤ ልጆችሽ እናገኛቸው ይሆን? የነርኤ ቤተሰብ ማነው? ከኛ ጋር ስለነበረው ቤተሰባዊ መስተጋብር እንደሚከተለው እተርካለሁ

የነርኤ ቤተሰብ

አባቴና ነርኤ በደርግ ጊዜ ወዳጅና ጎረቤታሞች ነበሩ። እናቴና ባለቤቱም እንዲሁ፤ አባቴ ኢትዮጲያዊ ነርኤ ደግሞ ኤርትራዊ ነው። እኔና ትንሹ ወንድሜ ሱራፌል እንዲሁም የነርኤ ልጆች ትልቁ ሀኒቫልና ትንሿ ሚሌና አብረን ያደግን፣ የምንዋደድና እንደ ቤተሰብም የምንተያይ ነበርን። ታዲይ አንድ ቀን ነርኤ በሻዕቢያነት ተጠርጥሮ ይታሠራል። ቢጠበቅ ቢጠበቅ ወደ ቤተሰቡ አልመጣም። ሁለት ወር ሆነው፣ ብዙ ኢትዮዽዊ በፍርሀት ወደ ሀገሩ መሸሽ ጀመረ። አባታችን እኛና የነርኤን ልጆች ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ ወሰነ። ከአንድ ሾፌር ጋር ተነጋግሮ እቃ ለመጫን ወደ ቤት ከመግባቱ ሻዕቢያ ወደ ከተማዋ አቅጣጫ ጥይቱን እያንጫጫ ሲገባ ሹፌሩ መኪናውን አስነስቶ ተፈተለከ። አባቴ ተስፋ ቆረጠ። አስገራሚው ነገር ግን በጥቂት ሠዕታት ውስጥ ታሳሪው ሻዕቢያ እንደገባ ከፈታችው አባልዋ አንዱ የአብሮ አደጎቼ አባት ነርኤ ነበር። ተቃቅፈን ( ሁለቱም ቤተሰብ) ተላቀስን። አባታችን ወዳጁ ነርኤ ልጆቹን በማግኘቱ ደስ ቢለውም ሻዕቢያን ለማምለጥ (በወቅቱ ሻዕቢያ ኢትዮጵያዊያንን ካገኘ ይገድላል ይባል ስለነበር) ተሠናዳ። ብዙዎች ኢትዮጵያዊያን ልጆቻቸውን ይዘው እየከነፉ ነበር።

በጓደኛው የነፍስ አውጭኝ ግስገሳ አንጀቱ የተላወሰው ነርኤ፤ እኔንና ወንድሜን ጥብቅ አድርጎ ይዞ እነዚህን ልጆች በረሀ የትም በረሀ መውደቅ የለባቸውም እኔምኮ እንዳንተው አሳድጌያቸዋለሁ። ሻዕቢ አትፍራ ከበደ። የየትኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል ስላለነበርክ ምንም አያደርጉህም እምልልሀለሁ። አንድ ነገር ካደረጉ (ሻዕቢያን) ሬሳዬን ተረማምደው ነው እና እባክህ ቅር ብሎ አባታችንን እንደ መለመንም እንደ ማስገደድም አደረገው። በእኛና በነርኤ ቤተሰብ መካከል ሠውነት ነበር። የደም ሳይሆን የስብዕና እግረ ሙቅ ነበር። ከደም ስለሚያይል ፖለቲካ እንጂ ህዝብ የፍቅር ችጋር እንዳልመታው ያላቸውን በመለጋገስ ስነ-ሰብዕ አስተምረውናል….

ለ6 ዓመት ከተማዋ ላይ ተቀመጥን። በአባቴ ጡረታ ምክንያት ወደ ሸገር ከጦርነቱ አንድ አመት በፊት መጣን ሆኖም የአብሮ አደጎቼ አባት ነርኤ ባልታሰበ ሁኔታ ድንገት የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ሲጀመር አረፈ። ስድስት ወር ሳይሞላ አብሮ አደጌ ሀኒቫል በጳጉሜ ባህር እየዋኘ ሰመጠ። እናቱ ከጥቂት ወራት በኋላ አረፈች። ይህ ሁሉ ሲሆን እኛ አዲስአበባ እነሱ እዛው አሰብ ነበሩ። እናትና አባት ከዚች ምድር ሲሰናበቱ አብሮ አደጋችንን ሚሌናንና ሁለት አዲስ ሴት ልጆች ነበሯቸው። ይህ መሆኑን ከሠማን እነሆ 22 ዓመት ሆነ። ድንበሩ ዝግ በመሆኑ ስለነሱ ማወቂያ መንገድ አልነበረንም። እነሆ የህይወት ኡደት እንደተሽከረከረች ነው። ፍለጋው እነዚህን ቀሪ ሶስት ልጆች ያካትታል።

ሳልተኛ ባሷ በመኪናዋ ጥሩምባ ተነሱ አለችን። ወደ ባሱ አመራን ከለሊቱ አስር ሰዓት ግድም የመኪናችን ሾፌር የቀረ መኖር አለመኖሩን እንዲያረጋግጥ ለረዳቱ አዘዘው። የሂድ ምልክቱን አይቶ ገሰገሰ። ኮሶስት ሠዐት ጉዞ በኋላ ‹ቤይሉል› የምትባል  ከተማ ደረስን። ከተማዋ በአካት ዛፎች የደመቀች ነች። ጥቂት ነፋስ ወስደን ወደ ህልማችን ከተማ በጥቂት ሰዐታት ውስጥ ለመድረስ መክነፍ ጀመርን። ሙዚቃው ይንቆረቆራል። ኣነ አደይ ክብል እሳ ከኣ ወደይ ወይም እኔ እናቴን እላለሁ እሷ ደግሞ ልጄ” የሚለውን የአል አሚንን ዘፈን እየሰማው እመሠጣለሁ። ባህሩ በስተግራ ይወራጫል። ባህሩን ይዤ ስጨረስ ወደ ጓጓሁለት ያደርሰኛል? አርጅታ ይሆን ? እንዳላማረባት ነግረውኛል። ይህንንም አይኔ ማየት አለበት ብያለሁ።

ከ3፡00 ሠዐት ተከታታይ አሰልች ጉዞ በኋላ ህልሜን እውን አደረግኩት። በሚንቀጠቀጥ እጄ ላቤን እየጠረግኩ ጥቂት ተጓዝን። “ዋይ አለው” ወዳሚባለው አሰብ ሆቴል እየተጓዝን ያሣደገንን ሚካኤል እንደተኮፈሰ አየነው። ሆቴል ከመያዛችን በፊት እንድንሳለም አመነታን። በፍጥነት ወደ አሰብ ሆቴል ሄድን። ባለቤቶቹ እርግት ያሉ 60ዎቹን የተሻገሩ ባልና ሚስቶች ሲሆኑ በሚገርም ፈገግታ ተቀበሉን። የአሰብ ተወላጅ ኢትዮጵያዊያን መሆናችንን ስንነግራቸው ይበልጥ እኛን የማወቅ ጉጉታቸው ጨመረ። የጉዞ እቃችንን አስቀምጠን እንድንመጣ ቁልፍ ሠጡን፣ ሻወር ወስደን እቃችንን አስቀምጠን ስንመለስ ቡና ተፈልቶ ከቆንጆ ቁርስ ጋር ቀረበልን። እየተበላ እየተጠጣ የት ሰፈር እንደነበርን? አባታችሁ ማን ይባላል? የት ነበር የሚሰራው እያሉ የጥያቄ መዓት ከቁርስ ብፌያችን ጋር ቀረበልን። አባቴን ያውቁት እንደነበር ሠውዬው ነገሩኝ። የተለመደ የኤርትራውያን ቡናና ከቡናው ጋር የሚቀርብ የተፈጨ ዝንጅብል ቀረበልን። እየጠጣን ልዩ መዓዛ እንዳለው ተረዳን። ታዲያ ድንገት አንድ ቃል ከሰውዬው አፍ ተወረወረች። የነርኤ ልጅ ከአስመራ መጥታለች የሚል። ትኩረታችንን ሁሉ ወደ ሰውዬው አደረግን። በተራችን በጥያቄ አጣደፍናቸው። ማነው ነርኤ? በህይወት እኮ የለም እሱን ነው የምትሉት? አስቴር የምትባል ሚስት ነበረችው?” ጮኸን። ሠውዬው የሚያወራው ስለምንፈልገው ነርኤ ሲሆን “ከአሰመራ የመጣችው ልጁ ማን ትባላለች?” አልነው። ቆይ አጣራለሁ” አለና ስልኩን ሞከረ። ስልኩ አይነሣም፣ ደጋግሞ ቢሞክርም ኣይነሣም። ለመሄድ ከመጓጓታችን የተነሣ ቡናውንም ሆነ ምግቡን እረስተነው ነበር። ሠውዬው መንገዱን ነገረንና ፍለጋ ያዝን።

ፍለጋችንን ላይ አንድ አስመራ ሆኜ የደወልኩለት መርከበኛ ተቀላቀለን። ስንነግረው ወደ ቤት ወስደን፣ በሩን አንኳኳን ቀጭን አበባ የመሰለች እንስት በሩን ቀፈተችልን። መርከበኛው ሰላምታ ሰጥቷት እንግዶች ከአዲስ አበባ ሊጠይቁሽ መጥተዋል” አላት። “ግቡ” አለችንና ገባን። መርከበኛው ነገ እደውልላችኋለሁ ብሎ ወጣ። ቤቱ ውስጥ የቤተሰቦቿ ፎቶ አለ። ስንተኛ ልጅ እንደሆነች? ስሟን? ሚሌና የት እንዳለች? ጠየቅናት። እሷ ህፃን እያለች በቤተሰባችንና በቤተሰቧ ስለነበረው ከዝምድና የበለጠው ግንኙነት ነገርናት። ዊንታ እባላለሁ። የቤተሰቡ ሶስተኛ ልጅ ነኝ። አባትና እናቴ ከሞቱ በኋላ የተረፍነው እኔ ሩትና አብራችሁ ያደገችው ሚሌና ነን። ሩትና ሚሌና ለንደን ናቸው አለችን። ተደሰትን። ሚሌናን ባናገኝም ከቤተሰባቸው አንዱን አገኘን።

ደስ አላት፣ ፎቶ ጋበዘችን። ፎቶው ውስጥ ሟች እናቷ የምወዳት አስቴር እኔን ይዛ አለ። የአባትና የእናቴም ምስል አለ። ቤቱ ደመቀ እኛም እህት እንዳገኘን እሷም ወንድም እንዳገኘች ተቆጠረ። ብስራቱን ለእናታችን ለመንገር ቸኮልን። ከአሰብ ወደ አዲስ አበባ ደውለን አገናኘናቸው። ይበልጥ እልልታ ከአዲስ አበባ ተሠማ። ፍጥምጥም አለ ነገሩ። እናታችን ስትሞትእነዚህን ህጻናት ጥዬ  የትም አልሄድም ብላ ከጦርነቱ በኋላ እዚሁ አሰብ የቀረች ኢትዮጵያዊ የቤት ሠራተኛ አለች ጠብቋት አለችና ይህችን ጀግና እስክትመጣ ጠብቀን ተዋወቅናት።

የኖርንበት ቤት

ከሰዐት ተያይዘን ወጣን። መጀመሪያ ወደ ኖርንበት ቤት ሄድን። ራሻን ካምፕ ይባላል። የኖርንበት ቤት ግማሽ በግማሽ ፈርሷል ማለት ይቻላል። አዝነን ወደ ሚካኤል ቤተክርስትያን መጓዝ ጀመርን። ካየኋቸው ቤተክርስቲያኖች ሁሉ የአሰቡን ሚካኤል የሚልቅ አላውቅም።  እንኳን ለኦርቶዶክስ አማኝ ለኢአማኒውም የሚካኤል ውበት እጅ ያስነሳል። ጥቂት ዞርነው፣ ከጀርባው የልዕለ ሀያላን ስሜት የሚቆነጥmው ቀዩ ባህርን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሰገነት አለው። ሳይመሽ ራስ ገንቦ የተባለውን ደርግ-ሰራሽ ሆቴል ገባን። ቢቹ አጠገብ ነው፣ አስመራ ቢራ አዝዤ ጥቂት ከራሴ ጋር ታገልኩ። የእውቁን ድምፃዊ አብርሃም አፈወርቂ ከፍቼ አንድ ሁለት ስንኝ እየተነሣ ከሚፈረጠው ባህር ጋር ተቀያየርን።

ልበይ ምለሰለይ ካልእ ከፍቅረሉ ትብልኒ

ልበይ ሂዝኪ ልቢ ትሓትኒ

ተዝምለስ ንኣይ ዶ መሓሸኒ

ከምዝደለናዮ ዶ ንነብር

ከምዝሰለጠ እምበሪ

ትርጉሙም

ልቤን መልስልኝ ሌላ ላፍቅርበት ትይኛለሽ

ልቤን ይዘሽ ልብህን ትይኛለሽ

ለኔ ግን ቢመለሰልኝ ይበጀኛል

እንደፈቃዳችን አንውልም

እንደሆነልን እንጂ

አሰብን ወደ መሰናበቱ ነኝ። ከተማዋ ከጥልቅ እንቅልፍ ባንና፣ አዳዲስ ተስፋዎችን ዝናር አድርጋ የምትጠብቅ ወይም ምርኮኛ ንግስት ትመስላለች። ወደ ከተማዋ እንደገባን ኢትዮጵያዊያን መጡ ሲባል የከተማው ሠው ድንበሩ የተከፈተ መስሎት ፈንጥዟል። ኑሮ በሷ በኩል እንዳልረከሠ ዛሬ ታማለች። ኢትዮጲያም ብትሆን ያለ አሰብ ሠው ሠራሽ መተንፈሻ የተገጠመላት ሠው ትመስላለች። ጥቂት በተፈጠረው የሠላም ጊዜ ከኢትዮጲያዊያን ያረገዙ እናቶችም እባክህንአብይድንበሩን ክፈተውና ባሎቻችንን እናግኝ” ብለዋል። የነርኤ ቤተሰብ ከሆነችው ዊንታም ጋር ልብ በሚነካ ስሜት ተሠናበትን። ቀሪዋ አብሮ አደግአችንን ሚሌናን ለንደን ብትኖርም በወንድሜ በኩል እንደምናገኛት እርግጠኛ ሆንን ።

አሰብን አይቼ ጥሜን አልቆረጥኩም። ደግሜ እንደማይሸና፤ ባንድ ወቅት አሰብ መጽሀፍ ላይ ተፅፎ እንዳነበብኩት ሼህ ሳፊ የተባሉ የበቁ ሰው እንዳሉሸ አሰብ ሆይ ማንም ከየትም ቦታ የመጣ ይጠቀምብሽ፣ ይደሰትብሽ፣ ይምነሸነሹብሽ፣ እዚሁ ይለፍለት። ከዚህ ሲወጣ ግን ገንዘብ ሽን ይዞ አይውጣ እኔም ደግሜ አልኩሽ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top