መጽሐፍ ዳሰሳ

ቁምነገራም ገጾች

ርዕስ፡- የሴቶች ሁለንተናዊ አበርክቶ     

የገፅ ብዛት፡- 220 + 20

አርታኢ፡- አብዱራህማን አህመዲን

ዘውግ፡- የጥናት ጽሑፎች ስብስብ

የሕትመት ዘመን፡- ጥቅምት 2012 ዓ.ም.

አሳታሚ፡- የሴቶች ስትራቴጂካዊ ልማት ማዕከል

“መጻሕፍት ለምን ይጻፋሉ?” ለሚለው ጥያቄ የምናገኘው መልስ ብዙ ነው። ከእነዚህ በርካታ መልሶች ውስጥ መጻሕፍት በአንባቢው ሕብረተሰብ የተስተዋለን ጉድለት ለማረም፣ የተረሱ እሴቶችን ለማስታወስ፣ እንዲሁም የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ወ.ዘ.ተ… የሚሉ መልሶች ይገኙበታል። ለዛሬ የመጽሐፍ ዳሰሳችን የመረጥነው መጽሐፍ ተመሳሳይ ዓላማ ያነገበ ነው። ስለሴቶች ያለንን ማኅበረሰባዊ የዐተያይ ጉድለት ለማረም፣ የተረሱ ታላላቅ ታሪካዊ ሴቶቻችንን ለማስታወስ፣ እንዲሁም በሴቶች ላይ ያለንን ማኅበራዊ ግንዛቤ ለማሳደግ ይሰናዳ እንጂ በዚህ ዓላማ ከተዘጋጁት በእጅጉ ይለያል። ጊዜ ተወስዶ በጥልቅ ጥናት እና ምርምር የተዘጋጀ ነው። በዚህ ዳሰሳችን ይዘቱን እና ተያያዥ ነጥቦችን በጥቂቱ እናነሳሳለን።

ጥቂት ስለ አሳታሚው

‹የሴቶች ስትራቴጂካዊ ልማት ማዕከል› የተሰኘው ተቋም ይህን መጽሐፍ ለማሳተም መነሻ የሆነው በ2008 ዓ.ም. በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጉባኤ ነው። ከመላው የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ሴት አመራሮች በተሳተፉበት ስብሰባ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው መጻሕፍት ለንባብ እንዲበቁ ሐሳብ ቀርቧል። ሴቶች ለሃገር ግንባታ ያደረጉትን አስተዋፅኦ የሚያሳዩ የጥናት ውጤቶች የሚታተሙበት አካዳሚያዊ ጆርናል እንዲዘጋጅ የቀረበውን ሐሳብ ተከትሎ እንቅስቃሴዎች ተጀመሩ። ከነሐሴ ወር 2009 ዓ.ም. ጀምሮ የሴቶች ስትራቴጂካዊ ልማት ማዕከል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት፣ ጥናትና ምርምር ተቋም (Institute of Educational Research – IER) ጋር በመተባበር ስለመጽሐፉ ይዘት፣ አስተዋፅኦ፣ አሰራር፣ ወ.ዘ.ተ… የሃሳብ ልውውጦች እና የፕሮጀክት ቀረጻ ተከናውኗል።

የመጽሐፍ ፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ

  1. በተለያዩ ማኅበራዊና ባህላዊ ሁነቶች ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ የሚያሳዩ መረጃዎችን መሰነድ እና አበርክቷቸውን ማሳየት
  2. ለተቋማት (በተለይም በሴቶች እኩልነት ላይ ለሚሰሩ) በእውቀት ላይ የተመሰረቱ መረጃዎችን ማዳረስ

ናቸው። በርዕሱ ላይ እንደተገለፀው “የሴቶች ሁለንተናዊ አበርክቶ” የሚለውን አድማሰ-ሰፊ ሃሳብ ይህ መጽሐፍ በ12 የጥናት ጽሑፎቹ ለመዳሰስ ሞክሯል።  

የኢትዮጵያ ሴቶች ከታሪክ፣ ከፍልስፍና፣ ከኅብረተሰባዊ ለውጥ፣ ከበዓል አከባበር፣ ከአመራር፣ ከዲፕሎማሲ፣ ወ.ዘ.ተ…. ምህዳሮች አንፃር ያላቸውን አበርክቶ “ባህርን በጭልፋ” ሊባል በሚችል መልኩ ዳሰሳ፣ ጥናትና ቅኝት አድርጎበታል።

15 አጥኚዎችን ያሳተፈው መጽሐፉ ሁለት ክፍሎች እና 12 ምዕራፎች አሉት። የመጀመሪያው ክፍል ስድስት ምዕራፎች (የጥናት ጽሑፎች) ይዞ በአማርኛ ቋንቋ የቀረበ ነው። ሁለተኛው ክፍልም በተመሳሳይ ስድስት ምዕራፍ ሲኖረው በእንግሊዘኛ ቋንቋ ተሰናድቷል። ባለ ሁለት ምእራፍ የመሆኑ ተቀዳሚ ሰበብ በሁለት ልሣኖች መጻፉ ነው። አንድ ጥናት አንድ ምዕራፍ እንዲይዝ ተደርጓል።

የሽፋን ምስል

ለመጽሐፉ የሽፋን ገፅ የተመረጠው ቀለም ሮዝ (PINK) ነው። ይህ ቀለም በተለምዶ ሴታዊ ቀለም (Feminine color) ተደርጎ ይወሰዳል። ነገርየው ታስቦበት መደረጉን ያሳብቃል። የሽፋን ምስሉ የተዘጋጀው በሰለሞን ኃይሉ ሲሆን፤ የመጽሐፉን መንፈስ በስዕሉ በደንብ ገልፆታል። በስዕሉ ላይ ስምንት ሴቶችና ሁለት ወንዶች (አንድ ህፃን፣ አንድ ተመራቂ) ይታያሉ። ከሌሎቹ ስእሎች አንጻር ገዘፍ ባለ መጠን አንባቢውን በግማሽ ፊቷ ፊትለፊት የምትመለከተው ሴት በእጇ የተቀረውን ግማሽ ፊቷን የሸፈነ ስዕል ይዛለች። የሴቲቱን ግማሽ ፊት የሸፈነው በእጇ የያዘችው ስዕል ውስጥ በጀርባዋ ላይ ከባድ ሸክም ተጭኖ ያጎበጣት ሴት ትታያለች። ይህች ሴት በኅብረተሰባችን ውስጥ ያለ በሴቶች ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድረውን የቤት ውስጥ ኢ-ፍትሃዊ የሥራ ድልድል የምትገልጽልን ናት። ሌላኛዋ ሴት ደግሞ ህፃን ልጇን ጡት እያጠባች ያልደረሰች ልጅ በጎኗ የያዘች ሴት ነች። ይህች ሴት በኅብረተሰባችን ልጅ የማሳደግ ኃላፊነት በአብዛኛው በእናቶች ትከሻ ላይ የተጣለ መሆኑን ታሳየናለች። ሌላዋ ሦስተኛ በስዕሉ ላይ ያለች ደግሞ የተመረቀችና አጠገቧ ሌላ ወንድ ተመራቂ ያለ ሴት ነች (ወንድየው የፍቅር ወይም የትዳር አጋሯ ሊሆን ይችላል)። ይህች ሴት በማኅበረሰባችን ውስጥ ያሉ ስኬታማ ሴቶችን ትወክላለች። በሀገራችን ያለው የሴቶች ዕጣ ፈንታ ሙሉ በሙሉ የጨለመ እንዳልሆነና ብርሃናማ ተስፋ እንዳለ ከዚህች ሴት ለመረዳት እንችላለን። ስዕሉን በእጇ ይዛ ከቆመችው ሴት ጀርባ በሌላኛው ጎን የሚታዩት አራት ሴቶች ናቸው። የሐመር፣ የትግራይ፣ የወለጋ ኦሮሞ፣ የሐረርጌና ሶማሌ ልብሶችን የለበሱት ሴቶች ከሃገራችን አራት አቅጣጫዎች የመጡ ናቸው። ይህም ሆነ ተብሎ ሁሉንም የኢትዮጵያ ክፍል ለመወከል የተደረገ ጥረት ነው።

በመጽሐፉ የገፅ ሽፋን ላይ የኢትዮጵያውያን ሴቶችን ለማሳየት የተደረገው ሙከራ ስኬታማ ነው ማለት ይቻላል። የሽፋን ስዕሉን የሳለው ሰለሞን ኃይሉ በዚህ ስራው ያሳየው ትጋትና መራቀቅ “እጅህ ይባረክ” አስብሎ የሚያስመርቀው ነው።  

ክፍል ፩

የመጀመሪያው ምእራፍ በአብዱራህማን አህመዲን የተፃፈ ሲሆን “ዲፕሎማሲ፣ ጦርነትና ሰላም፤ ከእሌኒ እስከ ምንትዋብ” የሚል ርዕስ አለው። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የንግስት እሌኒ ሙሐመድ፣ ባቲያ ድል ወንበራ ማህፉዝ፣ እቴጌ ሰብለወንጌል፣ እና እቴጌ ምንትዋብ ታሪኮቻቸው፣ አበርክቷቸው፣ ገድሎቻቸው፣ በሃገር ግንባታ፣ በአመራር እና በዲፕሎማሲው መስክ ለኢትዮጵያ ሃገራቸው ያበረከቱት አስተዋፅኦ ጥፍጥ እና ምጥን ባለ መልኩ የእያንዳንዳቸው ታሪክ በአጭሩ ቀርቧል። አቶ አህመዲን አብዱራህማን በእነዚህ የአኩሪ ታሪካችን ጉልላት ብለን ልናወሳቸው በምንችል ታላላቅ እንስት መሪዎቻችን ታሪክ ላይ አንድ ወጥ ጽሑፍ ለማሰናዳት መትጋቱ የሚያስመሰግነው ነው።

ጸሐፊው በምዕራፉ የቀረበውን ጥናት ሲያጠቃልልም ከባድ የሆነ አደራ-አዘል ምክሩን ለታሪክ ምሁራን አቅርቧል። መልእክቱም እንዲህ የሚል ነው፡-

“…ከላይ ታሪካቸውን በአጭር በአጭሩ ያቀረብነው ሴቶች ብቻ አይደሉም አገራችን ያፈራቻቸው። በርካታ ሴቶችን መጥቀስ ይቻላል። ይሁን እንጂ የአገራችን ሴቶች ታሪክ በአግባቡ ባለመጠናቱና በጽሑፍ ሰፍሮ ባለመገኘቱ ከትውልድ ወደትውልድ ሊተላለፍ አልቻለም። በመሆኑም በዘርፉ የተሰማሩ የታሪክ ተመራማሪዎች ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩበት ይገባል።” (ገፅ 18)

በምእራፍ ሁለት የቀረበው “ነገረ-ሴትነት በሐተታ ዘርኣያዕቆብና ሐተታ ወልደሕይወት” የሚል ርዕስ የተሰጠውን ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረበው ዳዊት ግርማ ነው። ሁለቱ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ፍልስፍና አምድ ተብለው የሚጠሩት ዘርኣያዕቆብና ወልደሕይወት ስለሴቶች ያላቸው አመለካከት ተብራርቶ የቀረበ ሲሆን፤ ዘመናቸውን የቀደመ አስተሳሰብ በያዙት በእነዚህ ፈላስፋዎች ርዕዮት ጽሑፉን ያነበበ ሁሉ ይደነቃል። በተለይም ዘርኣያዕቆብ በነገረ-ፆታ ላይ የነበረው አስተሳሰብ ከኖረበት ዘመን ብቻ ሳይሆን፤ ከአሁኑ ዘመን ወንዶችም ጭምር የተሻለ እንደሆነ ከጽሑፉ ለመረዳት እንችላለን።

ዳዊት ግርማ በጽሑፉ ስለሁለቱ ፈላስፎች የነገረ-ፆታ ዕይታ የሚከተለውን ብሏል፡-

“…በምዕራቡ ዓለም የሁለቱ ኢትዮጵያውያን ፈላስፎች ዘመን-ተጋሪ የሆኑ አብዛኛዎቹ ፈላስፎችና አሳቢዎች በ‘አባዊ’ ተፅእኖ ስር ወድቀው ሴትነትን ባቃለሉበት ወቅት፤ አፍቃሬ-ሴት ንቅናቄዎች ከመደርጀታቸው ምዕት ዓመታት በፊት፤ የኢትዮጵያ ጽሑፋዊ ፍልስፍና ለሴትነት ዋጋ ሰጥቶ እንደነበር ሐተታ ዘርኣያዕቆብና ሐተታ ወልደሕይወት በተሰኙ ሁለት የፍልስፍና ድርሳናት ማሳያነት መደምደም ይቻላል።” (ገፅ 20)

ዳዊት ግርማ በሐተታ ወልደሕይወት ላይ በሚያተኩረው አስገራሚ ጽሑፉ ወልደሕይወት ስለወሲብ ያለውን ዕይታ እንደሚከተለው ገልፆታል፡-

“በእኛ ማኅበረሰብ ስለወሲብ ማውራት አሁንም ድረስ ጸያፍ ተደርጎ ይወሰዳል። በ17ኛው ክፍለ ዘመን የነበረው ወልደሕይወት ግን ርእሰ-ጉዳዩን በግልፅ አንስቶ ተናግሯል። አሁንም ድረስ ወንዱ ለግል ሰሜቱ እርካታ ይጨነቃል እንጂ ስለሴቷ ደንታ የለውም። ወልደሕይወት ይህን ሁኔታ ተቃውሞ ለወንዱ ብቻ ሳይሆን ለሴቷም የስሜት መርካት ወንዱ ድርሻ እንዳለው አበክሮ ያስገነዝባል።” (ገፅ 34)

ዳዊት ግርማ ከ400 ዓመታት በፊት ለነበረው ፈላስፋው ዘርኣያዕቆብ አስተሳሰብ ያለውን ክብር የተሞላ ምልከታ ሲያቀርብም፡-

“ዘርኣያዕቆብ ትዳር ባሰበ ጊዜ የሴቷን ምርጫ አክብሮ ፈቃደኝነቷን ጠይቋል። ይህም አካሄድ የሴቶች መብት እንዲከበር ራሱ በተግባር ያሳየበት ነው። ፍቅርን በእኩልነት መሥፈርት ተቀብሎ በመስጠት ያምናል። ስለወደደችውም እንዲሁ ተቀብሎ አልተዋትም። ይልቁንም እሱ መልሶ አብልጦ እንዴት እንደሚወዳት ይጨነቅ ነበር። በንብረት ክፍፍል ረገድ የሚያገኙትን ሁሉ እኩል እንዳገኙና እኩል የንብረት ተካፋይነት መብት እንዳላቸው ይናገር ነበር። በስራ ክፍፍልም እንደዚሁ። እርሱ በመጻፍና በማስተማር ገቢ ያገኛል፤ እሷ በበኩሏ ተግታ በመፍተል ገቢ ታስገኛለች። ከሴት ልጅ ጋር አብሮ በፍቅር በመኖር በእኩልነት ያምናል።” (ገፅ 35)

በጥራዙ ከተካተቱ የጥናት ጽሑፎች መካከል በእኔ ዕይታ በዳዊት ግርማ የቀረበው የምእራፍ ሁለት ጽሑፍ የተሻለና ብዙ ቁምነገሮች በውስጡ ያዘለ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

“የቃቄ ወርደወት የሴቶች መብት ትግል ንቅናቄ አንትሮፖሎጂያዊ ዕይታ” የሚለው በሦስተኛው ምዕራፍ ያለው ጥናታዊ ጽሑፍ በደስታ ሎሬንሶ በጥሩ አቀራረብ የተገለፀ ነው። ደስታ ሎሬንሶ የቃቄ ወርደወትን ገድል አጠር ባለ መልኩ ያቀረበ ሲሆን፤ የወርደወት ታሪክ ላይ የቀረበው ጥናት ምን ያህል ለሌሎች ምርምሮች መነሻ ሊሆን እንደሚችል ጽሑፉን ሲያጠናቅቅ እንዲህ አውስቷል፡-

“…የወርደውት ታሪክ የፆታም ሆነ የነፃነትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ለዘመናት የቆየ እሴት መሆኑንና በሃገራችን የማኅበረሰብ ጥያቄን በሃገር-በቀል ዕውቀት፣ በባህላዊ አስተዳደር፣ በዳኝነትና ግጭት አፈታት ስርዓት፣ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት መደረጉን የምናይበት ታሪክ ነው። የጉራጌ ‹ጆይካ› ባህላዊ ምክርቤት በቃቄ ወርደወት የተመራውን የተደራጀ የሴቶች የመብት ጥያቄ በብዙ ውይይትና ምክክር መፍትሄ ለመስጠት ጥረት አድርጓል። በዚያ ታሪካዊ ወቅት ምክር ቤቱ የወርደወትን ጥያቄ ተመልክቶ በምክርቤቱ ጉባኤ ሚዛናዊ ክርክርና ዳኝነት ለመስጠት ሞክሯል። በዚህ ግፊት የጉራጌ ማኅበረሰብ ባህላዊ ሕግ ወይም ‹‹ቂጫ›› እንዲሻሻል ተደርጓል። ጨቋኝ የነበረው ባህላዊ ድንጋጌ በወርደወት ትግልና ተቃውሞ እንዲቀየር ጥረት ተደርጓል። ይህ የጥናት ውጤት በሃገራችን አልፎም በአህጉራችንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚካሄዱ የሴቶች መብት ትግል ዘመቻዎች፣ እርምጃዎችና ምርምሮች ጠቃሚ መነሻ እንደሚሆን አምናለሁ።” (ገፅ 51)

በአማርኛ በቀረበው ክፍል አንድ ላይ ከላይ ከተመለከትናቸው በተጨማሪ

  • ምዕራፍ አራት – የሻደይ ጨዋታ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር (በዶክተር አፀደ ተፈራ)
  • ምዕራፍ አምስት – እያደገ በመጣ ተለዋዋጭ ሁኔታ ውስጥ ህይወትን ማቆየት፤ የሐመር ሴቶች በመሬት አስተዳደር ያላቸው ተሳትፎ (በዶክተር ሣሙኤል ተፈራ ዓለሙ)
  • ምዕራፍ ስድስት – የጓጉሳ ሽኩዳድ ወረዳ ሴቶች የባህላዊ ግብርና እውቀት ትንተና (በዶክተር ሰዋገኝ አስራት እና በዶክተር ጉዳይ እምሬ)

ይገኙበታል።

ክፍል ፪

በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተሰናዳው የመጽሐፉ ክፍል ፪ ልክ እንደቀደመው ክፍል ሁሉ አስተማሪና አስደማሚ ጽሑፎች ተካተውበታል።

በዶክተር አለልኝ አስቻለ የተፃፈው ‹‹“Yodit Gudit” – The Defamed Queen of Ethiopia›› (“ዮዲት ጉዲት” – ስሟ የጠለሸው የኢትዮጵያ ንግስት) የሚለው የምእራፍ ሰባት ጥናት በአቀራረቡም ማራኪ፣ አመራማሪ ቁምነገሮችን ያዘለ ነው። ስለአክሱማዊቷ ንግስት ዮዲት ከዚህ በፊት የማናቃቸው ብዙ የታሪክ እውነታዎች አሉበት። ብዛት ስላላቸው ስሞቿ፣ ስለሷ ስለፃፉ የውጭ ሃገር ተወላጆችና አሳሾች፣ ስለ40 ዓመታት የአገዛዝ ዘመኗ እና ሌሎችም ዶክተር አለልኝ በ21 ገፆች ከሽነው አጣፍጠው አቅርበውታል። በመደምደሚያው ላይ ከተጻፉት ሃሳቦች ጥቂቶቹን ወደ አማርኛ መልሼያቸዋለሁ።

 “…እናም ዮዲት አመፀኛ፣ ጨካኝ መሪ፣ የዘር ጨፍጫፊ፣ ለባህላዊ የኢትዮጵያ ልማዳዊ ሃይማኖት የተገዛች፣ አይሁድ፣ እምነት-የለሽ፣ ወይም እምነት-የለሽ አይሁዳዊት፣ አፍሪካ-ኢትዮጵያዊ፣ ፈላሻ፣ ሱዳናዊት፣ ዳሞቴ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማ፣ ጠላት፣ የጠለፋ ሙከራዎች ተጠቂ፣ ወይ ደግሞ ከሃዲ አክሱማዊት የንጉሳውያን ቤተሰብ…

በተቃራኒው በኩል ደግሞ፤ ብልህና ታላቅ እንስት መሪ የነበረች፣ ማራኪ ውበት ያላት፣ አፍቃሪ፣ አቻ-የለሽ ኃያል ተዋጊ፣ ታላላቅ ተሰጥኦዎች የነበሯት ንግስት፣ ከአርባ ዓመታት በላይ በቆየው ዘመኗ ለባህላዊ የኢትዮጵያ ልማዳዊ ሃይማኖት ያላት ቀናኢነት ያልተከበረላትና ተቀባይነት ያጣች። ከዮዲት ጋር የባህሪ ውርርስ ያደረጉ ቀጣይ ነገስታት እናታዊ ስርዓትን (የሴቶች አገዛዝ) በኢትዮጵያ ውስጥ መስርተው ለብዙ ዘመናት የቆየውን አባታዊ አገዛዝ መሻር መቻላቸው። በዚህም ‘የተቆጡት’ ወንዶች በታሪክ ውስጥ ስራዎቿ እንዳይወሱ ስሟን ማጠልሸትና ስለሷ ጭራሽኑ ምንም ዓይነት መረጃ እንዳይገኝ አድርገው ማጥፋታቸው። በኢትዮጵያ ውስጥ አሉታዊ ቃል ከስማቸው ጋር የሚደረብላቸው የእውነት በታሪክ የነበሩ እንደሆነ ማወቅ ይገባል። ለዛም ነው የንግስት ዮዲት እውነተኛ ታሪክ ልናውቀው የምንችለው አሉታዊ ስሞቿን ባፋጣኝ በመቀየር፣ የተሰጣትን ትንሽ ቦታ፣ እና እንዲጠለሽ የተደረገ ሰብእናዋን ወደበጎ ምስል እና ክብር በመለወጥ ነው።” (ገፅ 125-126)

በእንግሊዝ ልሳን በቀረበው ክፍል ሁለት ላይ ደግሞ፣

  • ምዕራፍ ስምንት – Menen – the ILL-Famed Empress: a New Historicist Reading of Sahle Sellassie Birhane Mariam`s Warrior king (By Solomon Girma)
  • ምዕራፍ ዘጠኝ – The Role of Women in the Politico-Military Affairs of Ethiopia (1270-1855) (by Minale Adugna)
  • ምዕራፍ አስር – Traditional Forms of Resistance against Patriarchal Control: Siiqqee and Atteetee Rituals among the Guji and Borana Oromo of Ethiopia (By Firaol Belay and Sehin Tefera (PhD))
  • ምዕራፍ አስራ አንድ – The Art, Aesthetics and Gender Significance of Ashenda Girls` Festival in Tigray, Northern Ethiopia (By Selam Balehey and Mulubrhan Balehegn)

የተሰኙት ምዕራፎች ይገኛሉ።

መደምደሚያ

በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ምዕራፍ ሙሉ መጽሐፍ የመሆን አቅም አለው። ሁሉም ምዕራፎች በተትረፈረፉ ሃሳቦች እና ቁምነገሮች የተሞሉ ናቸው። መጽሐፉ በኢትዮጵያውያን የሴቶችን መብት የማረጋገጥ እንቅስቃሴ ውስጥ የራሱን ጉልህ አሻራ ማሳረፍ እንደቻለና ወደፊትም ታሪክ ከሚዘክራቸው መጻሕፍት መካከል ሊሆን እንደሚችል፤ አሁን ላይ ሆነን በድፍረት መተንበይ እንችላለን። ነገሮችን ከፍ ባለ የመረጃ ጥልቀት መመርመር እንደሚገባ የሚያስተምርም ነው።

መጽሐፉ በሁለት ቋንቋዎች መቅረቡ ተነባቢነቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳርፍ ይችላል። አስራ ሁለቱን ምዕራፎች ሙሉ በሙሉ በአማርኛና በእንግሊዘኛ በሁለት የተለያዩ መጻሕፍት ማሳተሙ የተሻለ አማራጭ ነው ብዬ ለመሟገት እደፍራለሁ።

ሌላው አስራ አምስት ጸሐፊያን በተሳተፉበት በዚህ መጽሐፍ የሴቶች ተሳትፎ በሰባት መወሰኑ ለትችት ያጋልጠዋል። የሴቶችን እኩልነት ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የራሱን ሚና መጫወትን ዓላማው ያደረገው ፕሮጀክቱ ሴት ጸሐፊያንን በ46.67% የመወሰኑ ተገቢነት ያጠያይቃል።

የቃላት አመራረጥ ህጸጾች እና የፊደላት ግድፈት በጥቂት ቦታዎች ላይ ቢታይም የአርትኦት ስራውን ዝቅ በሚያደርግ ደረጃ ላይ አልደረሰም። በአብዛኛው የመጽሐፉ ገፆች ላይ ያለው የአርትኦት ስራ ጥሩ ነው። በጥቂት ቦታዎች የታየው የቃላት ግድፈት ግን በቀጣይ ህትመቶች ሊሻሻል ቢችል መልካም ነው።

በኅብረተሰባችን ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ እንደዚህ ዓይነት መጻሕፍት፤ ገንቢ ሚናቸውን እንዲጫወቱ የበለጠ ሊበራከቱ ይገባል። አሳታሚው “የሴቶች ስትራቴጂካዊ ማዕከል” ደግሞ እንደዚህ ያሉ የመጽሐፍ ፕሮጀክቶችን በተጠናከረ መልኩ ሊቀጥል ይገባል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top