ቀዳሚ ቃል

ቀዳሚ ቃል

የሰው ልጅ ውልደት ሰው የመሆን ጉዞው የመጀመሪያ ምዕራፍ ነው። ከውልደቱ በፊት ባለው ጊዜ የነበረው ሰው የመሆን ጉዞ በውልጀት ቢጠናቀቅም ወደ ሌላ የሰውነት ጉዞ ምዕራፍ ያሻግረዋል እንጂ ሂደቱን አይቋጭም። በቁመት በማደግ፣ በሰውነት በመፋፋት፣ በእድሜ በመግፋት፣… ሂደቱ ይቀጥላል። ይህ የተለመደ ብቻ ሳይሆን የማይቀር የተፈጥሮ ሕግ ነውና እንለፈው። ልንለውጠው የምንችለው እና የሚለውጠን ላይ ስናተኩር አዲስ ምዕራፍ እንጂ መቋጫ የለውም።

የሰው መሆን ጉዞ ማብቂያው ከሰውነት መነጠል ወይም ሞት ነው። ከእስትንፋስ መቋረጥ በፊት ባለው እና ከመጀመሪያው የደረቅ ምድር እስትንፋስ መካከል ጉዞ አለ፣ ፍለጋ አለ፣ የቅርጽ ቅያሪ አለ፣ የይዘት ለውጥ አለ…

ባለፉት የታዛ መጽሔት ሕትመቶች ይህንን እና ይህንን መሰል የሰውነት ጉዞ መስመሮችን አስነብበናል። ዛሬ ደግሞ መሆን በአለመሆን ይተካል። ሰው ያለ መሆን ጉዟችን እንደምን ያለ እንደሆነ ሰፋ ባሉ ገጾች እንመለከታለን።

የተለመዱት ሁሉም ምዕራፎቻችንም ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል። ፍልስፍና፣ ግጥም፣ የጉዞ ማስታወሻ፣ የጥበብ ዳሰሳ፣ የመጻሕፍት ዳሰሳ፣ ስፖርታዊ ጉዳይ፣… ተካቷል።

የታዛ መጽሔት የዘወትር ትጋት ከዕለት ንባብ የዘለለ ሐሳብ ያላቸው ጽሑፎችን ለአንባቢ ማድረስ ነው። ተሳክቶልን ከሆነ የምታበረታቱበት፣ ስተን ከሆነ ወደ ቀናው መስመር የምትመልሱበት አድራሻዎቻችን እንደቀድሞው ክፍት ናቸው። ለጽሑፍ አበርክቶ ፍላጎት ያላችሁም ብታደርሱን ደስ እያለን እናስተናግዳችኋለን።

በንባባችሁ ላይ በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው ጽሑፎች ማጠንጠኛቸውን ሴቶች ላይ አድርገዋው ብታገኙ ይሆነኝ ብለን ያደረግነው መሆኑን ተረዱልን። የዓለም የሴቶች ቀን ከተከበረ ቀናት ያስቆጠረ ቢሆንም ጉዳዩ የዘወትር ነውና ዕለቱን በዚህ አስበነዋል። የሴት ጸሐፊዎችን ቁጥር እያሳደግን መምጣታችንም ከትላንት ዛሬ የተሻሻለ ጉዟችን ነው። በዚህ አጋጣሚ በታዛ መጽሔት ቁጥር 29 ሕትመት የዓድዋ ድልን አስመልክተን በሰራነው ልዩ እትም ደስታችሁን ለገለጻችሁልን ምስጋናችንን እናቀርባለን። ገበያ ላይ ፈልገን አጣነው ያላችሁን አንባቢዎቻችን በዌብሳይት አድራሻችን www.tazadebreyaredpublisher.com ላይ እንደምታገኙት እየጠቆምን በመልካም ምኞት እንዝለቅ- መልካም ንባብ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top