አድባራተ ጥበብ

ሶፎክለስ

ከ125 በላይ የሚሆኑ የትራጄዲ ሥራዎችን ለመድረክ ያበቃው ሶፎክለስ፤ አሁን በተሟላ ሁኔታ ላይ ያሉና ዓለም የሚያውቃቸው ስራዎቹ 7 ያህል ብቻ ናቸው።

የሶፊለስ ልጅ የሆነው ሶፎክለስ “ሂፒዎስ ኮሎነስ” በሚባል የአቲካ የገጠራማ ክፍል በምትገኝ ቦታ የሚኖር ሃብታም ሰው ነበር። ይህ ቦታ የተወለደበት ብቻ ሳይሆን፤ በርከት ያለ ቁጥር ያላቸውን ተውኔቶቹን የጻፈበትና ለመድረክ ያበቃበትም ጭምር ነው።

ሶፎክለስ የተወለደው በ490 ዓ.ዓ. ከተደረገው “የማራቶን ጦርነት” ጥቂት ቀደም ብሎ በ497 ዓ.ዓ. ነው። የጦርነት መሳሪያዎችን በማምረት እና በመሸጥ የሚተዳደረው የሶፎክለስ አባት ባለጸጋ ነበር።

በአቴናውያን ታላቅ የእውቀትና የአብርሆት ዘመን የተወለደው ሶፎክለስ፤ ተማሪ በነበረበት ዘመን በሙዚቃና በትግል (ሪስሊንግ) ሽልማቶችን በማሸነፉ እና በሚያሳየው የእረፍት አልባነት ባህርይ ምክንያት “የአቲካው ንብ” የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶት ነበር።
 

ሶፎክለስ ከሁለት ትዳር ሦስት ልጆች አፍርቷል። ‘ሎፎን’ እና ‘ሶፎክለስ’ የተባሉ ሁለት ወንድ ልጆቹን ያገኘው ‹ኒኮስራታ› ከተባለችው የመጀመሪያ ባለቤቱ ሲሆን፤ ሦስተኛ ልጁ ‹አሪስቶን› ደግሞ ‹ቲዮሪስ› ከተባለችው ሁለተኛ ሚስቱ የወለደው ነው።

የሶፎክለስ የመጀመሪያው የኪነጥበብ ዝና የመጣው በ468 ዓ.ዓ. የተካሄደውን የዳዮኒስያ ን የቲያትር ውድድር ሲያሸንፍ ነበር።

ምንም እንኳፕሉታረክ የሚባል የታሪክ ጸሐፊ፤ ሶፎክለስ ያሸነፈበት ተውኔት የመጀመሪያ ስራው ነው ቢልም፤ በአሁኑ ዘመን ግን የሶፎክለስ የመጀመሪያ ስራ “ትሪፕቶሌመስ” የተባለ ድል ካደረገበት ዘመን ሁለት ዓመት ቀደም ብሎ ያለው ስራው መሆኑ ተረጋግጧል።

ሶፎክለስ ህይወቱ ያለፈችው በ91 ዓመቱ ነበር። ከአሟሟቱ ጋር በተያያዘ በርካታ አጠራጣሪ አፈታሪኮች ይነገራሉ። ታዋቂ ከሆኑት መካከል

“ትንፋሹን ሳያሳርፍ በአንቲገን ትያትር ላይ ያለ ረጅም ቃለተውኔትን ሲያነበንብ ስቅ ብሎት ሞተ” የሚለው አንዱ ነው።

“አንቴስትሪያ ተብሎ በሚጠራ ፌስቲቫል ላይ የወይን ዘለላዎችን ሲበላ አንቆት ሞተ” የሚለው ሁለተኛው ሲሆን ሦስተኛው ስለአሟሟቱ የተነገረ ዝነኛ አፈታሪክ

“በዳዮኒስያ ከተማ የተደረገውን ቴአትር ለመጨረሻ ጊዜ ሲያሸንፍ በተሰማው ከፍተኛ ደስታ ሰበብ ሕይወቱ አለፈ”

የሚሉት ይገኙበታል። የሶፎክለስ ህይወት ካለፈ ከጥቂት ወራት በኋላ ስለሶፎክለስን ታላቅነት አስመልክቶ አንድ ገጣሚ

“ሶፎክለስ ብሩክ ነው። ረጅም ዕድሜን ታድሏል። ደስተኛ እና ባለተሰጥኦ ሰው ነበር። የብዙ ጥሩ ትረጄዲዎች ጸሐፊም ነበር። እናም የህይወቱ መጨረሻ ስቃይ ያልተሞላበት ነበር”

ሲል ምስክርነቱን ሰጥቶለታል።

ሶፎክለስ ለቴአትር ዓለም አስተዋወቃቸው ከሚባሉት ነገሮች ውስጥ አንዱ “3ኛ ገፀባህሪ” የሚባለው ነው።

ሶፎክለስ በተውኔቶቹ ውስጥ ዋና ገፀባህሪያቱን በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንዲያልፉ ያደርጋል። ብዙ ጊዜ ተከታታይነት ባላቸው ፈተናዎች ውስጥ ካለፉ በኋላ የድል ፍሬን እንዲያጣጥሙ ያደርጋቸዋል። ሶፎክለስ የዋና ተዋናዮችን ቁጥር ከሁለት ወደሦስት እንዲያድግ፣ ለመድረክ ገጽ የተዘጋጀ ሲነሪ (የመድረክ ስዕል) ማዘጋጀት የጀመረውም እሱ እንደሆነ ይነገርለታል። ከነዚህም በተጨማሪ ሶፎክለስ የአጃቢ ተዋኒያን ቁጥር ከ12 ወደ 15 እንዲያድግ አድርጓል። የሶፎክለስ መዝሙሮች ተወዳጅ እና ውብ አወቃቀር የነበራቸውም ተነግሮለታል።

ሶፎክለስ በ18 የዳዮኒስያ ፌስቲቫሎች እና በ6 የሌናያ ፌስቲቫሎች ላይ በቴአትር ውድድር አሸንፏል። የግሪክ ወርቃማ የቴአትር ዘመን እንደሆነ በሚነገርበት በዛ ዘመን፤ ሶፎክለስ ያለተቀናቃኝ ሽልማቶችን ጠራርጎ የብቻው አድርጓቸዋል። ሶፎክለስ የአንደኝነት ሽልማት ባላሸነፈባቸው ውድድሮች ላይ ሁለተኛ ነው የወጣው ተፎካካሪው ከሁለተኛ ደረጃ ዝቅ ብሎ አለማወቁ ሌላው አስገራሚ ገጠመኝ ነው።

በሶፎክለስ ቴአትሮች ውስጥ ያሉ ገፀባህርያት የሚታነፁት በታላቅ ጥንቃቄ ነው። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም አይረሴ ናቸው። የቴአትሮቹ ተፅዕኖ እጅግ በጣም ኃያል ከመሆኑ የተነሳ፤ ከግሪክ ውጭ ባሉ ነገስታት የግብዣ ጥሪዎች ደርሰውታል። ሶፎክለስ ግን ግብዣዎቹን ተቀብሎ አያውቅም ነበር። ከሃገሩ ለመውጣትም አልፈቀደም።

ታላቁ ፈላስፋ አርስቶትል በ335 ዓ.ዓ. በጻፈው ግጥም የሶፎክለስን “ኤዲፐስ” ጠቅሷል። በትራጄዲ ሊደረስበት የሚችል የመጨረሻው ታላቅ ደረጃ አድርጎም አሳይቶታል። ይህም ሶፎክለስ ከዘመኑ ቀጥሎ በመጡ ትውልዶች ላይ ሳይቀር የነበረውን የከበረ ስም የሚያሳይ ነው።

ለእኛ ሃገር በጣም የሚያስደንቀው ነገር ከ125 ከሚበልጡት የሶፎክለስ ስራዎች መካከል “The Ethiopians” (ኢትዮጵያውያኖቹ) የሚል ድርሰት መኖሩ ነው።

ሶፎክለስ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያያይዘው ይህ ታሪክ ብቻ አይደለም። ከትልልቅ ስራዎቹ መካከል “ኤዲፐስ ንጉስ” እና “አንቲገን” የተባሉት በአማርኛ ተተርጉመው በሃገራችን ውስጥ ባሉ የቴአትር መድረኮች ላይ መታየት ችለዋል።

የሶፎክለስ ቴአትሮች ተፅእኗቸው ላቅ ያለ ከመሆኑ የተነሳ፤ በሌሎች መስኮች ላይ ስማቸው ሰፍሯል። ለምሳሌ በስነልቦና ላይ “ኤዲፐስ ኮምፕሌክስ” የሚባል የአዕምሮ ህመም ሞያዊ ቃል አለ። “ኤዲፐስ ኮምፕሌክስ” ያለበት ሰው እናቱን በጣም የሚወድ ነገር ግን አባቱን በጣም የሚጠላ ነው። ሌላው ምሳሌ ደግሞ “ኤሌክትራ” ከሚባለው ቲያትር የተወሰደ “ኤሌክትራ ኮምፕሌክስ” የሚባል የአዕምሮ ህመም ሞያዊ ቃልም አለ። “ኤሌክትራ ኮምፕሌክስ” ያለበት ሰው አባቱን በጣም የሚወድ ነገር ግን እናቱን በጣም የሚጠላ ነው።

እንግዲህ የሶፎክለስን ታላቅነት በሌሎች ሙያዎች ላይ ባሳደረው ተፅዕኖ ለመገመት እንችላለን። ከዛም በተጨማሪ ታላላቅ በሚባሉት እንደነ አሪስቶትል በመሰሉ ፈላስፋዎች የተከበረ እና የተደነቀ የዘመኑ ግዙፍ የጥበብ አድባር እንደሆነ ለመገመት አይከብደንም።

ስለታላቁ ሶፎክለስ ብዙ ብንል በወደድን፤ የቴአትር ባለሙያዎች ብዙ ስለሚያወሩለት የጥበብ አድባር፤ እኛ ከብዙ በጥቂቱ እንዲህ ፃፍን። ሰላም!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top