ፍልስፍና

ሰው የ-አለ-መሆን ጉዞ? (በዘመነ ቴክኖሎጂ)

ሰው የመሆን ጉዞ በሚል ርእስ የጀመርነው ሐቲት አንዱን ጉዳይ ስናነሳ ሌላ ሐረግ እየሳበ የሰውነት ቋጠሮ ትብታቡ እየተወሳሰበ መሄዱ አልቀረም። ባለፉት ጽሑፎች ሰው የመሆንን ጉዞ ከሃይማኖት፣ ከባህል፣ ከፍልስፍና እና ከሳይንስ አንጻር አይተነዋል። ጽሑፎቹ የተከታታይነት ባህርይ የላቸውም። አንድን ርእሰ ጉዳይ በተለያየ አቅጣጫ ለማየት ታሳቢ በማድረግ የቀረቡ ናቸው። የቀደሙት ሁለት ጽሑፎች በአስተሳሰባዊ መዋቅር ውስጥ ሰው ራሱን የተረጎመበት እና ራሱን ካገኘበት ህልው ሁኔታ በመነሳት የመሻቱን ጥግ እና የህልውናውን እውነታ ለማስታረቅ በሄደባቸው መንገዶች ያካበታቸው ገዥ ሐሳቦችን የሚመለከቱ ሐተታዎች ናቸው። ይኸኛው ጽሑፍ ደግሞ በዘመነ ቴክኖሎጂ የሰው ልጅ ጉዞ ሰው የመሆን ወይስ ከሰውነት የማምለጥ ጉዞ ነው? የሚል በአያዎ ዘይቤ የተቃኘን ዓብዪ መጠይቅ ይመረምራል። ለዚህ ጥያቄ እንደመነሻ ምክንያት የሆነው የዘመናችን የቴክኖሎጂ ዕድገት በሁለት አቅጣጫ የሰውነትን ጉዳይ እየበየነው ስለሆነ ነው። በአንድ በኩል የቴክኖሎጂ ምጥቀት የሰውን ልጅ ኅሊና እስከመቆጣጠር የሚያደርስ ማሰብ የሚችሉ ሰው መሰል ማሽኖችን (ለምሳሌ ሮቦት) እየፈበረከ ሰውን የመተካት ሂደት ላይ የመድረሱ እውነት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በጀነቲክ ኢንጂነሪንግ መስመር የሳይንስ ምርምር የሰውን ልጅ የተፈጥሮ ጂን መሰረት ያደረጉ ነገር ግን ከተፈጥሯዊው ሰው የተለየ ሕመምን የመቋቋም፣ ረጅም ዕድሜ የመኖር፣ የሩቁን የማስታወስ፣ ክህሎት ያላቸው ፍጡሮች መፍጠር የሚያስችለው ደረጃ ላይ የመድረሱ እውነታ ነው። እናም የነገው ሰው ማን ነው? የነገው ሰው ምንድን ነው? በቴክኖሎጂ ዘመን የሰው ልጅ ጉዞው ሰው የመሆን ወይስ ሰው ያለመሆን? የሚሉ መነሻ ጥያቄዎች ለውይይት ቀርበዋል።

ለዛሬው ጽሑፍ መነሻ የሆነን ቴክኖሎጂ የሳይንስ አንድ አካል እንደመሆኑ ባለፈው ክፍል የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ተቃርኖ ሰው የመሆንን ጉዞ እያወከው እንዳይሆን እንደማስጠንቀቂያ የቀረበችው አንቀጽ ናት።

 “ሰውነትን ከነበረው የተፈጥሮ እና የሰው ሰራሽ ፈተናዎች ነፃ እንዲወጣ በማስቻል ረገድ የሳይንስ አስተዋጽኦ ተዘርዝሮ የማያልቅና በርግጥም ተፈጥሮን የመቀየር ያክል የሚተካከል ነው ማለት እንችላለን። በዚሁ ልክ የሳይንስ መንገድ የዘነጋው ጉዳይ፣ ያልዘጋው ቀዳዳ እና የከፈተው አንጋዳ (አዘቅት) መኖሩንም ማጤን ይገባል። ይህንን የሳይንስ ተቃርኖ በሌላ ጽሑፍ በሰፊው የምመለስበት ይሆናል።” የሳይንስ ከቴክኖሎጂ መሳሪያ ጋር ሲቀናጅ ተፈጥሮን የመቆጣጠር እና የመቀየር አቅሙ እጅጉን ይጨምራል። በዚህም ሰው የመሆንን ጉዞ አቅጣጫውን ይቀይረዋል። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ልዩነታቸው ሳይዘነጋ በተቀያያሪነት ተጠቅሜባቸዋለሁ። ሳይንስ በአመዛኙ መላምታዊው፣ አስተሳሰባዊ ገጽታ ሲሆን ቴክኖሎጂ ደግሞ ቁሳዊ ገጽታው፣ መከወኛ መሳሪያው ነው። የሳይንስ ፈጠራ ቴክኖሎጂን መሣሪያ ሲፈጥር የቴክኖሎጂ መሣሪያ ደግሞ ሳይንሳዊ እንቅስቃሴዎችን ያግዛል። አንዱ በአንዱ ውስጥ የመኖሩ እውነት የተረጋገጠ ስለሆነ የቃላት ብዥታ ሊፈጥር አይገባም።

  ቴክኖሎጂ ባለሁለት ስለት

 ቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ ፈተናዎች በማቅለል ረገድ ይኸ ቀረሽ የማይባል ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው። የሰው ልጅ ከሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ፈተናዎች ነፃ እንዲወጣ የቴክኖሎጂው እገዛ ከፍተኛ ነው። ሁለንተናዊ ችግሮችን ለመቅረፍ እና ተፈጥሮን ለሰው ልጅ ለማስገበር ሁነኛው መሣሪያ ቴክኖሎጂ ነው። የሰው ልጅ ድንጋይን እንደ መሳሪያ ተጠቅሞ ከማደን ጀምሮ እሰከ ዘመናችን የሮቦት፣ የሳይቦርግ እና ናኖ ቴክኖሎጂ (ማይክሮ ቺፕስ) ድረስ በበርካታ ዘመናት ሂደት ያካበተው የቴክኖሎጂ ዕድገት ሰውነትን ከተጋረጡበት ፈተናዎች ነፃ እያወጣው፣ አንዳንዴም ሰውነት የተፈጥሮ ተሰጥኦውን እስኪዘነጋ ድረስ በቴክኖሎጂ እምነት በመጣል የቴክኖሎጂ ጥገኛ እየሆነ ነው። የቴክኖሎጂ በዚህ ስለት የማይቆርጠው የማይፈልጠው ጠንካራ ፈተና የለም ወደሚል አዝማሚያ ተደርሷል። ባጭሩ ቴክኖሎጂው ሁሉንም ችግሮች መፍታት እችላለሁ የሚል የእግዜርነት ባኅርይን ተላብሷል ማለት እንችላለን። ሰው ለዘመናት ይዞት የነበረውን የዓለምን መረዳት የሚያስቀይሩት የቴክኖሎጂ ግኝቶች የባህልን፣ የቀደመ ፍልስፍናን፣ የሳይንስን የራሱን፣ የሃይማኖትን ብያኔዎች እየተፈታተኑት ይገኛሉ። ምንም እንኳ ይህ የቴክኖሎጂ ጠንካራ ክንድ ለበርካታ ችግሮች መፍትሔ እንደሚያስገኝ የሚያምኑት በሙሉ ልባቸው ቢቀበሉትም፣ ቴክኖሎጂን በጥርጣሬ የሚያዩትም አልጠፉም።

የቴክኖሎጂ ሌላኛው ስለት የማይነኩ ስስ ብልቶችን እንዳይቆራርጣቸው የሚሰጉ በርካቶች ናቸው። እዚህ ላይ ነው ቴክኖሎጂ ሰው የመሆንን ጉዞ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ በመምራት ሰውነት ወደማይወጣበት ፈተና እንዳይከተው ሃይ ሊባል ይገባዋል የሚሉት ሙግቶች ወደ መድረክ የወጡት። ይህንን ስጋት የሚጋሩ አካላት የሳይንስና የምርምር ተቋማት በመንግስታዊ አካላት ቁጥጥር ሊደረግባቸው ይገባል፣ ሳይንስም ከችግር ፈችነት ባሻገር ያልተገደበ ፈጠራዎች ላይ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች መነሻቸው፣ መንገዳቸውና መዳረሻቸው በደንብ ሊተኮርባቸው ይገባል የሚሉ አሉ። አንዳንዶቹ የቴክኖሎጂ ትችቶች ከጭፍን አድሃሪነት፣ ካልተረጋገጠ መረጃ የመነጩ፣ የባህል፣ የሃይማኖት ጠበቃ ነን ከሚሉ ብስሉን ከጥሬው ያልለዩ ጥቅል ፍረጃዎች ናቸው። ለምሳሌ በቀደመው ዘመን ስልክ እና ሬዲዮ በኢትዮጵያ የሰይጣን መሣሪያዎች እንደሆኑ ሲፈረጁ፤ ዘመናዊው ትምህርት ልጆቻችንን ከባህላቸው እና ከሃይማኖታቸው ያሸሽብናል በሚል ሰበብ ከፍተኛ ተቃውሞ እንደገጠመው እነ መርስዔ ኃዘን ወልደ ቂርቆስ ጽፈውልናል። እንደዚህ ዓይነቶቹ ተቃውሞዎች መጤው ባህል፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ከነባሩ ጋር እንዴት መታረቅ አለበት የሚል ሙያዊ ጣልቃ ገብነት ያካተቱ ትችቶች ሳይሆኑ በጥቅል ፍረጃ እና የጋራ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረቱ ስለሆኑ ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያይላል። እዚህ የምንመለከተው በፍልስፍናዊ እና ሳይንሳዊ እይታ የተደገፉ በርካታ የቴክኖሎጂ እና የሳይንስ ትችቶችን ነው። የተወሰኑትን ሙግቶች እንመልከት፡፡

 ቴክኖሎጂን በጥርጣሬ የመመልከት መነሻዎች በርካታ ናቸው። አንዳንዶቹ ባይተዋር ሳይንስና ቴክኖሎጂ በአገር በቀል ዕውቀቶች እና በዕውቀቶቹ ባለቤቶች ላይ የማሕበረሰባዊ ስነ ልቡና ተቃርኖ በማምጣት ዕውቀትን በመግደል ማኅበረሰቡን የማጥፋት ሚና ይጫወታሉ የሚሉት ናቸው። በጥቅሉ ሲታዩ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ነባሩን ስነ ምግባራዊ በጎነት፣ ነባሩን የዕውቀት አማራጭ፣ ባህላዊውን የችግር አፈታት ዘዴ ሙሉ በሙሉ እንተካለን በሚል የነበረንን በማስጣል ላይ እንዳያተኩሩ መያዝ ያለበትን በመያዝ፣ መጣል ያለበትን በመጣል የተሻለ ውህድ እንፍጠር የሚሉት ናቸው። በዚህ ጎራ እነ እጓለ ገብረ ዮሐንስ፣ Albert Schweitzer፣ ሳንቶስ እና ሳንድራ ሃርዲንግ ይመደባሉ። Albert Schweitzer የብልጽግና ምኞት አውሮፓዊውን ሰብዓዊነት በእጅጉ ተገዳድሮታል ይለናል። “European humanity is infused and impelled by a will to progress which is superficial and improperly oriented.”

 እንደ ሳንቶስ እና ሃርዲንግ ሙግት “ትክክለኛው እውቀት የአውሮፓ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንጂ አገር በቀል ዕውቀቶች ያልተረጋገጡ እምነቶች እና ጥንቁልናዊ ባህርይ አላቸው፣ ስለዚህ በዘመናዊ ዕውቀት መተካት አለባቸው” የሚለው ስሑት ሐሳብ ባንድ በኩል ነባሩን እውቀትና ባለቤቶቹን የኅሊና ቅኝ ግዛት ሥር የሚጥል ሲሆን በሌላ በኩል የሰው ልጆች የዕውቀት ዕድገት ከተለያዩ ባህሎች ግብዓት እንዳያገኝ በሩን መዝጋት ነው። ለሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሙሉ ልብን መስጠት እንደ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ታሪክ ወዘተ መሰል ጥናቶች ሳይንሳዊነት እየተተኩ ሰውነትን ከጫወታ ውጭ ያደርጉታል፤ በተቃራኒው ደግሞ ሳይንስ የማይደርስባቸውን የሰዋዊነት ሚስጥሮች ተጋላጭ በማድረግ አደጋ ላይ ይጥላቸዋል። እንደ ሃከር እና ግሎክ ሐተታ ምሉዕ እውነት በምክንያታዊነት እና ሳይንሳዊ ምርምር ብቻ ይደረስበታል የሚለው የሳይንስ እብሪትም ተገቢ አይደለም፤ እንደ ካንት ምክንያታዊነት ሲያልቅ የእምነት በር ይከፈታል፤ እነ ኬጋርድ እና ኒቼ ደግሞ የሰው ልጅ ትክክለኛ የኑባሬ ሁነቶች ከምክንያት፣ ከሳይንሳዊ ማብራሪያና ከቋንቋ አድማስ ውጭ ናቸው ይላሉ። የሰው ልጅ ጉዞ ቀደምት ዕውቀትን እና ይትበሃልን ከሙታን ጋር በመቅበር ላይ የተመሰረተ ሳይሆን የሙታንን ኅያው መንፈስ፣ የኅያዋንን ሙት መንፈስ ለማዳን በሚደረግ ዱላ ቅብብል ላይ የተመሰረተ ነው የሚለን ደግሞ Jaroslav Pelikan ነው። የዚህ ሙግት ማጠንጠኛው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት የቱንም ያክል ቢራመድ፣ ባህል፣ ሃይማኖት እና ይትበሃልን ሙሉ በሙሉ ከቦታቸው ማፈናቀል የለብንም የሚለው ድምዳሜ ነው።

ሁለተኛው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትችት ደግሞ በራሳቸው በሳይንስ ሰዎችም ተቀባይነት ያለው ነው። ዋና ትኩረቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራዎች መጭውን የሰው ልጅ ነጻነት እና ተፈጥሯዊ ምንነት የመበየን አዝማሚያ እያሳዩ መሆናቸው ነው። በአንድ በኩል የስነ ኅሊና ምርምሮች የሰውን ልጅ አንጎል አስተሳሰቡን የሚተካ የኒውሮ ሳይንስ ዕድገት ሰዎች ከልጅነት እስከ ዕውቀት ያጠራቀሙትን የኅሊና ማስታወሻ ወደ ኮምፒውተር ገልብጦ የማንበብ ደረጃ ላይ ደርሷል። የተለያዩ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን በመጠቀም የመጠቀ አስተሳስብ ደረጃ ላይ እና ሌላ “ዓለም መመልከት የሚያስችል” ብቃት ከተራው ሰው ጋር እንዳይግባቡ ያደርጋቸዋል። በዚህም በኅሊናቸው ምጥቀት ግማሽ ሰው ግማሽ ማሽን የሆኑ ፍጡሮችን ማየት የሚያስችለን ደረጃ ላይ ደርሰናል። ከነዚህ ፍጡሮች ጋር ስለ ሞራሊቲ፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ማሕበራዊ ኃላፊነት እና ግዴታ፣ ስለ ስሜት በምን መግባባት የሚቻል አይመስልም። ለዚህ ማሳያ የሚሆኑን እንደ DMT ዓይነት ኅሊናን የሚያመጥቅ መድኃኒት በወሰዱ ሰዎች ላይ የተሰሩ ዶክመንቴሪዎች ናቸው። ይህ የኒውሮ ሳይንስ ምርምር ዕድገት ከሰው ልጅ ነጻነት እና ገመና ጋር በተያያዘ የሚያመጣው ተቃርኖ ቀላል አይደለም። ማንም ሰው ፈቃዱን ባልገለፀበት ሁኔታ የግል ገበናው በኮምፒውተር ተገልብጦ የሚነበብበት መንገድ እየቀለለ ነው።

ሌላኛው የሳይንስና የቴክኖሎጂ ተቃርኖ የባዮ ቴክኖሎጂ ዕድገት ነው። አሁን ላይ ሰዎችን በላባራቶሪ ማምረት ከባድ አይደለም። የጀነቲክ ኢንጂነሪንግ ዕድገት እንደ ኮምፒውተር፣ ሞባይል ስልክ፣ እና ማንኛውም የፋብሪካ ምርት ማሽን የሚመስሉ ሰዎችን እንደ ዶሮ ጫጩቶች በፋብሪካዎች አማካኝነት በገፍ ማምረት እንደሚቻል አመላካች ነገሮች አሉ። በ1932 እ.አ.አ ሃክስለይ Brave New World በሚል ርእስ የጻፋት ልቦለድ የዚህ መነሻ ሞዴል ነች። እንደ ሃክስለይ አስተሳሰብ በላቦራቶሪ የሚመረቱት ‘ሰዎች’ አምራቹ በሚፈልገው ዕድሜ እና የሥራ ባህርይ፣ መኖሪያ ቦታ ምርጫ፣ የአየር ፀባይ መቋቋም አቅም ይወሰናሉ። በሌላ አነጋገር እነዚህ የፋብሪካ ውጤቶች አምራቹ ቀድሞ በበየነላቸው ምርጫ እና ተክለ ሰውነት የሚፈበረኩ ናቸው።

 ሌላው የባዮ ቴክኖሎጂ ስኬት የሰው ልጆችን እድሜ የሚያራዝም፣ በሽታን የሚቋቋም፣ የማስታወስ ችሎታቸውን የሚያሻሽል የጂን ጣልቃ ገብነት ላይ የተመሰረተ ነፃ አውጭ ባዮሎጂ (Liberation Biology) የሚባለው ነው። የነፃ አውጭ ባዮሎጂ ዋና ዓላማ የሰው ልጆችን ከፈታኝ ተግዳሮቶች ነፃ ማውጣት ነው። ነገር ግን ሄዶ ሄዶ ሰውነትን ከተፈጥሮ ስሪቱ የማሸሽ አዝማሚያ ይኖረዋል። በዚህ ረገድ የሳይንስ ተመራማሪዎች ራሳቸው የሚፈሩት ነገር ይህ ልቅ የሆነ የሳይንስ ግስጋሴ አንድ ቀን ከሳይንቲስቱ ቁጥጥር ውጭ ይሆን እና እንደ ኒኩለር ቦምብ የሚያወድም ሃይል ሊገጥመን ይችላል ይላሉ። ለምሳሌ ፖላክ የተባለ ሳይንቲስት ለአንድ ሪፖርተር በሰጠው ቃለ መጠይቅ በባዮቴክኖሎጂ ምርምር ላይ አንዳች ስህተት ቢፈጠር የሚያስከትለውን ጥፋት ሲያብራራ በቅድመ ሂሮሽማ ዘመን ላይ እንዳንሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል ይለናል። ለምሳሌ ስለ ካንሰር ስርጭት የሚደረግ በላቦራቶሪ ሙከራ ላይ ያለው እንስሳ ሰው ቢሆን እና የሆነ ስህተት ቢፈጸም መቆጣጠር የማይቻል የካንሰር መስፋፋት ቢከሰት ሄሮሽማን እና ናጋሳኪን እንዳጠፋ ኒኩለር ቦምብ የዛሬውን የሰው ልጅ ሊያጠፋ የሚችል ሃይል አለው ይላል። በዚህም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ከላቦራቶሪ ወጥቶ ተግባራዊውን የሰው ልጅ ሕይወት በሚያንኳኳበት ጊዜ የሚያመጣው ጣጣ ከባድ ነው። ምክንያቱም ከበስተጀርባው የሚዘውረው የፖለቲካ እና የገንዘብ ድጎማ ሳይንስ ራሱን የቻለ ነፃነት የለውም። በዚያ ላይ ሳይንስ ራሱን የቻለ ቢዝነስ እየሆነ ነው። ሳይንስ ከችግር ፈቺነት ወደ የንግድ እና የፖለቲካ ውድድር ከገባ ደግሞ የሰውነትን ጉዞ በእጅጉ ሊጎዳው ይችላል። ምናልባትም መጭው ጦርነት ከቴክኖሎጂ ጋር ሊሆን ነው። በቀልጣፋው ሊፈውሱ የሚችሉ መድኅኒቶችን የሚያመርት ሳይንስና ቴክኖሎጂ በቀላሉ ሊስፋፉ የሚችሉ በሽታዎችን ማምረቱ አያጠራጥርም። ይህም ሰው የመሆንን ጉዞ ይገዳደራል።

 እንደዚህ ዓይነቶቹ ስጋቶች በእንደኛ ያሉ የቴክኖሎጂ እድገታችው ወደ ኋላ በቀሩ ማኅበረሰቦች ዘንድ ምን ዓይነት ተቃርኖ፣ ጸጋና ፍዳ ይዘው ይመጣሉ? የሚለው ጥያቄ ጥናትና ምርምር ያስፈልገዋል። ሳይንቲስቶቻችንስ የዓለም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት እንዲህ ሰው በመፍጠር ደረጃ በደረሰበት ዘመን ቦታቸው የቱጋ ነው? የሳይንስና ምርምር ሥራዎቻቸውስ በማኅበረሰቡ ነባር ይትበሃል፣ ባህል፣ ቋንቋ እና ሃይማኖት አንፃር እንዴት ይጓዛል? የሚሉት ጥያቄዎች ለባለሙያዎቹ እና ለፖሊሲ አውጭዎቹ የተተዉ ናቸው።

እዚህ ላይ ሊባል የሚገባው አንድ ነገር ቢኖር የኛ ማኅበረሰብ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የሚጠቀምበት የሥልጣኔ ደረጃ ምን ይመስላል? የሚለው ነው። ምንም እንኳ በርካታ የሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ የባዮቴክኖሎጂ ምርምሮች በየትምህርት ተቋሞቻችን ያሉ ቢሆንም የዕድገት ደረጃቸው፣ የሚያመጡት ትርፋማነት እና የያዙት ተጓዳኝ ችግሮች ላይ ያለው ጥናት ትኩረት ይፈልጋል። በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን በኩል እየገጠመን ያለውን እክል በታዛ መጽሔት የቀደሙ እትሞች ላይ በተከታታይ ተመልክተናል። ከግብርና ምርምር ጋር በተያያዘ፣ ከጤና ተቋሞቻችን ጋር በተገናኘ እየሄድንባቸው ያለንበት የቴክኖሎጂ ትግበራ መንገዶች ላይ ከወዲሁ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። በራያና ወጀራት አካባቢዎች በለስ ላይ በተደረገ የሳይንስ ጣልቃ ገብነት የአካባቢውን በለስ ሙሉ በሙሉ በማውደም ያስከተለውን ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። የግብርና ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ምርምራችን የቤንሻንጉል ጉሙዝን የማንጎ በሽታ ሙሉ መፍትሔ ማምጣት እንዳልቻለ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። ከማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ ፀረ-ተባይ እና ፀረ-አረም ጋር የተያያዙ ኬሚካሎችም የመሬቱን ዘላቂ ጥቅም ምን ያክል ያበለፅጋሉ ወይም ይገዳደሩታል? የሚሉት ነጥቦችም ትኩረት ያሻቸዋል። የውጭ ኢንቨስተሮች ለአበባ እርሻና ለሌሎች የግብርና ምርቶች በሚከራዩዋቸው ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ላይ የሚጠቀሙበት ምርት አበልጻጊ ቴክኖሎጂ የኪራይ ጊዜያቸው ካለፈ በኋላ መሬቶቹ የማምረት ተፈጥሯዊ ክህሎታቸውን አሟጦ ባዶ እንደማያስቀራቸው ዋስትና የለንም። አንዳንዶቹ የአበባ እርሻዎች አገልግሎታቸውን ከጨረሱ በኋላ ለእርሻም ሆነ ለህንጻ ግንባታ የሚሆን አቅም እንደሌላቸው የሚናገሩ ሰዎች አሉ። በማድለቢያ ስፍራዎች የምናደልባቸው ከብቶች ሥጋ የተመጋቢዎቹን ጤና በማዛባት ሊያስከትሏቸው የሚችሉት የጤና እክል ምን ሊሆን እንደሚችል ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል። ከዘላቂ ልማት እና የምግብ ዋስትና አንፃር ካየናቸው እንደዚህ ዓይነቶቹ የቴክኖሎጂ ተቃርኖዎች የነገውን ትውልድ ሰው የመሆን ጉዞ ያገናዘቡ አይመስሉም።

 ለመሆኑ መጭው ‘ማኅበረሰብ’ ምንድን ነው?

 በዚህ ጽሑፍ ማዕከላዊውን ስፍራ የያዘው አንዱ ጥያቄ ይህ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግስጋሴ በመጭው ቅርብ ወይም ሩቅ ጊዜ ምን ዓይነት ሰዎችን ይፈጥራል? ማኅበረሰቡስ ምን ዓይነት ነው? የሚል ነው። አሁን ላይ ይህ ዓይነቱ ጥያቄ ለኢትዮጵያውያን ወለፈንዲ ወይም ትርጉም የለሽ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ሰዎች በሚበሉት የምግብ ዓይነት የጤናቸው ሁኔታ እንደሚቀያየረው ሁሉ በምንጠቀምባቸው የሳይንስ ውጤቶች አማካኝነት የባኅሪያችንም ነገር ይወሰናል። ስለ ሞት፣ ስለ ሕይወት፣ ስለ ሌሎች ሰዎች፣ ሰለ ማሕበረ-ሰብ ማሰብ በራሱ ሰዋዊ ባህርይ ሆኖ ሳለ እንደ ሮቦት እና ማንኛውም የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ “ሰዎች” እንደነዚህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ ያላቸው ትኩረት በማሕበራዊ እሴቶች ተቀርጾ እንደወጣው ተፈጥሯዊ ሰው አይሆኑም። ምናልባትም በምንጠቀመው የቴክኖሎጂ ቁስ አማካኝነት ነጋችንን እና እጣ ፈንታችንን በርግጠኝነት የምናውቅ ከሆነ ሕይወት ትርጉም አልባ ነው የምትሆነው። ዛሬ ላይ በወላጆቹ ወይም በሳይንቲስቶቹ ፈቃድ እና ብያኔ የተፈጠረውን ሰው ነገውን በመወሰን ረገድ ነጻነቱን መጋፋት ነው። ለምሳሌ ሙለር የተባለ ጸሐፊ፣ የሕይወት ትርጉም ሰው ስለ ነገው እርግጠኛ ካለመሆኑ ይመነጫል ይላል። ለዚህም ነው መጭው ማኅበረሰብ ምንድን ነው? ብለን መጠየቅ የግድ የሚለን።

በያዝነው ርእሰ-ጉዳይ ሰው መሆን እና ቴክኖሎጂ ያላቸውን መስተጋብር በመተንተን እና ሙግቶችን በማስተናገድ ከተጻፉት መጻሕፍት ውስጥ ሁለቱን ለአንባቢ መጠቆም በጉዳዩ ላይ የተሻለ ግንዛቤ ይፈጥራል። አንዱ በ2005 የታተመ Liberation Biology: The Scientific and Moral Case for the Biotech Revolution የተሰኘ የRonald Bailey መጽሐፍ ሲሆን ሁለተኛው በ Sheila Jasnoff 2019 የታተመው Can Science Make Sense of Life? የተሰኘው ነው። ባይለይ የሳይንስ መርምር በመንግሥት ቁጥጥር ስር መሆን አለበት ከሚሉት ጀምሮ ሳይንሳዊ ምርምሮች እና የባዮ ቴክኖሎጂ ጉዞዎች ነፃ መሆን አለባቸው የሚሉ ሙግቶችን አካቷል። የጃስኖፍ ሥራ የባዮሎጂ ዕድገት ጉዞ፣ ባዮ ቴክኖሎጂ በሕይወት ትርጓሜ ላይ የወሰደውን የበላይነት እና እየሄደበት ያለውን መንገድ ተቃርኖ ለመገንዘብ የሚያስችለን ጥንቅር ነው።  

በሳይንስና ቴክኖሎጂ ያልተገደበ ግስጋሴ መጭው ማኅበረሰብ ማሽን መሰል ሰዎች ስብስብ የመሆን ዕድሉ ግነት ቢመስልም ስጋቱ ግን ውሃ የሚቋጥር ነው። አንድ ፍሪንጅ የተሰኘ ሳይንቲፊክ ፊልም ላይ እንዲህ የሚል ንግግር አለ። “The advances of science, which is supposed to expand our knowledge of the universe will if not carefully controlled, destroy the world as we know it. I will take the logical ambitions if not only driven us to the point of catastrophe. But the catastrophe has already begun.” ስለ ዓለም ያለንን ዕውቀት ለማስፋት የታለመለት ሳይንስ ግስጋሴ በጥንቃቄ ካልተያዘ የምናውቀውን ዓለም ሊያወድመው ይችላል። መቅሰፍቱም በይፋ ተጀምሯል ማለት ይቻላል እንደማለት ነው።

 እንደዚህ ዓይነቶቹ ሙግቶች ለሦስተኛው ዓለም ትርጉም አልባ ቢመስሉም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ጸጋ ተቋዳሽ እንደመሆናችን የሚያመጣውም እዳ ገፈት ቀማሽ ነን። በተለይ በአስተሳሰባዊ ገጽታው የነባሩን ዕውቀት ከአደባባይ በማባረር መድረኩን የተቆጣጠረው ‘ዘመናዊ’ አስተሳሰብ የኅሊና ተገዥ በማድረግ ሥጋው አፍሪካዊ ነፍሱ/ኅሊናው አውሮፓዊ የሆነ የተማረ ማኅበረሰብ እንዳይፈጥር መስጋቱ ትርጉም አልባ አይደለም። በሌላ በኩል ለወሊድ መቆጣጠሪያ፣ ለምግብ ማጣፈጫ፣ ለጉልበት መስጫ፣ ለኅሊና ርካታ ወዘተ ብለን የምንወስዳቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች በትክክል የተጠኑ ሊሆኑ ይገባል። ጥናቱ ደግሞ በራሱ በሳይንስ ወይም ቴክኖሎጂ ምርምር ይሁንታ ላይ ብቻ የተመሰረተ መሆን የለበትም። ይኽማ ዞሮ ዞሮ ከሳሹን፣ ወይም ተከሳሹን ምስክር፣ ፈራጅ ዳኛ አድርጎ ማቅረብ ይሆናል። ይልቁን የስነ ሰብ፣ የሃይማኖት፣ የባህል፣ የፍልስፍና፣ የሥነ ምግባር፣ የሥነ ልቡና፣ የሥነ ማሕበረሰብ ወዘተ ባለሙያዎች ሊመክሩበት ይገባል። የነገሩን ሁለንተናዊ ጥቅም እና ተቃርኖ፣ ከሳይንሳዊ መንገድ ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰቡ ይሁነኝ በሎ ይዟቸው ከኖራቸው እሴቶች እና የሕይወት ትርጉም መበየኛ ፍልስፍናዎቹ አንጻር ሊጠኑ ይገባል። ቆዳ ላይ በተቀበረች ትንሽዬ ነገር የተቆጣጠርነውን ጽንስ በክኒን መልኩ በምትወሰድ ትንሽዬ ቅመም የምንወልደውን ልጅ ማንነት መበየናችን ከባድ አይሆንም። ቆዳ ላይ በምትቀበር ማይክሮ ችፕስ በርካታ ነገሮችን የሚያቀላጥፍ ከሆነ ያችው ትንሽዬ ችፕስ የሁለ ነገራችንን ምሥጢር ዘርግፋ ለሦስተኛ ወገን እንካችሁ ማለቷ አይቀርም። በኢንኩቤተር የተፈለፈሉ ጫጩቶች ዕድገት እና ምንነት በተፈጥሮ ከሚፈለፈሉት የተለዩ ከሆኑ ነገ ላይ በአንድ ማሽን የተፈለፈሉ ሥጋና ደም የተዋሃዳቸው ሰው መሰል ማሽኖች መፍጠሩ ቀላል ነው። የእነዚህ ማሽኖች ሕብረት ደግሞ ‘ማኅበረ-ሰብ’ ለማለት አያስደፍረንም። እናም በዘመነ ቴክኖሎጂ የሰው ልጆች ጉዞ ሰው የመሆን ወይስ ከሰውነት የመሸሽ?

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top