ታሪክ እና ባሕል

ሞራ፤ የኮንሶዎች ልዩ ስፍራ

በአገራችንም የሚገኙ ማኅበረሰቦች ያላቸው ቃላዊ፣ ቁሳዊና መንፈሳዊ ባህሎች እጅግ በርካታ መሆናቸው ኢትዮጵያን “የባህል ሙዚየም” የሚል ስያሜ አሰጥቷታል። የስያሜዋ ምክንያት ከሆኑት በቁጥር የበዙ ማኅበረሰቦች ውስጥ አንዱ ኮንሶ ነው።

የኮንሶ ማኅበረሰብ በደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በሰሜን ኦሞ ዞን በኮንሶ ይገኛል። ዞኑ በደቡብ የሰጋን ወንዝ፣ በምዕራብ የወይጦ ወንዝ፣ በደቡብ ምዕራብ የአሌ፣ በሰሜን የደራሼ፣ በሰሜን ምስራቅ የቡርጂ ወረዳዎች፣ በምስራቅ የቦረና ዞን ያዋስኑታል።

የኮንሶ ዞን ዋና ከተማ ካራት ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ 595 ኪ.ሜ ርቀት አለው። በኮንሶ ማኅበረሰብ ውስጥ ዘጠኝ ጎሳዎች (ካፋ) ሲገኙ፣ ከምስራቅ ኩሽቲክ የቋንቋ ቤተሰብ የሚመደበው የ“አፋኾንሶ” ቋንቋ ተናጋሪ ናቸው።

የኮንሶ ማኅበረሰብ የሚታወቅባቸው በርካታ ቃላዊ፣ ቁሳዊና መንፈሳዊ የባህል ሀብቶች አሉት። ከእነዚህም መካከል “ሞራ” አንዱ ነው። ሞራ ኮንሶዎች በየመንደሮቻቸው የሚሰሩት የህዝብ መሰብሰቢያ አዳራሽ ነው። የሞራው ምሰሶ (ቱዳ) ጽድ ሲሆን፣ ዙርያውን የሚከቡት ቋሚዎች ከላልታ ከሚባል እንጨት የተዋቀሩ ናቸው።

የአዳራሹም ጣሪያ ከሳር ይሰራል። ከስር ዙርያውን ክፍት ነው። በርም ሆነ መስኮት አይኖረውም። የኮንሶ ባህላዊ ቤት ከሀያ እስከ ሰላሳ ሰዎችን ማስተናገድ የሚያስችል ከእንጨት የተሰራ ቆጥ ይኖረዋል።

ፎቶ፤  ሞራ

የሞራ አዳራሽ ዙርያውን በድንጋይ ካብ የታጠረ ነው። በቅጽር ግቢው ውስጥም የኮንሶዎችን የትውልድ ሀረግ እንዲያሳዩ የተተከሉ ረጃጅም እንጨቶች (ኦላሂታ)፣ በተለያዩ ወቅቶች የተከሰቱ ልዩ ማኅበራዊ ገጠመኞችን የሚያሳዩ ትክል ድንጋዮች (ዲካ ዲሩማ)፣ እያንዳንዱ የኮንሶ ትውልድ ስልጣን ሲይዝ የሚያስቀምጣቸው ክብ ድንጋዮች (ኡሩማ)፣ ለመሰብሰቢያ የሚያገለግል ሰፊ ቦታ (ፓህፓህ)፣ ለጥላ እንዲሆኑ የተተከሉና ማንም የማይቆርጣቸው ዛፎች (ቆይራ ኮታ)፣ የእንሰሳት ማደሪያ (ቆቃታ)፣ የተለያዩ ቅርጻ ቅርጾች (ዋካ) እንዲሁም ሌሎች የማኅበረሰቡን ማንነት የሚያሳዩ በርካታ ቁሳዊ ባህሎች ያሉበት ነው።    

ሞራ የተለያዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሀይማኖታዊና ታሪካዊ ጉዳዮች የሚከወኑበት ቦታ በመሆኑ በማኅበረሰቡ ዘንድ ልዩ ስፍራ የሚሰጠው ቅርስ ነው። በሞራ ውስጥ ጠቀሜታቸው ከፍ ያለ በርካታ ማኅበራዊ ጉዳዮች ይፈጸማሉ። ከዚህ ውስጥ ዋነኛው የአካባቢው ማኅበረሰቦች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙርያ ተሰባስበው የሚያካሄዱት ውይይት ተጠቃሽ ነው።

በግለሰቦች፣ በቤተሰብ ወይም በጎሳዎች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶች እንዳይባባሱ ያስችላል። አለመግባባቶቹ ወደከፋ ማኅበራዊ ቀውስ እንዳያመሩ በአገር ሽማግሌዎች እርቅ ይከናወንበታል። የሐገር ሽማግሌዎች በቀየው ደንብ ሁለቱን ወገኖች ባህላዊውን የእርቅ መንገድ ተከትላው የቀደመ ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ ያደርጉበታል።

ሞራ የኮንሶ አዛውንቶች፣ ወጣቶች፣ ህጻናት… ማኅበረሰባዊውን ሀይማኖት (እምነት)፣ ልማድ እና የአስተዳደር ስርአት የሚማሩበት እና የሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት ነው። የተለያዩ ሀይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላት ይከናወኑበታል። ማኅበረሰቡ በአካባቢው በተከናወኑ አዳዲስ ጉዳዮች ዙርያ መረጃ የሚለዋወጥበት የመረጃ ማዕከልም ነው። በተጨማሪም የመዝናኛ ጨዋታዎችን ለመጫወት እና ጊዜ ለማሳለፍ የሚገለገሉበት የመዝናኛ ማዕከል ነው።

በየዕለቱ ከሀያ እስከ ሠላሳ የሚሆኑ ወጣት ወንዶች የሌሊት ጥበቃ ያደርጉለታል። ተራ ገብተው በወረፋ በሞራው ውስጥ ያድራሉ። የዚህ ምክንያት በአካባቢው ድንገተኛ የእሳት አደጋ ቢከሰት፣ ሰው ቢታመም ወይም አውሬ ቢገባ ፈጥነው በመድረስ የአካባቢውን ሰላም በንቃት መጠበቅ እንዲያስችላቸው ነው።

ሞራ የእንግዳ ማረፊያ ነው። ወደ አካባቢው በእንግድነት የሚመጣ ሰው ወንድ ከሆነ የሚስተናገደውና የሚተኛው በሞራ ውስጥ ነው። ነገር ግን ሴቶች፣ ህጻናትና አዛውንቶች በሞራ ውስጥ ማደር አይችሉም።

በኮንሶዎች ዘንድ በተደጋጋሚ ወሲባዊ ግንኙነት ማድረግ የወንዱን ጉልበትና ጥንካሬ ይቀንሰዋል ተብሎ ስለሚታሰብ ባለትዳር ወንዶች በርካታ ቀናትን በሞራ ውስጥ እንዲያድሩ ይደረጋል።

አንዲት ሴት በተደጋጋሚ ልጆች በመውለዷ ምክንያት፣ መውለድ የማቆም ውሳኔ ላይ ከደረሰች ጉዳይዋ በሞራ ይታያል። ሚስት በልጆቿ ቁጥር መብዛት ምክንያት ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ያለመውለድ እቅድ ኖሯት ባለቤቷ በሀሳቧ ባይስማማ ለሐገር ሽማግሌዎች ታመለክታለች። ሽማግሌዎቹ በሞራ ተሰብስበው ችግሩን ለመፍታት ይጥራሉ።

የሀገር ሽማማሌዎቹ ባልየው ሴቲቱ እስከወሰነችው ዓመት ድረስ ውለጅልኝ እንዳይላት ያስጠነቅቁታል። ሚስቱን እንዳያስቸግር በማለትም የተፈረደውን ዓመት ያህል ሞራ ውስጥ እንዲያድር ይደረጋል። እዚህ ጋር ሞራ ባሕላዊ የወሊድ መቆጣጠሪያ ሆኖ እንደሚያገለግልም እንመለከታለን።  

ከእነዚህም በተጨማሪ ሞራ በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋት የሚከናወኑ ስራዎች ይተገበሩበታል። ለምሳሌ፤- በደርግ ስርዓት ወቅት የመሰረተ ትምህርት ይካሄድ የነበረው በዚሁ ስፍራ ነበር። በአሁኑ ወቅትም ስለጤና እና የአካባቢ አጠባበቅ ስልጠናዎች ይሠጥበታል።

ኮንሶዎች ካላቸው በርካታ ሀገር በቀል ባህሎች መካከል አንዱ የሆነው ሞራ ለማኅበረሰቡ በርካታ ጠቀሜታዎች በመስጠት ላይ ያለ ስፍራ ከመሆኑም በላይ የማኅበረሰቡን ፍልስፍና፣ እምነት፣ ዓለማዊ ዕይታ (worldview)፣ ታሪክ፣ ስርዓት ወዘተ… የሚያሳይ ልዩ ባህላዊ የአገራችን ቅርስ ነው። ይህንንም ልዩ የአገር ባህላዊ ሀብት በማጥናትና በመጠበቅ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል።   

1 Comment

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top