ጣዕሞት

ሙዚቃዊ ቴአትር

በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ እንደተጻፈ የሚታመነው ታሪካዊ ልብ ወለድ ወደ ሙዚቃዊ ቲያትር መቀየሩ ተሰምቷል። በ1977 ዓ.ም. ተስፋዬ የኋላሸት በሚል የብዕር ስም በትግርኛ ቋንቋ የተጻፈው ልብ ወለድ “ምንኩሕኳሕ ዘይፍለዮ ማዕፆ” (መንኳኳት የማይለየው በር) የሚል ርዕስ ያለው ነው፡፡

የፊውዳሉን የአገዛዝ ዘመን እና የማኅበረሰቡን የጭቆና ቀንበር እና ግፍ እንደሚያሳይም ተነግሮለታል። ይህንን ባለ ስምንት ምዕራፎች ታሪካዊ ልቦለድ፤ ደራሲ ዘርአጽዮን አርአያ ወደ ተውኔት ቀይሮታል። ምንም እንኳ ለመጋቢት 14 በሐገር ፍቅር ቲያትር ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ለተመልካች ዕይታ ይበቃል ቢባልም፤ በአሁን ሰዓት ዓለማችንን ከጫፍ እስከጫፍ እያናወጣት ያለው የኮረና ቫይረስ ምክንያት በማድረግ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ተደርጓል፡፡ ቲያትሩ 38 ተዋንያን ተሳትፈውበታል።

 አቶ መለስ “ተስፋዬ የኋላሸት” የሚለውን የብዕር ስም የተጠቀሙት የኢትዮጵያ ተስፋ ከፊውዳሉ የተላቀቀው የወደፊቱ ትውልድ ነው የሚል ዕምነታቸውን ለማንጸባረቅ እንደሆነም ሰምተናል፡፡ አዲሱ ተውኔት ያለፈው መጋቢት ወር ላይ መርሃግብር ተይዞለት እንደነበር ቢታወቅም ዓለማችን ከዚህ አስከፊ በሽታ እንደተላቀቀች፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች እና ከ30 በላይ በሚሆኑ የዓለም ሀገራት ለተመልካች ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።

ክስታንኛ መዝገበ ቃላት

ክስታንኛ፣ አማርኛ እና እንግሊዘኛ መዝገበ ቃላት መዘጋጀቱ ተሰማ። በ300 ብር ለገበያ የቀረበው አዲሱ መዝገበ ቃላት የዛሬው እና የመጪው ትውልድ ከታሪክ እና ከባሕሉ ጋር ራሱን ማዛመድ እንዲችል እድል እንደሚፈጥር ታምኖበታል። ለቋንቋው እድገት አንድ እርምጃ መሆኑ የተነገረለት መዝገበ ቃላት ተጠቃሚው በእለት ተእለት ሕይወቱ እንዲገለገልበጽ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው።

 መዝገበ ቃላቱ የተሰናዳው በክስታኔ ጉራጌ ሕዝብ የልማት ማኅበር እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባሕሎች አካዳሚ ትብብር መሆኑ ታውቋል።

የሰዋሰው መጽሐፍ

“ክመንታ ላንዃ” ወይም ቅማንትኛ ሰዋስው መጽሐፍ ለንባብ በቃ። አዲሱ መጽሐፍ ቀድሞ ለሕትመት የበቃው የቅማንትኛ-አማርኛ-እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ተከታይ ነው። አዲሱ የሰዋሰው መጽሐፍ ጥልቅ ጥናት ተደርጎበት እንደተዘጋጀ ተነግሯል። ከቀደምት ሥራዎች በመነሳት ነባራዊውን የቋንቋ አጠቃቀም ከግምት በማስገባት የተዘጋጀው የሰዋሰው መጽሐፍ

የአፕሊያርድ (1975)፣ የሮዚኒ (1912) እና የሬይኒሽ (1885)፣ የተሰኙት ሥራዎች ለዝግጅቱ ጥልቅ አበርክቶ ነበራቸው።

 መጽሐፉ ሁሉም የክመንታ ቋንቋ ዘዬዎች ማለትም የመረባ፣ የጭልጋ፣ የቋራ፣ የደምቢያ፣ የፈላሽኛ እና ካይልኛ ዘዬዎች ተካተውበታል።

የመጽሐፉ ዋነኛ ትኩረት የክመንታ ቋንቋ ሰዋስው ላይ ይሁን እንጂ ወደ ቋንቋ ጥናቱ ለመግባት የሚያስችሉ ታሪካዊ ዳራዎች የመጽሐፉ አንድ አካል ሆነዋል።

 የክመንታ ቋንቋ ታሪክ፣ የክመንታ ቋንቋ ለኢትዮጵያ ያለው አበርክቶ፣ በክመንታ ቋንቋ ላይ የተካሄዱ ቀደምት ጥናቶች እና የክመንታ ቋንቋ መፃኢ ዕድሎችና ተግዳሮቶች የሚሉ ጉዳዮች በመጽሐፉ የመጀመሪያው ምእራፍ ሥር ተካተው ቀርበዋል።

በሰዋስዋዊው ክፍል ደግሞ ሥነ ድምጾችን፣ ስሞችን፣ ቅጽሎችን፣ ተውላጠ ስሞችን፣ ግሶችንና፣ የግስ ሥልቶችን፣ ተውሳከ ግሶችን፣ መስተዋድዶችን ወይም ድህረ-ቅጥያዎችን፣ መስተፃምሮችን፣ ቃለ አጋኖዎችን፣ ሐረጎችን፣ አረፍተ ነገሮችን እንዲሁም ሥነ ጽሑፎችን አካቶ የያዘ ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top