ታዛ ወግ

መስቀል አደባባይ

ባንኜ ነው ከእንቅልፌ የተነሳሁት፡፡ ያለ ወትሮ የቴሌቪዥኔን መስኮት ከፍቼ ዜና እስኪጀምር ድረስ እዛው ጣቢያ ላይ አድርጌ ማየቴን ቀጠልኩ፤ ከአፍታ ቆይታ በኋላ ግን ዜና አንባቢው ፊት ለፊቴ ግስጥ ብሎ ግንባሩን የቲቪ ማስቀመጫ እስኪገጨው ድረስ ሠላምታ ሰጠኝ፤ ከዛ በኋላ ግን ብጠብቅ፣ ብጠብቅ፣ እንቅስቃሴ እንጂ ምንም ድምፅ አልነበረም፡፡ ይሔኔ እኮ ቅድም ሰላምታ ሲሰጠኝ የኒክ ማይክ ገመዱን በጥሷት ይሆናል ብዬ ሳኩበት፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ ነበር እጁን ከግራ ወደ ቀኝ እያወዛወዘ ሲሰናበተኝ የምልክት ዜና አንባቢ መሆኑን የተረዳሁት።

       ስቄ ሳልጨርስ ያሳቀቀኝን አምላክ አመስግኜ፤ ቤቴን ለቅቄ ቁልቁል ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደኝን መንገድ ያዝኩ፡፡ መስቀል አደባባይ ደመራን እና መደመርን ብለው እንዲሁም ተደናብረው በሚመጡ ሰዎች የተሞላች ናት፡፡

     መስቀል አደባባይ አያድርገውና ድንገት እንኳን ተፈጥሮ አስገድዶህ ብታስነጥስ፤ በፌደራል ግልምጫ የሚበተነው ወጣት ሀጥሴ…ሀጥሴ…እያለ ይከተልሀል፡፡

መስቀል አደባባይ ላይ “ሆ” ፊደል ታዋቂና የብዙ ወጣትን ህይወት የቀጠፈች ፊደል ናት “ሆ” ፊደልን ብሎ የወጣን ህዝብ ደግሞ የፌደራል ቁጣና ዛቻ ሳይሆን በ “ዷ” ፊደል ብቻ ነው የሚበተነው በእርግጥ እነ “ጦ” እነ “ቷ” መጠነኛ ሰልፎችን እንደሚበትኑ እረግጥ ነው።

     አያድርገውና መስቀል አደባባይ የቀትር ፀሀይ አማሮህ እጅህን ግንባርህ ላይ ብታደርግ፣ አራት ሚሊዮን ህዝብ ከኋላ እጁን ግንባሩ ላይ አድርጎ ወንድሜ…ወንድሜ… የምን ሰልፍ ነው? ብሎ ይጠይቅሀል፡፡ መስቀል አደባባይ ላይ በፊት በአስለቃሽ ጭስ የሚበተን ወጣት ዘንድሮ የለም፡፡ ይልቁኑ አስለቃሽ ጭሱን ለምዶት የለቅሶቤት ማላቀሻ አድርጎታል፡፡ እንደውም ከ70% በላይ የሚሆነው ወጣት በአስለቃሽ ጭስ ሱስ የተጠቃ እንደሆነ ደርሼበታለሁ፡፡ አስለቃሽ ጭስ አንዳንድ የፊልም ባለሙያዎች ለሲኒማ አውቶግራፊ ጥበብ እንደሚጠቀሙበት ሳናውቅ የቀረን አይመስለኝም

 ይሔኔ ነው እንግዲህ “ዷ” የምትመጣው “ዷ” ፊደል ስትመጣ ከደቂቃዎች በፊት መስቀል አደባባይ አራት ሚሊዮን ህዝብ የያዘች ቦታ ሳይሆን እኩለ ለሊት ነው የሚመስለው፡፡ አሁን አሁንማ እንግዳ ሲመጣም እንግዳ ሲሔድም አቀባበል እና አሸኛኘት የምናደርገው መስቀል አደባባይ መሆኑ መስቀል አደባባይ የኤርፖርትንም ስራ በተጎዳኝ ደርባ እንደሚሰራ ሳይ ለመስቀል አደባባይ ክፉኛ አዘንኩ፡፡

ወጣቱ ቀን ላይ ከመንግሥት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ የገነባውን ህንፃ፤ ከሰአት ከእንትን ፖርቲ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ሲንደው ያመሻል፡፡ ሲለው ደግሞ ከዛሬ ጀምሮ ሰላምን እናሰፍናለን ብሎ ቀን ላይ መሀላ የፈፀመ ወጣት፤ ማታ የፌዝ ቡክ ገ’ፁ ላይ “የእንትን ብሔርን ውጋው” “የእንትን ብሔርን በለው” የሚል መግለጫ ይለቃል፡፡ ይህንን ያየሁት እኔ ወጣቱ ሁለት አምላክ የሰራው እስኪመስለኝ እገረማለሁ። በቀደም ለታ የሰፈሬን ወጣቶች ሰብስቤ ለምን? በታሪክ አንማርም?! ለምን?! ባጣናቸው ሰዎች አይበቃም?! ለምን!? በ”ዷ” ፊደል እንተናነቃለን እባካችሁ ሰላማዊ ሰልፍ ይቁም! ከማለቴ ‘ይቁም!’ ብለው መስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ ሲወጡ ሳይ ተስፋ ቆረጥኩ፡፡ ሰዉ.. የጋራ ጥያቄ አልቆበት በግል ሰላማዊ ሰልፍ ያካሒድ ጀምሯል፡፡ ፖሊሱ! ስራ ቀዝቅዟል ብሎ ሰላማዊ ሰልፍ ይወጣል፣ መንግሥት ታስሮ እንዲገባ ይሁን እንጃ፡፡ ሀኪሙ! ስራ ጠፍቷል ብሎ ሰላማዊ ሰልፍ ይወጣል፣ መንግሥት ታሞ እንዲገባ ይሁን እንጃ፡፡

 አንዱ በቀደም ለት መስቀል አደባባይ አንዲህ የሚል መፈክር ይዞ ዐየሁት!

“እኔ የሬሳ ሳጥን በመሸጥ ነው የምተዳደረው፡፡ ካለፉት አንድ ዓመት በኋላ ግን ምንም ዓይነት ስራ የለም እና መንግሥት በሙያዬ ድጋፍ ያድርግልኝ!”

ይላል ለዚህ ሰው መንግሥት በሙያው በምን መልኩ ነው ድጋፍ የሚያደርግለት፤ ሰው በመግደል? ጥያቄአችን ቅጥ ያጣ እየሆነ ነው። አስፋልት እንላለን መኪና ግን የለም፡፡ የድግስ ቤት ጭልፋ ይዘህ የአንተ ድስት ውስጥ ለማስገባት መታገልህን እስካላቆምክ ድረስ እውነቴን ነው ምልህ ጊዜህን አትጠቀምበትም!!

አንዳንዴ “ይሔ ትውልድ ወዴት እየሔደ ነው?” እላለሁ፡፡ ለነገሩ ከመስቀል አደባባይ ውጪ ምን መሔጃ አለው? ሰዉ የቤቱንም ጥያቄ መስቀል አደባባይ ይዞ ከወጣ ሰነበተ፡፡ በቀደም አንድ ራስታ የነበረ ወጣት የተቆረጠ ድሬድ ፀጉሩን በእጁ ይዞ እጁን ከላይ ወደታች እየዘረጋ ፀጉሬ ተቆርጦልና መንግሥት ያስተክልልኝ!!… መንግሥት ያስተክልሰኝ!! ሲል ሰምቼው ‘ስማ የኔ ወንድም የአንተ ፀጉር የመለስ ፋውንዴሽን አትክልት ነው እንዴ መንግሥት ሚያስተክልልህ’ ልለው አልኩና ፖለቲካ ስለማሎድ ብቻ ተውኩት፡፡ ትቼው መንገዴን ቀጠልኩ፡፡ ከቲኒሽ ርቀት በኋላ ግን አንዲት ሴት መንግሥት እና ዶክተር ቀርቶ ሙሉ በሬ ለጠንቆይ ብትሰጠው እማይፈታውን ቅጥልጥል ጽሑፍ ይዛ የወር አበባዬ ስለቀረ መንግሥት ያስመልስልኝ…!! ያስመልስልኝ…!! ስትል ሰምቼ “ማነሽ የኔ እህት የአንቺ የወር አበባ አክቲቪስት ነው እንዴ  መንግስት ይቅርታ ጠይቆ ሚያስመልስልሽ” ልላት አልኩና ፖለቲካ ስለማሎድ ትቻት ሔድኩኝ!

እውነቴን ነው ምለው’ እኔ ግን መስቀል አደባባይን ቢያደርገኝ ይኼ ሁሉ ደም ሲፈስብኝ ከማይ አክሱም ሔጄ ነበር ምደበቀው’ የሚል ሀሳቤን እያብላላሁ ወደ ቤቴ የሚመልሰኝን አውቶቢስ ከተሳፈርኩ በኋላ አንድ ነገር አሰብኩ በዚህ ሰዓት መንግሥት ራሱ ሰላማዊ ሰልፍ ቢወጣ ደስተኛ አይሆንም? እኛ እንደሆነ ድልድዩን የገነባነው በእግራችን ልክ ነው! ለዚህ እኮ ነው ከትውልድ ጋር መተላለፊያ መንገድ ያጣነው፡፡ መንገዱ ቀላል ነው ሚቸግረው መራመዱ ነው፡፡ ምክንያቱም ሦስት ክንድ ስትራመድ የአንተን መሬት ትጨርሳለህ ስለዚህ ድልድዩን አስፍተን እንገንባ ከትውልድ ጋር እንተላለፍ ‘ሆ’ ብለን ከመውጣታችን በፊት “ሀ” ብለን መሰረተ ትምህርት እንማር ከ’ዷ’ ፊደል ይልቅ ‘ለዱአ’ እንምበርከክ በገዳይ ዘመን ሞች ሆነን አንገኝ!!!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top