ጥበብ በታሪክ ገፅ

ለባርነት የተሸጡት ኢትዮጵያዊ ጀኔራል

የአብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባል ከ(1696-1781) አጭር ታሪክ

መግቢያ፡- አብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባል (በእንግሊዝኛ፣ በላቲንኛ፣ በጣሊያንኛና በፈረንሳይኛ ‹ሀኒባል›፣ በአረብኛ ‹አኒባል› እንዲሁም ‹አብርሃም ፔትሮቭ›) ከ1696 እስከ ግንቦት14 ቀን 1781 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ) በሕይወት የነበሩ፣ በሕፃንነት እድሜ በድንገት ታፍነው በባርነት ተሸጠው በምፅዋ ወደብ በኩል ወደ ኦቶማን ቱርክ ዋና ከተማ፣ ወደ ቆንስጣንጦኖጵል ወይም ወደ ዛሬዋ ኢስታንቡል ተወሰዱ። ከዚያም እንደገና በምስጢር ታፍነው ወይም ተሰርቀው ወደ ፒትስቡርግ – ሞስኮ – ተወሰዱ። ከተወሰዱ በኋላ ዕድላቸው ተቃንቶ የባርነትን ቀንበር በማውለቅ ነፃነት አግኝተው በታላቁ ቀዳማዊ ዓፄ ጴጥሮስ ቤተ-መንግሥት ውስጥ አድጉ። በፈረንሳይ ውስጥ ነፃ የውትድርና፣ የሂሳብና የጂአሜትሪ ትምህርት ከጨረሱ በኋላ ተመልሰው የታላቋ ሩሲያ ወታደራዊ መሃንዲስ፣ ሙሉ ጀኔራል እና ከዚያም አልፎ ለመሥፍንነት ደረጃ (nobleman) የበቁ ምናልባትም ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ጥቁር ናቸው። አብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባል ታላቁ ቀዳማዊ ዓፄ ጴጥሮስ ከሞተ በኋላ፤ የሩሲያ የዛሩ መንግሥት ንግሥተ-ንግሥት የኤልሳቤጥ ቀኝ እጅ፣ አድራጊ ፈጣሪ ቢትወደድ ሆነው በታማኝነት ያገለገሉ ታላቅና የተከበሩ ባለሥልጣን ተደርገው በታሪክ መዛግብት ይወሳሉ።

ጋኒባል የሜጀር ጀኔራል ፒትር አባትና፤ የሩሲያን ዘመናዊ ሥነ-ጽሑፍ መሠረት ከጣሉት ሊቃውንት መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው በአውሮፓ የዘረኝነት አስተሳሰብ በሰፈነበት ጨለማ ዘመን እኩልነትንና ሰብአዊነትን እያቀነቀነ፤ ይልቁንም በአፍሪካዊነቱ በአጠቃላይም በጥቁርነቱ እጅግ ይኮራ የነበረው የምጡቁ ባለቅኔ የአሌክዛንደር ሰርጌቪች ፑሽኪን ቅድመ-አያት ናቸው። ይህ ጽሑፍም ለአንባብያን ይዞ የቀረበው በእኚህ በሕፃንነት ዕድሜያቸው የባርነት ቀንበር  የተሸከሙ ነገር ግን ‹የሕይወት ዕጣ-ፈንታ መዘውር› አቅጣጫውን ቀይሮ በዘመኑ የዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪ ታላቅ ሰው ለመሆን  የበቁትን ኢትዮጵያዊ ጀኔራል ውጣ ውረድ የተሞላበት፣ ስኬታማና አስደናቂ ታሪክ ላይ በማተኮር ነው።

ብዙዎቹ ጸሐፍት የተጠቀሙበት የጀኔራል አብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባል ትውፊታዊ ምስል

ጀኔራል ጋኒባል ለባርነት ከመዳረጋቸው በፊት በቤተሰባቸው የተሰጣቸው ስም “አብርሃም” የሚል ነበር። “ጋኒባል” የሚለው መጠሪያ “ሀኒባል” ከሚለው ታሪካዊ ጀግና ስም የተወሰደ ሲሆን የተሰጣቸውም በባርነት ከተሸጡ ከዓመታት በኋላ ነው። በአጭሩ ‹ሀኒባል› የሚለው ስም ታሪካዊ መነሻ አለው። ይህም ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ247 – 183ዓ.ዓ. “ሀኒባል ባራቅ” (መብረቅ) በሚል ስም ይጠራ የነበረ፣ በሰሜን ምዕራብ አፍሪካ “ካርቴጅ” ተብሎ በታሪክ የሚጠቀሰው (የዛሬዋ ቱኒዝያ) ጥንታዊ መንግሥት ወደር የሌለው የጦር ጀኔራልን የጀግንነት ገድል የሚጠቅስ ሆኖ ይገኛል። ታሪክ እንደሚያወሳው ገድለኛው ጀኔራል ሀኒባል ባራቅ ከሰሜን ምዕራብ አፍሪካ ተነስቶ ከመቶ ሺህ ጦር በላይ በመምራት ሮምን ወግቷል። ከዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ በምዕራቡ ዓለምና በመላው አውሮፓ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ሥር ከሰደደው የዘረኝነት አስተሳሰብ በመነጨ የ‹ጥቁር ዘር› እንደሰው በማይቆጠርበትና ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ይፈፀምበት በነበረበት በዚያ ጨለማ ዘመን የባርነት ሰለባ የሆኑት አብርሃም የጥንታዊው ባለ ገድል ጀግና የ‹ሀኒባል› ስም ለምን ምክንያትና በማን ሊሰጣቸው ቻለ? የሚለው ይሆናል።

የጀኔራል አብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባል ታሪክ ባለፉት ሦስት ምዕተ-ዓመታት ውስጥ ከዘረኝነት ርዕዮተ-ዓለምና አስከፊ ድርጊት ጋር በተያያዘ የታሪክ፣ የሥነ-ሰብዕና የሥነ-ልቦና ምሁራንንና ተመራማሪዎችን፣ የፀሐፍትንና የከያንያንን ትኩረት ያለ ማቋረጥ በእጅጉ ስቦ ቆይቷል፤ ዛሬም ቀጥሎ ይገኛል። በመሆኑም በጀኔራል ፔትሮቪች ጋኒባል ሥራዎችና የሕይወት ታሪክ ላይ በተለያዩ ቋንቋዎች የተፃፉ ብዛት ያላቸው መረጃዎች ይገኛሉ። ጋኒባል ኢትዮጵያዊ ቢሆኑም በሰፊው በዓለማችን የተናኘው ድንቅ ታሪካቸው ግን እስከአሁን በሃገራችን ቋንቋዎች ተጽፎ ወይም ተተርጉሞ ለመነበብ አልበቃም። አልተነገረም። ለሀገራችን ለሚጠቅም የዲፕሎማሲ ግንነኙነት አልዋለም። ከዚህ ድክመት የተነሳም በቅርቡ ‹የታሪክ ሽሚያ› ሊሰኝ የሚችል ውዝግብ እየተፈጠረ ይገኛል።

በመጨረሻም ይህ ጽሑፍ በዚህ መልክ ተጠናቅሮ ለአንባብያን የቀረበው፡-

  1. ራሱ ፑሽኪን በሕይወት እያለ በአያቱ ስብዕና፣ ቅርስነት ባላቸው ሥራዎቻቸው፣ እነዚህ ሥራዎቻቸውም በዘመኑ አስተሳሰብ ላይ ያስከተሏቸውን ተፅዕኖዎች በሚመለከት በፃፋቸውና ባሳተማቸው ወይም ከሞተ በኋላ ለመነበብ በበቁ፣ በተጨማሪም በየጊዜው ለአንባብያን በጋዜጦችና በመጽሔቶች ባቀርባቸው መጣጥፎች
  2.  በጀኔራል ጋኒባል የሕይወት ታሪክ ላይ በማተኮር በተፃፉ መረጃዎች
  3. በተከታታይ በምሁራን በተጠኑ ሥራዎች
  4. በዘመኑ ጀኔራል ጋኒባልን በቅርብ በሚያውቁ ሰዎች(ወዳጆች) በተፃፉ እንደ ህያው ምስክር በሚጠቀሱ ደብዳቤዎችና ማስታዎሻዎች
  5. በጊዜው በተመዘገቡ ኦፊሴላዊ ሰነዶችና መዛግብትና በመሳሰሉ ምንጮች ላይ ተመርኩዞ ነው።

የጀኔራል አብርሃም ፔትሮቪች ጋኒባል የልጅነት ታሪክ

በዚህ ንዑስ ርዕስ ኢትዮጵያ ውስጥ አብርሃም የተወለዱት የት ነበር? ለባርነት የተዳረጉት በማንና መቼ ነበር? ከዚያስ ወዴት ተወሰዱ? ምን ገጠማቸው? የልጅነት ታሪካቸው ምን ይመስላል? የሚለውን እንመለከታለን። አብርሃም የተወለዱት (እ.ኤ.አ.) በ1696 ነበር። የተወለዱበት ሀገር ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን ልዩ ሥፍራው “ምደሪ-ባህር” ተብሎ ይጠራ በነበረው ክፍለ-ግዛት (በዛሬዋ ኤርትራ)፣ በሰሜን መረብ ወንዝ አካባቢ በሚገኝ ልዩ ስሙ “ሎጎ”“ላጎ”“ሎጎ-ሳርዳ” እንዲሁም “ሎጎ-ጨዋ” በተሰኘና በይበልጥ ክርስቲያን ትግሬዎች ሠፍረው የሚኖሩበት ቦታ መሆኑን የሕይወት ታሪኮቻቸው፣ በርካታ የምርምርና የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች በተጨማሪም መልክዓ-ምድራዊ ካርታዎች ያረጋግጣሉ።[1] ታሪካዊ ሰነዶቹ እንደሚጠቁሙት “አብርሃም” ለባርነት የተዳረጉት ገና የ7 ዓመት ከስድስት ወር ዕድሜ ሲደርሱ እንደነበርና ቤተሰቦቻቸው የባላባት ወይም የመሳፍንትና የአገሩ አስተዳዳሪዎች እንደነበሩ መረጃዎቹ ጨምረው ይገልፃሉ። ቱርኮች አብርሃምን ካገኙበት ጊዜ ጀምሮ ‹ኢብራሂም› በሚል ስም ይጠሯቸው ነበር።

አንዳንድ ምንጮች እንደሚገልጹት አብርሃም የባርነት ቀንበር ለመሸከም የበቁት የ9 ዓመት ዕድሜ ከደረሰ ትልቅ ወንድማቸውና “ላጋን” ከምትባል ትልቅ እህታቸው ጋር ነበር። ከእነሱ ጋር አብሮ የታፈነ ሌላ አንድ የአካባቢው ሕፃንም ነበረ። ሕፃናቱን ከቀያቸው በድንገት አፍነው የባርነት ቀንበር የጫኑባቸው በዘመኑ ሰሜን አፍሪካንና ምድረ አረብያን ጨምሮ በምሥራቅ፣ በደቡባዊና በማዕከላዊ አውሮፓ የግዛት መሥፋፋት ዘመቻ በማካሄድ ላይ የነበረው የኦቶማን ቱርክ ግዛት፣ ምናልባትም በአገሬው ፈንጋይ ሽፍቶች የታገዙ አልፎ ሂያጅ ወታደሮች ወይም የባሪያ ነጋዴዎች መሆናቸውን ይጠቁማሉ።

ቱርኮቹ እነአብርሃምን ወደ ቆንስጣንጢኖጵል የወሰዷቸው በምፅዋ ወደብ በኩል በመርከብ በመጫን ነበር። እነአብርሃም የወደፊት ዕጣቸው ምን እንደሚሆንና የመጨረሻ መድረሻቸው የት እንደሚሆን ለማወቅ አይችሉም። በመርከብ ተጭነው በጉዞ ላይ ሳሉ እህቲቱ “ላጋን” ተስፋ በመቁረጥ ከባርነት ሞትን በመምረጥ ቀይ ባህር ዘላ በመግባት ሰጥማ ሕይወቷን አጥታ የዓሣ ራት ሆና ቀረች። እህቲቱ በዚህ አኳኋን ሕይወቷን እንዳጣች ነገሩ ‹ከእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ› እንዲሉ ቱርኮቹ ሕፃኑን አብርሃም ሳይቀር እጃቸውን ጠምዝዘው የኋሊት አሰሯቸው። የእህቲቱ አሟሟት ቱርኮቹን ዕቃ የጠፋ አልመሰላቸውም። በአንፃሩ ግን የእነአብርሃምን ስሜት የሚያኮማትር፣ እስከመቼውም በህሊናቸው ሲያቃጭል የሚኖር፣ ለዕድሜ ልክ ፀፀት የሚዳርግ ዘግናኝ ድርጊት ነበር። እናም እነአብርሃም አንገታቸውን ደፍተው ሀዘናቸውን ውጠው ወደማያውቁት ዓለም ጎዟቸውን ከመቀጠል ሌላ ምርጫ አልነበራቸውም። <ቴሌቶቫ> እንደፃፈችው፡-

ከታፈኑት ልጆች መካከል አረቦች “ኢብራሂም” በሚል ስም ይጠሩት የነበረ ልክ 8 ዓመት የሚሆነው አንድ ትንሽ ልጅ ይገኝ ነበር። እሱም ከሌሎች ልጆች ጋር ለቱርኮች ተሸጦ በዚያው በተሸጠበት ዓመት ወደ ቆንስጣንጢኖጵል ተወሰደ። ልጁ ከታፈነበት ቀዬ እስከ ምፅዋ የተጓዘው ከእግረኛው መንገደኛ ጋር ነበር። ከዚያ በምፅዋ በኩል በመርከብ ተጭኖ ከሄደ በኋላ ወደ ወደ ቆንስጣንጢኖጵል (ኢስታምቡል) ተወሰደ።

በዚህ ሁኔታ ጎዟቸውን ቀጥለው ቆንስጣንጢኖጵል እንደረሱ ቱርኮቹ እነ አብርሃምን (እኤአ) ከ1703 እስከ 1730 ዓ. ም የኦቶማን ቱርክን ሱልጣኔት በማጠቃለል በበላይነት ይገዛ ለነበረው ለሱልጣን አህመድ ሳልሳዊ በስጦታ አስረከቡት። ከዚያም እነ አብርሃምን አንድ ሰሊም” በሚባል ስግብግብ ሱልጣን ቁጥጥር ሥር ይተዳደር በነበረ “የባሪያ ጉሮኖ” ውስጥ ለጊዜው እንዲቆዩ ተደረገ።

ምስል፡-ሱልጣን አህመድ ሣልሳዊ

በተለይም የሕይወት ገጠመኛቸውንና ትውስታቸውን መሠረት አድርጎ በጀርመንኛ ቋንቋ እንደተፃፈ በብዙዎቹ ጸሐፍት በሚጠቀሰው በጀኔራል ጋኒባል የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ውስጥ “እነ አብርሃም ከመሳፍንት ቤተሰቦች የተወለዱ ሲሆኑ ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ ለኦቶማን ቱርክ ሱልጣኔት ሙስሊሞች ሁሉ የበላይ ሱልጣን ተላልፈው የተሰጡበት ምክንያት አባቶቻቸው ፀረ-ቱርክ ድርጊት መፈፀም ካላቆሙና ይህን የመሰለውን ‹አጉል ጠባይ› ካልተው ልጆቹ እንዲገደሉ ወይም በባርነት እንዲሸጡ የሚል መያዦነትና የበቀል ዛቻና ማስፈራሪያ የተሞላበት ዓላማ እንደነበረው እንገነዘባለን።                                                           

ከታሪክ እንደምንረዳው የኢትዮጵያ ነገሥታት የኦቶማን ቱርክ በምሥራቅና በሰሜን አፍሪካ ጭምር ለዘመናት ሲያራምደው የቆየውን የመስፋፋት ህልም ከማክሸፋቸው አንፃር ቱርኮች ካደረባቸው ቁጭት የተነሳ በሕፃናቱ ላይ ይህን የመሰለውን ዛቻ የተሞላበት ማስፈራሪያ ማድረጋቸው ተቀባይነት ያለው ይመስላል።

የዕጣ መዘውር፡- እንደ ገና አፈና

እነአብርሃም በቆንስጣንጢኖጵል የባሪያ ጉሮኖ ውስጥ ለአንድ ዓመት ያህል ነበር የቆዩት። ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ግን (እ.ኤ.አ.) በ1704ዓ.ም. ከትልቅ ወንድሙና ከእነሱ ጋር አብሮ ታፍኖ የተወሰደው ሦስተኛው ልጅ እንደገና ሌላ አፈና እንደገጠማቸው አያሌ መረጃዎች ይገልፃሉ። በመሆኑም ቀጥሎ በእነ አብርሃም ላይ በቆንስጣንጢኖጵል የባሪያ ጉሮኖ አፈና የፈመው ማን ነበር? እንዴት? ከታፈኑ በኋላስ ወዴትና እንዴት ተወሰዱ? በሚሉት ነጥቦች ላይ በማተኮር እንመልከት።

በአንድ በኩል ጥቂት ጸሐፍት “ሕፃናቱ የተወሰዱት ለኦቶማን ቱርክ ጠቅላይ ሱልጣን ለአህመድ ሳልሳዊ ‹ክፍያ ተፈጽሞ› ነው” በሚል የፃፉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ “የቱርኩ ጠቅላይ ሱልጣን አህመድ ሳልሳዊ ሕፃናቱን ‹ታላቁ ቀዳማዊ ጴጥሮስ› ተብሎ ለሚጠቀሰው የሩሲያው ገናና ዛሩ (ንጉሥ) “በስጦታ መልክ አበረከተለት” የሚል መላምት የሰጡ ይገኛሉ። ይሁንና እነዚህ መላምቶች በዘመኑ በኦቶማን ቱርክና በሩሲያ መንግሥታት መካከል በነበረው የግዛት መስፋፋት ፍላጎትና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ምክንያት ከተፈጠሩት ከፍተኛ ቅራኔዎች አንፃር ሲታዩ ትክክል ናቸው ለማለት አስቸጋሪ ይሆናል። ይህን የሚያሰኘውም የኦቶማን ቱርክ ኢምፓየር በምሥራቅ አውሮፓ ጭምር ያደርግ በነበረው የመስፋፋት እርምጃ ከሩሲያ መንግሥት ጋር ከፍተኛ ውጥረትና ግጭት ውስጥ የገባበት፣ በኋላም አዞቭ ላይ የቱርክ ጦር በሩሲያና በተባበሩት የጦር ኃይል የተደመሰሰበት ጊዜ ስለነበረ ነው። በመሆኑም “ሳልሳዊ ሱልጣን አህመድ ‹ለታላቁ ቀዳማዊ ፔጥሮስ ሕፃናቱን በስጦታ አበረከተለት›” የሚለውን አስተያየት ተአማኒ ሊያደርገው አይችልም።

ከዚህ ሌላ ብዙዎቹ መረጃዎች የሚያረጋግጡት ከላይ ከተሰጡት ሀሳቦች ጋር የሚቃረኑ ሆነው እናገኛለን። ይህም እነአብርሃም ለአንድ ዓመት ያህል ከቆዩበት የባሪያ ጉሮኖ የተወሰዱት ምስጢር በተሞላበት ሁኔታ ‹ታፍነው› ወይም ‹ተሰርቀው› የመሆኑ ጉዳይ ነው። ይህንንም ብዙዎቹ ጸሐፍት አሥፍረውት ይገኛል። ለምሳሌ ናታሊያ ቴሌቶቫ፡- “የልጁ (የአብርሃም) ሕይዎት በቱርክ መንግሥት ሉኣላዊ ሱልጣን ሳልሳዊ አህመድ የባሪያ ማጎሪያ መኖር እንደጀመረ እንደገና ሌላ አፈና ተደርጎበት ወደ ሰሜን አቅጣጫ ወደ ሞስኮ ለመጓዝ ተገደደ።”  በማለት አሥፍራዋለች። አልበርት ፓሪም እንደዚሁ፡- “ጥቁሩ ኢትዮጵያዊ ባሪያ አብርሃም ፔትሮቪች ሀኒባል ወደ ኮንስታንቲኖጵል ከመጣ በኋላ በሩሲያ ዲፕሎማቶች ተሰረቆ ተወሰደ” ሲል ጽፎታል።

እነአብርሃም የታፈኑት ወይም የተሰረቁትም በጊዜው በቆንስጣንጢኖጵል ተመድበው ይሠሩ በነበሩ የሩሲያ ዲፕሎማቶች አቀነባባሪነት ነበር። ዲፕሎማቶች ይህን ያደረጉት የባሪያ ጉሮኖ ኃላፊ የነበረውን አንድ ሰሊም የሚባል ስግብግብ ሱልጣን በምስጢር በመገናኘት፣ በማባበልና፣ ጉቦ በማላስ እንዲተባበር በማድረግ ነበር። እነአብርሃም በዚህ መልክ በምስጢር ከነበሩበት ጉሮኖ እንዲወጡ እንደተደረገ በአስቸኳይ የተወሰዱት ወደሩሲያ ዋና ከተማ – ወደ ሞስኮ – ነበር። ምስጢራዊ ግንኙነቱን ያደረገው፣ ክፍያውን ለሰሊም የፈጸመውና እነአብርሃምን ወደ ሞስኮ እንዲሄዱ ያደረገውም በጊዜው የሩሲያ ምክትል አምባሳደር ሆኖ ይሠራ የነበረው ሳቫ ቭላዲስላቪች-ራጉዚንስካይ የተባለ ሰላይና ዲፕሎማት እንደነበር መረጃዎቹ ያረጋግጣሉ።

በእርግጥ ራጉዚንስካይ ይህን ያደረገው በራሱ አነሳሽነት አልነበረም። በጊዜው በቆንስጣንጢኖጵል (በኢስታንቡል) የሩሲያ ሙሉ አምባሳደር ሆኖ ይሠራ በነበረውና በሩሲያ የሥነ-ጽሑፍ ታሪክ በታላቅ ደራሲነቱ የሚጠቀሰው የሊዮ ቶልስቶይ አያት በፕዮትር አንድሪየቪች የበላይ አለቃው በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት እንጂ። የበላይ አለቃው ፕዮትር አንድሪየቪችም ቢሆን ለራጉዚንስካይ ትዕዛዙን የሰጠበት ምክንያት አለው። ይህም የሩሲያ ዛር ታላቁ ቀዳማዊ ጴጥሮስ የነበረውን “ፍላጎት” እና “ምኞት” በሚገባ ያውቅ ስለነበረ ያህን ለማሟላት ሲል ያደረገው መሆኑ ነው። ከዚህ ላይ “ፍላጎት” የተባለው ቀዳማዊ ጴጥሮስ በቤተ-መንግሥቱ ውስጥና ዙሪያ የተለያየ ዝርያ ያላቸው ባሮች እንዲኖሩት እጅግ የተለየ ስሜት ወይም ጉጉት የነበረው መሆኑን የሚያስታውስ ሲሆን ‹ምኞቱ› ደግሞ በዘመኑ አውሮፓን ጨምሮ በብዙዎቹ የዓለማችን ክፍሎች ከኦቶማን ቱርክ ኢምፓየር የመስፋፋት ፖሊሲና ርምጃ ጋር በተያያዘ የሩሲያው ዛር ከኢትዮጵያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ለመፍጠር የነበረውን ሀሳብ የሚመለከት ነው።

የሩሲያው ዛር ታላቁ ቀዳማዊ ጴጥሮስ የኢትዮጵያ ክርስቲያን ነገሥታት የኦቶማን ቱርክ ኢምፓየር በምሥራቅ አፍሪካም በተደጋጋሚ ያደረጋቸውን የመስፋፋት ሙከራዎች በመከላከል መክተው መቆየታቸውን ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። ስለዚህ ቀዳማዊ ጴጥሮስ ከኢትዮጵያ ክርስቲያን መንግሥት ጋር ዘላቂ ግንኙነት ለመፍጠር ከፍተኛ ምኞት እንደነበረውና ይህን ምኞቱን ዲፕሎማቶቹ ያውቁ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። ዲፕሎማቶቹ ሱልጣን ሰሊምን በምስጢር በማግኘት በባሪያ ጉሮኖው ውስጥ ከነበሩ ከተለያዩ ሀገሮች ተፈንግለው ከመጡ ብዙ ባሪያዎች መካከል አስወጥተው የወሰዱት ሦስት ኢትዮጵያውያንን ብቻ መሆኑም ይህን የሚገልጽ ይሆናል። ጄ. ቶማስ ሻው (2006) እንዳሰፈረው

ዛሩን በተለየ ሁኔታ የሚያጓጉት ልዩ ነገሮች ነበሩ። ሳቫ ራጉዚንስካይም ዛሩ የነበረውን ይህን ልዩ ተመስጦ በሚገባ ያውቅ ነበር። … ‹ታላቁ ጴጥሮስን በመወከልም ፕዮትር አንድሬየቪች ቶልስቶይ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ሳቫ ቭላዲስላቪች-ራጉዚንስካይ በሞስኮ ለዛሩ (ለንጉሡ) ቤተ-መንግሥት የሚሆኑ ጥቂት በዕድሜ ትንንሽ ንቁ አፍሪካዊ ባሪያዎችን መፈለግ ጀመረ። በኋላ የሱልጣን አህመድ ሳልሳዊ ንብረት ኃላፊ የነበረ ሰሊም የተባለ አንድ ስግብግብ ሱልጣን በምስጢር በመገናኘት ትብብሩን ጠየቀው። እሱም ለሚያደርገው ትብብር ጠቀም ያለ ክፍያ እንዲሰጠው ጠየቀው።› ከዚያም ሱልጣን ሰሊም አብርሃምን ጨምሮ ሦስት ጥቁር ታዳጊ ልጆችን በሚስጢር በማስወጣት አስረከበው። እንዳስረከበውም ጠቀም ያለ ጉቦ ተከፈለው። ራጉዚንስካይ በዚህ ሁኔታ ሕፃናቱን በቀላሉ ሰርቆ፣ ከዚህ የተሻለ የዛሩን ፍላጎትና ምኞት የሚያረካ ምንም ነገር እንደማይኖር በማመን ጊዜ ሳይወስድ (እኤአ) በ1704 ዓ. ም. (በበጋ ወራት) በየብስ ወደ ሞስኮ እንዲጓዙ በማድረግ ለታላቁ ጴጥሮስ በስጦታ እንዲሰጡ አደረገ።

ዲፕሎማቱ እነአብርሃምን ወደ ሞስኮ እንዲጓዙ ሲያደርግም የቱርክ መንግሥት ባለሥልጣናት ሊጠረጥሩ በማይችሉበት ሁኔታ ከተለመደው መንገድ ውጭ ወደ ሰሜን አቅጣጫ በማምራት በቡልጋሪያ በኩል እንዲጓዙ በማድረግ ነበር። ይህንንም ራሱ ራጉዚንስካይ ሞስኮ ውስጥ ለነበሩት የበላይ ባለሥልጣናት የፃፈው ደብዳቤ በግልፅ ያስረዳል። ይህም ሳቫ ቭላዲስላቪች-ራጉዚንስካይ ይህን የመሰለውን ምስጢር የከበበው የጉዞ ቅያስ ለማውጣት ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው? ብለን እንድንጠይቅ ይጋብዛል።

መልሱም ቢያንስ ሦስት ግምቶችን የሚያመላክት ይሆናል።

  1. በእርግጥም ሕፃናቱ በሩሲያ ዲፕሎማት ተሰርቀው የተወሰዱ መሆናቸውን የሚያመለክት ሲሆን ድርጊቱ የኦቶማን ቱርክ መንግሥት በማስቆጣት በሁለቱ ሀገሮች መሀል የነበረውን ሆድና ጀርባ ግንኙነት ጨርሶ እንዳያባብስ ጥንቃቄ ለማድረግ መመረጡን ይጠቁማል።
  2. ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው ታላቁ ቀዳማዊ ዓፄ ጴጥሮስ የተለያየ ዝርያ ያላቸው ባሪያዎች በቤተ-መንግሥቱ ዙሪያ እንዲኖሩት የነበረውን ልዩ ግላዊ ፍላጎት ያለ እንቅፋት ወይም ያለ ችግር ለማሟላት ተብሎ የተወሰደ ምርጫ ነበር ለማለት ያስችላል።
  3. የኦቶማን ቱርክ ኢምፓየርን የመስፋፋት ፍላጎት ለምዕተ-ዓመታት መክታ ከቆየችውና በመካከለኛው ምሥራቅና በአፍሪካ መሀል ስትራቴጂያዊ መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ ካላት ኢትዮጵያ ጋር የትብብር ግንኙነት ለመፍጠር የሩሲያው ዛር (ታላቁ ቀዳማዊ ጴጥሮስ) የነበረውን ምኞት እውን ከማድረግ አንፃር ለወደፊት እንደ እርሾ ሊያገለግሉ ይችላሉ በሚል እሳቤ እነአብርሃምን በጥንቃቄ ሞስኮ ለማድረስ ሲባል የተወሰደ አማራጭ ሊሆን ይችላል የሚሉ ናቸው።

ጄ. ቶማስ ሻው (2006፡- 83-84) እንዳሠፈረው ሳቫ ራጉዚንስካይ ወደ ሞስኮ ልጆቹን የላካቸው ለእርሱ እጅግ በጣም ታማኝ የሆነ አንድ የቫሲሌቭ ተወላጅ ይዟቸው እንዲሄድ በማድረግ ነበር። ቱርኮች ተከታትለው እንዳይዟቸው በመፍራት የጉዞውን አቅጣጫ ከተለመደው መንገድ ውጭ በቡልጋሪያና በሙንቴና ግዛቶች በኩል በመጓዝ እንደገና ወደ ሰሜን አቅጣጫ በማቅናት ነበር ሲል ጽፏል። በተመሳሳይም ቴሌቶቫ (2006፡-53-54) ተጓዦቹ ሕዳር 15 ቀን፣ 1704 ከቆንስጣንጢኖጵል ተነስተው ሞስኮ የደረሱት (እ.ኤ.አ.) ሕዳር13 ቀን፣ 1705 መሆኑን፣ ሳቫ ራጉዚንስካይ የፃፈውን ደብዳቤ ስፓፋሪዮስ ወደ ሞስኮ ይዞ በመምጣት ከስዊዶች ጋር ናርባ ላይ በተደረገውና በነሐሴ ወር በድል በተጠናቀቀው ጦርነት ከታላቁ ቀዳማዊ ጴጥሮስ ጋር አብሮ ዘምቶ ለነበረው አምባሳደራዊ ቻንስለር ዳይሬክተር ለኤፍ፣ ኤ፣ ጎሎቪን መስጠቱንና ራሱ ስፓፋሪዮስም ለዚሁ ባለሥልጣን (ለጎሎቪን) የፃፈው ማስታዎሻ ሞስኮ ከደረሱ በኋላ እነአብርሃም ለነማን በገፀ-በረከትነት እንደተሰጡ የሚያረጋግጥ ጠቃሚ መረጃ አስፍራለች። የማስታዎሻ ደብዳቤው ፍሬ ነገርም የሚከተለውን ይመስላል።     

ለውድ ጌታዬ፣ ለፌዶር አሌክሲቪች ጎሎቪን። ሰኔ 21 ቀን ከቆንስጣንጢኖጵል ተነስቼ ጉዞ ከማድረጌ በፊት የክቡርነትዎ ግርማ-ሞገሥ ለሚስተር ሳቫ ራጉዚንስካይ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት በፃፈልኝ ደብዳቤ ለሕይወቱ እጅግ በጣም አስጊና አደገኛ በሆነ ሁኔታ ነበር ከቱርኮች ሁለት ትንንሽ ጥቁር ባሪያዎችን (ብላክ አሙሮችን) እንዲሁም ሌላ ሦስተኛ ልጅ ለአምባሳደር ፒትር አንድሪቪች ይዞ የመጣው። እነዚህን ብላክ አሙሮች የላካቸው ለእርሱ ታማኝ ከሆነ ሰው ጋር ሲሆን ለደህንነት ሲባል በሙልቲያኒያንና በቮሎስክ በኩል በእግር እንዲጓዙ በማድረግ ነው። እና ጌታዬ፣ ዛሬ ሕዳር 13 ቀን፣ ያ የሳቫ ታማኝ ሰውዬ እነዚህን ብላክ አሙሮች ይዞ በሰላም ደርሷል። ከእነዚህ ከሦስቱ ብላካ አሙሮች መካከልም የተሻሉትንና ይበልጥ ንቃት ያላቸውን ሁለት ወንድማማቾች መርጨ እጅግ በጣም ከተከበረው ቤትዎ፣ እጅግ በጣም ለተከበሩት ወይዘሮ ባለቤትዎ እና እጅግ ለተከበሩት ልዑላን ልጆችዎ ሰጥቻለሁ። ሦስተኛውን ለእርስዎ ተስማሚነት አይኖረውም ያልኩትን ለፒትር አንድሪየቪች ሰጥቻለሁ። ይህን ያደረግሁበት ምክንያትም ከሳቫ በተሰጠኝ መመሪያ መሠረት ሲሆን ለሳቫ ታማኝ የሆነው ሰውየም እንደዚሁ የነገረኝ ይህኛው ልጅ ለእርስዎ ለጌታየ ተስማሚነት የሌለው መሆኑን ነው። ትንሹ ልጅ በጉዞ ላይ ሳለ በሙልቲኒያኑ አገረ ገዥ የእህት ልጅ “አብርሃም” በሚለው ስም ክርስትና ተነስቷል። ትልቅ ወንድሙ ግን አልተሳም። ሙስሊም እንደሆነ ነው። ሳቫ ራጉዚንስካይ የላካቸው ሁሉም ዕቃዎች ከእህቱ ልጅ ጋር በሰላም አዞቭ ደርሰዋል። ክቡርነትዎ በፈለገ ጊዜ እቃዎቹ እንዲመጡ ይደረጋል።

ይህ ደብዳቤ የሚያረጋግጠው ከቱርክ ወደ ሞስኮ የመጡት ሦስቱ ኢትዮጵያዊ ጥቁሮች (ብላክሙሮች) መሆናቸውን፣ ከእነዚህ መካካልም ሦስተኛው በመታመሙና ዳካማ በመሆኑ ለንጉሡ ተስማሚ አለመሆኑን፣ ሁለቱ ወንድማማቾች ግን ተለይተው አምባሳደራዊ ቻንስለር ዳይሬክተር ለነበረው ለጎሎቪን መሰጠታቸውን፣ ጎሎቪንም ለታላቁ ቀዳማዊ ጴጥሮስ በቀጥታ በስጦታ ማስረከቡን እና ለዚሁ ተግባር ሲልም ሳቫ ራጉዚንሰካይን ‹ለሕይወቱ አስጊና አደገኛ ሁኔታ ገጥሞት› እንደነበር የሚገልጽ ነው።

ሻው እንደሚለው ከእነአብርሃም ጋር አብሮ የመጣው ሦስተኛው ልጅ በጉዞ ላይ ሕይወቱ ማለፉንና ለሞት የበቃው በፈንጣጣ በሽታ ነው። ከስፓፋሪዮስ ደብዳቤ መረዳት እንደሚቻለው ደግሞ ልጁ የሞተው ከአምባሳደር ፒ. ኤ. ቶልስቶይ ቤት ወዲያ እንደደረሰ ሲሆን አብርሃምና ትልቅ ወንድሙ ደግሞ ለታላቁ ጴጥሮስ ተበርክተው ለእርሱ የባለቤትነት ስልጣን ተላለፉ። ከተበረከቱበት ጊዜ አንስቶም ንጉሡ የእነአብርሃምን ሁኔታ በቅርብ ለማየት፣ ለማስተዋልና ያላቸውን ተሰጥኦና ችሎታቸውን ለመመዘን እንደቻለ ይናገራል። ትልቅ ወንድሙ ክርስትና ተነስቶ ‹አልክሲ› የሚል ስም እንደተሰጠው፣ ከዚያም ንጉሡ ለክፍለ ጦር ሙዚቀኛነት እንደመረጠው፣ ለዚህም ሳይቸገር በቂ ትምህርት እንዲያገኝና በሙያው ተሰማርቶ እንደሠራ ጸሐፍቱ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ አሌክሲ ምን ያህል በሙያው ስኬታማ ለመሆን እንደበቃ የተፃፉ መረጃዎች አይገኙም። በአንፃሩ ንጉሡ ታላቁ ጴጥሮስ ከመጀመሪያው ዕይታ አንስቶ በአብርሃም ልዩ የሆነ ብሩህ አእምሮ የተሰጠው ልጅ እንደሆነና የወትድርና ተሰጥኦ እንዳለው በመገንዘብ ታላቁ ጴጥሮስ ገና ከጅምሩ አንስቶ ትኩረቱን እጅግ በጣም ስቦት ሰለነበር ልጁን ወደ መኖሪያ አፓርታማው የወሰደው መሆኑን ጸሐፍቱ (ፑሽኪንን ጨምሮ) በአጽንኦት ያስረዳሉ። ለምሳሌ ቴሌቶቫ፡- “The Czar liked the rare present and almost from the beginning distinguished Abrham from other slaves. Peter drew the younger one closer to himself.” በማለት ገልፃዋለች።

ሻውም እንደዚሁ “ትንሹ ልጅ (አብርሃም) ከዕድሜው አኳያ ሲታይ ፈፅሞ ለማመን የሚያዳግት ብሩህ አእምሮ ነበረው። የራሻን ቋንቋና ፊደሎች የተማረው እጅግ በጣም በአጭር ጊዜ ነበር። የፒትስበርግን ቤተ-መንግሥትንም የገዛ ቤቱ ለማድረግ ጊዜ አልወሰደበትም። ታላቁ ጴጥሮስም ይህን አብርሃም ያለውን ልዩ ተሰጥኦ በመረዳት ከራሱ የመኖሪያ አፓትመንት እንዲቀመጥ አደረገው።” ሲል አስፍሮታል።

አብርሃም በ1705 ቪለኖ ውስጥ ሳለ ነበር በኦርቶዶክስ ደንብና ሥነሥርዓት ክርስትና የተነሳው። ክርስትና ያነሳው ወይም የክርስትና አባቱ ራሱ ታላቁ ቀዳማዊ ጴጥሮስ ነበር። አብርሃም ክርስትና እንደተነሳ በጴጥሮስ የሚጠራ አዲስ ስም ተሰጠው። በዚህ ጊዜ ምርር ብሎ አለቀሰ። ንጉሡ በዚሁ ስም በጠራው ጊዜም ‹አቤት› ብሎ መልስ አልሰጠም ነበር። “… የታወቀው የካርታዠኒያውን ጥንታዊ ጀግና ‹ሀኒባል› የሚለውን ስም ለመስታዎሻነት የሰጠው ራሱ ንጉሡ (ዛሩ) ነው። (ሻው 2006፡-360-61)።

አብርሃም በ1705 ዓ ም. በቅዱስ ሊቲዋኒያ በኦርቶዶክስ ሥነሥርዓት ክርስትና የተነሱበት ጠቃሚ ሰነድ የሚከተለውን መሠረታዊ መረጃ ይዞ በቪልኖ ማኅደራዊ መዘክር ይገኛል። ይህም፡-

“በዚህ ቤተ ክርስቲያን፣

ታላቁ ቀዳማዊ ዓፄ ጴጥሮስ፣

በ1705 በቻርልስ 3ኛው ላይ ለተገኜው ድል

የምስጋና ጸሎት አደረገ።

ከስዊድን ጦር ሜዳ የተማረከ ባንዲራም አበረከተ።

እንዲሁም ከዚህ የተቀደሰ ቦታ ኢትዮጵያዊውን ጋኒባልን አጥምቆ ክርስትና አነሳው።”

የሚል ነው (ቴሌቶቫ 2006)።

ፑሽኪን ዘ ብላክ አሙር ኦፍ ፒተር ዘ ግሬት በሚለው መጽሐፉ ይህ “የተደረገው የክርስትና ሥነ-ሥርዓት በጸሐፍት ዘንድ ‹ዳግም ክርስትና› ነበር መባል የሚገባው። ምክንያቱም አብርሃም በመሠረቱ ከአሀገሩ ከኢትዮጵያ ሳይወጣ ክርስቲያን ነበረና!” በማለት ተችቶታል።

አብርሃም በሩሲያ ውስጥ ዛሩ ለዘመቻ በሄደባቸው ቦታዎች እንዲሁም በአውሮፓ አገሮች ባደረጋቸው ጉብኝቶች ሁሉ አብረው ለመሄድ ዕድል አግኝተዋል።

የወጣቱ አብርሃም ፔትሮቭ መስል

ዕድሉን ያገኙትም እንደቤተሰብ አባል እንጂ እንደባሪያ ተቆጥረው አልነበረም። ታላቁ ጴጥሮስ በሩሲያና በስዊድን መካካል በነበረው ጦርነት ምክንያት በተከታታይ ወደ ሠራዊቱ በሄደ ቁጥር አብርሃምም ክርስትና አባቱ እንዲያውም ጸሐፍት እንደሚሉት ‹ጓደኛ-ጌታው› የገጠመውን አደጋ የከበበው ሕይወትና ውጣውረድ ሁሉ በሙሉ እምነትና ታማኝነት አብረው ተሳትፈዋል። ዛሩ (ንጉሡ) ባደረጋቸው በሌሎች ዘመቻዎችና ወሳኝ በሆኑ ጦርነቶች ሁሉ አብረው ተካፍለዋል። ታላቁ ጴጥሮስ በእነዚህ አጋጣሚዎች ሁሉ ታዳጊው አብርሃም በነበረው ሙሉ እምነት፣ ጥልቅ አስተውሎት፣ ንቃት፣ ፈጥኖ የመማር ተሰጥኦ፣ አስደናቂ እምቅ ችሎታና ብቃት ትልቅ ተስፋ እያሳደረበት መጣ። ይህ ደግሞ የአብርሃምን የወደፊት ዕጣ-ፈንታ ያመራበትን ስኬታማ አቅጣጫ አመልካች ለመሆን ቻለ።

ይቀጥላል …


Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top