አድባራተ ጥበብ

ያልደመቀው ታሪክ ፩ የሴት አርበኞች ሚና

በኢትዮጵያ ታሪክ አጻጻፍ ላይ እንደ እንከን ከሚታዩት ጉዳዮች ውስጥ የታሪኩ ፍሰት የነገሥታቱን እና የመኳንንቱን ውጣ ውረድ ብቻ መያዙ አንዱ ነው። መጻሕፍቱ ከርእሳቸው ጀምሮ የዛሬ አንባቢያን የወቅቱን ተራ ሕዝብ እንቅስቃሴ እንዲመለከቱ የሚያስችል ዕድል አልሰጡም። ሀገራችን ቀደምት የጽሑፍ ታሪክ ይኑራት እንጂ፤ የፊደል ባለቤት ትሁን እንጂ፤ የተሟላ የታሪክ ሰነድ የላትም። የህዝቡን ጥንታዊ አኗኗር፣ የህዝብ ለህዝብ መስተጋብር፣ ማኅበረሰባዊ ፍልስፍና፣ ኢኮኖሚያዊ አስተሳሰብ፣ ሀይማኖታዊ ልምድ፣… እና የመሳሰሉት ታሪኮች በቅጡ አልተሰነዱልንም።

የነገሥታቱ ዜና መዋዕል ጸሐፊዎችም የንግሥና፣ የሹመት፣ የጦርነት፣… ጉዳዮች ሲኖሩ በንጉሡ ትዕዛዝ ለታሪክ የሚሆን ዘገባን ሲከትቡ፣… ሕዝቡን ይረሱታል። ቀረብ ባለው ዘመን የተፈጠሩ የታሪክ ጸሐፊ እና ተመራማሪዎች በውጭ ምንጮች ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ከሚያደርጓቸው ሰበቦች ውስጥ አንዱም ይህ ነው።

በዓድዋ ጦርነት ሕይወት ያለው ብቻ ሳይሆን መልክአ ምድሩ እና የአየር ንብረቱ ሳይቀር አስተዋጽኦ ነበረው። የሚበሉት እንስሳት ለምግብነት እየዋሉ፣ የሚጫኑት እንስሳት ለማጓጓዣ እየዋሉ ተሳትፈዋል። ጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረሥላሴ “ታሪከ ዘመን ዘ-ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ-ነገሥት ዘ-ኢትዮጵያ” በተሰኘው ድርሳናቸው

“እንዲሁም ሆኖ የእልፍኙን፣ የጓዳውን፣ የአዳራሹን፣ የግምጃ ቤቱን፣ የቅጥሩን፣ የፈረሰኞቹን ድንኳን ባዩት ጊዜ በከብት ጫንቃ ተጭኖ የሚሄድ አይመስልም”

ሲሉ የሁነቱን ምስል ገልጸዋል።

ጸሐፊ ትዛዝ ገብረ ሥላሴ የዓድዋ ውሎ በምልአት እንዳልተዘገበ የሚጠቁመውን መደምደሚያቸውን ሲያሰፍሩ

“…ከብዙ በጥቂቱ ጻፍን እንጅ ያደዋን ጦርነት ዓይናችን እንዳየው ጆሯችን እንደሰማው መጻፍ አይቻለንም።”

በማለት ነበር።

እንደ አጼው ትዕዛዝ ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ የሌለው በጸሎቱ ረድቷል። የቀሳውስቱ የቁም ፍትሐት፣ ለስጋው ያልሳሳው ወታደር ለነፍሱ እንዳይጨነቅ አድርጎታል። የታቦቱ አብሮ መጓዝ ተጨማሪ መለኮታዊ ጥበቃ መኖሩን የሚያመሰጥር ነው። አዝማሪው በማሲንቆ ወኔን ይቀሰቅሳል፣ ታሪክ ይዘግባል። ሴቶች የተጎዳን በማከም፣ የፈራን በማጀገን፣ ምግብ በማብሰል፣… ሳይገደቡ አመራር እስከመስጠት ተሳትፈዋል። ዓድዋን ያለ እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ ማሰብ ታሪኩን ምሉእ አያደርገውም።

“እኔ ሴት ነኝ ጦርነት አልወድም። ሆኖም ይህን ኢትዮጵያን የኢጣሊያ ጥገኛ የሚያደርግ ውል ከመቀበል ጦርነት እመርጣለሁ”

የሚለው የእቴጌዋ ታዋቂ ንግግር ከሁሉ ቀድሞ የፈሪን ልብ በወኔ የሞላ ቃል መሆኑ አይዘነጋም።

ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም “የሕይወቴ ታሪክ” በተሰኘ ጥራዛቸው በዓድዋው ጦርነት ወቅት ሴቶች የነበራቸውን ወሳኝ ሚና ሲያብራሩ

“ሴት አገልጋይ የተባለችው […] ከዘመቻው ላይ በጣም አገለገለች።”

ይላሉ።

“ከቶ እሷ ባትኖር እንዴት እሆን ኖሯል፣ እያልኩ ዘወትር ሳስበው ያስደንቀኛል። ዕቃ ተሸክማ ስትሔድ ትውላለች፤ ከሰፈርን በኋላ ውሃ ቀድታ፣ እንጨት ለቅማ፣ ቂጣ ጋግራ፣ ወጥ ሰርታ ታበላናለች። ወዲያው እንደዚሁ ለማታ ታሰናዳለች።

እንደዚህ የወለተ አማኑኤልን አገልግሎት እያሰብኩ ስደነቅ ደግሞ፣ በየሰፈሩ እንደዚህ እንደርሷ ስንት ሴቶች እንደሚያገለግሉ ይታሰበኛል።

የሴቶቹን አገልግሎት ስገምት፣ ደግሞ የበቅሎዎቹ አገልግሎት ይታወሰኛል። በመጨረሻው ድምሩን ስገምተው፣ የዓድዋ ድል የተገኘው በሴቶች አገልጋዮች እና በበቅሎዎች ብርታት መሆኑ ይታወቀኛል።”

በማለት ነበር። እዚህ ላይ የመጨረሻውን ዓረፍተ ነገር ልብ ይሏል። “…የዓድዋ ድል የተገኘው በሴቶች አገልጋዮች እና በበቅሎዎች ብርታት…”

የአቅርቦት (ሎጀስቲክ) እና የወኔ፣ የሞራል፣ የእችላለሁ ባይነት፣… ስሜቶች መሟላት ለድል ግስጋሴ የሚያደርገውን አስተዋፅኦ በቅጡ ከመገንዘብ የተሰጠ የዐይን ምስክርነት ነው።

ጳውሎስ ኞኞ በበኩሉ “አጤ ምኒልክ” በሚለው ድርሳኑ እቴጌ ጣይቱ ወታደሮቻቸውን እንዲህ እያሉ ያበረታቱ እንደነበር ከትቧል።

“…ከሜዳው ላይ ሞት እንዳትፈሩ ተስፋ አለኝ። በህይወት ያለውንም ባዘዝኳችሁ ነገር እሸልመዋለሁ። የሞተውንም ተስካሩን አወጣለሁ። እግዚአብሄር ከናንተ ጋር ይሁን ብለው አሰናበቷቸው።…”

ብዙ ታሪክ ጸሐፊዎች ነገሬ ብለው የማያነሱትን የሴቶች ተሳትፎ አስመልክቶ በዕውቀቱ ስዩም “ከአሜን ባሻገር” የተሰኘ ጥራዙ ላይ ሲጽፍ፤ ሴቶች ዘመናዊ መሳሪያ ባልነበረበት ዘመን “ዳሄራ” የተባለ ባሩድ ያሰናዱ እንደነበር ይጠቁማል። ለነገሩ ማጠናከሪያ ይሆነው ዘንድም ንጉሥ ምኒልክ ከራስ አዳል ጋር ለጦርነት በተሰናዱበት ጊዜ የተቋጠረ ቅኔ ይጠቅሳል።

ሴቶች ተሰብሰቡ እንውቀጥ ዳሄራ

ክርክር አይቀርም ከራስ አዳል ጋራ

የዓድዋ ከተማ ባህል እና ቱሪዝም ጽ/ቤት ም/ኃላፊ የሆኑት አቶ ጽጌ ኃ/ማርያም ደጃች ለተእግዚአብሄር ስለተባሉ አርበኛ ገድል እንዲህ ይተርካሉ።

‹‹ወይዘሮዋ ወራሪውን ጣልያን ለማጥቃት ጦርሜዳ አልሄዱም። የቤታቸውን ወጋግራ ተንተርሶ የተጋደመውን የንብ ቀፎ ለጥቃት ተጠቀሙበት። ከነበረበት አንስተው የጣልያን ወታደሮች ወደመሸጉበት ስፍራ ወረወሩት። ከቀፎው የበረገገው ድንገቴ ደራሹ የንብ መንጋ ደፈጣ ላይ የነበረውን ወታደር እየነደፈ በተነው››  

የቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊው አክለው ራስ አሉላ እና ራስ መንገሻ የዓድዋ ከተማ ነዋሪን በማስተባበር የአሰላለፍ እቅድ ማውጣታቸውን ያብራራሉ።

‹‹ራስ አሉላ መልክዓ ምድሩን እና የነዋሪዎችን አቅም ያገናዘበ የጦርነት አሰላለፍ ተከትለዋል። ጠና ያሉ ሴቶች እና አረጋዊያን ምድባቸው የተራራው ጫፍ ነበር። ከላይ ሆነው በእልልታ፣ በጭብጨባ፣ በፉከራ ሁለት ትርጉም ያለው ስራ ይከውናሉ። በድርጊታቸው የጠላት ጦር ሲሸበር የወገን ወታደር ሞራል ተሰምቶት ወደፊት ይገሰግሳል። ጉልበት እና ንቃት ያላቸው ወጣት ሴቶች ምድብ ደግሞ የተራራው ግርጌ ነው። የቆሰለን ማከም፣ ምርኮኛን መጠበቅ እና መንከባከብ፣ ምግብ ማሰናዳት እና ማቅረብ፣ ውሃ መቅዳት፣ የወገን ወታደር ሲወድቅ እሱን ተክቶ መዋጋት፣… በዚህ ምድብ ያሉ ሴቶች ተግባር ነው። እስካሁን ድረስ “ማይ አብኡር” (የበሬዎች ውሃ) በመባል የሚታወቀው አካባቢ ከድል በኋላ ለእርድ የቀረቡ 50 የሚጠጉ በሬዎች ውሃ መጠጫ ቦታ እንደነበረ የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ። በተጨማሪም ሴቶቹ በርበሬ እና ወስፌን የመሰሉ የማጀት መሳሪያዎች በመጠቀም ጣልያንን ተዋግተዋል››

Women and welfare in Ethiopia የተሰኘውን የምናለ አዱኛ ጥናት በመጥቀስ የሴቶቹን ተጋድሎ የዘገበው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በአንድ ጽሑፉ ሴቶች በዓድዋ ጦርነት የነበራቸውን ሚና አስመልክቶ እንዲህ ብሏል።

“ለተዋጊው ምግብ እና መጠጥ ማዘጋጀት (የበግ እና የበሬ እርድ በወንዶች መከወኑ ሳይዘነጋ)፣ ባህላዊ መድሃኒት መቀመም፣ ልብሶችን ማጠብ፣ የመንገድ ሥራና ምሽግ ግንባታን ማገዝ፣ የቆሰለውን ማከም፣ የሞተውን መቅበር፣ የጦር ሰፈርን ከጥቂት ወታደሮች ጋር መጠበቅ፣ ጠላት ወረዳ ድረስ በመግባት መረጃ ማነፍነፍ፣ ከምርኮኞች የሰበሰቡትን መሳሪያዎች እና ቁሳቁሶች ማደል፣ በውጊያ መካከል የግንኙነት መስመራቸው የተበጠሰ አሃዶችን መልሶ ማገናኘት፣ ለጠላት ወታደሮች የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ቀለበት ውስጥ ማስገባት፣ በእልልታ እና በጩኸት የተዋጊውን ሞራል መገንባት፣ ጠመንጃ አንስቶ በውጊያ መሳተፍ እና ሌሎች መሰረታዊ ጠቀሜታ ያላቸው አገልግሎቶችን ግንባር ድረስ ተገኝተው መወጣታቸውን በስፋት ጠቅሰዋል።”

የተጠቀሰው የ40 ገጽ የጥናት ወረቀት የተዘረዘረው የሴቶቹ ተግባር በዓድዋ ጦርነት ወይም በማይጨው ብቻ የተገደበ እንዳልነበረ ይልቁንም እስከ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ድረስ መዝለቁን ያትታል።

ባህሩ ዘውዴ (ፕ/ር) “የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983” የሚል ስያሜ ሰጥተው ባሰናዱት ጥራዝ “የአርበኞች ትግል” ሲሉ በሰየሙት ርዕስ ስር ያሰፈሩት ታሪክ በተጠቀሰው ጥናት ላይ የሴቶቹ የማይናቅ ተሳትፎ ከአርባ ዓመት በኋላም ስለመቀጠሉ ምስክር የሚሆን ነው።

በውስጥ አርበኝነቱ ሥራ ላይ መረጃ ማሰባሰቡን፣ ዘመቻዎች ማካሄድ የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች፣ ለአርበኞች የይለፍ ፈቃድ እና መታወቂያ በድብቅ መስጠትን እና የመሳሰሉትን ተግባራት ይከውኑ ስለነበሩት የውስጥ አርበኞች በገለፁበት ጊዜ

“ለዚህ ሁሉ ስራ ሴቶቹ ስለማይጠረጠሩ በተለይ አመቺ ነበሩ።”  

ይላሉ። ነገሩን ዘርዘር ሲያደርጉት

“ከሴት አርበኞች ውስጥ ከፍተኛ ዝና ያገኘችው አርበኞች አዲስ ዓለም የመሸገውን የጠላት ጦር እንዲደመስሱ ሁኔታዎችን ያመቻቸችላቸው ሸዋረገድ ገድሌ ናት። […] ባጠቃላይ ጣልያኖቹ ናላቸው የዞረው አርበኞቹ ከሚያደርሱባቸው ጥቃት ይልቅ የውስጥ አርበኞቹ በሚያደርጉባቸው ግዝገዛ ነበር ማለት ይቻላል።”

ጣይቱ ብጡል በዓድዋ ጦርነት ራሳቸው አስታጥቀው የሚመሯቸው 5ሺህ ወታደሮች ነበሯቸው። ከማዋጋት በተጨማሪ የትግሉ የጀርባ አጥንት የሆነውን የ‘ሎጀስቲክ’ ቡድን መርተዋል። የሴት አርበኞቹ ሚና ጦርነቱን ማእከል አድርገው በተሰናዱ ድርሳናት ላይ የዋጋቸውን ያህል ባይጎላም ለበለጠ ጥናት የሚገፋፉ ጥቁምታዎች ይገኛሉ።

“የመቀሌ የጠላት ምሽግ በወንዶቹ ጀግንነት አልፈታ አለ። የሴት ብልሐት ተተካ።“

ይላል ጳውሎስ ኞኞ ጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴን ጠቅሶ እንዲህ ተርኮታል።

“…አንተ ሂድና ውሃውን ለመያዝ ይመች እንደሆነ ውሃውን ሰልለው። ለሊቀ መኳስ አባተንም አማክረው ብለው አዘዙ። […] እናንተ ከጉድባ ገብተን ካልተዋጋን እያላችሁ ስትመኙ ነበር። ነገር ግን ለብዙ ሰራዊት ጥቂት ስፍራ አይበቃውምና ከኢጣሊያው ነፍጥ ይልቅ እናንተ እርስ በእርሳችሁ ትተላለቃላችሁ። ከውሃው ተኝታችሁ ውሃ እንዳይቀዳ ጠብቁ።…”

የንግሥቲቱ መላ ሰምሮ ቅድመ ዓድዋው የመቀሌ ጦርነት በሀገር ልጅ አሸናፊነት ተጠናቀቀ።

ነገራችንን በተንኳሽ የአዝማሪ ግጥም እንደምድመው። አዝማሪው ንግሥቲቱ በጦርነቱ የነበራት ሚና ከንጉሡ ይበልጣል፣ ማሰቢያው ጣይቱ ናት የሚል አቋሙን በዜማ ለውሶ፣ በመሰንቆ አጅቦ፣… በተከታዮቹ ስንኞች ተንፍሷል።

ጥልያን ሲመትረን እንዲያ በጥይቱ

እጅግ ጨቅላ ነበር ገና በወጣቱ

ነግ-ነግ ምኒሊኩ ራስ የጣይቱ

፪ የአዝማሪዎች ሚና

ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” ሲል ባሰናዳው ድርሳን ላይ በርክሌይ የጻፈውን የጉዞ ማስታወሻ ጠቅሶ ይህንን አስፍሯል።

 “በሠራዊቱ መሐል አዝማሪዎችም አብረው ይዘምታሉ። በዚያ ሁሉ ሁካታ አዝማሪዎቹ ዘማቹን እያጫወቱ ይሄዳሉ። አብሯቸው የሚሄደው ሠራዊትም ለአዝማሪዎቹ ግጥም ይነግሯቸዋል። አዝማሪዎቹም የደከመውን በግጥም እያበረታቱ ይጓዛሉ። […] የጦርነቱ ዕለት ኢትዮጵያውያኑ ደማቅ ቀለም ያለው ካባ ለብሰው ጠ መንጃ እና ጦር ይዘው፣ ጎራዴ ታጥቀው፣ የነብር ና የአንበሳ ቆዳ ለብሰው፣ አዝማሪዎች እየዘፈኑ ቄሶቹ፣ ልጆቹ፣ ሴቶቹ ሳይቀሩ ፀሐይዋ ፈንጠቅ ስት ል በተራራው ላይ በታዩ ግዜ የኢጣሊያንን ጦር አሸ በሩት” የጊዜው አዝማሪዎች ተግባር በጉዞ ላይ የማዝናናት ብቻ ሳይሆን በጦርነት ላይ ወኔ የመስጠትም ጭምር ነው። ከዚህ በተጨማሪም የታሪክ ሁነቶችን መዝግበው ላለንበት ዘመን አቆይተውልናል። በፉከራም ሆነ በሙሾ የተሰናኙት ግጥሞች ስሜትን ብቻ ሳይሆን ታሪክን ሰንደዋል። ከጸሐፌ ትዛዝ ገብረሥላሴ ዘገባ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነንን እንጥቀስ። የሐረርጌው ገዢ ራስ መኮንን ሞት በተሰማ ጊዜ አዝማሪ  እንዲህ ብሎ ማዜሙን “ታሪከ ዘመን- ዘዳግማዊ ምኒልክ” ከትቧል

ዋ አጼ ምኒልክ እግዚአብሄር ያጥናዎ

በየበሩ ቋሚ ከልካይ ሞተብዎ

የመረጃ ቅብብሎሹ እንዳለንበት ዘመን ከመፍጠኑ በፊት፣ የመዝናኛ አማራጮች ቁጥር ከማሻቀቡ በፊት፣ የሕትመት እና የስርጭት ቴክኖሎጂው ከመዘመኑ በፊት፣… የኅብረተሰቡ ዐይን እና ጆሮ የሆኑት አዝማሪዎች

አንድ ካህን ለነፍስህ ይቅርታ መማጸኛ

አንድ አዝማሪ ለስጋህ መዝናኛ

በሚል ከሰማያዊው ዓለም ባልተናነሰ የምድር አስፈላጊነታቸው ተወስቷል።

ኧረ ጉዱ በዛ ኧረ ጉዱ በዛ

በጀልባ ተሻግሮ አበሻን ሊገዛ

የሚለው የአዝማሪ ግጥም የካቲት 22 ሌሊት የአልቤልቶኒን ጦር ፊትለፊት እየተመለከቱ እንዳ ኪዳነ ምህረት የተባለ አካባቢ ላይ ሲዜም ማንጋቱን የጳውሎስ ኞኞ መጽሐፍ ያስረዳል።

 ባህር ዘሎ መምጣት ለማንም አይበጅ

እንደ ተልባ ስፍር ትከዳለች እንጂ

አትረጋም ሐገር ያለ ተወላጅ

የሚለውን ከላይ ካነሳነው ስንኝ ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው ግጥም ሰርጸ ፍሬ ስብሃት ተመሳሳይ ይዘት ባለው ጽሑፉ ጠቅሶታል።

አላጌ ላይ ከፊታራሪ አባ ውርጂ ሌላ ጊድን ገብሬ የሚባሉ የላስታ እና የዋግ ጦር መሪ እና እህታቸው ይገኙበታል። እህታቸው ጥይት በቀሚሷ ጫፍ እየቋጠረች ስታቀብል አብራ ሞታለች። እነዚህ ሁለት ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ አዝማሪ

የጊድን ነገር አይተኛም በውን

ጦር መጣ ቢሉት ይነሳል አሁን

ጊድን ገብሬ የሜዳ ዝሆን

ፈረሱን ጫኑት ይነሳ እንደሆን

.

የጊድን እህት ምጥን ወይዘሮ

ጥይት አቀባይ እንዳመልማሎ

ባልቻ ሳፎ (አባ ነፍሶ) በመድፍ ጠላትን እያሻገሩ በሚያጠቁበት ጊዜ ከጠላት በተተኮሰ ጥይት ጆሯቸው ተቆርጦ ነበር። በዚህ ጊዜ አዝማሪ

ማን እንዳንተ አርጎታል

የእርሳሱን ጉትቻ

የዳኘው አሽከር አባ ነፍሶ ባልቻ

በማለት አይረሴ በሆኑ የስንኝ ድርድሮች ታሪክን ከውዳሴ አጣምሮ በአዝማሪዎች መሰንቆ ታሪክ ይሻገራል። ጀግና ይወደሳል።

ያድዋን ሥላሴ ጠላት አረከሰው

ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው

የሚለው የአዝማሪ ግጥምም የአካባቢውን ሁኔታ እና የጀግኖቹን ግብር በእኩል የሚገልጽ የታሪክ ምእራፍ አስታዋሽ ነው።

 ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ

መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ

*

አበሻ ጉድ አለ ጣልያን ወተወተ ዐይነ ጥሩ ተኳሽ ቧ ያለው አባተ “የኢትዮጵያ ታሪክ” በተሰኘው የተክለ ጻድቅ መኩሪያ መጽሐፍ ላይ ደግሞ ተከታዮቹ የአዝማሪ ስንኞች ተከትበዋል።

 አሉላ አባ ነጋ የደጋ ላይ ኮሶ

በጥላው ያደክማል እንኳንስ ተኩሶ

*

ሰባት ደጃዝማች አስር ፊታውራሪ የጠመቀውን

የወሌ ፈረስ ጠጣው ብቻውን

ወሌ በጉሎ ዘሎ ቢወጣ

ይመስላል ሐምሌ ክረምት የመጣ

የሚሉት መወድስ ስንኞች ይገኛሉ። የቴጌ ጣይቱ ብጡል ወንድም ራስ ወሌ ብጡልን ያወደሰው የአዝማሪ ስንኝ ለዛሬው አድማጭ ታሪክ ነጋሪ ሰበዝ ያቀብለዋል። ቀኛዝማች ባሻሕ ለተባሉት አንድ ዐይና አርበኛ የተገጠመው የአዝማሪ ግጥም ጀግንነታቸውን ብቻ ሳይሆን የሰውነት አቋማቸውንም የሚያስነብብ ነው።

 አፉ ጎራዴ የለው አሽሟጣጭ

ባሹ አባ ሳንጃ ባንድ ዐይኑ አፍጣጭ

በጎንደር ስልጣኔ ወቅት አዝማሪነት ከፍ ያለ ልዕልና ላይ የደረሰበት ወቅት ነበር። ‹ሊቀ መኳስ› የሚል ማዕረግም ተችሯቸዋል።

ቢያብጥ ቢደነድን ቢከመር እንደ ጭድ

ደንዳናውን እንዶድ ይቆርጠዋል ማጭድ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ልሳን ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ስርግው ገላው አዝማሪን በተመለከተ የመድረክ ንግግራቸው የአዝማሪ ግጥሞች ሰም ለበስ በመሆናቸው አመራማሪ እና ከመጠቀ ምናብ የሚፈልቁ ናቸው ይላሉ።እንደ ዶክተር ስርግው በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን የነበረው የዓለም ዐተያይ እና ፍልስፍና ከአውሮፓውያን የሚልቅ እንደነበር ማስረጃዎች ስለመኖራቸው አብራርተዋል። የማኅበረሰብ ስምምነቶች እና ደንቦች፣ ፍላጎቶች እና እሳቤዎች በአዝማሪዎች ይገለፃሉ። ከዜማ ጋር ተዳምሮ በግጥም የሚገለጸው ፍልስፍና በቅጡ አለመጠናቱ እንጂ የሚናገረው ነገር ቀላል አይደለም።

 ክፉ አረም በቀለ በምጥዋ ቆላ

አሁን ሳይበረክት አርመው አሉላ።

.

እነዚያ ጣሊያኖች ሙግት አይገባቸው

አሉላ አነጣጥረህ ቶሎ አወራርዳቸው።

.

ዳኛው ወዴት ሄዷል እስኪ ወጥተህ ዕይ

አክሱም መንገሻዬ እስኪ ያዝነወይ።

.

ዓድዋ ላይ ጣሊያኖች የዘፈኑለት

ምኒልክ ጎራዴህ ወረደ ባንገት።

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ማኅበረሰብ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙሉነሽ አበበ በበኩላቸው አዝማሪዎች የአልገዛም ባይነት እና የወኔ ትጥቅ አስታጣቂዎች በመሆናቸው በጣሊያን ወረራ ወቅት በብርቱ ጠላትነት ከተፈረጁት መካከል መገኘታቸውን ያነሳሉ።

 በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ወቅት 40 ያህል አዝማሪዎች መርካቶ አካባቢ መረሸናቸውን Ethiopia a cultural history የተሰኘው መጽሐፍ ዘግቧል። የቀደመውን ለመበቀል እና የአሁኑን ተግባር ለመግታት ያለመው የጣሊያን ግድያ አርበኞቹ አዝማሪዎች ማኅበረሰቡን በማንቃት የነበራቸውን ጉልህ ሚና የሚያሳይ ነው።

አውድማው ይለቅለቅበሮችም አይራቁ

ቀድሞም ያልሆነ ነውውትፍትፍ ነው እርቁ

በሚለው አንቂ እንጉርጉሮዋ የምትታወቀው አዝማሪ ጻዲቄ ታሪካቸው ካልተጠና ባለ ታሪኮቻችን መካከል የምትመደብ ናት።

ደራሲ በእውቀቱ ስዩም ከላይ ያነሳነውን ግጥም ጠቅሶ፡-

አብዛኛው ዘማች ገበሬ ስለሆነ ፃዲቄ ጦርሜዳውን በአውድማ፣ አርበኞችን በበሬ መስላ መግጠሟ ነው። አዝማሪዎች ጀግኖችን ከማወደስ፣ ፈሪዎችን ከመውቀስ አልፈው የንጉሥን ውሳኔ የሚሞግት ሐሳብ እንደሚያቀርቡ ያሳያል።… በዓድዋ ድል ዋዜማና ማግስት ከተገጠሙት ግጥሞች መካከል የትኞቹ የእሷ እንደሆኑ ለማወቅ አልተቻለም። ግን ብዙ ቀስቃሽ ግጥሞች ከመግጠሟ የተነሳ ሃኪም መረብ የተባለ የፈረንሳይ ጎብኝ ከዝነኛው የስፓርታ የጦር ሜዳ ገጣሚ ከጠርየስ(ቴርየስ) ጋር ያወዳድራታል። ፃዲቄ በዓድዋ ጦርነት ላይ ላደረገችው አስተዋፅኦ ከምንሊክ እጅ ሽልማትና የወይዘሮነት ማዕረግ ተቀዳጅታለች…” ሲል ጽፏል።

 የጻዲቄ ግጥሞች በውል ተለይተው

ባይታወቁም እቴጌ ጣይቱ ሲሞቱ ያወረደችው ሙሾ ከግጥሞቿ መካከል ተጠቃሽ ነው።

የመካን ቤትና ባመድ የነገደ

እቴጌ ቤትዎ ምን ጊዜ በረደ

ራቴን አብኩቼ

ምሳዬን በልቼ

መጣሁ ሰከም ብዬ

ልጅሽ አይቆጣኝ አንቺ አታይኝ ብዬ

ሔኖክ ያሬድ “እንደ አያት እንደ አባት” ሲል ስለእውቁ ሰዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታ ባሰናዳው ጽሑፍ ላይ ደግሞ አዝማሪ ፃዲቄን እንደሚከተለው ጠቅሷት ነበር፡-

 “… የገብረክርስቶስ አያት በ19ኛ ምዕት ዓመት መገባደጃ ከተነሱት ግንባር ቀደም ሠዓልያን ዝነኛ የነበሩት በላቸው ይመር፣ ትውልዳቸው የሚነሳው ከጎጃም ጠቅላይ ግዛት ብቸና አውራጃ፣ የጠም አቦ አጥቢያ ነው። በኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ታሪክ በተለይ የሚወሱበት የንግሥተ ሳባ ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ያደረገችው ጉዞና ቀዳማዊ ምኒልክን ስለመውለዷ የሚያሳየው ሥዕላዊ ተረካቸው ነው። የሠዓሊ ገብረክርስቶስ አያትና አባትሌላው የሚጠቀሱበት በወራሪዎቹ ጣሊያናውያን ላይ በዓድዋ ጦርነት የተገኘውን ድል በሚያሳዩበት ሥዕሎቻቸው ነው።

በሥዕሉ ጐልተው ከሚታዩት ከጠቅላይ አዝማቹ ዳግማዊ ምኒልክና እቴጌጣይቱ በተጨማሪ አዝማቾች፣መካከል ፊታውራሪ ገበየሁ፣ራስ መንገሻ፣ራስ አሉላ፣ራስ አባተ፣ደጃዝማች ባልቻ ይጠቀሳሉ። ከአዝማሪዎች መካከልም አዝማሪ ፃዲቄ እየሸለለችና እየፎከረች ስታዋጋ የሚያሳይ ሥዕልም የዘመኑ ትሩፋት ነው።

 አርቲስት ሱራፌል ወንድሙበሴት ከያኒያን ላይ ትኩረቱን አድርጎ ባቀረበው የጥናት ወረቀት፤ መረብ፣ ኃይለማርያም ገመዳ አና ተክለሃዋርያት ተክለማርያም የተባሉ ፀሃፊያንን ጠቅሶ እንዲህ ይለናል፡- “…አዝማሪዎችን ማግለል በተመለከተ መረብ እንደፃፈው ፃዲቄ እና ሌሎች አዝማሪዎች ታዋቂ ቅምጦች ነበሩ። በተጨማሪም ፃዲቄ በዓድዋው ጦርነት ላይ ላሳየችው ጀብዱ ዳግማዊ ምኒልክ ‹እመቤት› (ወይዘሮ) የሚል ማእረግን ሰጥተዋት ነበር። “የቆነጃጅት አለቃ” የሚለውን ሹመትም ተቀብላለች። ተክለሃዋርያት ተክለማርያም (1884-1977) እንደሚሉት በአዝማሪ ፃዲቄ ስም የሚጠራ የሴተኛ አዳሪዎች ሰፈር ነበር። ኃይለማርያም ገመዳ “ጥቂት ስለኢትዮጵያ ህዝብ ጤንነት” በሚለው ፅሁፉ ላይ እንደሚለው ዳግማዊ ምኒልክ የ”ዘመናዊ ህዝቦችን ስርዓት” ነው የተከተሉት። እናም በአዲስ አበባ የሚገኙ ሴተኛ አዳሪዎችን በመሰብሰብ በአንድ ሰፈር እንዲሰባሰቡ አድርገዋል። ሰፈሩም ያኔ ‹የአዝማሪ ፃዲቄ ሰፈር› ይባል ነበር። ይህም ሰፈር በአራዳ (አሁን ፒያሳ የምንለው) እና በለገሃር መካከል የሚገኘው አካባቢ ነው። የሰፈሩ መጠሪያም በ1940ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በሰዎች ዘንድ ሊዘነጋ እና ሌላ መጠሪያ ሊይዝ በቅቷል።

ልብ ልንለው የሚገባ ነገር ቢኖር መረብም ይሁኑ ተክለሃዋርያት አካባቢውን አዝማሪዎችን ለማግለል ተብሎ የተመሰረተ አድርገው አያስቡም። እንዲያውም መረብ እንደሚናገረው ዳግማዊ ምኒልክ አዝማሪ ፃዲቄን ክብር ሰጥተው ከመኳንንቶቻቸው እንደአንድ እንዲታዩ በማድረግ አስከብረዋቸዋል። ምንም እንኳ ተክለሃዋርያት አዝማሪነት እንደውጉዝ እና የሰነፎች ሙያ አድርገው ቢቆጥሩትም፤ አንዳንድ መኳንንት እንደ ልጅ ኢያሱ እና አማካሪው አዝማሪ ተሰማ እሸቴ ያሉ በአዝማሪ ፃዲቄ መከበር ላይ ምንም ዓይነት ተቃውሞ አልነበራቸውም። ” ኃይለማርየም ገመዳ “ጥቂት ስለኢትዮጵያ

ህዝብ ጤንነት” ብለው ባቀረቡት ፅሁፍ ላይ በጥልቀት ጉዳዩን እንዲህ አብራርተውታል፡- “…በአብዛኛዎቹ በውጭ ሰዎች በተፃፉ ታሪኮች ላይ እንዳለው እና እኛም እውነትነቱን እንደምናምነው፤ ኢትዮጵያውያን ጥብቅ የሆነ የጋብቻ ባህል ያላቸው፣ በጨዋ አስተዳደግ ያደጉ እና ስርዓት ያላቸው ስለሆኑ ለረጅም ዘመናት ጤነኞች ሆነው ሊኖሩ ችለዋል። ከዓድዋ ድል በኋላ ግን የከተማዋ ህዝብ ቁጥሩ እየጨመረ ስለመጣ እና ከሴተኛ አዳሪዎች በሚመጣ በሽታ ምክንያት ህዝቡ እንዳይጎዳ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመናዊ ህዝብ ሊከተለው የሚገባን ስርዓት አበጁ። በእድሜ የገፉ ሰዎች እንደሚያስረዱት ከሆነም በአዲስ አበባ የሚገኙ ሴተኛ አዳሪዎች በአንድ አካባቢ እንዲሰበሰቡ ሆነ። ይህም አካባቢ “ገዳም ሰፈር” የሚባል ሲሆን፤ የአካባቢው ዋና አስተዳዳሪም አዝማሪ ፃዲቄ ነበረች። በዚህም ምክንያት በአሁኑ ዘመን ከምናየው በላይ ጥሩ የሴተኛ አዳሪዎች አያያዝ በዛ ዘመን ነበር። የህዝቡንም ጤና በዚህ መልኩ ለመጠበቅ ሙከራ ተደርጓል”

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top