ታዛ ወግ

የየካቲት ወግ

የየካቲት ወግ

የየካቲት ሃያ ሦስቱ የዓድዋ ድል የኩራታችን ምንጭ መሆኑ አያጠያይቅም። ከኢትዮጵያዊያን አልፎ አፍሪካዊያንን ብሎም በዓለም የተበተነውን ጥቁር ሕዝብ ሁሉ ያኮራ የነጻነት ፋና ወጊ ዕለት ነው። በዚሁ በየካቲት ወር በአስራ ሁለተኛው ቀን የተፈጸመ ሌላ የታሪክ አጋጣሚም አለ። በቀደመው የድል ጽዋችንን ስናነሳ በተከታዩ መራራውን ሽንፈት ቀምሰናል።

በዚህ ጽሑፍ የካቲት ሃያ ሦስትን እና የካቲት አስራ ሁለትን አንጻር በአንጻር አስቀምጠን አንዳች ምስስሎሽ አለያም ተለያይነት ልንነቅስባቸው እንጥራለን። በቀደመው ጣልያን እና አርባ ዓመታት ዘግይቶ በመጣው ሁለተኛው ጣልያናዊ ትውልድ መካከል በነበረን የአልደፈርም ባይነት ፈተና ያገኘነው ውጤት ተቃራኒ ነው።

ከቁርቆራዋ አንስቶ ከአንድ መቶ ሃያ ዓመታት በላይ ላስቆጠረችው አዲስ አበባ የየካቲት አስራ ሁለቱ የፋሺስት ጣሊያን ጭፍጨፋ ትልቁ ጠባሳዋ ነው። በየካቲት ወር ከዓድዋ ድል ቀጥሎ የተከሰተ ከወራሪ ጣሊያን ጋር ተያይዞ የሚወሳ ሁለተኛ ታሪካችን ነው።

 በተመሳሳይ ወራት የምናስባቸው የታሪክ ገጠመኞቻችን የሚፈጥሩብን ስሜት እንደተገኙበት ወር ተመሳሳይ አይደለም። በዓድዋ ድል ብንኮራም በየካቲት አስራ ሁለት ሰማዕታት እናዝናለን። ታሪክ ደግሞ የሚያኮራውና የሚያስደስተው ብቻ ሳይሆን፤ የሚያሳዝነውና የሚያስጸፅተው ጭምርም ነውና በእኩል መጠን ልንዘክረው እና ልናስበው ግድ ነው።

 ፲፪

የየካቲት አስራ ሁለቱ የሰማዕታት ማስታወሻ በዓል ንጹሐን ዜጎቻችንን በግፍ ያጣንበት ቢሆንም የመነሻ ሰበቡ ሐገር ወዳድነት፣ አልገዛም ባይነት፣… መሆኑ ከፍ ያለ ትርጉም እንድንሰጠው ያስገድደናል።

 ለየካቲት አስራ ሁለት የደመቀ የትውስታ መርሃግብር ሲሰናዳለት አለመስተዋሉ ሽንፈትን ደጋግሞ ማውሳት ምቾት ስለሚነሳ ነው የሚሉ ተንታኞች አሉ። በአምስት ዓመቱ ወረራ ንጉሡ ከሐገር ውጭ ቆይታቸው ሲመለሱ ማክበሩን አልፈለጉትም። በእሳቸው አልጋ የተተካው ወታደራዊ መንግሥትም ዕለቱን መዘከር ፊውዳልን እንደማወደስ ቆጠረው ፡፡

የካቲት አስራሁለት በአዲስ አበባ ብቻ ከሠላሳ ሦስት ሺህ በላይ ንፁሃን ያለጥፋታቸው በጥቂት ቀናት ውስጥ ብቻ በፋሺስቶች እጅ ተጨፍጭፈዋል። ይህ ዘግናኝ እልቂት በዓለም ታሪክ ውስጥ በዘግናኝነታቸው ከሚታወቁ የጅምላ ጭፍጨፋዎች ተርታ የሚሰለፍ ነው። ለምሳሌ የርዋንዳው ጭፍጨፋ ስምንት መቶ ሺህ ሰው  ያለቀበት ነበር። ያ የሆነው ግን ወደሁለት ወር በሚጠጋ ጊዜ ነው። ይህም በአንድ ቀን የተገደሉት ሰዎች ቁጥርን በአማካይ ከ10-15 ሺህ አካባቢ ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት እንችላለን። የአዲስ አበባው የየካቲት 12 ጭፍጨፋ ግን ከሁለት ቀናት የሚዘል አልነበረም። በአንድ ቀን በፋሺስት ጣልያን ጭካኔ የረገፉት ወገኖቻችንን ቁጥር ከ15- 20 ሺህ ያጠጋጋዋል። ሌላው ደግሞ በዓድዋው ጦርነት ከሁለቱም (ከጣሊያንም ከኢትዮጵያም) የሞቱት ቁጥር በድምር ከ10 – 13 ሺህ ባለው ነው። ይህም በየካቲት 12 የተጨፈጨፉትን ንፁሃን ወገኖቻችን ቁጥር ከዓድዋው ከ 3 እጥፍ በላይ የሚልቅ እንዲሆን ያደርገዋል።

 አነዚህን የቁጥር አሃዞች ስንመለከት፤ የካቲት 12 ምን ያህል ለኢትዮጵያ ታላቅ የሐዘን እለት እንደነበረ፤ ለአዲስ አበባችን ደግሞ የመጨረሻው አሳዛኝ ጥቁር ዕለቷ እንደሆነ፤ ልንገነዘብ ግድ ይለናል።

፳፴

በዓድዋው የኢተዮ-ኢጣሊያ ጦርነት፤ ሪቻርድ ፓንክረስት The Ethiopians በሚለው መፅሃፋቸው ከገፅ 191 – 192 ላይ እንዳሰፈሩት፤ 6 ሺህ ጣሊያናውያን እና ከ3 እስከ 5ሺህ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን የጦርነቱ ሰለባዎች ሆነዋል።

 በጦርነቱ ህይወታቸው ላለፈ ሰዎች ክብር ሲባልም፤ ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አፄ ምንሊክ እስከ 7ኛ ዓመት ድረስ የዓድዋ ድል መታሰቢያ እንዳይከበር አድርገዋል።

 የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን ኩራት ብቻ ሳይሆን፤ በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ለነበሩ የአፍሪካ ህዝቦችም በጨለማው ዘመን ብርሃንን በመፈንጠቅ ታላቅ ተስፋን ያሰነቀ ልዩ ቀናቸው ነው።

የአፍሮ-ሴንትሪክ ምሁሩ ሞሊፌ አሳንቴ እንደሚሉትም፤ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ በመላው ጥቁር ህዝብ ልዩ የሆነ የክብር ቦታ እንዲሰጣት ዋነኛ ምክንያት ሆኗል።

 ፲፪ እና ፳፴

 የየካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ ከየካቲት 23ቱ የዓድዋ ድል ባላነሰ ልናከብረው የተገባ ነው። ከየካቲት 12ቱ በዓል የምንማረው፤ ከዓድዋ ድል ከምንማረው በየትኛውም መስፈርት አይተናነስም።

ምክንያቱም ታሪክ በመልካሙ እንደሚያስተምረን ሁሉ፤ በከፋውም ያስተምረናል። ታሪክ በአስደሳቹ እንደሚያስተምረን ሁሉ፤ በአሳዛኙም ያስተምረናል። ታሪክ ድል ባደረግንበት እንደሚያስተምረን ሁሉ፤ በተሸነፍንበትና በተዋረድንበትም ያስተምረናል። ከታሪክ በላይ መምህር ልናገኝ አይቻለንም።  የትላንትን ታሪክ ያለፈ፣ ያበቃለት፣… ብለን እንደዋዛ የምንተወው አይደለም። ለዛሬ ተምረንበት ለነገም የምናቅድበት ጭምር ነው እንጂ።

 “በአድዋ የተገኘው ድል፤ ለምን በማይጨው አልተደገመም?” ብለን ስንጠይቅ፤ ከታሪክ ምሁራን የምናገኘው መልስ “በዓድዋ ድል ጊዜ የነበረን አንድነት፤ በማይጨው ጦርነት ጊዜ ስላልነበረን” የሚል ነው።

 ከማይጨው ጦርነት በኋላ ባለው የአርበኞች ተጋድሎ ላይ ኢትዮጵያውያን በጀግንነቱ ረገድ ከአባቶቻቸው ባይተናነሱም፤ አንድ ሆኖ በኅብረት ጠላትን በመውጋት ላይ ግን በብዙ ይታሙ ነበር። ለዚህም ይመስላል ከግጥሞቻቸው መካከል በአንዱ ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ

 “…ሁላችንም ተሰባስበን – ካልረገጥን እርካብ

ነገራችን ሁሉ- የእንቧይ ካብ የእንቧይ ካብ…”

ሲሉ፤ ኢትዮጵያውያን ተባብረው የጋራ ጠላታቸውን እንዲዋጉ ጥሪ ያቀረቡት።

 እኚህ ታላቅ የኪነጥበብ ሰው እዚሁ ግጥማቸው ላይ ይህንን የእንተባበር ጥሪያቸውን ሲያቀርቡ፤ በዓድዋ የወደቁትን ጀግኖች ከተቀበሩበት አፈር አውጥተው አጥንት እስከመልቀም የሚያደርስ፤ በእውነታው ዓለም ሊደረግ የማይችል መሻታቸውን እስከማሳበቅ ደርሰዋል።

“…አጥንቱን ልልቀመው- መቃብር ቆፍሬ

 ጎበናን ከሸዋ- አሉላን ከትግሬ…”

ብለው፤ የእነሱን ኅብረትና ጀግንነት የያኔው ትውልድ አርበኞች እንዲደግሙት ከሃገር ፍቅር በሚመነጭ ልባዊ ምኞት በስንኞቻቸው የትውልድ አደራ የሚሆን ስንቅ አሸክመዋል።

 ይህ መልእክት ደግሞ ለያኔው ትውልድ ብቻ ሳይሆን፤ ለእኛ ለአሁኑ ትውልዶችም ታላቅ የሆነ ትርጓሜና እውነታ አለው። አጥንቱን መልቀሙ እንኳ ይቆየን ብንል፤ ለመተባበሩ ግን ልንሰንፍ የተገባ አይደለም። አሊያ ግን ከየካቲት 12ቱ የማይተናነስ ውርደት ዳግም ሊገጥመን ይችላል።

 የካቲት ወር ሁለት ገፆች ያሉት እና ብዙ የምንማርበት ነው። በእኛ በኢትዮጵያውያን መካከል ኅብረት ሲኖር ማንም እንደማያሸንፈን “የዓድዋ ድል” ሲያስተምረን፤ በመሃላችን መለያየት እና ጥላቻ ሲኖር የሚደርስብንን ውርደት ደግሞ የየካቲት 12 የአዲስ አበባ የፋሽስት ጭፍጨፋ በደንብ አድርጎ ትምህርት ይሰጠናል።

ስለዚህ በመሃላችን ልዩነት ቢኖርም በሃገር ጉዳይ ኅብረት ሊኖረን ይገባል። ከእኛ የተለየውን የሃገራችን ዜጋ፤ እንደራሳችን ዐይተን ልንወደው ልናከብረው ይገባል። ልዩነቶቻችን ውበት ሆነውን ለሃገራዊ ኅብረታችን እሴት መሆን እንጂ የመለያያ መድረክ ልናደርጋቸው አይገባም።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top