አድባራተ ጥበብ

የዘመናዊ ሙዚቃ መሳሪያዎች ትውውቅ

ኢትዮጵያ ከምዕራባዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች ጋር መተዋወቅ የጀመረችው የመጀመሪያው ሚሊኒዬም ከባተ አራት ምዕተ ዓመት በኋላ ነው። ወቅቱ ሀገራችን ከፖርቹጋል መንግሥት ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የመሰረተችበት ነበር። በዚህ የተነሳም የአውሮፓዊት ሀገር ሰዎች ለንጉስ በዕደ ማርያም (1468-1478) እጅ መንሻ ኦርጋን አበረከቱ። አጋጣሚው ብልጭ ብሎ የሚቆም ሳይሆን እየሰፋ የሚሄድ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት በአከባቢው ያለው የበላይነት እየሟሸሸ እስላማዊ መንግሥታት መውጫ መግቢያ ሲያሳጡት አውሮፓዊ የክርስትያን መንግሥታትን መማፀኑ የግድ ሆነ።

 አጼ ንበለ ድንግል ድንግል (1501-1540) ወዳጅ አላጡም። የቀደሙት ነገሥታት የጀመሩትን ቅርርብ  አጠናከሩ። ፖርቹጋሎች አሁንም ባዶ እጃቸውን ቤተ-መንግሥት ሊገቡ አልደፈሩም። ሮዲርጎ ዴሊማ የተባለው አምባሳዳር ሞኖኮርድ የተሰኘውን የሙዚቃ መሳሪያ ለእጅ መንሻ አቀረበ። ጦርነት የፈጠረው ቅርርብ ትውፊታዊውን የሙዚቃ መንገዳችንን በወቅቱ ሊገዳደረው አቅም ቢያጣም በጊዜ ሂደት ግን የሚፈለግ መሆኑ አልቀረም። በዚህ የተነሳም ምዕራባዊያኑ መሪዎች የሙዚቃ መሳሪያን ለሀገሬው ነገሥታት ማቅረብን ልማዳቸው አደረጉ።

ድዋ ድል ማግ

የዓድዋ ድል የጣሊያንን ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለምን የፖለቲካ ሂደት ተገዳድሯል። አዳዲስ አሰላለፎች እንዲፈጠሩም ምክንያት ሆኗል። ወዲህ ዳግማዊ ምኒልክን በጦር ሜዳ ውሎ ማሸነፍ ያልቻሉት ቀኝ ገዥዎች ዲፕሎማሲዊ ወዳጅነቱን ለማጠናከር ጥያቄን ያቀርቡ ይዘዋል። ከዚያ ወዲያ አፍሪካ እንደ ቅርጫ ለምዕራቡ ዓለም ስትከፋፈል የበት ተመልካች የነበሩት መንግሥታት ኢትዮጵያን አጋር ማደረግ ለአዲስ ስትራቴጂያቸው አዋጭ መሆኑን አስልተዋል።

የሩሲያው ዛር ኒኮላስ ከዚህ ወገን ናቸው። የፒተርስ በርጉ ሰው ግንኙነታቸውን ደረቅ ፖለቲካዊ ሊያደረጉት አልፈለጉም። የሀገራቸውን ቀይ መስቀል ልከው በዓድዋ ጦርነት የተጎዱትን ለማከምም የቀደማቸው ባዕድ ሀገር አልተገኘም። ከዚህ ቡድን ጋር ወደ ኢትዮጵያ የመጣው አሌክሳንደር ቡላቶቪች በድርሳኑ ላይ የሚነግርን እውነት ሩሲያ ኢትዮጵያን ለምን ፈለገቻት የሚለውን ሙግት ደርዝ ያስይዛል።

 “ለኛ ሐበሻ የሚከተሉትን ጥቅሞች ልትሰጥ ትችላለች። የመካከለኛው አፍሪካ እና ኢትዮጵያን የሚያሳይ ካርታ ላይ ዓይናችንን ብናሳርፍ ነጭ ባይ አጠገብ የእንግሊዝ ግዛት በሆኑት በግብጽና በታላላቆቹ የአፍሪካ ሐይቆች መካከል የምትገኘው ሰፊ፣ ሐብታምና ብዙ ሕዝብ የሚኖርበት መሬት በቁጥጥሯ ሥር በማድረግ ከዓመት ዓመት ግዛቷን የምታስፋፋው ሐበሻ ለእንግሊዝ ዋና ጠላት እንደምትሆን በቀላሉ መረዳት እንችላለን። እንግሊዝ ደግሞ የኛ ዋና ጠላት መሆኗ የታወቀ ነው። ስለዚህም የጠላታችንን ጠላት መርዳትና በተቻለ መጠን ሐበሻን ማጠናከር የእኛ ዋና ላማ መሆን አለበት።

ሩሲያ የቀኝ ገዥዎች ሽንፈት የእሷን ምኞት ለመተግበር አቋራጭ በመሆኑ የዓድዋ ድል ከማንም ሀገር  በላይ ያስደሰታት ይመስላል። በዚህ የተነሳም ለአርበኞች ህክምናን ለጤነኞች ደስታን ለመለገስ ተጣድፋለች። የጥቁር ህዝቦች የድል በዓል አንደኛ ዓመት በደማቅ ሆኔታ እንዲከበርም ከአዲስ አበባ ባልተናነሰ ጓጉታለች። ለዚህም 40 የሙዚቃ መሳሪዎችን ልካለች። ዛር ኒኮላስ የምዕራባዊያን ሽንፈት በጉልህ እንዲታወስ መፈለጋቸው፣ በአንድ በኩል ተቀናቃኞቻቸውን ለማብሸቅ ቢያስመስልባቸውም፤ በሌላ በኩል ዳግማዊ ምኒልክን የልብ ወዳጅ ለማድረግ የነበራቸውን ምኞትም ይገልጣል።

 ከሁለቱ የታሪክ እርሾዎች ወጣ ያለ አስተያየት የሚሰነዝረው ወገን ደግሞ የሙዚቃ መሳሪያዎቹ ጥያቄ ከኢትዮጵያ መንግሥት ቀርቦስ ቢሆን ብሎ ይሞግታል። የዚህ ሀሳብ ሰልፈኞች ለንጉሡ ቅርብ የነበረው ሊኦንቴቪ የተባለው ሰው አጼ ምኒልክን ሳያግባባቸው አልቀርም ብለው ያምናሉ። ከላይ ያለውንነመላምት ማጥራቱ የነገ የቤት ስራችን ቢሆንም ኮለኔል ኒኮላይ ሲቲፓኖቪች ሊኦንቴቭ ግን በድሉ ማግሥት የሩሲውን ንጉሥ ኒኮላስ ሁለተኛ ስጦታ ይዞ ከዳግማዊ ምኒልክ ፊት መቅረቡ እውነት ነበር።

በዚህ ወቀት ፒተርስበርግ ከጦር መሳሪያ ስጦታ በተጨማሪ አርባ ያህል የትንፋሽ ሙዚቃ መሳሪያዎችን ለአዲስ አበባ አበርክታለች። የዓድዋ ድል በታሪካችን ውስጥ አንዳንድ እያለ ለእጅ መንሻነት ይመጣ የነበረውን የምዕራቡ ዓለም የሙዚቃ መሳሪያ በተደራጀ መልክ እንድንተዋወቅ ብቻ ዕድል ፈጥሮ የሚያልፍ አልነበረም። ዝነኛው ሀገር አሳሽና ዲፕሎማት ሊኦንቴቪ ኢትዮጵያዊያኑን መልምሎ ሙዚቃን ለማስተማር እንቅስቃሴ ጀመረ።  ይሁን እንጂ በሀልዮም ይሁን በገቢር ለዚህ ሀሳብ  የሚሆን የሀገሬውን  ሰው  ማግኘት አዳጋች ሆነ።  

ጳውሎስ ኞኞ ሞንዶን ቪዳሌን ጠቅሶ እንደፃፈው የሙዚቃ ትምህርቱን አማራዎች አንማርም ስላሉ የወላይታ እና የቤንሻንጉል ጉምዝ ሰዎች ተመልምለዋል። ነገር ግን የምዕራባዊያን ሙዚቃ መሳሪያዎችን መንካት አይደለም ዐይተው የማያውቁት ኢትዮጵያዊያን የሊኦንቲቨን ስኬት አራቁት። ከጊዜያት በኋም ሚሊውስኪ የተባለ አዲስ መምህር ተመድቦ ለዓድዋ ድል አንደኛ ዓመት የሚደረገው የሙዚቃ ዝግጅት ቀጠለ። ሩቅ የሚባለው ቀንም ቀረበ።  የዓድዋ ድል ከሌላ ታሪክ ጋር ተሳሰረ።

ኢትዮጵያዊያን የምዕራቡን ዓለም የሙዚቃ መሳሪያ እየተጫወቱ ከንጉሡ ፊት ተሰየሙ።  ማርሴል የተባለው የፈረንሳይ ህዝብ መዝሙርም የስራቸው ማሟሻ ሆነ። አፍታ ሳይወስዱም “አምላክ ዛር ኒኮላስን ጠብቅልን” የተባለውን የሩሲያ ህዝብ መዝሙር ለማሰማት ቻሉ። የዓድዋ ድል አንድም የመጀመሪያውን የሀገራችን ዘመናዊ የሙዚቃ ባንድ ሲያስተዋውቀን፣ አንድም ዘመናዊ የሙዚቃ ትምህርት በኢትዮጵያ እውን እንዲሆን መሰረት ጥሏል። ተከታዩ የአጼ ምኒልክ ደብዳቤ ይህን የሚያረጋግጥ ነው። 

“ይድረስ ለጀነራል ብላስፍ

ከሞስኮብ አገር የመጡት ሁለት ሙዚቃ ነፊዎች ወደ ሐገራቸው መመለሳቸው ቢሆን የሞስኮብ መንግሥት ሙዚቃ ወድቆ እንዳይቀር ከእኔ ሁለት አሽከሮች ከእነዚያ ጋር ወደ ሞስኮብ መስደዴ ነው። የሙዚቃ ስራ እንዲጀምሩልኝ፣ ከትምህርት ቤት እንዲገቡልኝ፣ አንተ ለሞስኮብ መንግ  ሥት እንድታስታውቅልኝ እለምናለሁ። በሙዚቃውም የሞስኮብ መንግሥት መታሰቢያ። (ነሐሴ 1 ቀን 1889 . አዲስ አበባ)

የንጉሱ ተማፅኖ እንዲሁ የሚቀር አልነበርም። በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት  ጄነራል ብላስፋ ከመንግሥታቸው ጋር ተነጋግረው ለዳግማዊ ምንሊክ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ሰጡ። ይሁን እንጂ ንጉሡ ሕመማቸው እየበረታ በመሄዱ የደብዳቤያቸውን ፍሬ ለማዬት አልታደሉም።

ዓድዋ የጠረገው የሙዚቃ ፍኖት ግን ዛሬም አላንቀላፋም። አዕላፍት በዚህ ሀዲድ ይመላለሳሉ። ሺዎች በሳክስና ጊታር በትራንፔትና ኦርጋን እየታጀቡ ያዜማሉ። ይሁን እንጂ ጥቂቶች ብቻ አድዋን ይዘክራሉ።

አመድ አፋሹ

የዛሬ ሙዚቃችን የዓድዋ አብራክ ክፋይ ነው። ነገር ግን አባትና ልጅ ተኳርፈዋል። ምዕተ ዓመት የተሻገረው “ዘመናዊ” ሙዚቃችን ድላችንን ለመለፈፍ ይተናነቀዋል። ጀግንነታችን ለማሲንቆና ክራር ተጫዋቾች ከተውነው ውለን አድረናል። አሁንም ካሳ ተሰማ፣ ሜሪ አርምዴ፣ ለማ ገብረህይወት እና ከተማ መኮንን የካቲት 23 ሊያደምቁ አቧራቸው ተራግፎ ሲያንጎራጉሩ ይውላሉ። መቶ ዓመት የተሻገረው የአፍሪካዊያን ኩራት የእጅጋየሁ ሽባባውን አይነት “ዓድዋ” ሙዚቃ ለማግኘት ከምዕተ ዓመት በላይ መጠበቁን ስንመለከት ለዓድዋ ጀርባ የሰጠው እንቅልፋችን ዘላለማዊ ይሆን እንዴ ያስብላል።

ስጋታችንን የሚያነዝረው ግን ትናንት የተሰሩት ቁጥር ማነስ ብቻ ሳይሆን ባለፈው ዘመን ያባከነው ወርቃማ አጋጣሚም ጭምር ነው። የሀገራዊ ብሄርተኝነት የሙዚቃ ዘውግ አሁን ላይ ከኪን ሰገነቱ ላይ ወርዷል። እንደ ቴዎድሮስ ካሳሁን ያሉት ድምፃዊያን የሙዚቃ ሙግትም ከዓመታት እንዴ ብልጭ የሚል ሆኗል። ከዚህ ቀደም የነበረው ዓድዋን በሚመጥነው ደረጃ ለማክበር የሚካሄደው መንግሥታዊ ተነሳሽነትም የዕለት የመድረክ ጭብጫን ከመጠማት የዘለለ ፋይዳ አጥቷል። ይህ ደግሞ የዓድዋን ድል አመድ አፋሽነት ያረጋግጣል።ረርከባበትያኑወረከከከከከከ

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top