ጥበብ በታሪክ ገፅ

የአካለ ጉዛዩ ነብር

ደጃዝማች ባህታ ሓጎስ የአካለጉዛይ አስተዳዳሪ ነበሩ። ከሃብታም የገበሬ ቤተሰብ የተወለዱት ደጃዝማች ባህታ ሓጎስ፤ በኤርትራ ውስጥ የነበረውን የፀረ-ጣሊያን አገዛዝ እንቅስቃሴ ከመሩ ታዋቂ የጦር መሪዎች ውስጥ አንዱ ነበሩ። ህይወታቸው ያለፈውም የህላይ ጦርነት ተብሎ በሚታወቀው ውጊያ ከጣሊያን ሠራዊት ጋር ታላቅ ፍልሚያ ሲያደርጉ ታህሳስ 19፣ 1894 እ.አ.አ. ነው። (ከዓድዋው ጦርነት ሁለት ዓመት አስቀድሞ)

በብዙ መፃህፍት እንደ ተከስተ ነጋሽ NO MEDICINE FOR THE BITE OF A WHITE SNAKE በሚል ፅሁፋቸው እና ሪቻርድ ኮውልክ Between the Jaws of Hyenas በሚል ጽሁፋቸው ውስጥ፤ እንዲሁም ሌሎች ምሁራን የሰገነይቲ አመፅን እና የህላይ ውጊያን፤ በጣሊያን እና በኢትዮጵያ ለሚደረገው የዓድዋ ውጊያ እንደመነሻ ነጥብ በማድረግ ይገልፁታል። ለዚህም እንደምክንያት የሚያቀርቡት በጣሊያን በኩል ያለው የመስፋፋት ጉዞ ከዛም በኋላ የቀጠለ በመሆኑ ነበር። የጣሊያን ሠራዊትም ራስ አሉላንና ደጃች ባህታን አጥቶ ብቻውን ቀርቶ  የነበረውን የራስ መንገሻን ጦር እስከ አምባላጌ ድረስ ለመግፋት ችሎ ነበር። ስለዚህ እነኚህ ምሁራን ለዓድዋው ጦርነት የሰገነይቲን ዓመፅ እንደ አንድ መነሻ ይመለከቱታል።

ደጃዝማች ባህታ ሐጎስ የአካለጉዛይ አስተዳዳሪ የነበሩበት ዘመን፤ ከባድ የሆነ ውጥረት ያለበት ነበር። ጣሊያን፣ ግብፅ፣ መሀዲስቶች፣ ኢትዮጵያውያን በአካባቢው ላይ ከፍተኛ የሆነ ተፅዕኖ እያሳደሩ በነበረበት በዚያ ዘመን፤ የአካለጉዛይ አስተዳዳሪ የሆኑት ደጃዝማች ባህታ ሐጎስ ምን ዓይነት ውጥረት ውስጥ ሆነው አካባቢውን ያስተዳድሩ እንደነበር ለመገመት አይከብደንም። ደጃዝማች ባህታ ውጥረቱ እየበዛባቸው ሲመጣ በከረን ከሚገኘው የግብፅ ሠራዊት ጋር ተቀላቀሉ።

 ኪልዮን ቶም በ1998 እ.ኤ.አ የጻፈው Historical Dictionary of Eritrea በሚለው መጽሐፉ ክስተቱን እንዲህ አብራርቶታል “በ1885 (ሁሉም ዓመተ ምህረቶች እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር ናቸው) የጣሊያን ቅኝ አገዛዝ ተስፋፍቶና ግብፆችንም በማሸነፍ ከአካባቢው እንዲለቁ አደረገ። በዚህም ጊዜ ባህታ ሐጎስ ከግብፅ ጋር ያላቸውን ኅብረት በመተው ለጣሊያን አደሩ። ያኔ ጀኔራል የነበረው ኋላ ላይ የኤርትራ ክፍለ  ሃገር ገዢ ከሆነው ኦሬስቴ ባራቴሪ ጋርም ኅብረት ፈጠሩ።”

ሲልቭያ ፓንክረስት በዚህ ርዕስ ላይ ብቻ ባተኮረው “Eritrea on the Eve: the Past and Future of Italy’s ‘first-born’ colony. Ethiopia’s Ancient Sea Province”. የሚል ርዕስ በሰጡት ጥናታቸው “ጣሊያኖች ይህንን ያደረጉት ኤርትራውያን በኢትዮጵያ ስር እያሉ ከነበራቸው የተሻለ ነፃነት ከሰጠናቸው ይገዙልናል በሚል ተስፋ ነበር። በዚህም ሳቢያ ደጃዝማች ባህታ አካለጉዛይን እንዲያስተዳድሩ በማድረግና ሌሎች መሰሎቻቸውንም በመጨመር፤ ጣሊያን “ኤርትራ” የሚባለውን ቅኝ ግዛት ፈጠረች። ኤርትራ የቀይ ባህር መጠሪያ ስም እንጂ የሃገር አልነበረም። ባህረ-ነጋሽ የሚለውን ኢትዮጵያዊ መጠሪያ በመተው፤ ‘ኤርትራ’ በሚለው መጠሪያ አካባቢውን ጣልያን የሰየመበት ምክንያት ለአገዛዝ እንዲመቸው በማሰብ ነበር። ”

ደጃዝማች ባህታ ሐጎስ፤ ጣሊያኖች ከማሀዲስቶች ጋር ባደረጉት የዓቑርደት ጦርነት (ታህሳስ 1893) ላይ ከጣሊያን ጎን ተሰልፈዋል። እንዲያም ሆኖ ግን በጣሊያን ቀኝ ገዢ መንግሥትና በጣሊያን ወታደሮች ላይ ቅሬታ ማሳደር ጀመሩ። በተለይም የቤተክርስቲያን መሬት መወረስ ከፍተኛ ቅሬታ አሳደረባቸው። ምኒልክ ወደደቡብ የሚያደርጉት ዘመቻ ከጣሊያን ጋር ለሚኖራቸው አይቀሬ ግጭት በማሰብ እንደሆነም መረዳት ጀመሩ። እ.አ.አ. በሰኔ 1894 ራስ አሉላና ራስ መንገሻ ለምኒልክ አንዳደሩ ለማረጋገጥ ወደአዲስ አበባ ሲሄዱ፤ ደጃች ባህታም አብረው በመሄድ ከባራቴሪ ጋር መስራታቸው ስህተት መሆኑን በመረዳት ንጉሠ ነገሥቱን ይቅርታ ጠየቁ። ምኒልክም ደጃች ባህታን ይቅር ብለው፣ ራስ መንገሻንም የትግራይ ገዢ አድርገው ሾመው አሰናበቷቸው። ራስ አሉላን ግን ሸዋ እንዲቀር አደረጉ።

 የሰገነይቲ ዓመፅ

በታህሳስ፣ 1894 ባህታ 1600 የሚሆኑ ሠራዊቱን ይዞ በጣሊያን ጦር ላይ አመፀ። የአካለጉዛይ አካባቢ ዋና ከተማ የሆነችው ሰገነይቲን በመቆጣጠር ዋና አስተዳዳሪዋንም አሰረ። የአካለጉዛይ ነፃ ግዛትን በማወጅ ራሱን “በጣሊያኖች የደረሱ በደሎች ተበቃይ” በማለት ሾመ። ጣሊያናዊው አስተዳዳሪ ሲያዝ “ጣሊያን ታላቅ ናት!” ሲል፤ ባህታ ደግሞ “ኢትዮጵያ የበለጠች ታላቅ ናት!!” ሲሉ መልስ ሰጡት።

ሲልቪያ ፓንክረስት ከላይ በተጠቀሰው ጥናታቸው አካለጉዛይ አካባቢ ለነበረው ህዝብ “ጣሊያኖች አዋረዱን፣ መሬታችንን ነጠቁን፣ እኔ ነፃ አወጣችኋለሁ። […] ጣሊያኖችን እናባርርና የራሳችን ገዢዎች ራሳችን እንሁን” የሚል ጥሪያቸውን አቀረቡ።” ማለታቸውን ጽፈዋል።

 ከሰገነይቲ አስመራ የሚያገኛኘውን የቴሌግራፍ መስመር በመቁረጥም የጣሊያኖችን የመረጃ ልውውጥ በማስተጓጎል፤ በቂ የሆነ ሠራዊት ለማደራጀት የሚያስችላቸውን ሰፊ ጊዜ አገኙ። ራስ መንገሻን ወደጦርነቱ ገብተው እንዲተባበሯቸውም መልእክተኛ ላኩባቸው። ጀኔራል ባራቴሪ ግን የራስ መንገሻን ያልተለመደ እንቅስቃሴ ለማስተዋል ስለቻሉ፤ በማጆር ቶዜሊ የሚመራ አንድ ባታሊዮን ጦር ወደሰገነይቲ ላኩ።

ማጆር ቶዜሊ ሰገነይቲ እንደደረሰ ከባህታ ጋር ድርድር ጀመረ። በይቅርታ በተሞሉ ሰበባ ሰበቦች፣ በመደለያዎችና በማባበያ የቃል ተስፋዎች ሊያታልላቸው ሞከረ። ቶዜሊ ይህንን እያደረገ ባለበት ተጨማሪ 1500 የጣሊያን ሠራዊትና 2 መድፈኛ ቡድን ከአካባቢው ደረሰ። ቶዜሊ ባህታ ይገኛል ብሎ ወዳሰበበት ቦታ ጥቃት ከፍቶ ሲደርስ፤ ደጃዝማች ባህታን ከቦታው አጣቸው። ምክንያቱም ባህታ ሠራዊቱን በመያዝ ማታ ተጉዞ ‘ህላይ’ ከሚባለውና፤ በካፒቴን ካስቴላዚ የሚመራ 220 የጣሊያን ወታደር ወደመሸገበት ቦታ ማቅናቱ ነበር። የባህታ እቅድ በምሽጉ ያሉትን ጣሊያኖች  መደምሰስና ምሽጉን በመቆጣጠር፤ የራስ መንገሻ አጋዥ ኃይል እስኪመጣ በደንብ እየተከላከሉ ለመቆየት ነበር። ማጆር ቶዜሊ በባህታ ብልጠት መበለጡ በጣም አበሳጨው። ዕድል ፊቷን አዙራለት ስለነበር ግን የባህታን ቀጣይ እርምጃዎች በትክክል ለመገመት ቻለ። 

የህላይ ውጊያ

ባህታ በምሽጉ ሠራዊቱን ይዞ የተደበቀውን ካፒቴን ካስቴላዚን በሰላም እጁን እንዲሰጥ አግባባው። 7፡30 ሲል የባህታ ትዕግስት ስላለቀ በካስቴላዚ ላይ ጥቃት እንዲከፈት ትእዛዝ ሰጠ። በምሽጉ የነበሩ ጣሊያኖችም እስከ 10፡45 ድረስ አቅማቸውን አሟጠው ተከላከሉ። ምሽጉ የመያዙ ጉዳይ አይቀሬ መሰለ። ጣሊያኖቹም ደጃዝማች ባህታ ያቀረበላቸውን አማራጭ ባለመጠቀማችው መፀፀት ጀምረዋል። ድንገት ግን የኃይል ሚዛኑን 180 ዲግሪ የሚገለብጥ፤ በምሽግ ውስጥ ላሉ ጣሊያኖች ተአምር፤ ለእነ ደጃዝማች ባህታ ደግሞ ዱብ እዳ የሆነ አጋጣሚ ተከሰተ። ሌሊቱን እና ቀኑን ሙሉ ደጃዝማች ባህታን ፍለጋ የባተለው ማጆር ቶዜሊ ከቦታው ደረሰ።

 የደጃዝማች ባህታን ሠራዊትን ከኋላ ማጥቃት ጀመረ። የደጃዝማች ባህታ ሠራዊት ከፊትና ከኋላ የሚደርስበትን ጥቃት መቋቋም ተስኖታል። የራስ መንገሻ ሠራዊት ደግሞ በጀነራል ባራቴሪ መንገድ ተዘግቶበታል። በራስ መንገሻና በደጃች ባህታ ሐጎስ መካከል የነበረው የመረጃ ልውውጥ የተሳለጠ አለመሆን ሁለቱንም አደጋ ውስጥ ከቷል። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የኢትዮጵያውያን የመረጃ ልውውጥ በዘመኑ ቴክኖሎጂ ከሚታገዘው ከጣሊያኖች የመረጃ መለዋወጫ መንገድ ጋር ሲነፃፀር የዘገየ በመሆኑ ነበር። ጫናው እየጨመረ ሲመጣ የደጃዝማች ባህታ ሠራዊት ተፈታ። የደጃች ባህታ በአልበገርም ባይነት እስከመጨረሻው የህይወታቸው ፍፃሜ ድረስ ተዋግተው ተሰዉ። የተፈታው የባህታ ሠራዊት ጀግና አርበኞችም፤  በምሽት ተጉዘው ከራስ መንገሻ ሠራዊት ጋር ተቀላቀሉ። የራስ መንገሻ ሠራዊት ከዛ በኋላ በኳዓቲት ጦርነት ሊሸነፍ ችሏል። ምኒልክ የክተት አዋጅ አውጀው እስከሚዘምቱበት ጊዜ ድረስም የኢትዮጵያን ድንበር በተቻለው ያህል ለ2 ዓመታት እስከሚሆን ጊዜ ለመከላከል ሞክሯል። በምኒልክ የሚመራው የኢትዮጵያ ጦርም የደጃች ባህታን መስዋእትነት በመቀሌው ውጊያ ማጆር ቶዜሊን በመግደል በሚገባ ተበቅሏል።

 የደጃዝማች ባህታ ተጋድሎ ከፍ ያለ ስለነበር፤ ቅኝ ገዢው የጣሊያን መንግሥት እንዳይቀበሩ አገደ። በገበያ መሃል ለረጅም ጊዜ ሬሳቸውን ሰው እንዲያየው ከተደረገ በኋላ፤ በምስጢር ህላይ አካባቢ እንዲቀበሩ ተደረገ። ይህ የሆነበት ምክንያት የሰገነይቲውን አመፅ እሳቸው ስለመሩት እና የተቀበሩበት ከታወቀ፤ ለመጪ አመፆች መነሳሻ እንዳይሆን ከሚመነጭ የጣሊያን ስጋት ነበር። በ1953 ሬሳቸው ወደሰገነይቲ ተመልሷል። ERITREA PROFILE የተሰኘው በእንግሊዘኛ ልሳን የሚሰራጨው ጋዜጣ በቅዳሜ ማርች 10፣ 2007 እትሙ እንደገለፀው፤

 ደጃዝማች ባህታ ሐጎስ (አባ ጥመር) ከተው 113 ዓመታት በኋላ በማርች 4፣ 2007 ኤርትራ ውስጥ ሰገነይቲ በተባለው ታሪካዊ ስፍራ የመታሰቢያ ሐውልት እንደቆመላቸው ዘግቧል። በእለቱ ታላላቅ ባለስልታናት በተገኙበት በወታደራዊ ክብር ታስበው ውለዋል። ያለው በኤርትራ የሚሰራጨው ጋዜጣ ቅሪታቸው በፊት ከነበረበት ሕላይ ወደ ሰገነይቲ የተዘዋወረው በ1953 ጃንዋሪ ላይ መሆኑን አስታውሷል።

ብዙዎች “ጣልያን ታላቅ ናት” ለሚለው የጣልያናዊው መፈክራዊ ማስፈራሪያ ኢትዮጵያ የበለጠ ታላቅ ናት በሚለው ምላሻቸው ያስታውሷቸዋል። የኤርትራው ተወላጅ ባህታ ሐጎስ ከዓድዋ ጦርነት በፊት ታሪክ የማይዘነጋው ገድል የፈጸሙ ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን ማሳያ ናቸው።

በባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ከተጻፈው ‹ዘርአይ ደረስ› ቲያትር ጥቂት መስመሮች በመዋስ የረጅሙን ታሪክ አጭር ምልከታ ልደምድም።

 …ያላባቴ ያለቅርሴ- እኮ ማነው የበከለኝ

ይህን የመንፈስ ዝቅጠት- ማን አባቱ ነው የካነኝ

ከቶም አልነበር በአበው ዘር

 ይህን የመሰል የዝቅጠት ሥር

 የባህታ ሐጎስ አጽም ይመስክር ይመስክር

 ያ ደገኛወ ወንድ፤ የአካለ ጉዛዩ ነብር

 ይመስክር የህላይ ምድር

 ባህታ የበረከኞች ጓድ፤ ሕዝባዊነቱን የማይጥል

 የነሳንጎኒቲ ጌታ፤ “ጣልያን ኃይል የት” ብሎ ሲል

 የኢትዮጵያን የበላይነት፤ በቡጢ ከንትሮ እሚያስምል

 በአንበሳ ክንድ እንደየሎስ

 ጀርባ ሰባሪ በመደቆስ

 የነባላቲየር ጦስ

 የነካርሲሊቲን ጌታ፤ ይመስክር ባህታ ሐጎስ…

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top