ታሪክ እና ባሕል

ዓድዋ የሀገራዊነት ትርጓሜ አስኳል!

ታሪካችን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ውጣ ውረዶች የሞሉበት ነው። ሦስት ሺህ ዘመን ከተሻገረው የታሪካችን ምዕራፍ ውስጥ ከ18ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ አንስቶ እስከ 19ኛው አጋማሽ ባለው ጊዜ ሀገራችን ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት አልነበራትም። በየአካባቢው በተነሱ መሳፍንት የእኔ እበልጥ አንተ ታንስ ፉክክር ስትናጥ “ዘመነ መሳፍንት” በሚል በሚታወቀው ዘመን ቆይታለች። ሁኔታው በዓለም ፈጣን ለውጥ ላይ ተሳታፊ እንዳትሆን ብቻ ሳይሆን ጥሩ ተመልካች እንዳትሆንም አድርጓታል።

ያ ጊዜ በዓለም ታሪክ ውስጥ የአብዮት (Age of Revolution: 1774-1849 እ.አ.አ) (በተለየ ሁኔታ ካልተገለፀ በቀር ሁሉም ዓመተ ምህረቶች በጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን ቀመር የተቀመጡ ናቸው) በመባል የሚታወቅ ነው። በተለይ አሜሪካ እና አውሮፓ ከፍጹም ዘውዳዊ ስርአት ወደ ሕገ-መንግሥት እና ሪፐብሊክ አስተዳደሮች የተቀየሩበት ነው። በዚህም አሜሪካ (1765- 1783)፣ ፈረንሳይ (1789 – 1799)፣ የአይሪሽ አመፅ (1798)፣ የሃይቲዎች በፈረንሳይ ቅኝ ግዛትና ባሪያ ንግድ (1791- 1804)፣ የባሪያዎች አመፅ በደቡብ አሜሪካ፣ የመጀመሪያው የጣልያን የነፃነት ጦርነት (1848- 1849)፣ የሲሲሊያኖች (1848)፣ እና በጣልያን (1848)፣… እነዚህ እና እነዚህን መሰል አመፆች እና አብዮቶች ተካሂደዋል። የወቅቱ እንቅስቃሴ የዓለምን ህዝብ አኗኗር በመለወጥ ረገድ ጉልህ ሚና ነበረው። ለከተሜነት ሕይወት መስፋፋት እና ለዘርፈ ብዙ ለውጦች ትልቅ ግብአት የሆነው የኢንዱስትሪ አብዮት (1760- 1840) በ18ኛው ክፍለ ዘመን የምክንያታዊነት (Age of Reason) አልያም የአብርሆት ጊዜ (Age of Enlightment)ን ተከትሎ እንደመጣ ማስተዋል ያስፈልጋል።

ከዘመነ መሳፍንት ወደ አንድ ጠንካራ ማእከላዊ መንግሥት ምስረታ የመሸጋገር ጉዞው የተጀመረው በአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት (1855- 1868) ነው። በአጼ ተክለ ጊዮርጊስ II (1868- 1871) ተሞክሮ፣ በአጼ ዮሃንስ IV (1871- 1889) ተጠናክሮ እና በአጼ ምኒሊክ II (1889- 1913) ዳብሮ ኢትዮጵያ ወደ ቀደመ የሥልጣኔ ታሪኳ ሳትመለስ፣ ግማሽ ክፍለ-ዘመን ሳይሞላ፣… ከውጭ ኃይሎች ጋር ጦርነቶች ገጠመች።

ከግብፅ (ጉራዕ /1874- 1876/፣ ጉንደት /1875/) እና ከመሃዲስቶች (ሱዳን) (1889) ጋር ያደረገችው ጦርነቶች ተጠቃሽ ናቸው። ከጣልያን ጋርም ተደጋጋሚ ጦርነቶችን ገጥማለች። በዶጋሊ (1887) ያሸነፈችበት ጦርነት ከመካከላቸው አንዱ ነው። ከጦርነቶቹ ሁሉ በስፋቱ እና በተፅእኖው ጥንካሬ ቀዳሚው ግን የዓድዋ ጦርነት ነው።

ጣሊያን ለምን መጣ?

በ1831 በጁሴፔ ማዚኒ (Giuseppe Mazzini) የተጀመረው ጣልያንን አንድ የማድረግ እንቅስቃሴ ፍሬ አፍርቷል። ከውስጥ የርስ በርስ እና ከውጭ ኃይሎች ጋር ከነበራት ዘርፈ ብዙ ችግሮች በተወሰነ መንገድ መውጣት የቻለችበት ወቅት ነበር። ከአቻዎቿ ጋር መፎካከር፣ ኃያልነቷን ማሳየት የምትሻበት ወቅት ነው። ለአላማዋ ቆርጣ የተነሳችው ጣሊያን በ1869 የስዊዝ ካናል (Suez Canal) መከፈት ተከትሎ የመጀመሪያዋን የቅኝ ግዛት ጉዞ በአፍሪቃ ሐምሌ 05፣ 1882 አሰብን በመያዝ ጀመረች። በ1885 ደግሞ በበርሊን ኃያላን የአውሮፓ አገሮች አፍሪካን ለመከፈል ስምምነት ላይ መድረሳቸው ጉዞዋ ‘ሕጋዊ’ እውቅና እንዲኖረው አግዟል።

የጥያቄው አጭር መልስ ቅኝ ለመግዛት የሚያክል ነው። ቅኝ መግዛት በውስጡ ብዙ ነገሮችን ይይዛል። ጦርነቱ በኃይል ላይ ብቻ ሳይሆን ኃይሉን መከታ ያደረገ የፍላጎት/ቶች ጦርነት ነው። ይህ ጦርነት የፍላጎት/ቶች ውክልና ጦርነት ነው። ጦርነቱ መንገድ (means) አንጂ መጨረሻው (End) አይደለም። አባቶቻችንም ጦርነትን የገጠሙት በውጭ (explicitly) የኃይል ቢመስልም በውስጡ (Implicitly) ፍላጎቶችን ጭምር ነው የተዋጉት።

ጦርነቱ የመግዛትና ያለመገዛት፣ በመገዛት የሚገኝ ጥቅምን ለማስጠበቅና በመገዛት ከሚመጣ ሁለንተናዊ ውርደትና ዝቅጠት ከመዳን፣ ታሪክ ከመስራትና ታሪክን ከማስጠበቅ፣ አዕምሮን የመቆጣጠርና አዕምሮን ነፃ ከማድረግ፣ባሕልን የማስፋት የሌላውን የማጥፋት (ካልተቻለ የማዳከምና የመበረዝ) እና ባሕልን የማስጠበቅ፣ ሰዎች ለራሳቸውና ከዓለም ግንኙነት ጋር ያላቸውን ዕይታ መቆጣጠርንና ራሳችን በምንፈልገው መንገድ ዓለምን ለማየት የመታገል ወዘተ… ጋር በየወገኑ የተደረገ ነው።

በዚህም ሂደት የውጫሌ ስምምነት አልያም በነጠላ (specifically) የ17ኛው አንቀጽ ትርጉም ጉዳይ መቀስቀሻ መሪ መነሻ (immidiate cause) እንጂ ጦርነቱ ከስምምነቱ የላቀ ነው።

በጦርነቱ ብዙ ሺ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ የመጣ ኃይል ታሪካዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ቀን ከለሊት ከተጋ ኃይል ጋር ተፋጦበታል። የወቅቱ የሀገራችን ሥርዓተ-መንግሥት ለረዥም ዘመናት እንደነበረው በንጉሠ-ነገሥት ይመራ ነበር። በአንፃሩ ጣልያናዊያን በሂደት ባዳበሩት ሥርዓተ-መንግሥት ተቋማዊነትን ማዕከል አድርጎ በሚንቀሳቀስ ኃይል በመመራት መምጣታቸው ይታወቃል።

ይህንን እውነታ አለመዘንጋት ያስፈልጋል። ለምን ቢሉ የኃይል አሰላለፉን ለመረዳት ብሎም ማን ከማን? ምን ከያዘ ኃይል ጋር?… እንደተጋጠመ መረዳት ይቻላልና ነው። በዚህም ትርጉም ባለው መንገድ አሸናፊነትን ከአሸናፊነት ሂደት ጋር ለመረዳትና የአሸናፊነቱን ከፍታና ልዩነት ለመረዳት የሚያሰችል ይሆናል።

በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ በንጉሠ-ነገሥት ዘ-ኢትዮጵያ አጼ ምኒሊክ II የተመራው የአባቶቻችን ጦር በየካቲት 23፣ 1896 ዓ.ም. በተደረገው ጦርነት ወራሪውን ኃይል ዓድዋ ላይ ድል በማድረግ የዓድዋን ጦርነት በድል እንድናጣጥም አድርጓል።

ድሉም ከላይ እንደተቀመጠው ድንበርን የማስከበር፣ ሉዓላዊነትን የማስጠበቅ፣ ነፃ ፈቃድን የማረጋገጥ፣… ብቻ ሳይሆን ካለማስከበር፣ ካለማስጠበቅና ካለማረጋገጥ አሉታዊ ገፅታዎች ራስን ብቻ ሳይሆን ትውልድን ጭምር የመታደግ ድሎችን ለማጣጣም ያስቻለ ታላቅ ድል ነው።

ዓድዋ ምናችን ነው?

ኢትዮጵያውያን እነማን ናቸው? ኢትዮጵያዊነት ምንድነው? ተብለን ብንጠየቅ አልያም ሌሎች ቢጠየቁ፤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለራሳችንም ሆነ ከኛ ውጪ ላሉ መሰሎቻችን የምንመልሳቸው መልሶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሀገራዊነት ዕይታ ስንመለከተው ዓድዋን የምናነሳበት ብዙ ምክንያቶች አሉን።

አንድን ሰው በነጠላ ለማወቅ፡- የህይወት ፍላጎቱን ማወቅ፤ ደካማና ጠንካራ ጎኑን መረዳት፤ ለራሱ ያለውን እና ሌሎች እርሱን የሚመለከቱበትን ዕይታ መገንዘብ አስፈላጊ ነው። የአንድ ሀገር ህዝብም የትላንት ማንነቱ፣ የዛሬ ሁለንተናዊ አኗኗሩ እና የነገ ነጠላና የጋራ ፍላጎቱ እርሱን የማወቂያና የመተርጎሚያ ትልቅ መሣሪያዎች ናቸው።

ስለሆነም እንደ ሀገር ዓድዋ እኛነታችንን መመልከቻ መነፅራችን፣ የማስታዋወቂያ አምዳችን ነው። ነገሮችን በሁለንተናዊ አቅጣጫ የመተንተኛ መንገዳችን፣ ራሳችንን ከተቀረው ዓለም ጋር የማስተሳሰሪያ ገመዳችን ነው። የባለቤትነት ስሜት የማዳበሪያ ሀብታችን፣ (በአዎንታዊ ብቻ ሳይሆን በአሉታዊም) በተለይ ከኤርትራ ጋር ተያይዞ ለሆነውና እየሆነ ላለው የቁጭታችን ምንጭ ነው። ትናንትን ከዛሬ፣ ዛሬን ደግሞ ከነገ ጋር የማስተሳሰሪያ ድልድያችን ነው።

በሌላ በኩል ዓድዋ ሌሎች ለእኛ ያላቸውን ዕይታ ቀይሯል። የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ለመሆን የቻልነው ከሌላው የበለጠ ኢኮኖሚያዊ አቅም ስለነበረን አልያም ፖለቲካዊ ተፅዕኗችን ስለበረታ አልነበረም። የዓድዋ ድል ለኛ የሰጠን ህዝባዊና ትውልዳዊ የአሸናፊነት ስሜት፣ ሌሎች ደግሞ በአንጻሩ ለዛ ዕውነታ የሰጡት ይሁንታ በወቅቱ በነበሩ መሪዎቻችን ትጋት እንደተገኘ ስናስብ ዐቢይ ድርሻውን የሚወስደውና ለመሪዎቻችን ሸክም ያቀለላቸው፣ ሌሎች አይሆንም እንዳይሉ ያከበደባቸው ዓድዋና የዓድዋ ድል ተፅዕኖ እንደሆነ ማስተዋሉ ተገቢ ይሆናል።

ዓድዋ ደቡብ አሜሪካውያን በስፋት እንዲያውቁን እና ከኛ ጋር የቀረቤታ ስሜት እንዲሰማቸው አስችሏል። ትውልዶችን መሻገር የቻለ፣ በበርካታ ዓለም አቀፍ የተማሪዎችና የነፃነት ትግሎች ውስጥ አርማ፣ መለያና አብነታዊ መሆን የቻለ ድል ነው። በርካታ ሀገራት የሀገራዊ ማንነት ትንታኔ ማሳያ በመሆን ሀገራዊ ባንዴራቸውን ከኛ ጋር እንዲያመሳስሉ አስችሏል። ድሉ ከሀገራዊነት ባሻገር ወደ ዘር ከፍ ብሎ በየትኛውም ዓለም የሚገኙ ጥቁሮችና የነፃነት ታጋዮች ማሸነፍ እንደሚቻል የተረዱበት ነው። William Du Bois: “ድሉ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኙ ጥቁሮች በዘረኝነትና በጭቆና ላይ የተደረገ የራሳቸው ድል አድርገው ወስደውታል።” ያለው ለዚህ አባባል ዐቢይ ምስክር ነው።

በሀገር ውስጥም ቢሆን ሰሜኑን ከደቡብ፤ ምዕራቡን ከምሥራቅ – ማዕከሉን ከተቀረው አካባቢ ጋር የተሳሰረ ስለመሆኑ ማስተሳሰሪያ ዐቢይ ነጥብ ስለመሆኑ ማንም የማይስተው ታላቅ ዕውነት (Truth) ና ዕውነታ (Reality) ነው።

ዓድዋ ከየትኛውም የሀገራችን ታሪካዊ ፍፃሜ በላይ የርስ በርስ ትስስር የመፍጠሪያ ዐምድ ነው። ራስን ለራስም ሆነ ለሌላው ብሎም ከሌላው ጋር ለማነፃፀር የሚያስችልና ያስቻለ ነው። በዐቢይ ትርጓሜውና በተሻጋሪ ኹለንተናዊ ተፅዕኖው ደግሞ ለሀገራዊነታችን ትርጓሜ አስኳል መሆኑ የማይካድ ሃቅ ነው።

ፈጣሪ ሀገራችን ነፃ ፍቃድን የሁሉ ነገር ማዕከል ወደሚያደርግ የእሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top