ታዛ ወግ

ዓድዋ ዛሬ ቢሆን ኖሮ!

ጣልያን ዘግይቶ ቢሆንና አሁን ባለንበት ጊዜና ዘመን ቢመጣ፣ የሚል ሐሳብ ድንገት ሽው አለብኝ። የአስቂኙን ሐሳብ አስደንጋጭ መልሶች እያሰብኩ በመዝናናት ላይ ነኝ። ተከተሉኝ!

ዓድዋ ዛሬ ቢሆን፣ ሀገር የማዳኑ ታሪክ በዛሬ ዘመነኞች ላይ ቢወድቅ፣ እውነት ይህ ወጣት ከጫት ቤት ወጥቶ ይዘምት ነበር? ብዬ ጫት እየቃምኩ አሰብኩ፡፡

ጣልያናዊ ለመሆን ስል ጦርና ጋሻ ሳይሆን አበባ ይዤ እጠብቅ ነበር? እናቶችስ የምናውቃትን መፈክር ይዘው ኤርፖርት ከወር በፊት ይቆማሉን? ወይንስ… እንደቀድሞው ማማሰያ ሸክፈው ወንዱን እያነሳሱ ይዘምቱ ነበር? ለነገሩ ልጆቻቸው ጣልያን ይዘዋቸው ከሔዱ ሰነበቱ። ከየት ወደየት ይዝመቱ?

እነ ባራቴሪስ ቢሆኑ የትግል ስትራቴጂያቸውን ከዘር ጨራሽ ወደ ዘር ቆጣሪ ይቀይሩ ነበር። የእንትን ብሔር ነፃ አውጭ ሆነው ይመጣሉ። የፈረደበት መስቀል አደባባይም ካሳለፋቸው መስቀለኛ ታሪኮች አንዱ ተብሎ የሚመዘገብ አቀባበልም በተደረገ ነበር። ከሰብአዊነቱ በፊት ብሔሩን ያስቀደመ ንፁህ ነኝ ባይ በመስቀለኛው መንገድ ኑሮ አመሳቃይ ቦንብ ሐሳብ በወረወረ ነበር።

ጀግንነታቸውን ያፀደቅንላቸው ሰዎቻችን ሳይቀሩ በሴት ጭን ውስጥ ተሸጉጠው ሽጉጥ ቀርቶ ሀሳብ መተኮስ ባቆሙበት ወቅት ዓድዋ ዛሬ ቢሆን…? እንደቀደምቶቼ ድንጋይ አልወረውርም፣ ጦር የመወርወር ወኔም የሚኖረኝ አይመስለኝም፤ ይልቁኑስ ቆንጆ ቆንጆ ጣልያናዊያን እንስት እየፈለኩ ራሴው እንደምወረወር ባለሙሉ ተስፋ ነኝ።

ካልተወሻሸን የሴቶቹም ተመሳሳይ ነው። የጓዳ ጉድጉዳቸውን ትተው፣ ለታጋዮች ቀለብ ሸክፈው፣ ወንዱን የሚያነሳሱ፣ ልጆቻቸውን መርቀው፣… ወደ ትግል ዘመቻ የሚልኩ አይኖሩም። ይልቅ እነ አንቶኔሊን ለማማለል፤ ኩል ተኩለው፣ ሜካፕ ተቀብተው፣ ሒውማን ሔር ተሰፍተው፣… ወዲያ ወዲህ የሚሉ ይበረክታሉ። እነ አንቶኔሊም በሴቶቻችን ውበት ተማርከው ሳይገዙልን አይቀርም እንጂ፤ በዚህ ጊዜና በዚህ ዘመን ዓድዋን ማሰብ ለእኔ ይከብደኛል። እናንተ አይከብዳችሁም?

የቅድመ አያቴን የጀግንነት ባህል፣ ሀገር ወዳድነት፣ ለክብር መሞት፣… እያወራሁ ዓድዋን ማሰብ ይከብደኛል።

ከዕለታት አንድ ቀን ጣሊያን ነበርኩ። ለትምህርት በሄድኩበት ሀገር ካገኘሁት የሐገሬው ሰው ጋር ስለ መጣሁበት ሀገር በማውራት ላይ ሳለሁ በንግግራችን መኻል፣

“አባቴ ጀግና ነው። ጣልያንን በባዶ እጁ ታግሎ አሸንፏል” አልኩት። ጣልያናዊው ወዳጄ ጭንቅላቱን በአሉታ እየነቀነቀ “እውነትም የተከበሩ አባት አሉህ ግን…” ብሎ ትንፋሽ ወሰድ አደረገ። ከግራ መጋባቴ በቅጡ ከመመለሴ በፊት የስላቅ ፈገግታ እያሳየኝ “ታዲያ ምን ያደርጋል ያንተን ዓይነት እንከፍ ወልደው ረከሱ እንጂ” ብሎ ኩም አደረገኝ። ሐፍረቴን ተከናንቤ “እበትም ትል ይወልዳል…” ልለው አሰብኩና ተውኩት። ማን በራሱ ጎል ላይ ግብ ያስቆጥራል?

…ንግግሩ ንቀትም መሰለኝ፣ ቅናትም መሰለኝ፣ ለማብሸቅም መሰለኝ፣… ብዙ ነገር መሰለኝ። አስተያየቱ ቅድመ አያትህ ቅድመ አያቴን በኩርኩም መቶት ነበርና እበቀልሀለው የሚል ይመስላል። ያው አባቱ በአባቴ ስለተሸነፈ፤ ስለ አባቱ የሚያወራው ጀብዱ ባይኖር ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩኝ።

ዓድዋ ዛሬ ቢሆን ኖሮ በቅኝ ለመገዛት የጦር መሳርያ አያስፈልገንም። መቶ ዶላር በቂ ነው። ዶላርን እምቢ ባይ ፎካሪ፣ ከሱ በፊት እኔን ያስቀድመኝ ባይ ጎበዝ አሁን አለ? የጥቁር እና የነጭ ገበያው ተዋንያን ምስክር ይሁኑኛ እንግዲህ…

ለነገሩ በግሎባላይዜሽን ዓለም ከጣልያናዊ ወንድ ጋር እህታችንን ድረን፤ ልጆቻችንን ጣልያን ስኩል እያስተማርን፤ ጣልያን ሔደን ቤተሰብ ከመሰረትንባት ሀገር ጋር፤ እነ ካሳንቺስ እነ ፒያሳ የመሳሰሉ የጣልያን የውሰት ቃሎችን እየተጠቀምን፤ የእነርሱን ባህላዊ ምግብ እዚህ ዘመናዊ ብለን እያዘጋጀን፤ ሌላው ቢቀር ለእርዳታ እጃችንን ስንዘረጋ ፊቷን ካላዞረችብን ሀገር ጋር መዋጋቱ ‘ፌር’ ነው? የበላንበትን እጅ መንከስ አይሆንብንምን? ገበታ መርገጥ፣ ወጭት መስበር ጡር አይደለምን?

ዓድዋ ዛሬ ቢሆን… “መደመር” የሚለው ቃል ራሱ “መደበር” በሚለው ቃል ተተክቶ ጣልያኖች ሲደበሩብን ይኖሩ ነበር።

ለአባቶቻችን ክብር ይሁንና ናፖሊዮን ሳይሆን ዮሐንስ ተብዬ እንድጠራ፤ ተሳቆ ፓስታ ከመብላት በክብር ሽሮ መብላትን፤ ተዋርዶ ከመጫማት የባዶ እግርን ክብር አቆይተውልኛልና ለአባቶቼ በሀገሬና በህዝቧ ስም ክብር ይሁን።

እውነት ግን ዓደዋ ዛሬ ቢሆን ኖሮ ራሴን እታዘበው ነበር። ጣልያን ለመሄድ ስደትን መፍትሔ ባደረኩበት በዚህ ጊዜ ጣልያን ደጃፌ ቢመጣ ከገንዘብ ክብሬን አስበልጥ ይሆን? ከሆዴ ሀገሬን አስቀድም ይሆን? ከራሴ በፊት ለወገኔ እል ነበር? ከምር ግን… ከዶላር ባህሌን ብዬ ዶሮ አረባ ነበር?

ከመልካምነት ይልቅ ስም በሚፈራበት ጊዜ፣ ከቀሳውስት በላይ አዝማሪ በሚደመጥበት ወቅት፣ ስም ከእውቀት በላይ በሆነበት ዓለም፤ እውነቴን ነው የምለው እነ አንቶኔሊን ለማባረር ሳይሆን ለመቀበል ታቦት ይዘን እንደምንወጣ አልጠራጠርም።

ይልቁንስ ጣልያን ሔዳችሁ ተዋጉ ቢባል ሳይሻለን አይቀርም! ብንሞትም አፈሯን ረግጠን መሞታችን አንድ ነገር ነው ብሎ የሚሰለፍ ወዶ ዘማች አይጠፋማ!

ዓድዋ ዛሬ ቢሆን፤ ጣልያን በመትረየስ ሳይሆን በፕሮፖዛል ብትመጣ… “የእውቀት ሽግግር” የሚል ርዕስ ያለበት ፕሮፓዛሏን ይዛ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎችን በጣልያናዊ ጠበል አጥምቃ ለመላክ የሚያስችል ሀሳብ ይዛ ከች ብትል ዐይኑን የሚያሽ ይኖራል?

ለትምህርት ሳይሆን ከሀገር ለመውጣት ፅኑ ፍላጎት ያለው ኅብረተሰብ ሆ…! ብሎ አቀባበል ያደርግ ነበር።

እውነት ዓድዋ ዛሬ ቢሆን… የውጪ ሀገራትስ እንደ ቀድሞ ይደግፉን ነበር? ስል ለራሴ ላቀረብኩት ጥያቄ መልስ ያገኘሁት ከአፍታ ማሰላሰል በኋላ ነው።

አዎ! በትክክል ደጋፊ አናጣም!

“ሪፐብሊክ ኮንጎ ሴት አርበኞች በእግር መሔድ እንደሌለባቸው ከግምት ውስጥ በማስገባት የኮንጎ ጫማ ድጋፍ እንደምታደርግ አምናለሁ”

“አሜሪካ አርበኞቻችን የጦር መሳርያ ግዢ መፈጸም እንዲችሉ ወጪውን አውርዳ አውጥታ ካሰላሰለች በኋላ የሞራል ድጋፍ እንደምታደርግ አምናለሁ”

“እስራኤል አርበኞቻችን ወደ ትግል ሲሄዱ መብላት መጠጣት እንዳለባቸው ታሳቢ በማድረግ በፀሎት ድጋፍ እንደሚያደርጉልን አምናለሁ።”

“ካሜሮን ጦርነቱን የምንዘግብበት ካሜራ፣ ዚምባብዌ ጦርነቱ ልማታዊ ጦርነት እንዲሆን በማሰብ የዘንባባ ዝንጣፊ፣ ፈረንሳይ የፈረስ ድጋፍ እንደሚያደርጉልን አንዲት ታህል አልጠራጠርም።”

ለነገሩ ዓድዋ ዛሬ ቢሆን ጣልያንን ድባቅ ለመምታት ራሷን ጣልያንን ድጋፍ ሳንጠይቅ አንቀርም ነበር።

ዓድዋ ዛሬ ቢሆን ኖሮ ያ ጥቁር ሰው ራሱ “ያልሰማህ ስማ… የሰማህ ላልሰማ አሰማ” የሚል አዋጅ አያስነግርም። “ወስልተህ ከቀረህ ማርያም አትለመነኝ” የሚል ግዝት ውስጥም አይገባም። ምክንያቱም ከጫት ቤት ወጥቶ የሚመጣ የለማ! ይልቅ ወጣቱ ጫት ቤት ቁጭ ብሎ በፌስ ቡክ ቅስቀሳ እንደሚያደርግ አምናለሁ። ጦርነቱም በአካል መስዋዕትነት ሳይሆን በኢንተርኔት ፖስት በሆነ ነበር። ሁሉም ጥጉን ይዞ ውጣና ተጋደል ሲል የሚጋደል ጠፍቶ፤ ነበር የምንለው የትናንት ታሪካችን እንዳልነበር በሆነ ነበር።

ዓድዋ ዛሬ ቢሆን… ያቺ ጀግኒት ብቻዋን ዓድዋ ሄዳ አትዘምትም። ማልዳ ስለ ትውልዷ አትፀልይም። የጊዮርጊስ ፅላት ከመንበሩ የሚወጣ ከሆነም የተሸካሚዎቹ ዓላማ ቅርስ መሸጥ በሆነ ነበር።

አያድርገውና ዓድዋ ዛሬ ቢሆን ‘እዘምት ነበር?’ ስል ራሴን ጠየኩት አዎ! እኔ እሄድ ነበር፤ ግን ጦር ይዤ አይደለም፣ ሽጉጥ ይዤ አይደለም፣ ስንቅ ሸክፌም አይደለም፣ ካሜራ ብቻ ይዤ ነው የምሔደው። የሞት እና የጦርነት ዜናዬን እየቀረፅኩ እፖስታለሁ። ዩቱብ ከተመልካች ብዛት የሚከፍለኝ ገንዘብ እንዲጨምር፣ ተከታታይ እና ሰብስክራይበር እንዲበዛልኝ አሰቃቂ አሰቃቂውን እየቀረፅኩ ‘ፖስቼ’ እበለፅግበት ነበር።

ከቅዠት ሀሳቤ ስባንን ግን ለራሴ ይህንን አንጎራጎርኩለት፤

የተሰጠኝ ህይወት ዛሬ በነፃነት

ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ካጥንት።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top