ታሪክ እና ባሕል

ክብር ይሰጠው

ክብር ይሰጠው

በ1888 የዓድዋ ጦርነት የተገኘው የኢትዮጵያ ድል፤ የጣሊያንን ወረራ በአህጉሩ ላይ እንዲያከትም በማድረጉ ተከብሮ እና በደንብ ተሰንዶ፤ ለዘመናዊዋ አፍሪካ የተሻለ ማስተማሪያ ሊሆን ይችላል።

የ“100 Great African Kings and Queens“ ደራሲ እና የኒው አፍሪካን መጽሔት አምደኛ ፑስች ኮሚ

ዓለም አቀፍ ታሪካዊ ክስተት

የዓድዋ ድል በጦርነቱ ዋዜማ በዓለም ልዕልና የነበረውን የተሳሳተ አስተሳሰብ በአፍጢሙ የደፋ ክስተት ነበር። በየካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም፤ ከዓድዋ ከተማ ብዙም ባልራቀ ቦታ አንድ የአፍሪካ ጦር በአውሮፓ ጦር ላይ አስደናቂ ድልን ተቀዳጀ። በዓድዋ ጦርነት ኢትዮጵያ በጣሊያን ላይ የተቀዳጀችው ድል የጣሊያንን ወራሪ ጦር ግስጋሴ የገታ ነበር። በማያባራው የአውሮፓውያን የመስፋፋት ዘመን፤ ኢትዮጵያ ብቻዋን በስኬት ነፃነቷን ጠብቃለች።

የኢትዮጵያውያን ድል የተተረጎመው “አፍሪካዊው ጦር አውሮፓዊውን ጦር አሸነፈ” ተብሎ ብቻ ሳይሆን “ጥቁር ሠራዊት ነጩን ሠራዊት አሸነፈ” ተብሎም ጭምር ነበር። የዓድዋ ድል በዚያን ዘመን አይቀሬ ተደርጎ ይታሰብ የነበረውን የአፍሪካውያንን ሙሉ በሙሉ በአውሮፓውያን አገዛዝ ስር የመውደቅ ዕጣፈንታ የደመሰሰ ነበር። ዓድዋ በዘመናዊዋ ኢትዮጵያ ላይ አስደናቂ ድል፤ ትንሽ ዕድሜ ባለው የዘመናዊዋ ጣሊያን ታሪክም አሰቃቂ ሽንፈት ብቻ አይደለም። ዓድዋ በእኔ እምነት የዓለም ቅርስና “ዓለም አቀፍ ታሪካዊ ክስተት” ከምንላቸው አጋጣሚዎች ውስጥ አንዱ ነው። ምክንያቱም ዘመኑን ስናስብ፤ ሁነቶች ለየት ባለ አካሄድ ቢሄዱ ኖሮ፤ አሁን ያለንበት ዓለም ሌላ ዓይነት ነበር። ዓድዋ ለሁለተኛው የዓለም ጦርነትና ከ50 ዓመታት በኋላ ለመጣው የአውሮፓውያን ከአፍሪካ አገዛዝ እየለቀቁ መሄድ፤ መንገድ የሚሆን ቀዳዳ ከፍቷል። የአፍሪካ ቀለም ምን መሆን እንዳለበት ወስኗል።

ሬይሞንድ ጆናስ (The Battle of Adwa – AFRICAN VICTORY IN THE AGE OF EMPIRE)

 የትግል እና አልበገር ባይነት ምልክት

“ከ1888ዓ.ም. የዓድዋ ድል በሁዋላ፤ ብቸኛዋ ያልተገዛች አፍሪካዊት ሃገር ስለነበረች፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካውያን ዓይን ልዩ ቦታ ነበራት። ከዓድዋ ድል በኋላ፤ በአውሮፓውያን ወረራ እና በደል ድንጋጤ ውስጥ ሆነው የበታች እንደሆኑ የሚናገረውን አፈታሪክ ምንጭ በመመርመር ላይ ለነበሩ በሺህ የሚቆጠሩ አፍሪካውያን፤ ኢትዮጵያ የትግል እና አልበገር ባይነት ምልክት በመሆን የተስፋቸው እና ክብራቸው ምሽግ ሆናለች።”

የአፍሮሴንትሪክ ምሁሩ ሞሌፌ አሳንቴ

ኢትዮጵያውያን ስልጡን አካሄድ የሚከተሉ ናቸው

የኢትዮጵያ የድል ዜና እንደተሰማ፤ እንግሊዞች ለኢትዮጵያ ያላቸው አመለካከት በፍጥነት ተቀይሯል። ታይምስ የተባለው የለንደን ጋዜጣ ከጥቂት ቀናት በፊት ኢትዮጵያውያንን “ያልሰለጠኑ አውሬ ህዝቦች” ብሎ እንዳልጠራ፤ በማርች 8 ደግሞ በግልባጩ ኦሬስቴ ባራቴሪ ኢትዮጵያውያንን “ስርዓት የሌላቸውና መሳሪያ በአግባቡ የማይጠቀሙ ኋላቀሮች” አድርጎ ማሰቡ ልክ እንዳልነበረ በመግለፅ የወቀሳ ናዳ አዘነቡበት። ጋዜጣው ያለምንም እፍረት “ኢትዮጵያውያን በጦርነት ላይም፣ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጊዜም፣ ስልጡን አካሄድ የሚከተሉ ናቸው” ብሎ ፅሁፍ አወጣ።

ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top