ጥበብ በታሪክ ገፅ

ከዕለት ዝክር ወደ ቋሚ መዘክር መሸጋገር ያልቻለው ድል

የካርቴጅ ሥርወ-መንግሥት ቅድመ ልደተ-ክርስቶስ 200 ዓመትና ከዚያ በፊት በአፍሪካ ሰሜናዊና ምዕራባዊ አካባቢዎች ግዛቱን ያደረገ አገዛዝ ነበር። በተመሳሳይ ጊዜ ሮማውያን ከፍ ያለ የግዛት መስፋፋት በማካሄድ በሁሉም አቅጣጫ እንቅስቃሴ ጀምሩ። በዚህ ተግባራቸው ከወረሯቸው አካባቢዎች አንዱ የካርቴጅ ግዛት ነበር። የ“ፑኒከ ጦርነት” ተብሎ በታሪክ የሚታወቀው ጦርነት የተካሄደው በዚህ የወራሪው የሮማና የተወራሪው የካርቴጅ ሥረወ-መንግሥት መካከል ነበር።

ሮማውያኑ የገነቡት ግዙፍ የወራሪ ኃይልና ያበጠው ጉልበታቸው ከፍ ባለ የመታበይ ስሜት እየነዳቸው የካርቴጅ ግዛትን ወረሩ። ካርቴጂያውያኑ በመጀመሪያው የፑኒክ ጦርነት የፀረ-ወረራ ፍልሚያቸው ባለመሳካቱ በሮማ እጅ ወደቁ። ነገር ግን ሽንፈታቸው ከፍ ያለ ቁጭት ፈጥሮባቸው ለዳግመኛ የፀረ-ወረራ ትግል አነሳሳቸው። ለዚህ ደግሞ ጄኔራል ሃኒባል የተባለ ጀግና የጦር መሪ ነበራቸው።

ካርቴጂያውያን ቅድመ ልደተ-ክርስቶስ ከ218 እስከ 204 ዓመተ ዓለም ባለው ጊዜ በጦር መሪያቸው ሃኒባልን እየተመሩ ባካሄዱት ሁለተኛው የፑኒክ ጦርነት ሮማውያንን ድባቅ መትተው፣ እስከ ሮማ ዘልቀው፣ ወራሪያቸው ላይ ድል ተቀዳጁ። በጦርነቱ ሮማውያን ከፍተኛ ኪሳራ ከማስተናገድና በሽንፈት ከመሸሽ አልፈው ዘመናትን የተሻገረ ስነ-ልቦናዊ ጉዳት አስተናገዱ።

ሮማውያን ከዚያ ጊዜ አንስቶ በየትኛውም ሁኔታ የሚያጋጥማቸው ፍርሃትና ጭንቀት ሁሉ ከካርቴጂያኑ ጀግና የጦር መሪ ሃኒባል ጋር የተገናኘ ሆኖ ዘለቀ። የድባቴ እና ፍርሃት ስሜት ሲጎበኛቸው በቋንቋቸው “Hannibal ante portas /ሃኒባል ከደጃችን ቆሟል/” በሚል ጩኸት ሊያባርሩት ይጥራሉ። አባባሉ እስካለንበት ጊዜ ድረስ በላቲኖች ዘንድ የተለመደ መሳለቂያ ሆኖ ሲነገር ይደመጣል።

ሁለተኛው የፑኒክ ጦርነት በሮማውያን ዘንድ ከፍተኛ ኪሳራ ያደረሰና የማን አለብኝነት ስሜታቸውን የደረመሰ እንደሆነ በታሪክ ድርሳን ይነገራል። በርካታ የሥልጡኑ ዘመን ታሪክ ተመራማሪዎች፤ ጣልያን በ1896 (የዘመን አቆጣጠሩ በጎርጎሲዮናዊውን ቀመር ነው) ኢትዮጵያን ለመውረር ዘምታ የተከናነበችው ሽንፈትን ከዛ ውደቀቷ ጋር ያመሳስሉታል። “የዓድዋ ድል ሁለተኛው የፑኒክ ጦርነት ታሪክን የደገመ አሰቃቂ ሽንፈት” በማለት።   

ሁለተኛው የፑኒክ ጦርነት በዓለም ዙሪያ ብዙ ይነገርለታል። የጦር ጀግኖቹ ካርቴጂያውያኑና የጦር አዛዣቸው ጄነራል ሃኒባል ከፍ ያለ መታሰቢያ ተገንብቶላቸው እስከዚህ ዘመን የዘለቀ ክብር ተችሯቸዋል። የጦር ጀብዳቸውን የሚዘክር ቋሚ ቤተ መዘክር፣ ሐውልት፣ በርካታ የኪነ-ጥበብ ስራ፣ የመማሪያ ግብአት ሰነዶች ተበጅቶላቸዋል። ከፑኒኩ ጀብዱ የማይተናነሰው በሥልጡኑ ዘመን ኢትዮጵያውያኑ በተጋድሏቸው ያስመዘገቡት የጥቁር ህዝቦች ነፃነት ፋና ቀዳጁ የዓድዋ ድልስ?

ይህ ጽሑፍ የዓድዋ ድልን ከዚህ አበይት ጉዳይ አንፃር ይፈትሻል። የድሉን አገራዊ፣ አፍሪካዊና ዓለም አቀፋዊ አንደምታ በወፍ በረር እየቃኘ፤ ድሉ በድል አድራጊዎቹ ዘንድ የተቸረውን የክብር ቦታ ይመለከታል።

የዓድዋ ድል በተወራሪው እና በወራሪው ጎራ

ተወራሪዋ ኢትዮጵያ፤ በጣልያን ኃይሎች ዐይን የገባችው ምእራባውያኑ አገራት በተስማሙበት “አፍሪቃን የመቀራመት” ውል መሰረት ነበር። አውሮፓውያኑ የአፍሪካ አንጡራ ሀብትን እንደልባቸው ለማጋበስና የህዝቦቹን ጉልበት ለመበዝበዝ ተስማምተው የጥቁሮቹን መንደር እንደ ሰንበቴ ዳቦ ተቃርጠው ተንሰራፉ። የቅኝ ገዢ ኃይላቱ ለዚህ እንቅስቃሴ የበቁት አፍሪካውያንን እጅግ ኋላቀርና የማሰብ አቅማቸው ጭምር የደከመ አድርገው በመቁጠራቸው ነበር።   

አኬና ኤ.ኤፍ የተባለ ጸሐፊ አውሮፓውያኑ ለአፍሪካውያኑ ያላቸውን ንቀት “Africans have no history and the western knowledge delegitimized other ways of knowing as savage, superstitious, and primitive” (አፍሪቃውያን ይህ ነው የሚባል አኩሪ ታሪክ የላቸውም። ምዕራባውያኑ ደግሞ አረመኔ፤ የማሰብ አቅም የሌላቸውና ኋላቀሮች እንደሆኑ ነው የሚረዱት) ብሎ ቅኝ ገዢ ኃይላቱ ለጥቁር ህዝቦች የነበራቸውን ግንዛቤ ያስረዳል።

በዚህ ንቀታቸው በቀደመው ዘመን የአፍሪካ ህዝቦችን በባሪያ ፍንገላ እየወሰዱ በየአገራቸው ለጉልበት ብዝበዛና ለኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ሲዳርጓቸው ቆዩ። በዘመነ-ስልጣኔው ደግሞ ፍላጎታቸው ይበልጥ አይሎ የጥቁር ህዝቦቹን አንጡራ ሀብት ወደማጋበስ በመሸጋገሩ ለቅኝ ግዛት ድርጊት አነሳሳቸው። የተነሱበት ተግባራቸው እርስ በራስ እንዳያጋጫቸው በጋራ ተማክረው ሲያበቁ “አፍሪቃን መቀራመት” የተሰኘ ስምምነት ፈፅሙ። በዚህ ስምምነታቸው በመመራት ባህር ተሻግረው የጥቁር እንቁዎቹ ምድር አፍሪካ ላይ ተንሰራፉ።

ከምዕራባውያኑ ቅኝ ገዢ ኃይላት አንዷ የሆነችው ጣልያን ስምምነቱ የፈቀደላትን ኢትዮጵያን ለመውረር የተነሳችውም በዚሁ መንገድ ነበር። በ1889 ከኢትዮጵያው ንጉሥ ዳግማዊ ምኒልክ ጋር “የውጫሌ ስምምነት” የተባለ ውል በማከናወንና ስምምነቱ ላይ የትርጉም መዛባት እንዲከሰት በማድረግ አገሪቱን በእጇ ለማስገባት ሞክራለች። ነገር ግን ውሉ በኢትዮጵያውያኑ ዘንድ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ፈርሷል። ጣልያንም የውሉ መፍረስ ስላስቆጣት ወደ ሁለተኛው አማራጭ ተሸጋገረች። እርሷን መሰል ወራሪ አውሮፓውያን የሚያካሂዱትን የኃይል አማራጭ በመጠቀም ኢትዮጵያን በመውረር በእጇ የማስገባት አማራጭ።

የጣልያን ወራሪ ኃይል ጉልበቱን አፈርጥሞ የገባበት የወራራ እንቅስቃሴ የከሸፈው በጥቂት ጊዜ ውስጥ ነበር። ኢትዮጵያውያኑ ለወረራው የሚንበረከኩ አልሆኑም። ከፍ ባለ የጀግንነት ስሜትና ቆራጥነት ነገር ግን እጅግ ኋላቀር በሆነ የጦር መሳሪያ ታግዘው በገቡበት የፀረ-ወረራ ፍልሚያ ጣልያንን በአንድ ጀንበር አንኮታኩተው ለሽንፈት ዳረጉ።

“የዓድዋ ጦርነት /1896/ ከሃኒባል በኋላ በአውሮፓ ወራሪ ኃይሎችና በአፍሪካውያን መካከል የተካሄደ ከፍተኛ የጦር ዘመቻ ነው። ለአሸናፊዎቹ እጅግ ወሳኝና አንፀባራቂ ድል ነው። ለተሸናፊዋ ጣልያን ደግሞ በሁሉም ገፅታው ሙሉ በሙሉ የሚባል ውድመት ያስከተለ ነው፡” በማለት መሳፍንት ታረቀኝ የተባለ የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ተመራማሪ ድሉን ይገልፀዋል።

መሳፍንት ጣልያን በጦርነቱ የደረሰባትን ውድመት ከአጠቃላይ የሠራዊቷ አደረጃጀት አንፃር 70 በመቶ እንደሚደርስ አስረድቷል። አጠቃላይ የጦር መሳሪያዋና ከአራት የጦር ጄነራሎቿም አንዱ መማረኩን፤ እንዲሁም በጦርነቱ ከተሰማሩ ግማሽ ያህሉ የጦር መኮንኖቿ መገደላቸውን ያወሳል።

የዓድዋ ድል የፑኒክ ጦርነት ታሪክን በእጥፍ በተባዛ ጀግንነትና አሸናፊነት ደግሞ አረጋግጧል። ነገር ግን የፑኒኩ ጦርነት ያህል ክብርና ዝክር ሳያገኝ እዚህ ደርሷል።

ድሉ በጥቁር ህዝቦች ዘንድ

በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁር ህዝቦች ኢትዮጵያውያን ያስመዘገቡትን ድል በሰሙበት አፍታ ከተደፉበት የበታችነትና የተገዢነት ስሜት ተላቀው፣ አንገታቸውን ለማቅናት በቁ። የታሪክ ድርሳናት እንደሚያረጋግጡት የአፍሪካ ብሔርተኝነት “ፓን አፍሪካኒዝም” አስተሳሰብ የተወለደው ከዓድዋ ድል አብራክ ነው።

የጥቁር ህዝቦች ነፃነት ታጋይ አሜሪካዊው ማርከስ ጋርቬይ “Ethiopian thou land of our fathers… /የአባቶቻችን ምድር ኢትዮጵያ ሆይ…/” የተሰኘውን የአፍሪቃውያን ብሔራዊ መዝሙር የጻፈው በዓድዋ ድል ማግሥት ነው።

ታዋቂው የ19ኛው ክፍለ ዘመን ገጣሚ ፖውል ሎረንስ ደንባር “Ode to Ethiopia” የተሰኘ ርዕስ በሰጠው ግጥም የዓድዋ ድልና የኢትዮጵያውያን ጀብዱ በስፋት አወድሷል።

የአፍሮ ሴንትሪክ አጥኚው ሞሌፍ አሳንቴ በበኩሉ “በ1896 ከተገኘው የዓድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያ በአፍሪቃውያን ሁሉ የተለየ ቦታ ያላት የነፃነት አገር ተደርጋ መታየት ጀመረች። ከዓድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያ የፀረ ጭቆናና ነፃነት መገኛ ታላቅ አገር እንደሆነች አፍሪቃውያን ሁሉ የሚያምኑባት ለመሆን በቃች። ኢትዮጵያን የነፃነት ሰንደቅ አድርገው ያሰቧት አፍሪቃውያን ሁሉ፤ ከሚደርስባቸው የአውሮፓ ቅኝ ገዢ ኃይላት አሰቃቂ ጭቆና ነፃ ለመውጣትና ከተዘራባቸው የበታችነት ትርክት እራሳቸውን ለማላቀቅ አዲስ ጎዳና ማፈላለግ ጀመሩ” ሲል ድሉን ገልፆታል።

ጥቁር ህዝቦች ከባርነትና ከቅኝ ግዛት ለመላቀቅ ቁርጠኛ እርምጃ ውስጥ የገቡት የዓድዋ ድል በፈጠረላቸው መበረታታት ነው። ምዕራባውያኑ ለዘመናት ከዘሩባቸው የተሳሳተ የበታችነት ትርክት በመላቀቅ ገዢዎቻቸውን በገሃድ ለመጋፈጥ ችለዋል። የነፃነት ትግላቸውን አርማ በኢትዮጵያው አረንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ማድመቃቸው ለዚህ አባባል አስረጂ ነው።

ስሚዝ ዊትኒ “Flag of All Nations” በተባለ መጽሐፉ ሁኔታውን ሲያስረዳ “ሁሉም የአፍሪካ ነፃነት እንቅስቃሴ መለያ አርማውን በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት ማድረጉ ለፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ መወለድ የኢትዮጵያው የዓድዋ ድል ዋና ምክንያት መሆኑን ያረጋግጣል። ይህች አገር በነፃነቷ ኮርታ የኖረች ጥንታዊት የጥቁሮች ሁሉ መመኪያ ምድር ለመሆን በቅታለች” ብሏል።  

የዓድዋን ድል ተከትሎ የተቀሰቀሰው “የጥቁሮች ዘመን /Black Decade/” ዋና ምንጩ የኢትዮጵያውያኑ ጀብዱ እንደሆነ ፕ/ር ክንፈ አብረሃም ይናገራል። ማርከስ ጋርቬይ በአፍሮ ሴንትሪክ እንቅስቃሴ በመመራት በ1914 በጃማይካ እንዲሁም በ1917 በኒውዮርክ “ወደ አፍሪቃ እንመለስ /Back to Africa/” የሚል ንቅናቄ መስርቷል። “አንድ ዓላማ፤ አንድ አምላክ አንድ መዳረሻ” በሚል መሪ ቃል እየተመራ የተካሄደው የጋርቬይ ንቅናቄ የዓድዋ ድል ዓይነት ጀብዱ  በመቀዳጀት የጥቁር ህዝቦችን ሁለንተናዊ ነፃነት ማረጋገጥ ህልሙ ያደረገ እንደነበረ ፕ/ር ክንፈ በጽሑፉ አስረድቷል።

ፋይዳውን የሚመጥን ስፍራ ያላገኘው ድል

ዓድዋ በዓይነቱ፤ በይዘቱም ሆነ በፋይዳው ከአንዲት አገር ያለፈና ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ መፍጠር የቻለ አንፀባራቂ ድል ነው። ያም ሆኖ ግን ድሉ ትውልድ ተሻጋሪ ሆኖ የሚዘልቅበት ቋሚ ቅርስ ሊገነባለት ሲገባ፤ እስካሁን ድረስም ለዚህ ዕድል ሳይበቃ ቀርቷል። በዚህ ንዑስ ርዕስ-ነገረ ጉዳዩን ሰፋ አድርገን እንመለከተዋለን።

የአክሱም ዩኒቨርስቲ የቱሪዝም ዲፓርትመንት ተመራማሪ የሆኑት ተ/ብርሃን ለገሰ ኃ/የሱስ እና ዳንኤል ዓለምእሸት በ2019 “The Outstanding Heritage of Adwa, Ethiopia” በሚል ርዕስ ሰፊ የጥናት ጽሑፍ ይፋ አድርገው ነበር። በዚህ ጥናታቸው ላይ

“ዓድዋ በርካታ ለአርኪዎሎጂካል ምርምር የሚውሉ ታዋቂ ስፍራዎችን ይዛለች። አንፀባራቂ የታሪክ ክስተቶችን አስተናግዳለች። ታሪካዊ የእምነት ቦታዎችን በውስጧ አቅፋለች። እጅግ ቀልብ የሚማርክ ውብ ሰንሰለታማ ተራራዎችና ደጋማ የስነ ምድር አቀማመጥን ታድላለች” ሲሉ የዓድዋ አካባቢን ይገልፁታል።

አጥኚዎቹ እንደገለፁት ቀልብ ማራኪው የዓድዋ ሰንሰለታማ ስፍራ፤ ተፈጥሮ ካደለው ውበት በተጨማሪ የግዙፍ አፍሪካዊ ታሪክ ባለቤት ነው። እንደ አድማ በታኝ ፖሊስ እጅ ለእጅ ተያይዞ አድማሱን ከጥግ እስከጥግ የከበበው ማራኪው የዓድዋ ሰንሰለታማ ተራራ፤ የዛሬ 124 ዓመት መላው የጥቁር ህዝቦች ነፃነት ተምሳሌት የሆነውን አንፀባራቂ ጀብዱ አስተናግዷል።

ኢትዮጵያውያኑ ዘር፣ ቀለም፣ እምነት፣ ቋንቋና የውስጥ ቅራኔ ሳይለያቸው በተባበረ ክንዳቸው ዓድዋ ተራራ ላይ የመከቱትና እጅግ አሳፋሪ የሽንፈት ፅዋ ያከናነቡት የጣልያን ወራሪ ኃይል ከፍ ያለ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ድቀትን አስተናግዷል። በዚያው ልክ በጭቆና ስር ሲማቅቅና ይህ ነው የማይባል የዘር መድሎ ሲደርስበት የኖረው መላው ጥቁር ህዝብ የነፃነት ሰንደቁን ለማውለብለብ አንገቱን ቀና አድርጓል። የዓድዋ ሰንሰለታማ ተራራዎች የዚህ ዓለም አቀፋዊ ገድል ባለቤቶች ናቸው።

ተ/ብርሃንና ዳንኤል

“በጣም የተለየ መልክአ-ምድራዊ አቀማመጥ የተቸረው የዓድዋ ተራራ የጥቁር ህዝቦች የኩራት ቤታቸው እንደሆነ በቅኝ ገዢ ኃይላቱ ይታመናል። ማንም ቢመለከተው በተራራው የተለየ ተፈጥሯዊ ገፅታ ሳይደነቅ ማለፍ ይቸግረዋል። ይህ ተፈጥሮ የቸረችው ገፅታ ነዋሪው ስትራቴጂክ የሆነ የፀጥታ ደህንነት ክትትልና ውጊያ ለማድረግ የሚያስችለው ዕድል ፈጥሮለታል። በመሆኑም እራሱ የዓድዋ ሰንሰለታማ ተራራ ኢትዮጵያ በጣልያን ወራሪ ላይ ድል ለመቀዳጀቷ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው ማለት ይቻላል”

ይለናል።

እንዲህ ያለ አንፀባራቂ ድል የተመዘገበበት የዓድዋ ተራራ ዛሬም ከ124 ዓመት በፊት ከነበረው ገፅታው ብዙም አልተቀየረም። ዛሬም የዓድዋ አርሶ አደሮች እንደ ቀድሞው ጤፍ፤ ስንዴና ገብስ እያመረቱ በመሸጥ ኑሯቸዋን ይገፋሉ። እንደ መስቀል ወፍ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ጎብኚዎች ሲገኙ ደግሞ በየቤታቸው የሚሰሩትን የሸክላ ቁሳቁሶችና የሽመና ልብሶች በመሸጥ ገቢያቸውን ይደጉማሉ።

“የጥቁር ህዝቦች ኩራት ቤት” የሚባል ስም የተቀዳጀ ግዙፍና ቀልብ ማራኪ ተራራ በእጇ የሚገኝ አገር የእጇን ወርቅ ከመዳብ ቆጥራዋለች። በታሪካዊ ሀብቷ መጠቀም ተስኗታል። የትምህርት መዛግብቷ ትውልዱን ብዙ ሊያስተምርበትና የአገር ፍቅር ስሜትን በህሊናው ሊቀርፅበት የሚችለውን የዓድዋ ድል በመማር ማስተማር ሰነዱ ላይ የሚገባውን ቦታ አላገኘም።

በርካታ ጥናትና ምርምር ሊካሄድበት የሚችል ማዕከል የማቋቋም አቅም ያለው ዓድዋ፤ ትርጉም እንደሌለው ተቆጥሮ ተዘንግቷል። ቋሚ መዘክር ተገንብቶ ትውልድ ተሻጋሪ ታሪክ የማስተላለፍ ሰፊ ዕድል በውስጡ አምቆ የያዘው ይህ ስፍራ፤ ዞር ብሎ ተመልካች እስካሁን አላገኘም።

በጣም ብዙ የኪነ-ጥበብ ስራዎች ሊፈልቁበት የሚቻለው የዓድዋ ድል ታሪክና የዓድዋ ቀልብ ማራኪ ሰንሰለታማ ተራራዎች የሚዳስሳቸው ብዕር አላገኙም። ሚዲያዎች በዓመት አንዴ የክብረ-በዓሉን ቀን አስመልክተው “ዓድዋ ዓድዋ…” እያሉ ከመለፍለፍ በቀር ቋሚ አገራዊ ፋይዳ እንዲኖረው በማስቻል ረገድ የተጫወቱት ሚና አናሳ ነው።

የመንግሥት ባለሥልጣናት፤ ምሁራን፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ አደረጃጀቶች፣ ስመ ጥሩ ግለሰቦች፣… በዝክሩ ዕለት “ትውልዱ ከጀግኖች አባቶቻችን የዓድዋ ድል ሰፊ ትምህርት በመቅሰም አገሩን ከተጋረጠባት ችግር በወኔ ታግሎ ሊያላቅቃት እንደሚገባ መልዕክት እናስተላልፋለን…” በሚል ይዘት ከተቃኘ ተደጋጋሚ ንግግር በቀር፤ መልዕክታቸው በቋሚነት ትውልዱ ውስጥ የሚሰርፅበትና ዘመናትን ሊሻገር የሚችልበትን ቋሚ ዕድል ሲፈጥሩ አልታዩም።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ተመራማሪ ቢኒያም ወ/ገብርኤል “ማንኛውም ኅብረተሰብ ያለፈ ታሪክ አለው። ከዚህ ታሪኩ ሰናዩን እየመረጠ ለሚኖርበት ዘመን የሚመጥን የአንድነት ማስተሳሰሪያ ዝክር ያውለዋል” ካለ በኋላ ‘ሆብስ ባውን’ የተባለን ምሁር አባባል ቃል በቃል ተውሶ “ያለፈ ታሪኩን እየዘነጋና እያጠፋ የሚሄድ ኅብረተሰብ፤ ከሌላው ብቻ ሳይሆን ከራስ ማንነቱ ተለያይቶ ይቀራል” በማለት መልዕክቱን ያስተላልፋል።

የዓድዋ ድል ከጅማሮው አንስቶ ተመሳሳይ ችግር ማስተናገዱን ታሪክ ያወሳል። ለዚህ አባባል ድሉ በ1896 የተገኘ ሆኖ ሳለ ብሔራዊ ክብረ በዓል ለመሆን የበቃው ከ45 ዓመታት በኋላ መሆኑን መጥቀስ ብቻ በቂ አስረጂ ነው። ከታሪክ እንደምንረዳው ዓድዋ ብሔራዊ ክብረ በአል ሆኖ እንዲዘከር በነጋሪት ጋዜጣ የታወጀው በ1941 ነው። በዚህም ሳያበቃ ዓድዋ የራሱ የታሪክ ቦታ እንዳለው እየታወቀ የክብረ-በዓሉ መዘከሪያ ስፍራ አዲስ አበባ ሆኖ ለዘመናት ቆይቷል። 

በመግቢያችን ላይ ወዳነሳነው ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ከ218 እስከ 204 የተካሄደ ሁለተኛው የፑኒክ ጦርነት እንመለስ። ካርቴጂያንውያኑ የሮማ መስፋፋትን ከመመከት አልፈው ሮም ድረስ ዘልቀው የገቡበት አንፀባራቂ ታሪክን ከድሉ አፍታ አንስቶ ታላቁ ኩራታቸው አድርገው በክብር አድምቀውታል። እነርሱ ለገዛ ድላቸው የሰጡት ቦታ ተሸናፊው የሮማ ወራሪ ኃይል ጭምር እንዲያከብራቸው አድርጎታል። ማክበር ብቻ አይደለም የሚከበሩበት ቋሚ “የካርቴጂያን መታሰቢያ” ሃውልትን ጣሊያን ሮማ ገንብቶላቸዋል።

የካርቴጂያን ጦር መሪ ሃኒባል በዚህ የፑኒክ ድል የሚወደስባቸው የታሪክ መዛግብት እንደ ባህር አሸዋ በዝተው የተገኙት፤ የአገሩ ሰዎች ለድሉና ለጦር መሪያቸው ታላቅ ክብርና ቦታ ሰጥተው በመቆየታቸው እንደሆነ ድርሳናት ያወሳሉ። የሮማ ታሪክ ጸሐፍት አብዛኛዎቹ ካርቴጂያናውያኑንና ሃኒባልን ሳያወሱ አያልፉም። እስከ ቫቲካን ካቶሊካዊ ቤተ-እምነት ድረስ ያሉ ድርሳናት በዚህ ረገድ ብዙ ፅፈው ታሪኩን ዘክረውታል። እንደ ፍሮይድ ያሉ የስነልቦና ሊቃውንትም ቢሆኑ በፑኒኩ ድል ላይ አትኩረው ሰፊ ትንታኔ አቅርበዋል።

የካርቴጂያን ሥረወ-መንግሥት ዋና መቀመጫ የሆነችው የአሁኗ ቱኒዚያም በ1993 ባወጣችው አዲስ የመገበያያ ገንዘቧ ባለ አምስት ዲናር ላይ የሃኒባልን ፎቶ አሳትማለች። “ሃኒባል” የተሰኘ የቴሌቪዥን ጣቢያም በዚህችው አገር ይገኛል። በፑኒክ ወደብ አካባቢ “ካርቴይጅ ጎዳና” ተሰይሟል። በቱኒዝ ከፍታው ተወዳዳሪ የማይገኝለት ባለ 17 ሜትር ሃውልት የቆመው ለሃኒባል ነው። በካርቴጂያን ተጋድሎና በጦር መሪያቸው ሃኒባል ብቃት ላይ ያተኮሩ በርካታ ቤተ መዘክሮች፤ የጥናት ማዕከሎችና ቤተ መዘክሮች በቱኒዚያና በሮም ተመስርተው በቋሚ ቅርስነት እያገለገሉ ይገኛሉ።

የታሪክ ጸሐፍትና ተመራማሪዎች “ዳግማዊ ፑኒክ” የሚሉት የዓድዋው ድል ግን ለዚህ ሁሉ አልታደለም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፓን አፍሪካን ጥናትና ምርምር ተቋም የመመስረትና ቋሚ ቅርስ ማሳያ የመገንባት ሃሳብ ሲነገር ይሰማል። እስካሁን መሬት የወረደ ውጤት ባይታይም ዓድዋን ወደ ቋሚ ቅርስነት ለማሸጋገር የተወሰኑ እንቅስቃሴዎች መኖራቸው ተሰምቷል።

ፕ/ር ማሞ ሙጬ በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ከፍተኛ የታሪክ ተመራማሪ ናቸው። እኚህ ምሁር ከሦስት ዓመት በፊት በፃፉት አጭር ዳሰሳዊ ትንታኔ “ምዕራባውያን  የድዋ ድልን ‘የአፍሪቃውያን ጅልነት የተረጋገጠበት’ ብለው ታሪኩን እያዛቡት ነው። ትውልድ በእንዲህ ያለ የተንሻፈፈ ታሪክ ተጠልፎ ከመማረኩ በፊት ልንደርስለትና የጥቁር ህዝብ የነፃነት ነፀብራቅ ያበራበት ድል እንደሆነ ልንመሰክርለት ይገባል” ብለው ተናግረዋል።

“ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል” እንደሚባለው የኢትዮጵያ አኩሪ ታሪክ ከደጇ ተጠልፎ በተዛባ ሁኔታ ተተርጉሞ እየተጠመዘዘ ይገኛል። ሳይቀደሙ መቅደም ባይቻል እንኳ፤ እኩል መተናነቅና ለአገሩም ሆነ ለዓለሙ አዲስ ትውልድ እውነቱን ማሳወቅ በዋናነት ኃላፊነቱ የሚወድቀው ኢትዮጵያውያን  ላይ ነው።

ፕ/ር ማሞ “ሁሉም የአፍሪቃ አገራት በአንድነት የአፍሪቃ- ዓድዋ ታላቅ ቋሚ ቅርስ ሊገነቡ ይገባል። የዓድዋ ድል በዩኔስኮ ቋሚ የትግል ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ማድረግ ይጠበቅብናል። ትውልዱ መረጃ የሚያገኝበት ሰፊ ማዕከል በማቋቋም ከዓድዋ ድል ጀግንነትና አገር ወዳድነትን እንዲማር የሚችልበትን ዕድል መፍጠር ተገቢ ነው። አፍሪካውያን ከዓድዋ ታሪክ እውነተኛ የነፃነት ትግል መነሻቸውን የሚማሩበት ግዙፍ ዩኒቨርሲቲ ሊመሰረትላቸው ይገባል። ዩኒቨርሲቲው ከዓድዋና ኢትዮጵያ አልፎ በሁሉም የነፃነትና አንድነት ወዳድ ዓለም አቀፍ አገሮች ጭምር ሊስፋፋም ይገባል” በማለት ሀሳባቸውን ይደመድማሉ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top