ጥበብ በታሪክ ገፅ

ከዓድዋ ድል ባሻገር

ከዓድዋ ድል ባሻገር

የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ዘንድሮ ለ124ኛ ጊዜ ይከበራል። ስለድሉና ጦርነቱ በርካታ የታሪክ ተመራማሪዎችና የጥበብ ሰዎች ብዙ ብለውለታል። የዓድዋ ድል ዓለም የመሰከረለት፣ ለአፍሪካ ነጻነት አብነት የሆነ፣ የኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ኩራት ነው። የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ የተነገረውን ለመድገም፣ ወይም በታሪክ ጥናት ውስጥ አዲስ ግኝትና ንባብ ለማስተዋወቅ አይደለም፡፡ ከዓድዋ ድል ባሻገር ያሉ ቅድመ ዓድዋ፣ በጦርነቱ ወቅትና ድህረ-ዓድዋ እስከ ዘመናችን ድረስ ያሉ የአገራዊ አንድነት፣ የያኔው የኢትዮጵያዊ አልሸነፍ ባይነት ስነ-ልቡናዎችን እና ከትውልድ ወደትውልድ ሊተላለፉ የሚገባቸውን የድል ሰንሰለት ወይም ድሮችን መመልከት ነው።

ቅድመ ዓድዋ

ስለ ቅድመ ዓድዋ ስናስብ ሦስት መሠረታዊ ነገሮችን መመልከት ያስፈልጋል። እነሱም አገራዊ፣ አካባቢያዊ (የአፍሪካዊያን ገጠመኝ)፣ እና ዓለም አቀፋዊ (የአውሮፓውያን ትኩረት እና ፍላጎቶች በአፍሪካ) የሚሉት ናቸው። እነዚህን ሦስቱን ጉዳዮች መመርመር የዘመኑን መንፈስ ለመፈተሽ ይረዳናል። የዓድዋን ድል ሙሉ ይዘት ለመገንዘብ የሚያስችሉን ቁልፍ መረጃዎች የሚገኙትም እነዚህ ሦስቱን የትኩረት ምሕዋሮች ይዘን ስንመረምር ነው። እያንዳንዳቸውን በየተራ በአጭሩ እንመልከት።

ሀ/ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ፡ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ የሚለው በዋናነት በቅኝ ግዛት ተቀዳሚ ተሳትፎ የነበራቸውን አውሮፓውያን ሁኔታ የሚመለከት ነው። ይህም አውሮፓውያን በአፍሪካ የነበራቸውን ተግባራዊ ተሳትፎ፣ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ዕይታና ምኞት እንዲሁም ፍልስፍናዊ አስተሳሰቦችን የሚመለከት ነው። በኢኮኖሚያዊ ሁናቴ አፍሪካውያን በአውሮፓውያን በኩል እጅግ በጣም ኋላ ቀሮችና ያልሰለጠኑ ተደርገው ተስለዋል። በዚህም የሃይማኖት ሚሺነሪዎቻቸውን እና ሰላዮቻቸውን በመላክ የአፍሪካውያንን ስነ-ልቡና ለመስለብ ሙከራ ተደርጓል። ከዚህ የከፋው ደግሞ ፈላስፎቻቸው ስለአፍሪካውያን የነበራቸው አመለካከት ነው። እንደ ካንት እና ሄግል ያሉ ጫና ፈጣሪ ፈላስፎች አፍሪካውያን ለዓለም ታሪክ ምንም ዓይነት አስተዋጾ ያላደረጉ በጫካ ውስጥ የሚኖሩና የሥልጣኔ ጮራ ያልዳሰሳቸው አድርገው ስለዋቸዋል። በዚህም ምክንያት ቀደም ሲል በባሪያ ንግድ፣ ኋላ ደግሞ በቅኝ ግዛት አፍሪካውያንን መቆጣጠር ቀላል እንደሆነ አውሮፓውያን አምነዋል። ከኢኮኖሚ አንጻር ደግሞ የአፍሪካ ተፈጥሮ ሃብት ለአውሮፓውያን የኢንዱስትሪ እድገት አማራጭ የሌለው ግብዓት ነበር። እነዚህ እሳቤዎችና ምኞቶች በይፋ በበርሊን ኮንፈረንስ ህጋዊ ሆነው አፍሪካን ለመቀራመት፣ እንደ እቃ ለመከፋፈል እንደ ቅድመ-ሁኔታ አገልግለዋል።

ለ/ አካባቢያዊ ሁኔታ፡ ለዚህ የአውሮፓውያን አመለካከትና ተግባራዊ እርምጃ የአፍሪካውያን ምላሽ ምን ነበር? በቅኝ ግዛት ዋዜማ የአፍሪካውያንን ሁኔታ ስንመለከት አብዛኛዎቹ በውድም ሆነ በግድ “የማይቀረው” ቅኝ ግዛት ሰለባ ሆነው ነበር። አውሮፓውያን በሃይማኖት ሚሺነሪዎቻቸው እና “በልማት ልዑኮቻቸው” አማካኝነት የአፍሪካውያንን ልቡና ሸርሽረውት ስለነበር፤ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በኃይል ለመቆጣጠር አልከበዳቸውም። ምክንያቱም ሁሉም በሚባል ደረጃ አፍሪካውያን ለቅኝ ግዛት በሮቻቸው ዝግ አልነበሩም። እያንዳንዳቸው ያደረጓቸውን የአልሸነፍ ባይነት ትግሎች ዋጋ ማሳጣት ሳይሆን፤ መጨረሻ ላይ ግን ሁሉም በቅኝ ግዛት ሥር መሆናቸው የሚጠበቅ ሐቅ ነበር። የራስ ቤት አጥር ምንም እንኳ በቂ ነው ተብሎ ቢታሰብም፤ የጎረቤት አጥር ሲፈርስ ጠንካራው የራስ ቤት ቅጥር በራሱ ጠላትን የመቋቋም አቅሙን እንደሚያጣ እሙን ነው። የአፍሪካውያን የመወረር ሁኔታ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለኢትዮጵያ ሳይተርፋት አልቀረም። በቀጥታ ካየነው አንዳንዶቹ ጎረቤት አገራት ከቅኝ ገዥዎቻቸው ጋር በማበር እና በመመሳጠር፤ ሌሎቹ የቅኝ ግዛት ኃይሎች ከኢትዮጵያ ጋር ነበራቸው ብለው በገመቱት ግንኙነት አንድምታ ኢትዮጵያን ለመውጋት ሲሰለፉ ነበር። ምናልባትም ማንም አፍሪካዊ ከቅኝ ግዛት እጣ-ፈንታ ሊያመልጥ አይችልም የሚል አስተሳሰብ የዘመኑ ገዥ መንፈስ ነበር ማለት ይቻላል።

በተዘዋዋሪ ደግሞ የያኔዋ ኢትዮጵያ የነበራትን ድንበር በግልጽ ለማስቀመጥ እንደ ፈተና የሆነባት፤ ቀደምት አፍሪካውያን የየራሳቸው ጥንታዊ ድንበር አለመያዛቸው ነው። በዚህም ኢትዮጵያ “ከኢትዮጵያ ውጭ” ካሉ ቅኝ ግዛቶች ጋር የተዋዋለቻቸው የድንበር ውሎች አልፎ አልፎ በቅኝ ገዥዎች መልካም ፈቃድ ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ ተገድዳለች፡፡ በዚህም  የውጫሌው ውል፣ በሶማሌ በኩል ከእንግሊዝ ጋር ያደረገቻቸው ውሎች፣ እንዲሁም ከፈረንሳይ ጋር በጅቡቲ በኩል የተደረጉ ውሎች አወዛጋቢ ነበሩ። በተለይ የውጫሌ ውልና የመረብ-ምላሽ ጉዳይ እስከዘመናችን ድረስ አወዛጋቢ ሆኖ ብዙ ዋጋ ያስከፈለን ነው።

የነዚህ አካባቢያዊና ዓለማቀፋዊ ሁኔታዎች ድምር ውጤት፤ ኢትዮጵያ ለምታደርገው ከቅኝ ግዛት የመከላከል ጦርነት ከአፍሪካ በኩል በመተባበር ከጎኗ የሚቆም ማጣቷ፤ እና በአውሮፓውያን በኩልም ሰሚ መንግሥት አለማግኘቷ ነበር። በዚህም ኢትዮጵያውያን ‘ብቻችንን ቀረን’ ብለው ከመበርገግ ይልቅ በራሳቸው ኃይል እንዲተማመኑ ያደረጋቸው ጉዳይ ከላይ ካየነው ጋር ይስማማል። አሁን ውጊያቸው ከውጭ ቅኝ ገዢ ጋር ብቻ ሳይሆን ከራሳቸው ጎረቤቶችም ጋር ጭምር ሆነ። የነበረው አካባቢያዊ አጣብቂኝ እንዲህ የሚታይ ነው። በእርግጥ በአፍሪካውያን ሙሉ በሙሉ ተስፋ እንዳንቆርጥ የሚያደርገን የታሪክ እውነታ፤ ኢትዮጵያን እንደ አብነት በማየት በዓድዋ ድል ተምሳሌትነት የራሳቸውን የነጻነት ትግል መጀመራቸው፣ ‘ኢትዮጵያኒዝም’ እንደ አንድ የእንቅስቃሴ መልዕክት መደረጉ ነው።

ሐ/አገራዊ፡የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የሚመለከቱባቸው መነጽሮችና ነገሥታቱ ይህንን አገራዊ ስሜት ለማስተናገድ የሚወስዱት ቁርጠኝነት ናቸው። የዓድዋው ድል መነሻውን የሚያገኘው ከዚህ የአገር ህዝቦች ስሜትና ከነገሥታቱ ምላሽ ነው። የኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ትርጓሜዎችና አረዳዶች ላይ የተለያዩ ክርክሮች አሉ። በዋናነት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ድንበር የቱጋ ነው? አሁን ኢትዮጵያ ተብላ በምትጠራው አገር ያሉ ህዝቦችስ በርግጥ የኢትዮጵያ ታሪካዊ አካላት ነበሩ ወይ? የሚሉ ክርክሮች ይነሳሉ። እንደዚህ ዓይነት ክርክሮች ምናልባትም “መንግሥት” እና “አገር” የሚሉትን ጽንሰ-ሐሳቦች የምንተረጉምባቸው አስተሳሰባዊ መሠረቶችን በመፈተሽ የጋራ ስምምነት ላይ ለመድረስ ያስችሉናል። በርግጥ የዘመናችንን የመንግሥትና የአገር ምንነት ትርጓሜ ይዘን ከሄድን አከራካሪ ነው። በጥንታዊው የኢትዮጵያ ታሪክና አተራረክ ካየነው ግን ኢትዮጵያ አሁን ከምናውቃት የሰፋች፣ ኢትዮጵያውያን ደግሞ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ካርታ ክበብ ውጭ ያሉትንም ህዝቦች የሚያካትት እንደሆነ የታሪክ መዛግብቶች ያመላክታሉ። ለዚህ እንደ ምሳሌ የተክለጻድቅ መኩሪያ አተያይ እንደሚከተለው ቀርቧል።  

“…የጥንት ጽሐፊዎች ግብጾችም፣ እስራኤሎችም ግሪኮችም ግማሾቹ የኩሽ አገር የቀሩት ኢትዮጵያ እያሉ ሲጠሩን አሁን ባለንበት የፖለቲካና ያገር ክፍል የምንገኘውን ኢትዮጵያኖች ብቻ አይደለም [] ነገር ግን ከዛሬው ቱኒዚና ማሮክ ከሊብያና ግብጽ ከፍልስጥኤም ወደ ደቡብ በኤርትራ ባህር ግራና ቀኝ እስከ ህንድ ውቅያኖስ ጠረፍ ድረስ ያለውን የዛሬውን የዓረብንም የሱዳንንም በመካከል የሚገኘውን ያሁኑን የኛንም አገር አንዳንድ ጊዜ እየለዩ ብዙ ጊዜ እየደባለቁ ነው።

ይህም እንደ ሙሉ ስህተት እንዳይቆጠር በዙሪያችን ከሚገኙት ከነዚህ ህዝቦች ጋር ዘራችን ልማዳችን ቋንቋችን ከሥር ከመሠረቱ እየተገናኘ ተደባልቆ በመኖሩ ነው፤ ደግሞም ረኃብ በተነሳ ጊዜ አንደኛው ነገድ ተሰዶ ወደ አንደኛው ነገድ አገር ሄዶ ይደባለቃል። (፲፱፻፶፩ገጽ ፲፬)

እንደዚህ መሰሎቹ ትርክቶች በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ላይኖራቸው ይችላል። ነገር ግን እንዲሁ አገራዊ አንድነት ለማምጣት የተነገሩ የስሜት ሐተታዎች ናቸው ለማለትም አያስደፍርም። ቀድሞ በነበሩ የማዕከላዊ መንግሥታት ኢ-ፍትሃዊነትና የነገሥታቱ ባለሟሎች በፈጸሟቸው ስህተቶች ተገፋፍቶ ተቃራኒውን ትርክት መፍጠርም የራሱ የሆነ እንከን አለው። ይህም የዛሬዋን ኢትዮጵያ የጋራ አድርገን እንዳንቀበል፤ ይባስ ብሎም የድህረ ቅኝ ግዛትና የአውሮፓውያንን አገረ-መንግሥት ትርጓሜ በመያዝ እያንዳንዳችን አገር ወደ መመስረት የሚወስደን መንገድ ሊያደርግብን ይችላል። የጥንታዊቷን ኢትዮጵያ ስናስብ ማዕከሏ ከአክሱም ወደ ላሊበላ፣ ከላሊበላ ወደ ሸዋ፣ ከሸዋ ወደ ጎንደር፣ ከጎንደር ወደ የጁ፣ ከበጌምድር ወደ ትግራይ እንዲሁም ተመልሶ ወደ ሸዋ እየተዘዋወረ የማስገበር አቅምና የትኩረት አቅጣጫው እየተቀያየረ የኖረ “ልል” ድንበር የነበረው እንደሆነ መረዳት ይቻላል።

ከዚህ ልል ድንበር በመነጨም ኢትዮጵያ እንደ ሃገር በህዝቦቿ ልቡናና ህሊና ሰፊ መሬት ያላት፣ አንዳንዴም በሃይማኖታዊ አመለካከትና ባህላዊ እሳቤዎች የተመረጠች “ቅድስት” አገር፣ መሬቷም የአያት ቅድመ አያት መንፈስ የረበበባት በሚለው ብያኔ ከማንኛውም የውጭ ወራሪ መጠበቅ ያለባት እንደሆነች ይታመን ነበር። በዚህ አረዳድ በማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ጠላት የሚባል ወራሪ ቢመጣ በዚያ አካባቢ (ጠረፍ) ያሉ ህዝቦች በቅድምና ለአካባቢው ዘብ በመቆም ለአገራቸው ያላቸውን ጥብቅና ይገልጻሉ። ስለዚህ ጉዳይ ግርማቸው ተክለሃዋርያት “አርአያ” በተሰኘ ታሪካዊ ልቦለድ ሥራቸው ሲያትቱ ኢትዮጵያ ተጠብቃ የኖረው በማዕከላዊው መንግሥት ምሉዕ በኩለሄ የሆነ ጠንካራ ጡንቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ህዝብ አካባቢውን ነቅቶ በመጠብቅ ዘብ በመቆሙ ነው ይሉናል።

ምናልባትም የታሪክ ድርሳኖቻችን የተሟሉ ባይሆኑ ነው እንጅ እንደ ራስ አሉላ ያሉ ለአካባቢያቸው ዘብ የቆሙ ጄኔራሎች በሁሉም የኢትዮጵያ ድንበሮች እንደሚኖሩ አያጠራጥርም። የአገርን ህልውና በአጠቃላይ የሚገዳደር እንደፋሺስት ጣልያን፣ የኦቶማን ቱርክ፣ ግብጽ፣ የሱዳን ማሕዲስትና የሶማሊያ ወረራ መሰል ኃይል ሲመጣ ደግሞ ከሁሉም ቦታ ‘ሆ’ ብሎ ተጠራርቶ በመዝመት ለነገሥታቱ ያለውን ታማኝነትና ለሃገሩ ያለውን ፍቅር ይገልጻል። እንደ ሰቨን ሩቢንሰን አገላለጽ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ምንም እንኳ እርስበርሳቸው የፖለቲካ ሽኩቻ ወይም ለንጉሶቻቸው ጥላቻ ቢኖራቸውም የአገርን ህልውና ጥያቄ ውስጥ የሚከት ችግር ሲገጥማቸው ግን የውስጥ ችግራቸውን በይደር አቆይተው ተስማምተው አብረው ይዘምታሉ።    

ሌላው የህዝብ ለህዝብ ሰንሰለቱን የሚያጠናክረው ደግሞ ኢትዮጵያውያን በተለያየ መልኩ የፈጠሩት ትስስር ነው። በንግድ፣ በስደት፣ በሥራ ምክንያት፣ በጦርነት ወዘተ የፈጠሩት መዋሃድና ዝምድና አገራዊ አንድነቱን በማጠንከር፣ ከሩቅ ያለውን ወገኑ ሲቸገር እንደራሱ ችግር በመቁጠር የደረስኩልህ ወገናዊ ቁርጠኝነቱን ያሳያል። በርግጥም የኢትዮጵያውያን ሁኔታ ሲታይ ይህንን ስብጥር ያመላክታል። በዚያ ላይ አንድ ማኅበረሰብ ከአካባቢው በተለያየ ምክንያት ርቆ ወደ ሌላ አካባቢ በሚጓዝበት ወቅት ከነባሩ ማኅበረሰብ ጋር ተስማምቶ የመኖር ልምድ እንዳለው በዘመነ መሳፍንት ኢትዮጵያን የጎበኘው ‘ዲ አባዴ’  ትዝብቱን አስቀምጧል። ይህ መዋሃድ እና መዋለድ አገራዊ አንድነቱ እንዲጠነክር በማድረግ ትልቁን ድርሻ ሲወስድ እንደ ሌቪን ያሉት ተመራማሪዎች ደግሞ የኢትዮጵያውያን ብዝሃ ባሕል ከአንድ የባሕል ግንድ የመነጨ ወይም ወደ “አንድ ኢትዮጵያዊ ባህል” (የትኛው ባህል ነው ኢትዮጵያዊ? የሚለውን ለክርክር ትተን) ያደገ እንደሆነ መላ ምታቸውን ያስቀምጣሉ።

ይህንን ዲስኩርና ህዝባዊ ስሜት ነገሥታቱ በተለያየ መልኩ ይጠቀሙበታል። አንዳንዴም ለዚች የተመረጠች አገር “ከእግዚአብሔር የተላክሁ ንጉሥ”፣ “ትንቢት የተነገረለት ንጉሥ”፣ “ሁሉም በሙሉ ልብ ሊገዛለት የሚገባ ቅቡዕ ሥዩመ እግዚአብሔር” የሚሉት አገላለጾች ለጭቆና ተግባር ጥቅም ላይ ውለዋል የሚሉ በርካታ ናቸው። የንጉሡን ማንነት የማይቀበሉ አሜን ብለው ላለመገዛት በሚያደርጉት ተቃውሞ በርካታ የውስጥ ጦርነቶችና ህዝቡን የማስገበር ዘመቻዎች ተካሂደዋል።

እንዲህ ዓይነቶቹን የውስጥ ተቃርኖ ጉዳዮች ለፖለቲካ ታሪክ ጸሐፊዎች በመተው ከተነሳንበት ርእሰ-ጉዳይ አንጻር እንመልከተው፡፡ ነገሥታቱ የአገሪቱን አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር በወሰዱት የዲፕሎማሲ እንዲሁም የኃይል ምላሽ ህዝቡን ለማነቃቃት ተጠቅመውበታል። በዘመቻ አዋጆቻቸው ሳይቀር “አገር የሚወር፣ ሃይማኖት የሚለውጥ፣ ማንነት የሚያጠፋ ጠላት መጣብህ፤ ህዝቤ ሆይ ካሁን በፊት አልበደልሁም፣ አንተም አላስከፋኝም፣ አሁንም ከጎኔ ሁን” እያሉ በማራራትም፣ በማነቃቃትም፣ በማስፈራራትም ህዝቡን ሲቀሰቅሱ ይስተዋላል።

ከላይ እንዳየነው ከህዝቡ ቁርጠኝነትና አገራዊ ስሜት በተጨማሪ በዘመነ ቅኝ ግዛት የነበሩት ነገሥታት ያሳዩት ቁርጠኝነት ዓድዋ ጦርነት ላይ ለተስተዋለው ድል መሠረት ነው። የመጀመሪያው የአጼ ቴዎድሮስ አልበገር ባይነትና የአርቆ አስተዋይነት አስተዋጾ ማንኛውንም የኃይልም ሆነ የተንኮል ቅኝ ግዛት ሙከራዎችን አክሽፏል። አጼ ዮሐንስም ራሳቸውን አሳልፈው እስከ መስጠት የሚያደርስ አርአያነትን ወስደዋል። አጼ ምኒልክም እሰከ ጦር ሜዳ ድረስ ከነባለቤታቸው ከወታደሩ ጋር በመዝመት ለአገር የሚከፈል መስዋዕትን አሳይተዋል።

የአገራዊን የውስጥ ጉዳይ ስናጠቃልለው የአልደፈር ባይነት ስነ ልቡና፣ አልሸነፍ ባይነት፣ ጀግንነትና የአገር ወዳድነት ስሜት ያስተሳሰራቸው የኢትዮጵያ ህዝቦችና ጠንካራ ታሪካዊ ተጠያቂነትን ያነገቡ ነገሥታት፤ ኢትዮጵያን ከማንኛውም የውጭ ወራሪ ታድገዋታል ማለት ይቻላል። ይህም ሆኖ ብዙ መስዋዕት ከመክፈል፣ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በውጭ ወራሪ ከመገዛት፣ እንዲሁም ከክፍፍል አልዳንም።  

በዚህ ረገድ በበርሊን ኮንፈረንስ ባጸደቁት መሠረት አፍሪካን የመከፋፈልና የመቀራመት ውላቸውን የሚቃወም ነገር ሲገጥማቸው ከምኒልክ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን አቤቱታ ጆሮ አልሰጡትም። የራሳቸው ፍላጎት ስለነበራቸውም ከተለያዩ የኢትዮጵያ ነገሥታትና መሳፍንቶች ጋር በመስማማት፣ አሻጥር በመስራት ኢትዮጵያ እንድትዳከም ይጥሩ ነበር። አፍሪካዊ አገርና ህዝብ ሆኖ ከቅኝ ግዛት ነጻ መሆንን መቀበል በራሱ ከአውሮፓውያን እሳቤ ጋር ስለሚፃረር ጣልያን ያካሄደችውን ወረራ አውሮፓውያን በይፋ አልተቃወሙትም። ይህም ወደማይቀረው ጦርነት መንደርደሪያ ሆነ።

ቅድመ-ዓድዋ ጦርነት በእነዚህ አገራዊ፣ አካባቢያዊና ዓለማቀፋዊ እውነቶች የተቃኘ ነው። ባንድ በኩል ኢትዮጵያ በነበራት የራሷ ትርክት በማንም ስር የማትንበረከክና ለማንም የማትገዛ እንደሆነች ይታሰብ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ለዚህ የውስጥ ስሜት ትርጉም የማይሰጡ፣ እንዳንዴም ከዓላማው ተቃራኒ የቆሙ ውጫዊ ሁኔታዎች ነበሩ። ስለዚህ ጦርነቱ በርግጥም ከጣልያን ጋር ብቻ አልነበረም። ከኢትዮጵያ በኩል ደግሞ ድጋፍ ሊያደርግላት የፈቀደ ማንም ውጫዊ ኃይል አልነበረም። የያኔዋን ኢትዮጵያ እንደግለሰብ ብናስባት የሕልውና ተግዳሮት (Existential Threat) የተጋረጠባት በአውላላ ሜዳ ላይ ብቻዋን የቀረች፣ ከራሷ ኃይል (“ከፈጣሪ በቀር”) ውጭ ምንም ረዳት የሌላት ሆና ትታየናለች። ያላት ብቸኛ አማራጭ ወይ እጅን አጣጥፎ መቀመጥና ለሚመጣው ሰባሪ፣ ዋጭ ሰልቃጭ አውሬ ሰለባ መሆን፤ ወይ ደግሞ ኃይል በፈቀደ የውስጥን ጉልበት አሟጦ በመጠቀም ራስን ነጻ ማውጣት። ኢትዮጵያም ሁለተኛውን መንገድ በመከተል ወደማይቀረው ጦርነት አዘገመች።

የማይቀረው ጦርነት እና የዓድዋ ዋዜማ

ዓድዋ የአንድ ቀን ውጊያ እንዳልሆነ እሙን ነው። የራሱ የሆኑ የቅርብ ርቀት መንሰኤዎችና ገፋኤ-ኃይላት ነበሩት። በዓድዋ ዋዜማ የተካሄዱት ጦርነቶች የውስጥና የውጭ ተብለው ሊከፈሉ ይችላሉ። በውስጥ በኩል በቀጥታ የዮሐንስና የምኒልክ ሽኩቻ አለ። በንግሥና ጉዳይ የራሳቸውን ችግር በሙሉ ያልፈቱት የሸዋው ንጉሥ ምኒልክና የኢትዮጵያው ንጉሠ-ነገሥት ዮሐንስ ያልፈቷቸው የቤት ሥራዎች ነበሩ።

የምኒልክ ከዮሐንስ ጋር በሙሉ ልብ አለማስማማት ለጣሊያን ቀዳዳ ከፍቷል። ጣሊያኖች በየት በኩል ኢትዮጵያን እንውረር እያሉ በሚዘጋጁበት ወቅት የአጼ ዮሐንስ ወደ መተማ መዝመትና በዚያው መሞት ትልቅ ዕድል ፈጠረላቸው። በውጭ በኩል ደግሞ ምንም እንኳን አጼ ዮሐንስ የእንግሊዞች ወዳጅ ሆነው ከማሕዲስት ሱዳን ጋር ያጋጫቸውን የ“ሒወትን ውል” ቢዋዋሉም፤ እንግሊዞች በበኩላቸው የንጉሡን ወዳጅነት ችላ በማለት ከጣልያን ጋር በአሻጥር በመዋዋል ጣልያን ምጽዋ ላይ እጇን እንድታስገባ ተባበሯት።

በዚህ ግራ የተጋቡት ዮሐንስ ከእንግሊዝ መንግሥት ማብራሪያ ጠየቁ። ከጣሊያን መንግሥት ጋር ወዳጅ ለነበሩት ምኒልክ ደግሞ የጣልያንን ጉዳይ እንዲያጣሩ ትዕዝዝ ሰጡ። በሁለቱም በኩል አጥጋቢ መልስ ሊመጣ አልቻለም። እንዲያውም የጣልያኑ መንግሥት ባለሟል አድሚራል ካይሚ “ምጽዋ የገባነው በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ፈቃድ ነው የሚል የቅጥፈት መልስ ሰጠ” ይሉናል ጳውሎስ ኞኞ። ባንድ በኩል በዚህ ማጭበርበሪያ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከማህዲስቶች ልንከላከልላችሁ ነው በሚል ማዘናጊያ፤ ጣልያኖች ቀስ እያሉ በግለሰብ ስም ከተገዛ የባህር ዳርቻ ቦታ፣ ከምጽዋ ወደ ሰሐጢ እና ወደ መረብ-ምላሽ ግዛት መስፋፋት ጀመሩ። የወቅቱ የመረብ-ምላሽ ገዥ ራስ አሉላ ከጣልያኖች ጋር ሽኩቻ ውስጥ ገቡ። በዶጋሊ ላይ በተካሄደ ጦርነትም ጣልያንን አሸነፉ።

በተደጋጋሚ ጦርነቶች ራስ አሉላ ድል ቢቀናቸውም ጣልያኖች ቀስ በቀስ በሰሜን ኢትዮጵያ ምድር የተደላደለ ቦታ መያዛቸው አልቀረም። ለዚህ ደግሞ የራስ አሉላ ከመረብ-ምላሽ ገዥነታቸው በንጉሠ ነገሥቱ መነሳታቸው ምቹ መደላድልን ፈጥሮላቸዋል። ይህም ብቻ ሳይሆን ሹም ሽር አድርገው ከአስመራ የተመለሱት አጼ ዮሐንስ ወደ መተማ ዘምተው መሞታቸው ሲሰማ ለጣልያን ሰርግና ምላሽ ሆነ። በዚህ ጊዜ

“አጤ ዮሐንስ መተማ ዘምተው መሞታቸው እንደተሰማም በ1882 ዓ.ም. ኢጣልያኖች መረብ-ምላሽ ቅኝ ግዛታቸውን ኤርትራ ብለው ሰየሙት” (ጳውሎስ ኞኞ፣ 2009 ገጽ 138) ።

ቀደም ሲል በአጼ ዮሐንስ ቅሬታ የነበራቸው የአካባቢው ባላባቶች፣ ኋላ ላይ ደግሞ ዮሐንስ በመሞታቸው ራስ መንገሻ እንዳይነግሱ የፈሩ መሳፍንቶች ከጣልያን ጋር ስምምነት ማድረጋቸው አልቀረም። በዚህም ምክንያት ጣልያን በአካባቢው ከባድ ፈተና ሳይገጥማት ቀረ።

ከዚህ ሁሉ የከፋው ደግሞ ከምኒልክ ጋር በውጫሌ ያደረጉት ውል ነው። ይህ ውል በአንድ በኩል የጣልያንን ግዛት የሚያጸና ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በጣልያን መሰሪነት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነበር።

አጼ ዮሐንስ እንደሞቱ ንጉስ ምኒልክ ከጣልያን ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ተገን በማድረግ በ1881 ዓ.ም. ከጣልያን ጋር የጥድፊያ ውል ተዋዋሉ። ይህንን ውል አለመፈረም እየቻሉ ወይም ማስተካከል እየተቻለ ምኒልክ ለምን ችላ አሉት? ምናልባትም ባልተረጋጋ ስሜት ውስጥ ስለነበሩ ወይም ስለተታለሉ። ምኒልክ ውሉን በሦስት ዝብርቅርቅ ስሜቶች ውስጥ ሆነው እንደተዋዋሉት ተክለጻድቅ መኩሪያ ያስቀምጣሉ።

በዮሐንስ መሞት የደስታ እና የሃዘን ስሜት፤ በሌላ በኩል ደግሞ የጣልያን አሻጥር፣ የራስ መንገሻ ወደ ሥልጣን የመምጣት አዝማሚያ ወደ ንጉሠ ነገሥትነት የሚያደርጉትን ጉዞ እንዳያደናቅፍባቸው በስጋት ውስጥ ሆነው ነው የፈረሙት። በዚህም ውሉ በጣልያን በኩል በተንኮል የተቃኘ ሲሆን (ከሮማ የተረቀቀ)፤ በምኒልክ በኩል ደግሞ በተረጋጋ ህሊና ያልተደረገ ነበር ማለት ይቻላል። ለዚህም ነው ኋላ ላይ ምኒልክ ውሉን ለማፍረስና ለጦርነት ምክንያት የሆናቸው።

 “ንጉሥ ምኒልክ ባንድ በኩል የውጭ ተጽዕኖና ወረራ በሰሜን እና በምሥራቅ ኢትዮጵያ በሚያንዣብብበት፡ በሌላ ወገን በአፄ የሐንስ ሞት ምክንያት በየክልሉ የሚገኙት መሣፍንት የራሳቸውን አደላድለው ለመያዝ በሚራኮቱበት ወቅት በመሆኑ፡ እነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች አስገድደዋቸው ለጊዜው ውሉን እያንገራገሩ ለመፈረም በቁ። በእርግጥም ሕሊናቸው ፈቅዶና ሙሉ እምነት አድርገው አለመፈረማቸውን ሊያረጋግጥ የሚችለው፡ የኋላ ኋላ ውሉን መሠረዛቸውና እንዲያውም የኢትዮጵያ የግዛት ክልል ከምጥዋ አልፎ ሕንድ ውቅያኖስ መድረሱን ማሳወቃቸው ነው” (ተክለጻድቅ 1983፣ ገጽ 46)

የዚህ ውል ሁለት ቁልፍ ጉዳዮች አንደኛው በ3ኛው አንቀጽ የተቀመጠው ጣልያን የወረረችውን መሬት “ህጋዊ” የሚያደርግ ሲሆን፤ ሌላኛው በ17ኛው አንቀጽ የተቀመጠው ጉራማይሌ ሐሳብ በአማርኛው እንደየአስፈላጊነቱ “የወዳጅ ጣልያንን” እርዳታ የሚያሳየው በጣልያንኛው ደግሞ “ጣልያንን የኢትዮጵያ የበላይ” አድርጎ የሚያስቀምጠውና፤ ኢትዮጵያ ከማንኛውም የውጭ አገራት ጋር በምታደርገው ግንኙነት በጣልያን መልካም ፈቃድ ማድረግ እንዳለባት የሚያስገድደው ነው። ዞሮ ዞሮ በዚህ ውል ጣልያን የበላይነቱን ወስዳ ነበር፤ ኢትዮጵያም ውሉን እንድታፈርስ እና ወደ ጦርነት እንድትገባ ተገዳለች።

የክተት አዋጅና ሦስቱ ጦርነቶች

(አላጄ፣ መቐለ፣ ዓድዋ)

አከራካሪው የውጫሌ ውል በጣልያንና በኢትዮጵያ መካከል ይፋዊ ጥል ፈጠረ። ከዚህ በተጨማሪ ጣልያን በ3ኛው አንቀጽ ከተቀመጠው ድንበር በማለፍ መላውን ትግራይ ወረረ። ምኒልክ በዲፕሎማሲ ለመፍታት ወደ ዓለም መንግሥታት አቤቱታቸውን ቢያስገቡም ሰሚ አላገኙም። ከላይ እንዳየነው ኢትዮጵያ ብቻዋን ቀረች። ያለው ብቸኛ አማራጭ በጦርነት ድል ማድረግ ነው። ምኒልክ ይፋዊ የክተት የጦር አዋጅ አስነገሩ። ሙሉ ቃሉ በተለያዩ የታሪክ መጻሕፍት ውስጥ ስለሚገኝ። ከሞላ ጎደል የሚከተለው ነው።

እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ፣ አገሬን ጠብቆ አኖረኝ። እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ። እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለኔ ሞት ኣላዝንም። ደግሞም እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም። እንግዲህም ያሳፍረኛል ብየ አልጠራጠርም።

አሁንም አገር የሚያጠፋ፥ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል። እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ የሰውንም መድከም ዐይቸ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ዠመር።

አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። ያገሬ ሰው! ካሁን ቀደም የበደልኹህ አይመስለኝም። አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም። ስለዚህ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለሚስትህ፥ ለሃይማኖትህ፥ ለሀገርህና ለታሪክህ ስትል በጸሎትህ እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፣ አልተውህም! ማርያምን! ለዚህ አማላጅ የለኝም! ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ።

በምኒልክ የክተት አዋጅ ውስጥ በርካታ ቁም ነገሮችን ማየት እንችላለን። አንደኛው ጥሪያቸው እከሌ ከእከሌ ሳይል በጥቅሉ “የአገሬ ሰው” በሚል የተላለፈ ነው። ሁለተኛው ወታደር ወይም ነፍጠኛ ብቻ አልተጠራም። ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ ጉልበት የሌለው በጸሎቱ፣ በእዝነቱ፣ በምኞቱ እንዲረዳ ነው። ዋናው ቁም ነገር ደግሞ “በሚስትና በርስት ቀልድ የለም” እንዲሉ ለሚስትህ፥ ለሃይማኖትህ፥ ለሀገርህና ለታሪክህ የሚለው ሐረግ ነው። ምንም እንኳ ለሃይማኖትህ የሚለው ሐሳብ በዚያን ዘመን የነበረው ትርጓሜ የትኛውን ሃይማኖት እንደሚመለከት የታወቀ ቢሆንም ለሃገርህና ለታሪክህ ስትል የሚለው አጽንኦት ግን የማንነትን ጉዳይ የሚመለከት ነው። በመጪው ትውልድ ዘንድ የተገዥነት ታሪክ እንዳይዘገብብህ፣ የተሸናፊነት ታሪክ እንዳይጻፍብህ ተነስ የሚል ነው። ሌላውና የሚገርመው ነገር ደግሞ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፣ አልተውህም!  የሚለው ‘ማስፈራሪያ’ መሳይ የትንቢት ቃል ነው። ባንድ በኩል እንደ ንጉሥ ተፈሪነታቸውን በመጠቀም ወላዋዮችን ያስፈራሩበት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የአሸናፊነት ስነ-ልቡናና ትንቢትም ጭምር ነው። እንደሚያሸንፉ እርግጠኛ በመሆን ከድል በኋላ በአገር ጉዳይ ላይ ያልተሳተፉትን እንደሚቀጡ ያመላከቱበት ነው።

የህዝቡም ምላሽ ከአቅራቢያው ከሚገኘው የትግራይ ህዝብ ማንም በወታደራዊ ሥርዓት ሳያደራጀው በቻለው አቅም ሲዋጋ ከረመ። ለምሳሌ ጣልያን በመቐለ አካባቢ ጠንካራ ምሽግ በሰራበት ወቅት የአካባቢው ህዝብ ያሳየውን ምላሽ ጳውሎስ ኞኞ እንዲህ በማለት ይገልጹታል።

“አገር ወዳዱ የትግራይ ህዝብ ሳይታዘዝ በራሱ ፈቃድ እየወጣ በጣሊያኖች ላይ ሲተኩስ ከረመ።” (ጳውሎስ ኞኞ፣ ገጽ 176)

ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጣ ዘማች ሴት፣ ህጻን፣ አዋቂ፣ አካል ጉዳተኛ ሳይቀር እንደዘመተ በርካቶች መስክረዋል። ካፒቴን ሞልቴዶ የተባለን የዘመኑ የጣልያን ጋዜጠኛና መድፈኛ ቃል ጳውሎስ ኞኞ እንደሚከተለው ጠቅሰውታል።

“ህዝቡ ከሁሉም ብሔረሰብ ተውጣጥቶ ቀርቧል። […] ጦርነቱን ከወታደሮች ጋር ብቻ አልገጠምንም። በጦርነቱ ውስጥ ሴቶች፣ ሽማግሌዎች፣ ሕጻናት፣ ቄሶችና [አካል ጉዳተኞች] ሳይቀሩ ወጉን” (ገጽ 162)።

እንደዚህ ዓይነቶቹ ህዝባዊ ተሳትፎዎች የጦርነቱን ዘመን ህዝባዊ ትዕይንት፣ አጠቃላይ ክስተት (Phenomena) የሚያሳዩ ናቸው። እነዚህ እንደወረደ የህዝቡን ምላሽ የሚያሳዩ ሲሆኑ ወደ እውናዊ ጦርነት ሲገባስ የወታደሩ ሥርዓትና ስሪት እንዴት ነበር? የሚለውን መመልከት ያስፈልጋል።

አንዳንዶቹ የኢትዮጵያ ሠራዊት ኋላ ቀር በሆነ መንገድ እንጨቱን ድንጋዩን፣ ጦሩን አንስቶ እንደተዋጋ ሊስሉት ይችላሉ። ነገር ግን እውነታው ከዚህ የተለየ ነበር። በታሪክ ጸሐፊዎችም በያኔው የንጉሡ ጸሓፌ ትዛዝ የነበሩት ገብረሥላሴም የተመሠከረው የጦርነት ስትራተጂ የተወጣለት ነበር።

ሦስት ጊዜ ተዋግቶ ጣልያንን በአላጄ፣ በመቐለና በዓድዋ ድል የነሳው የኢትዮጵያ ሠራዊት ዘመናዊ የሚባለውን የጣሊያን ጦር ያሸነፈው በብዛት ብቻ ሳይሆን በታክቲክም ጭምር ነው።

አላጄ ላይ የመሸገውን ጣልያን ያባረረው የኢትዮጵያ ጦር፤ መቐለ ላይ ከባድ ፈተና ገጥሞት ነበር። አራት አጥር ያለውን ምሽግ (ግንብ፣ የብርጭቆ ስባሪ፣ እሾሃማ ሽቦ፣ ሹል እንጨቶች) (ጳውሎስ ኞኞ፣ ገጽ 175) ለመቆጣጠር እጅግ ከባድ ነበር። በእቴጌ ጣይቱ ምክርና በሠራዊቱ ምክር ሰሚነት የጣሊያኖችን የውሀ ምንጭ በመዝጋት ሊያሸንፉ ችለዋል። የጦርነት ብልሃት ይህ ነው። ከባዱን ነገር በቀላል ዘዴ ማሸነፍ እንደሚቻል የታየበት ተምሳሌታዊ ሁኔታ ነው።

ወደ ዓድዋ በቀረቡ ጊዜ ደግሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት ‘ሆ’ ብሎ ጣልያኖችን ለመዋጋት ፍላጎት ቢያሳይም በጉድባ ውስጥ መድፎችን ደግኖ ስትራተጂያዊ ቦታ ይዞ ይጠባበቅ እንደነበረ መጀመሪያ ራስ ስብሐትና ደጃች ሐጎስ ከጣልያን ሰፈር ገስግሰው በመምጣት ለንጉሡ ምስጢር አካፈሉ። ጣልያን

“ካቡንም እርዱንም አጠንክሮ፤ ቦታ ቦታውንም ለመድፍ አልቦት ተቀምጧል። ወደዚያ ብንሄድ ባንድ ጊዜ ብዙ ሰራዊት ያልቅብናል። ይልቁን ከኋላ ዙረን (ቆረጣ) የስልክ ሽቦውን እና የስንቅ መስመሩን እንያዝ። በርሃብ ይሸነፍልናል” (ገብረሥላሴ፣ 2008 ገጽ 197)

የሚል ምክር ሰጡ። ንጉሡም በይሁንታ ተቀበሏቸው። ከዚያም በመቀጠል በጣልያን አድፋጭነት የተናደደው የኢትዮጵያ ሠራዊት መኳንቶቹ ጋር መክሮ ገፍቶ ሊወጋው ከወሰነ በኋላ ራስ መንገሻ በፈረስ ጋልበው፣ ከሠራዊታቸው ጋር ተሰልፈው መጥተው ወሳኔውን እንደሰሙ

“አንድ ነገር ልናገር ይፈቀድልኝ ብሎ ወደ ንጉሡ ቀርቦ ‘እንደ ተርታ ነገር ካልሆነ ስፍራ ሄደን ይህን ሁሉ ልናስፈጀው ነውን አጼ ዮሐንስ መተማ ሄደው ከዚያ እንኳ ያን ሁሉ ሠራዊት አስፈጁ እኛም ከካብ ውስጥ ሄደን ይህን ሁሉ ሠራዊት አናስፈጅም” አለ። አጼ ምኒልክም ይህን ምክር ሰምተው “እንግዲህ ከሰፈሬ መጥቶ ተኩስ ካልዠመረ፣ ባይኔ ካላየሁት ተሰልፌ አልወጣም ብለው እንደ ትንቢት ተናገሩ።” (ገብረሥላሴ፣ 2008 ገጽ 199) ።

በጦርነት ወቅት ትልቁ ስኬት የጦር መሳሪያ ኃይል ወይም የወታደር ጀግንነት እንዲሁም የአልሸነፍ ባይነት ወኔ ነው። ከዚህ ባሻገር ደግሞ መረጃን፣ ስትራቴጂን፣ የጠላትን ሁኔታ መገንዘብና ምክርን መስማት አስፈላጊ እንደሆነ እነዚህ ማሳያዎች ናቸው። ምኒልክ የነራስ ስብሐት፣ ደጃች ሓጎስን እና ራስ መንገሻን ምክር መስማታቸው ለድል እንዲበቁ ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ ቢያንስ ብዙ የሰው ሕይወት መስዋዕት ከማድረግ ታድጓቸዋል። የነባሻይ አውዓሎምና መሰል አርበኞች ሚናም የዚሁ አካል ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሠራዊት ወኔንና አልሸነፍ ባይነት ስነ-ልቡናን ብቻ ሳይሆን፤ ወታደራዊ ብልሃትና ስልትንም ዘመኑ በሚመጥነው ደረጃ ተጠቅሞበታል።

ከአሰላለፍ ጋር በተያያዘም ሥርዓት ባለው መልኩ ሁሉም ቦታ ቦታውን ይዞ ለውጊያ እንደተዘጋጀ ጳውሎስ ኞኞ በገጽ 204 ላይ፣ ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ ደግሞ ገጽ 198 አስቀምጠውታል። ጳውሎስ ኞኞ የሠራዊቱን አሰላለፍ ግልጽ በሆኑ ቃላት እንዲህ ያስቀምጡታል።

“በኢትዮጵያውያን በኩል የኢጣልያ መንቀሳቀስ ወሬ እንደተሰማ ራስ መኮንን የሐረርጌን ጦር እየመሩ ገስግሰው ዓድዋ ከተማን ያዙ። ራስ ሚካኤል የወሎን ሠራዊት አስከትለው ሰላዶ [ሶሎዳ] የሚባለውን ተራራ ያዙ። በንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የሚመራው የጎጃም ጦር ፊት ለፊት ወደ ኢጣልያኖች ምሽግ አመራ። ራስ መንገሻ፥ አዲ አቡን ላይ የትግራይን ሠራዊት አሰለፉ። አጤ ምኒሊክ፥ እቴጌ ጣይቱ፥ ራስ ወሌና ዋግሹም ጓንጉል በስተኋላ ደጀን ሆኑ። የኦሮሞ ፈረሰኞች 13 ኪሎ ሜትር ያህል ከሚርቅ ቦታ ሁሉ ያሉትን የውሃ ምንጮች እየፈለጉ ከበው ያዙ”

ከዚህ በተጨማሪ አዝማሪዎች፣ ሴቶች፣ ህጻናት፣ ቄሶች እና ሽማግሌዎች የየራሳቸውን ድርሻ ወስደዋል። ሌላው የሚደነቀው ደግሞ የኢትዮጵያውያን መሣሪያ አጠቃቀም ብልሃት ነው። የጀኔራል ባራቴሪ ዓይን እማኝነት ለዚሁ በቂ ማስረጃ ነው። ከምርኮ ተለቆ አገሩ ከገባ በኋላ ለጋዜጠኞች የሰጠውን ቃል ጳውሎስ ኞኞ ሲያስነብቡን

“እኛ የሰለጠነው ዓለም ሥልጡን ወታደሮች ምንም አያውቁም ከሚባሉት ኢትዮጵያውያን የምንማረው ትምህርት አለ። አበሾች ለባሩድና ለጥይት ይሳሳሉ። የሚገድሉ ካልሆነ በስተቀር አይተኩሱም። ለዚያውም ቢሆን አስርና 15 ያርድ ያህል ቀርበው ባንድ ጥይት ደራርበው መግደል ይፈልጋሉ። ያለዚያ ተደበላልቀው በጎራዴ መምታት ይመርጣሉ እንጂ ጥይት ማበላሸት አይወዱም። ይህም በማስጮህ ብቻ ጥይት ለሚያባክነው ለሰለጠነው ወታደር ጥሩ ትምህርት ነው”

የሚል ቃል ይገኝበታል (ጳውሎስ ገጽ 207)። የዓድዋ ድል የዚህ ሁሉ ህዝባዊ ተሳትፎ፣ ወታደራዊ ብልሃት፣ የአልሸነፍ ባይነት ሥነ ልቡና ድምር ውጤት ነው።

መልካም የዓድዋ ድል በዓል!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top