ጥበብ በታሪክ ገፅ

ነጯ ኢትዮጵያ

በሬይመንድ ጆናስ የተፃፈው “The Battle of Adwa: AFRICAN VICTORY IN THE AGE OF EMPIRE” በተሰኘ መጽሐፉ ላይ Menelik Abroad (ምኒልክ በውጭው ዓለም ዕይታ) በሚለው ርዕስ ስር ተከታዩን አስገራሚ ቁምነገር አስፍሯል።

በ1896 ዓ.ም. እ.አ.አ. አንድ ከሰዓት ላይ ፍሬድ ሆላንድ ደይ፤ የፒንክኒ መንገድ ላይ ከሚገኘው ፎቶ ስቱዲዮው ለቅቆ በመውጣት፤ ጉዞውን ወደ ደቡብ ቦስተን አደረገ። ለፎቶግራፍ ስራው የሆነ ሃሳብ መጥቶለታል። ያንን ለማሳካት ደግሞ ለፎቶው የሚሆን ጥሩ ሞዴል ያስፈልገዋል።

ደይ ከዚህ ቀደም ብዙ ወጣ ያሉ ‘ሞዴሎችን’ ለፎቶ ስራው ተጠቅሞ ያውቃል። በ19ኛው ክፍለ-ዘመኗ ቦስተን እነዚህን ሞዴሎች መፈለግ ብዙም አያስቸግርም። በ1890ዎቹ ቦስተን ሲሶ የሚሆነው ህዝቧ መጤ እና ምንም ሰራ የሌለው፤ እንዲሁም በግለሰቦች ልገሳ ድጋፍ የሚኖር ነበር። አብዛኛዎቹ ድጋፍ የሚያገኙ ሰዎችም ቢሆኑ ራሳቸውን ለማሳደግ አማራጭ ሊኖር ይችላል ከሚል ተስፋ በመነሳት ያገኙትን ስራ ይሰሩ ነበር። ፍሬድ ደይ ከከበርቴ ቤተሰብ የተወለደ ስለነበር፤ የእናቱን የበጎ ድጋፍ ስራ በመከተል፤ እሱም የቦስተን የግለሰቦች የእርዳታ ትስስር ውስጥ ራሱን ሊከት ችሏል። ደይ በማስጠናትና በማስተማር በበጎ ስራዎች ላይ ይሳተፍ ነበር። በዚህም የማኅበራዊ ድጋፍ ሰራተኞች ጥሩ ንቃት ያላቸውን ታዳጊዎች ሲያገኙ ወደ ፍሬድ ይልኳቸዋል።

ደይ ባለተሰጥኦ ታዳጊዎችን ያግዛል። ይህንን አጋጣሚም በመጠቀም ለፎቶግራፍ ሙያው እነዚህን ታዳጊዎች እንደሞዴል ይጠቀማል። ለምሳሌ ደይ እጅግ በጣም አስደናቂ የሆኑ ተከታታይነት ያላቸውን ፎቶዎች ታዳጊ ወጣቱን ካህሊል ጂብራን አንስቶታል። ኋላ ላይ ካህሊል ጂብራን ታዋቂና ታላቅ ደራሲ ለመሆን የቻለ ነው። “ነብዩ” በሚለው ስራው ብዙ ሰው ያውቀዋል።

በዛ ቀን ፍሬድ ሆላንድ ደይ የሚፈልገው ጥቁር አፍሪካ-አሜሪካዊ ሰው ነበር። ወደስቱዲዮው አንድ አፍሪካ-አሜሪካዊ ጥቁር ሰው ወስዶ እንደሞዴል በመጠቀም አንድ አፍሪካዊ ንጉሥ ይኖረዋል ብሎ ባሰበው ዓይነት ልብስ አለበሰው። ለአንዱ ስራው እንዲያውም የሱፍ ጨርቅ ሞዴሉን በማልበስ፤ ጥቁር የእርግብ ላባም እንዲያደርግ አድርጓል። በሌላ የፎቶ መነሻ ቀን ደግሞ ሞዴሉ ጦር እንዲይዝ፤ የነሐስ አምባር እንዲያጠልቅ፣ ደረቱ ላይ ሜዳሊያ እንዲኖረው እና፤ በግስላ ቆዳ ላይ እንደተቀመጠ ዘውድ በራሱ ላይ እንዲደፋ በማድረግ ፎቶ አንስቶታል።

ከሁሉም በበለጠ ዝነኛ ለሆነውና እስካሁን ድረስ በተለያዩ ቦታዎች “የምኒልክ ምስል” ተብሎ ለሚታወቀው ስራው፤ ሆላንድ ደይ ያዘጋጀው ሞዴል በራስ መተማመን ያለውና የተረጋጋ ስሜት ውስጥ ሆኖ ቀርቧል። ሞዴሉ ወደ ሆላንድ ደይ ካሜራ ሌንስ በመመልከት ፈንታ፤ ከሌንሱ በላይ አርቆ የሚያይና፤ ከተመልካች ዕይታ አንፃር በግራ ትከሻ ትይዩ በኩል እንዲመለከት አድርጎ አንስቶታል።

ምንም እንኳ የፍሬድ ሆላንድ ደይ አንዳንድ አመለካከቶች ገራገር ቢመስሉም፤ የእርግብ ላባ፣ ልል የሱፍ ኩታው፣ የነሐስ ሜዳሊያውን ስንመለከት፤ እንደተለመደው የተሳሳተ የአፍሪካዊ መልክ ግንዛቤ ያለው ባንል እንኳ፤ ሆላንድ ደይ አካሄዱ ወዴት እንደሆነና ምን ለማለት እንደፈለገ ለመገመት አያስቸግረንም።

የሆላንድ ደይ ፎቶ ዓድዋን እና ኢትዮጵያዊ ኩራትን በደንብ መግለፅ የቻለ በመሆኑ፤ የምዕራቡ ዓለም በምስራቃውያንና በአፍሪካውያን ላይ የበላይነት እንዳለው የሚናገረውን አስተሳሰብ፤ ሰብሮ የጣለ ነበር። የሆላንድ ደይ ስራ የሆነው “ምኒልክ” የተሰኘው ፎቶ በጥቁሮች የነፃነት ትግል ላይ የራሱን የሆነ በጎ አስተዋፅኦ ለማሳረፍ ችሏል።

የዓድዋ ድል ከመጠናቀቁ አንድ ቀን በፊት “ATLANTA CONSTITUTION” የተባለው ጋዜጣ፤ ወደአፍሪካ እንመለሳለን በሚሉ ጥቁሮች ላይ የሚሳለቅ ጽሑፍ አውጥቶ ነበር። አህጉሪቷ ሙሉ በሙሉ በነጭ አውሮፓውያን እጅ ውስጥ እንደምትወድቅም ትንቢቱን አስቀምጦ ነበር። ዓድዋ ላይ የሆነው ግን ከዛ በተቃራኒ ነው። የመጽሔቱ ነጥብ በሰዓቱ ምክንያታዊ እና ስሜት የሚሰጥ ቢሆንም ከአንድ ቀን በኋላ ግን አመክንዮው ፈረሰ።

የ“ATLANTA CONSTITUTION” የማርች 4 ዜና (ከዓድዋ ድል ከ3 ቀናት በኋላ) ገዢ አስተሳሰብ ሆኖ የነበረው ጥቁሮች የበታች እንደሆኑ የሚያስረዳውን ንግግር ፉርሽ አድርጎ ያስቀረ ነበር። በጋዜጣው ላይ የወጣው “የምኒልክ ምስል” የፍሬድ ሆላንድ ደይ ስራ ነበር። የጋዜጣው ዜና አቀራረብ ኢ-ሚዛናዊ የነበረ ሲሆን፤ የኢትዮጵያውያንን ድል 3ሺ ጣሊያኖችን ገደሉ በሚል ብቻ አሳንሶ፤ ጣሊያኖችን ግን በጀግንነት እንደተዋጉ በመጥቀስ፤ ባራቴሪ በሽንፈቱ እፍረት ስለተሰማው ራሱን እንዳጠፋ በማስመሰል አቅርቦ ነበር። (ሙሉ በሙሉ ውሸት ነው)

የ“ATLANTA CONSTITUTION” በዚህ ብቻ አላበቃም፤ በተከታይ በወጡ እትሞቹ “The Abyssinian Question” በሚል ርዕስ የኢትዮጵያውያንን ‘ጥቁርነት’ ጥያቄ ውስጥ እያስገባ ጽሑፎች ማውጣት ጀመረ። አፅንኦት ሰጥቶ ከገለፃቸው ጉዳዮች ውስጥ፤ ኢትዮጵያውያን እንደሌሎች አፍሪካውያን በተለይም ኮንጎ እንደሚገኙት ጥቁሮች ደፍጣጣ አፍንጫና ጠፍጣፋ እግር ያላቸው እንዳልሆኑ ጠቅሶ፤ የዘር ሃረጋቸውም ከነጮች እንደሚመዘዝ ፃፈ።  አስገራሚው ነገር በሆላንድ ደይ “የምኒልክ ምስል” ተብሎ በቀረበው ፎቶ ላይ በመመርኮዝ፤ ምን ያህል ከሩሲያው ንጉስ ዛር ኒኮላስ 2ኛ ጋር እንደሚመሳሰሉ ጠቅሶ አንባቢዎቹን ለማሳመን ጥሯል።

እንደዚህ ያሉ አስተሳሰቦች፤ ምን ያህል በጥቆሮች ላይ ያለ የጥላቻ እና የዘረኝነት መንፈስ በደቡብ የአሜሪካ ክፍል ይቀነቀን እንደነበር ያሳየናል።

የጣሊያን በጥቁር ህዝብ መሸነፍ ዜና፤ በሰፊው የአሜሪካ አንባቢያን ዘንድ ግራ መጋባትን የፈጠረ ነበር። ነገር ግን የተለመደውን የደቡብ አሜሪካ ክፍል የዘረኝነት ዕይታ የሆነው ምንሊክን “ነጭ” የማድረግ ሐተታ በመተው ፈንታ፤ “New York World” የተሰኘው ጋዜጣም ተመሳሳይ ዘገባ አሰናዳ። “Chicago Tribune”ም  የ“New York World” ዘገባን እንደምንጭ በመጠቀም ተመሳሳይ ሐተታ አቅርቧል። በዚህም በደቡብ አሜሪካ ክፍል እና በአትላንቲክ ውቅያኖስ ጠረፍ የሚገኙ ጋዜጦች “Caucasian Ethiopia” (ነጯ ኢትዮጵያ) እስከማለት ደፍረዋል። “New York World” በተለይ ያለምንም እፍረት “አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ነጮች ናቸው” ከማለቱም በተጨማሪ “ጥሩ የሰውነት አቋም ያላቸውና መልከ መልካሞች ናቸው” በማለት፤ የኢትዮጵያውያንን ቁንጅና ለማጉላት የተቀረውን የአፍሪካ ክፍል አስቀያሚ መልክ የሰጠ ኢ-ሚዛናዊነት ጽሑፍ አስነብቧል።

የአውሮፓ ጋዜጦችም የአሜሪካውያኑን ጋዜጦች አተራረክ በመቀበል አስተጋብተውታል። በዓድዋ የጣሊያን መሸነፍ እንደተሰማ “Times of London” ለምሳሌ፤ የድሉ ተፅዕኖ በ “Triple Alliance” (የሦስትዮሽ አጋርነት) ላይ ስለሚፈጥረው ጫና ተዘግቦ ነበር። “Triple Alliance” በጣሊያን፣ ኦስትሪያ እና ጀርመን መካከል የተደረገ የጦር ስምምነት ጥምረትና ትብብር ነው። እንዲያውም ለ “London Times” የሚዘግብ የበርሊን ጋዜጠኛ “ጣሊያን በአፍሪካ ውስጥ የተደረገን ጦርነት ማሸነፍ ካቃታት፤ ስምምነቱ የሚያስገድዳትን የአውሮፓ ኃላፊነቶቿን ለመወጣት የምትችለው እንዴት ነው?” ብሎ እስከመጠየቅ አድርሶታል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top