መጽሐፍ ዳሰሳ

ታላቁ ጥቁር (ኢትዮ-አሜሪካ ዘዳግማዊ ምኒልክ)

ማዕረጉ በዛብህ

“ታላቁ ጥቁር” በንጉሤ አየለ ተካ ተዘጋጅቶ በ2010 ዓ.ም. በማንኩሳ ማተሚያ ቤት የታተመ መጽሐፍ ነው። ይህ 473 ገጾች ያሉት፣ በከፍተኛ ጥናትና ምርምር የተዘጋጀ መጽሐፍ በፊት ሽፋኑ የዳግማዊ ምኒልክ ፎቶግራፍ፣ በኋላ ደግሞ የፕሬዝዳንት ቴዎዶር ሩዝቬልት ፎቶግራፎች ታትመውበታል። የፕሬዝዳንት ሩዝቬልት ፎቶግራፍ ፕሬዝዳንቱ ፈርመው ለአጼ ምኒልክ ለወዳጅነት ሰላምታ መግለጫ የላኩት ሲሆን በፎቶው ላይ የተጻፈው መልዕክትም “TO His Majesty King Menelik II of Abyssinia, Negus Negist of Ethiopia, From Theodore Roosevelt, August 28th, 1903” “(ለአቢሲንያው ንጉሥ፣ ለግርማዊ ዳግማዊ ንጉሥ ምኒልክ፣ ንጉሠ-ነገሥት ዘ-ኢትዮጵያ)” ይላል።

ይህች አጭር ጽሑፍ የተዘጋጀችው እንደተለመደው በመጽሐፉ ላይ ሥነ-ጽሑፋዊ ሂስ ለማቅረብ ሳይሆን፣ መጽሐፏ የያዘቻቸውን ቁምነገሮች በጥቂቱም ቢሆን ለመፈንጠቅ ነው።

ከዚያም ባለፈ፣ አጼ ምኒልክ “ጨለማዋ አፍሪካ” እየተባለች ትታወቅ በነበረችው ኋላቀር አህጉር አርቆ አስተዋይ እና ተደናቂ ብቸኛው “ታላቅ መሪ” በመባል ዕውቅና ማግኘታቸውን ለማሳየት ነው። በተጨማሪም የወቅቱ የዓለም መሪ የነበረችው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት፣ ከምኒልክ ጋር ወዳጅነት ለመመስረት የወሰዱትን ተደናቂ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ ታሪካዊነትም እንመለከታለን።

ያ ግንኙነት በዓለም አቀፍ ዲፕሎማቲክ ግንኙነት ታሪክ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥበብ ችሎታን የሚገልፅ ድርጊት ሲሆን፣ ዛሬ እኛ ከ109 ዓመት በፊት የተከናወነውን ድርጊት ወደኋላ ተመልሰን ስናስብ፣ የሁለቱን መሪዎች ልዩና ብሩህ የአስተሳሰብ ልዕልና የሚመሰክር ተግባር ሆኖ እናገኘዋለን።

ፕሬዝዳንት ሩዝቤልት ከዳግማዊ ምኒልክ ጋር ሊመሠርቱት የተነሱትን ወዳጅነት ምክንያት በጊዜው ከነበራቸው እያደገ የመጣ እና እውነተኛ፣ አካታች፣ ተራማጅ፣… የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የመነጨ እንደሆነ ደራሲው ንጉሤ አየለ በገጽ 99 እንደሚከተለው አስቀምጠውታል፤

መልዕክተ ሩዝቬልት ለዳግማዊ ምኒልክ

“ለትልቅም ሆነ ለትንሽ አገር ያለን አመለካከት፣ እኩል አክብሮት የተሞላው እና በእውነተኛ ወዳጅነት መመስረት ተገቢና ፍትሀዊ ነው። ይህንንም በቃላት ብቻ ሳይሆን በተግባር የምንገልፀው መሆን አለበት።”

ፕሬዝዳንት ቴዎዶር ሩዝቬልት ዋሽንግተን ዲሲ፤

ከላይ እንደተባለው ፕሬዝዳንት ሩዝቬልት የውጭ ግንኙነት መርሃቸውን በተግባር ለመግለጽ በኮንሱል ጀኔራል ሮበርት ስኪነር የሚመራ አንድ የአሜሪካ የልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ሲልኩ “ለአቢሲንያው ንጉሥ፣ ለግርማዊ ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ-ነገሥት ዘኢትዮጵያ” የሚል ማስታወሻ የተጻፈበትን ፎቶግራፋቸውንም ለምኒልክ እንዲያደርሱላቸው አድርገዋል።

ጽሑፏ በሂስ ላይ አታተኩርም ብልም መጽሐፏ ምን እንደያዘች ለመጠቆም ጥቂት ነገሮችን መጥቀሱ አይከፋም። እናም ዶ/ር ግርማ አበበ (ገጽ 53) የሰጡት አስተያየት ለመጽሐፏ አመጣጥ በጣም ጠቃሚ መግለጫ ስለሆነ እዚህ ላይ መጥቀሱ የማይታለፍ ጉዳይ ሆኖ ይታየኛል።

  “ይህ መጽሐፍ በዘመን ርቀት ሳቢያ በዝርዝር ሳናውቃቸው ከነበሩ ጠቃሚ ታሪኮች ውስጥ፣ ልናውቀው እና ልንረዳው የሚገባን እውነት አጥጋቢ በሆነ መረጃ ይዞልን የቀረበ ሥራ ነው። ከዓመታት በፊት ደራሲው አቶ ንጉሤ አየለ ተካ ይህን አሁን በጥሩ ሁኔታ ያጠናቀቀውን ጥናት ሲጀምር አውቀዋለሁ። በጥናቱ የተጓዘበት የመረጃ ፍለጋና ውጣ ውረድ፣ በአብዛኛው ውስብስብ ሆኖ፣ ብዙ ጊዜም አስጨናቂ እና ትዕግስትን የሚፈታተን ውጥረት ነበረው።

ደራሲው ለዓመታት የደከመበት ሥራ ተቀነባብሮ እና ተጽፎ ዕድል አጋጥሞኝ አሁን ሳነበው፣ ይህ ሳይነካ የሰነበተ ታሪክ ምንኛ የማናውቀው የሚመስጡ ክስተቶች እንደነበሩት አስተውያለሁ። ታሪኩ በአጥጋቢ መረጃ ተተንትኖ በመቅረብ ያነበብኩት በጣዕመ ትዝታው ልቤን እየነካው በአድናቆት እና በደስታ ነው። ይህንን መጽሐፍ ለማግኘት የበቃው ግን፣ ንጉሤ በግሉ የራሱን ኑሮና ጥቅም ወደ ጎን ትቶ፣ በርትቶ በትዕግስት እና በፍላጎት ስለሰራ ነው።” (ታላቁ ጥቁር፣ 2010፣ ገጽ 53)

ሚስተር ሮበርት ስኪነር በዋና ቆንስል ማዕረግ የፕሬዝዳንት ቴዎዶር ሩዝቬልትን መልዕክት ለአጼ ምኒልክ እንዲያደርስ የተላከውን የአሜሪካ ልዑካን ቡድን በመምራት ወደ ኢትዮጵያ ይሄዳሉ የተባለው ጉዳይ በግልፅ ከታወቀ በኋላ በበርካታ አሜሪካውያን ዘንድ ስለ ኢትዮጵያ እና ስለ አጼ ምኒልክ ለማወቅ ከፍ ያለ ጉጉት በማደሩ፣ የአሜሪካ ጋዜጦች ስለ ኢትዮጵያ በብዛት ይጽፉ ነበር። የሮበርት ስኪነር ቡድን ተልዕኮ አሜሪካ ከሰሃራ በታች ወደሚገኝ የአፍሪካ ክልል ይህን የመሰለ የዲፕሎማሲና የወዳጅነት ግንኙነት ለመመስረት መነሳቷ በታሪኳ የመጀመርያ” ነበር። በወቅቱ የኒውዮርክ ሄራልድ ጋዜጣ ስለጉዳዩ ባወጣው ዜና “ይህ ምናልባትም በዲፕሎማሲ ታሪካችን ታይቶ እማይታወቅ የተልዕኮ ጉዞ ነው” ሲል እንደጻፈ ደራሲው በመጽሐፋቸው ጠቅሰውታል።

ምኒልክ በአሜሪካ ጋዜጦች

መጽሐፉን ልዩ እና ጠቃሚ የሚያደርገው ምክንያት አንዱ በአሜሪካ እና በኢትዮጵያ የተደረገውን የዓለም አቀፍ ግንኙነት በሰፊ መረጃ ከማቅረቡም በላይ በተለይ በአሜሪካ ጋዜጦች ስለ አጼ ምኒልክ ያወጧቸውን አስተያየቶች ደራሲው በሰፊው ስላስነበቡን ጭምርም ነው።

በዚያን ጊዜ ስለ አፍሪካም ሆነ ስለ መሪዎቿ በአሜሪካ ጋዜጦች ምንም ይጻፍ ባልነበረበት ወቅት ስለ አጼ ምኒልክ ልዩ ልዩ አስተያየቶችን ያወጡት ጋዜጦች ብዙ ነበሩ። ለቅምሻ ያህል ጥቂቶችን እጠቅሳለሁ።

ምንም እንኳን አብዛኛዎቹ የአሜሪካ ጋዜጦች ስለ ኢትዮጵያ በብዛት የዘገቡት የፕሬዝዳት ቴዎዶር ሩዝቬልትን የልዑክ ቡድን የመሩትን የዋና ቆንስል ሮበርት ስኪነርን የኢትዮጵያ ጉብኝት በተመለከተ ቢሆንም ከዚያም በፊት በተለይም ከዓድዋ ድል ጋር በተያያዘ ስለ ምኒልክ እና ስለ እቴጌ ጣይቱ አንዳንድ ዜናዎች ማውጣታቸው የሚታወስ ነው። ለምሳሌ “ሀርፐርስ ዊክሊ” የተባለ ሳምንታዊ መጽሔት የኢትዮጵያን ባህላዊ ሠራዊት በብዛት ከሚያሳይ ፎቶግራፍ ጋር የእቴጌ ጣይቱን ፎቶ ግራፍ አውጥቷል። ከዚያም ቀደም ብሎ በመጋቢት 7 ቀን 1896 ዓ.ም. ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ የንጉሠ-ነገሥቱን እና የንግሥቲቱን ፎቶግራፎች ጎን ለጎን በማድረግ ያወጣው ዘገባ “ምኒልክ ባለቤታቸውን ንግሥት ጣይቱ ለዓለም አቀፍ ኤግዚቪሽን በዓል ወደ አሜሪካ ይዘዋቸው ይመጣሉ” የሚል ዜና አውጥቷል።

በፊኒክስ አሪዞና የወጣ ጋዜጣ “Menelik, King of Abyssinia, the greatest black man” (የአቢሲንያው ንጉሥ ምኒልክ ታላቁ ጥቁር ሰው)፣ “ሲል የኢንዲያና ፖሊስ ጆርናልም በኤፕሪል 12 ቀን 1904 ዓ.ም. እትሙ “ምኒልክ ታላቁ ሰው” ሲል ጽፏል። የ“ካንሳስ ጆርናል” በበኩሉ “ታላቁ የጥቁር ገዥ ምኒልክ” በማለት የንጉሡን አይበገሬነት ከአውሮፓ ኮሎኒያሊስት ወራሪ መንግሥታት ጋር እያነፃፀረ ጽፏል። የሳውዝ ካሮሊናው “ላንካስተር ኒውስ” የተባለ ጋዜጣ ደግሞ “ታላቁ ምኒልክ የሚለውን አገላለፅ መደበኛ የዕውቅና ሥያሜ አድርጎ አቅርቦታል።” ይላሉ ንጉሤ አየለ። ዘሚኒያፖሊስ ጆርናል የተባለው ጋዜጣ የአጼ ምኒልክን ፎቶግራፍ ጨምሮ ባወጣው ሐተታ “በአውሮፓ ታላላቅ ኃያላን መንግሥታት ሁሉ በከፍተኛ ደረጃ የሚከበር አንድ የአፍሪካ ንጉሥ አለ። 150,000 የሆነ ቋሚ የጦር ሠራዊት አለው። በ1895 ዓ.ም. ኢጣሊያ ከንጉሡ ግዛት አንዷ የሆነችውን ክፍለ-ሀገር ወደ ራሷ ቀኝ ግዛት ለማቀላቀል ሙከራ ስታደርግ በአፍሪካዊው ንጉሥ ጦር ተሸነፈች። እኚህ ንጉሥ ዳግማዊ ምኒልክ ናቸው፤” የሚል አስተያት አቅርቧል።

የኦሪጎን ደይሊ ጆርናል፣ የኦሪዞናው “ቢስቢ ሪቪው” እንዲሁም የሲአትሉ “ስታር” እና የኔብራስካው “ኖርፎክ ኒውስ ጆርናል” የተባሉት ጋዜጦች “በአቢሲንያው ተልዕኮ ታላቅ የህዝብ ፍላጎት መከሰቱን በየበኩላቸው ገልፀዋል። ዊልያም ኢኮርቲስ የተባሉ አሜሪካዊ በሴፕተምበር 24 ቀን 1903 በቺካጎ ሄራልድ ባወጡት ጽሑፋቸው የሚከተለውን አስፍረዋል።

“ሴንት ሊዊስ በሚካሄደው የንግድ ትርኢት ላይ የአበሻው ንጉሥ ሚኒልክ እንዲገኙ የመጋበዛቸውን ዜና ከጋዜጦች ተረዳሁ። በብዙ ምክንያቶች ይህ ግሩም ሀሳብ ነው። በመጀመርያ ደረጃ የንጉሡ መገኘት ከማንም በህይወት ከሚገኙ የዓለማችን ንጉሦች ምናልባትም ከጀርመኑ ካይዘር (Kaiser Germany) ጭምር የተሻለ ትኩረት የሚስብ ይሆናል። የበለጠ የህዝብ ቁጥርም በትርኢቱ ላይ እንዲገኝ ያደርጋል። ንጉሡ ከይሁዳ አምበሳ በመወለዳቸው የንጉሥ ሠለሞንና የንግሥት ሳባን (ዙፋን) ታሪክ ይዘዋል። ረጅም ዕድሜ አላቸው የሚባሉት የጀርመን፣ የኢጣሊያ እና የሌሎችም የአውሮፓ ነገሥታት ሥርወ-መንግሥታትና ቤተ-ሰቦች የዘር ሀረግ ከንጉሡ ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።”

ምኒልክ የሰለሞንን ክብር (ጥበብ) ለማየት ኢየሩሳሌም ድረስ የሄደች ቅድመ አያት ያላቸውና በህይወት የሚገኙ ብቸኛ ሰው ናቸው” ይላል።

በዩናይትድ ስቴት አሜሪካ እና በኢትዮጵያ መካከል የንግድ ግንኙነት እንዲመሠረት መጀመርያ ሃሳብ ያቀረቡት ሮበርት ስኪነር የተባሉት በፈረንሳይ ማርሰይ የአሜሪካ ዋና ቆንስል የነበሩት ዲፕሎማት ናቸው። ዲፕሎማቱ ለንግድ ግንኙነቱ ምስረታ አስቀድሞ በሁለቱ አገሮች መካከል የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን ላገራቸው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ደጋግመው ሪፖርት አቅርበዋል። ስኪነር ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጃንዋሪ 8 ቀን 1900 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ፣ “በአፍሪካ ውስጥ ንግዳችንን ለማስፋፋት እና ለማጥናት የሚያስችል ተገቢው ግምት የሚያሻው መስክ አለ።” ካሉ በኋላ “በአቢሲንያ ሰፊ ህዝብ የሚኖር፣ የፖለቲካ ነፃነቱም የተጠበቀ እና ምርቶቻችንን ሊያገበያይ የሚችል ሁኔታ ያለ ሆኖ፤ ነገር ግን በኛ በኩል ኦፊሴላዊ ተጠሪ እንኳ የሌለን መሆናችንን ለማስገንዘብ እፈልጋለሁ” ነበር ያሉት። ሰኪነር አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የዲፕሎማቲክም ሆነ የንግድ ግንኙነት እንድትመሠርት ጥረት ያደረጉት በፈረንሳይ ዋና ቆንስል እንዲሆኑ በሾሟቸው በፕሬዝዳንት ዊልያም ማኪንሊ ጊዜ ቢሆንም፣ ምኞታቸው የተሳካው እና ያገራቸውን ተልዕኮ ይዘው ወደ አጼ ምኒልክ የተላኩት ግን ከማኪንሊ ቀጥለው ሥልጣኑን በያዙት በፕሬዝዳንት ቲዎዶር ሩዝቬልት ነው። ስኪነር ዲፕሎማት ከመሆናቸው በፊት በ“ኦሀዮ” የጋዜጣ አሳታሚ ነበሩ።

የስኪነር የልዑካን ቡድን በፕሬዝዳንት ሩዝቬልት ወደ ኢትዮጵያ የተላከው በሦስት ምክንያት ነበር። ቀዳሚው ምክንያት በሁለቱ አገሮች መካከል የንግድ እና የወዳጅነት ስምምነት የሚከተሉትን ጉዳዮች የሚያካትት ነበር። የሁለቱ አገር ዜጎች አንዱ በሌላው አገር ሄዶ የመሥራት እና የመነገድ ህጋዊ ፈቃድ እና መብት በእኩልነት እንዲያገኙ ማድረግ፣ ሁለቱም አገሮች በንግድ ሥራ ለሚሰማሩት ዜጎቻቸው አመቺ የጉምሩክ አፈፃፀም እና ድጋፍ እንዲሰጣቸው ማስቻል እና የፀጥታ ጥበቃ እና ከለላ እንዲያገኙ ማድረግ፣ በጋራ የሚስማሙባቸውን የመንግሥት እንደራሴዎች (ተጠሪዎች) አንዱ በሌላው አገር ማስቀመጥ መቻል፣ ማለት ዲፕሎማቶች መለዋወጥም ናቸው።

ሁለተኛው የተልዕኮው ዓላማ ስኪነር ከኢትዮጵያ የእህል ዘር እና የአዝርዕት ዓይነቶች ወደ አሜሪካ እንዲያመጡ ፕሬዝዳንት ሩዝቬልት የጣሉባቸውን አደራ ዕውን ማድረግ ነው። ሩዝቬልት ስኪነር በተፈጥሮ የበቀሉ የሩዝና የቡና ዘሮችንና፣ የዱር የወይራ ተክሎችን እንዲሁም ግርቪ በመባል የሚታወቁትን የሜዳ አህዮች ወንድና ሴትም ጭምር እንዲያመጡ አዘዋቸዋል።

ሦስተኛው ዓላማ ደግሞ በሚያዝያ ወር 1904 ዓ.ም. ሴይንት ሉዊስ ከተማ በሚከፈተው የንግድ ዓለም አቀፍ ኤግዝቪሽን እና በሉዝያና መሬት ገዥ መታሰቢያ በዓል ላይ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የክብር እንግዳ ሆነው እንዲገኙ የፕሬዝዳንት ሩዝቬልትን ግብዣ ለማድረስ ነው።

የአጼ ምኒልክ በዚያ ዓለም አቀፍ ትርኢት ላይ መገኘት መስሕብነቱ በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ታምኖበታል። ስለዚህ ጉዳይ የዋሽንግተን ታይምስ ጋዜጣ በኖቨምበር 8 ቀን 1903 ዓ.ም. ባወጣው እትሙ “የምኒልክ በበዓሉ ላይ መገኘት ወደ በዓሉ ለሚመጡ ጎብኚዎች በዘመናችን የዓለም ጉዳዮች መድረክ ላይ አስደሳች ውብና ማራኪ የሆኑትን ንጉሥ ለማየት ትልቅ ዕድል ይፈጥርላቸዋል” ብሏል። የምኒልክ በአሜሪካ ኤግዝቢሽን እንዲገኙ መጋበዝ ከሌሎች የዓለም መሪዎች በተከለየ ልዩ መስህብ እንደሚሆን በርካታ የአሜሪካ ጋዜጦች ጽፈዋል። “ዘቶፒካ ስቴት ጆርናል” የተባለው ጋዜጣ የኢጣሊያን ወራሪ ሠራዊት በማሸነፋቸው በዓለም ላይ ይበልጥ የሚታወቁት የኢትዮጵያ ንጉሠ-ነገሥት አጼ ምኒልክ የሴይንት ሉዊስ የንግድ ትርኢት እንግዳ ሆነው እንደሚገኙ ታውቋል” ሲል ጽፏል።

ምኒልክ በኢትዮጵያ የነገሥታት ታሪክ ውስጥ እጅግ ልዩና የአብርሆት እንፅብራቄን የተገነዘቡ እና ያሳዩ ንጉሠ-ነገሥት ነበሩ። የሚከተሉትን የአሜሪካ ጋዜጦች አስተያየቶች ልብ ብለን ያለ ብሔርተኝነት ስሜት ብናጤነው የርሳቸው ዓለም አቀፋዊ ተደናቂነትና ዝና የኛ የኢትዮጵያውያን ተደናቂነትና ዝና ስለሆነ ልንኮራበት የሚገባ የታሪክ እውነት ነው።

“ዘስያትል ሪፐብሊካን” የተባለው ጋዜጣ ማርች 14 ቀን 1902 ስለ አጼ ምኒልክ ባወጣው ጽሑፍ “ንጉሡ ከክፍለ-ዘመኑ ታላላቅ ሰዎች አንዱ ናቸው። ይህም በተጎናፀፉት ወታደራዊ ድልና በፖለቲካ ብልህነታቸው የተገለፀ ሲሆን፤ የተራራቁ የጎሳ አካባቢዎችን ወደ ፌደራላዊ አንድነት መንግሥት አምጥተዋል”

ዋና ቆንስል ሮበርት ስኪነር ከሁለቱ የልዑካን ቡድን አባሎች ዶ/ር አብርሃም ፒስና የቡድኑ ጸሐፊ ሆኖ ከተመደበው ከሚስተር ሆራሸዮ ዌልስ ጋር በመርከብ ከኒውዮርክ ተነስተው ኦክተበር 16 ቀን ሀቨር ከተባለችው የፈረንሳይ የወደብ ከተማ ደረሱ። ከዚያም በማግሥቱ ፓሪስ በመሄድ፣ ጁቡቲ ሲደርሱ ከጉምሩክ ቀረጥ እና ፍተሻ ነፃ እንዲደረጉ የፕሮቶኮል ትብብር እንዲደረግላቸው ጠየቁ። ፈረንሳይ የአሜሪካ ልዑክ ቡድን የጠየቀውን ከጉምሩክ ቀረጥ እና ፍተሻ ነፃ የሚያደርግ ፈቃድ እንደተጠበቀው በፍጥነት አልሰጠችም። ጥያቄው ጊዜ ወሰደ። ኦክተበር 27 ቀን 1903 ማለዳ ላይ የስኪነር የልዑክ ቡድን የኢጣሊያ የወደብ ከተማ ከሆነችው ናፖሊ/ ኔፕልስ ደረሱ። ከዚያ መቻያስ ወደ ተባለችው የዩናይትድ ስቴትስ መርከብ ተዘዋውረው ጉዟቸውን ወደ ጁቡቲ ቀጠሉ። ማቻያስ የሩዝቬልትን የልዑካን ቡድን ይዛ ኖቨምበር 17 ቀን 1903 ጁቡቲ ደረሰች። አሜሪካዊው የባህር ኃይል መኮንን ሌፍተናንት ፓርልስ ከሺ እና ጥቂት የጁቡቲ ባለሥልጣኖች ማቻያስ መርከብ ላይ ወጥተው ስኪነርንና የልዑክ ቡድኑን አባሎች በሰላምታ ተቀበሏቸው። ቀጥሎ የስኪነር ቡድን በጁቡቲ የኢትዮጵያ መንግሥት ተጠሪ ከነበሩት ከአቶ ዮሴፍ ጋር ተገናኙና በሳቸው አሳሳቢነት ወልደሚካኤል የተባለውን ፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ወጣት በአስተርጓሚነት በመቅጠር ወደ አዲስ አበባ ጉዟቸውን ቀጠሉ። አሜሪካዊያኑ የልዑክ ቡድን አባሎች የኢትዮጵያን መሬት ከረገጡ ጀምሮ አይተውት በማያውቁት ኢትዮጵያዊ ትህትና እና ልባዊ ፍቅር የተላበሰ አቀባበል በየቦታው ተደርጎላቸዋል። ይህንን መልካም አቀባበል የልዑኩ ቡድን አባሎች በየበኩላቸው በጻፏቸው አስተያየቶች ከመግለፃቸውም በላይ የአሜሪካ ጋዜጦችም ጉዞውን እየተከታተሉ ይገልፁ ነበር። ለምሳሌ የዋሽንግተን ታይምስ በኖቨምበር 29 ቀን 1903 እትሙ ዜናውን ሲያቀርብ፤

“የሀረር አስተዳዳሪ ራስ መኮንን፣ በአንድ ሺህ ወታደሮች ታጅበው ቡድኑን ከከተማው ውጭ በክብር ተቀብለውታል። … ሁኔታው ልዩ ውበት እና ድምቀት የነበረው ከመሆኑም በላይ፣ አሜሪካውያኑ አይተውት በማያውቁት ዓይነት የአክብሮት ሥነ-ስርዓት አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ራስ መኮንን አሜሪካውያንን በአዲሱ ቤተ-መንግሥታቸው እንዲያርፉም ጋብዘዋቸዋል።” ሲል ጽፏል።

የምኒልክ ባህርያት

አጼ ምኒልክ አርቆ አሳቢ፣ በህዝቦች መካከል መልካም ግንኙነት እና ወዳጅነት እንዲፈጠር የሚወዱ፣ አያሌ ደግ ባህርያት የነበሯቸው ሰው እንደነበሩ “ታላቁ ጥቁር ሰው” በሰፊው ያሳየናል። ስለ ህዝቦች ግንኙነት ጠቃሚነት አወንታዊ ባህርይ እንደነበራቸው ያገኟቸው የውጭ አገር ሰዎች በብዛት መስክረውታል። የህዝቦች ግንኙነትን በተመለከተ “ባህርና መሬት ሰውን ከሰው ቢያራርቅ፣ መልካም ሃሳብ ያቀራርባል” ሲሉ ነበር ምኒልክ ግንቦት 9፣ 1896 ለሃይቲ ፕሬዝዳንት በጻፉት ደብዳቤ ላይ ስለ ግንኙነት የገለፁት።

ምኒልክ በእንግዳ አቀባበል ላይ የሰለጠነና በደግነት የተመሠረተ ባህል እንደነበራቸው በግልፅ የሚታይ ነው። ሊጎበኛቸው የሚመጣው የአሜሪካ የልዑክ ቡድን ሀረር መድረሱን እንዳወቁ እንኳን ደህና መጣችሁ የሚለውን የመልካም ምኞት መልዕክት በራስ መኮንን በኩል አስተላልፈውላቸዋል። ይህ ደግነታቸውን እና ስልጡንነታቸውን የሚያሳይ ባህርይ ነው።

ስኪነር ወደ አሜሪካ ከተመለሱ በኋላ ስለ ኢትዮጵያ በሰጡት ምስክርነታቸው፣ በአገሪቱ መልካም፣ እንግዳ ተቀባይነት፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ የንጉሡ ተራማጅ አስተሳሰብ እና የሀገሪቷን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በማድነቅ ጽፈዋል። ከዚያም ባሻገር ከወደ ኢጣሊያ አልፎ አልፎ የሚመጡ ምንጭ አልባ ዜናዎች አገሪቱ እንደሌላው የአፍሪካ ህዝቦች በጨለማ የምትገኝ፣ አረመኔያዊ የጎሳ ግጭት ያልተረጋጋች አስመስሎ ያቀርብ የነበረውን ውዥንብር ዋጋ አሳጥቶታል። አገሪቷ የተያያዘችውን ጥረትም “የአፍሪካ ጃፓን” በማለት ገልፀውታል።

የአሜሪካ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ያደረገውን ጉብኝት አጠናቅቆ ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ፤ ስኪነር ለጋዜጠኞች የሰጧቸው ገፅታ በአወንታዊ አድናቆት እንዲታዩ የሚያደርጉ ነበር ማለት ይቻላል። ጥቂቶቹን የዜና ርዕሶች እንመልከት።

ንጉሥ ምኒልክ የሜዳሊያ ሽልማቶች ለአሜሪካ ላኩ፣ ንጉሥ ምኒልክ የመልካም ጓደኝነት ባህርይ ይታይባቸዋል፣ በአቢሲንያ ዕድገት ይታያል፣ የአሜሪካኑ የአቢሲንያ ጉብኝት ንጉሣዊ አቀባበል ተደረገለት፣ ንጉሥ ምኒልክ አስደሰቱን፣ ስኪነር በአቢሲንያ ጉብኝቱ እጅግ በጣም ተደስቷል፣ አቢሲንያ የአፍሪካ ጃፓን ነች፣ ንጉሥ ምኒልክ መልካም እንግዳ ተቀባይ ናቸው፣ ምኒልክ ዩናይትድ ስቴትን ይወዳሉ፤ ለአሜሪካውያኑ ጎብኝዎች ወዳጅነት አሳይተዋል፣ ዳግማዊ ምኒልክ በአፍሪካ ኃይለኛ ንጉሥ ናቸው፣ ሀገረ-ምኒልክ የአፍሪካ ጃፓን ወይስ የአፍሪካ ኤልዶራዶ?

“ስኪነር ስለ ኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ሲገልፁ “የአዲስ አበባው አቀባበል ሊረሳ የማይችል የፈረሰኞች አጀብ እና ሰልፍ፣ ቡድኑ አይቶት በማያውቀው ውበት እና ድምቀት ተከናውኗል። የንጉሠ-ነገሥቱ እንግዳ ተቀባይነት፣ ለአሜሪካውያን ያላቸው መልካም ግምት፣ ለንግድ እና ልማት ያላቸውን ፍላጎት፣ ለቡድኑ የተደረገውን ግብዣ፣… ለፕሬዝዳንት ሩዝቬልት ያበረከቱትን ስጦታና ለቡድኑ አባላት የለገሱትን ሽልማት ስኪነር ስዕላዊና ትሁት በሆነ ቋንቋ ነው የገለፁት” ይላሉ የመጽሐፉ ደራሲ ንጉሤ አየለ ተካ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top