ቀዳሚ ቃል

ቀዳሚ ቃል ትላንትን በማክበር ነገን መገንባት!

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ዓድዋን የሚዘክሩ መርሃ ግብሮች በመበራከት ላይ ናቸው። የካቲት ፳፫ እንደ አዘቦት ወይም ከስራ እንደሚያሳርፍ ተራ ቀን የመቆጠሩ የወል ስህተት በመታረም ላይ ነው። ማኅበራዊ ሚድያው ከበዓሉ አስቀድሞ ካሉት ቀናት አንስቶ በጀግኖቹ ምስል ይሞላል። ከታሪክ መዛግብት የተገኙ ጥቅሶች እና አባባሎችም የማኅበራዊ ሚድያው ጌጦች ሆነው ይሰነብታሉ። ድሉን የሚያደምቁ አልባሳትም ይዘወተራሉ። ከአዲስ አበባ እና ከሌሎች የሐገሪቱ ክፍሎች በመነሳት በእግር ጉዞ ዓድዋ ተራራ የሚሄዱ ቡድኖችም ዓመታት አስቆጥረዋል። ይበል የሚያሰኝ በጎ ጅምር ነውና ሊበራታም ሊበረታታም ይገባል።

 በዓሉን የራስ ብቻ ለማድረግ የሚካሄዱ ሩጫዎችን ወደ ጎን ጥለን ከታሪክ መማር በሚገባን መጠን መማር ችለናል ወይ? ዓለም የአፍሪካ ብቻ ሳይሆን የጥቁሮች ፈርጥ ስለመሆኑ ጮክ ብሎ የመሰከረለትን ድል ለሐገራዊ አንድነታችን ተጠቅመንበታል ወይ? የድሉን ግዝፈት የሚመጥን ጥበባዊ ክዋኔ አለን ወይ? የህልውናችን ቀዳሚ ማሳያ እንደ መሆኑ በቱሪዝም እና በኢኮኖሚው ዘርፍ አትርፈንበታል ወይ?… የሚሉ እና ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄዎች ካነሳን ግን የአዎንታ ምላሽ የማግኘት እድላችን ይጠባል፡፡

 የዓድዋ ድል አንድ መቶኛ ዓመት በሚከበርበት ጊዜ በፕሬዝዳንት ነጋሶ ጊዳዳ የመሰረት ድንጋይ ተጥሏል፡፡ በዓድዋ ተራራ እና በከተማዋ ለታሰቡ ቋሚ መዘክሮች ማስጀመሪያ የሚሆን የመሰረት ድንጋይ ያላስቀመጠ መሪ የለም ማለት ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ ሚሊንየም ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዎርጊስ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ታሪክ ያላቸው ሌላኛው መሪ ናቸው፡፡

በአፍሪካ ኅብረት እውቅና እና የገንዘብ ድጋፍ እንደ ሚካሄድ ከተነገረለት የፓን አፍሪካ ዩንቨርሲቲ ጀምሮ አዲስ አበባ እምብርት ፒያሳ ላይ እስከታቀደው የ“ዜሮ ኪሎ ሜትር” ፕሮጀክት ድረስ በርካታ ሐሳቦች ተደምጠዋል፡፡ ዓመታትን ያስቆጠረው ውጤት አልባ ውጥን የዓድዋ ሙዚየም፣ ቤተመጻሕፍት፣ ሐውልት እና ቋሚ መዘክር መገንባትን ዓላማው ያደረገ ነበር፡፡ ቢያንስም በባሻ ዐውአሎም ስም ከተገነባው አነስተኛ ሐውልት በስተቀር የተሳካ ጅምር የለም ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ አነስተኛ የኮንስትራክሽን እንቅስቃሴ ከሚታይበት ዜሮ ኪሎሜትር በቀር ውጥኑ ከውጥን ተሻገረ ከተባለ የተጓዘው መሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ ድረስ ብቻ ነው፡፡

ቀደምቶቻችን የዘመናቸውን ታሪክ በጉልህ ጽፈዋል፡፡ ዘመናዊው ዓለም ውስጥ የምንገኘው የልጅ ልጆቻቸው ከትላንት የታሪክ ሰበዝ ላይ ዛሬአችንን የሚያሳምሩ እና ነጋችንን ብሩህ የሚያደርጉልንን ክስተቶች መምረጥ ሀላፊነታችን ነው፡፡ ማንነታችንን በጥሩ አለት ላይ እንገነባ ዘንድ ሁሉ በእጃችን ነው፡፡ ከታሪክ መማር የሚቻለው ትልቅ ነገር ከታሪክ መማር ነውና የዓድዋ ድል የሐገራዊ አንድነት መሰረት፣ የቱሪዝም ግብአት፣ የሕብረ ብሔራዊነት ጌጥ፣… እንዲሆን አለመስራታችን የነገ ተወቃሽ ብቻ ሳይሆን የዛሬ ባለእዳ ያደርገናል፡፡ ድል አክባሪነታችን የሚለካው ትላንትን በማክበር ብቻ ሳይሆን ነገንም በመገንባት ነው!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top