አጭር ልብወለድ

መምህሩ

መምህርነት የሚወድደው ሙያ ነው። የባለፀጋ ልጆች በሚማሩበትና አማርኛ መናገር ደመወዝ በሚያሰቀጣበት ት/ቤት እጅግ በጣም ተወዳጅ አስተማሪ ነው። በተለይም ታሪክ ማስተማር አይታክተውም። ተወዳጅ ዕለታዊ ተግባሩ ከሆነ ሰንበት ብሏል። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ 10ኛ ክፍል ማስተማር ከጀመረ ዘጠኝ ዓመት አስቆጥሯል። ከንጋት እሰከ ምሽት በተከሸነ እንግሊዝኛ ብቻ ከአንዱ የጦርነት አውድማ ወደ ሌላኛው፣ ከጨለማው አህጉር ወደ ብርሃናማው ይሸጋገራል። ከሶሻሊዝም እስከ ካፒታሊዝም ሀሳቦች፣ ከአስቸጋሪ ወደ ፀጥተኛው፣ እንዲሁም ወደ መሀከለኛ ክፍል እየቀዘፈ የታሪክ ነጋሪቱን በፈረንጅ አፍ ይጎስማል።

የኢትዮጵያን ታሪክ በሚያስተምርበት ጊዜ ግን ይለያል። የተገለለውን የሐገር ውስጥ ቋንቋ ጣልቃ ያስገባል። በየመሐሉ አማርኛን ጣል ጣል ያደርጋል። ዘጋቢ ቪድዮዎች እያሳየ፣ ድምፁን ከፍና ዝቅ እያደረገ፣… ሲያስተምር የሚተውን ይመስላል። ድራማዊ አቀራረቡ፣ ለኢትዮጲያ ታሪክ የሚያሳያውን ተቆርቋሪነት ስሜታዊ ያደርጋል። የሚቀላቅለው አማርኛ ለተደጋጋሚ የገንዘብ ቅጣት ሲዳርገው “There is no condemnation among the contaminated people” እያለ ያልፈዋል።

የሚያስተምርበት ዘዬ ተተችቷል። ከመደበኛው የመማማሪያ መጽሐፍ ውጭ እንዳያስተምር፣ የታሪኩ አጋዥ ነው እያለ ለተማሪዎች የሚያድለውን የመፃሕፍት ቅጂ እንዲያቆም፣ የመጻሕፍት ጥቆማ እንዳያደርግ፣ በእረፍት ቀናት ከተማሪዎች ጋር የሚያካሂደውን የቤተ መዘክር ጉብኝት እንዲያቋርጥ፣… የትምሕርት ቤቱ አስተዳደር ከቃል እስከ ጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶታል።

ማስጠንቀቂያው ብዙ አያሸብረውም። ደጋግሞ

“የምሰራውን አውቃለሁ” ይላል። “ታማኝነቴ ለሙያዬ ነው”፣ “ስራዬ ኢትዮጵያዊ ልጆችን መገንባት ነው” የሚሉ አባባሎችን ደጋግሞ ሲጠቀምባቸው ተሰምቷል።

ባልደረባ ወዳጆቹ ነገሩን እንዲያርም ሲመክሩት

“የዕይታ መለያየት ነው። እነሱ ወንጀል የሚሉትን እኔ መብት እንደሆነ ተቀብያለሁ። ህሊናዬ ‘ሕግ ጣስክ’ ከሚለው ድምጽ በላይ ‘በራሱ የሚኮራ ትውልድ እየፈጠርክ ነው’ የሚለውን ጮክ ብሎ ይነግረኛል” የሚል ምላሽ ይሰጣል።

የካቲት 22 ቀን በዓድዋ ድል ዋዜማ እንዲህ ሆነ። የመማሪያው ክፍል በተማሪዎች ተሞልቷል። ብዙ ጊዜ እንደዚህ ነው። ከሌሎች የትምህርት ዐይነቶች በተለየ በርካታ ተማሪዎች ይኖራሉ። ተማሪዎቹ ከመምህሩ የሚወረወሩ ቃላትን እና ዓመተ ምህረቶችን ማስታወሻ ደብተራቸው ላይ ለማስፈር ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል። ባለፈው ክፍለ ጊዜ የተማሩትን እየከለሱ፣ “ነው!”፣ “አይደለም!” በሚል እየተከራከሩ ሲጠብቁ መምህራቸው ገባ። ሁሉም ከመቀመጫቸው ተነሱ።

“እንደምን አረፈዳችሁ?”

አላቸው። ከምላሻቸው በፊት ድንጋጤ ቀደማቸው። ለአማርኛ የራቁ ለእንግሊዘኛ የቀረቡ (ከራሳቸው የተነጠሉ በባእድ የተጠለሉ) ናቸው። የኑሮ ደረጃቸው ከጎረቤቶቻቸው ብቻ ሳሆን ከሐገራቸውም ይበልጣል።

“ፈረንጆቹ” ነው ስማቸው። የሚናገሩት ብቻ ሳይሆን የሚያስቡትም እንደ ባህር ማዶ ነው የሐሳባቸው ሚዛን የሚለካው በቁስ ብቻ ነው። ሀገራቸው ውስጥ ያለው አካላቸው ብቻ ነው። ሐሳባቸውም መንፈሳቸውም ባህር ከተሻገረ ሰንብቷል

ተማሪዎቹ የአስተማሪያቸውን ጥያቄ ”ግ…ድ” (Good) በምትል እጥር ምጥን ባለች እንግሊዝኛ መለሱ። እንዲቀመጡ በምልክት ከነገራቸው በኋላ እንዲህ አላቸው

“Today am gonna tell u about the greatest spy on the history of Ethiopia during the victory of Adwa in Amharic”

ማስታወሻ መያዝ የሚፈልግ ተማሪ በደብተሩ ጀርባ ማስታወሻ መያዝ ይችላል

ጠመኔውን ከገዋኑ አወጣ፡፡ ቀን ጻፈ፡፡ የጻፈው ነገር ቀን መሆኑን ከተጻፈበት ስፍራ የተረዱት ተማሪዎች የግዕዝ ቁጥሩን ተመልክተው እርስ በእርስ ተያዩ፡፡

“ዛሬ ነጭን ያንበረከክንበት ቀን ነው ስለዚህ አቆጣጠራችንም፣ አነጋገራችንም፣ አጻጻፋችንም፣… ኢትዮጵያዊ ብቻ ይሆናል” አላቸው፡፡

አማርኛ መምህር ሳይቀር በውጭ ቋንቋ በሚቆጥርበት፣ ሰዓት በሐገር ውስጥ በማይቆጠርበት ትምህርት ቤት፣ የታሪክ መምህሩ ድርጊት ከእብደት የሚስተካከል ነው፡፡

ረዘም ያለ ጢሙን እየፈተለ ጥቂት ከተከዘ በኋላ እንደ መባነን ብሎ ጎሮሮውን አጸዳ፡፡ ባሻይ አውዓሎምና የኢትዮጵያ የስለላ ታሪክ የሚለውን በየማነ ገብረመስቀል የተፃፈውን መጽሐፍ ይዟል።

ጥቁር ሰሌዳው ላይ የኢትዮጵያ የስለላ ታሪክ ብሎ ከጻፈ በኋላ ንግግሩን ጀመረ፡፡

“የዛሬ 124 ዓመት ልክ በዛሬዋ እለት ጀነራል ባራቴሪ በስሩ ያሉትን ጄነራሎች የኢትዮጵያ ሠላዮች በሠጡት መረጃ ላይ ተመስርቶ ባወጣው የጦርነት እቅድ ላይ እየተወያዮ ነበር። አራቱ ጀነራሎች ዳቦር ሜዳ፣ አሪሞንዲ፣ ኤሌና እና አልበርቶኒ ናቸው። አብዛኛዎቹ ምሽግ ውስጥ ከመቆየት ወደ ኢትዮጵያ ሠራዊት ተጠግቶ ማጥቃትን መርጠዋል። በእቅዱ ላይ ወደ ኢትዮጵያ፤ የኢትዮጵያን የጦር ሠፈር እንዲሠልሉ የተላኩ ሠላዮች እየተጠበቁ ነበር። ምናልባትም የጦርነቱን እቅድ የሚያስቀይር አዲስ ሐሳብ ካለ ተብሎ መሆኑ ነው። ውጊያው የሚከናወንበት ቀንና ሠዓት ገና አልተወሰነም።

ባራቴሪ ከዓድዋ አጠገብ የሚገኘው ‘ሶዎሪያ’ የተባለ ቦታ ከስብሰባው በኋላ ብቻውን ቆዝሟል። ቦታው በሰንሰለታማ ተራራ ተውጧል። ከእሱ ይልቅ የሀገሩ በቅኝ ግዛት ምኞት መዋጥ አሳስበው። ሽንፈትን ማሰብ ባይሻም የዶጋሊና እንዳኢየሱስ ኩርኩሞች ወደ አእምሮው እየመጡ ሀሳቡን ያናጥቡታል። ዲስክራስያቶ ሳይል አይቀርም። ደግሞ ኢትዮጵያን ያሸነፈ የመጀመሪያው ጣሊያናዊ የጦር መሪ ተብሎ በሀገሪቱ መሪና ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሸለም፣ ህዝብ አደባባይ ወጥቶ ባጀብ ሲቀበለው፣ የሀገሪቱ ጋዜጦች የፊት ገፅ ላይ ፎቶውን አድርገው ህዝብም እየተናጠቀ ሲያነበው፤ በምናብ ተመልክቶ ፈገግ አለ።

እንትጮ (ዓድዋ) ተወልዶ የራስ አሉላና የራስ መንገሻ አገልጋይ በመሆን፤ ቋንቋቸውን በማወቁ ለጣሊያን ወታደሮች እንቁላል፣ ማርና ነጭ ሽንኩርት ከአስመራ እስከ ምፅዋ ይሸጥ ስለነበረው፤ ብዙውን የኤርትራ መሬት እና የጣሊያንን የጦር ሠፈር ስለሚያውቀው፤ የኢጣሊያ ሰላይ በመሆን እነባራቴሪ የተሳሳተ መረጃ እንዲያገኙ በማድረግ ስለተሣካለት ሠው ጥቂት ልንገራችሁ፡፡ አውዓሎም ይባላል፡፡

ጥር 1825 ዓ.ም. ዓድዋ አሕፈሮም ወረዳ የሀገሪቱን ትልቅ ሰላይ ለመቀበል ጣር ላይ ናት፡፡ ወ/ሮ ሣህሉ ባህሩ ማርያም! ማርያም እየተባለላቸው ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ ዱብ ሲያደርጉ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ትንሽ የሚመስል ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ማንም አልጠረጠረም፡፡ እንደ አከባቢው ልማድ 7 ጊዜ እልል ተባለለት።”

ተማሪው በንቃት እና በተመስጦ እያዳመጠ ነው፡፡ መምህሩ ትረካውን ቀጥሏል፡፡

“የአቶ ሀረጎት ሠረቀ ብርሃን እና የወ/ሮ ሣህሉ ባህሩ ትዳር ሁለት ልጆችን ቢያፈራም ሁለቱም በጨቅላነት ሞተውባቸዋል። አውዓሎም በህይወት የቆየ ብቸኛ ነው።

ብርቅ ልጃቸውን አንቀባርረው አሳደጉት። ፈለገ ህይወት አስተማሪ ከነበሩት ካህን የዲቁና ትምህርቱን ጀመረ። ፊደል መለየትና ማንበብ ቢጀምርም በእርሻ ስራ ምክንያት ትምህርቱን አቋረጠ። በጉርምስና ጊዜው መዋኘትና መሮጥ ይወድ ነበር፡፡ “ቃርሳ” የተባለውን ባህላዊ የአካባቢው ጨዋታም ይወደው እና ያዘወትረው ነበር፡፡ (‹ቃርሳ› የትግራይ ልጆች በትንሳኤ ሰሞን የሚያዘወትሩት ባህላዊ ጨዋታ ነው)

አባቱን በድንገቴ ሞት ያጣው አውዓሎም ቤተሰቡን ለመርዳት በአባቱ ሙያ ተተካ፡፡ የጥብቅና ሙያ ላይ ተሰማራ፡፡ በውርስ ሙያው ላይ ጥበብ ጨምሮባት ጥሩ ጠበቃ ወጣው።”

የታሪክ መምህሩ የተማሪዎቹ በተመስጦ መከታተል ወሬውን እንዲቀጥልበት ብርታት ሰጥቶታል፡፡ “ጥሩ ጠበቃ የነበረ ቢሆንም ስራውን አልቀጠለበትም” ብሎ ጥቂት በክፍል ውስጥ ጎርደድ ጎርደድ ካለ በኋላ

“አውዓሎም የጥብቅና ስራውን ካቋረጠ በኋላ ቅቤ፣ ማርና ነጭ ሽንኩርት እስከ ምፅዋ እየሄደ ለጣሊያን ወታደር ይሸጥ ነበር። በሂደት አከባቢውን ሰላወቀ ለራስ አሉላና ለራስ መንገሻ ሰላይ ሆኖ ተቀጠረ።

የጄነራል ባራቴሪ ሰላዮች የኢትዮጵያን የጦር ኃይል ለመሰለል ዓድዋ ደርሰዋል። ከሰላዮቹ መሀል አንዱ (ባሻይ አውዓሎም) ዘመድ ጥየቃ በሚል ሊሰልሉ አብረዋቸው የመጡትን ነግረው ወደ ራስ አሉላ ነጎዱ፣ ራስ መንገሻንም አገኙ። የጠላትን መልክዓ-ምድራዊ  አቀማመጥ ሁኔታ አሳወቁ።

ራስ መንገሻ፤ ባሻ አውዓሎም እንዳይታወቁ የአሸከሮቻቸውን ልብስ አልብሰው ወደ አፄ ምኒልክ እልፍኝ አስገቧቸው። ለሁለቱ ራሶች የነገሯቸውን ለጃንሆይም (ምንልክ) አስታውቋቸው። ራስ አሉላ፤ ባሻይ አውዓሎም ለጣሊያን የተሳሳተ መረጃ እንዲያቀርብ ሀሳብ አቅርበው ጃንሆይ ፈቀዱ።

ከጃንሆይ እልፍኝ እንደወጡ ራስና አውዓሎም ስለሚሰጡት አሳሳች መረጃ ተነጋገሩ። መረጃውም የኢትዮጵያ ሠራዊት ስንቅ አልቆበት ወደየመጣበት እየተመለሠ እንደሆነ፣ በወረርሽኝ ማለቁን፣ ለመሳለም ወደ አክሱም ፅዮን የካቲት 21 እንደሚሄድና እስከ 23 ድረስ እንደማይመለስ፣ ንጉሰ-ነገሥቱም የካቲት 23 ቀን ፀሎት በማድረግ እንደሚውሉ ለጠላት ሰላዮች ወሬ ለማድረስ ተስማሙ። አውዓሎምም ወደ ባልደረቦቹ ተመለሠ፡፡

የጠላት ሠላዮች መረጃውን እንዳይጠረጥሩ “ስንቅህ ያለቀብህ ሁሉ ወደ ሀገርህ ሄደህ፤ ስንቅህን አዘጋጅትህ እንድትመለስ ተብለሀል” የሚል አዋጅ ተነገረ። የተወሠነው ጓዙን እየጠቀለለ እንዲጭንና ሠራዊቱ ግራ እንዳይጋባ ደግሞ ለጦር አበጋዞቹ ምስጢሩን የሚነግሩ ፈረሰኞች ተልከው በተጠንቀቅ እንዲጠብቁ ተደረገ። ንጉሱ መታመማቸውን፣ ወረርሽኝ መግባቱንና ብዙ ወታደሮች መግደሉን፣ ብዙ ሠራዊት ወደ ቤ/ክርስትያን መሄዱን ወደ ጀሯቸው ደረሰ። ጥብስቅ ያለ መረጃ ያገኘው የሰላዮች ግብረ ኃይል እሽቅድድም በሚመስል ሁናቴ ለአለቆቻቸው ወሬ ለመንገር ቸኩለዋል። 10 ሰዓት ተጉዘው  የካቲት 21 ቀን ሶዋሪያ ገቡ፡፡

በፍዘት ውስጥ የነበረው ጀነራል ባራቴሪ ሰላዮቹ መድረሳቸውን ተመለከተ። ትኩስ መረጃም እንደመያዛቸው ማምሻውን ብቻ ለብቻ ጠይቆ ያገኘውን መረጃ ሲገጣጥመው ያልተዛባና አንድ ሆኖ አገኘው። የካቲት 23 ወደ ዓደዋ ቢሄድ የደከመ፣ ያልተቀናጀና ቁጥሩ ያነሰ ሠራዊት እደሚገጥመው አውዓሎም አስረድቶታል”

ሰፊውን ክፍል በዝግታ እርምጃ እየተጓዘ ወደ ጥቁር ሰሌዳው አምርቶ የካቲት 22 ማለዳ ብሎ ጻፈ፡፡ የተማሪዎቹን ሐሳብ ለመቆጣጠር በመቻሉ ውስጡን ደስታ እየተሰማው ነው፡፡

“አራቱ ጄነራሎች በባራቴሪ ቢሮ ተሠብስበዋል። የሰላዮቹ መረጃ ሪፖርት ተደረገ። መረጃውን ተመስርቶ ውሳኔ ተላለፈ።

“ማንኛውም ወታደር 112 ጥይት፣ የሁለት ቀን ስንቅ፣ ከላይ የሚደርበውን ካፖርት፣ የውሃ ኮዳና የዳቦ ኮረጆ እንዲይዝ ይደረግ። በየሻለቃው መሀል መድሀኒት የጫኑ ሁለት በቅሎዎችና ጥይት የጫኑ ስምንት በቅሎዎች እንዲመደቡ ይሁን። ዕቃና ጥይት የጫኑ ሌሎች አምስት በቅሎዎች ለአንድ ነጂ ወታደር እየተሰጠው በባታሊዮን ከኋላ ይከተል። የእርድ ከብት ከነመሣሪያው ሠራዊቱን ተከትሎ  ይጓዝ። ስልከኞችና የቴሌግራም አስተላላፊዎች መሣሪያዎቻቸውን ይዘው በየክፍሎቻቸው ሆነው ከየክፍሉ የጦር አለቆች የሚሠጣቸውን መልእክቶች ለጠቅላይ ሹሙ በፍጥነት እንዲያስተላልፉ ትዕዛዝ ይሰጣቸው። ምንም እንኳን ጦሩ በቀኝ፣ በግራ፣ በመካከልና በኋላ ለአራት ቢከፈልም ከዋናው ሰፈር ለጦርነት ጉዞ በሚጀመርበት ሰዓት አንዱ ሌላውን ርቆት እንዳይሄድና ተነጥሎ በመገስገስ ከጠላት ጦር ጋር ብቻዉን ገጥሞ አደጋ እንዳይደርስበት ጥንቃቄ መደረግ አለበት፣ በጉዞው ላይ ማጨስ፣ መብራት ማብራት፣ መነጋገር ክልክል ነው”

የሚል መመሪያ ለእያንዳንዱ ተዋጊ ደረሰ፡፡”

መምህሩ በድራማዊ አቀራረቡ ድምጹን እያጎረነነ እና እያሰለለ፣ ፈጠን ብሎ እየተራመደ እና እየቆመ፣ እየሳቀ እና እየተኮሳተረ ትረካውን ቀጥሏል፡፡ ተማሪው በተመስጥኦ ያዳምጣል፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ጥቁር ሰሌዳው አምርቶ ሌላ ርእስ ጽፎ አሰመረበት፡፡ የካቲት 22 ምሽት 3፡00፣

“በሶዋሪያ ወታደራዊ ካምፕ የኢጣሊያ ብሄራዊ መዝሙር ጎላ ባለ ድምፅ ተዘመረ። ሰንደቅ አላማ ተሰቀለ። “ታላቋ ኢጣሊያ ለዘላለም ትኑር” ተባለ። ዳቦር ሜዳ 3800 ወታደርና 18 መድፍ ይዞ ‘በላህ አምባ’ የተባለውን ቦታ እንዲቆጣጠር፣ ጀነራል አሪምንዲ 2493 ወታደርና 12 መድፍ ይዞ የበላህን ተራራ እንዲቆጣጠር፣ ጀነራል አልቤርቶኒ 4076 ወታደርና 14 መድፍ ይዞ ኪዳነ ምህረት ተራራን እንዲቆጣጠር፣ ጀነራል ኤሌና 4150 ወታደርና 12 መድፍ ይዞ ራዕዮ ተራራን እንዲቆጣጠርና ሌሎች 500 የሚሆኑ ወታደሮች ደግሞ ከጄነራል ባራቴሪ ጋር ተመደቡ።

የጉዞው መሪዎች አውዓሎም ናቸው፡፡ ተራራውን እንደ እጃቸው መዳፍ ያውቃሉ ተብሎ ስለተገመተ፣ ለጣሊያን እንደሚሰሩ ስለታመነበት፣ ግዙፉን የጣሊያን ጦር የመምራቱን ኃላፊነት ወስደዋል፡፡ እነ አውዓሎም የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው ከጠላት ጦር ጋር ወደ ወገን ጦር አቅጣጫ መንገድ ጀምረዋል፡፡ የጣሊያን ወታደሮችን በእግር መንገድ ለማድከም ረጅሙን መንገድ መርጠዋል፡፡ ጉዞው በዝናብ እና ዝናቡ በፈጠረው ጭቃ አስቸጋሪ ቢሆንም አልተቋረጠም፡፡ ንጋት ላይ አብዛኛው ጦር ዓድዋ ደርሷል።”

ጥቁር ሰሌዳው ላይ የካቲት 23 ንጋት ብሎ ከጻፈ በኋላ የተለመደ ትረካውን ቀጠለ፡፡

“ሁሉም ጀነራሎች ካርታው ላይ በተቀመጠላቸው ስፍራ ደርሰዋል። በዚህ ጊዜ አውዓሎም ጠላትን ተሰውረው በማምለጥ ወደ ወገን ጦር ተቀላቀሉ፡፡ የጠላትን ጦር አመጣጥ እና አጠቃላይ ሁኔታ ለራስ ዓሉላ ተናገሩ። ራስ አሉላ የጠላትን መድረስ ለሌሎች የጦር መሪዎች ነግረው ጦራቸውን፤ ጠላት የተጫኑ መድፎችን አራግፎና ገጣጥሞ ምሽግ ለመያዝ ጊዜ እንዳያገኝ ፈጣን ጥቃት እንዲሰንዝር አደረጉ።

የራስ መንገሻ፣ የንጉስ ሚካኤል፣ የራስ መኮንን፣ የራስ ወሌ፣ የንጉስ ተክለሃይማኖት ጦር ተጨማሪ ድጋፍ ሰጥቶ ጣሊያንን ገጠሙት። ኢትዮጵያ ብልጫ ወሠደች። ጄነራል አልቤርቶኒ ተማረከ። ጄነራል አሪሞንዲና ዳቦር ሜዳ የሞትን ፅዋ ጠጡ። ጀነራል ኤሌናም ቆስሎ አመለጠ። የጦርነቱ እቅድ ነዳፊ ባራቴሪም ከመማረክ መሸሽን መረጠ። ነጭ ለብሰው የሚዋጉ ወኔያም የኢትዮጵያ ወታደሮችንም በጦር መነፅር ከሩቅ ተመልክቶ ምንም እንኳ ጠላት ቢሆኑም እንዲህ በማለት መስክሮላቸዋል

“ኢትዮጵያዊያኖቹ ደግሞ ከቋጥኝ ወደ ቋጥኝ እየዘለሉ ለህይወታቸው ሳይሰጉ በአበደ መንፈስ ጠላታቸውን ይጨፈጭፋሉ” 

ዛሬ ጥቁሮች ነፃነታቸውን ያገኙበት ቀን ነው። አውዓሎምም በትውልድ ሲዘከር ይኖራል። ክብር ለአባቶቻችን!!”

ታሪኩ መጠናቀቁን ያስተዋሉት ተማሪዎች ለመምህራቸው አጨበጨቡ፡፡ የሰሙትን ታሪክ ገሚሱ በግርምት፣ ቀሪው በደስታ፣ ሌላው በጥርጣሬ እንደተመለከቱት መምህሩ ገብቶታል፡፡

በመካከል አንድ ተማሪ “It doesn’t seem real” አለ።

“ለምንድነው ይህን ጀግና እስከ ዛሬ ያላወቅነው?” ሌላዋ ተማሪ ቀጠከለች፡፡

“አውዓሎምን የሚዘክር ምን ታሪካዊ ነገር አለ?”

መምህሩ መልስ አልነበረውም፡፡ ባሻ አውዓሎም ከድሉ በኋላ የእንትጮ አስተዳዳሪ ሆነው መሾማቸውን፣ በ97 ዓመታቸው ማረፋቸውን ሳይነግራቸው ከክፍሉ ሲወጣ ደስ እያለው ነበር፡፡

የእሱ እና የተማሪዎቹ ደስታ አለቆቹን እንደማያስደስት አውቋል፡፡ እንደተለመደው የትምህርት ቤቱን አማርኛ ያለማውራት ሕግ አፍርሰሃል፡፡ በመማሪያ መጽሐፋችን ውስጥ ያልሰፈረ ታሪክ ተናግረሃል ብለው ደሞዝ እንደሚቀጡት ጠርጥሯል፡፡ ከቀናት በኋላ “በተደጋጋሚ በተሰጦዎት የቃል እና የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ሊታረሙ ባለመቻልዎ ይህ የስንብት ደብዳቤ ተሰጥቶታል” የሚል ደብዳቤ እንደሚደርሰው ግን አልገመተም፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top