ታዛ ቲዩብ

ከአጤ ምኒልክ ቤተ-መንግሥት ግቢ ቁፋሮ አልማዝ እና እንቁ ተገኘ !!

የአጤ ምኒልክ ቤተመንግሥት ቅጥር ግቢ የግንባታ ማእከል መስሏል። ግሬዴር፣ እስካቫተር እና ገልባጭ መኪናዎች እግቢዉ ዉስጥ እያጓሩ ይርመሰመሳሉ።

ከቆፋሪዉ ግዙፍ መኪና ማማ ላይ የሰፈረችው ሜካኒክ ወዳኋላ – ወደፊት እያሽከረከረች፣ እያስጓራች፤ ማርሽ እየቀያየረች፤አፈር አስዝቃ፣ ከገላጣዉ ጥግ ትከምራለች። ግዙፉን የብረት አካፋ ከጉድጓዱ ሰደደች። ከመቅጽበት ከድማሚት ፍንዳታ የማይተናነስ ኃይለኛ ጩኸት አካባቢውን አናወጠው። ሜካኒኳ፣ አካፋዉ ከምን ነገር ጋር ተጋጭቶ ይህ ድምጽ ሊወጣ እንደቻለ ለማረጋገጥ፣ ከማማዉ ወርዳ እየተጣደፈች፣ በረጅሙ መቆፈርያ ዘንግ ቁልቁል እየተንሸራተተች ወደጉድጓድ ሰመጠች። ከሳሎን የማይተናነስ የብረት ሳጥን (ኮንቴነር) ተቦርድሶ፣ ክዳኑ በአንድ ወገኑ ተቦድሶ አየች። የሚያብረቀርቁ ክብ ነገሮች ሞልተዉበታል። እፈራች እጇን ሰደደችና አንዱን አነሳች። ከኛዉ የብረት ባለንድ ብርና ባለሃምሳ ሳንቲም ሰፋ ያለ፣ የሴት ምስል የታተመበት፣ የሚያምር ክብ ነገር ነዉ። ፈዝዛ ቆመች። ምን ማድረግ እንዳለባት ስታሰላስል ሃሳብ መጣላት። የሚቻላትን ያክል እየዘገነች ከቱታዋ ሰፋፊ ኪሶች አጨቀች። ከጉድጓዱ ወጥታ ወደ ኢንጂነር አለቃዋ ሮጠች። ከዛፍ ስር ሆኖ፣ሰፊ ሰማያዊ የፕላን ወረቀት ያያል።

 “ኢንጅነር አንዴ ላነጋግርህ ነበር።” አለች የቱታዋን እጅጌዎች በወገቧ ላይ እያሰረች።

ቀና ብሎ አያት። ከወገቧ በላይ ካናቴራውን የወጠረውን አጎጠጎጤዋን በአይኑ አንዴ ገረፈዉና ሳያስበዉ ምራቁን ዋጠ። መልስ ሳይሰጣት ወደ ወረቀቱ ተመለሰ።

“አልሰማኸኝም እንጂነር?”

 “ከተበላሸብሽ መካኒኩን አነጋግሪ።” አለ አይኑን ከወረቀቱ ሳይነቅል።

 ይህ ኢንጂነር ከሌሎች ሰራተኞች ጋር እየተሳሳቀ እሷ ላይ ሁሌ መኮሳተሩ ያናድዳታል። በተለይም ባለፈዉ ሳምንት በሴቶች የቴሌቪዥን ፕሮግራም ቀርባ፣እንዴት በዚያ ከባድ ስራ ላይ እንደተሰማራች ማብራሪያ ከሰጠችና፣ ተደናቂዋ ሜካኒክ እየተባለች ስትሞገስ ካየ በኋላ የበለጠ መኮሳተሩ አስገርሟታል።

 “ብልሽት አይደለም እኮ፤ ሌላ ከባድ ነገር ነው ኢንጅነር። አንዴ ወደ ጉድጓዱ ብንሄድ።”

“ምንድነው እሱ? ለምን እዚህ አትነግሪኝም?” አለ የብረት ቆቡን እያስተካከለ አይኑን ከደረቷ ተክሎ።

“ግራ የሚያጋባ ምስጢር ነው……ወደዚያ እንሂድ።” “እንዲህ ነችና!” አለ በልቡ.. በፍቅር እንደወደቀላት ነቅታበት፣ ልታግዘዉ እንዳሰበች ገምቶ።

 ይህቺ ሴት የማይደፈርን ሁሉ መድፈር የምትወድ እንደሆነች አልተጠራጠረም። እየኮራ በዝምታ ከጎን ጎኗ ሲራመድ ከኪሷ አንዱን ክብ ብረት አውጥታ ሰጠችው። ነገርየውን እንደተቀበለ ደንገጥ ብሎ ቆመ። አገላብጦ መረመረ፤ ወደ ሜካኒኳ አየ።

 “ምንድነው ይሄ?”

 “ታች ከጉድጓዱ አምስት ሜትር ላይ በብረት ሳጥን ተሞልቶ አገኘሁት።”

 ኢንጅነሩ የብረት ቆቡን አውልቆ፤ክብ ብረቱን ጭንቅላቱ ላይ አስቀመጠና ቆቡን ደፋበት። ወደ አፈር ቁልሉ ተጣደፈ። የመቆፈሪያውን ዘንግ አቅፎ እየተንሸራተተ ወደ ጉድጓዱ ተሰወረ። ብዙም ሳይቆይ በብረት ቆቡ ሞልቶት እያለከለከ ከጉድጉዱ ወጣ።

 “ስሚ፤ ይሄ ነገር ምን እንደሆነ ታውቃለሽ?” ትኩር ብሎ አያት። ደረቷን ሳይሆን አይን አይኗን።

 “ኪነቶች በክር ከአንገታችው አስረው እስክስታ ሲዘፍኑበት ያየሁ ይመስለኛል።” አለች ፈገግ ብላ።

“ኦኬ! ይሄ ነገር ምስጢር ነው። የቤተ መንግስት ሚስጢር። ያለኔና ያላንቺ የሚያውቀው የለም። ገባሽ?”

 “ምንድነው እሱ?”

 “የኪነት ጌጥ ነው። አሁን እሱን ጉድጓድ ተይና ዳርዳሩን ቆፍሪ። መጣሁ።”

 የብረት ቆቡን ከሞላው ነገር ላይ የዲዛይን ወረቀቱ ከድኖ፣ ሸፍኖ እየተጣደፈ ተሰወረ። ሜካኒኳ እመር ብላ፣ ከማማው ላይ ወጥታ የዳርዳሩን አፈር ማውጣቱን፣መቆለሉን፤መግፋቱን ተያያዘችው።

 ድንገት የብረት ቆብ የደፋ ፈረንጅ ወደ ማማው እያየ ጮኸ። የሰማይ ስባሪ ነዉ የሚያክለዉ።

 “ዩ…ዩ!፣፣ዩ!..”

 ደንግጣ ሞተሩን አጠፋች፣ ልትሰማው ስትል።

 “ኢንጂናሬ ካም ሂር፤ናዎ ጎ ዌር? ዌር?” አላት ፈገግ እያለ።

 “ጎ ዚስ ሮድ። ካም፤ናዎ ፋስት።” አለችው ቶሎ እንደሚመለስ ልታስረዳው ቁልቁል እያየችው።

“ዩ ዳዎን ዳዎን ካም።” አላት በፈግታ ተሞልቶ።

የዋናዉ የአለቃ ትዕዛዝ ሆኖባት ከማማው መውረድ ጀመረች። ደፋር ፈረንጅ መሆኑን ከዚህ ቀደም በሁኔታዉ ተረድታለች። ከመኪናው ዘላ ከመሬት ዱብ ስትል ተዘረገፈ።ፈረንጁ ግራ በማጋባት ቁጢጥ ብሎ እየለቀመ አገላብጦ መረመረ።ፈነደቀ።

 “ዚስ ጉድ ማሪያ ትሬዛ። ዩ ሃቭ ብዙ ብዙ?”

“ማሪያ ትረዛ?” ግራ ተጋባች።

 “ማርያ ትሬዛ. . .ኢታሊያ ዶላር… ፒክቸር ታይቱ።” አለና ወደ አጤ ምኒሊክ አዳራሽ ጠቆመ።

 “ጣይቱ?”

 “የስ። ታይቱ ኢታሊያ ። ማርያ፣ ማርያ ተሬሳ።”

 “ኖት አንደርስታንድ።” አለች በሀፍረት ፈገግ ብላ። ፈረንጁ አጠገቧ ቆሞ ትከሻዋን አቀፈ።

“አይ ሚኒሊክ…ዩ ታይቱ…ዚስ ኢታልያ ታይቱ።” ስርዓት በጎደለው ቀልድ፣ የሚያመለክት አስመስሎ ጉንጯን በሌባ ጣቱ እየነካካ።

 “እባክህን የምትለዉ እልገባኝም፤ሂድልኝ ስራዬን ልስራበት።” ፈገግ ብላ ወደ ማማዋ አመራች። ኩስ..ኩስ..ኩስ እያለ ደርሶባት ያዛት። ከኪሱ አስር ዶላር አወጣ፤አንዱን ማራያ ትሬዛ ከኪሱ ከትቶ አንድ ዶላር አስያዛት። ሌላዉን ከቶ ሌላ አስያዛት። አስር ከቶ፣ አስር ዶላር አስጨበጣት።

 “አዘር ኖ? ፖኬት ፉል. . .ዶላር ፉል።” በጣቱ የቅድሙን የሰውነቷን ቦታ ገፋ አደረገ። ድንግርግሯ የወጣው ሜካኒክ በዶላሩ ተገርማ የባሰውኑ ተደነጋገረች። “ዚስ ኢታሊያ ዶላር፣ ሲልቤሮ! ቬሪ ቬሪ ጉድ። ዶላር ሲልቤሮ።” አለና ተጨማሪ በርከት ያለ ዶላር ከኪሱ መዥርጎ ከካናቴራዋ አንገትጌ ወደታች ጣል ሊያደርግ ሲል ነገሩ ገብቷት እጁን ለቀም አደረገች።

 “ኖ! ኖ! ኖ!.. ኖ ተች እስቶማክ! ኖ ዋንት ዶላር!” ብስጭት ብላ ዶላሩን ከመሬት ወረወረች። የፈረንጁ ፊት ተለዋወጠ፤ የሚያስፈራ ሆነ።

 “ኖ ዋንት፣ ኖ ዎርክ። ዩ! ጎ ሆም!” ክው አለች። ከስራ ብትባረር የምትጦራቸዉ ሽማግሌ አባቷና እናቷ፣ያረፈችው እህቷ ሁለት ልጆች በርሃብ መሞታቸው ነው። ደነገጠች።

 “ዌር? ዌር ዩ ጌት ዚስ? ዌር? ዌር?” አፈጠጠባት። ድንጋጤዋን ለመቆጣጠር አልቻለችም። ወደጉድጓዱ ጠቆመችው። እየሮጠ ሂዶ፣ ዘሎ ከጉድጓዱ ገባ፡ ፡ተሰባብሮ ይሆን ብላ ወደ ታች ስታየው፤የግንባር ባትሪ አብርቶ በፍጥነት እየዛቀ ከኪሱ ይከታል። ሲኖትራክ እያጓራ መጥቶ ከጉድጉዱ ቀጥ አለ። ኢንጂነር ዱብ ብሎ ወደ ሜካኒኳ ፈጠነ። እንትን እንደቃመ ወይ እንደበላ ሰው አይኑ ተበልጥጧል። “በይ፣ እየዛቅሽ ከሲኖትራኩ ገልብጪ። ቶሎ ቶሎ! ፍጠኚ! . .ደግሞ በግልፅ ልንገርሽ። ላገባሽ ወስኛለሁ። የደስታ ኑሮ እንኖርበታለን። በመጀመር ቃል ግቢልኝ።” “እንጂነር፣ እኔ እኮ እጮኛ አለኝ…..” “እሱን ተይና ቶሎ ቶሎ ጫኚ!” “ግን እኮ…..” “ግን እኮ ወላጅኒ .. ለመስማት ጊዜ የለኝም። ወደ ላይ አውጪው ና ገልብጪ!” “ግን እኮ…..” “ዝምበይ! ሌባ! አውጪ!” “ፈረንጁ ኢንጅነር ከጉድጓዱ ውስጥ አለ።” አለች እየፈራች። “ምን? ምን? ነገርሺው? የመንግስት ምስጢር ለባዕድ አወጣሽ? ወንጀል? እስር ቤት ትላኪያለሽ።” “አስፈራርቶኝ ነዉ። ከስራ አባርርሻለው ስላለኝ………”

“ዝም በይ! በመጀመሪያ ታች ከጉድጓዱ እንዳለ በብረት አካፋዉ ደጋግመሽ አናቱን ምችው፡፡ ከዚያ…..”

 “እንዴ ጋሼ! እኔ ሰው አልገድልም።”

 “ያለዚያ ዋናው ሰውዬ አይለቅሽም። ሰውዬ ካመረረ ምህረት የሚኖረዉ አይምሰልሽ! ይሄ ፈረንጅ በህይወቱ ከወጣ… ባለበት ደፍጥጪው!”

 “አይሆንልኝም እንጅነር።ሀይማኖቴ አይፈቅድልኝም”

 “ነዉ? አንቺ ካላደረግሽው ሌላ ታዛዥ ሜካኒክ አይጠፋም። ከዚህች ደቂቃ ጀምሮ ከስራ ተባረሻል!” ፈትለክ ብሎ ሮጠ። ሜካኒኳ በቆመችበት ደርቃ ቆረች። ደግሞ ጉድጓዱ ውስጥ የሚሰማው የፈረንጁ የ‘አውጪኝ’ ጩኸት እንደ ህልም ተሰማት። ዞር ዞር ብላ ሰው አለመኖሩን አይታ መቆፈሪያዉን እያሽከረከረች አምጥታ ዘንጉን ወደ ጉድጓዱ ዶለች። ከዚያም ፈረንጁ ተፈናጥጦበት ወጣ። ማርትሬዛዉን በልብሱ ሙሉ አጭቆ ስለነበር ልትወልድ የደረሰች እንቁራሪት መስሏል። አፈጠጠባት።

 “አቢሲኒያ እስኒኮኒ . . . እስኔክ አበሻ እስኔክ! አዱዋ!” ወደ ጉድጓዱ እያሳየ በቋንቋው በስሜት ይጮኻል።

 “አይ አም ኖት አንደርስታንድ።” ኢንጅነሩ በሶምሶማ ሩጫ አንድ ሰው እስከትሎ ከተፍ አለ። አልቦታል። ቁና ቁና ይተነፍሳል። ፈረንጁ ወደሱ ሮጠና ጨብጦ እየጎተተው ትንሽ ራቅ ወዳለ ስፍራ ወሰደው።

 “ዩ ቴን ሚሌዮን. . . አይ ፊፍቲን ሚልዮን።” አለ ፈረንጁ።

“ኖ ኖ! ዩ ቴን ሚሊዮን. . .አይ ፊፍቲን ሚሊዮን” ሲል ኢንጅነሩ በቁጣ መለሰለት።

ትንሽ አሰብ አርጎ.. “ኦኬ! ኦኬ! … በት ዘ ውመን ሹድ ቢ ኮንትሮልድ! ቱ አቮይድ ሴክሬት።”

“ኮንትሮሌ ፣ ኮንትሮሌ፣ ሴክሬቶ ኖት ጉድ!” ደስ አለው ፈረንጁ።

ኢንጅነሩ ፈገግታ እያሳ ወደ መካኒኳ ሄደ። “ሲኖትራክ ውስጥ የምንመካከረው የስራ ጉዳይ አለ። ተከተይኝ።” ጉዞ ጀመሩ። የአለቃ ትእዛዝ ሆኖባት

ከሲኖትራክ ጋቢናው ገባች። አጠገቧ ተቀምጦ ጋቢናውን ዘጋ። ከደረት ኪሱ የሚያምር የሽቶ ብልቃጥ አውጣ። ክዳኑን ከፈተ። “እወድሻለሁ። እንቺ ውድ የአውሮጳ ሽቶ ስጦታ። አስሽቺዉ።” ደንግጣ በይሉኝታም አሸተተች። ራሷን ሳተች። አፍሶ ከሹፌር አልጋ ላይ አስተኝቷት ፣ፍራሹን ገልብጦ ከግድግዳው ጋር አስሮ ቆልፎባት ወጣ።

አዲሱ ሹፌር ከመቆፈርያ መኪናው ወጥቶ አስጓራው፤ ረጅሙን የብረት አካፋ ወደ ጉድጓዱ ሰዶ፣ ኮንቴነሩን ቆንጥጦ ያዘው። ፈረንጁና ኢንጅነሩ አንገታችውን ቁልቁል አስግገው የነገርዬውን ወደላይ መውጣት በጉጉት ይጠብቃሉ። መኪናው በሀይል እየተንገጫገጨ ኮንቴነሩን ከመሬት ብቅ አደረገ። መሬት ሊያሳርፈዉ ሲል ከስሩ ሌላ ነገር መኖሩን አየ። ወደ ላይ ከፍ ሲያደርገው ከኮንቴነሩ ጋር በወፍራም ሽቦ የተያያዘ ጠርሙስ ቅርጽ ያለው፣ በርሜል የሚያክል የብረት ጋን ብቅ አለ።

 “ወደ ላይ፣ ወደ ላይ!” አለ ኢንጅነሩ በምልክት እየመራ። የግቢዉ የሰላም ጸሀፊ ከምትመለከተዉ እስክሪን ላይ የኮንቴነሩን ግርግር አየች። ብድግ ብላ፣ ከሚቀጥለው ክፍል ካለው ከዋናው ሰውዬ ዘንድ ሄዳ ስለሁኔታዉ አስረዳችዉ። ፈጥኖ ተከትሏት ገብቶ ስክሪኑን ተመለከተ። ወዲያዉ መብረቃዊ ድምፅ ተሰማ። “ባለበህት! ባለህበት!’ የሚል የድምፅ ማጉያ ትእዛዝ ተሰማ።

በድንገተኛነቱ የተደናገጡት ፈረንጅ፣ ኢንጅነርና ሹፌር ባሉበት ደርቀዉ ቀሩ። አንዲት የጦር ኤሊኮፕተር ከየት መጣች ሳይባል ደርሳ ከተንጠለጠው ኮንቴነር እና ጋን አጠገብ እንደ ቢራቢሮ ተንሳፍፋ ቀጥ አለች። መሰላልዋን ቁልቁል ዘረጋች። ደመናውን እየሰነጠቀ የሚወረወረው፣ አይን የሚወጋ ኃይለኛ ሰማያዊ ብርሃን አካባዊዉን በስፋት እየዳሰሰ ይቃኛል። ከኤሊኮፕተሯ የድመፅ ማጉያ መመሪያና የአደጋ ማስጠንቀቂያ ያስተጋባል።

 “በዚህ አካባቢ ያላችሁ፤ከአራት ኪሎ አፄ ምኒልክ ቤተ መንግስት እስከ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለው መንገድ ላይ ያላችሁ በፍጥነት ከአካባቢው ገለል በሉ!!” ይሄን የአደጋ ማስጠንቀቅያ የሰማ ሁሉ መሰወሩን ትቶ፣ መንገዱን ሞልቶ ቀና ብሎ የኤሊኮፕተሩን ትርዒት ያያል። ማስጠንቀቂያው ይለፈፋል።

 “የእምዬ ምኒልክን አልማዝ ዘረፉት! አወይ ኢትዮጵያ!” አሉ ከጎኔ የቆሙ አባት። “አልማዝ አይደለም። ግርማዊ ጃንሆይ የቀበሩትን እንቁ ሲያወጡ ነው!” አሉ አንድ እናት።

“ዘ ኢታሊያን ኮንስፓይረሲ ዛት በሪድ አቶሚክ ቦንብ!” አሉ፤ ሙሉ ልብስ የለበሱ የአፍሪካ ህብረት ባልደረባ።

 “ደርግ የጅምላ መቃብር እንዳይነካ ሲል ያጠመደው ፈንጂ ነው።” አሉ ወደ ስልሳው የሚጠጉ የስፖርት ቱታ የለበሱ::

 “ወያኔ የምኒልክን ቤተ መንግስት ለማፍረስ የቀበረችው ቦምብ ነው” አለ ወደ አርባው የሚጠጋ ቆፍጣና።

 “እንዴ የምን ቦምብ ነው የሚናገሩት? ነፍጠኛ የዘረፈዉ ብጫ ወርቅ ነዉ።” አለ ጎረምሳዉ።

“ከአጤ ምኒልክ ቤተመንግስት ግቢ ቁፋሮ አልማዝና እንቁ ተገኘ።” የሚል ርእስ በፌስቡኩ ለጠፈ፣ ወጣቱ።

“ተበተን! ተበተን! ከዚህ ትሄዳላችሁ ወይስ አትሄዱም?” ሲል ከአጥሩ ማማ ላይ ሆኖ ስናይፐር ወድሮ የቆመዉ መለዮ ለባሽ በቁጣ ጮኸ። ህዝቡ የሰውየውን ንዴት እግሬ አውጭኝ አለ። እኔ ግን የኤሊኮፕተሯን መጨረሻ ለማየት ጓጉቼ ቆምኩኝ።

“አንተ ሰዉዬ ! ደምህ ደመከልብ እንዳይሆን!” አለ፣ የጠመንጃዉን አፈሙዝ ወደኔ ደግኖ። ብልጭ አለብኝ።

“ምን ትፎክራለህ! መንገድ ላይ መቆም ህገ መንግስታዊ መብቴ ነዉ። ተኩስና እንተያያለን!” አልኩት ተናድጄ።

“ተኩስ? እንዲህ ነችና! አንድ! ሁለት!

ሶስ……..”

ወዲያው ፊቴ፣ አፍና አፍንጫዬ፣ ገበቴ በሚያክል መዳፍ ሲሸፈን ተሰማኝ። አሾልቄ ሳይ፣ ወይን-ጠጅ ቆብ የደፋ፣ ቁመቱ ከሁለት ሜትር የማያንስ ስፔሻል ነው። ጭምድድ አድርጎ መተንፈሻዬን አጠበበው። ላስለቅቀው ተፍጨረጨርኩ፤ የብረት እንጂ የሰው እጅ አይደለም። ለመጮህ ሞከርኩ – እንዲለቀኝ ላስደነግጠው፤ ወይ ሰው እንዲደርስልኝ። የበለጠ መዳፉ አፍንጫዬን እና አፌን ደፈጠጠዉ። መተንፈስ ሲያቅተኝ፣ ያለ የሌለ ጉልበቴን በመሞትና መኖር ደመ ነብሴ አሰባስቤ በኃይል ጮህኩኝ። ጩኸቱ አባነነኝ። አበስኩ ገበርኩ! በላብ ተጠምቄአለሁ። ክፉ የቀን ቅዥት!

ምን ነበረበት እስቲ ያቺ ሜካኒክ እና ኢንጂነሮቹ የት እንደገቡ፤ የተንጠለጠለው ትዕይንት መጨረሻ ምን እንደሆነ አይቼ ብባንን። ኤጭ! ክፉ የቀን ቅዥት! እስቲ እንቅልፍ ልሞክር፤ የመጨረሻው ቢመጣልኝ። ተከናንቤ ኩሽ! ሊነጋጋ ሲል እንደሰመመን አርጎ ይዞኝ ዥዉ! የአሁኑ ህልም ደግሞ ብሶበት ከቤተመንግስቱ ሶስተኛ በር ሰተት አርጎ አስገባኝ። ነጋሪት ይጎሰማል። ለግብር የተጠራዉ ህዝብ ግቢዉን ሞልቶ ይተራመሳል። ወደ አዳራሹ ለመግባት ሲጋፋ አጋፋሪዎች በጨፈቃ እየገረፉ ስርአት ለማስያዝ ይሯሯጣሉ። አንድ ክፉ ልምጭ የቀመሱ መኮንን፣ በዚህ ግርግር የሚሰማኝ የለም ብለዉ ይነጫነጫሉ።

 “የንጉስ ግብርና ኡርባን አንድ በመሆኑ ኸረድኤቱ ለመኻፈልና፣ ጌታችን ኸተራ ህዝብ እንደምንለየበትን የሰጡንን ደረጃ ለመጠበእ ነበር ይ፣ እንጀራማ በየቤታችን ኸኛ ተርፎ ብዙ ሰዉ እናበላ የለ! ወደቤቴ ልመለስ።” አሉ በቅሬታ።

 ሀሜታቸዉ ከአጋፋሪዎች አለቃ፣ ከአጋፋሪ ጉደታ ጆሮ ገባ። ቱግ አሉ አጋፋሪ፤አራት ልምጭ ከጀርባቸዉ አሳረፉባቸዉ። “ኢሂ! ኢ! የኑጉሲ ጊቢሪ ኖ ሊመሪጌጢ ኖ? እናቲ አንጃራ ኖ ፈልጋለሽ በላል፣ ፈልጋለሽ አልበላል? አይ ማዳናላም ጎርጊስ! ..የኑጉሲ ጊብሪ በጊዲዳት በላለሽ ኢንጂ በዉዲዳት በላለሽ?” ሲሉ ተቆጡ።

 መኮንኑ ደንግጠዉ ወደ አዳራሹ ሲራመዱ፣ ተከተልኳቸዉ። መብላቱን ትቼ የአዳራሹን ሁኔታና የግብሩን ስነስርአት ማየት ጀመርኩ። የአዳራሹ መጠን በወርዱም በቁመቱም አገር ያክላል። ከመሀል ባንድ ከፍተኛ ድልዳል ላይ፣ ጠርዙ ሁሉ በወርቅ የተከፈፈና ራሱም ወርቀዘቦ ግምጃ የሆነ፣ ስፋቱ ከአንድ መጠነኛ ቤት የማያነስ አጎበር ይታያል። በዚያ አጎበር ዉስጥ በወርቅና፣ የቀለሙ ህብር የብርሀን ጸዳል ተከትሎ እየተለዋወጠ፣ አይን በሚያሳስት ሀር ያጌጠ፣ በጣም ከፍ ያለ ዙፋን ተዘርግቷል። በዚያ ላይ አንድ የለበሰው ልብስ እንደ ጸሀይ ጮራ አይን የሚገለጥ ሰዉ ተቀምጧል። ከታች ተኮልኩለው ያሉት መኮንኖች ብርንዶና ጠጅ ሲኮመኩሙ ለኔ ጥቁር አፈር የመሰለ እንጀራ፣ ጭቃ በመሰለ ወጥ ሲቀርብልኝ አይቼ በንዴት ፊቴን ሳጠቁር፣ በይነቁራኛ ይከታተሉኝ የነበሩት አጋፋሪ ተንደርድረዉ ደርሰዉ በጨፈጉ ደጋግመዉ ጀርባዬን ገረፉ። አይኔ ላይ ያረፈችዋ ባያሌዉ ስላንገበገበችኝ፣መቻል አቅቶኝ እሪ! አልኩ። ብንን!

 የዛሬዉ ቅዠት አያድርስ! የኋለኛዉ ደግሞ የማዉቀዉ የማዉቀዉ ሆነብኝ። የራስጌ መብራት አብርቼ ዞር ስል፣ ተጋድሜ አነበዉ የነበረው የሀዲስ አለማየሁን ፍቅር እስከ መቃብር ከጠረጰዛዉ ላይ አየሁ። ወዲያዉ ሞባይሌን አንስቼ ፉስቡክ ከፈትኩ። የቤተ መንግስት መጎብኛ የመግቢያ ቲኬት ዋጋ ሁለት መቶ ብር መሆኑን አነበብኩ። በጥድፊያ ለባብሼ ከቤት ወጣሁ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top