ቀዳሚ ቃል

ቀዳሚ ቃል

ወዳጅነት (Friendship) የተሰኘው ጽንሰ ሀሳብ በርካታ ቁጥር ያላቸው የፍልስፍና ምሁራን፣ የስነልቦና ባለሙያዎች፣ የሐይማኖት ሰዎች እና የማኅበረሰብ አጥኚዎች ብዙ የተባለለት ነው። ቁርጥ ያለ ቀመር ወይም ለድምዳሜ የሚያበቃ መቋጫ ሳያገኝ አሁንም አለ፡፡ ትወልድ እየተቀባበለ ያጠናዋል፣ የራሱን አሻራ እያስቀመጠ ለተከታዩ ያስተላልፈዋል፣… በዛሬው የታዛ መጽሔት ቁጥር 28 እትማችን ላይ ሰፋ ያሉ ገጾችን ለዚህ ጉዳይ ሰጥተናል። ምክንያታችን የግለሰቦች ግንኙነት ለማኅበረሰባዊ ተዛምዶዎች መሰረት እንደሆነ ማመናችን ነው።

በየስራ ዘርፋቸው በልዩ ልዩ መልክ ዓለም አቀፍ ሽልማት፣ እቅውና፣ ምስጋና፣… የተቸራቸው ግለሰቦችን አጭር ሐተታም አካተናል፡፡ ሐተታው ለመተዋወቂያም ለመታሰቢያም እንደሚሆን እምነት አለን፡፡ የግለሰቦቹ ውድድር ከዓለም ሐገራት ሰዎች ጋር ነውና የጋራ ኢትዮጵያዊ ስማችንን ማስጠራታቸው ሌላኛው ሰበብ ነው፡፡

በተጨማሪም በመጽሔታችን ቋሚ ተከታታዮች ዘንድ የሚታወቁት ነባር ጸሐፊዎቻችን የሚከትቡልን ቁምነገሮችም ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል። ማእደ ስንኝ፣ ከቀንዱም ከሸኮናውም፣… የተሰኙት አምዶቻችን ተዝናኖታዊ አበርክቷቸው ሰፊ ነው ያልናቸው ናቸው።

በመጽሐፍ ዳሰሳችን ቆስቋሽነት ተነሳስቶ መጽሐፉን የሚያነብ ሰው ወይም ክርክር እና ውይይት የሚከፍት ሰው ካገኘን፣… በስፖርታዊ ቁምነገሮቻችን የትላንትን ታሪክ ከዛሬ እውነታ ጋር ማዛመድ የቻለ ታዳሚ ቢገጥመን፣… በፍልስፍና ጽሑፎቻችን አንዳች የማሰቢያ ጡብ ማቀበል ከቻልን፣… በቃለ መጠይቃችን ታሪክ አቀባይ ድልድይ ከሆንን፣… በጉዞ ማስታወሻችን አዲስ የኑሮ ልምድን ማጋራት ከቻልን፣… ለእቅዳችን ግቡን መምታት ጽዋችንን እናነሳለን።

ታዛ መጽሔት ላይ ለሚሰነዘሩ ማናቸውም ሐሳቦቻችሁ ከርቀት መገናኛ መሳሪያዎች ጀምሮ ቢሯችንን እስከመጎብኘት ድረስ ፈቃዳችን ምሉዕ ነው። መልካም ንባብ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top