የታዛ እንግዳ

“ኢትዮጵያን ማን መሰረታት ብለህ ብትጠይቀኝ ኮሎኒያሊስቶች እልሃለው”

አህመድ ዘካርያ (ረ/ፕሮፌሰር)


እንደ አብዛኛዎቹ መሰሎቻቸው ራሳቸውን የሚገልጹት “የታሪክ ተማሪ” በሚል ነው። ታሪክ በጥቂት ዓመታት መደበኛ
የክፍል ውስጥ ትምህርት እንደማይጠናቀቅ ያምናሉ። በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ተቋም ውስጥ
የሙዚየም አስተባባሪ በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ረ/ፕሮፌሰር አህመድ ከታዛ መጽሔት ባልደረባ ጋዜጠኛ ዳዊት
አርአያ ጋር በዓድዋ ድል እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያደረጉት ጭውውት ለንባብ እንዲሆን በዚህ መልኩ ተሰናድቷል።
በዓድዋ ጦርነት ተሸንፈን ቢሆን ምን ይፈጠር ነበር?
ጨዋታው አከተመ ይባላል። አንድ መጨመር እኮ ነው። ጥቁሮቹ በየቦታው አስር ጊዜ ከተሸነፉ አስራ አንደኛው ይሆናል
ማለት አይደለም?
በዓድዋ ድል ምክንያት የተነቃቃው የጥቁሮች የነፃነት ትግል አይጓተትም?
ያየራሱ የሆነ የ‘ኢኮኖሚክ ዳይናሚክስ’ አለው። ነፃነታቸውን ሊያገኙት የቻለው የራሱን የሆነ ኮሎኒያል ነገር አለ። አሜሪካ
ለከፍተኛ ደረጃ መድረሷ መነሻው እነዚህን ያረጁ ኢምፔሪያሊስቶች መደቆሷ ነው። እሷ ናት ተጠቃሚ የሆነችው። በአንደኛም
በሁለተኛም የዓለም ጦርነት ማለት ነው እንግዲህ። ስለዚህ አዲስ ስርዓት መጣ ማለት ነው። አዲሱ ስርዓት እናንተም ነፃ
ሁኑ፣ ገበያ ክፈቱ፣ አብረን እንሰራለን፣… የሚለው ነገር አመጣ።
ታሪክ እምነት ነው ወይስ እውቀት?
እምነት ይገደባል። አንዴ አማኝ ከሆንክ ይቆማል። የሰው ልጅ አንጎል ደግሞ ማሰቡን አያቆምም። እያሰበ፣ የተለያየ ትርጉም
እየሰጠ፣ የሚያድግ ነው። ዕውቀት እሚገደብ አይደለም። ዕውቀት በሂደት የሚለወጥ ነው። የትናንትናው ዕውቀት በዛሬው
ሌላ ዕውቀት ይተካል። ቋሚ ዕውቀት ምትለው ነገር የለም።
ወደ ታሪክ ስንሄድ ወደ ዕውቀት እንደምንሄድ ማሰብ ይገባል። ስለተደገፍነው ጠረጴዛ አንድ አምስት ስድስት መጽሐፍ ቢጻፍ
የመጠኑን ያህል ዕውቀታችን ይሰፋል ማለት ነው። አንድ መጽሐፍ ብቻ ከሆነ ውስን ነው። ያሰውዬ የጻፈው አንተ
በተቀመጥክበት አቅጣጫ ያየውን ከሆነ በኔ በኩል ደግሞ እኔ ማየውን፣ በሱ በኩል እያለ በሁሉም አንግል ሚታየውን
ማሳየት ነው። የሰው ልጅ ማሰብ አያቆምም። ማሰብ እስከቻለ ድረስ አዳዲስ ትርጉሞች ይኖራሉ ማለት ነው።
አንድን ገጠመኝ የምንመለከትበት መንገድ ብዙ ነው። በተለያየ አቅጣጫ መመልከታችን የትርጉም ልዩነቶች ያመጣል።
ትርጉም መብዛቱ ለእውነት መቅረባችንን ያሳያል። እየመረጥን የትኛው ነው ወደ እውነት ሚቀርበው እሚለውን እንፈትሻለን
ማለት ነው።
በየራሳችን እውነት ብንጋጭ የታሪክ ተፈጥሮአዊ ሂደት ነው ማለት ነው?
ታሪክ በተፈጥሮ ውስጥ ሆነን ተፈጥሮን የምናይበት ሁኔታ፣ የምንመዘግብበት ስልት፣… ነው። ያስልት ለሁሉም አመለካከት
ክፍት ነው። ጥያቄው የመረጃ እና የማስረጃ ነው። ፍርድ ቤት ስትሄድ እውነት እና ውሸት ነው አይሰራም። የሚታየው ሥርአቱ
ነው። ማስረጃው የውሸት ሊሆን ይችላል። ዳኛውን የሚያየው ሥርዓት ነው።
የታሪክ አጋጣሚዎቻችን አሁን ድረስ የሚጦዙት ለምንድነው?
ታሪክ ሰፊ ነው። እኛጋ ደግሞ በጣም እሚጦዘው የነፃነት ሀገር ስለሆንን ይመስለኛል። የፖለቲካው ድባብ ነው፤ ፖለቲካ
ደግሞ ከስልጣን ጋር የተያያዘ ነው። አሸናፊ እና ተሸናፊ ያለበት ነገር ነው። ጎጂና ተጎጂ ያለበት ነገር ነው። እና የተጎዳው
ተጎዳሁ ይላል። ጎጂው ደግሞ አንድ ላድርግህ ብዬ ነው የጎዳሁህ ይላል። እዚያ ላይ “የወጋ እና የተወጋ” የሚባል ነገር አለ
አይደል? የተወጋው ጠባሳው አለ፤ ወጊው ግን ረስቶታል። በዚያ ሰበብ ሚኖረው ግጭት ሁሌም እያሳመመን ይሄዳል ማለት
ነው።
በትናንትና መጣላት የለብንም። የትናንትና ታሪክ ጉዳቱና ጥቅሙ ለመማር ነው ወይም ምንማርበት መድረክ ነው ብለን
ከተስማማን አይጎዳንም። መማር ዕውቀት ነውና ዕውቀት ደግሞ ሚሰፋ ነገር ነው ብለን ስለተስማማን የትናንትናን ጥፋት
ላለመድገም ማለት ነው። ለምሳሌ አጼ ቴድሮስን መልአክም ሰይጣንም ብታደርገው ችግር ነው። ሰው ብታደርገው ግን ችግር
አይሆንም። ሰው ነውና ያጠፋል፣ ያለማል። ያለማውን ነገር አጉልተህ መናገር ትችላለህ። ያጠፋውን ነገር ደግሞ መቀበል
አለብህ። አላጠፋም ስትል ነው ችግሩ።
ዘመነ ኮሎኒያሊዝም ኢትዮጵያ ላይ ምንም ተጽእኖ አላመጣም?
ታዛ 29 ቃለ መጠይቅ Edited
2
ኢትዮጵያን ማን መሰረታት ተብለህ ብትጠይቀኝ ኮሎኒያሊስቶች እልሃለው፤ ኮሎኒያሊስቶቹ ከበዋት የተፈጠረች ሀገር ናት።
እኛ ወደን ፈቅደን የፈጠርናት አይደለችም። ኮሎኒያሊስቶቹ በሁሉም ቦታ እየገፉን እየገፉን የተፈጠረች ኢትዮጵያ ናት።
ባይገፉን ኖሮ የተለየ ‘ዳይናሚክስ’ ይኖረን ነበር፤ የተለየ ህይወት ይኖረን ነበር።
ለምሳሌ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በደም፣ በሃይማኖት፣ በባህል አንድ ናቸው። ጁቡቲ እና ኢትዮጵያ ባህላዊ መሪያቸው ኢትዮጵያ
ውስጥ ነው ያለው። ሱማሊያም እንደዛው ነው።
አፍሪካን በበርሊን ኮንፈረንስ ላይ 1884/5 ላይ ሲወስኑ ቤታቸው ቁጭ ብለው ነው የከፋፈሏት እንደ ቅርጫ ሥጋ።
ኢትዮጵያ ናት የቀረችው፤ ኢትዮጵያንም ዙሪያዋን አፈኗት።
በዚህ ምክንያት ታሪካችን የተበጣጠሰ ነው። እንደ አንድ አገር መሆን የነበረበትን ኃይል አጥተናል ማለት ነው።
በማጣታችንም ሁሌ ችግር አለ ማለት ነው። ኢትዮጵያና ሱማሊያ መካከል የነበረው የሕዝቦች ችግር፣ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ
መካከል ያለው የወሰን ችግር ፈረንጆቹ የሰጡን ነው። እኛ የፈጠርነው ችግር አይደለም። በኮሊያኒስት ጊዜ የተፈጠረውን
ችግር ተሸክመን ነው ያለነው። እኛ ሙሉውን እንዳይጨፈልቁን ተከላከልን ማለት እንችላለን እንጂ የኢትዮጵያ ሁኔታ ይሄ
መሆን አልነበረበትም ብሎ መከራከር ይቻላል።
ለምኒልክ እየተሰጠ ያለው እውቅና ሌሎች ጀግኖችን አስረስቷል የሚሉ ሰዎች አሉ
አንድ ጦርነት የሚመራው በከፍተኛ አዛዡ ነው። ለምሳሌ አሁን ባለንበት ዘመን ጦሩ የሚመራው በጦር ኃይሎች ጠቅላይ
አዛዥ ማለትም በጠቅላይ ሚንስትሩ ነው። አጼ ምኒልክም በዛን ጊዜ በእንደዚህ ነው። ይህ ሲባል ከሥር የጦር አለቆች
አልነበሩም ማለት አይደለም።
በሁሉም አካባቢ እከሌ ያሸነፈው ጦርነት ነው ትላለህ። ጀነራል እከሌ ጀነራል እከሌ ብለህ ዝርዝር አትናግርም። በታሪክ
ስታናግራቸው በዚህ ዘርፍ የእከሌ ድርሻ ከፍተኛ ነበር፤ የእከሌም ድርሻ ከፍተኛ ነው ብለህ ትናገራለህ። ከኋላ ያሉትም
ሴቶችም፣ ምግብ ሚያበስሉትም፣ ነርሶችም፣ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል።
ውክልናው ነው ምትሰጠው እንጂ ጦርነቱ የሁሉም የመቶ ሺህ ነው። ሊሞቱ እኮ ነው የሄዱት። ስለዚህ ጦርነቱ ውስጥ
የሚናቅ ሰው የለም። ምኒልክ መሪ ነበር ብለህ መናገር ነው እንጂ። ወደ መልአክ ስትቀይረው ወይም መልአክ ነው ስትል
ነው ሚበላሸው። በሌላው ወገን ደግሞ ሴጣን ነው ሲለው ነው ሚበላሸው። ሰው ነውና በሰውነቱ የመሪነቱ ኃላፊነቱን ተዋጣ
ብለን መዝጋት እንችላለን። የጠላትህን ኃይል ካልገመትክ ማሸነፍ አትችልም።
ተራራው ራሱ እኮ ጦርነት ነው። የጦርነት አውድማው ሶሎዳ ተራራ እዛ ሄደህ ብታይ የማታምነው ተራራ ነው። እንደ ተራራ
ዓይነት አይደለም። እንደ ፎቆች ውጥት ውጥት ያለ ነውና ለየት ያለ ነው። ያንን ተራራ በደምብ ምታውቀው ከሆነ ለጠላትህ
በጣም አስቸጋሪ ትሆናለህ። ጠላቶችህ ያንን ተራራ አይተውትም አያውቁም ይሆናል። ተራ ወታደሮች ያንን የመሰለ ተራራ
አይተው አያውቁም። የምታውቀው ላይ አማራጭ ትወስዳለህ። ስለዚህ ተራራው ነው የተዋጋልን ማለት እንችላለን። ስለዚህ
የጦርነቱ ውጤት የነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ነው ማለት ነው። እነዚህን ሁሉ እያነሳን ምኒልክ መሪ ነበር ብለህ ብትዘጋው
አያቆስልህም። ብቻውን ተዋጋ እንዴ ምኒልክ? ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ ማይጠቅመን ክርክር ውስጥ ስንገባ ጊዜ ነው
ምናባክነው። ዕውቀት ያልኩህ ለዛ ነው። ወደ ዕውቀት ብንቀይረው ችግር አይሆንም። ወደ እምነት ሲሆን ነው ችግሩ።
በዓድዋ ጦርነት የምኒልክ ብቃቶች ምንድናቸው?
ለኔ ምንሊክ ማለት በጦርነቱ ሂደት ላይ የመረጃ አስተሳሰብ፣ የጠላት ኃይልን የመገመት፣ አልችልህም ብሎ ራሱን እያዳከመ
መቅረብ፣… ብዙ ነገሮች አሉት። በስርዓት አላጠናነውም።
ለምሳሌ የጨለንቆ ጦርነት ላይ የነበረውን በጥቂቱ አውቀዋለሁ። የመረጃው ኃይል ብዙ ነበረ። ከሀረር አካባቢ የነበሩት
ሰዎች በጣም ብዙ መረጃ ይሰጡት ነበረ። እናም የሚያጠና ሰውም ልኮ ነበረ።
ሁሉንም ነገር አጥንቶ መንገድ የሚያሳየው አግኝቶ ያ መድፍ ተያዘ። የጨለንቆ እውነተኛው ጦርነት በአጭር ጊዜ አለቀ፤ ብዙ
ህዝብ ያለቀበት ነው። ፊት ለፊት የነበረው ጦርነት በአጭር ጊዜ አለቀ። ምክንያቱም በሀረሬዎች በኩል ቁጥራቸው ትንሽ
ነው። በዚህ በኩል ደግሞ በጣም ብዙ ነው። ምክንያቱም ሀረሬዎች የተማመኑበት መድፉን ስለነበረ ነው። ቴክኖሎጂ ነው
ሁሌም ሚያሸንፈው። የተማመኑበት ቴክኖሎጂ የሚያፍን ኃይል ከመጣብህ ፀጥ ትላለህ ማለት ነው።
ይህ ሲባል ምኒልክ ጥሩ ነው መጥፎ ነው ማለት አይደለም። እዛ ውስጥ አልገባም።
በዓድዋ ዘመን የነበርንበትን ከፍታ ይዘን መቀጠል ያቃተን ለምንድነው?
ጠላት ሲመጣብን እንተባበራለን። ጠላት ሲተወን ደግሞ እኛ እንጨራረሳለን። ለጦርነት ብቻ ሆነ ነው እኮ ችግሩ። ይህንን
መተው ነው ችግራችን። የኛ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ቀንድ ህዝቦች አዋቂ ናቸው ብለው ፈረንጆቹም ይመሰክርሉሃል እኮ።
ታዛ 29 ቃለ መጠይቅ Edited
3
ፈጣን ናቸው አስተሳሰባቸው ጥሩ ነው፤ ብዙ ነገር ስለኛ የሚናገሩት አላቸው። አሁን ሱማሌዎቹን ሳይቀር የዛሬ መቶ ምናም
ዓመት በፊት አንደርስባቸውም ብሎ ሚፎክሩ ዓይነት ሰዎች አሉ።
በዓድዋ ጦርነት ምንሊክ ጦርነቱን ለምን እስከመጨረሻ አልቀጠሉም?
ይችል ነበረ ወይ ብሎ መጠየቅ ነው። ቀላል ነገር ነው እኮ መቶ ሺህ ወታደሮች ይዘህ በዛ አካባቢ ስትሰፍርበት የቱን ያህል
ያቆይሃል ነው። ማስላት ነው። በየቀኑ እንደ ፋብሪካ አይመጣልህም። ማምረት ምትችለው በዓመት ነው። ምርቱስ ለምን
ያህል ጊዜ ይበቃሃል? በአካባቢው ያለውን በሙሉ ጨምቀህ ብትሰበስበው ለመቶ ሺህ ሰው በየቀኑ ለሚቀለብ ወታደር የቱን
ያህል የሚያስኬድ ይሆናል ብሎ ማሰብም ተገቢ ነው።
አቅማቸው በሙሉ የተዳከመበት ጊዜ ነበር። ከጣሊያን ሀገርም ሚያስቸግርበት ጊዜ ነበር። በዚህም በኩል የመቶ ሺህ
ወታደር ቀለብ ለማግኝት የሚያስቸግርበት ወቅት ነው የነበረው። ጦርነት የራሱ ሎጂክ አለው። ሁሉ በሙሉ መጨራረስ
ማለቅ አለበት የሚለው ነገር ዓይነት አይደለም። ትዋጋና በቃኝ ትላለህ። ሳይኮሎጂካሊ ያልቃል ማለት ነው ጦርነቱ። በራሱ
ሎጂክ ያልቃል። ከዛ ስምምነት ውስጥ ትገባለህ። እነሱም አቅም አልነበራቸውም። ቀለብ ያስፈልጋቸዋል። ቦታውንም
አያውቁትም።
ሌሎች ምክንያቶችን እንኳን ምክንያቶች ብንተው መደራደር አለ። ምኒልክ ከጣሊያኖችም ጋር የቀደመ ጠላትነት የለውም
ስላስቸገሩት ነው የተዋጋቸው። የመጀመርያው ስምምነት መረብ ምላሽ እኮ አለ። በአጼ ዮሐንስ ጊዜ እኮ ብዙ ተሞክሯል።
ሦስት አራት ጦርነቶች ተካሂደዋል።
ለምሳሌ ዶጋሊን ብናነሳ እዛላይ ተሸንፏል። እነሱ በቁጭት የሚያነሱት ጦርነት ነው። እነዚህ ነገሮች ቀደም ብለው የመጡ
ናቸው። ምኒልክም ራሱን ለማደራጀት ብሎ ከጣሊያኖች መሳሪያም ምንም ስምምነት ነበራቸው። እነዚህን ነገሮች ረጋ ብሎ
ማዬት ነው።
በነበረው መረጃ እና ማስረጃ ከተነጋገርን ዕውቀት ነፃ ታደርገናለች። እንደ እምነት የያዝናቸው እየሟሸሹ ሲሄዱ በስብዕና
ምናስተካክለው ዓይነት ይሆናል እና ብዙ ነገር አለ።
የዓድዋ መቶኛ ዓመት ጊዜ እንዴት ነበር? ዝግጅቱ ውስጥ እንደነበሩ ሰምቻለሁ።
የመቶኛ ዓመት ጊዜ ሁለት ዝግጅት ነበረ። በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር የተሰራ ነበረ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ
የተቋቋመ ኮሚቴ ያዘጋጃቸው ሥራዎች ነበሩ። እሚጣረሱ ነገሮች ነበሩ። ያኔ ብንስማማ ብዙ መስራት እንችል ነበረ።
አቅማችንን ብናዋሃህድ የነበረንን የገንዘብ አቅም ብናዋሃህደው በጣም ብዙ ነገር እንሰራ ነበር። የገመድ ጉተታ የበዛበት፣
የምኒልክ እና የዮሐንስ ልጆች የምንላቸው ዓይነት ስሜት ነበረው። የሁላችንም አላደረግነውም። ውስጡ ስለነበርኩ ቁስሉን
አውቃለሁ።
ታሪክን ከተመራማሪዎች በስተቀር መጻፍ የለበትም የሚል ክርክር አለ። የትኛው ይስማማዎታል?
ማስገደድ ይቻላል እንዴ? አንተ እንቅልፍ አጥተህ መጻፍ ከፈለግክ መጻፍ ትችላለህ። እሚያነብልህ ሰው ካገኘህ ደግሞ ጥሩ
ነው። ከኪሳራ ትድናለህ። ቅዠት ዓይነት ከሆነ ያው የታሪክ ተመራማሪዎች የዚህ ቦታ ማስረጃ ትክክል አይደለም ብሎ ምክር
ለመስጠት ይሞክራል። ማረም ሳይሆን..
ታሪክን በጥልቀት ያጠና ሰው ለስህተቱ እርማት መስጠት የለበትም?
የአተረጓጎም ልዩነት ስላለ በዛሬው ላይም ብዙ ጭቅጭቅ አለን። አሁን አንድ የመኪና አደጋ ብንመለከት እንከራከራለን
አይደል? አይ ነጩ መኪና ነው አይ ቀዩ መኪና ነው እንደዚህ ስላደረገ ነው እንባባላለን። ይህ የሆነው ዕይታችን ስለሚለያይ
ነው።
ባላየነው ነው አሁን ምንገነባው። ለአንጎላችን መጫወቻ ነገር ነው አንጂ እውነት እና ውሸት አይደለም ሚነገረው። ሁሉም
ቢጽፍ ጥሩ ነው። ቅዠቱንም ቢጽፍ ጥሩ ነው። እየተማረ ይመጣል ማለት ነው። ሌላው አንድ ቅዠት ያነሳ እና እዚህ ላይ
ትክክል አይደለም ማስረጃው ይህንን ይመስላል እና በዚህ ዓይነት ብታየው ብሎ ይመክሩሃል ማለት ነው።
ታሪክን ለአእምሮ ማፍታቻ እንጠቀምበታለን ማለት ከዚያ የዘለለ አገልግሎት የለውም ማለት ነው?
ምንድነው መሰለህ ታሪክ ሳይንስና ስነ-ጥበብ ናት። ስለዚህ የሁለቱ ድብልቅ ናትና ለመፍረድ ታስቸግራለች። በአርት ላይ
የፈጠራ ነው ብለህ እንደ ልብህ ልትሄድ ትችላለህ። በዚህ ላይ ግን የሳይንስም አለው። እነዚህን ሁለቱን ምታዋህድበት ጥበብ
ነውና ሁሌም አስቸጋሪ ነው። ሳይንሱ የት ቦታ ተጀምሮ የት ቦታ ያልቃል ዓይነት ነው።
ታዛ 29 ቃለ መጠይቅ Edited
4
በቀና መንፈስ ማስረጃ ማሰባሰብ፣ ጥሩ ቋንቋ፣… እነዚህ ነገሮች ሁሌም ያስፈልጉሃል። እና የሰው ልጅ አስተሳሰብ
አያቆምም፤ እስካላቆመ ድረስ ልክና ልክ አይደለም እውነት እና ውሸት እየተከራከርን እነሄዳለን።
በትላንትና ታሪክ አለማስማማት የታዳጊ ሐገሮች ችግር ነው?
ህዝቡ አይደለም እኮ ችግር የሆነው። ከሥልጣን አከባቢ ያለው ኤሊት ነው ሚያስቸግረው እንጂ…
ኤሊቱን ህዝቡ አልተከተለም?
በኢሊቱ የተዛባ አመለካከት በኢሊቱ ውይይቶች ማስተካከል ነው ያለባቸው። ወደ ህዝቡ አስገብቶ ደም ማቃባቱ ትርጉም
የለውም። አሸናፊ የሌለበት ውጤት ነው የሚሆነው። እኛ ምንፈልገው ሁለቱም ሃሳብ ያላቸው ወገኖች የሚያሸንፉበትን
ነው። ግን አምርረህ ለሥልጣን መጠቀሚያ ስታደርው ነው ችግር የሚሆነው።
ሚኒልክ እንደዚህ ቦታ ጉዳት አደረሰ፤ አሁን እኛ እንዳናደርስ ምን እናድርግ ነው መሆን ያለበት። አሁን እያደረግን ከሆነ ግን
አልተማርንም ማለት ነው። ዛሬ እየሆነ ያለውን ጉድ ስንሰማ ትደነግጣለህ። የሚዘገንን ነው።
አሁን ላለንበት ሁኔታ ዓድዋ ምን ያስተምረናል?
በዓድዋ ከተባበርን ብዙ መስራት እንደምንችል ለነገ ተምረናል። ብንተባበር ድህንነታችንን እንዋጋለን ማለት ነው። የድህንነት
ውጤት ብዙ ነገር ያሳስብሃል። ከሰራህ፣ ካመረትክ፣… ለማይሆን ዓይነት ትርክት ጊዜ አይኖርህም። በትናንትና አትኖርም፤
በነገ ተስፋ ነው ምትኖረው። ትናንትና ማስተማሪያህ ነው እንጂ መኖሪያህ ዓይነት አይደለም። መቀበሪያህም መኖሪያህም
ወደፊት ነው። ለነገው ስንቅ ምትይዝበት ጥሩ ጥሩውን ከዚህ ወስደህ ወደፊት ትሄዳለህ ማለት ነው። መጥፎውንም
ለመማሪያ አድርገህ ትተወዋለህ። መማሪያነቱን ይቀንሰዋል ማለት አይደለም። በታሪክ አትኖርም። ለመኖር ትሞክራለህ ግን
አትኖርም። ምክንያቱም በዛሬው እውነታ ነው ምትኖረው።
እንዳነሳነው ብዙ ፋክተሮችንም መተንተን አለብን። ከተባበርን የሚያቅተን ኃይል የለም። ሁሌም ምንዘክረው ለመዘከር ብቻ
ሳይሆን ተምረንበት ዛሬ ያለውን ችግር እንዴት እንቀርፍበታለን ብለን ብንጠቀምበት ከተዛባ ትርክትም ብዙ ነገር ማስተካከል
እንችላለን። ትልቁ ነገር የትርክት ብዛት ነው። ብዙ ችግር ሲኖር ብዙ ነገር ይወራል አይደል?
አመሰግናለሁ!
እኔም አመሰግናለሁ!


Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top