ከቀንዱም ከሸሆናውም

ጥቂት ነጥቦች ስለ ህፃናት መጻሕፍት አዘገጃጀት

ምናልባትም የተዋጣሎት ደራሲ ሊሆኑ ይችላሉ። አንቱ የተባሉ ጦማሪ ወይም የልቦለድና የኢ-ልቦለድ ደራሲ ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም ግን የህጻናት መጻሕፍትን ለማዘጋጀት ራሳችን በህፃናቱ ቦታ አድርገን
በማየት መጻሕፍቱን ማዘጋጀትን ይጠይቃል። የህፃናት መጻሕፍትን ስናዘጋጅ በርካታ ያሳለፍናቸውን የህፃንነትና የልጅነት ዓመታትን በዕድሜ ዕርከን እየመነዘርን ስንኖርባቸው የነበሩ ሂደቶችንና የባህርይ
ለውጦችን ጭምር በማጤን መጻህፍቱን ማዘጋጀት ይጠይቃል። በእያንዳንዱ የዕድገት ደረጃ ሀፃናቱ ያሳለፋትን የዕድገት ደረጃ የዋጀ የአጻጻፍ ስልት፣ አወቃቀርና የቋንቋ አጠቃቀምን ከግምት ያስገባ ሊሆን ይገባል። የህፃናቱን ‘’እያንዳንዱን የጭንቅላት የዕድገት ደረጃንና ሁለንተናዊ ዕድገታቸውን መሰረት ያደረገ መጽሐፍ ማዘጋጀት አለብን’’ ብለን ወስነን ከተነሳን በርግጥም የምናዘጋጀው መጽሐፍ ለህፃናቱ ትርጉም የሚሰጥ፣ ትምህርታዊና አዝናኝ ሆኖ እናገኘዋለን።
የምናዘጋጅላቸው መጻሕፍት መሰረት ሊያደርጉ የሚገባው በዕድሜ ዕርከናቸው ላይ ተመስርቶ ሊመጥናቸው በሚችል መልኩ የተዋቀረ ሊሆን ይገባል። የምናዘጋጃቸው መጻሕፍት ትኩረት ላደረግንባቸው የዕድሜ
ዕርከን ላይ ለሚገኙ ህፃናት የሚመጥኑ ገጾችን ፣ገለፃዎችን፣ ምስሎችንና የቃላት ብዛት ሳይቀር ተመጥነው መሰደር ይገባቸዋል። እያዋቀርናቸው ያሉ ታሪኮችንም ህፃናቱ የተቀዱበትን ማህበረሰብ ባህልና ወግን መሰረት
ያደረጉ መሆኑን መዘንጋት የለብንም።

የህፃናት መጻሕፍትን ስናዘጋጅ ከታች
የተመለከተውን ሰንጠረዥ በዕድሜ መለየት ይቻላል

ክፍል ዕድሜ የቃላት ብዛት ገጽ መግለጫ
የስዕል መጽሐፍ 0-3 0 32 በእያንዳንዱ ገጽ
የታዳጊ ስዕል መጽሐፍ 2-5 200-400 32 በእያንዳንዱ ገጽ
ስዕሎችና ውስን ገለጻ 4-8 400-800 32+ በእያንዳንዱ ገጽ
ስዕሎችንና ታሪክን የያዘ 6-10 1,000-3,000 32+ በእያንዳንዱ ገጽ
ምዕራፎች ያለው መጽሐፍ 6-10 3,000-10,000 32+ ሁሉም ገጾች ላይ
መካከለኛ ክፍል ተማሪዎቸ 8-12 15,000-40,000 82 12+ መግለጫዎች

በህፃናቱ መካከል ያለውን የዕድሜ እርከን ልዩነት፣ በእያንዳንዱ የዕደሜ እርከን የሚንፀባረቅባቸው የባህርይ ለውጥና ሌሎች ከግምት መግባት ያለባቸው መካትቶችን መሰረት በማድረግ የህፃናቱን መጻሕፍት ለተመረጠው የዕድሜ እርከን ማዘጋጀት ይቻላል። ከዚሁ ጎን ለጎን የህፃናት መጻሕፍት ብዙውን ጊዜ በየዕድሜ ዕርከኑ ላሉ ህጻናት ተጠቃሚ የሆኑ ወላጆችን በዕድሜ ዕርከንና በጾታ መለየት አስፈላጊ መሆኑን አጽንዖት ሊሰጥ ይገባል። አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያስነብቡት የህጻናት መጻሕፍትን ከሚገዙ ወላጆች መካከል 70% ሴቶች ሲሆኑ
የዕድሜ እርከናቸውም ከ33 እስከ 44 የሚገኙ መሆናቸውን ያስረዳሉ።
ከዚህ መረጃ መረዳት የሚቻለው የህፃናትን መጻሕፍት ሰናዘጋጅ ከግምት ልናስገባቸው የሚገቡን ቅድመ ዝግጅቶች መኖራቸውን ነው። አንድም መጻሕፍቱን ለማዘጋጀት ትኩረት ባደረግንበት የዕድሜ ዕርከን ላይ የሚገኙ ህፃናትን በመቅረብ በእንቅስቃሴአቸው አግባብ ሁሉ የሚጠቅሟቸው ቃላትና አጠቃላይ በሀሪያቸውን ማጥናት ያስፈልጋል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ወላጆችና መምህራኑን በመቅረብ መጽሐፍ ሊዘጋጅበት በተመረጠው የዕደሜ ዕርከን ላይ ህፃናቱ ስለሚላበሱት ባህሪያት መረጃዎችን የማሰባሰብ እና በተለይም የህፃናቱ
እናቶችን በመቅረብ ጠቃሚ መረጃዎችን ለማግኘት መሞከር ያስፈልጋል።

ህፃናቱን ለማስደሰት መጻሕፍቱ ምንን ማካተት ይኖርባቸዋል?

የህፃናት መጻሕፍትን ከማዘጋጀታችን
በፊት ከግምት የምናስገባቸው ወሳኝ መካትቶች እንዳሉ ሆኖ ወላጆችንም ጭምር ማስደሰት እንዲችል ልንከተለው የሚገባ ይዘትና አወቃቀርን ማየት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ስለ ምናዘጋጀው ታሪክ አገላለጽ፣
የአጻጻፍ ስልትና የቋንቋ አጠቃቀም ስልቶችን ከግምት ማስገባት ይኖርብናል። ‘’ለምን?’’ ቢባል የምናዘጋጀው ልዩና መሳጭ የታሪክ ሀሳብ ፍሰት ከሚነገረው በላይ ጠንካራ ሊሆን ይገባል። ጥሩ የታሪክ አወቃቀር በጥንቃቄ
የተዋቀረና ቀለል ያለ መሆን ስላለበትም ጭምር ነው። የሆነ ሆኖ ለህፃናቱ የምናዘጋጀው መጻህፍት አምስቱን አላባውያንን ማካተት የግድ ሆኖ እናገኘዋለን። የአይረሴ ገፀ ባህሪያት በመጻህፍቱ
ውስጥ ተካቶና ተዋቅሮ መገኘት አንዱና ወሳኝ የተነባቢነት፣ የጥንካሬና የደስታ ምንጭነት ነው። አይረሴው ገፀ-ባህርይ ሊረሱ የማይችሉ አንድ ወይም ሁለት ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉ ባህሪያትን እንዲላበስ ተደርጎ ሊዋቀር ይገባል። የምንቀርፀው ገፀ-ባህርይ ጠንካራ ሰብዕና ያለው፣ ብልህና የሚገጥሙትን እንቅፋቶች ሁሉ በድል አድራጊነት እንዲወጣ አድርገን የምንስለው ነው። እንዲፀባረቅ የምንፈልገው ዋነኛ ባህሪይ በሰዕል፣ በአጫጭር ዓረፍተ ነገሮችና አንቀጾች መግለጽም አስፈላጊ መሆኑን ልንረዳ ይገባናል። በእርግጥ በጽሑፍ አወቃቀር
ላይ ዝርዘር ገለጻና ገፀ-ባህሪውን ለማሳየት ዝርዝር መግለጫ አያስፈልግም። ይህ ሲሆን ህፃናት በገፀ-ባህሪው ፍቅር ይወድቃሉ፤ እንደ ገፀ-ባህሪውም ለመሆን ይመኛሉ። ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ እራሳቸውን እንደ ገፀ-ባህሪው
በመቁጠር ለመተወን ይሞክረሉ። አይረሴው ገፀ-ባህሪይ በውስጣቸው ተቀርጾ የመኖርም አጋጣሚን በሚፈጥር መልኩ ሊቀረጽ ይገባል።
ታሪኩ ጠስቆ የሚይዝና ልብ አንጠልጣይ ማድረግ ሌላው ለህፃናት መጻሕፍት ዝግጅት አንዱ ነው። ብዙ የህፃናት መጻሕፍት ደራሲያን ከጅምሩ የታሪኩ አወቃቀር በድርጊት እንዲሞላ አድርገው ያዋቅሩታል። ይህ አቀራረብ በተለይም ወደ መጀመሪያዎቹ የዕድሜ ዕርከን ላይ የሚገኙ ህፃናትን ልብ በመግዛት ታሪኩን እስከ መጨረሻው በስሜት እንዲያነቡ ያደርጋቸዋል። ይህን ለማድረግ ደራሲያኑ መጻሕፍቱን ሲያዘጋጁ የታሪኩ ፍሰት
የማይዋዥቅና እያንዳንዱ ምዕራፍ የህፃናቱን ልብ ማንጠልጠል እንዲችል አድርገው ሊያዋቅሩት ግድ ይላቸዋል።


የታሪኩ ፍሰትና በውስጡ የሚገኙ ሁነቶችንም ማጤን ያስፈልጋል። በምናዘጋጃቸው የህጻናት መጻሕፍት ታሪክ ፍሰት የተለያዩ እንቅፋቶችንና ፈተናዎችን ማዋቀራችንን ልብ ልንል ይገባናል። ከዚሁ ጎን ለጎን ገጸ ባህሪያቱ ለእንቅፋቶችና ፈተናዎች የተለያዩ መፍትሄዎችን ተላብሰው አሸናፊነትን ሲቀዳጁ ለህፃናቱ ማሳየቱ አንድም አተያያቸው እንዲሰፋ ያደርጋል በሌላ በኩል ደግሞ የሚገጥሟቸውን እንቅፋቶች ማለፍ እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። አሸናፊ ተደርጎ የተሳለው ገፀ-ባህሪይ ድርጊት ይቻላልን እንዲላበሱ ያደርጋቸዋል።

በገሀዱ ዓለም ህፃናቱ የሚያደርጉትን ዓይነት ምልልስ አካሄድ በምናዘጋጀው የህፃናት መጻሕፍት ውስጥ ሊካተት ይገባል። ህፃናቱ
በዕለት ተለት እንቅስቃሴያቸው የሚያደርጉትን ምልልስ፣ የቋንቋ አጠቃቀማቸውን መሰረት ያደረገ አጻጻፍን መከተል ያስፈልጋል። በእርግጥ ይህን ከማድረጋችን በፊት ልናዘጋጅ በወጠንነው የዕድሜ እርከን ላይ የሚገኙ ህፃናትን ቀርቦ ምልልሳቸውን ማጥናት፣ የህፃናት መጻሕፍትን ማንበብ፣ መመርመርና የቋንቋ አጠቃቀማቸውን
መረዳት ግድ ይለናል።
የምናዋቅረው ታሪክ በድርጊቶች የተሞላና ቀጣይነት ያለው ሊሆን ይገባል። ታሪኩ የህፃናቱን ስነ ልቦና መሰረት ተደርጎ ከተዋቀረ ህፃናቱ ደግመው ደጋግመው መጻሕፍቱን ማንበብ ወይም እንዲነበብላቸው ይጎተጉታሉ። ህፃናቱ እየተደጋገመ እንዲነበብላቸው ወይም ማንበብ ከፈለጉ ያዘጋጀው መጽሐፍ ደራሲ የተዋጣለት መሆኑን እማኝ መጥቀስ አያሻም።

ታሪኮቹ ተከታታይነት ባላቸው ልብ አንጠልጣይ ድረጊቶች እንዳዋቅርነው ሁሉ የእያንዳንዱ የመጽሐፉ ዓረፍተ ነገሮች፣ አንቀጾች፣ ምዕራፎች እጥር ምጥን ማድረጉን መዘንጋት የለብንም። የዘርፋ ጸሐፍት መጻሕፍቱ ሲዘጋጁ የዓረፍተ ነገርና አንቀጽ አወቃቀር ቀለል ያሉና አጫጭር መሆን እንዳለባቸው ያስገነዝቡናል። ድርጊት ፈፃሚውን ገፀ-ባህሪይ በግልፅ አጉልቶ በማሳየትና ወሳኝ የሆኑ አላባውያንን በመጠቀም ተነባቢነቱን ይበልጥ ማጉላት ይቻላል። በእያንዳንዱ ገጽ መጨረሻን በጥያቄ በመጨረስ ህጻናቱን ይበልጥ በቀጣዩ ገጽ ምን ሊፈጠር ይችላል በማለት ልባቸው ተንጠልጥሎ እራሳቸውን እንዲጠይቁ በማድረግ የአጻጻፍ ስልታችንን
ልናንፀባርቅ ይገባል።

በምናዋቅረው ታሪክ ውስጥ ዋና ገፀ- ባህሪው ሊገጥሙት የሚችሉ ግጭቶች በግልፅ የተለየና ዋና ገፀ-ባህሪይ
ከአንድ ገፀ-ባህሪይ፣ ከተፈጥሮ፣ ከማህበረሰቡና ከራሱ ጋር ገጭት ሲፈጥር ባልተወሳሰበ የአጻጻፍ ስልት ማቅረብ
ይጠበቅብናል። በታሪክ አወቃቀራችንና የግጭት ድርጊት አገላለፃችን ዋና ገፀ-ባህሪው ካለ ማንም እርዳታ በራሱ
ገጭቶችን አሸናፊ ሆኖ ድልን ሲቀዳጅ ማሳየት የታሪክ አወቃቀራችን አንዱ ገፅታ ነው።

ጥሩ ሊባል የሚችል የህፃናት መጻሕፍትን ለማዘጋጀት ለታሪኩ ፍሰት የተዋጣለት ትልም ማዋቀርም ወሳኝ ነው። በትልሙ የግጭቶች መፍትሄ ተደርጎ መዋቀር ያለበት ትምህርት ሰጪነቱ ሲሆን ይህም ሊገለፅላቸው የሚገባው በትልሙ የተለያዩ ሁነቶች ወስጥ መሆን ይገባዋል።

ስለ ምን መጻሕፍትን ማዘጋጀት ይቻላል?
የህፃናትን መጻሕፍት ስናዘጋጅ የሚከተሉትን ነጥቦች ከግምት ብናስገባ መነሻ ሀሳቦችን ማግኘት አንችላለን። ተፈጥሮን መሰረት በማድረግ፣ አትክልትን በማሰብ፣ ፍራፍሬን በምናብ በመሳል፣ የእንስሳትን ተፈጥሯዊ ባህሪይ በማሰብ፣ ምትሀታዊ ፍጡራንን በማሰብ፣ ስለ ህፃናት፣ ህዋን ምናባዊ በማድረግ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን
በማሰብ፣ ምናባዊ ታሪክንና ሃሳብን በማፍለቅ፣ አሻንጉሊቶችን አስመልክቶና ሌሎች ሳቢና መሳጭ ታሪኮችን ‘’እንዴት ልፃፈው? ለማን ልፃፈው? በምን ቋንቋና አገላለፅ ላዋቅረው?’’ የሚሉትን ጥያቄዎችን በመመለስ መጻሕፍቱን ማዘጋጀት ይቻላል።

ከላይ ለመጥቀስ የተሞከሩትን መነሻ ሀሳቦችን መሰረት በማድረግ በቀላሉ የህፃናት መጻሕፍትን ለማዘጋጀት መንደርደር ይቻላል። በርግጥ ለመጻሕፍቱ ዝግጅት ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊተኮርበት የሚገባው የምናዘጋጃቸው መጻሕፍት የህፃናቱን ስሜት መኮርኮር ይችላሉ? የህፃናቱን ስሜት ይገዛሉ? የማዝናናት አቅማቸውስ እስከምን ድረስ ነው? እና ሌሎች መካትቶችን ልናጤን ይገባናል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top