አጭር ልብወለድ

የገናው ዛፍና ሠርጉ

ደራሲ –  ፍዮዶር ኤም. ዶስቶይቭስኪ

ትርጉም – መኮንን ዘገዬ

አንድ ቀን አንድ ሰርግ ዐየሁ…። ግን ቆይ ሠርጉ ይቅርና! ስለ ገና ዛፉ ልንገራችሁ። ለነገሩ

ሠርጉም ቢሆን ግሩም ነበር። በጣም ነበር የወደድኩት። ቢሆንም ሌላኛው ገጠመኝ የበለጠ ነበር። ግን ሠርጉ የገና ዛፉን ታሪክ እንዴት ሊያስታውሰኝ እንደቻለ አላውቅም። ከአምስት ዓመት

በፊት ለአዲስ ዓመት ዋዜማ አንድ የታወቀ ነጋዴ የልጆች የዳንስ ምሽት ላይ እንድገኝ ጋብዞኝ

ነበር። የነጋዴው ጓደኞች፣ የሚያውቃቸው ሰዎችና የአሻጥር አበሮቹ ጭምር ተገኝተው ነበር።

ለነገሩ የልጆቹ ዳንስ ለወላጆቻቸው ተገናኝተው የጋራ ጉዳይ በሆኑ ነገሮች ላይ ለመወያየት

ምክንያት ነበር የሆነው።

እኔ ግን ጉዳያቸው ስለማይመለከተኝ ጣለቃ ገብ ነኝ ማለት ይቻላል። እና ምሽቱን ከሌሎች

ተነጥዬ በነፃነት እንዳሳለፍኩት ነው የሚቆጠረው። ሌላም አንድ ሰው ልክ እንደኔ እግር ጥሎት

ይህን የደስታ ምሽት ተቀላቅሎ ነበር። ይህ ሰው በዚህ ምሽት የመጀመርያው ትኩረቴን የሳበ

ሰው ነበር። ገፅታው የተከበረ ቤተሰብ አባል አለመሆኑን ይናገራል። ቁመቱ ረጅም፣ ሰውነቱ

ቀጭን፣ በጣም ኮስታራ ነበር። ታዲያ አሳምሮ ለብሷል። ለዚህ የቤተሰብ ግብዣ ስሜትም

አልነበረው። ወደ ጥግ ሂዶ እንደተቀመጠ ወዲያው ፈገግታው ከፊቱ ጠፋና ግንባሩ ተኮሳተረ።

ከቤቱ ባለቤት በስተቀር ሌላ የሚያውቀ ሰው አልነበረም። ደሞ እስከ መጨረሻው ደስተኛ

እንዳልነበረ እያንዳንዱ እንቅስቃሴው ይናገር ነበር። ግን በደንብ መደሰትና መዝናናት

የሚሰጠውን ጥቅም አሳምሮ ያውቃል። ቀስ በቀስ ሰውየው ከገጠር የመጣ መሆኑን ተረዳሁ።

ወደ ከተማ የመጣው ለብርቱ ጉዳይ ነበር። ለአስተናጋጃችን ተባበረው የሚል የአደራ ደብዳቤ

ይዞ ስለመጣ አስጠግቶታል። እና አክብሮት ነው በልጆቹ የዳንስ ምሽት እንዲገኝ የጋበዘው።

ሌሎቹም አንግዶች ቢሆኑ ይህን የገጠር ሰው አብሯቸው ካርታ እንዲጫወት አላደረጉትም

ሲጋራም አልሰጡትም። አንደኛቸውም አላናገሩት። ማንነቱን ከሁኔታው ያወቁ ይመስላል። እና

ሰውየው በእጆቹ ምን እንደሚያደርግ ግራ ስለገባው ምሽቱን ሙሉ ሪዙን ሲያፍተለትል ነበር

ያሳለፈው። ሪዙ ደስ የሚል ነው። ግን ያለእረፍት ያፍተለትለው ስለነበር ተመልካች መጀመርያ

ወደ ዓለም የመጣ ሪዝ ሳይሆን አይቀርም ብሎ ማሰቡ አይቀርም።

በዚህ የዳነስ ምሽት ትኩረቴን የሳበ ሌላም አንድ እንግዳ ሰው ነበር። ይሄኛው ደግሞ የተለየ

ነበር። የተከበረ ሰው ነበር። ጁሊያን ማስታኮቪች ይሉታል። አስተናጋጆቹ፣ ባልና ሚስቱ

ያለማቋረጥ ነበር ፍቅራቸውን የሚገልጡለት። ትኩረታቸው አልተለየውም ነበር። ዙርያውን

ያንጃብቡበት ነበር። የተለያዩ ሰዎች እያመጡ ያስተዋውቁት ነበር። አሱን ግን ወደማንም

አያገናኙትም ነበር። ጁሊያን ማስታኮቪች እንደህ ያለ አስደሳች ምሽት ጥቂት ጊዜ ነው

የገጠመኝ በማለት አስተያየት ሲሰጥ አስተናጋጃችን ዐይኖቹ እንባ ሲያቀሩ አስተውል ነበር።

ለማንኛውም የዚህ ሰው በቦተው መገኘት ምቾት እየነሳኝ መሄድ ጀመረ። በልጆቹ ደስታ ራሴን

አዝናናሁ። አምስት በእንክብካቤ የተያዙ ወጣቶች ነበሩ። ከዚያ ወደ አንድ ሰው

የሌለበት ትንሽ የእንግዳ ማረፍያ ክፍል ሄጄ ተቀመጥኩ።

ልጆቹ ደስ የሚሉ ነበሩ። ታላላቆቻቸውን መምሰል በፍፁም አይፈልጉም ነበር። ልጆቹ በአንድ

ጊዜ የገና ዛፉ ላይ የነበረውን ጣፋጭ ተሻምተው ጨረሱት። መጫወቻቸውን ግማሽ ያህሉን

በአንዴ ሰባበሩት።

ከመካከላቻው አንደኛው ልጅ በጣም ቆንጆ ነበር። ዐይኖቹ ጥቋቁር ናቸው። ፀጉሩ ከርዳዳ

ነው። ታዲያ ልጁ ከእንጨት የተሠራ ጠመንጃውን ያለማቋረጥ ወደኔ ይደግን ነበር። ግን

የበለጠ ትኩረት ትስብ የነበረችው ልጅ አህቱ ነበረች። እድሜዋ ወደ አስራ አንድ ዓመት ገደማ

ይሆናል። እንደ ኩፒድ ደስ የምትል ነበረች። ዝምተኛና በሃሳብ የተዋጠች ትመስል ነበር።

ዓይኖቿ ትላልቅ ሆነው ሕለመኛ ናቸው። የተቀሩት ልጆች ስላበሳጯት  ትታቸው እኔ ብቻዬን

ተገልዬ ወደ ተቀመጥኩበት ከፍል መጣች። ከዚያ አሻንጉሊቷን ይዛ ጥግ ይዛ ተቀመጠች።

አባቷ ሲበዛ ገንዘብ የተረፈው ነጋዴ ነው። እንግዶች ሁሉ የልጅቷ አባት ለልጅቷ ሠረግ

ለጥሎሽ የሚሆን ሦስት መቶ ሺ ሩብል ያስቀመጠላት መሆኑን በማድነቅ ያወሩ ነበር።

እና እኔ ይህን ወሬ ወደ ሰማሁበት አቅጣጫ ስመለከት ጁሊያን ማስታኮቪችን ተመለከትኩ።

አሰልቺና የተደባለቀ ንግግራቸውን ትኩረት ሰጥቶ አጁን ወደ ኋላ አድርጎ አራሱን ወደ አንድ

በኩል ዘመም አድርጎ ቁሞ ያዳምጥ ነበር። እኔ ደግሞ ጋባዣችን ለልጆቹ ስጦታ ሲያከፋፍል

ዕያሳየ ያለውን ብልጠት እየከታተልኩ ነበር። በዙ ለጥሎሽ የሚሆን ገንዘብ ለተቀመጠላት ልጅ

ደንበኛው አሻንጉሊት በስጦታ ተሰጣት። ለተቀሩት ደግሞ እንደ ወላጆቻቸው የሀብት አቅም

ደረጃ ስጦታ ተደረገላቸው። የመጨረሻውን ስጦታ የተቀበለው አንድ ኮሳሳ፣ ቀጭን፣ ፀጉሩ

ቀይ፣ፊቱ ጠቃጠቆ ያለበት የአስር ዓመት ልጅ ነበር። የተሰጠው ስጦታ ስለተፈጥሮ ታሪክ

የሚያወራ ምንም ዓይነት ሥእላዊ መግለጫ የሌለው ነበር። ልጁ የሞግዚቷ ልጅ ነበር።

ሞግዚቷ ባሏ የሞቶባት ምስኪን ነች። ልጇ አለባበሱና አጠቃላይ ሁኔታው የሚያሳዝን ነበር።

አጠቃላይ ሥነ-ልቦናው ተጎድቷል። ልጁ የሃባታሞቹን ልጆች አሻንጉሊት ቢያገኝ ደስ ባለው

ነበር። ግን መድፈር አልቻለም። ለነገሩ ለተመልካች ልጁ ደረጃውን ያወቀ ይመስላል።

እኔ ደግሞ ጥሎብኝ ልጆችን አተኩሬ መመልከት እወዳለሁ። ልጆች በውስጣቸው ያለውን

ግለኝነት ለማሳየት ሲታገሉ ማስተዋል በጣም አስገራሚ ነገር ነው። አሁንም ፀጉረ ቀዪ ልጅ

የሀብታሞቹ ልጆች የያዟቸውን ስጦታዎች በጣም ፈልጓቸዋል። እና ቀስ ብሎ ልጆቹን አባብሎ

አብሯቸው ለመጫወት ወሰነ። ፈገግታ አሳይቶ አብሯቸው ለመጫወት ስለለፈገ  ያለችውን

አንድ ብርቱካን ብዙ ጣፋጭ ነገሮች በኪሱ አጭቆ ለያዘ አንድ ልጅ ሰጠው።

ግን በዚህ መሃል አንድ ባለጌ ልጅ ድንገት የሞግዚቷን ልጅ ጣለውና ይደበድበው ጀመር። ልጁ

መልሶ ሊመታው ቀርቶ ለማልቀስ እንኳ አልደፈረም ነበር። እናቱ መጣችና አትረብሻቸው

አለችና እኔና  ልጅቷ ወደ አለንበት ከፍል አምጥታ ልጅቷ አጠገብ አስቀመጠችው። ሁለቱ

ልጆች በውድ ዋጋ የተገዛውን አሻንጉሊት ልብስ እያለበሱ መጫወት ጀመሩ።  

ያለሁበት እንደተቀመጥኩ ግማሽ ሰዓት ያህል አለፈ። ባለቀይ ፀጉሩን ልጅና ለጥሎሽ የሚሆን

ገንዘብ የተቀመጠላትን ልጅ ጫዎታ በከፊል ሳዳምጥ እንቅልፍ ሊወስደኝ ሲል ጁሊያን

ማስታኮቪች በድንገት ወዳለንበት ክፍል ገባ። አንደገና ከክፍሉ ጫጫታውን ምክንያት አድርጎ

ወጣ። ከጥቂት ግዜ በፊት በቅርብ ከተዋወቀው ከሃብታሟ ልጅ አባት ጋር በደንብ ሲያወራ

ዐይቼው ነበር።

አንድ ቦታ ቁሞ ለብቻው ያጉተመትም ጀመር። ጣቶቹን እየቆጠረ ሂሳብ የሚያስብ

ይመስላል። ሦስት መቶ፣ ሦስት መቶ አስራ አንድ፣  አስራ ሁለት፣ አስራ ሦስት፣ አስራ

ስድሰት፣… በአምስት ዓምስት!  አራት በመቶ ቢሆን እንኳ አምሰት ጊዜ አስራ ሁለት፣ ስድሳ

ይሆናል። ይሄን ደግሞ በአምስት ዓመት ስናባዛው ሰድሳ ይሆናል፣ ስድሳው ደግሞ በአምስት

ዓመት አራት መቶ ይሆናል። ይገርማል! ግን ብልጡ ቀበሮ ሽማግሌ በአራት ከመቶም በሆን

የሚረካ አይመስልም

አይሆንም። የሚያገኘው ምናልባት ስምንት ወይም አስር ሊሆን ይችላል። አምስት መቶ ቢሆን

እንኳ፣ አምስት መቶ ሺ እንደሚሆን የተረጋገጠ ነው። ከዚህ በላይ የተገኘው ደግሞ ለኪስ

ይሆናል። ይገርማል።

ተናፈጠና ልጅቷን ቆም ብሎ ዐየት አደረገና ከክፍሉ ወጥቶ ለመሄድ ተዘጋጀ። እኔ ደግሞ

ባለሁበት ክፍል እፅዋት ስለተከለልኩ ዕይታው አላገኘኝም ነበር። ሰውዬው በደስታ ስሜት

የሚንቀጠቀጥ መሰለኝ። ይህን ስሜት የፈጠረበት ሂሳቡ ሳይሆን አይቀርም። እጆቹን እያፋተገና

እየተንጎራደደ እንደ መደነስ ሞከረ። የደስታ ስሜቱ የበለጠ ተነሳሳ። በመጨረሻ ስሜቱን  ተቆጣጠረና ቀጥ ብሎ ቆመ። ከዚያ ትኩር አድርጎ የወደፊት ሚስቱን ተመለከተና ወደ አጠገቧ

ለመሄድ ፈለገ። ግን አስቀድሞ ዙሪያውን ቃኘት አደረገ። ከዚያ ቀስ ብሎ የፀፀት ስሜት

የተሰማው መስሎ ወደ ልጅቷ ተጠግቶ ፈገግታ ዕያሳየ ጎንበስ ብሎ ልጅቷን ራሷ ላይ ሳማት።

ድርጊቱ ያልተጠበቀ ስለሆነ ልጅቷ የድረሱልኝ ዓይነት ድምፅ አሰማች።

“እዚህ ምን ታደርጊያለሽ ልጄ?” አለ፣ ዙሬያውን ዕየቃኘና ጉንጯን ቆንጠጥ እያደረገ።    

“እየተጫወትን ነው።”

“ከሱ ጋር ነው የምትጫወቺው?” አለ ጁሊያን ማስታኮቪች የሞግዚቷን ልጅ በጥርጣሬ

እየተመለከተ። ከዚያ “ማሙሽ ወደ እንግዳ ማረፍያው ክፍል ሄደህ ተጫወት” አለው። 

ልጁ ዝም እንዳለ ቀና ብሎ ሰውየውን ዓይኖቹን አፍጦ ተመለከተው። ጁሊያን ማስታኮቪች

በጥንቃቄ ዙርያውን ቃኘና እንደገና ወደ ልጅቷ አጎነበሰ።

“ምንድን ነው የያዝሽው፣ አሻንጉሊት ነው የኔ እመቤት?”

“አዎ” አለች ልጅቷ በፍርሃት ስሜት ግንባሯን አጨማዳ።

“በአሻንጉሊት ነው የምትጫወቺው? ለመሆኑ አሻንጉሊት ከምን እንደ ሚሠራ ታወቂያለሽ፣ የኔ

እመቤት?” 

“አላውቅም የኔ ጌታ” አለችና ጎንበስ አለች።

“አሻንጉሊት ከቁርጥራጭ ጨርቃጨርቅ ነው የሚሠራ የኔ እመቤት። እንደ ገና “አንተ ልጅ

ልጆቹ ወዳሉበት ማረፍያ ክፍል ሂድ” አለው ኮስተር ብሎ።

ሁለቱ ልጆች ኮስተር አሉ። ተያያዙና አንላቀቅም አሉ።

“አሻንጉሊት ለምን እንደሰጡሽ ታውቂያለሽ?” ሲል ጠየቀ ጁሊያን ማስታኮቪች ድምፁን ዝቅ

አድርጎ።

“አላውቅም” አለች ልጅቷ።

“ሳምንቱን ሙሉ ጥሩ ልጅ ስለሆንሽ ነው የሰጡሽ” አለ።

ይህን ካለ በኋላ ጁሊያን ማስታኮቪች ስሜቱ በጣም ተነሳሳ። ከዚያ ዙሪያውን ቃኘና ድምፁን

ዝቅ አድርጎ በስሜት እየትቁነጠነጠ “ወላጆችሽን ለመጠየቅ ብመጣ ታፈቅሪኛለሽ?” በማለት

ጠየቃት።

ከዚያ ልጅቷን ለመሳም ሙከራ አደረገ። የዚህን ጊዜ ልጅቷ ልታለቅስ ስትል የተመለከተው በለ

ቀይ ፀጉሩ ልጅ የልጅቷን እጅ ይዞ በሃዘን ስሜት ጮክ ብሎ አለቀሰ። ድርጊቱ ሰውየውን

አስቆጣው።

“ከዚህ ሂድ! ከዚህ ሂድ! ጓደኞችህ ወዳሉበት ሂድ” በማለት ልጁ ላይ ጮኸበት።

“እንዲሄድ አልፈልግም። እንዲሄድ አልፈልግም! አንተ ሂድ!” በማለት ልጅቷ ጮኸች።

“አትንካው! አትንካው!” እያለች ለማልቀስ ቃጣት።     

ከበሩ በኩል የእግር ኮቴ ተሰማ። የዚህን ጊዜ ጁሊያን ማስታኮቪች ካጎነበሰበት ቀና አለ። የዚህን

ጊዜ ባለቀይ ፀጉሩ ልጅ የበለጠ ደነገጠ። ፈራ። የልጅቷን እጅ ለቀቀና በእንግዳ ማረፍያው ክፍል

አቋርጦ ወደ መመገብያ ክፍሉ እየሮጠ ሄደ።

ትኩረት ላለመሳብ ፈልጎ ጁሊያን ማስታኮቪችም ወደ መመገብያ ክፍሉ ሄደ። በጣም ቀይ ነው።

ራሱን በመስታወት ሲያይ የሚጨንቀው ይመስላል። በስሜት ተገፋፍቶ ራሱን መቆጣጠር

ባለመቻሉ ተናደደ። ለማንነቱና ለክብሩ ምንም ግምት ባለመስጠቱ አዘነ።  የባንክ ወለዱ

የሚያስገኘውን ትርፍ ሲያሰላው እንደወጣት ስሜቱን መቆጣጠር ተሳነው። ነገሩ የሚፈፀመው

ገና ከአምስት ዓመት በኋ ነው። ይህን ትልቅ ሰው ተከትየ ወደ ምግብ አዳራሹ ሄድኩ። እዚያ

ደግሞ አዲስ ነገር ዐየሁ።

ጁሊያን ማስታኮቪች በንዴት ባለቀይ ፀጉሩን ልጅ ያስፈራራው ጀመር። ልጁ በፍርሃት መሸሽ

እሰከሚችልበት ጥግ ድረስ አፈገፈገ። ሰውየው ግን አልለቀቀውም።  እየተከተለ “ከዚህ ውጣ

እዚህ ምን ታደርጋለህ? አንተ የማትረባ! ፍራፍሬ እየሰረቅህ ነው አይደል? አዎ ፈራፍሬ

እየሰረቅህ ነው! ውጣ! ውጣ ነው የምልህ! ሂድ ወደ ብጤዎችህ! አስቀያሚ!” በማለት  

አሰቃየው።

ልጁ ምንም ማድረግ ስለአልቻለ ጠረጴዛው ሥር ገባ። ሰውየው ግን አሁንም አልተወው።

የናይለን መሃረቡን ከኪሱ አውጥቶ እንደ ዱላ በመጠቀም ከተደበቀበት ሊያስወጣው ሞከረ።

እዚህጋ አንድ አስተያየት መስጠት አለብኝ። ጁሊያን ማስታኮቪች ወፍራም ሰው ነው። በደንብ

የተመገበ፣ፊቱ ድንቡጭቡጭ ያለ። ጡንቻው ፈርጣማ ነው። እና ትንሹን ልጅ ከጠጴዘው ሥር

አስወጣለሁ ብሎ ጎንበስ ቀና ሲል ላብ በላብ ሆነ። ቁና ቁና ይተነፍስ ጀመር። በልጁ ላይ

ያደረበት ጥላቻ ወይም ቅናት ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ ድርጊቱ የጤነኛ ሰው ሳይሆን የእብድ

ነበር የሚመስል።

እኔ በሰውየው ድርጊት በጣም ከመገረሜ የተነሳ አላስችል አለኝና ከልቤ ሳቅኩ። የዚህን ጊዜ

ጁሊያን ማስታኮቪች ዞር አለ። ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ግራ ገብቶት ነበር። የተከበረ ሰው

መሆኑን ጭምር እስከ መርሳት ደርሶ ነበር። በዚህ መካከል አስተናጋጃችን ፊት ለፊት ባለው

በር በኩል ብቅ አለ። ልጁ ከጠጴዛው ሥር ወጣና ጉልበቱን እና ክንዱ ላይ ያለውን አቧራ

መጠራረግ ጀመረ። ጁሊያን ማስታኮቪች መሃረቡን አፍንጫወን ለማፅዳት ሊጠቀምበት የፈለገ

ይመስል ወደ አፍንጫው አስጠጋ። አስተናጋጃችን ሦስታችንንም በጥርጣሬ ተመለከተን። ግን

ዓለምን ጠንቅቆ እንደተረዳና ፈጥኖ እንደሚመሳሰል ዐይነት ሰው ሆኖ አጋጣሚውን እንግዳውን

ለማነጋገርና የሚፈልገውን ለማግኘት ተጠቀመበት።         

“ያ ያልኩህ ልጅኮ ይሄ ነው” አለ ቀይ ፀጉር ወደ አለው ልጅ እያመለከተ። “እና ስለ እሱ ሆኜ

እኔ ላመሰግንህ እፈልጋለሁ” አለ ጋባዣችን።

“ግን ራሱን ገና መቆጣጠር አልቻለም” አለ ጁሊያን ማስታኮቪች።

“የሞግዚቴ ልጅ ነው። ምስኪን ሰው ነች። ባሏ ታማኝ መኮንን ነበር። ለዚህ ነው የሚቻለህ

ከሆነ…” አለ በልመና ዓይነት።

“በፍፁም የሚሆን አይደለም!” በማለት ጁሊያን ማስታኮቪች በፍጥነት ጮኸ። “ይቅርታ

አድርግልኝ ፊሊፕ አሌክሴቪች። ጠይቄ ክፍት የሥራ ቦታ እንደሌለ ነግረውኛል። በዚያ ላይ

አስር የሚሆኑ ከረፍት የሥራ ቦታ ተጠባባቂዎች አሉ።”

“በጣም ያሳዝናል። ግን ልጁ ዝምተኛና በሰው ጉዳይ ጣልቃ የማይገባ ነው።

“በጣም ባለጌና ወስላታ ልጅ ነው” አለ ጁሊያን ማስታኮቪች በመቆጣት። “ሂድ ከዚህ። እዚህ

ምን ታደርገላለህ? በል ልጆች ወዳሉበት ሂድ።”

ራሱን መቆጣጠር አቅጦት እኔን የጎሪጥ ተመለከተኝ። እና ራሴን መቆጣጠር አቃተኝ። በቀጥታ

ፊት ለፊት ተመለከትኩት። ከዚያ ዞረና አስተናጋጃችንን ለኔ ሊሰማ በሚችል ድምፅ ያ ለየት

ያለ ወጣት ማነው በማለት ጠየቀው። ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው ከተነጋገሩ በኋላ እኔን ከቁብ

ሳይቆጥሩ ከክፍሉ ወጥተው ሄዱ።   

እኔ ግን በጣም ሳቅሁ። ከዚያ እኔም ወደ እንግዳ ማረፊያ ክፍል ሄድኩ። የተከበረው ሰውየ

አባቶች፣ እናቶችና ጋባዣችንና ሚስቱ ጭምር  ከበውት በቅርብ ለተዋወቃት ሴት በጉጉት

መለስ እየሰጠ ነበር። ሴትየዋ የሃብታሟን ልጅ እጅ ያዘች። ጁሊያን ማስታኮቪች ልጅቷን

ከልቡ። ውበቷን፣ ችሎታዋን፣ ግርማ ሞገሷን፣ ከተከበረ ቤተሰብ መገኘቷን እየጠቀሰ አደነቀ።

የዚህን ጊዜ እናትየው ከመደሰቷ የተነሳ እምባዋን ማቆም አልቻለችም ነበር። አባትየው ደግሞ

የተሰማውን ደስታ በእርካታ በታጀበ ፈገግታ ነበር ይገልፅ የነበረው።

በወቅቱ የነበረው ደስታ ተላላፊ ነበር ማለት ይቻላል። ሁሉም ነበር የተደሰተ። ልጆቹ እንኳን

ሳይቀሩ ውይይቱን ላለማቋረጥ ጫወታቸውን ተው። አየሩ በአድናቆት ተሞላ። ጁሊያን

ማስታኮቪች በተመረጡ ቃላት ስለልጅቷ በሚሰነዝረው አድናቆት እናትየው የተሰማት ደስታ

በጣም ጥልቅ ነበር። ጁሊያን ማስታኮቪች ከመጀመርያው የግብዣው ጥሪ ሲደረግለት ወደር

የሌለው ደስታ እንደተሰማው ሰምቻለሁ። ከዚያ እንግዶቹ በየአቅጣጫው ተበትነው ሃብታሙን

ነጋዴ፣ ሚስቱን፣ ልጃቸውንና በተለይ ደግሞ ጁሊያን ማስታኮቪችን ማድነቅ ጀመሩ።

“አግብቷል እንዴ?” በማለት ጁሊያን ማስታኮቪች አጠገብ የቆመ አንድ የማውቀውን ሰው ጮክ

ብዬ ጠየቅኩት።

ጁሊያን ማስታኮቪች በቁጣ ተመለከተኝ።

“አላገባም” አለኝ ሆን ብየ ባሳየሁት ግዴለሽነት በመደንገጥ።

በቅርብ ቀን እየተጓዝኩ ሳለ አንድ ቤተከርስትያን ወስጥ ሰዎች ተሰብስበው ዐየሁ። ተጠግቼ

የተሰበሰቡት ለሠርግ መሆኑን አወቅሁ። ቀፋፊ ቀን ነበር። ዝናብ መዝነብ ሊጀምር ነው።

ተሸሎክልኬ ወደወስጥ ገባሁ። ሙሽራው በደንብ ተቀልቦ የሰባ ወፍራም ሰው ነበር። በደንብ

ለብሶ አምሮበታል። ወዲያና ወዲህ እያለ ያስተባብራል። ትንሽ እንደ ቆየሁ ሙሽሪት መጣች

መጣች ተባለ። እንደምንም ተጋፍቼ ሙሽራዋን ለማየት እድል አገኘሁ። ውብ ነች። ግን ውበቷ

የደበዘዘና የሚያሳዝን ነው። የተረበሸች ትመስላለች። እነዲያውም በቅርብ ጊዜ ያለቀሰች ይመስል

ዐይኖቿ ቀልተዋል። እያንዳንዱ የፊቷ መስመር የተረጋጋ ውበቷን ይገልፃል። ግን በዚህ

የመረጋጋት ገፅታዋ አልፎ የልጅነት የዋሕነቷ ያንፀባርቃል። ከፊቷ ላይ የሚነበበው ሊገለፅ

የማይችል ገራገርነት ይቅርታ እንዲደረግላት የሚጠየቅ ይመስላል።

ሰዎች ገና አስራ ሰድስት ዓመቷ ነው እያሉ ያወራሉ። ቀስ ብዬ ሙሽራውን ተመለከትኩ።

ወዲያው ከአምስት ዓመት በፊት ያየሁት ጁሊያን ማስታኮቪች ትዝ አለኝ። እንደገና ሙሽራዋን

ዐየሁ። ከዚያ አቤቱ አምለኬ! ብየ ከቤተክርስቲያኑ በፍጥነት ወጥቼ ሄድኩ። የሠርጉ ታዳሚ

አሁንም ስለ ልጅቷ ሃብትና ስለ አምስት መቶ ሺ ሩብል ጥሎሽ ነው የመያወራ።

“ለካስ ስሌቱ ትክክል ኑሯል” ብዬ አሰብኩና ወደ መንገዴ ገብቼ ጉዞዬን ቀጠልኩ።             

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top