ታዛ ስፖርት

የጄኔራሉ ቤት (ማሞ ወልዴ ደጋጋ)

የቢቢሲ ጋዜጠኞች ከሜክሲኮ ኦሎምፒክ የማራቶን አሸናፊው ማሞ ወልዴ ጋር ቃለ ምልልስ እያደረጉ ነው። ከርሱ ጋር ለሦስት ቀን ይቆያሉ። የኢትዮጵያ አትሌቶች በአበበ ቢቂላ ጀማሪነት ሦስት ጊዜ በተከታታይ የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘታቸው ዓለም ስለተገረመና በሀገራቸው ጥሩ እንክብካቤ ይደረግላቸዋል ተብሎ ስለተወራ “የአትሌቶች አያያዝ እንዴት ነው?” የሚል ዘገባ ለመስራት ፈልገው ነው የመጡት። ጋዜጠኞቹ የኢትዮጵያን ምድር የረገጡት ማሞ ከሜክሲኮ ሜዳሊያውን ይዞ በተመለሰ በአስራ አምስተኛው ቀን ነበር። አሁን በአትሌቱ ህይወት ዙሪያ ዶክመንተሪ ፊልም እየሰሩ ነው።

ጋዜጠኞቹ ትላንትና በልምምድ ሜዳ ላይ ነው የቀረፁት። ዛሬ ደግሞ መኖሪያ ቤቱ እየቀረፁት ነው። ቤቱ በጣም ምርጥ ነው። ከኢትጵያ ህዝብ ኑሮ አኳያ ጋዜጠኞቹ የማሞን ቪላ ቤት ዐይተው ከውጤቱ አንፃር “ይገባዋል” ብለው ደምድመዋል። ግቢው ሰፊ ነው። ቤቱም የተለያዩ ክፍሎች አሉት። ጋዜጠኞቹ ማሞ ቤቱን እያዞረ እንዲያሳያቸው ፈለጉና ጉብኝቱ ተጀመረ። ስለእያንዳንዱ ክፍል እየጠየቁት ነው። አስገራሚው ነገር ማሞም እንደ ጋዜጠኞቹ ቤቱን አለማወቁ ነው። አስጎብኚና ጎብኚ በቤቱ ሁኔታ ግራ ተጋብተዋል።

Sep 1972: Mamo Wolde of Ethopia in action during the Marathon event at the 1972 Olympic Games in Munich, Germany. Wolde went on to win the Bronze medal with a time of 2.15.08.4 Hours. \ Mandatory Credit: Tony Duffy/Allsport

ጋዜጠኞቹ የማሞን ታሪክ በፊልም ቀርፀው በቴሌቪዥን ሊያስተላልፉ ቢፈቀድላቸውም መንግሥትን ያሰጋው ነገር አንድ ጉዳይ ነበር። ማሞ የሚኖርባት ቤቱ ደሳሳ ነች። እዚህ ቤት ውስጥ ፊልም ከተቀረፀና ለዓለም ከተላለፈ የኢትዮጵያን ገፅታ ያበላሻል ተብሎ ስለታሰበ የአንድ ጄኔራል ቤት  ተሰጠው። ትዕዛዙ የመጣው ከላይ በመሆኑ ሰውየው ቤቱን ለማሞ በፍጥነት አስረከበ። ነገሮች በጥድፊያ ስለተደረጉ ጄኔራሉ እቃቸውን ከቤት አላወጡም።

አንድ ቀን ከሰዓት ማሞ ከእንግዶች ጋር ሆኖ ደሳሳ ቤቱ ውስጥ እየተጫወተ ሳለ ሰዎች እንደሚፈልጉት ተነገረው። ከአንደኛው በስተቀር ሌሎቹን አያውቃቸውም። ሰውየው ትልቅ ባለሥልጣን ናቸው። “ሰለም ነህ ማሞ” አሉት።

“ደህና ነኝ… ቤት ግቡ”

ሰዎቹ ወደ ግቢው ዘለቁ። እኚህ ባለሥልጣን ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ ማሞ እንዴት እንደሚያስተናግዳቸው ግራ ገብቶታል። ሶፋ ቢኖር እዚያ ላይ ያስቀምጣቸዋል። ቤቱ ውስጥ ደህና ወንበር እንኳን አልነበረውም። የግቢውን አጥር እንኳን ያጠሩለት የክብር ዘበኛ ወታደሮች ናቸው። አቀባበል ካደረጉለት በኋላ ቤቱን ቀለም ቀቡለት አጥሩንም አስተካከሉት።

ማሞ አሁን ግቢ ውስጥ የዘለቁትን ሰዎች ምን እንደሚያረጋቸው ግራ ገባው። ለነርሱ የሚመጥን የተዘጋጀ ነገር የለም። ግን ዝም ማለት የለበትም። በድጋሚ “ወደ ቤት ግቡ” አላቸው።

“አንገባም”

“ቡና ይፈላል ምሳም ትበላላችሁ”

“ችግር የለም እዚሁ እናናግርህ”

“አሺ”

“በንጉሱ ትዕዛዝ የተሻለ ቤት እንዲሰጥህ ተወስኗል”

“ለእኔ?”

“አዎ ላንተ”

“በጣም ደስ ይለኛል”

“አሁን ከኛ ጋር ትሄዳለህ”

“የት?”

“ቤቱን ልታይ”

ማሞ እውነት አልመሰለውም። ይዋሻሉ እንዳይል ባለሥልጣን ናቸው። ከሰዎቹ ጋር ወደ ቦታው ሄደ። ቤቱን ሲያየው በፍፁም አላመነም “ይሄ ለኔ ነው?” ብሎ በመገረምና ባለማመን ጠየቃቸው። እነርሱም የቤቱን ቁልፍ እየሰጡት። “እዚህ ቤት አንድ ጀኔራል ይኖር ነበር። ለጊዜው ሌላ ቦታ እስኪሰጠው ላመጣኸው ውጤት ቤቱ ላንተ በሽልማት መልክ ተሰጥቶሀል። ውስጥ ያለውንም ዕቃ ተጠቀምበት” አሉት። ወዲያውኑ ቤቱ በአስቸኳይ ቀለም እንዲቀባ ተደረገና ማሞ ገባ። እርሱ እንደገባ በነጋታው የቢቢሲ ጋዜጠኞች መጡ። ጉብኝቱ ቀጥሏል። ማሞ ይሄ ነገር ይመጣል ብሎ ስላልጠበቀ አልተዘጋጀም። ሳሎን የጀኔራሉ ፎቶ ተሰቅሏል ጋዜጠኞች “ይሄ ፎቶ የማነው?” አሉት።

“አርበኛ ናቸው”

“በህይወት አሉ?”

“ጦርነት ላይ ሞተዋል”

“በየትኛው ጦርነት”

“ማይጨው”

 የመጣለት ሀሳብ ይሄ ነበር። ጄኔራሉ በህይወት አሉ። ጥያቄው ድንገት ስለመጣ ሞተዋል ለማለት ተገደደ። የጄኔራሉ የወታደር ጫማ ተደርድሯል ስለጫማዎቹ ጠየቁት አድርጎ እንዲያሳያቸው ጠየቁት አደረገ። ጨማው ሰፊ ነበር ለርሱ የሚበቃው አልሆነም። ልብስ እየቀያየረ ሊቀርፁት ፈለጉ። ሰውየው ወፍራም ስለሆኑ ልብሱ ከማሞ ጋር የሚሄድ አልሆነም። ነገሩ ለማሞ አስጨናቂ ሆነ። ጋዜጠኞቹና ማሞ ግቢ ውስጥ እየተዘዋወሩ ነው። የጄኔራሉ መኪና ቆማለች “ይህች መኪና ገዝተህ ነው ተሸልመህ?” አሉት።

“ገዝቼ ነው”

“ስንት ገዛሃት?”

“በቅናሽ ነው”

“እስኪ ግባና እየነዳህ እንቅረፅህ?”

ማሞ መኪና መንዳት ችግር አለበት “ዛሬ የመኪና መንዳት ፕሮግራም የለኝም” ብሎ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ።

የጄኔራሉ ወንድም ራቅ ወደ አለ ክፍለ ሀገር ሲሄድ መኪናውን እዚህ ግቢ ነበር የሚያቆማት። አሁን ከጉዳዩ ስለተመለሰ ግቢ ውስጥ ያቆመውን የራሱን መኪና ሊያወጣ መጣ። በሩን አንኳኳ፤ ማሞን ለማስተናገድ ከተመደቡት ሰዎች አንዱ በሩን ከፈተ። ሰውዬው ወደ ውስጥ ሲገባ “ማንን ፈልገህ ነው?” አለው።

“መኪና ልወስድ ነው”

“የምን መኪና?”

“መኪናዬን ነዋ!!!”

“የትኛው?”

“ይሄኛው”

“ይሄማ የማሞ መኪና ነው”

“እንዴት ሆኖ?”

“ንጉሱ ነው የሰጡት”

“የኔን?”

“አዎ”

“እኔ ሳልጠየቅ?”

ሰውዬው በነገሩ ግራ ተጋባ ለማን አቤት ይባላል ብሎ ግራ ተጋባ። በሁለተኛው ቀን የጄኔራሉ ሚስት ዕቃ ልትወስድ መጣች። ከአስተናጋጁ አንዱ ተደብቆ በሬድዮ ለአለቃው ነገረው። ከግቢው ውጭ ለዚህ የተዘጋጁ ሰዎች ስላሉ ሴትየዋ በአክስትነት አዘጋጇትና ለጋዜጠኞቹ ተነገራቸው። ጥሩ አጋጣሚ በመሆኑ ጋዜጠኞቹ ስለማሞ አስተዳደግ አክስት ተብዬዋን ጠየቁ። ወተት እየጠጣ እንዳደገ። ሩጫ ጎበዝ እንደሆነ አስረዳች። የተነገራትም እንደዚህ እንድትል ነበር። ወዲያውኑ ከግቢ አስወጧት። ከ3 ቀን በፊትም ድንገት መጥተው ነው ሴትዬዋን ከነባለቤቷ “በአስቸኳይ ልቀቁ የተባሉት “አሁን ደግሞ የማታውቀውን ምስክርነት ሰጥታ ቶሎ ከግቢ ሸኟት። ሴትዬዋ “እዚህ ግቢ ምን እየተደረገ ነው?” ብላ አሰበች። ማሞንም ልታናግረው ፈለገች ግን አልተሳካላትም።

Mamo Wolde of Ethiopia waving to the crowd after winning the men’s marathon during the Summer Olympic Games in Mexico City, circa October 1964. (Photo by Ed Lacey/Popperfoto via Getty Images/Getty Images)

በሦስተኛው ቀን ጋዜጠኞቹ ተጨማሪ ቀረፃ ያደርጋሉ። ስለ ማሞ የሚያውቁ አንዳንድ ሰዎችን ያነጋግራሉ። ከምሳ በኋላ ነው የሚሄዱት። በጠዋት አትክልት ሲያጠጣ ግቢ ውስጥ ያሉትን ውሻና ከብት ሲንከባከብ ተቀረፀ። ጄኔራሉ ሁለት ፈረሶች ግቢ ውስጥ ነበራቸው። አንዱ ያልተገራ ነው። ማሞን ፈረሱ ላይ ሆኖ ሊቀርፁት ፈለጉ። ሌጣውን ፈረሱ ላይ ፈንጠር ብሎ ጀርባው ላይ ወጣ። ነገር ግን ፊልሙ ሲቀረፅ ማሞ ፈረሱ ላይ አልነበረም። ፈረሱ ያልተገራና አስቸጋሪ በመሆኑ እዚህና እዚያ ተንፈራግጦ ማሞን አንስቶ አፈረጠው። ባለቤቱ ፈረሱን ገና ያልገራው መሆኑን ማሞ አላወቀም ነበር። ቢጎዳም “አንዳንዴ ይሄ ፈረስ ያስቸግረኛል። ግን ከምወደው አንዱ ነው። በልጅነቱ ነው የገዛሁት” አላቸው። በሌላኛው ፈረስ እንዲቀረፅ ነገሩት። ከዚያ ይልቅ የሚበላ ነገር እየሰጣቸው ተቀረፀ። ያኛውን ግን ብዙም አልተጠጋውም።

የምሳ ሰዓት ደረሰና እየተበላ ቀረፃ ተካሄደ። የፈረንጅና ሀበሻ ምግቦች በቡፌ መልክ ቀረበ። ለዚሁ ሲባል የማሞን መስተንግዶ የሚመሩት ሰዎች አቅርበውለታል። ወጥቤቶቹም ከትላልቅ ሆቴል የመጡ ናቸው። ማሞ ፈረንጆቹን ለማስተናገድ ምንም አቅም የለውም። ላድርግ ቢል እንኳን ይሄን ሁሉ ወጪ እንዴት ይችለዋል? ማን እንደሸፈነ ባይነግሩትም ከበላይ አካል ነው ስለተባለ ነገሩን በፀጋና በደስታ ተቀብሎታል። ምሳ እየተበላ ሰሞኑን የተቀረፀው የማሞ ፊልም እየታየ ነበር። በእንግሊዝ ሀገር ስለእርሱ በጋዜጣ ላይ የወጣውን ፎቶግራፎችን ተመለከተ። ፎቶዎቹ እነርሱ አንስተው የላኩት ነበሩ። ጋዜጠኞቹ የኢትዮጵያ አትሌቶች ጥሩ እንክብካቤ ስለተደረገላቸው ነው ውጤት የሚያመጡት በሚል እንደማሳያነት ተመለከቱና ሌሎችንም አትሌቶች በዚህ ዓይነት እንደሚንከባከቧቸው አመኑ።

የከሰዓቱ ቀረጻ ወደተለያየ ቦታ ሄደው ማሞ ከኅብረተሰቡ ጋር ያለውን ግንኙነት ለመቅረፅ ቀጠሮ ይዘዋል። ለሚቀረፁት ሰዎች መባል ያለበትን አስተናጋጆቹ በቅድሚያ ይነግሯቸዋል። ማሞ ወደ ቀድሞ ሰፈሩ ሲሄድ አስተናጋጆቹ ከለከሉት። አስተናጋጆቹ ከማሞ ወገን ሆነው ነገሮችን የሚቆጣጠሩ ናቸው። ማሞን አጣድፈው ነው ወደ አዲሱ ቤቱ ያስገቡት። ከቀድሞ ቤቱ ዕቃውን አላወጣም ነበር። በቀረፃና በሌላም ጉዳዮች ሲዋከብ ወደ ቀደሞ ቤቱ አልሄደም። አሁን ግን በዚህ አጋጣሚ ወደ ቤቱ ደረስ ሊል ፈለገ። ከአስተናጋጆቹ ለአንዱ “ዕቃዎቼን ከቤት ላምጣ?” አለው።

“ምን ያደርግልሃል? የተሟላ ነገር አለህ”

“አንዳንድ የምፈልጋቸው ነገሮች አሉ”

“ለምሳሌ ምን”

“ፎቶዎች….ሌላም”

“ሌላ ፎቶ ትነሳለህ”

ነገሩ ለማሞ ግራ የሚያጋባ ቢሆንም አሁን በሽልማት የተሰጠው ቤት ከምንም ነገር ይበልጥበታል። ነገር ግን የቀድሞ ቤት ውስጥ ያሉት ከበፊት ጀምሮ የተነሳቸው ፎቶዎች፣ የስፖርት ትጥቆች፣ ሌላም የሚፈልጋቸውን ዕቃዎች ብወስድ ምን ችግር አለበት ብሎ አሰበ። እቃውን ለመውስድ አንድ ዘዴ መጣለት ለአስተናጋጆቹ “ጋዜጠኞቹ የቀድሞ ቤቴን ማየት ይፈልጋሉ” አለ።

“አይቻልም”

“ለምን”

“ካሳየህ ወይም ከነገርካቸው አሁን የተሸለምከውን ቤት ታጣለህ”

“ምን ችግር አለው?”

“ምንም”

“ላሳያቸዋ!!”

“ቤቱ የለም”

“እንዴት”

“ለሌላ ተሰጥቷል”

“ዕቃዬስ?”

“ሌላ ቦታ ስለተቀመጠ በተመቸህ ጊዜ ትወስዳለህ”

ማሞ በነገሩ ቢስማማም እነዚህ ጋዜጠኞች የድሮ ቤቱን ቢቀርፁለት ጥሩ እንደሆነ አሰበ። ቤቱ ያለመቀረፁ ምን ያህል ጉዳት እንዳለው አልተገነዘበም። ጋዜጠኞቹ በማሞ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥነውን ፊልም ቀርፀው ጨረሱና በስፖርተኞች አያያዝ የኢትዮጵያ መንግሥትን አድንቀው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።

    አንድ ቀን ጠዋት ማሞ በአዲሱ ቤቱ ገንዳ ውስጥ በሞቀ ውሃ ሰውነቱን እየታጠበ ነው። በሚያምረው ገንዳ እየተንፈላሰሰ ብዙ ነገር አሰበ። በእንዲህ ዓይነቱ ገንዳ የሚጠቀመው ውጭ አገር ለወድድር ሲሄድ ነው። ከዚያ ውጭ የገንዳ ሻወር አያገኝም። ገንዳ ውስጥ ሆኖ ያችን ደሳሳ ቤቱን አሰባት። ሻወር ሲፈልግ በባልዲ ውሃ አምጥቶ ብረት ምጣድ ላይ በጣሳ ሰውነቱ ላይ እያፈሰሰ ነው የሚታጠበው። ዛሬ ያቺ ቤቱ ትዝ አለችው። እዚያው ገንዳ ውስጥ ሆኖ ማሞ ስለቤቱ አሰበ። ከአቅሙ በላይ የሆነ መኖሪያ ነው የሰጡት። የክፍሎቹ ብዛት፣ የግቢው ስፋት፣ የቤቱ ውበት የሚያስገርም ነው። ይሄን ቤት ሽጦ መለስተኛ ቤት ሰርቶ በቀረው ገንዘብ ሊጠቀምበት ፈለገ። ይሄን ሀሳቡን ቀየረና ማከራየት እንደሚቻል ወሰነ። ሊያከራየው ፈለገ።

ለማንኛውም የሚቀርቡትን ጓደኞቹ ነገ ስለቤቱ ሁኔታ ያዋያቸዋል። ዛሬ ቤቱ ትልቅ ግብዣ ጠርቷል። በስጦታ ያገኘውን ቤት የሚያስመርቀው ዛሬ ነው። ጓደኞቹንና የቅርብ ዘመዶቹን እዚህ ግብዣ ላይ እንዲገኙለት ጠርቷል። ክቡር ዘበኛ ያሉት በቅርቡ የሚያውቃቸው ወዳጆቹ ሙዚቃ ሊጫወቱለትና ግብዣውን ሊያደምቁለት እንደሚመጡ ነግረውታል።

ቤቱን ከትናንት ጀምሮ እያሰማመረ ነው። የጄኔራሉ ፎቶ ተነስቷል። ይሄ ትልቅና ዘመናዊ ቤት የማሞ መሆኑ ተረጋጧል። አሁን ግድግዳዎች በማሞ ፎቶዎች ተሞልተዋል። በሜክሲኮ ኦሎምፒክ አሸንፎ ሜዳሊያ ሲቀበል፣ ከንጉሱ ጋር ሰላምታ ሲለዋወጥ፣ በአዲስ አበባ አቀባበል ሲደረግለትና ሌሎችም የማሞን ድል የሚገልፁ ፎቶዎች ቤቱን አድምቀውታል ሜዳሊያውንም በሳሎን ግድግዳ ላይ ተሰቅሏል።

ዛሬ ግን ሜዳሊያውን ያወርደዋል። እንግዶች ከመምጣታቸው በፊት የማዕረግ ልብሱን ይለብስና ሜዳሊያውን በደረቱ ላይ ያኖረዋል። ከዚያም በማራቶን እንዴት እንዳሸነፈ ለተጋባዦቹ ገለፃ ያደርጋል። ይሄን ግብዣ እርሱ ቢጠራም አብዛኛው ወጪ በጓደኞቹ ተሸፍኗል። ሽንጥ ስጋ ገብቷል። ተጨማሪ በጎች ተገዝተዋል። ከምግብ በኋላ ለማወራረጃ የሚያስፈልግ ነገር ሁሉ ተሟልቷል። አንዳንድ ወዳጆቹ በጊዜ መጥተው ምሳ እስኪደርስ ከማሞ ጋር እየተጫወቱ ነው። ቤቱን እያዞረ አስጎበኛቸው። እነርሱም በጣም ተደነቁ። አንደኛው ባልደረባው።

“በኦሎምፒክ ስላሸነፍክ ነው ይሄን የመሰለ ቪላ ቤት የተሰጠህ?” አለው።

“አዎ”

“ለአበበ ለምን አልተሰጠውም?”

“መስጠታቸው አይቀርም”

“እንደርሱ ነው?”

“ይመስለኛል ወይምን መሸለም ከአሁን ጀምረው ይሆናል”

“እኔ ብሮጥና ባሸንፍ እንዲህ ዓይነት ቤት ይሸልሙኛል?”

“አዎ”

“በል እንግዲህ ነገ ሩጫ ጀምራለሁ”

የምሳ ሰዓት እየተቃረበ እንግዶችም በብዛት ወደ ቤት እየገቡ ነው። ጭፈራውን የሚያደምቁ ሰዎች መጥተዋል። ሁለት ሰዎች ከውጭ ሆነው እያንኳኩ ነው። አንድ ሰው ከፈተላቸው “ግቡ” አላቸው።

“አንገባም”

“ሌሎች እንግዶች እኮ እየገቡ ነው”

“እዚሁ እንሆናለን”

“ምሳ ደርሷል እኮ”

“ማሞን ጥራልን”

“ከእንግዶች ጋር ነው”

“ፈልገነው ነው”

“ግቡና አናግሩታ”

“ግድ የለም እዚህ ጥራልን”

ሰውዬው እንዲገቡ ቢጎተጉታቸውም ወደ ውስጥ አልዘለቁም። ማሞን ሊጠራው ሄደ። እርሱ ግን በመስተንግዶው ተወጥሮ ስለነበር ፈላጊዎቹን ገብተው እንዲያነጋግሩት ላከባቸው እነርሱም ለመግባት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው አንደኛ ስሙን ሰጠውና ለማሞ እንዲነግረው ላከው። ማሞም ስሙን ካየ በኋላ ይሄን ሰውዬ ያውቀዋል። ምን ፈልጎ ነው የመጣው? በግብዣው ጥሪ አልተደረገለትም። ይሄን እያሰላሰለ በር ላይ የቆሙትን ሰዎች ሊያናግር ወጣ አንደኛው “ልናናግርህ ፈልገን ነው” አለው።

“ቤት ግቡና እናውራ”

“እዚሁ መነጋገር እንችላለን”

“ምንድ ነው ጉዳዩ?”

“ቤቱን ልቀቅ ተብለሃል”

“እየቀለዳችሁ ነው?”

“አልቀለድንም!!”

“ማነው ልቀቅ ያለው?”

“ተወስኗል”

“ቤቱ እኮ የኔ ነው”

“ማነው የሰጠህ?”

“ንጉሱ”

“እንኳን ለአንተ ለአበበ ቢቂላም አልተሰጠም”

“ቤቱ ለእኔ እንደተሰጠኝ ምስክር አለኝ”

“ምንም ምስክር አያስፈልግም። ቤቱ ያንተ ለመሆኑ በሰነድ የተላለፈ ነገር አለ?”

“ጋዤጠኞቹ ምስክር ናቸው”

“የሚበቃህን ያህል ቤቱ ውስጥ ተንፈላሰሀል። አሁን ውጣ”

“ወጥቼስ?”

“ወደ ቀድሞ ቤት ትገባለህ”

“ቤቴ እኮ ለሌላ ሰው ተሰጥቷል”

“ለማንም አልተሰጠም”

“እቃዬም እንደወጣ ተነግሮኛል”

“ስትሄድ ሁሉንም ነገር ታገኛለህ። አሁን ይሄን ልቀቅ”

“አለቅም!”

“ችግር ውስጥ እንዳትገባ”

ማሞ ማስጠንቀቂያውን ሰምቶ ለጊዜው ከቤቱ ባይወጣም የደህንነት ሰዎች መጥተው “ቤቱ ለአስቸኳይ እንግዳ ስለሚፈለግ በቶሎ ውጣ” የሚለው ትዕዛዝ ስለመጣ ከዚህ በኋላ ምን እንደሚከተል ስላወቀ በድራማው እያዘነ ወደ ደሳሳው ቤቱ ተመለሰ። በነገሩ በጣም ተከፋ።

በሌላ ቀን ጓደኞቹ አገኙት። በተለይ አንደኛው ይቀርበዋል። ብዙ ሀሳብም የሚያማክረው ለእርሱ ነበር። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ተገናኝተው አያውቁም። ጓደኛው “አለፈልህና እኛን ረሳኸን አይደል?” አለው።

“ምን ተገኘና ረሳሀለሁ”

“ምን የመሰለ ቤት አገኘኽ”

“የምን ቤት?”

“የተሰጠህ”

“ቲያትር ሊሰሩበት ነው”

“የምን ቲያትር?”

“በነፍሴ ተጫወቱብኝ”

“እንዴት?”

“አሳይተው ነሱኝ”

ጓደኛው ተገረመ እንደገናም አዘነ። የተደረገውን ነገር አንድም ሳያስቀር ማሞ ለጓደኛው አጫወተው። ጓደኛውም፡-

“ለምን አትጠይቅም?” አለው

“ማንን?”

“የበላይ አካል”

“የሰጡኝ እነርሱ ናቸው”

“እና”

“የወሰዱትም እነርሱ ናቸው”

“ለንጉሱ ለምን አትናገርም?”

“ምን ብዬ?”

“ተወሰደብኝ ብለህ”

ጓደኛውና ማሞ ለንጉሱ የሚፁፉበትን ደብዳቤ ማዘጋጀት ጀመሩ።

ደብዳቤው ውስጥ ከተፃፉት ነገሮች ውስጥ “…ቤቱን ተነጥቂያለሁ፣ ተለዋጭ ቤት ይሰጠኝ፣ ግማሹ ቤት ይሰጠኝ፣ በሚቀጥለው ኦሎምፒክ በትጋት እንድሮጥ ተመጣጣኝ ቤት ይሰጠኝ…” የሚሉ ተካተውበታል።

የቢቢሲ ጋዜጠኞች እንደሄዱ በነጋታው አንድ ባለሥልጣን ቤቱ መጥቶ ነበር “ማነው ይሄን ቤት የሰጠህ?” አለው።

“ንጉሱ ናቸው”

“ለሌሎች ለምን አልተሰጠም?”

“እርሱን አላውቅም”

“ይሄ ቤት ይፈለጋል”

“ምን ማለት ነው?”

“ቤቱን መልቀቅ አለብህ”

“ለምን?”

“ሌላ ቤት እኔ አሰጥሃለሁ”

“ሌላ ቤት አልፈልግም ይሄኛው ተስማምቶኛል”

ማሞ በሁኔታው ግራ ተጋብቶ የርሱ አስተናጋጅ ለነበሩት በስልክ ደውሎ “አንድ ሰው መጥቶ ቤቱ ይፈለጋል አለኝ” ብሎ ነገረው።

“ማነው?”

“ባለሥልጣን ነው”

“ስሙ ማን ይባላል”

(ማሞ ስሙን ነገረው)

ሰውየው እንዳትወጣ ብሎ ነገረው። አሁን ያንን ባለሥልጣን አሰበ እርሱ “ይሄን ልቀቅና ሌላ ቤት ልስጥህ ነው” ያለው። ያኔ እርሱን እሺ ብዬው ቢሆን ጥሩ ነበር ብሎ አሰበ። ሌላም ነገር አሰበ። ጋዜጠኞቹ የድሮውን ቤት አሳይቷቸው ቢሆን ኖሮ ሌላ ጥያቄ ስለሚያነሱ ምናልባት ይሄን ፍራቻ ትልቁን ቤት አይነጥቁትም ነበር። አሁን ሁሉ ነገር አልፏል። የደህንነት ሰዎችም ከቤቱ ሲያስወጡት አስጠንቅቀውታል። ስለዚህ ጉዳይ ለማንም ቢያወራ ችግር እንደሚፈጠርበት አስረግጠው ነግረውታል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top