መጽሐፍ ዳሰሳ

የተገፉ ነፍሶች ድምጽ

የመጽሐፉ ርዕስ – ጨው በረንዳ

ደራሲ – ምስራቅ ተረፈ

የገጽ ብዛት –

የታተመበት ዓመት – 2009 ዓ.ም

የሽፋን ዋጋ –

ገጣሚ፣ ተርጓሚና ጋዜጠኛ ነቢይ መኮንን “ግጥም ከትክክለኛ ህመም ይወለዳል” ይላል። አንድ ገጣሚ የትና በምን መነሻ ትክክለኛ ህመም ታሞ ግጥም እንደሚወልድ እርግጡን ማወቅ ባልችልም ከትክክለኛ ህመም የተወለደ ግጥም በእኔ እምነት በቃላት እማሬው፣ በፀነሰው ሃሳብ፣ ለማለት የፈለገውን አንዳች ነገር እንዴትና በምን ዐይነት ኪናዊ ለዛ እንደገለፀው ወ.ዘ.ተ. ማወቅና መረዳት የሚቻል ይመስለኛል።

በዚህ መጣጥፌ የምሥራቅን “ጨው በረንዳ” አንብቤ ከግጥሞቿ መካከል ቀልብያዬን ሰቅዘው ከከረሙ፣ አሁንም ድረስ ከህሊናዬ ሊደበዝዙ ካልቻሉ ስንኞቿ የተወሰኑትን ላጋራችሁ እሞክራለሁ፤ እግር መንገዴንም መድበሏን እንድታነቡላት እቆሰቁሳችሁ ይሆናል – ከተሳካልኝ።

የምሥራቅ ተረፈን ግጥሞች እንዳስተዋልኳቸው ዘመናቸውን የሚወቅሩ እና ነቅሰው የተቹ፣ ፍቅርና ውዴታን ያገነኑ፣ ሀገርና ወገን ያባተላቸው፣ ወጣትነትንም በተኮሰ የነባር እሴት ማሰሻ ያሠሱ ናቸው።

ገጣሚዋን ምሥራቅ የዛሬው ማኅበራዊ ኑሯችን አስጨንቋታል፤ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አተኩራ በትውልዳችን ሁኔታ ሳስታለች። በባህል፣ በፆታዊ ወዳጅነት፣… እና በመሰል ጉዳዮች የዛሬ እኛነታችን የሚስተዋልበት መንጋደድ፣ ከገዛ የራስ ማንነት ተነጥለን መንጎዳችን ሲብስም መጠፋፋታችን አባትሏታል።

ምሥራቅ የሸገር ልጅ ነች! ለያውም ጨው በረንዳ ተወልዳ ያደገች። እና ምሥራቅ እምብዛም ባልተለመደ መልኩ በመድበሏ ከምስጋናዋ እና በዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ እና በጋዜጠኛ፣ በሥነ-ጽሑፍና በቴአትር ባለሙያው በቀለ መንገሻ ጥምረት የተፃፈውን መግቢያ አንብበን ወደ ግጥሞቿ ከማለፋችን በፊት በእውነታዊው የጨው በረንዳ ኑረቷ ሰቅዛ ትይዘናለች፤ ለያውም በልጅነት አስተዳደጓ።

በጨው በረንዳ ምሥራቅን እየተቀባበሉ ያሳደጓት እነ “ብርሃኔ ጅሩ /ባዬ/” የልብወለድ ገፀ ባህሪያት ይመስላሉ፤ ግና አይደሉም እውነተኛ አሳዳጊዎቿ ናቸው። ምሥራቅ ስለወላጆቿና ቤተሰቦቿ አይደለም የምትነግረን፤ ስለቀዬው እናትና አባቶቿ እንጂ፤ 4 ገፆችን በያዘው የምሥራቅ የጨው በረንዳ እውነተኛ የኑሮ ተረክ ለዛሬዋ ምሥራቅ ጨው በረንዳና እነ “ፋጡማ መንሱር” (የውቅሮዋ ባልቴት) መሠረት እንደጣሉ ተረኳ ይመሰክራል።

ገጣሚዋ ከጁርዬዋ ብርሃኔ /ባዬ/ ምስር በስጋ በልታ፣ የውቅሮዋ ፋጡማ “ለሀዘንም ቢሆን ለደስታ የሚታረደው ከብት እኩል ይካፈላል፤ ግማሹ ላይ ክር ይታሰርና በአንድ ድስት ይሰራል፤ ወጡ ሲደርስና ሲጨለፍ ክር ያለበት ቅልጥም ከወጣ ክርስቲያኑ ይበላዋል…” እያለቻት ከፋጡማ ድስት የወጣን ቅልጥም ቆርጥማ፣ ዘነበች በተባለች የጋሽ ዘሪሁን “ጉዴ” አለንጋ በጥፋቷም፣ ሌላ ባልንጀራዋ ሲያጠፋ በዝምታ በማየቷም ተለጥልጣ (ተገርፋ)፣ “ወለዬዋ አታታይ” ከሀገር ቤት ስትመለስ የከሸነችውን በበርበሬ እና በዘይት የታሸ የጤፍና የስንዴ ቅይጥ ዳቦ ቆሎ በልታ ያደገች ናት።

“… ጨው በረንዳ ሀገሬ ነው። ይህ ማንነቴ በመንፈስም ሆነ በአካል እንዲጠረቃ ፋጡማ መንሱርን ከውቅሮ፣ ባዬን ከአባዶ፣ ወርቅውሃን ከወልዲያ፣ ጋሽ ዘሪሁንን ከሸዋ በጉርብትና ያመጣልኝ… ዕድለኛ ሴት ነኝ። በእነዚህ ሰዎች ምክንያት ኅብረት፣ እኩልነት፣ እኛነትን፣… ተምሬያለሁ፤ ማንም የሃይማኖቱንና የዘሩን ከፍታ የሰበከኝ የለም።… በየጊዜው የሚነሱ የዘርና የሃይማኖት ውዥንብሮችን በዘመኑ ቋንቋ “አይሰማም” ብዬ አልፋቸዋለሁ። ከእነኚህ፤ አስተሳሰቦች ወገን መቆም ከተሰራሁበት መሠረት አንድ ብልት እንደማጉደልና ውለታን እንደመካድ እቆጥረዋለሁ” ትለናለች።

ይህ አጭር ተረኳ እንደተደመደመ በቀጣዩ ገፅ (ገጽ 13) ባለ 4 መስመር ስንኞቿ ይህንኑ ተረኳን ይበልጡኑ ያቀልሙታል። “ጎረቤቶቼ” ትልና፡-

“በዘይነባ ምክር፣ በፋጤ ቸርነት፣ በባዬ ድንች ወጥ፣

በአይሻ ፈገግታ፣ በወርቅ ውሃ ቁጣ፣ በጋሽ ዘሪሁን ቁንጥጥ፣

እንዳልተገነባ፣ እኔ ያልኩት እኔ፣ ውለታ ሲረሳ፣

አንተ የማነህ ሲሉት፣ የአባቱን ስም ብቻ በኩራት አነሳ”

የገዛ ራሷን ትወቅስና “የእነ ፋጤ ልጅ ነኝ እንዴት አላልኩም?” ዐይነት ቁጭት ትቆጫለች።

ወደ ሌሎቹ ለዚህ ሐተታ የተመረጡ ግጥሞቿ እንዝለቅ። ምሥራቅ በሀገሯ ፍቅር አብዝታ የነሆለለች፣ በሴትነት ጉዳዮች ላይ በተለይ አፍቅሮ በመከዳት፣ ወዶ በመጠላት፣ እንዳይሆን እንዳይሆን ሆኖ በመለያየት፣ ከባህልና ከማንነት አንፃርም በዘመንና በትውልዳችን ተንጋዳጅነት ትኩሳታም ናት።

ሀገር ተኮር ግጥሞቿ በርከት ይላሉ፤ በዚህ መድበሏ ቀደም ሲል “አሻራ” በተሰኘው የግጥም “ቪሲዲዋ” ያቀበለችን ጥቂት ሀገርኛ ግጥሞቿን ያካተተች ቢሆንም አዳዲሶቹ ሀገር ተኮር ግጥሞቿ ህመሟ መቀጠሉን የሚያረዱን ናቸው።

ወጣት እንደመሆኗ ፍቅር ተኮር ግጥሞቿ ትኩስ ናቸው፤ በትኩስነታቸው ላይ በሰንካላ ፍቅር በመለየት የታሹ መሆናቸው ደግሞ የገጣሚነት ብቃቷ ታክሎበት ግጥሞቿ ይበልጡን ይመጥቃሉ። ለአብነት በገፅ 82 ላይ “ግርሽና ክትባት” የተሰኘውን አጭር ግጥሟን እንመልከት።

“ካንተ ጋር አውርቼ፣ እንደተቋረጠ፣

ፍቅረኛዬ መጥቶ፣ አበባና ሻማ፣ ከፊቴ አስቀመጠ፤

ምን ትላለህ አንተ? ብትሆን በኔ ቦታ፣

ሲፈራረቁብህ፣ ትናንት ከነገ፣ ተስፋ ከትዝታ።”

ቆርጠው የተውት እና ያከተመለት የትላንት ፍቅርና አፍቃሪ ከትዝታ ክርታስ እየወጣ ድቅን ባለበት ቅፅበት የዛሬው ፍቅርና አፍቃሪ ውዴታውን ሲገልጽ ሊጋጭ ይችላል።

ይህ የምሥራቅ ግጥም ከግጥምጥሞሽ ባሻገር የትላንቱ ማገርሸቱን እና የትላንት ትዝታ ባረበበበት ቅፅበት በተለምዶ አፍቃሪ ላፈቀራት አበባ በመስጠት ውዴታውን በሚገልፅበት የነገ ተስፋ መካከል ውርክቡን ገሃድ ያደርጋል። “ግርሻና ክትባት” እንዲህ አይደል?

ይህንን ሃሳብ እንደዋዛ በቀላሉ “ተጋጠሙብኝ” ብሎ መደምደም ይቻል ነበር። ገጣሚዋ ግን ከ“ተጋጠመብኝ” በላይ ትዝታ እና ተስፋን ነግራናለች፤ “ምን ትላለህ አንተ?” ብላ በጥያቄ ስትደመድመው ተጠያቂው ሁለት አካል ነው አንዱ የትላንቱ ወዳጅ (ደዋዩ) ሁለተኛው አንባቢው።

ይህንን ሁሉ ሃሳብ፣ ይህን ሁሉ እውቂያና መንታ ጥያቄ በ4 መስመር መከተቡ የምሥራቅ የገጣሚነት ምናብ እና ተሰጥኦ መጎልመሱን ይነግረናል። እንዳልኳችሁ ምሥራቅ ሴት ተኮር ነች። ደፈር እንበል ካልን ደግሞ “ፌሚኒስት” እንደሚባሉት ዐይነት፤ በጨው በረንዳ መድበሏ ሴትነትን በገጠገጠችባቸው ግጥሞቿ ያሉ ሴት ገፀ ባህርያት ታማሚያን፣ ተሰባሪ፣ እዬዬ ባይና ሙሾ አውራጅ ናቸው። “ያላየሁ እንዳይመስልህ፣ ገጽ 29” “ሁለት ሃሳብ፣ ገጽ 79” “ፎንቃ፣ ገጽ 22” እና “ትዝታ፣ ገጽ 35” የተሰኙ ግጥሞቿ ለአብነት ይጠቀሳሉ። 

በዚሁ መሰል ጭብጥ አንዲት እዬዬ ባይ እንስትን “ሮዝ የገላ ሳሙና” በሚል ርዕስ፣ ገፅ 105 ላይ እናገኛታለን።

አንዲት “ቁራጭ የገላ ሣሙና፣ የህይወቴ ናሙና” ነው የምትል፤ እንስቷ ገላዋን ልትታጠብ ሰልፍ (ተራ) ጠባቂ ሆና አካባቢዋን በመማተር ላይ እንዳለች ማታሪ ዐይኗ “የተነኳኰተች ቁራጭ የገላ ሳሙና” ላይ ያርፋል።

እናም “ . . . ይህቺ የገላ ሣሙና ስንቱን መዳፍ አዳፋ፣

            ገላዋን እየገበረች ሳትሰስት አኩረፍርፋ፣

            በሙቅ ስትለበለብ ደሞ አንዴ በቀዝቃዛ፣

            ከመዳፍ መዳፍ ስትዘል ስትቀባበል ነፋዛ፣

            አዳሜን ከእድፍ እንዳላነፃች ሞሽልቃ፣

አካሏ ተቆራርጦ ትታየኛለች ወድቃ” ትላታለች።

ታዲያ ይህችን የሟች ሮዝ የገላ ሣሙና ሰልፈኛው እያያት ያልፋል እንጂ አያነሳትም፤ ይልቅስ…

“አጠገቧ ያለውን፣ ወፍራም ሣሙና ጨምቆ፣

እያራገፈ አለፈ ፊቱን በውሃ ለቅልቆ”   

ደግሞ አንድ ጎረምሣ ውለታዋን ዘንግቶ፣ መክሳቷን ንቆ… ከጎኗ ያለችን ወፍራም ሣሙና መርጦ ሲያነሳ አስተውላ፣

“የዚህ ጎረምሣ እጆች

       ውለታዋን ዘንግተው የደለበውን ያነሱ፣

       ነገር ቢገባቸው ነው፣ ጊዜው መጉላት ነው ምሱ፣

       በእብለት መድመቅ ነው ሱሱ”

ትለዋለች።

እውነት አላት! ጊዜያችን የእብለት ሆኖ ምን ትላንት ከትላንት ወዲያ ውለታ ሰሪ ቢሆን ዛሬ ጎላ ያለ ይታያል እንጂ የኮሰመነ ተመልካችም አንሺም አያገኝም። ምሥራቅ ትቀጥላለች።

ጎላ ያለ የሸፈናቸው፣ ለመታየት ዐይን ያልሞሉ፣ በየስርቻው ትንንሾች መኖራቸው፣ እነዚህ ትንንሾች ደግሞ መንፈሳቸው ሳይሆን መጠናቸው ዕየታየ እንደሚተዉ ትነግረንና፣

“… ከክሱ ገላ ጀርባ ውበት እንዳለ ተቀብሮ፣

ከሟሟ ወዘና ኋላ ቅስም እንዳለ ተሰብሮ፣

ከጣመነ ጅስም ስር፣ ህልም ሳስቶ ደንብሮ፣

አንገቱን እንደደፋ መታየትን ገብሮ፣

በመድመቅ የታበተ፣ የዚህ ጎረምሳ ተፈጥሮ፣

ይህንን መስዋዕትነት አያሳየውም አሻግሮ”

በማለት “ጎረምሳው” እንዳልታየው እኛ የዛሬዎቹ በመድመቅ መታበታችንንና ከክሳት፣ ከስብራትና ከአንገት ተሰባሪ ስር ህልም እንዳለ ማየት የሚችል ተፈጥሮም እንደሌለን ልካችንን ትነግረናለች።

ገጽ 105 “አያሳየውም አሻግሮ” በሚለው ሀረግ ስለሚያልቅ ግጥሙ ያለቀ ቢመስለንም… ገና ነው “ህይወቴ ይህችን ቁራጭ የገላ ሣሙናን ይመስላል” ባይዋ ለገላ መታጠብ ወረፋ ጠባቂ እንስት ገጸ ባህርይ ይህ አልበቃ ብሏት፣

“ባለተራ እኔ፣ በዚህች ሳሙና ፊት፣ ራሴን አስቀምጬ

የኋሊት፣ የኋሊት፣ ፈርጥጬ፤”

በማለት በመታሸትና በመቆራረጧ ብዛት ሽታዋ ባልጠፋው የደቃቃዋ ሳሙና ጠረን ትዝታ ይመጣበትና፣

“በማይተነው ጠረን በማይጠፋው ሽታ፣

መጣብኝ… መጣብኝ… መጣብኝ ትዝታ፣

መጀመሪያ ጊዜ የሸተተኝ ቦታ፤”

እያለች “ትዝታን ማነው በድምጽ ሰፍሮና፣ በማየት ብቻ ያጠረ?” ብላ በመጠየቅ በጠረንና በሽታ ተንደርድራና ተሰፈንጥራ…

“ገላዬን ስታጥበኝ እኔ ሳለቀልቅ፣

ነገርህ ተጣባኝ ርቀህም እንዳይለቅ፣

ሄደህም እንዳይለቅ፣

እኔና ይህች ሣሙና እንመሳሰላለን፣

በደፈጠጡን እጆች ላይ አሻራ እንተዋለን፣

የታጠበባት ሁሉ ይኖራታል እንዳሸተተ፣

ሀቄም ይከተልሃል እጅህ ላይ እንዳሸተ››

ትለዋለች! የትላንት ገላ አጣቢ ፍቅሯን፤ እሷ ዱካውን እየተከተለች ያለመታከትም መፈለጓንና እርሱ የነካውና ያጠበው ገላዋም በማንም ሳይነካ እርሱ እንዳይኖረው መኖሩን አስረድታ ትተክዛለች… ግን ደግሞ ትዝታ ያረበበበት ትካዜዋ የደቂቃ እንኳን ዕድሜ አይኖረውም፤ አንዲት መንቃራ ትከሰትባታለች።

“ደግሞ አንዲት መንቃራ ከትዝታዬ አናጥባ፣

በጎረምሳው ትራፊ እጅ ባቷን አጣጥባ፣

ጨምቃ፣ ፍቃ፣ አሽታ፣ አልባ፣

እዛው በመደንዘዜ ከመታጠቢያው ስፍራ፣

ናቀችው አቋቋሜን አየችው ተኮሳትራ”

ብላ ትማረርና እልህ እያነቃት፣ ይችኑ በጎረምሳ እጅ ባቷን ያጠበችን እንስት፣

“አካሌ ፊት ለፊቷ ያለምክንያት ተገተረ?

እኔስ መቦረቂያ ጊዜዬስ አልነበረ?

እሷስ ቀን የጣለውን ገላ ከምታልፍ ገፈታትራ፣

ህይወቷን አታቀናውም ከእኔ ህይወት ተምራ”

እያለች ትሞግታታለች። መራር ነው! ይህቺ ቁራጭ ሣሙና መሳይ ደቃቃ እንስት ምን ጊዜዋ ቢሆን ታሽታ ታሽታ ሟሙታለች። እና ከፆታና ዘመን አቻዋ እኩል መቦረቅ አለመቻሏን ስትለፍፍ ታስተክዛለች፤ ሆድ ታባባለች። እወቂ! ባይም ናት። ከእኔ ህይወት ተምረሽ ህይወትሽን አቅኚ፣ ታሽቶ ታሽቶ መሳሳትና መድቀቅ፣ ከዚያም ለጥቆ አለመፈለግ ይመጣል ብላ ታስጠነቅቃለች። “እኔን ያየች ትቀጣ” ብላ ትለፍፋለች።

በጎረምሳ እጆች ታጥባና ተለቅልቃ የወጣች ባለጊዜዋ፣ (ወፍራም ሣሙናን ወካይ) አፍለኛ ሴት በወረፋ ጠባቂዋ ሟሚ እንስት…

“ዐይኗን ከመስተዋት ላይ ያልነቀለች ጉልቻ፣

ጥርስ፣ ፀጉር፣ ባት፣ አፍንጫ፣ ስጋ ብቻ”

ተብላ በጽኑ ትተቻለች። መች በትችት ብቻ ተወቻት?

“ደግሞ፣ ከእኔ እጥፍ ባየለ በረዘመ ትዝታ፣

በመገፍተር ሳትነቃ ከናፍቆቷ ጋር ተሰፍታ፣

የፋንታዋን ልትዘግን ምን አልባት እዚህ ቦታ፣

በምን እርግጠኛ ናት እንደማይቆም ሃውልቷ፣

የት አባቷ”

እያለች ከላይ “ቀድመሽ ንቂ! እንደኔ እንዳትሆኚ” ያለቻት አቻዋን “እንደኔ እንደማትሆኚና የእኔ እጣ ባንቺም እንደማይደርስ እርግጠኛ ነሽ?” ትላታለች፤ በዐይነ ህሊናዋ እንደርሷ እንደምትሟሟ ታያት መሰል!… “የታአባቷ” ብላ እሰይ አለች። እዛው ወረፋ እየጠበቀች… ለያኔው (የትላንት) ፍቅሯ… ገላዋን ያጥባት ለነበረው…

“አየህ…

ናፍቆትህ ገሽልጦብኝ የመቻሌን ከለላ፣

ዕየኝ ሲያነጫንጨኝ ከአካባቢዬ ስጣላ፣

ከምግብ ጋር ስጣላ፣ ከአየሩ ጋር ስጣላ፣

እየተከተለኝ ናፍቆትህ እንደጥላ፤

እልቤ ጎበኑ ላይ ስምህ ስለተከተበ፣

የሚያጨኝ ይመለሳል አንተን እያነበበ፣

ከመታጠቢያው ስፍራ በአንተ ሃሳብ ደንዝዤ

ዛሬዬን ትቼው መጣሁ ትናትናዬን ይዤ”

ራሮት፣ ቅጥለት ይህ ሁሉ እያለ ከልቧ ጎበን ላይ ስሙን ከመከተብ ያልቦዘነች፣ ይህንኑ ክትባት እያዩ ያጯት የተመለሱባት። ለገላ መታጠብ ተራ ጠባቂ የነበረች፣ ሕይወቷን በማንፀር በሟሟችና በሰለለች ቁራጭ የገላ ሣሙና ራሷን በመመሰል፣

“ቁራጭ የገላ ሳሙና

የህይወቴ ናሙና”

ብላ ስታበቃ ግጥሙም ያበቃል።

ግጥሙ አልቋል፣ እንስቷና ታሪኳ ግን ከህሊናችን አይጠፋም! ግጥሙን አንብቤ ቀጣይ ገፁን የመግለጥ አቅም አጥሮኝ ለደቂቃዎች ቦዘዝኩ። ክሷ ሳሙና ስለኮሰመነችበት (ለስንቱ አረፋ በመድፈቋ ምክንያት በመሟሟቷ) ከጎኗ ያለን ወፍራም ሳሙና መርጦ ያነሳ ጎረምሣ፣ በጎረምሳው ባቷን አሳጥባ የምትመናቀር “የኔ ጊዜ ነው” ባይ እንስት፣ ዕድሜዋ ሳይመሽባት በመታጠብ ብዛት የኮሰመነች፣ ገላ አጣቢዋ ምን ቢለያት ጠረኗ እንደማይለቀውና በሄደበት እንደሚከተለው ያመነችና ዛሬም እምነቷ ሳይጎድል ገላዋን በሌላ ሳታስነካ ከምግብና ከአየሩ የምታጣላ፣ ያጯት የሚመለሱ.. የኋላ ኋላ ግን ከዚህ የገላ መታጠብ ሰልፍ በሃሳብ ደንዝዛ ዛሬዋን ትታ፣ ትላንትናዋን ይዛ የምትወጣ መንፈሰ ግዙፍ ግን ደግሞ ገላ ኮስማና…! ከዚህች እንስት መለያየት፣ ራሮቷን መርሳት፣ እዬዬዋን አለመጋራት ይቻል ይሆን? እኔ አልተቻለኝም!

በመድበሉ ገጽ 113 ላይ “የዘመን ማዲያት” በሚል ርዕስ በምናነበው ግጥም የአንድ ቤተሰብ አባሎችን እናገኛለን፤ ዕድሜያቸው የመሸ ሴት አያትና ሁለት የዛሬ ወጣት እንስቶች በአንድ ጎጆ… በዘመን ሲወራከቡ፤ አያትየው ብርቱ ፀሎተኛ ናቸው።

“ሰርክ ወፎች ሲንጫጩ፣ ከድቅድቅ ሲፍታታ፤

መቋሚያዋን ተደግፋ ጋቢዋን አጣፍታ”

ትላቸዋለች አንደኛዋ የልጅ ልጃቸው። ይህቺኛይቱ ወጣት እንስት (የግጥሙ ላይ ተራኪ ነች) ዘመነኛ እህቷንና ሴት አያቷን ታዛቢ ናት፤ የእናቷን ፀሎተኛነት

      “ቆሞ ቆሞ ቆሞ… ዝንፍ አይልም ጉልበቷ፣

ለምኖ ለምኖ ለምኖ አይሸነፍም እምነቷ፣

ዘንቦ ዘንቦ ዘንቦ አያባራም ፀሎቷ፣

የጥበቃ ፅናቷ የተማፅኖዋ ስፍራ ልክ፣

ከእግሩ ስር አትነሳም ሀገሯን ሳታስባርክ፣

ኢትዮጵያን ሳታስባርክ”

በማለት ብርቱ አማኝነታቸውን (አማኝነታችንን) ትነግራለች፤ ታዲያ ከሰርክ ከማለዳው ፀሎታቸው በኋላ በጎጇቸው ረፈድ ሲል ንዝንዝና ንትርክ ይቀጥላል። ተነታራኪዎቹ አያቷ የዚያኛውን (የትላንት ወዲያውን) ዘመን፣ እህቷ ደግሞ የዚህኛውን (የዛሬውን) ዘመን ወክለው ነው።

“የዛኛው ዘመን ሥርዓት

የዛኛው ዘመን ወግ

የዛኛው ዘመን ታሪክ

አያቴን እየጎተተ ጉሮሮዋን እያነቀ፣

የዚኛው ዘመን ክፋት

የእህቴን አረማመድ

      ዱካዋን እያሳተ ማንነቷን እያስናቀ፣”

ታዲያ እነዚህ ሁለት ዘመናት “የሁለቱን ስጋ ለብሰው”፣ መንፈሳቸው ተነጣጥሎ ቢነካከሱም ደምና ስጋ ሆኖባቸው አብረው እንደሚኖሩ ታትታለች።

የዚህ ቤተሰብ አባሏ ወጣት (የክስተቱ ተራኪ) ሁለቱን ተነታራኪዎች (“አያቷንና እህቷን) የምትገልፅባቸው ስንኞች እማሬያቸው ደስ ይላል፤ ዘመናቸው መለያየቱን፣ እዛና እዚህ መቆማቸውን ከመንገሯም በላይ…

“አያቴ የማወቋ ጥልቀቱ ወገቧን አጎበጠ፣

እህቴ የማነሷ ጥልቀቱ ደረቷን አሳበጠ”

ተመልከቱ! ማወቅ ሲጠልቅ ወገብ ያጎብጣል፣ ማነስ ከጠለቀ ደግሞ ደረት ያሳብጣል። ለወትሮው ግን ማወቅ አልነበረም ደረት የሚያሳብጠው? ተራኪዋ ትቀጥላለች።

“ያለፈው ዘመን አሻራ፣

አረማመድ፣ አለባበስ፣ አነጋገር፣ አመጋገብ፣

                                    አቀማመጥ እያለ፣

ባያቴ ሥጋና መንፈስ፣ ላይበቅል በቀለ፣

ይኸው በስተርጅናዋ፣ ሞገሷ እንዳበራ ፀጋዋ እንደጠለለ፣

የእህቴ ዘመን መምታታት ቃርሚያው ሥላልተገታ፣

እግሯ ሺውን ይረግጣል በመሰተሩ ፈንታ፣

ይኸው ግንባሯ ላይ ዝብርቅርቅ ያለ ካርታ፣”

ተራኪዋ እንስት ወጣትነቷ እየበሰለ ያለ እንጂ ከ30ዎቹ ያልራቀች የእርጅና ጉዞም ያልጀመረች መሆኗን የግጥሙ አውድ ያሳብቃል። እናም ይህ የታናሽ እህቷ ጉደኛ ዘመን የእርሷም ዘመን ነው፤ ግና ታዲያ የአያቷንና የታናሽ እህቷን ልዩነት በጥልቀት ተመልክቶ ለመታዘብ የዕይታ ጥሩር የተቸራት ናት።

የሁለቱን /የአያትና የእህቷን/ ልዩነት በመግለጫ አስደግፋ በዝርዝር ከነገረችን በኋላ፣ አያቷን “ፍፁም ኢትዮጵያዊት”፣ እህቷን “ያልለየለት ፍፁም ምንም “አዊት” ብላ በፍፁምነት በተለበጠ ሁለት መደብ ትከፍላቸዋለች።

እንግዲህ ተመልከቱ! እየጃጀ ያለ ባልቴትነት፣ በሽበት ልክ ከደለበ ህይወታዊ የሀበሻ ኑሮ ተሞክሮ ጋር ተደምሮ ፈጣሪን በፅኑ የሚማፀነው ፍፁም የሆነ “ኢትዮጵያዊ”ነት፤ ለጋነት ከሚያካልበው፣ ይረግጠውን ከማያውቅና ከሚጠፋው ለያውም ደግሞ ካለየለት “ፍፁም ምንም አዊነት” ጋር ምን ደማዊ ዝምድና ቢኖረው በአንድ ቤት የማንነት ፍልሚያ ይገጥማል። ፍፁም ኢትዮጵያዊቷ ሴት አያት የዘወትር ፀሎታቸው ቅጥ አጥነት፣ ያልየለየት ፍፁም ምናምናዊነት ከልጃቸው ላይ “ጦስ ጥንቡሳሱ ተነቅሎ እንጦሮጦስ እንዲጠልቅ ነው።

ዘወትር ፈጣሪን ይለምናሉ፣ በስሟ /በልጃቸው/ ስም ስለት ተስለው ዝክር ይዘክራሉ፣ በዝክር ብቻ መቼ አቆሙ በ”መሪጌታ አንዳርጌ” አማካኝነት በቅባው አስደባብሰው ቡራኬን ሲጠባበቁ፣

“በቅባው ልታስዳብሳት፣ ስትጠባበቅ ቡራኬ

አጅሪት ቀለል አድርጋ “ኢትስ ኦኬ”

መሪ ጌታ አንዳርጌ ቅኔ እየመሰጠሩ፣

ዜማ እየደረደሩ፣ ትውፊት እየነገሩ፣

ያቀኑት ያያቴን ልብ በምን ይግባው ነገሩ”….

አያቲቱ “ምንድን ነው ይሄ “ሶኬ”?

ብለው ጥያቄ ቀጥለዋልና ተራኪዋ ዐይኖቿን በሁለቱ /በአያትና በታናሽ እህቷ/ ዘመን ላይ እያንከባለለች ከንፈሯ የሞት ሞቱን “እ… ምንም አይደል፣ ይሁና” እንደሚባለው ዐይነት” ብሎ ያቀብላል፤ ያን ጊዜ…

“…

የአያቴ ድምጽ ከረረ… በሰማው ፍቺ ቅልት፣

አይሄሄሄ…

ከጣራ በላይ ማውካካት ምንም አይደል?

በሁለት ጉንጭ ማላመጥ ምንም አይደል?

እንጀራ በላስቲክ አሽጎ፣ ቁሌት

                  ከኪዮስክ ማንጠልጠል፣

ምንም አይደል?

ለመማር ብላ ሄዳ፣ ዜግነቷን ለውጣ አበሻነቷን ቀይራ

(ሌላ ጉድ እየነገሩን ነው ማለት ነው)

ይኸው የልጇ ቆዳ፣ የጠጉሩ ቀለም ነጣ፣

ማንነቱ ፈዘዘ ኢትዮጵያዊነቱ ገረጣ…”

ይህቺ ዘመነኛዋ ታናሽ እንደወትሮዋ ሁሉ “ወግና ታሪክ” በተነገረ ጊዜ መወራጨት ትጀምራለች። ተከላቢነቷ እያየለባት ሃሳብ ማስጨረስ አይሆንላትም እና፣

“…በቃ! ነገር አታካብጂ

አታድርጊው ኩነኔ

አባቱ ምንም ቢነጣ “ኢትዮፕያዊ” ነኝ እኔ”

ብላ ትጮሃለች። የተራኪዋ ታናሸ እህት እንደ ተራኪዋ አመዳደብ “የለየላት ፍፁም ምንም አዊት” ከመሆን በላቀ በትምህርት ሰበብ ባህር ተሻግራ ነበርና የገዛ የራስ ማንነቷን ከመጣሏም በላይ ከነጭ (ከሌላ ሀገር ዜጋ) በተለምዷዊ አጠራራችን “ክልስ” ወልዳለች። ይህ እውነት በአያትየዋ ሲገለፅ ከራስ ባህል፣ ወግና ትውፊት መፋታቷንና መነጠሏን ይበልጡኑ ያቀልመዋል።

የሁለት ዘመን ውርክቡ ይበልጡን ይጦዛል። የታናሽየዋ “እኔ ኢትዮፕያዊ ነኝ” ማለት በሴት አያቷ ዘንድ ሌላ ጥያቄን ይጋብዛል፤ አያቲቷ

“ጦቢያ ማለቷ ነው?”

“ኢትዮጵያ ማለቷ ነው?”

ብለው ያፈጥጣሉ። ዘመነኛዋ አጅሪት ግን ምን ገዷት።

“…

ጥርስ፣ ምላሽ፣ ላንቃዋን፣ ባንድ ላይ እያጣበቀች፣

ከዛ ከምላሷ ስር፣ የምታወጣት ድምፅ አለች

እ…ም… ጥ…ቅ…”

ይህ አመላለሷ ሁለቱን ዘመን ስታስተውል የነበረችው ተራኪያችንን (ታላቅዬዋን ያስቆጣል)።

“…

ያያቴ ዝንጉርጉር አንገት፣ እቶን ንዳዱን ተፋ፣

አጓራች አንዘፈዘፋት ያገሯ ስሟ ጠፋ፣

“ኢትዮፕያ፣ ኢትዮፕያ”

ዘራፍ አልኩኝ ሳላውቀው ቀፎው እንደተነካ፣

ምላሴ ተቆለፈ ትናጋዬ ላይ ተሰካ፣

ቁርጥራጭ፣ ሽርፍራፊ ብናኝ አለብኝ ለካ?”

የታላቅየዋ “ዘራፍ” ማለት፣ ምላስን አቆላልፎ ትናጋ ላይ እስከመሰካት የደረሰን እልህ ያየ የሴት አያት መንፈስ ደግሞ አረፍ ይላል።

“…ዘጭ አለ ምድርን ነካ፣

ተማምኖ በፍላቴ አንድ ዘር እንደተካ”

ትለናለች፤ በሁለት ዘመን ውርክብ የተካረረው ጉዳይ አሁን ታላቅየዋን በፍላት ቀላቅሏል።

“የሦስትዮሽ ትንቅንቅ በጎጃው እንዳረገደ፣

ዳኛ፣ መልስ ሊሆነን፣ ፊደላችን ወረደ፣

እሰይ….

ጰ – ግእዙ የፊደል ዘር፣

ጱ – የጰ ካዕቡ፣

ጲ – ጲላጦስ እጀ ንፁ፣

ጳ – ጳጳስ የኤጲስ ቆጶስ በላጭ ገፁ፣

ጴ – ሀምሷ ባላምባሯ፣

ጵ – ሳብዕ አጭር እግሩ፣

ጶ – ጷግሜ ድምፁ የጰፍንፅቅ ዘሩ፣

“ጰ”ን በ“ፐ” ከምታቀያይሪ፣

እስኪ “ፐ” ያለችበት መጤ ያልሆነ ስም ጥሪ?”

ፊደልን እማኝ ያረገ የታላቅየው ጥያቄ የታናሺቷን ምላሽ ሳይጠብቅ ራሱ ምላሽ ይሰጣል።

በተራኪዋ አንደበት፣ በሀገርኛው ፊደላችን ምስክርነትና ዳኝነት በታናሽዬዋ ቅንጡ ልሳን “ኢትዮጵያን” “ኢትዮፕያ” በማለቷ በ“ጵ” እና በ“ፕ” መነሻነት ልክ መንገር እንግዲህ እንዲህ ነው።

የ“ዘመን ማዲያት”ን የምተርክልህ “ታላቅ እህት ነኝ” ባይዋ ራሷ ምሥራቅ ናትና በጎጇቸው ያረበበን የሦስትዮሽ ትንቅንቅ በፊደል ዳኝነት ካበረደች በኋላም፣ የአያቷ መንፈስ አረፍ ቢልም የእርሷ ትካዜ፣ ቁዘማና ፅሞናዋ ግን አያርፍም…!

የእድሜ ካስማቸው እያዘመመ ያለን ሴት አያቷንና እኩዮቻቸውን በዐይነ ህሊናዋ (በልበ ልቦናዋም ጭምር) ላይ በተርታ ታሰልፍና በዚህ ባህልና ወግ በነጠፈበት፣ ምንምነት አይሎበት ግድም ተንጋዳጅ ትውልድ በበረከተበት ዘመን አያቷን በህይወት በማቆየቱ

“አያቴ እኩዮቿ፡-

ይህን፣ ራስን የማውለቅ ትግል፣ ቆዳን የመላጥ አባዜ፣

ከንስር ከፍታ አውርዶ፣ ልምጥምጥ የውሻ ሚዜ፣

መሆንን ሳያዩ አልፈው መቃብራቸው እንዳጌጠ፣

ለምን – ያገር ቆነጃጅት ሚስጢር በልቧ ላይ ገለጠ?

ለምን – ልፋቷ እያየችው መዳፏ ላይ ቀለጠ?

ለምን ያየችው መዓት ሳያንስ፣ ተጨማሪ ዕድሜ ሰጠ?”

ብላ ለአያቷ ዕድሜ ቸሮ ያቆየ ፈጣሪን ትጠይቃለች።

ምሬትና ጥያቄዋ (ምሬቱ ፅንፍ አልባነው!) የገዛ የራስን አያት የእናትን እናት ትልቋ እማማን! “ይህንን ሁሉ መዓት ከምታይ ምናለ እንደ እኩዮቿ መቃብሯ አላጌጠም? ብሎ መጠየቅ አይከብድ ይሆን?

ለወትሮው ተማራሪና አዛኝ በራሱ አንደበት “ምነው ይህንን ከማይ ሞቼ ባረፍኩት!” ማለቱ የተለመደ ነው።

እንዲህ እንደተራኪዋ ግን “ይህንን ከምታይ ሞታ ባረፈችው!” ባይነት ግን አልተለመደም! ሹለቱ ከባድ ነው። ታዲያ ተራኪዋ ይህ ተማራሪነቷ ከባህልና ወግ ንጥፈት የመነጨ ነውና ግጥሟን /ተረኳን/ የምትደመድመው እንደዋዛ ከእኛነታችን እየተፋቱና፣ እየራቁ፣ የጠፉብን ነባር ሀገራዊ ይትበሃሎችና እሴቶች አማሩኝ ብላ ኡኡታዋን በማሰማት ነው። የገዛ አያቷ ትውፊታዊ ተግሳፅና ምክር የሚሰጡበት ድምፃቸው ነው። (አምሮቷን መርጬ /ቀንሼ/ ባቀርበው ሙሉ ስሜቱን አትጋሩኝ ይሆናል በሚል ስጋት እንደወረደ እነሆ)

“…

እኔ ግን ድምጿ አማረኝ፣

ትናንት አማረኝ፣

  • የክብራችን ባንዲራ ከዘንጉ ጫፍ እስኪደርስ፣

በቆማችሁበት ፅኑ እግራችሁ አይላወስ፣

አማረኝ

  • ቀድመሽ ደጅ ሳትወጪ ቡሃቃውን አትንኪ፣

ሰላቢው እንዲታሰር በስመአብ ብለሽ ባርኪ፣

አማረኝ

  • ወተቱን ስታመጪ ሽፍን፣ ጅቡን አድርጊ፣

ዐይን የገባ ክፉ ነው ደሃውን አታጓጊ፣

አማረኝ

  • በሌሊት የተደፋ እንሶስላ እንዳትረግጡ፣

ለስራዩ ማርከሻ የፌጦ ፍትፍት አላምጡ፣

አማረኝ

ተግባሩ ካገር ሲሰደድ ቃሉም የተሰደደ፣

ጫፍ ጭራውን ላይዘው ልቤ አምሮትን ወለደ፣

ጥሎሽ አማረኝ…

የምሥራች አማረኝ…

ብር አምባር አማረኝኝኝ እእ…

ውይ… አያቴ ታሳዝናለች…!!!

            2007 ዓ.ም

እናንተዬ… ጥሎሽና ብር አምባር፣ ባንዲራ ሲወጣና ሲወርድ ቆሞ በክብር ቆሞ እግርን አለማላወስ… አላማራችሁም? ውይ…! ምሥራቅ ታሳዝናለች!

መደምደሚያ

የምሥራቅ ተረፈ “ጨው በረንዳ” ጭው! ያረገኝ እንግዲህ እንዲህ ነው፤ ያው እንደምታውቁት ምሥራቅ ወጣት ነች የግጥም መድበሏ ግን ከአረጋዊ ዕድሜ በላይ በሳልና የጃጀ ነው፤ ሀገር ሀገር፣ ባህል ባህል፣ ወግ ወግ፣ ትውፊት ትውፊት፣ ትውልድ ትውልድ ይሸታል።

ምስሩ… እባክሽ ደግመሽ ደግመሽ ፃፊ!? እናንተም ሙሉ መድበሏን አፈላልጋችሁ አንብቡ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top