ፍልስፍና

“አብሮ መብላት ወንዝ ያሻግራል” (የጓደኝነት ውል)

 መክፈቻ

 ዛሬ ስለ ጓደኝነት እንነጋገራለን። የጓደኝነት (Friendship) ጉዳይ ፈላስፎችን፣ የማኅበራዊ ጥናት ባለሙያዎችን (Sociologist)፣ የሥነ ልቡና ባለሙያዎችን የሚያነጋግር እና በሥነ ጽሑፍ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው ጉዳይ ነው። ጓደኝነት ምንድን ነው? ጓደኝነት ዓላማው ምንድን ነው? የጥሩ ጓደኝነት መገለጫዎች ምን ምን ናቸው? ለዛሬ ከፈላስፎቹ ሙግት፣ ከአበው ተረቶች፣ እንዲሁም ከጠቢባን ጽሑፍ ውስጥ ስለ ጓደኝነት የተነገሩትን እያነሳን ትንሽ እንነጋገራለን። መልካም ጓደኝነት ማኅበራዊ መስተጋብርን የማቅናት፣ ፖለቲካዊ ሰላምን የመፍጠር አቅም እና ኃይል አለው። ዝቅ ሲል በግለሰቦቹ ቤተሰቦች መካከል ትሥስርን በማምጣት፤ ከፍ ሲል ደግሞ በመንግሥታት መካከል (በDiplomacy መልክ) መተባበርን፣ በዜጎቻቸው መካከል መዋሃድን የሚያመጣ የትስስር ሰንሰለት ነው እና ለዚህ ጽሑፍ መነሻ ሆኗል። በርግጥም በጣም የሚዋደዱ ናቸው በምንላቸው ጓደኛሞች መካከል የሚደረግ “ያልተጠበቀ” መለያየት እና ጥል የሚያስደነግጠንን ያክል በጓደኝነት ምክንያት የሚከፈል መሥዋዕትም ያስገርመናል፣ ያስደንቀናል። በመሆኑም የጓደኝነት ውሉ (ቅጡ እና ቅርጹ)፣ ምሥጢሩ ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም። ርእሱ ላይ በጥቅስ የተቀመጠው ሐረግ ከአበው/እመው አባባል የተወሰደ ሲሆን መጨረሻ ላይ ትንሽ ማብራሪያ ተደርጎበታል።

ጓደኛ (ጓዳኛ?)

የአማርኛ መዝገበ ቃላት ጓደኛ የሚለው ቃል ባልንጀራ፣ አብሮ አደግ፣ ወዳጅ የሚል ፍች ይሰጡታል። አብሮ አደግ የሚለው አገላለጽ በቦታ ተራርቀው ያደጉ፣ በአንድ አጋጣሚ ተገናኝተው ወዳጅነት የመሰረቱትን ስለማያካትት ጓደኝነትን በምልዓት አይገልጠውም። የቃሉ ሥርወ ቃላዊ ፍች (Etymological Definition) ምን እንደሆን ባይታወቅም ጓደኛ የሚለው ቃል ጓዳኛ (የውስጥ የሚያውቅ፣ ጓዳን የሚያውቅ፣ ምሥጢር ተካፋይ) የሚል ትርጓሜ ሊሰጠው ይችላል። ባልንጀራ የሚለው ቃልም አብሮ መብላት የሚል መሠረት ያለው ይመስላል። ወዳጅ፣ ምሥጢር ተካፋይ፣ የደስታ እና የሐዘን ተጋሪ የሚሉት ገለጻዎች የጓደኝነት ማገለጫዎች ናቸው። የቃሉን ትርጓሜ፣ መሠረቱን ለቋንቋ ባለሙያዎች እንተውላቸው እና ነገረ ጓደኝነትን የሚመለከቱ ጉዳዮችን እየጠቃቀስን እንነጋገር።  

ከዚህ ቀጥላ የምናያት ተረት የተለያየ አተራረክ ይኖራታል። የተረቷ ዋና ሐሳብ በአጭሩ እንዲህ ቀርቧል።

አንድ በዕድሜ የገፉ ሽማግሌ ሁለት ልጆች ነበሯቸው። ከእለታት በአንዱ ቀን ሁለቱንም ጠሩና “ልጆቼ እንግዲህ እኔ ዕድሜዬ እየገፋ ነው። ለወደፊት መኖሪያ ይሆናችሁ ዘንድ በየቦታው ቤትን ሥሩ” የሚል ምክር ይለግሳሉ። ሁለቱም በገባቸው ልክ የአባታቸውን ምክር ለመፈጸም ይተጋሉ። አንደኛው ልጅ በየተራራው፣ በየጎራው እንጨት እየቆረጠ፣ ድንጋይ እየፈለጠ በብዙ ድካም ‘የሚያማምሩ’ ቤቶችን ሠራ።

ሁለተኛው ልጅ የአባቱን ምክር በማሰላሰል የራሱን ትርጉም ይሰጠው እና “መቼም አባቴ በየቦታው ቤት እንድሠራ የመከረኝ በየተራራው ባዶ ቤት እንዳቆም መሆን የለበትም” በሚል የብልህ ሐሳብ በየሚሄድበት ቦታ ሁሉ መልካም ጓደኞችን እየተዋወቀ፤ ያለውን ተካፍሎ በመብላት፤ በመመካከር እና በመረዳዳት ማኅበራዊ ግንኙነቱን እያሰፋ ጥሩ ጥሩ ወዳጆችን አፈራ። በየተራራው የእንጨት ጎጆ መቀለስ፣ የድንጋይ ካብ መደርደር ጉልበትን ከማድከም፣ ልብን ከማፍሰስ የዘለለ ረብ ያለው ነገር አይደለም። በየቦታው የሚገኙ ወዳጆቹ ልብ የማይናወጥ የጓደኝነትን ቤት መገንባት ግን ዘመን የማይሽረው ቤት እንደሆነ ተረዳ። እከሌ ዘመዴ፣ እከሌ የወንዜ ልጅ፣ የሰፈሬ ልጅ፣ የብሔሬ አባል፣ የሃይማኖቴ ተከታይ ሳይል አጋጣሚው የፈጠረውን ግንኙነት ወደ ጓደኝነት መንበር ከፍ እያደረገ ወንዝ ተሻጋሪ የግንኙነት ሰንሰለትን ፈጠረ።

ሽማግሌው የሁለቱንም አካሔድ ሳይደግፉም ሳይቃወሙም ሲከታተሉ ቆይተው ከጊዜ በኋላ ድጋሜ ልጆቻቸውን ጠርተው “ልጆቼ የሠራችሁትን ቤት አሳዩኝ፣ ልመርቅላችሁ” ይሏቸዋል።

ሁለቱም በጉጉት የሠሩትን ቤት አባታቸውን ማስጎብኘት ጀመሩ። የመጀመሪያው ልጅ የሠራቸውን ቤቶች ለማስመረቅ አባቱን ተራራ ለተራራ፣ ሸለቆ ለሸለቆ ሲያንከራትታቸው ውሎ፣ በውሃ ጥም እና በርሃብ፣ በድካም ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ሁለተኛው ልጅ በተራው አባቱን ከጓደኞቹ ጋር አስተዋወቃቸው። የልጃቸው ወዳጆችም “የውድ ጓደኛችን አባት” እያሉ በየሔዱበት ሁሉ በታላቅ ክብር እየተስተናገዱ፤ መብል መጠጡ፣ ማረፊያ ቦታው እየተሰጣቸው ከመሸባቸው እያደሩ ሰነበቱ። ሊሄዱ በተነሱ ጊዜም ከእኛ ጋር ትንሽ ይሰንብቱ እየተባሉ በምቾት ሰነበቱ። የልጃቸውን ወዳጆች እየመረቁ እያመሰገኑ ወደ ቤታቸው በተመለሱ ጊዜም በልጃቸው ታላላቅ ቤቶች መሥራት ደስ ብሏቸው በትፍስህት ልጃቸውን መረቁት። ያኛው ልጅም ይማርበት ዘንድ የዚህኛው ልጅ ተግባር ምሳሌ ሆነ። “ተረቴን መልሱ” እንዲሉ የተረት አባቶች ተረቷ ስለ ጓደኝነት ጥቅም እንጅ ስለ ጓደኝነት ምንነት ያልመለሰችው ነገር አለ።

ጓደኝነት ምንድን ነው? ዓላማውስ ምንድን ነው? የጓደኝነት መገለጫ መስፈርቶች ምንድን  ናቸው? የሚሉ ዓበይት ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችል አይደለም። በርግጥ የተረቱ አንኳር ሐሳብ የሰው ልጅ ከሌሎች ሰዎች ጋር በመልካም ተግባቦት ቢኖር፣ ፍቅር ቢመሰርት ለማኅበራዊ ሕይወቱ የተገባ እንደሆነ ማሳየት ነው። አባቶች ልጆቻቸው ከሰዎች ጋር በፍቅር ይኖሩ ዘንድ፤ በየሔዱበት ቦታ ቢመሽባቸው የሚያድሩበት፣ ቢደክማቸው የሚያርፉበት፣ ቢጠማቸው የሚጠጡበት፣ ቢርባቸው የሚበሉበት፣ ጸሐይ ቢሞቅ፣ ዝናብ ቢዘንብ የሚጠለሉበት ቤት-ወዳጅ ይኖራቸው ዘንድ ልጆቻቸውን ከሚመክሩባት ኢ-መደበኛ ትምህርት እርስ የተወሰደች ናት። ወንዝ የሚያሻግር ወዳጅ እንዲኖራቸው፣ በማያውቁት አገር መንገድ ጠቋሚ ወዳጅ እንዲያበጁ የተሰነዘረች የአርቆ አሳቢ አባት/እናት ምክር ናት።  

ጓደኝነት፣ ዓላማው እና መገለጫው

የጓደኝነት ነገር ታላላቅ የጥንት የግሪክ ፈላስፎችን ያነጋገር እንደነበር አፍላጦን (Plato) አንድ ውይይት (Dialogue) ሙሉ ሰጥቶ ጽፎበታል። እንደሚታወቀው የአፍላጦን ጽሑፎች በአንድ ርእሰ ጉዳይ ዙሪያ ክርክር ወይም ውይይት በመፍጠር ስለዚያ ጉዳይ የተወያዮችን ሐሳብ ማዳመጥ ነው። ታዋቂው ፈላስፋ፣ ሶቅራጥስ፣ የጽሑፎቹ ዋና ገጻ በሕርይ ሲሆን በአዋላጅ ነርስ መንገድ በተጠየቃዊ ሙግት (Elenchus) ተወያዮችን ሐሳብ እንዲያቀርቡ በማድረግ ምክንያታዊ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ጥረት ይደረጋል። ለምሳሌ The Republic ስለ ሀገረ-መንግሥት፣ ስለ ፍትህ፣ ስለ ጥበብ፣ ስለ ትምህርት ያተተበት ዘመን ተሻጋሪ ሥራው ነው። Phaedo ስለ ነፍስ ኢ-መዋቲነት፣ ስለ ሞት ስለ ሕይወት፤ Symposium ስለ ፍቅር፤ Apology ራሱን ከግሪክ ከሳሾች የተከላከለበት፤ Crito ከእስር ቤት በተንኮል ማምለጥ ተገቢ ስላለመሆኑ የሞገተባቸው እውቅ ሥራዎች ናቸው። ስለ ጓደኝነት ደግሞ Lysis በተባለው ጽሑፍ ውስጥ በደንብ ያብራራል።  

Lysis ላይ ሶቅራጥስ ከተወያዮቹ ጋር በሚነጋገርበት ወቅት ትልቁ ጥያቄ ጓደኝነት ምንድን ነው? ሁለት ሰዎች ጓደኛሞች ናቸው ስንል ምን ማለታችን ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን እያነሱ መላምቶችን እየመረመሩ የሚወያዩበት ጽሑፍ ነው። ከተነሱት ሐሳቦች ውስጥ ለምሳሌ ጓደኝነት በአለው እና በሌለው መካከል የሚደረግ ሽርክና ነው። የሚል ይገኝበታል። ለምሳሌ በበሽተኛ እና በሃኪም መካከል የሚደረግ ወዳጅነት በሽተኛው ሕክምናን ከመሻቱ የመነጨ ነው ይላል። ይህን ውድቅ ሲያደርገው ሐኪሙ ከበሽተኛው ምን ሊያገኝበት ይችላል? የሚል ማፍረሻ ያስነሳል። እንዲሁም “ጓደኝነት በተመሳሳዮች መካከል የሚደረግ አብሮነት ነው” የሚለው መላ ምት ውድቅ የሚደረገው አንዱ ያለውን ነገር ከተመሳሳዩ ጋር ስለሚኖር ለጉድኝት ምክንያት መሆን አይችልም የሚል ማጣጣያ ያስነሳል። በዚያውም መጥፎ ከመጥፎ ጋር መወዳጀቱ ምን ለማግኘት ነው? የሚል ጥያቄ መመለስ አይችልም። በርግጥ ፕሌቶ እንደ ሌሎች ሥራዎቹ ሁሉ በዚህ ሥራውም ለተነሳው ዓብዪ ጥያቄ መልስ የሚሰጥ አዋቂ፣ የመጨረሻውን ብያኔ የሚያስቀምጥ ዳኛ ሳያስተዋውቀን፣ ጓደኝነት ይህ ነው የሚል ስምምነት ላይ ሳይደረስ ነው የቋጨው።

ነገር ግን ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ተነስተዋል። አንደኛው ጓደኝነት በቁሳዊ ነገሮች ላይ የተመሠረተ እንዳልሆነ የሚያመላክተው የሶቅራጥስ ሐተታ ነው። ተወያዮቹን ጓደኛሞች ከሁለታችሁ የተከበረው ማን ነው? ፍትሐዊዉስ ማን ነው። እያለ ከጠየቀ በኋላ የጥያቄዎቹ መቋጫ ላይ “መቼም ‘ከሁለታችሁ ሀብታሙ ማን ነው?’ ብዬ መጠየቅ የለብኝም። እንደዚህ ዓይነቱ በሀብት መበላለጥ በጓደኛሞች መካከል ይኖራል ብዬ ስለማላስብ ነው” የሚል ቁም ነገር ይነግረናል። ጓደኝነት ከጊዜያዊ የሃብትና ንብረት ፉክክር፣ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ራስ ወዳድነት ነጻ የሆነ አብሮነት እንደሆነ ሲጠቁመን ነው።

ሁለተኛው እና ስለ ጓደኝነት የተሻለ ግንዛቤ የሚሰጠን ጓደኝነት ይህ ነው ለሚባል ዓላማ፣ የታሰበለት የእንካ አምጣ (Give and Take) ሽርክና ሳይሆን እርስ በርሳቸው የሚናበቡ ነፍሶች ውህደት (Congenial Rentionship) ነው የሚል ትርጓሜን ይሰጠናል። እዚህ ላይ ነው የጓደኝነት ውሉ የሚፈታው። የሁለት ነፍሶች መዋሃድ፣ በተፈጥሯቸው የሚፈላለጉ አካላት መገጣጠም መልካም ጓደኝነት ይወጣዋል እንደማለት ነው።

ሁለት ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ደራስያንን እናንሳና ስለጓደኝነት ግብዓት የሚሆነንን ነገር እንፈትሽ። የመጀመሪያው ዳኛቸው ወርቁ ነው። “አደፍርስ” በተባለው ድርሰቱ ውስጥ ከሚያነሳቸው ጉዳዮች ውስጥ የሴት እና የወንድ ጓደኛ (የባልና ሚስት ትስስር) መረጣ ላይ የሚያጠነጥነው ክፍል ይገኛል። አንድ ወንድ ወይም ሴት የትዳር ጓደኛውን የሚመርጥበት መስፈርት ልቡሰ ጥላው ባመላከተው የበጎና የመጥፎ መመዘኛ መስፈርት ይመሠረታል ይለናል ዳኛቸው። ሰው ከልጅነቱ ጀምሮ እስከ እውቀት ድረስ በማኅበረሰቡ፣ በባህሉ፣ በሃይማኖቱ፣ በየዕለት ተዕለት መስተጋብሩ ወይም ከተፈጥሮ የሚማራቸው ቅቡል እና ነውር ነገሮችን የሚለይበት መነጽር፣ ሥነ ልቡናዊ መሰረቱ ልቡሰ ጥላው ነው። በዚህ የልቡሰ ጥላው መመዘኛ መሠረት ሚስቱን ይመርጣል ወይም ሴት ባሏን ትመርጣለች። ትዳራቸው የሚጸናው ወይም በፍች የሚጠናቀቀው በዚሁ በልቡሰ ጥላቸው የመቀበል ወይም የማውገዝ ብያኔ ነው። ይህንን ነው ሶቅራጥስ በተፈጥሮ የሚናበቡ ነፍሶች ጥሩ ጓደኝነት ይወጣቸዋል የሚለን። ሁለት በጓደኝነት የሚዘልቁ ጥምርታዎች የእያንዳንዳቸው ልቡሰ ጥላ ባመላከታቸው የይሁን አይሁን መናበብ መሠረት መሆኑ ነው። “የአገሬ ሰዎች ኮከባቸው ገጥሟል”፣ “እህል ውሃቸው ረጅም ነው”፣ ሲል ዕውቅና የሚሰጠው እንዲህ ዓይነቱን የነፍሶች መናበብ ነው።

ሁለተኛው ጠቢብ ስብሐት ገብረ እብዚአብሔር ነው። “እነሆ ጀግና” በተሰኘ የታላላቅ ሰዎችን ጀብዱ ባተተበት መጽሐፉ የጓደኝነትን ምስጢር ለሚፈትሹ ሰዎች አንድ ጋት የሚያራምድ ትዝብት ማግኘት ይቻላል። ስለ አጼ ቴዎድሮስ በጻፈው መጣጥፍ የንጉሡን እና የዮሃንስ ቤልን (John Bell) ጓደኝነት ያሰፈራት ነገር የጓደኝነትን ውል ለመረዳት ጠቃሚ ናት። እንደሚታወቀው ሊቀ መኳስ ዮሃንስ የንጉሡ የቅርብ አማካሪ ነበር። ሊቀ መኳስ ማለት የንጉሡን አለባበስ ለብሶ፣ በንጉሡ መንበር በቅርብ የሚቀመጥ፣ ንጉሡን በመምሰል ንጉሡን ለመግደል የሚመጣ ሰው እርሱን እንዲገድል የንጉሡ ቤዛ ሆኖ የሚያገለግል የንጉሡ የቅርብ ሰው ነው። እንደ ስብሐት ሐተታ የሊቀ መኳስ አሟሟትም ይህንኑ ያረጋግጣል። ከልጅ ጋረድ ጋር በተደረገ ጦርነት ለንጉሡ በተተኮሰች ጥይት ንጉሱን ለማዳን ራሱን አሳልፎ በመስጠቱ ተገድሏል። ስለዚህ ጉዳይ ስብሐት ሲጽፍ የሁለቱ ግንኙነት የሚያሳየን ጓደኝነት ፍቅር የወንዜ፣ የአገሬ ልጅ፣ የቋንቋዬ ተናጋሪ የሚል ድንበርን የሚሻገር የሁለት ነፍሶች መናበብ ነው። አንዱ ራሱን ስለሌላው አሳልፎ ለመስጠት እንደዚህ ዓይነት ጓደኝነትን ይጠይቃል ይለናል ስብሐት። የፍቅርን ምስጢር፣ የጋደኝነትን ውል ታሳየን ዘንድ ያችን የስብሐት  የአድናቆት ማስታወሻ ደግመን አስታወስናት።

ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ የአክሱም እና የእንፍራንዝ ሰው ዘርዓ ያዕቆብ ስለ ፍቅር እና ከሰዎች ጋር አብሮ በሰላም ስለመኖር ሲያትት ከግል ገጠመኙ በመነሳት “በዕውቀት እና በሰው መውደድ ከሁሉ እበልጥ ነበር እና ጓደኞቼ ቀኑብኝ። በዚህም ተንኮል ሰሩብኝ” ይለናል። በዚህ ምክንያት ተከዜን ተሻግሮ እንፍራንዝ የኖረው ፈላስፋው በዘመኑ በሰዎች መካከል በሃይማኖት ምክንያት ስለነበረው መከፋፈል እና መገዳደል “ስለ እግዚአብሔር ወንጌል እንዴት እንዲህ ይገዳደላሉ?” እያለ ማኅበራዊ ትችቱን  የጻፈው የጓደኝነት ምሥጢር እና የሰው ፍቅር የሃይማኖትን ወይም ሌላ ርእዮተ ዓለምን ድንበር መበጣጠስ እንዳለበት ሲመክረን ነው።  በዚሁ ወደ ዋናው ርእሳችን እንሸጋገር “አብሮ መብላት ወንዝ ያሻግራል”።

“አብሮ መብላት ወንዝ ያሻግራል”

ይህች አባባል በእነ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በኩል “ሐበሻ የሆዱ ነገር ሞቱ ነው” ተብላ ትተረጎም እንደሆን አላውቅም። ለማንኛውም የያዘችው መሠረተ ሐሳብ ሆዳምነትን ሳይሆን አብሮ መብላት የዘምን እና የድንበርን ተሻጋሪነት የምታሳይ ስለሆነች የጓደኝነትን ምሥጢር ቋጠሮ ይዛለች። ሌላም እህት አባባል አለች። አባባሏን አዲስ ዓመትን በማከብርበት በገጠሩ ክፍል የሰማኋት ስትሆን በርግጥም ይህንን ጽሑፍ በማዘጋጅበት ወቅት ትክክለኛ ቦታዋን እዚህ እንደሆነ ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀብኝም። “አብሮ መብላት ቅዱስ ዮሐንስ አይሽረውም።” ትላለች ቅዱስ የሐንስ የዘመን መለወጫ በዓላችን ነው። ማንኛውም መጥፎ ነገር፣ በሽታም ሆነ ድግምት፣ መተትም ሆነ ጥላቻ ቅዱስ ዮሐንስ ይሽረዋል ተብሎ ይታመናል። ከዚህ ሁሉ አብሮ መብላት ቅዱስ ዮሐንስ አይሽረውም።

ሁለቱን አባባሎች በአንድ ላይ ስንተነትናቸው አብሮ መብላት ወንዝና ዘመንን ያሻግራል። የቦታ ድንበር አያግደውም ወይም የዘመን መለወጥ አይሽረውም። ሰፋ ያለውን ትንታኔ ለባህል እና የቃላዊ ጽሑፎች ተንታኞች ትተን ለያዝነው ዓውድ የሚመጥነው ትርጓሜ ግን አብሮ መብላት ክፉና በጎን አብሮ መጋራትን፣ የጓደኝነትን  እህል ውሃ የሚገልጽ ነው። አብሮ መብላት ከዘመዴ ወገኔ ወይም ከ ጊዜያዊ ጥቅም ሕብረት የተለየ የሁለት ነፍሳት የተፈጥሮ ትስስር ሰንሰለት ነው።

እዚህ ላይ እንደዚህ ዓይነቱን ተረት ወይም አባባል ለምን መጥቀስ እንዳስፈለገኝ ግልጽ ነው። በዘመናችን የጓደኝነት ትርጉም ውሉን ያጣ ይመስለናል። መግቢያዬ ላይ እንደገለጽሁት ጓደኝነት የሁለት ቤተሰቦችን ትስስር ብሎም የሃገራትን ውህደት የሚያመጣ እንደሆነ ጠቆም አድርገናል። በዚሁ የአገራችንን ጉዳይ እንመለከትበት ዘንድ ጓደኝነትን የንግግራችን መዘውር አድርገነዋል። በቋንቋ እና በሃይማኖት፤ በብሔር እና በርእዮተ ዓለም አጥር ተከልለው “ሌሎች” የሚሏቸውን በጠላትነት የፈረጁ አካላት የጓደኝነት ምሥጢር የገባቸው አይመስለንም። አንድ የጋራ ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ እና ጠንካራ አገራዊ አንድነት ለመገንባት የግለሰቦች ጓደኝነት እዚህ ግባ የሚባል አስተዋጽኦ ያለው የማይመስለው የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኝ እንኳን የተመሳሳይ ጾታ ጓደኝነት እና የተቃራኒ ጾታ ተፈጥሯዊውን የፍቅር ግንኙነት እንኳን ከብሔር ውጭ ለማሰብ ሕሊናው የታወረ ይመስላል። ሰው ትክክለኛ ልቡሰ/ልብስተ  ጥላውን ወይም እንደ ቤል ዓይነት ሊቀ መኳሱን ለማግኘት አንዳንዴ ወንዝን መሻገር፣ ፈታኝ ዘመንን ማለፍ ያስፈልጋል።

ጠቢቡ እስክንድስ ስለ ጓደኝነት ተጠይቆ የሰጠው መልስ እንዲህ የሚል ነው።

 “Freindship is a desirable good nam; [a friend] is a man  not showing himself everywhere; [friendship] is a spring difficult to find out; it is a strength in days of misery and hardship, the protector in days of war, the good road, the need, the joy of all those who posseses it, the strength of him for whom it is needed, a vigilant mind, a choosen vessel, a gain for the soul, an incoprehensible acquisition.”  (Skendes, 1981, 48-49)        

እንደወረደ ሲተረጎም ጓደኝነት በማንኛውም ቦታ የማይገኝ፣ የተከበረ እቃ፣ ለማግኘት የሚከብድ ውድ ነገር፣ በችግር ጊዜ ደራሽ፣ የጥንካሬ መሠረት፣ የነፍስ ገጸ በረከት፣ የቀና ጎዳና፣ የደስታ ሁሉ ምንጭ የሚል ጭብጥ ይይዛል። ለጓደኝነት መስፈርቱ የሰውን የልብ ትርታ አዳምጦ ለችግር መፍትሔና ለፍላጎቶች መልስ መስጠቱ ላይ ነው።

መውጫ

በዘመናችን ትኩረት የማይሰጣቸው ነገር ግን ትልቅ ርእሰ ጉዳይ እና ምርምር ከሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች አንዱ የጓደኝነት ነገር ነው። ብዙ ጥናቶች በትዳር ዙሪያ ወይም በማኅበራዊ ግንኙነቶች ዙሪያ ይደረጋሉ። በጓደኝነት ዙሪያ ግን የተደረገ ጥናት አልገጠመኝም። በእኛ ዘመን ሰዎች አብረው ተምረው፣ አብረው እየሰሩ ኖረው፣ ወይም በተለያየ አጋጣሚ በርካታ ፈተናዎችን እና ደስታዎችን አብረው ተጋፍጠው ወይም አጣጥመው እንዲሁ በማንነት ፖለቲካ ምክንያት ያለፈውን ባንዴ ረስተው ሲሰዳደቡ ወይም ሲጣሉ ማስተዋል እየተለመደ ነው። ለዚህ ነው ዘመንና ቦታን የሚሻገር ጓደኝነት የሚያስፈልገን። መልካም ጓደኛ መስፈርቱ የነፍስን መሻት ከማሟላቱ፣ ሰው መሆኑ ላይ እንጅ ማንነቱ ላይ እንደሆነ የሚሞግት ሰው አልገጠመኝም።

እንደ መውጫ ይሆነን ዘንድ ሁለት የአገራችን ጠቢባን ስለ ወዳጅ የተናገሩትን ብንጠቅስ ንግግራችን የተሟላ ያደርገዋል። ባለቅኔው የፍታሔ ንጉሤ በዘመን ተሻጋሪ ስንኞች ጓደኝነት እንዲህ ሲሉ ይገልጹታል:-

“ወዳጅ ማለት አብሮ ሲባክን ነው እንጅ

እንዳይን እንደጆሮ እንደግር እንደጅ፣”

ሰዓሊው እና ባለቅኔው ገብረ ክርስቶስ ደስታ ደግሞ የስንኞቹን ይዘት እንዲህ ሲል ያብራራልናል:- “ይኽን ግጥም ካነበብን በኋላ የምናየው የወዳጅ መልክ ማንኛውንም ዓይነት አይደለም- በመስታወት ውስጥ እንደምናየው መልካችን እኛኑ የመሰለ፣ እንደ ዐይናችን፣ እንደ ጆሯችን፣ እንደ እግራችንና እንደ እጃችን ከእኛ የማይለይ የእኛው አንዱ የአካላችን ክፍል ነው” ጓደኝነት በስሜት መናበብ እና ዘላዊ በሆነ መዋሃድ፣ በ‘አንድ አካል-አንድ አምሳል’ነት አገራዊ አንድነት እና በሰዎች መካከል መልካም ተግባቦትን በመፍጠር ረገድ የማንነትን ወንዝ፣ የዘመንን ፈተና ካልተሻገረ ምኑን ጓደኝነት ተባለው? ሰላም!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top