ስርሆተ ገፅ

“በሥራዬ ማንም እንዲበልጠኝ አልፈልግም”

ራሳቸውን አንጋፋ ከሚባሉት ተርታ አሰልፈዋል። በፊልም ማንሳት ሙያ ለረዥም ዘመናት ሰርተዋል። ጋዜጠኛም ናቸው። “በሥራዬ ማንም እንዲበልጠኝ አልፈልግም” በምትል ተደጋጋሚ አባባላቸው እና በእምቢ ባይነታቸው ብዙዎች ያስታውሷቸዋል። በሀቀኛ ዘጋቢነታቸው፣ በፊልም አንሺነታቸው እና በጋዜጠኝነታቸው የሚታወቁት አቶ ኤልያስ ብሩ አሁን የ78 ዓመት አዛውንት ናቸው።

የማስታወቂያ ሚኒስቴር አለቆቻቸው ስለ ወሎ ድርቅና ረሃብ የመንግሥትን ቸርነት እና ደራሽነት የሚያሳይ ፊልም አንስተው እንዲመጡ ተላኩ። እውነታው ተቃራኒውን ሆኖ በማግኘታቸው ከአለቆች ቅጣት በላይ የህሊናቸውን ዱላ ፈሩ። ከበላዮቻቸው ሙገሳ በላይ በችግር ውስጥ ያሉትን ዜጎች መትረፍ ናፈቁ። እውነታውን በካሜራቸው አስቀርተው ተመለሱ።

ድርጊታቸው በአለቆቻቸው አንደሚያስወቅሳቸው ቢያውቁም ብዙዎች የጠበቁት የተለሳለሰ አቋምም አልነበራቸውም። ዐይናቸው ያየውንና ሕሊናቸው ያስመለከታቸውን የድርቁን አስከፊነትና የወገንን የረሃብ ሰቆቃ በካሜራቸው ቀርጸው፣ የሃቀኛ ጋዜጠኝነትን መልካም አርአያነት አስመስክረዋል።

ደርግ አቋቁሞት በነበረው የወሎ ድርቅ ጉዳት አጣሪ ኮሚሽን ዘንድ ቀርበው ያዩትንና የተገነዘቡትን በካሜራቸው መዘገባቸውን መስክረዋል።

ዛሬ ላይ ሆነን የያኔውን የአቶ ኤልያስን ሙያዊ የጀግንነት ተግባር ስናስብ፣ እንደነ ዮናታን ዲምብልቢይ ሁሉ የወሎ ድርቅን ጉዳይ በጋዜጠኝነታቸው በማጋለጥ ዓለም አቀፋዊም ሆነ ብሔራዊ ሽልማት ሊሸለሙ የሚገባቸው ብርቱ ሰው መሆናቸውን እናምናለን።

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ቋሚ ፊልም አንሺና ፎቶ ሪፖርተር ሆነው ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል። ከነዚህ ሁለት መሪዎች ጋር ሁነው ብዙ አገራትን ዞረዋል። በሐገር ውስጥም ብዙ ከተንቀሳቀሱ ጋዜጠኞች መካከል አቶ ኤልያስ ብሩ አንደኛው ናቸው።

አንጋፋው ጋዜጠኛ የሕይወት ታሪካቸውን እና ሥራቸውን በተመለከተ ከቤተልሄም መአዛ ጋር የነበራቸው ቆይታ እንዲህ ይነበባል።

ተወልጄ ያደኩት በቀድሞው የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ነበር። በመጀመሪያ ቄስ ትምህርት ቤት ገብቼ ከቀለም ጋር የተዋወቅሁትም እዚያው ነው። በሰዓቱ አባቴ በሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ በነጭ ለባሽነት ያገልገል ነበር። በዚህም ምክንያት ወደተለያዩ አካባቢዎች ሲዘዋወር አብሬው እየተጓዝኩ ትምህርቴን እከታተል ነበር። ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ክፍል በሲዳሞ ሚሲዮን ትምህርት ቤት ብማርም፣ አባቴ የሚሲዮን ትምህርት ቤቱን ስላልወደደው ወደ አለታ ወንዶ አመራን። ሚሲዮን ትምህርት ቤቱን ያልወደደው ሃይማኖቱን ከኦርቶዶክስ ወደ ፕሮቴስታንት ያስቀይርብኛል በሚል ሰበብ ነበር። እናም በአለታ ወንዶ ከስድስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ትምህርቴን ተከታትያለሁ። አባቴ ወደ ይርጋለም በተዘዋወረ ጊዜም ከዘጠነኛ እስከ አሥረኛ ክፍል በራስ ደስታ ዳምጠው 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሬያለሁ።

ወታደር ቤት እንዴት ገቡ?

2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሆኜ አንድ ቀን ከእድሜ ጓደኞቼ ጋር በመጫወት ላይ እያለሁ፤ በአንድ ቀላል ምክንያት ከአንድ ልጅ ጋር አለመግባባት ተፈጠረና ተጣላን። ስንደባደብ የተጣላሁት ልጅ ክፉኛ ስለተጎዳ፣ አባቴ ይህንን በሰማ ጊዜ በዛኑ ቀን ማታ አዲስ አበባ ወደሚኖሩ ዘመዶቻችን ላከኝ። አዲስ አበባ ከመጣሁ ከጥቂት ቀናት በኋላ ከሲዳሞ አብሮ አደግ ጓደኞቼ ጋር ተገናኝተን በመጨዋወት ላይ ሳለን፤ አንደኛው አብሮ አደግ ጓደኛችን በዙ መኩሪያ ይባላል አራተኛ ክፍለ ጦር ውስጥ በወታደርነት ተቀጥሮ ይማራል የሚል ዜና ሰማን። ከመሃላችን እኔና አንዱ ጓደኛችን እሱን ለመጠየቅ መሿለኪያ ወደ ሚገኘው የወታደሮች ካምፕ አመራን። በቦታው እንደ ደረስን ጓደኛችንን ከጥቂት የማፈላለግ ቆይታ በኋላ አገኘነው።

እዚያም ቆመን በዙን እያነጋገርነው እያለን፤ የወቅቱ የሰልጣኞች ሀላፊ የነበረው መቶ አለቃ አሰፋ ከበደ (ኋላ ኮሎኔል) ወደኛ መጣና የትምህርት ደረጃችንንና ከየት እንደመጣን ጠየቀን። በመቀጠልም የጦር ሠራዊቱ ቤት የተለያዩ ትምህርቶችን ወደ ተለያዩ የውጭ ሀገራት ልኮ ጭምር ወታደሮችን እንደሚያስተምር ከነገረን በኋላ፤ ወደ ወታደር ቤት በቅጥር እንድንገባ ጥያቄ አቀረበልን። አብሮኝ የሄደው ጓደኛችን መግባት ስላልፈለገ አሻፈረኝ አለ። እኔ ግን ከምኖርበት ከሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ከሰው ጋር ተጣልቼ ስለመጣሁና አዲስ አበባ ላይ ተደብቄ ስለነበር፤ ያለኝ አማራጭ ወደ ወታደር ቤት መግባት ብቻ ነው ብዬ ወሰንኩ።

ስምዎን ቀይረው ነበር ሲባል ሰማሁ እውነት ነው?

አዎን… በሰዓቱ “ተስፋዬ ብሩ” ተብዬ ነበር የምጠራው። ነገር ግን ተደብቄ ስለመጣሁ፤ “እፈለግ ይሆናል” በሚል ስጋት ስሜን ቀይሬ “ኤልያስ ብሩ” ተብዬ ተመዘገብኩ። ይህንን ሳደርግ ግን ቤተሰቦቼና ዘመዶቼ አያውቁም ነበር። ዘመዶቼ ዘንድ በመሄድ ሥራ መግባቴን ገልጬላቸውና የሥራ ቦታው ስለማይመቸኝ እዚያው እያደርኩ እንደምሠራ ነገርኳቸው። እንግዲህ ይህ የሆነውና ውትድርና የተቀጠርኩት በ1953 ዓ.ም. መሆኑ ነው። ወታደር ቤት ከገባሁ ከጥቂት ቀናት በኋላ፤ በወቅቱ በነበረው የታህሳስ ግርግር ምክንያት ክቡር ዘበኛና ጦር ሰራዊት ተጋጭተው ክቡር ዘበኛ ተሸነፈ። ከዚያም የኛ ሠራዊት የጦር ሠራዊት የጦር ኃይሎች ማስታወቂያ ክፍል ሆኖ ወደ ፖፖላሬ ተወሰድን። በዚያ አካባቢ ከኛ ቢሮ አጠገብ ‘ማግና የአሜሪካን ሚሊተሪ ኤድ’ የሚባሉ ድርጅቶች ነበሩ። ክቡር ዘበኛ በተሸነፈ ጊዜም የእሱ የነበሩ ካሜራዎችና ጠቅላላ የስቱዲዮ እቃዎች ተጠቃለው ወደኛ መስሪያ ቤት በውርስ ተወስደዋል። በአጠገባችን የሚገኘው የአሜሪካ ኤድ የተለያዩ ሙያዊ ሥልጠናዎችን ይሰጥ ስለነበር፤ የፎቶ ግራፍ አንሺነት ቴክኒኮችን በትርፍ ሰዓቴ እየሄድኩ እማር ጀመር። ከዚያ ተምሬ ስመለስ በኛ ስቱዲዮ ውስጥ በሚገኙ መሳሪያዎች ልምምድ አደርግ ነበር። ስለፎቶግራፍ አንሺነት ያለኝን እውቀት በቢሮ ለሚገኙ ጓደኞቼ አካፍላቸውም ነበር። በዚያም ተወዳጅነትን አተረፍኩ። በሌላ በኩል ደግሞ ተወዳጅ ፎቶግራፍ አንሺ ሆንኩ።

ተጨማሪ ስልጠናዎችስ አልወሰዱም?

ወታደር ቤት በገባሁ በሁለተኛ ወሬ አለቃዬ ከፎቶ ሊቴ ባለቤቶች ጋር አስተዋወቀኝ። እናም ለፎቶግራፍ ትልቅ ፍቅር ስለነበረኝ በትርፍ ጊዜዬ እየሄድኩ ልምምድ አደርግ ነበር።

ኮንጎ ዘምተው ነበር ሲባል ሰምቻለሁ። እንዴት ዘመቱ?

ከእለታት አንድ ቀን አለቃዬ መቶ አለቃ አሰፋ ጠራኝና ወደ ኮንጎ እንድሄድ አዘዘኝ። በዚያም “የጠቅል ብርጌድ” የሚባል በተባበሩት መንግሥታት ስር የሚሰራ፣ የሰላም አስጠባቂ ኃይል አለ። እዚያ ሄጄ ከእሱ ጋር እንድሠራ አዘዘኝ። በማግስቱም ወደ ኮንጎ በረርን “መኖኖ” እምትባል ስፍራ ነበር ያረፍነው። በዚያም ቆይታዬ ፊልምና ፎቶግራፍ በማንሳት ሠራሁ።

እንዳጋጣሚ ሆኖ ጠቅል ብርጌድ ሥራውን ጨርሶ በስምንተኛ ወሩ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ። እኔ ግን ለሁለት ዓመታት በመቆየት ግዳጄን መጨረስ ነበረብኝ። በወቅቱ የሥራ ጫና ይበዛብኝ ስለነበርና ነፃነት ስለሌለኝ ወደ አዲስ አበባ እንደተመለስኩ አንድ እርምጃ ወሰድኩ። በቀጥታ ወደመስሪያ ቤት ሄጄ በስሜ ተመዝግበው የነበሩ ንብረቶችን አስረክቤ፣ ዘመድ ለመጠየቅ እንደምሄድና በማግስቱ እንደምመለስ ነግሬያቸው ወጣሁ። ከዚያም መርካቶ ወደሚገኝ ዘመዴ ቤት ሄድኩ። ከዚያን ቀን ጀምሮ ወደ ወታደር ቤት አልተመለስኩም። እንደጠፋሁ ቀረሁ፣ እነሱም መጥፋቴን አወቁ። አዛዦቹም በጥብቅ ያፈላልጉኝ ነበር። ለብዙ ጊዜያት ተደብቄ ከቆየሁ በኋላ፣ ለፊልምና ለፎቶግራፍ አንሺነት ትልቅ ፍቅር ስለነበረኝ ወደ ‘ፎቶ ሊቴ’ በመሄድ (ከዚህ በፊት ባለቤቱን አውቀው ስለነበር) አሁን ላይ ያጋጠሙኝን ችግሮች ነገርኩት። ከዚያም ቀን ቀን ተደብቄ እየሄድኩ ስለ ከለር ፎቶግራፍ አነሳስ መለማመድ ጀመርኩ።

ከእለት ወደ እለት  የፎቶግራፍ እውቀቴ  እየጨመረ መጣና  ከፎቶ ሊቴዎች ጋር  መስራት ጀመርኩ። በወቅቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ የሥራ ቅጥር ማስታወቂያ ማውጣቱን እንደሰማሁ ወደ ጣቢያው ሄድኩ። በወቅቱ የቴሌቪዥን ጣቢያው ሥራ መሪዎች ነጮች ነበሩ። በቀጥታ ወደ ድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወደ ‘ሚስተር ቻርልስ’ ቢሮ በመሄድ ሥራ መቀጠር እንደምፈልግ ነገርኩት። የትምህርት መረጃዎቼን ተመለከተና ከአምስት ቀን በኋላ ፈተና እንደሚኖር ነገረኝና ተመለስኩ። በአምስተኛውም ቀን ሄጄ ተፈተንኩ። ከ18 ተወዳዳሪዎች መካከል ሁለታችን ብቻ አለፍን። በቋሚነትም መሥራት ጀመርኩ።

(በ1957 ዓ.ም) ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የቴሌቪዥን ስርጭት ጀምሮ ስለነበር ለሙያው ትልቅ ጉጉት አሳድሮብኛል። በዚህም የተነሳ ስለ ፊልም አንሺነት ወይም ስለ ፎቶግራፍ የተጻፉ ጽሑፎችን ከተለያዩ መጻሕፍት አንብቤያለሁ። በበቂ ሁኔታም ስለ ፊልም አንሺነት ያለኝን እውቀት አዳብሬያለሁ። እናም ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ብቃት ያለኝ ባለሙያ ነኝ የሚል እምነት ነበረኝ። እንግዲህ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተቀጠርኩት በ1959 ዓ.ም ነበር ማለት ነው።

ቤተመንግሥት ከመላክዎ በፊት አንድ አስቸጋሪ ስራ ታዘው ነበር የት ነው?

በአንድ ወቅት እኔና አቶ አባተ መኩሪያ አሰብ ለሥራ ተልከን ነበር። አካሄዳችን “ሰሊና” የሚባል የፈረንሳይ ኩባንያ ውኃ ከቀይ ባህር አውጥቶ ካተነነው በኋላ፤ ወደ ጨውነት እየቀየረ ለአውሮፓ ገበያዎች ያቀርብ ነበርና የሥራውን ሂደት ለመዘገብ ነበር አካሄዳችን። ፊልሙን ለማንሳት ከምንገለገልባቸው መሣሪያዎች መካከል አንዱ ከአሜሪካ የመጣ “ኦሪፈን” የተባለ የድምጽ መቅጃ መሣሪያ ነበር። የሄድንበት አካባቢ የጨው ምርት የሚሰበሰብበት በመሆኑ ለሥራችን አመች አልነበረም። ከፍተኛ የፀሐይ ሙቀት አለ። እንደሚፈለገው አድርጎ ቀርፆ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ነበር። የፊልም ቀረጻ ሥራዬን በመስራት ላይ እያለሁ ለማጠናቀቅ ጥቂት ሲቀረኝ፣ የካሜራው ባትሪ ዘጋብኝ። በወቅቱ የምናደርገው ነገር ግራ ገብቶን ተረበሽን። እንዳጋጣሚ ሆኖ ላንድ ሮቨር መኪና ይዘን ሄደን ስለነበር፣ የመኪናውን ባትሪ ካስነሳን በኋላ፣ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ከብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በኋላ ቀርጸን የተመለስነውን አልረሳውም። ያ ቀርጸን ያመጣነው ፊልም ተስተካክሎ ለእይታ በቃ። ወደ ቤተመንግስት ከመላኬ በፊት ይሄ እንደ መመዘኛ ፈተና እንደሆነልኝ አለቆቼ ገለጹልኝ። በተሠራው ሥራ መደሰታቸውንም ገለጹልኝ።

በሥራ ዓለም ቆይታዎ አይረሴ ሥራዎቼ ናቸው የሚሏቸው የትኞቹ ናቸው?

በፊልም አንሺነት ሙያ ከ1959-1983 ዓ.ም. ማለትም ለ24 ዓመታት ቆይቻለሁ። ከሠራኋቸው ሥራዎች አይረሴ ነው የምለው፣ የጃንሆይን የሕይወት ታሪክ ማለትም ከተወለዱበት ዘመን ጀምሮ እስከ እርጅናቸው ዘመን ድረስ ሠርቼ ለቀ.ኃ.ሥ. መታሰቢያ ድርጅት ያበረከትኩት ነው። በተጨማሪም በ1965 ዓ.ም. አስከፊውን የወሎ ድርቅ ቦታው ድረስ በመሄድ ያለውን አስከፊ ገፅታ ቀርጨ መንግሥት እንዲደበቅ ይፈልገው የነበረውን ምስጢር አጋልጫለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ ከጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ ጋር በመሆን “አባይ አባይ” የተሰኘውን ፊልም ሰርተናል።

ቤተ መንግሥት በምሠራበት ጊዜ ደግሞ፣ ጃንሆይ ለመጨረሻ ጊዜ በቤተ መንግሥት እያሉ የደርግ ወታደሮች መጥተው፤ “የወታደሩ እንቅስቃሴ እያየለ መጥቷል። ስለዚህ ለእርሶ ደህንነት ስንል ቦታ ስላዘጋጀንልዎት እንሂድ…” ብለው በሚወስዷቸው ጊዜ የነበረውን ሁኔታ በካሜራዬ ተከታትዬ ቀርጫለሁ። ከሌሎች የሥራ አጋሮቼ ጋር አቀነባብረነው የነበረው ፊልም እስከ ዛሬ ድረስ ለዕይታ ይቀርባል።

የወሎ ድርቅን ጉዳይ ካነሳን አይቀር በወቅቱ የነበሩትን ሁኔታዎች ቢያስታውሱን?

ወደ ወሎ ተልኬ በሄድኩበት ሰዓት የተነገረኝና ቦታው ላይ ያየሁት እጅግ በጣም የተለያዬ ነበር። ቦታው ላይ እጅግ በርካታ ሰዎችና የቤት እንስሳት በረሀብ ምክንያት ሞተው ሬሳቸው መሬት ላይ ወድቆ ተመለከትኩ። በህይወት ያሉት ደግሞ እጅግ በጣም አሳዛኝ በሚባል ሁናቴ ላይ ይገኙ ነበር። ወደ እርዳታ ተቋሙ ሄጄ የእህልና የመድሃኒት አቅርቦቱ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ጠየቅኳቸው። በምላሻቸውም  በጣም ጥቂት እህልና መድሃኒት እንደመጣና ያም ማለቁን ገለጹልኝ። እነዚህን ሁሉ ምላሾችና ትእይንቶች በካሜራዬ ቀርጬ፣ በመሬት ላይ ያሉ እውነታዎችን፣ በየስፍራው የወዳደቁ ሬሳዎችንና ረሃብተኞችን በፊልሜ አካትቼ ሠራሁ። በወቅቱ ምንም ዐይነት ነገሮች አላስጨነቁኝም። ሕሊናዬ ያየውን እውነት በሃዘንና በእንባ እያጀበ መቆጨት ብቻ ነበር። ለምሳሌ ከሥራ መባረር ወይም መታሰር ከቶም አላሳሰበኝም። እንደ ሙያዊ ግዴታዬ እና እንደ ሰብአዊ ፍጡርነቴ ስመለከተው ማድረግ ያለብኝን ነገሮች አድርጌያለሁ።

ፊልምዎ ወደ ሕዝብ እንዳይቀርብ አለቆችዎ ያዘገዩት ቢሆንም፤ ለዕይታ ከቀረበ በኋላ የመጡት መረጃዎች ምን አይነት ለውጦችን አስከትለው ነበር?

የሠራሁት ሥራ ሙሉ በሙሉ ባይተላለፍም ያመጣቸው የተወሰኑ ለውጦች አሉ። ለምሳሌ ከተለያዩ የውጭ ድርጅቶች የምግብና የመድሃኒት እርዳታዎች ወደ ሃገር ውስጥ ገብተዋል። በድርቁ የተጎዱ ዜጎችን ለመታደግም በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ርብርብ ተደርጓል።

አስደንጋጩ ሽማት የት ነበር?

ከጃንሆይ ጋር ሩሲያ (የያኔው ሶቪዬት ሕብረት) በሄድኩበት ወቅት ፊልም እየቀረጽኩ ሳለሁ፣ በድንገት ተጠርቼ ሜዳሊያ የተሸለምኩበትን ሁኔታ አልረሳውም።

የሚቆጭዎ ነገር አለ?

በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ታሪካዊ ይዘት ያላቸውን ነገሮች ሰብስባችሁ ፕሮግራም ሥሩ ተብለን ወደ ቀይ ባህር አመራን። በዚያም አካባቢ ሦስት መቶ ደሴቶች ያህል ይገኛሉ። ከእነሱም መካከል “ደሂል” ወደ ተባለችው ደሴት በጀልባ በመሄድ ላይ ሳለን፣ ናኩራ ደሴት ላይ “ናኩራ” የተባለ ጥንታዊ የጣሊያን እስር ቤት ይገኛል። ትንሽ ወረድ እንዳልን የተከመረ የቀንድ አውጣ ሼል ተመለከትን። ትንሽ ዞር ዞር እንዳልን ድሮ ጣሊያን አስሮ ያሰቃያቸው የነበሩ ኢትዮጵያውያንና የሌሎች ሀገር ዜጎች ስሞችና ከየት እንደመጡ የሚገልጽ ጽሑፍ በግእዝና በሳባዊያን ፊደል ተፅፎ አገኘን። ይህንን ታሪክ ቀርፀን ከጨረስን በኋላ ወደ ደሂል ደሴት ሄድን። በዚያም እጅግ በጣም ረጃጅም ስድስት መድፎች ተሰልፈው ተመልክተናል። ይህን ሁሉ ቀርፀን ወደ አዲስ አበባ ከተመለስን በኋላ “አስፈላጊ አይደለም” ተብለን ሳይተላለፍ የቀረው ድንቅ ሥራ ሁሌ ሲቆጨኝ ይኖራል።  

ለ24 ዓመታት በቆየው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሥራ ዘመንዎ ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ጋር እንዲሁም ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማሪያም ጋር በቅርበት የመሥራት እድል ነበረዎት። እስኪ የነዚህን ሁለት ርእሳነ ብሔር ሰብእና ይግለጹልን?

ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ስንጀምር፣ በአንድ ወቅት ጃንሆይ ጣሊያንን በጎበኙ ጊዜ የጣሊያን ህዝብ ከአየር ማረፊያ እስከ ቤተ መንግሥት ድረስ በደማቅ ሁኔታ ተቀብሏቸው ዐይቻለሁ። ወደ አሜሪካ በሄዱ ጊዜም የአሜሪካ ዜጎች በሙሉ ነጭና ጥቁር ሳይል ተመሳሳይ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ይህ በሥራ ዘመኔ ሌላው የማይረሳ ትውስታዬ ነው።

የጃንሆይን ባህሪ ስንመለከት ምንም ዐይነት ስህተት ማየት አይፈልጉም።  አንዴ ከጠሉ ጠሉ ነው። ወደ መንግሥቱ ኃ/ማሪያም ስንመጣ፣ እጅግ በጣም ቆራጥና ጠንካራ ወታደራዊ አስተዳደርን የተላበሱ መሪ ናቸው። ሆደ ባሻ ነበሩ። አልቃሻ ናቸው። ገር ናቸው። እንደ ጃንሆይ ሁሉ መንግሥቱ ኃ/ማሪያምም ወደ ኩባ በሄዱ ጊዜ እጅግ በጣም ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ከስራ ታግደው ያውቃሉ?

አዎን… አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት በረከት ስምኦን ነው የፖለቲካ ውሳኔ ሰጥቶ ያባረረን። ከሦስት ቀናት ጭቅጭቅና ንትርክ በኋላ 60 ጋዜጠኞችን ኢሕአዴግ ከነባር የሥራ ገበታችን ላይ አባሮናል። እንደ ብዙ ወንድማገኘሁ የመሳሰሉትን ቆራጥ ጋዜጠኞች የደርግ ሰላይ ነበራችሁ ብሎ ማባረር በጋዜጠኝነት ላይ የተሠራ ግፍ ነበር። እኔ በግሌ ከሥራ ብታገድም ዝም ብዬ ቁጭ አላልኩም። ጦቢያ በምትባል መጽሔት እሠራ ነበር። በዛም ከ60-80 ሺህ እትሞችን ወደ ተለያዩ ቦታዎች በሀገር ውስጥና ውጭ ለአንባቢያን እናቀርብ ነበር። አሁንም በድጋሚ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ጦቢያ መጽሔት ታገደችብን። ከዚያም በኋላ ወደ መምህርነት ሙያ መጣሁ። ሻሎም ቪድዮግራፊ በተባለ ትምህርት ቤት ለተወሰኑ ጊዜያት በመምህርነት ሰርቻለሁ።

ከባለቤትዎ ጋር የተገናኙበትን አጋጣሚ እናንሳው

ከባለቤቴ ጋር የተገናኘንበት አጋጣሚ ጃንሆይን ተከትዬ ለሥራ ጉዳይ ወደ ሐረር ሂርና ሄጄ በነበረበት ወቅት ነው። ሥራዬን ጨርሼ አካባቢውን ለመቃኘት ስወጣ እንዳጋጣሚ ሆኖ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ተለቀው በመውጣት ላይ ነበሩ። እና ከምሄድበት መንገድ ፊት ለፊት ሦስት ሴት ተማሪዎችን ተመለከትኩ። ከሦስቱ መካከል ካንደኛዋ ልጅ ጋር ዐይን ለዐይን ተፋጠጥንና ተላለፍን። እናም በዚያች ቅፅበት ልጅቷን ወደድኳት። ከዚያም ስለ ልጅቷ ሳጣራ ኮማንደር ዘውዱ ገ/ማሪያም አጎቷ መሆኑን ሰማሁ። የሥራ ቆይታዬን ጨርሼ ወደ አዲስ አበባ እንደመጣሁ ወደ ኮማንደር ዘውዱ መስሪያ ቤት ሄጄ የወንድሙን ልጅ እንደወደድኳትና ላገባት እንደምፈልግ ነገርኩት። እርሱም ከየት እንደመጣሁ፣ ሥራዬ ምን እንደሆነ፣ ደሞዜ ምን ያህል እንደሆነና ልጅቷን ማስተዳደር እችል እንደሆን ጠየቀኝ። እኔም በቤተ መንግሥት ካሜራ ማን ሆኜ እንደምሠራና ልጅቷን ማስተዳደር እንደምችል ነግሬው ወጣሁ። በወቅቱ ምንም ምላሽ አልሰጠኝም ነበር።

አሁንም በድጋሚ ተስፋ ሳልቆርጥ የኮማንደር ዘውዱ አለቃ የነበሩት ኮማንደር እስክንድር ደስታ ዘንድ የቅርብ ጓደኛዬን ልኬ አጎቷን እንዲጠይቅልኝ አደረኩ። ከዚያ በኋላ ኮማንደር እስክንድር ኮማንደር ዘውዱን አነጋገሩት። እንዳጋጣሚ ሆኖ ትምህርት ቤት ተዘግቶ ስለነበር ልጅቱ ለእረፍት ወደ አዲስ አበባ መጣች። ኮማንደር ዘውዱ ስለ ጋብቻው ጠየቃት። እሷም ፈቃደኛ እንደሆነች ገለፀችለትና ተጋባን። ከጋብቻውም ሁለት ልጆችን አፍርተናል። …ዛሬ በሕይወት የለችም።

የጡረታ ጊዜዎን በምን መልኩ እያሳለፉ ነው?

የጡረታ ጊዜዬን በቁጭታ አላሳልፍም። የተለያዩ ሥራዎችን በመስራት ጊዜዬን በቁምነገር ለማሳለፍ እየጣርኩ ነው።

ስለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ!

እኔም አመሰግናለሁ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top