የታዛ ድምፆች

በሕግ አምላክ!

የሕግ ባለሙያው በባቡር እየተጓዘ ነው። አሰልቺውን የባቡር ጉዞ እያንቀላፋም፣ እያነበበም፣ እየተከዘም ለመግፋት ይጥራል። በጉዞው መካከል አንዲት ወጣት ፊትለፊቱ የሚገኘው ወንበር ላይ ተቀመጠች። እንደዋዛ ቀና ብሎ ተመለከታት። ውበቷ አስደንጋጭ ነበር። ዐይኖቹን መንቀል አልተቻለውም። የተጫጫነው መሰላቸት ሲለቀው ታወቀው። ደስታ ሲጎበኘው ተሰማው። ቀና ብሎ ይመለከታታል። አቀርቅሮ ቀና ሲል እያየችው ይይዛታል። እርሷም ሰረቅ አድርጋ እየተመለከተችው አፈር ትላለች። ከጥቂት መተያየቶች በኋላ ማፈሩ ወደ መሽኮርመም ተቀየረ። መሽኮርመሙ ወደ ፈገግታ አደገ። የሁለቱም ደስታ ናረ። መቀራረብ እንደፈለገች ተረድቷል። ከጥቂት የዐይን ጨዋታ በኋላ ሴቲቱ ከጎኑ የሚገኝ ወንበር ላይ ተቀመጠች። አዝማሚያዋን የተረዳው የሕግ ሰው ደስታው ይበልጥ ጨምሯል። የቃላት ለውጥ ሳይኖር ተግባቡ። ድንገት ወደ ጆሮው ጠጋ ብላ በሹክሹክታ ያናገረችው ነገር ግን አስደንጋጭ ነበር።

“ኪስህ ውስጥ ያለውን ጥሬ ገብዘብ፣ የኤቲኤም ካርድህን ከነ ፓስወርዱ፣ የሞባይል ቀፎህን፣… አሁኑኑ ስጠኝ”

ደፋሩን ትእዛዝ ያደመጠው የሕግ ሰው በጥያቄ ዐይን እየተመለከታት ነው። ማመንታቱን ያስተዋለችው ቆንጆ እንስት “ትእዛዜን የማታከብር ከሆነ እጮሀለሁ” የሚል ማስፈራሪያ አከለችበት።

እሱ አጠገቡ ያለችውን መርዘኛ ሴት እንዴት እንደሚገላገላት እያሰበ ነው። እሷ በፍጥነት ትእዛዟን ካልፈጸመ የሚገጥመውን መከራ በመዘርዘር እያስፈራራችው ነው።

“ያለ ፍላጎቴ ጾታዊ ትንኮሳ እያደረስክብኝ እንደሆነ ጮኬ እናገራለሁ። በዚህ ወንጀል እንድትጠየቅ የኔ ጩኸት እና ያንን የሰሙ ሰዎች ምስክርነት ብቻ እንደሚበቃ አትዘንጋ። ያልኩህን በፍጥነት ፈጽም!”

አጣደፈችው። መለኛው ሰው ፈገግ አለ። አንድም ቃል ሳይተነፍስ ኪሱን መዳበስ ጀመረ። በፈገግታ እየተመለከተችው ነው። የጠየቀችውን በቀላሉ እንደሚሰጣት አልጠበቀችም። የሚሰጣትን ተቀብላ ለመሄድ እየተጣደፈች ነው። ምንም የስሜት ለውጥ ሳይታይበት፣ አንዲትም ቃል ሳይተነፍስ የጠየቀችውን ሊሰጣት መሆኑ አስገርሟት ሳያበቃ እጆቹ በካርድ እና ሞባይል ፋንታ ወረቀት እና እስኪርቢቶ ይዘው ከኪሱ ሲወጡ በማየቷ ደስታዋ ወደ ንዴት ተቀየረ። ሁኔታዋን እያስተዋለ ያለው ዝምተኛ ሰው አቀርቅሮ መጻፍ ጀመረ።

“ጠረንሽ ያማረ፣ አለባበስሽ የተስተካከለ፣ ዐይንንም ቀልብንም የምትገዢ አንቺ ውብ ሴት እኔ መናገር እና መስማት የተሳነኝ ነኝ።” ቀና ብሎ ተመለከታት። የሚጽፈው ለእርሷ መሆኑ ገብቷታል። የጻፈውን ለማንበብ ቸኩላለች። ያቋረጠውን ጽሑፍ በመቀጠል “እባክሽን ማለት የፈለግሽውን ነገር እዚህ ወረቀት ላይ ጻፊልኝ።”

ከጽሑፉ ግርጌ ፊርማውን አስቀምጦ ያቀበላትን ወረቀት አንብባ ስትጨርስ የቀደመ የሹክሹክታ ንግግሯን በጽሑፍ ደገመችለት። የሕግ ባለሙያው የተቀበለውን ወረቀት በጥሩ ሁኔታ አጣጥፎ ኪሱ ከከተተው በኋላ ከመቀመጫው በዝግታ ተነሳ። ፈገግ ብሎ ጉሮሮውን ለንግግር ከጠራረገ በኋላ ዘለግ ባለ ጎርናና ድምጹ እንዲህ አለ።

“አሁን እንደፈለግሽ መጮህ ትችያለሽ!”

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top