ማዕደ ስንኝ

ም ነው ሰላሌ ?! Maaloo Salaalee?!

ምነው ሰላሌ ያልለመደብህን፣ ያላደግክበትን ማደግደግ ከሳጥናዔል ጫማ ስር ወድቀህ፣ እታች ወርደህ ማሸርገድ ታዳጊ ወጣት አሳርደህ፣ አዝነህ ተቀምጠህ መንደድ

ከየት መጣብህ? ከየት ለመድከው? ከማን ወረስከው ይሄን ጉድ? ምነው ሰላሌ? ምነው ፍቼ? ምነው መንጠራ?

ተወልደን አድገንብህ፣ የተገንብህ ጎራ

ያ መልካም ስምህ፣ እንዴት በበላዔ ሰብ ይጠራ? አንቺ ፍቼ…

ሰማእቱ አቡነ ጴጥሮስ፣ የፈለቁብሽ ከተማ የእትብታቸው መቀበሪያ፣ ክፉ ነገርሽ ተሰማ፤ ቀለም ቆጣሪው ተሜ፣ እጅሽ ላይ ደሙ ፈሰሰ ብርሃን ጠፍቶ፣ ጨለማው ባገር ነገሠ፤

¨Salaalee yaa Salaalee Biyyaa naghenyii daararee¨¨ ማለት ከእንግዲህ ቀረ?

ቶርባን አሼን፣ አብሮ መጠጣት ተነወረ? አባ ቶርቤ፣ አባ ሸኔ

ይህን አያውቅም ወገኔ አርቲ ቡርቲ ገለመሌ ይህን አያውቅም ሰላሌ! Ni daarbitti yeroonni…

Xuriidha cubbuunii Ni murtiisa waqni

Ni tortooraa gadheenni Ni lalissa dhuganii

Ni jabaataa tokumani!!!

ሰላሌ ዛሬ ልውጥ አልክብን፣ መጥተን አጣንህ ከደጃፍህ መለስከን፣ እያለህ የለሁም ብለህ

ልሳነ ብዙ የነበርከው፣ ራስህን እንኳ መግለጽ አቃተህ፤

 እግዚኦ አምላክ!… እግዚኦ ፈጣሪ!… ከምን ዘመኑ ዶልከን ከምን ደጃፍ አዋልከን፣ ከምን ትውልድ ጣልከን

‹‹ወንድም ወንድሙን ቀጥቅጦ እተኛበት ጨፈለቀ›› የሚል ዜና የሰማ ሁሉ፣ ደጁን ዘግቶ ተጨነቀ፤ ጎፈሬውን ተላጭቶ፣ ኩታውን ቱቢት አስመትቶ፣ ሁለመናውን ማቅ አልብሶ…

ጥቁር ቆቡን አርጎ፣ ጥቁር ከረባቱን አስሮ፣ ጦቢያ አነባ፣ አለቀሰ ‹‹እግዚኦ በበጊዜሃን›› ዘምሮ

‹‹ምነው ሰላሌ? ምነው ፍቼ? ምነው መንጠራ?…›› እያለ አንድ… ሁለት… ሦስት… ሙታንን ቆጠረ

ተረኛውን ሟች፣ ከቃሬዛ ላይ እየማተረ፤

ምነው ሰላሌ? ምነው ፍቼ? ምነው መንጠራ?

የዋሽራዋ ባለቅኔ እናት፣ ቅኔዋን ቋጥራ ተደጃችን አፈሰሰችው ተመንጠራ-

እውነትም ቀለም ገባው ልጇ እሳት ሆነላት ቀኝ እጇ!

ምነው ሰላሌ? ምነው ፍቼ? ምነው መንጠራ?

ያ መልካም ስምህ፣ በበላዔ ሰብ ይጠራ?

¨Salaalee yaa Salaalee Biyyaa naghenyii daararee¨¨

 ማለት ከእንግዲህ ቀረ?

ቶርባን አሼን፣ አብሮ መጠጣት ተነወረ?

 አባ ቶርቤ፣ አባ ሸኔ

ይህን አያውቅም ወገኔ

አርቲ ቡርቲ ገለመሌ ይህን አያውቅም ሰላሌ!

Ni daarbitti yeroonni…

Xuriidha cubbuunii

Ni murtiisa waqni

Ni tortooraa gadheenni

Ni lalissa dhuganii

Ni jabaataa tokumani!!!

አቦ የሚባል ቅዱስ እንጂ፣ የዛር ውላጅ እኛ አናውቅ

 ደም አፍስሶ የሚጠጣ፣ አገር ምድር እሚያስጨንቅ

 ብሎ ብሎ ሰላሌ ገባ? ከጦቢያ አርበኞቹ አገር

 ከነታደሰ ብሩ፣ ከነኃይለ ማርያም ማሞ መንደር?

ከነአበራና ከነአስፋው ወሰን ካሣ ኬላ?

ከነገለታ ቆርቾ ከነሙሉ አሰኑ ፊላ?

 ከነእምአእላፍ ኅሩይ ከነበሼ ልጆች አምባ

 ከነሸንቁጥ ዥግኖቹ ሰፈር፣ ከነአሼ ሩፎ ጉባ

ከነሞሩ ሳንዳፋ ቀዬ፣ ከሸበሎቹ፣ ከእንሳሮዎቹ፣ ካዲስጌዎቹ ደጃፍ

 ከቀለም ቀንዱ ከአለ ፈለገ ሰላም ጨፌ፣ እንዴት ለግላጋ ወጣት ይርገፍ??

 በእኩለ ሌሊት ይታረድ?? በእኩለ ሌሊት ይጨፍጨፍ??

ይህን የዛር ውላጅ፣ ደም የጠማውን እብድ ውሻ

በተክልዬ ጸበል አውጡት፣ ከተደበቀበት ዋሻ፤

ሰላሌ የኢትዮጵያዊነት ማኅተም፣ ያብሮነት ቀለበት እንጂ

ጊዜ የሰጠው ቅል አይሰብረውም፣ እምዬ ጦቢያ ፍረጂ!!!!

ከሸበሎቹ፣ ከእንሳሮዎቹ፣ ካዲስጌዎቹ፣ ከደሮዎቹ

 ከግራሮቹ፣ ከጃርሶዎቹ፣ ከኩዩዎቹ፣

ከሌመን፣ ከደገም፣ ከኤጄሬዎቹ አምባ

ዳግም ኡኡታ ይቅር፣ ዳግም አይፍሰስ እምባ፤

 ከነአለቃ ጥበቡ፣ ከነተሰማ ግጽው ሰበካ

 ከነማርጋ ዳራሳ፣ ከነአበበች ጎበና መልካ

 ከነአብቹ የማይጨዉ ጀግናችን ዋርካ

 ከሙገር፣ ከጉለሌ፣ ከግምቢቹ ቡርቃ

መርዶ አይምጣ፣ ሃዘን ሽብሩ ይብቃ!!

ሰላሌ የኢትዮጵያዊነት ማኅተም፣ ያንድነት መቀነት እንጂ

አሽክላ የበላው ማድጋ አይደለም፣ እናት አገሬ አርግጂ!!

የለም… የለም አይሆንም፣ መንጠራ የጥንት ስምክን ጠብቅ

 ይህን የውርደት ካባ አውልቀህ፣ ወጣቱን በቀለም አጥምቅ፤

 ጀግና ሰልጥኖ ዘምቶብሃል፣ ልጅ ቦርቆ አድጎብሃል

 ጨርቅና ፓሎኒ ኳስ፣ ስንትና ስንት ሺህ አልቆብሃል

ይህ የዛሬው ቦረንትቻ ፣ ደም ደም ማለቱ ያጠላብሃል፤

 ምነው ሰላሌ? ምነው ፍቼ? ምነው መንጠራ?

ያ መልካም ስምህ፣ በበላዔ ሰብ ይጠራ?

የሜጫው የቱለማው ጥንስስ ጌሾ

የኃይለማርያም ገመዳ እትብትመነሾ

 ሰላሌኮ ነው፣ ውልደት ብቅለቱ

‹‹ኢትዮጵያዊ ኦሮሞነት፣ ni lalissa! ይሸግናል!…›› ያለበቱ

 እስር ቤት ተቀጥቅጦ፣ ማቆ… ማቆ… የሞተበቱ፤

¨Salaalee yaa Salaalee Biyyaa naghenyii daararee¨¨

 ማለት ከእንግዲህ ቀረ?

ቶርባን አሼን፣ አብሮ መጠጣት ተነወረ?

አባ ቶርቤ፣ አባ ሸኔ

ይህን አያውቅም ወገኔ

 አርቲ ቡርቲ ገለመሌ

 ይህን አያውቅም ሰላሌ!

 Ni daarbitti yeroonni…

 Xuriidha cubbuunii

Ni murtiisa waqni

Ni tortooraa gadheenni

 Ni lalissa dhuganii

Ni jabaataa tokumani!!! (ሰላሌ  ዩኒቨርስቲ  ውስጥ  ለተሰዉት ወጣቶች   መታሰቢያ፣ ሰኔ 29 ቀን 2011 ዓ.ም.  አዲ ስ አበባ)

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top