አድባራተ ጥበብ

የአብርሃም አፈወርቂ ስንኞች

ሙዚቃ ረቂቅ እና ምትሀታዊ ኃይል ነው። ሙዚቃ የሰው ልጅ የህይወቱን ልዩ ልዩ መልክ የሚገልጽበት ነው። ችግሩን፣ ሐዘኑን ወይም በህይወቱ የሚያካሂዳቸውን እንቅስቃሴዎች የሚያንጸባርቅበት መሳሪያ ነው። የመግባቢያ ቋንቋውም ጭምር ነው። የመልዕክቱ ማስተላለፊያ ብቻ ሳይሆን የህይወቱ መምህርም ጭምር ነው፤ ብለው ከፍ ያለ ማእረግ የሚሰጡትም ጥቂት አይደሉም። ብቸኝነትን ያሸንፋል። ሆነ ብለህ ላለመስማት ብትፈልግ እንኳን እንድትሰማው ያስገድደሃል። ድንበር አይገድበውም፤ ድንበር ተሻጋሪ እና ድንበር የለሽ ነው።

ሙዚቃ እንደየ አድማጩ የራሱ ግዜና ቦታ አለው። በራሱ ጊዜና ቦታ እንድታጣጥመው ያደርግሃል። የራሱ ጊዜና ቦታ አለው ያልኩበት ዋናው ምክንያት ወቅትን እንድታስታውስበት ስለሚያደርግ ነው። አንዳንድ ዘፈን ዛሬን አጣጥመኸው ያልፋል። ከአምስት ወይም ከአስር ዓመታት በኋላ ደግመህ በአጋጣሚ ስትሰማው ግና የመጀመሪያውን ወቅት አለማስታወስ ከባድ ያደርገዋል።

ሙዚቃውን ስትሰማ ምን ዓይነት ጊዜ ነበር?፣ በዙሪያህ የነበሩትን ሰዎች፣ የአየር ሁኔታው፣ የሳብከው መአዛ፣ ያጣጣምከው ምግብ፣… የመሳሰሉትን ከኋላ ጎትቶ ፊትህ ያመጣብሃል። በእኔ አገላለፅ ሙዚቃ ማለት አንድ ራሱን የቻለ የማስታወሻ ደብተር ነው።

አብርሃም አፈወርቂ በርካታ አድናቂዎች፣ አድማጮች እና ተከታዮች ያሉት ድምጻዊ ነው። በርካታ ዘመነኞቹ “የሙዚቃን ጥቅም ያወቅኩት በተወዳጁ የትግርኛ ሙዚቃ አቀንቃኝ አብርሃም አፈወርቂ አማካኝነት ነው” ብለውለታል። የአብርሃም ዘፈኖች በስንኞቻቸው ያዘሉት መልእክት ያጋጠሙ እና የሚያጋጥሙ ነገሮች ያሉባቸው ናቸው። ህልም ሳይሆን መሬት ያለን እውነት ያቀነቅንልናል። ዘፈኖቹ የህይወት ፍልስፍና እንዴት እንደሆነ እንድንመለከት ያደርጉናል። ለምሳሌ ተስፋ በምንቆርጥበት ጊዜ፣ ሀዘን በሚሰማን ጊዜ፣ ደስታ በሚሰማን ጊዜ፣ ሰውን በምንናፍቅበት ጊዜ፣ ለመፅናናት ወይም ደስታ ለማግኝት፣… ስንል በዘፈኖቹ አማካኝነት ህይወት ምን ዓይነት መልክ እንዳላት እንመለከትበታለን። “ምንባር” (መኖር)፣ “ተስፋ ‘ያ ስንቀይ” (ተስፋ ናት ስንቄ)፣ “ግዜ” (ጊዜ)፣ “ዝኣምና ሃይማኖት ፍቕሪ ‘ያ ሽማ” (የማምናት ሃይማኖት ፍቅር ነው ስሟ)፣ “ፍቕሪ ‘ዩ መንገደይ” (ፍቅር ነው መንገዴ)፣ “ሰማይ”፣ የመሳሰሉትን ለዚህ አባባል እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል። የነዚህ ዘፈኖች ይዘት ተቀራራቢ ነው። ተስፋ፣ መኖር፣ ሰላም፣ ፍቅር ወዘተ… የመሳሰሉ ጉዳዮችን ያነሳሉ።

“ሓሳብና እዋሰብ -ሽግርና ይመሳሰል

ትምኒትና ሓደ ካብ ኮነ፤

ሰብ ሰብ’ዩ ዝደሊ- ጽምዋ ሕሱም’ዩ

ሂወት ፍቐድለይ -ምሳኺ መሪጸ’የ ኣነ”

(ሃሳባችን ውስብስብ ችግራችን ተመሳሳይ

ምኞታችን አንድ ዓይነት መሆኑ ካልቀረ

ሰው ነው የሰው ፍላጊ ምን ሊበጀን መለያየት

ልቤ ፈቃድሽን ይለምናል ቆየ አንቺን ካፈቀረ)

የግጥምን ትርጉም አስቸጋሪነት እምትረዱ እንድትረዱኝ በመማጸን ልቀጥል። ለሰው መድሃኒቱ ሰው ነው የሚለውን ሐገራዊ ብሂል በፍቅር ስም ያመጣዋል። “ሰው ከሰው በላይ ምን ይፈልጋል?”፣ “ሰው ያለ ሰው ምንድነው?” ግዙፍ ጥያቄ ነው። የሰው ልጅ ጠላት ራሱ የሰው ልጅ መሆኑም የታመነ ነው። ገጣሚው ስንኙን ሲያደራጅ ፍቅር እፈልጋለሁ ወይም ሴት ልጅ እከጅላለሁ ያላለበት ምክንያት፤ እንደዚህ ከፍ አድርጎ በመመልከቱ ይመስላል።

“ምንባር” (መኖር) እንዲሁም “ትምኒተይ” (ምኞቴ) የተሰኙ ሁለቱ ዘፈኖቹ በግጥም ይዘታቸው የማይነኩት የሕይወት ክፍል የለም።

ምንባር ወይም መኖር ከሚለው እንጀምር፤

ፊት ጩራ ወጋሕታ ኣዕዋፍ ክዝምራ…

ከም ትማል ከምፅባሕ መዓልተይ ጀሚራ…

ምንባር…

ንጉሆ ንጉሆ ምጅማር።

(የንጋት ፀሐይ ጮራ ፊት ወፎች ሲዘምሩ

እንደ ትናንት እንደ ነገ ዛሬዬን ሊያስጀምሩ

መኖር…

በንጋት በንጋት መጀመር)

ከዚህ ዘፈን ብዙ ነገሮች ማንሳት ይቻላል። የዘፈኑ ርዕስ “ምንባር” (መኖር) ሆኖ፤ በውስጡ ብዙ ነገሮችን አካትቷል። ወፎች ጥዋት ላይ ከጎጇቸው ወጥተው አዲሱን ቀን ሲቀላቀሉ በፈለጉት መንገድ በተስፋ ለመኖር ይንጫጫሉ። ጫጩት ወፎችም (ልጆቻቸው) እናቶቻቸውን ማታ በፉጨት እስከሚቀበሏቸው በፉጨት ይሸኟቸዋል። እግረ-መንገዳቸውም ለሌላኛው ፍጡር ወይም ለሰው ልጅ ንጋትን ያበስራሉ። ከእንቅልፍ ይቀሰቅሳሉ። አዲሱን የተስፋ ቀን ያስጀምራሉ።

ሌላው የግጥሙ አንድምታ ጅምር አያልቅም የሚል አመክንዮ ያመጣል ‹‹በንጋት በንጋት መጀመር›› ሲል የሚያልቅ ወይም ያለቀ ሕይወት የለም የሚል አመክንዮ ይታጠቃል። የትላንትን ኪሳራ ረስቶ ለአዲስ ጅማሬ መነሳትን ይሰብካል።

አብርሃም በዚህ የዘፈን ግጥም የሚያነሳው ዋናው ርዕሰ ጉዳይ መኖር ነው።

“ምንባር ንጉሆ ንጉሆ ምጅማር”

(ለመኖር ንጋት ንጋት መጀመር) ይላል።

ማለዳ በወፎች ዝማሬ ስንነቃ ነጋ እንላለን። አእምሮአችን ትናንት ያቀድነውን ለመስራት በአዲስ መንፈስ እና ጉልበት ይነሳል። የትላንቱ እቅድ በማለዳ ተስፋ ሊሻሻል የሚችልበት ገጠመኝም ብዙ ነው። በዚህ መሃልም ተስፋ ውስጣችንን ይቆጣጠራል። ምክንያቱም ተስፋ አንዱ የህይወታችን መንፈሳዊ ምግብ ወይም ስነ-ልቦናችን የሰጠን ስጦታ ስለሆነ ነው። ተስፋ ከሌለህ ስራህ ውጤት አይኖረውም፤ ቢኖረውም አርኪ አይሆንም።

ወፎች ጠዋት ላይ ሀ ብለው መኖር ሲጀምሩ በራሳቸው ቋንቋ ብዙ ዕቅዶችን አቅደው ነው። ችግር ይገጥመኛል ብለው ሳያስቡ ሁሉንም ነገር በተስፋ ይጠብቁታል፤ ‹‹የሰማይ አእዋፋትን ተመልከቱ›› እንዲል መጽሐፉ፤ ሰውም ልክ እንደ ወፎቹ ችግር ያጋጥመኛል ሳይል ለነገ፣ ለቀጣይ ሳምንት፣ ለሚመጣው ዓመት… ብዙ ያቅዳል። ምናልባት “በማንኛውም ጊዜ ማቀድ አይችልም ወይ?” የሚል ጥያቄ ከተነሳ፤ መልሱ “አዎ ይችላል!” ነው። በውጣ ውረድ በዛለ መንፈስ ከታቀደው ይልቅ በአዲስ ቀን በውብ ዝማሬ ታጅቦ የታቀደው ይበልጥ ሚዛን ቢደፋ የሚገርም አይሆንም።

ሰናይ ሓሲብና ሰናይ ክንፅውዕ፤

ብርሃን ንጉዕዘይ ኢልና…

ተስፋ ሽግና ንወልዕ፤

ኣብ ውሽጥና ኣሎ ሓይሊ ከውሒ ዘልምዕ።

(በጎ እንስራ ሰናይ አስበን

ብርሃን ለጉዞዬ ብለን…

ይለኮስ የተስፋ ችቧችን

አለት የሚያለመልም ኃይል አለ ውስጣችን)

ውብ ስንኞች ናቸው። የስሜትን ኃይል ያንቀሳቅሳሉ። “ሰናይ” ከግዕዝ የተወሰደ ቃል ነው። ትግርኛ ቋንቋም ከግዕዝ በመቀበል እየተገለገለበት ይገኛል። አማርኛ ቋንቋም ይጠቀምበታል። በአማርኛ “መልካም፣ በጎ” የሚሉ ሌሎች ተተኪ ቃላት አሉት።

“ሰናይ ሓሲብና ሰናይ ክንፅውዕ” (ሰናይ አስበን ሰናይን እንጥራ) ማለት በውስጣችን መልካም ነገርን እያሰብን መልካም ነገርን ስንጠራ፤ መልካም ነገር ይዞልን ይመጣል።

መልካም ስንሆን ሁሉም መልካም ይሆናል። ምክንያቱም አንተ መልካም ሰው ሆነህ በመልካምነትህ ሌላውን ትማርካለህ። ሌላው መልካም ከሆነ ደግሞ ካንተ ጋር የመቀራረብ ፍላጎቱ እየጨመረ ይሄዳል። በሂደትም አብሮነት ይነግሳል። የህይወት ጉዞህም ወደ ምትፈልገው ምዕራፍ ያደርስሃል።

 ብርሃን ለጉዞዬ ብለን…

እንለኩስ የተስፋ ሻማ

ውስጣችን ኃይል አለ – አለት የሚያለማ)

ጉዟችን ጨለማ ቢሆን እንኳን በተስፋ ችቦ እናደምቀዋለን። ተስፋ ብርሃን ያለው ችቦ ነው። ምትፈልገውን ነገር በጉጉት እና በተስፋ ካላከናወንከው የመሥራት ፍላጎትህ ወይም የሰራኸውን ውጤት የማየት ዕድልህ ሊቀንስብህ ይችላል። ተስፋን ካልሰነቅን ግን ትልቁ የስኬታችን መንገድ ነው ብለን ወደምናስበው ለመሄድ፤ መጀመር አንችልም።

ውስጣችን ኃይል አለ አለት የሚያለማ ሲል በቅድሚያ በውስጣችን የምንተማመንበት ተስፋ ካለ ከባድ የሚባል ነገር እንደሌለ መግለጹ ነው። ተስፋ ራሱን የቻለ ኃይል ነው። ተስፋ እምነትን ይወክላል። እምነት ትጋትን ያበዛል። ትጋት ስኬትን ያመጣል።

ተስፋ እና እምነት ካለን በውስጣችን የራስ መተማመንን ቋጥረን፣ አንድ ወደሚያደርገን ቦታ በራሳችን መንገድ እንጓዛለን፤ አጠቃላይ የዘፈኑ መልእክት ነው።

ትምኒተይ (ምኞቴ)

በባህላዊ የትግርኛ የአዘፋፈን ስልት ከሚዘፍናቸው ዘፈኖች አንዱ የሆነው “ትምኒተይ” ወይም በአማርኛው ፍቺው “ምኞቴ” በተሰኘው ግጥም ላይ ያለው እኔ ባይ ገጸ ባህርይ ‘እንደ ወፍ በርረሽ ካለሽበት ቦታ ነይልኝ’ ይላታል። እዚህ ጋር ያለው የወፍ ምስስሎሽ በሌላ ዘፈን ተደግሟል። ሆነ ብሎ ከሆነም መልእክቱን ሊያጠናክርበት ፈልጓል በደመነፍስ ከሆነም ገጣሚው ደጋግሞ የወፍን ባህርይ በመመልከት ፍቅር አድሮበታል የሚል ድምዳሜ ላይ ያደርሳል። ሆነም አልሆነም እኛ እንቀጥል።

‘እንደምናፍቅሽስ ታውቂ ይሆን?’ እያለ ሲያስታውሳት ልዩ ልዩ ቦታዎችን በማንሳት ነው። በቦታዎቹ ውስጥ ደግሞ የሚያፈቅራትን ልጅ ይፈልጋታል። ዘፈኑ ከመጀመርያ እስከ መጨረሻ ሲደመጥ ሲፈልጋት እንጂ ሲያገኛት አይሰማም። ቀድሞ በቀጠራት ቦታ ይፈልጋታል።

አብርሃም በዚህ ዘፈኑ ፍቅረኛውን ለማግኝት በሚያደርገው ጉዞ ልዩ ልዩ የኤርትራን መንደሮች ያካልላል። ሁሉንም አዳርሶ ሳዋ የወታደሮች ካምፕ ውስጥ እንዳለች ይሰማል። በሳዋ ፍለጋውም ሳይሳካለት በከረን ከተማ ሂጃብ ተሸፍና ያያታል።

የዘፈን ግጥሙ በተራኪ አካሄዱ የእያንዳንዱን ኤርትራዊ ወጣት የሕይወት ጉዞ ያስቃኛል። በዚያ የኑሮ ባህር ያልቀዘፍነውንም ቢሆን በምናብ እንድንቀላቀላቸው ያስገድዳል።

እኔ ባይ ተራኪ ገጸ ባህሪው በምፅዋ ወደብ ዳርቻ በባህሩ ወጀብ ታጅበው የዘላለም ቃልኪዳን ሲገቡ የነበራቸው ገጠመኝ ይታወሰዋል። ‘እባክሽን ንገሪኝ ያለሽበትን ቦታ’ ይላታል። ‘በቃልኪዳኔ መሰረት እየጠበኩሽ ነው’ ይላታል።

ዛሬ ሌሊት በህልሜ በጥንቷ የአዱሊስ ከተማ አክሱም ሀውልት ስር ቁጭ ብለሽ አየሁሽ እያለ ያዜምላታል።

የግጥሙን አወራረድ ተመልክተን የዘፈነላት አንዲት ተፈቃሪ ሴት ናት ብለን እንድንደመድም አያደርገንም። ኤርትራም ኢትዮጵያም ውስጥ ያሉ ሴቶችን ገጠመኝ ማንሳቱ፣ የቀደመውን ታሪክ ለማስተሳሰር የፈለገ ያስመስለዋል። ለዚህ አባባል ማስረጃ የሚሆነው ለገጣሚው አክሱምን የሚተካ መናገሻ ቦታ ኤርትራ ውስጥ መፈለግ ለምን ተሳነው የሚለው ጥያቄ መልስ ነው። ከዚህ በመነሳት ተፈላጊዋ ፍቅረኛውን የታሪክ ነገራ ሚና እና መሸፈኛ በማድረግ የደበዘዘውን ታሪክ እንዲጎላ አድርጓል። ከኦሪት ጀምሮ አንድ የነበረው፣ በባህል እና በታሪክ የተሳሰረው ሕዝብ መከፋፈሉ የቆጨው ይመስላል። “ትምኒተይ” (ምኞቴ) በተሰኘው ነጠላ ዘፈኑ አማካኝነት አንድነትን እየሰበከ እንዳለ ይሰማኛል።

ትምኒተይ በተሰኘው የዘፈን ግጥም የተወሰኑትን ስንኞች በጨረፍታ እንያቸው፡-

“ዋይ ተራኢኽኒ ሎሚ ምሸት

ከረን ኔርኪ ተሸፊንኪ ልዌት”

(ወይኔ ዛሬ ምሽት ዐየሁሽ

ከረን ነበርሽ ሂጃብ ተሸፍነሽ)

በከረን ሂጃብ ለብሳ ያየበት ምክንያትም፤ አብዛኛዎቹ ከረን ያሉት ህዝቦች የብሌን ብሄረ-ሰብ ሰዎች ናቸው። በብሌን ማኅበረ-ሰብ ያሉ ሴቶች የሚለብሱት ልብስ ቀይ ሂጃብ ነው። አብርሃምም ከረን ውስጥ ያሉት ማኅበረ-ሰብ ለኛ (አድማጮቹ) ምን ዓይነት አለባበስ እንዳላቸው ለማሳየት የሚወዳት ልጅን የነሱን አለባበስ በማልበስ ነው እያሳየን ያለው።

“ብሕልሚ ርኤኪ ሎሚ ለይቲ

ተፀጊዕኺ ናይ ኣኽሱም ሓወልቲ

ኣብ አዱሊስ ነይርኪ መሬት ጥንቲ

እንታይ ርኢኺ ናቕፋ ዓዲ ርስቲ”

(በህልም ዐየሁሽ ዛሬ ምሽት

ተጠግተሸ ከአክሱም ሐውልት

በአዱሊስ ነበርሽ መሬት የጥንት

ምን ዐየሽ በናቅፋ የአገራችን ርስት)

እነዚህ አራት ስንኞች ከላይ ከጠቀስኳቸው ስንኞች የተለዩ ናቸው። የሚያነሱት ኤርትራ ውስጥ የሌለን ቦታ ነው። ቀደም ስል እንደገለፅኩት “የአብርሃም ፍቅረኛ አክሱም ድረስ ምን አስመጣት?” ነው ጥያቄው። ወይም ደግሞ ድምፃዊው ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ቦታዎች ለምን አክሱምን ብቻ መርጦ ለመዝፈን ቻለ? ለምንስ አዲስ አበባ፣ ጎንደር፣ አዳማ እያለ አልጨመረበትም? እነዚህን ጥያቄዎች ማሰብ ይገባል።

አክሱም የኢትዮጵያ መሠረት ናት በሚለው ተረክ መሰረት፤ የአክሱም ግዛት ኤርትራን ጨምሮ እስከ ደቡባዊ አረብ ይዘልቅ ነበር በሚለው የታሪክ ማስረጃ መሰረት፤ የተሰናኘ ይመስላል። እዚህ ላይ አዱሊስና መጠራ የአክሱም አካል ሆነው ዋነኛ የንግድ ማስተላለፊያ እንደነበሩ ስንጨምርበት ጥርጣሬአችንን ወደ እውነት ያስጠጋዋል።

“በህልም ዐየሁሽ” ያለበት ምክንያትም ሊሰመርበት የሚገባ ትልቅ ጉዳይ ነው። ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ከተለያዩበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ሁለት አገሮች ናቸው። ለዛም ነው በ“ህልም አየሁሽ” ያለው። ምናልባትም ከእንቅልፉ ቢባንን ኖሮ የሚወዳት ልጅ ከአክሱም ሐውልት ጎን ተጠግታ ሳይሆን አስመራ ላይ ከተኛበት ቤት ውስጥ ከአጠገቡ ቁጭ ብላ ፀጉሩን ስትዳብሰው ነበር የሚሆነው። ስለዚህም በሀሳቡ ወይም በህልሙ አንድ የነበረው ህዝብ ወይም አገር ሲታየው ነበር ማለት ነው። በሌላ አገላለፅ አሁን ያለውን የሁለቱም አገሮች ነባራዊ ሁኔታን በማየት “ታሪካችን እኮ እንደዚህ አልነበረም!” እያለ ለማስታርቅ እየጣረ ያለ ይመስለኛል።   

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top