አጭር ልብወለድ

ከስነ-ቃል

በአንዱ የገጠር ቀበሌ ነው። ጥቂት ጎረምሶች የአንዱን ሀብታም ገበሬ በግ በመስረቅ አርደው ይበሉና የበሉበትን ሰው በቅኔ ለመዝለፍ ተነሳሱ። ለተዘራፊው ያዘኑለት በመምሰል በሰም ለበስ ቅኔ እንዲህ ሲሉም ተቀኙ፡-

 እርስዎም ሳይነግሩን እኛም ሳንፈልግ አሁን የት ይገኛል እንደእርስዎ በግ ባለበጉ ገበሬ የጎረምሶቹ ቅኔ ገብቶታል። ይሄ ነው የሚለው ማስረጃ በማጣቱ እንጂ አርደው እንዳጣጣሙት አውቋል። በተከታዩ ስንኝ ‹‹በግ›› የሚለውን ስድባቸውን እንዳልሰማ በማለፍ ሥራችሁን ደርሼበታለሁ ይላቸዋል። ቆየ ሰነበተ ከጠፋብኝ በጉ እስቲ እየጋጣችሁ እናንተም ፈልጉ።

መናጆ

በርካታ በጎች ያሉት ሰው ከበጎቹ መካከል አንዷን ነጥሎ መሸጥ ፈልጓል። ለመሸጥ ያሰባትን በግ ከመንጋዋ ነጥሎ ለመውሰድ ግን አልተቻለውም። የበግ ተፈጥሮ እንዲያ አይደለም። በግ ተከታትሎ ነው መንገድ የሚወጣው፣ በግ በደቦ ነው የሚጓዘው። በግን በአዲስ ጎዳና ለማራመድ የከጀለ ማንም ሰው የሚጠበቅበት ከመካከላቸው አንዷን ጎተት አድርጎ በታቀደው ቦታ እንድታልፍ ማድረግ ነው። በር ከፋቿን ያዩት ሁሉ በየተራ ተግተልትለው ያልፋሉ። ተከታትለው ያዘግማሉ።

 ይህንን የተረዳው በግ ነጋዴ፣ የሚሸጠው አንዷን በግ ብቻ እንደሆነና ቀሪዎቹን ይዞ እንደሚመለስ እያወቀ፣ ሌሎች ሦስት አራት አጃቢዎችን (መናጆዎችን) ይዞ ወደገበያ ይወጣል። የምትሸጠው በግ የታለመላትን ተግባር እስክታከናውን የተቀሩት ከገባችበት ሲገቡ ወደ ወጣች ወረደችበት ሲመላለሱ ይውላሉ። ይህ ተግባር የሚያቆመው የባለቤቱ አላማ ከግብ እስኪደርስ ነው።

ይህንን ተግባር በኑሯችን ላይ እያስተዋልነው ያለን አይመስላችሁም? ቁጥራችን ጥቂት የማይባለው በሰው ሀሳብ እየተወዘወዝን፣ በሰው ኑሮ አቅል እያጣን፣ በሰው ጌጥ እየተሽቀረቀርን፣… አይመስላችሁም? ከትላንት በስቲያ በሰሜን፣ ትላንት በምዕራብ፣ ዛሬ በደቡብ ሀሳብ የምንናጥ አቅጣጫችንን የእለቱ ነፋስ የሚወስንብን፣… በፖለቲካ ማዕበል ተንጠን እፎይ ሳንል የሀይማኖት ሱናሚ ጠራርጎ አቅጣጫ የሚያስቀይረን፤ በዘረኝነት ሴራ ተተብትበን ከርመን የዘለፋ፣ የስም ማጥፋት፣ ነፋስ የሚጠራርገን፣ አንዱ አላማውን እስኪያሳካ ጉዳይ አስፈጻሚው የሚያደርገን በራሱ ቦይ የሚያፈሰን፣… አይመስላችሁም?

ፍተላ

በአንድ ቲያትር በሚያስተምር መንግስታዊ ተቋም የሚሰለጥን ሰው ነው። ፒሪሪም ፓራራም ለተባለ ፊልም በተዋናይነት ይታጫል። ታጭቶም አልቀረም፤ ስክሪን ቴስት አድርጎ ያልፋል። ይተውናልም…

 የተሰጠችው ቦታ አጠር ያለች ብትመስልም ረዘም ላሉ ደቂቃዎች ለጥቂት ቀናት ይቀረጻል። ፊልሙ የዝግጅት ጣጣውን ጨርሶ ለእይታ ሲበቃ ሰዎችን እንዲጋብዝ የተሰጠው ወረቀት ፊልሙ ላይ ካለው ቦታ የበለጠ ነበር። የቀረው ዘመድ አዝማድ የለም። አብረውት የሚማሩ በሙሉ ታዳሚዎች ናቸው።

 ለአብዛኞቹ እሱ ለጋበዛቸው እድምተኞች አንድ ቀን ከምናምን ሙሉ ስላሳለፈው አድካሚ የቀረፃ ጊዜ ተርኳል። ስክሪፕቱን ለመያዝ የፈጀበትን ጊዜ አውርቷል። የዳይሬክተሩን ቁጡነት ለፍፏል። ስለተዋንያን፣ ስለካሜራ ደስኩሯል።

አሁን ፊልሙ በመታየት ላይ ነው። አጋማሹ ላይ የደረሰ ቢሆንም ተዋናዩ እስካሁን አልታየም። ከግማሽ አልፎ ወደመጠናቀቁ ሲቃረብ ተዋናዩ ውልብ ብሎ ጭልም ቢልም፣ ጥቂት ቃላትን ተናግሮ ድምጹን ቢያሰማም ያላስተዋሉት በዙ። “ታይቷል!”፣ “አልታየም!” እያሉ የሚከራከሩ በረከቱ።

በማግስቱ የተቀረጸው ብዙ እንደነበር ነገር ግን ሰዓት ለማሳጠር እና በአንዳንድ የኤዲቲንግ ስህተቶች ምክንያት በዚህ መልኩ እንዳጠረ … ይህ በመሆኑም ፕሮዲውሰሩን እና ዳይሬክተሩን ጨምሮ በርካታ የፊልሙ አባላት እንዳዘኑ ለወዳጆቹ ለማስረዳት እያሰበ ወደሚማርበት ቦታ አዘገመ። ሆኖም ገና ምክንያቱን ከመግለፁ በፊት፣ ችግሩን ከማስረዳቱ በፊት፣ ምንም ከማለቱ፣ ምንም ነገር ከማድረጉ በፊት ጥቁር ሰሌዳው ላይ የተጻፈውን ሲያነብ ነው ቅስሙ የተሰበረው፣ የተበሳጨውና የተናደደው። ነገርየው የተባለው እሱ ላይ በመሆኑ እንጂ ባይሆን ኖሮ ከተከት ብሎ በሳቀ ነበር። ጥቁሩ ግድግዳ ላይ በነጭ የተነቀሰው ጽሑፍ እንዲህ የሚል ነው።

 “የአፋልጉኝ ማስታወቂያ ወዳጃችን እከሌ እከሌ ፒሪሪም ፓራራም የተባለ ፊልም ላይ ገብቶ የገባበት ስለጠፋብን ያለበትን የሚያውቅ ካለ ቢጠቁመን ወሮታውን የምንከፍል መሆኑን እንገልጻለን።”

ክር ባጭር

በድሮ ጊዜ ነው። በሀገር ወግ በሕግ እና በስርዓት ያሳደጓትን ልጃቸውን ላግባ ባይ ጠያቂ የበዛባቸው አባወራ ማንን ከማን ለይተው ለማን እንደሚድሯት ግራ ቢገባቸው ፈተና አዘጋጁ።

ፈተናው ጋቢ መስፋት ነው። አስፈላጊው መሳሪያ ሁሉ ተሟልቷል። ጋቢ፣ ክር፣ መርፌ ሁሉም ቀርቧል። ያፈቀራትን ሴት በእጁ ለማስገባት የጓጓው የአዳም ዘር ውድድሩን ጀመረ። ሁሉም ጥድፊያ ላይ ነው። ማንም ማንንም አያይም። አባት እና ልጅ ብቻ ሁኔታውን ይታዘባሉ።

ከቀረቡት ተወዳዳሪዎች ውስጥ ዐይኗ ያረፈበት ጉብል የግሏ እንዲሆን የሻተችው ልጃገረድ የወጣቱ አያያዝ  ባያምራት፤ ክሩን አንከርፎ ሲጎትት ሊውል መሆኑ፣ በዚህ ከቀጠለ ደግሞ እንደሚሸነፍ እና ለሌላ ልትሰጥ መሆኑ ቢገባት፤ እቃ ላነሳሳ በሚል ሰበብ ወደ ጉብሉ ተጠጋች። ጉድ ጉድ የምትል አስመስላም እንዲህ አለችው። “ሰውየው! ክር ባጭር።” ወጣቱም ምክሯን ሰምቶ ክሩን አሳጠረ። ቶሎ ቶሎ ሰፍቶም አሸናፊ ሆነ።

 እኛም እንድናሸንፍ ክር አሳጣሪዎች ይብዙልን! የምንገነባው ካሰብነው በላይ እንዳያስወጣን፣ የምናወራው እንዳያስሰለቸን፣ የምንጽፈው እንዳይንዛዛ ክር ባጭር አያሻንም?

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top