ጥበብ በታሪክ ገፅ

ታሪከ ሀዲድ ከተርኪስ ባቡር ጀምሮ

“…በመጀመሪያ ከአውቶሞቢልና ከሰረገላ በፊት የተርኪስ ባቡር (ሎኮሞቢል) በ1896 ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል፤ ይኸውም ከጀምጀም አዲስ አበባ እንጨት እና ግንድ በማጋዝ፣ ለቤት ሥራም ድንጋይ በማመላለስ፣… ምንም ባይፈጥን በየጊዜው የተቻለውን ርዳታ አድርጓል” ይላል በብላቴን ጌታ ማኅተም ሥላሴ ወልደ መስቀል የተዘጋጀው “ዝክረ ነገር” የተባለው ዝነኛ፣ ግዙፍ የምርምር ድርሳን።

በዚሁ ዝክረ ነገር በተባለው ግዙፍ መጽሐፍ የተጻፈውና “የተርኪስ ባቡር” የተሰኘው የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪ እንደተተረከለትም በወቅቱ የተቻለውን ድጋፍ ማድረጉን በብዙ ሌሎች ጸሐፍት የተጠቀሰ ነው። ለአብነት ያህል በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የተመለከተው የተርኪስ ባቡር ድርሳን “መንኮራኩሩ እጅግ ከፍ ያለ አገልግሎት መስጠቱ” እና ለቀሩትም መንኮራኩሮች ፈር ቀዳጅ  መሆኑ ይነገርለታል።  

እንዲያው የተርኪስ ባቡርን ምንነት በትንሹ ለማወቅ ያህል ያ በሸመገለው ዘመን የእንጨትና የግንድ ማጋዣ ሆኖ ሲያገለግል የነበረው ተሽከርካሪ በአውሮፓም ቆየትየት ባለው ዘመን እጅግ እንደጠቀመ ድርሳናት ያወሳሉ። ያ በድንጋይ ከሰል ይቀንሳቀስ የነበረ መጫኛ ምንም እንኳ እንደ አውሮፓውያኑ በእንፋሎት ወይም በናፍጣ እንዲሽከረከር፣ ሐዲድም የተዘረጋለት የዘመኑ ዘመናይ ባይሆን እንጨቱን፣ ድንጋዩንና ግንዱን ሌላውንም የወቅቱን ለማምረቻ ግብአት እና የማምረቻ ውጤት የሆነውን ሁሉ በማመላለስ ረገድ ትርጉም ያለው ተግባር እንዳከናወነ ይነገራል።

የዝክረ ነገር ትረካ በተርኪስ ባቡር ብቻም ከእልባት አልደረሰም። በዚህ ብቻም አላበቃም። ስለ “ምድር ባቡር” ም ያስነበበው አለ። እንዲህም ይነግረናል፡-

“…አዲስ አበባ ሳይቆረቆር ዋና ከተማው እንጦጦ ሆኖ በነበረ ጊዜ ከጅቡቲ ሐረር፣ ከሐረር እንጦጦ፣ ከእንጦጦም ነጭ ዓባይ ድረስ በሦስቱ ክልል ተመድበው ባቡር እንዲገባ የንጉሠ ነገሥቱ ምኞታቸውና ፈቃዳቸው በመሆኑ ለሙሴ አልፍሬድ ኢልግ የመጀመሪያውን ክፍል ኩባንያ አቋቁመው እንዲያሠሩ በመጋቢት 1 ቀን 1886 ዓ.ም. ውል ሰጡ” ይላል የተመራማሪው ድርሳን። ንጉሠ ነገሥቱ ያለው እንግዲህ የቀድሞውን ዝነኛውን ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ አፄ ምኒልክ መሆናቸውን ልብ ይሏል።  

በዚህም መሠረት ከጅቡቲ ድሬዳዋ ያለው መስመር ከተዘጋጀ በኋላ እንደገና በጥር 21 ቀን 1900 ዓ.ም. በቀድሞው ሚስተር ኢልግ እግር ዶክተር ቢታሊያን የሚባሉ ሰው ተተክተው ከጅቡቲ አዲስ አበባ ድረስ ላለው የምድር ባቡር ተግባር አዲስ ውል እንደተቀበሉ ያትትና ተፈላጊው የምድር ባቡር ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ አበባ ከተማ በ1909 ዓ.ም. ለመግባት እንደበቃ ይተርካል።

በመሠረቱም “ባቡር” ሲባል ለኢትዮጵያም ሆነ ለዜጎቿ ፍጹም ባይተዋር እንዳልሆነ ለመግለጽ ያህል ነው ይህን የብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀልን “ዝክረ ነገር”  መጽሐፍ ዋቢ ለማድረግ የተገደድኩት።

“ባቡር” ሲባል ከብረት በሚሠሩ በሁለት ሐዲዶች ላይ የሚጓዝ፣ ድሮ በድንጋይ ከሰል፣ በኋላ ሥልጣኔ ያዘመነው ጊዜ በተገኘበት ወቅት ደግሞ በነዳጅ፣ ማለትም በናፍጣና በመሳሰለው ወይም ውሎ አድሮ በኤሌክትሪክ ጉልበት በመገፋት የሚንቀሳቀስ የመጓጓዣ ብልሃት መሆኑን ለብዙዎች የሀገራችን ሰዎች እንደ እንግዳ ሊቆጠር ወይም አንዳንዴ ልንታዘብ እንደተሞከረው “ከሰማየ ሰማያት እንደ ወረደ ልዩ ፍጡር” ሊታሰብ የተገባው አይደለም።

ከአፄ ምኒልክ ቆርቋሪነት ጀምሮ የነበረ ነው። አፄ ኃይለ ሥላሴም በ1916 ዓ.ም. ገና ወራሴ መንግሥት ሆነው በባለ ሙሉ ሥልጣን እንደራሴነትም ሲሠሩ በነበረበት በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመነ ሥልጣን ወቅት በመጀመሪያ ወደ አውሮፓ ሲሄዱ ጅቡቲ ድረስ የተጓዙት በባቡር እንደነበር መጻሕፍት ይተርካሉ።

ይበልጡን ግን ምንም እንኳ ዘመኑ በሚጠይቀው ዘመናይነት “በቁጥር 1” ተርታ የሚሰለፍ ሆኖ ሊገኝ ባይበቃም በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን የትራንስፖርት ታሪክ ልዩ ምዕራፍ የሚጨብጠው እና አዲስም የሆነው በከተማችን በአዲስ አበባ ሐዲድ ተዘርግቶ በኤሌክትሪክ ኃይል ይንቀሳቀስ ዘንድ የተደረገበት ዓይነተኛ የመጓጓዣ ዘዴ ነው ብንል የተሳሳትን አይመስለኝም።

እያንዳንዱ መንግሥት በየትኛውም ሥርዓተ ማኅበር ቢሆን ወይም መጠሪያው የትኛውም ዓይነት ሆኖ ቢገኝ አንድ ልዩ ነገር በታሪክ ሠርቶ ያልፋልና ኢሕአዴግም ዐቅሙ በፈቀደለት መጠን  በዘመኑ ያከናወናቸው ሌሎች በርካታ ተግባራት በክብር እንደተጠበቁ ሆነው በዚህ በከተማ ባቡር ሐዲድ ዝርጋታ ረገድ ልዩ ነገር ማከናወኑ የታመነ ነው።

ይህን በዚህ አቆይተን ስንቶች ስለዚህ ቀላል የመጓጓዣ ብልኃት በሚገባ ዐውቀው፣ በግንዛቤ ጸድቀው ተገኝተዋል? ከሰሜን አዲስ አበባ ጫፍ እስከ ደቡብ አዲስ አበባ ጫፍ ያለው መስመርስ ተዘርግቶ ለስንቶች ግልጋሎት ሰጥቷል? ከምሥራቅ አዲስ አበባ ጫፍ እስከ ምዕራብ አዲስ አበባ ጫፍ ድረስ ያለውስ እንደተባለው መስመሩ ተዘርግቶ ለተጠቃሚ ክፍት ሆነዋል? ጦር ኃይሎች ሲደርስ የሚያቆም አይደለምን? እዚህ ላይ ሰዎች አንዳንዴ በተለይ በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት እንደ ሰርዲን ታጭቀው፣ በብዛት ታምቀው፣ እጅግም ተጨናንቀው ሲጓዙ የሚስተዋልበትን ኩነት በመመልከት ብቻ እንደ ዓቢይ የግንዛቤ ምስክር አድርጎ መውሰዱ እጅግም የሚያወላዳ አይመስለኝም።

“ምነው?” ቢባል አሁንም ከሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ውጪ ሰዎች ዛሬም እንደ ጥንቱ ከመሿለኪያ ወደ ሳሪስ የሚጓዘውን ሚኒባስ ታክሲ እየጠበቁና ተገፋፍተው እየተሻሙ ሲሳፈሩ ዕናያለንና!!

ይህ ለምን ይሆናል? ባቡሩ የሰው ጭነት በዝቶበት እንዳይከብደው አዝነውለት እንዳልሆነ መቼም በትክክል ልናረጋግጥ እንበቃለን። ነገርን ነገር ያነሳዋልና ከመሿለኪያ ወደ ሳሪስ ያለውን የባቡር ሐዲድ ብንመለከት አንድ ሰው በመኪና መንገዱን በመሐል አቋርጦ ለመሻገር ቢፈልግ በቅድሚያ ሳይፈልግ በግድ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ደርሶ ተሳልሞ መመለስ ያለበት መሆኑን እናያለን።   

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ በብዙ የአስተያየት ዓይነቶች ከበርካታ አስተያየት ሰጭዎች ይደመጣል። የሕዝብ አስተያየት ደግሞ ለአንድ የተግባር ሂደትም ሆነ አጠቃላይ ክንዋኔ ወሳኝነት አለው። የአሠራርን ጉድለት፣ የአካሄድን ስንፈት ለማረም ሕዝባዊ አስተያየት የማይናቅ ድርሻ ያበረክታልና!  

የቲኬት መቁረጫዎቹን በተመለከተም አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት የቲኬት መቁረጫ ጣቢያዎቹ አመቺ ቦታ ባለመሆናቸው የርቀታቸውን ሁኔታ በባቡር ላለመጠቀም  እንደ ምክንያት ያደርጋሉ። ከታክሲ ጋር ሲነጣጣርና ዋጋውም ሲታሰብ ልዩነቱ እስከዚህም ብዙ እንዳልሆነ የሚናገሩም አልጠፉም።  

አንዳንዶች ደግም “ከጫፍ እስከ ጫፍ እጓዛለሁ” ብሎ የሚሳፈረውን የሞባይል እና የሌላም ንብረት ቀበኛ በመፍራት ይህንንም እንደ መሠረታዊ ችግር ጠቅሰው ለማሳመን ይሞክራሉ። ሌሎች ደግሞ እንዲያው በደፈናው “ስላልተለመደ ይመስለኛል” ብለው ዝርዝር ሁኔታ ውስጥ ከመግባት ራሳቸውን ያቅባሉ።  

ከእነዚህ ሁሉ የተለየ ግን አንዳንዶች ለማለት የሚቃጡት ነው። ይኸውም “እኔ እንጃ… ሳየው ገና ተሳፈር፣ ተሳፈር አይለኝም… በሐሳቤም አይመጣልኝም… ወዘተ” የሚሉት ይጠቀሳሉ። ምኑን ሲያዩት ይሆን የባቡሩን ውበት ወይስ የነጂውን ደምግባት ሲያዩት ነው የማይዋጥላቸው? እነዚህን መሰል የአቻምና ሰዎች የዘመኑን ቀልጣፋ ትውልድ በአጉል አመለካከት የሚበክሉ ይመስለኛል።   

እንግዲህ የሚመለከተው የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ክፍል በሚገባ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባር ባገኘው መድረክ ሁሉ መሥራት ያለበት በዚህ ላይ መሆኑም አያጠራጥርም። የቲኬት ቦታው ሁኔታም ሊታሰብበት ሳይገባ አይቀርም። የሞባይሉ ቀበኛ ዕቅድም እንዲፈርስ ተገቢው እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል። የባለመብቱ አካል ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ደግ ደጉን ብቻ ዛሬ እያወራ ክፉ ክፉውን ለተነገ ወዲያ በቀጠሮ የሚያቆየው ከሆነ ግን የሚፈለግበትን ተግባር በኃላፊነት መወጣቱን አያሳየንም። እርሱንም አያስመሰግነውም። ይህን ቢያውቅ መልካም ይመስለኛል።  

ከዚህም በላይ “ሰው ራሱ ሲቸግረው ያኔ የግዱን ይመጣል” የሚለው አጓጉል የሸበተ የአስተሳሰብ ዘዬ ይዞ ችግር እንዲያስተምረው ለችግር ቅድሚያ ሰጥቶ የሕዝብ ግንኙነቱ ክፍል እራሱን ከተጠያቂነት ገለል ለማድረግ ቢሞክርም ይህም የሚያስኬደው ነው አይባልም። ከኃላፊነትም ነጻ ለመሆን ያልሆነ ምክንያት በመደርደር የሚወጡት ሊሆን አይችልምና!

በተረፈ ግን ምንም እንኳ ባቡሩ ራሱ በአውሮፓ ወይም በማናቸውም የባሕር ማዶ ሀገር አኳያ ሲታይ ተወዳዳሪ ነው ተብሎ ሊከራከሩለት ባይቻል የዚህ የከተማ ባቡር መመሥረት እራሱ እጅግ ታላቅ የድርሳን ምዕራፍ ይዞ ለታሪክ የሚቀመጥ መሆኑን ለመካድ መሞከር ከእውነት መራቅ ይመስለኛል። መንግሥት በዚህ ረገድ ያደረገው እጅግ አስመስጋኝ ተግባር ነው።

የከተማ ባቡር ሲባል “አዲስ ነገር” በመሆኑ ግን “ሕዝብ ዛሬም ቢሆን ስለ ጥቅሙ ያወቀውና የተረዳው ነው” ብሎ መመስከር አጉል እማኝነት ስለሆነ ተገልጋዩ ኅብረተሰብ ጠንቅቆ እንዲያውቀው ማድረግ የተገባ ይመስለኛል። ስለ ጥቅሙ በሚገባ ባለማወቁ እና ስለ ግልጋሎቱ ባለመገንዘቡ የትራንስፖርቱን ችግር ሊያቃልል አልበቃም። ለዚህም በተለይ በሥራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓታት ያለውን ሰልፍ መመልከት በቂ ምስክር ነው። ይህም መታሰብ ይኖርበታል። በተለይ በትምህርት ገበታ ያሉ ወጣቶች በባቡር ለመመላለስ ጉጉታቸው እጅግ የበረታ ሆኖ መታየቱን ከመታዘብ ብዙም አልራቅንም።

 በዚህም ምክንያት ከምሥራቅ አዲስ አበባ ጫፍ ወደ ምዕራብ አዲስ አበባ ከተማ ጫፍ፣ ከሰሜን የአዲስ አበባ ዳርቻ እስከ ደቡብ የአዲስ አበባ ከተማ ዳርቻ ይዘልቅ ዘንድ የሚወደደው የከተማ ባቡር መስመርም በቅርቡ ተጀምሮ የከተማውን አሳዛኝ የመጓጓዣ ትንቅንቅ እና መጨናነቅ እንደሚያቃልልና ከዚህም ጋር በተያያዘ መልኩ በመሐል የመኪና ማቋረጫ ብልኃት ተዘይዶለት፣ እንዲሁም እራሱ የከተማው ባቡር ጊዜ በሚጠይቀው መንገድ ዘመናዊነቱን ይጎናጸፍ ዘንድ ለማየት ተስፋችን ጽኑዕ ሆኖ ይቆያል። ለቀና ጉዞ ቀና አስተሳሰብ ማስፈለጉ ፈጽሞ የሚያጠያይቅ አይደለምና በዚህም ረገድ የቲኬት መቁረጫውን ቦታ እንኳ አሠራሩን በሚገባ አጥንቶ፣ በሥርዓት ተመልክቶ አስፈላጊውን ማድረግ የተገባ ነው እንላለን።        

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top