ታዛ ወግ

ባዕድ መንታ

ያሰበችው እና ያላሰበችው በአንድ ላይ ከሆኑ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በኋላ ፀሃይ ባየለችበት፣ ወበቅ በፀናበት አንድ ተሲያት ከሸለብታዋ ያነቃት ታላቅ ውጋት ነበር። ነፍሷን ሰቅዞ የያዛትን ስሜት መግለጫ ቃል፣ እርዳታ መጥሪያ ፊደል ቢጠፋት ለሰባት ትውልድ ብሶት ማሰሚያ የሚበቃ ጩኸቷን ለቀቀችው። 

“እሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪሪ…”

በዛ ቅፅበት እርሷ ከአፍንጮ በር ያሰማችው ጩኸት፤ በምን ተአምር ክንፍ አብቅሎ በአሰብ ሙቀት ሳይቀልጥ፣ በእንባ ሳይርስ እና የናቅፋ ተራሮች ጉልበት ሳይዝል፣ ተምዘግዝጎ አስመራ አባሻውል “ሆቴል ጨርሒ” ደርሶ፣ ክብሮም የተጎነጨውን ሜሎቲ ቢራ ትን እንዳስባለው እግዜር ይወቅ። ብቻ ይሄ ሲሆን የመጠጥ ቤቱ ኮመዲኖ ላይ በኤርትራ ባንዲራ ቀለም የተሰራ ዳንቴል ከለበሰ ናሽናል ቴፕ የምትንቆረቆር ፀሃይቱ ባራኪ እዛው ቴፗ ውስጥ ሆና ያጀባትን የባህል ባንድ “እስኪ ነቲ ሙዚቃ ደው አብልያ” አለች አሉ፤ እስቲ አንዴ ሙዚቃውን አቁሙ! ይሄንን ያዩ  የሰሙ በዚያ የነበሩ ሁሉ “እንታይ ጉድ” ኢሎም ተደነቖም ፤ ምን ጉድ ነው ብለው ተደነቁ አሉ።

እዚህም ያንን ጩኸት ሰምቶ የተደናገጠው ባሏ ሰለሞን የመኝታ ቤቱን በር በርግዶ ቢገባ እርሷ ሚስቱ በታላቅ ምጥ ተይዛ፣ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ከብቧት እነሆ በዚያ ታላቅ መሸበር ሆኖ ነበር።

ባሏ የሚስቱን ጭንቅ ሲያይ የገንፎ እህል ፍተጋ ላይ የሰነበቱ ተሰብስበው ቡና የሚጠጡ ጎረቤቶቹን ጠራ። ከሴቶቹ መሃል አዋላጇ እትዬ አሰገድ እየከነፉ ወደ እነ ሰለሞን ቤት ሲሄዱ ላያቸው አየር ላይ ከሚንሳፈፍ ነጭ ነጠላቸው ጋር መልአክ ይመስሉ ነበር። መኝታ ቤት ገብተው እዛች ድርስ እርጉዝ እግር ስር ቁጭ እንዳሉ የሰፈሩ ሴቶች “ማርያም ማሪያት” ዜማ የመንደሩ ሰማይ ላይ ሲናኝ ከወላዷ ጣር የነርሱ ልመና በለጠ መሰለኝ በእናትየዋ ጩሃት የተቃኘ የሚመስል የህፃን ልቅሶ ተሰማ።  ይሄኔ በጭንቅ የተያዙ ሴቶች እልልታ ድምፅ (የእልልታ ኦርኬስትራ) መንደሩን አቀለጠው። 

አዋላጇ እትዬ አሰገድ ህፃኗን አፋፍሰው አጠገባቸው ለነበረችው አመዘነች ሰጧትና እትብቷን ሊያስሩ ወደ ወላዷ ተመለሱ። ግን የወላዷ ምጥ እንኳን ሊያበቃ ጨርሶ አልታገሰም ነበር።  እርሳቸው እጃቸውን ሰድደው ቢዳብሷት የሌላ ህፃን ጭንቅላት ነኩ። ሌላኛይቱ፣ በቀዳማይቱ መንታ ለቅሶዋን የተቀማች የመሰለችቱ በታላቅ ዝምታ ይሄን ዓለም ተቀላቀለች። አሰገድ ሁለተኛዋን ህፃን እንደያዙ አለመጠን ማነሷን ዐይተው “ይህችስ ምርቃት ናት” አሉና በዚያ ለተሰበሰቡት ሁሉ የመንታዎቹን ብስራት አበሰሩ። እነሆ ታላቅ ፌሽታም ተደረገ።

ስም ወትሮም ከጎረቤት መውጣት ደንቡ ነውና የመጀመሪያዋ ስጦታነት የሁለተኛዋ ምርቃትነት ፀና። ከፍ እያሉ ሲመጡ እናታቸው ከምታለብሳቸው ተመሳሳይ ልብስ ውጪ መንታ ለመባል የሚያመሳስላቸው ነገር ጠፋ።

ስጦታ ሰፈር ሁሉ የሚቀባበላት፣ አባቷ እንኮኮ ብሎ መንደሩን የሚያዞራት፣ መልካም ፀጉር፣ ዛጎል ዐይን፣ ሰልካካ አፍንጫ፣ ብሩህ ፈገግታ፣… የታደለች።

ምርቃት ከስጦታ የተረፈ ስስ ብናኝ የአናት ፀጉርና የሞጨሞጩ ዐይኖች ያሏት፣ ለንቋሳ፣ ፉንጋ እና አኩራፊ ፍጡር ናት። ባላወቀችው ምክንያት ተፈጥሮና ዓለም ፊታቸውን ያዞሩባት። ሰፈርተኛው  “እግዜር አንድ እንቁላል ሰብሮ ሁለት እጣ ፋንታ ሲፅፍ፣ አንዷ ላይ አድምቆ ቀለም ቢያልቅበት ይቺኛዋ በደበዘዘው የተከተበላትን ይዛ ደብዝዛ የምትኖር ናት” ይላል።

አባቷ ድንገት  አተኩሮ  ካያት ንዴት በደም ስሩ ስለሚፈስ ሰርክ እለት መኖሯን በቸልታ ይዘነጋል፤ አባባ ባለችው ቁጥርም አፉን ደም ደም ይለዋል። እናቷ ባየቻት ቁጥር ልጆቿ ከመወለዳቸው ዘጠኝ ወር በፊት በአንዲት በተረገመ ቀን ወደተፈፀመ ድርጊት ትነጠቃለች።


ያ ቀን የእርሷና የሰለሞን ገና ጤዛው ያልረገፈ፣ ወዙ ያልደረቀ፣ የጫጉላቸው ሰሞን የተሰመረ ቀን ነበር። እንደ አዲስ ሙሽራ ወግ ጧት ተነስታ፣ ቁርስ ሰርታ፣ ባሏን ቁርሱን አጎራርሳና ከረባቱን አስራ ወደ ስራ ከሸኘች በኋላ ሳሎን ውስጥ ፎቴ ወንበሯ ላይ ነጠላዋን ጣል አድርጋ ጋደም ባለችበት የቤቷን በር መበርገድ ሰምታ ቀልቧ ሲገፈፍ፣ ቀና ብትል ቁና ቁና የሚተነፍስ ክብሮም ተገትሮ… 

“ምነው እንዲህ ቀልቤን የምትገፈው?” ብትለው መሬት መሬቱን እያዬ “ልሰናበትሽ ነው የመጣሁት፣ አውቶብሱ ሊሄድ ነው ሃገር ልቀቁ ተብለናል። አስመራ ልሄድ ነው” አላት። 

ክብሮም የልጅነት ወዳጇ እንደሞት ለመሰለ መለየት ሊሰናበታት ፊቷ ቆሞ ላታቅፈው አትችልምና፣ ፊቷን ደረቱ ላይ አድርጋ ላታለቅስ አይሆንላትምና፣ እንዲያ እንዲያ ሆነው ተሰናበቱ። እና ምርቃትን ሰርክ ልብ ብላ ባየች ቁጥር፣ ወደዛ ሁነት በተነጠቀች ቁጥር ዐይኖቿን ወደ ሰማይ ቀና አድርጋ፣

 
“እንዴት የአንድ ቀን ስህተት፣ የቅፅበት ውስልትና፣ ህያው ሃጢያት ሆኖ ከደሜ ደም ቀድቶ ከስጋዬ ስጋ ቆርሶ ነፍስ ዘርቶ ዘመኔን በሙሉ በፊቴ ሊንከላወስ ይችላል? እውነት ለኔ ከዚህ የቀለለ ቅጣት አጣህ?” እያለች አምላኳን ትጠይቃለች።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top