ታሪክ እና ባሕል

በተወራለት መጠን ያልተሰራበት ጉዳይ

“ቀጥተኛ የሕዝብ ተሳትፎ” የሚለው ቃል ተደጋግሞ ከመነገሩ የተነሳ የተሰለቹ
ብሂሎች ውስጥ ገብቷል። ሕዝብ ተሳትፎበት፣ ማኅበረሰቡ ተወያይቶበት፣
የነዋሪውን ይሁንታ አግኝቶ፣… የሚሉት ሐረጎች የዜና ማድመቂያ ከመሆን
የዘለለ ፋይዳ አልነበራቸውም። መንግሥታት ዲሞክራሲያዊ ለመምሰል
የሚከወኑ የሽፋን ተግባራት ነበሩ። ተቆጥቦ በጥቂቱ የሚለገስ ተገዳዳሪ የሆነ
ሲመስል፣ ተጽእኖ ሲያሳድር፣… የሚታፈን ሆኖ ኖሯል፡፡ ሕዝቡም ወንበር
ከማስጠበቅ እና ሥልጣን ከማስቀጠል የዘለለ አበርክቶ አልነበረውም።
በዜጎች ጠንካራ ተሳትፎ ውስጥ የሲቪክ ማኅበራት ጥንካሬ፣ ተቋማዊ እና
ሙያዊ ነጻነት፣ መረጃ የማግኘት መብት፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት፣
የመደራጀት እና ሕጋዊ ከለላ የማግኘት መብት፣… ተያይዘው የሚመጡ ናቸው።
ለእውናዊነታቸው ያለን ፈቃደኝነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ጭማሪ እያሳየ ቢመጣም
ተፈላጊው ግብ ላይ ለመድረስ የሚቀረን ርቀት ግን ረጅም ነው። እነኚህን
እና እነኚህን መሰል አደረጃጀቶች ከትላንት እና ከዛሬ የተሻለ ነገን እንድንገነባ
የሚያስችሉን ግብአቶች ናቸው።
በዛሬው የታዛ መጽሔት ቁጥር ፪፯ እትም የህዝብ ተሳትፎን በተመለከተ
ሰፋ ያለ ጽሑፍ አካተናል። በሐተታው ከታሪክ እስከ ፍልስፍና፣ ከቀደምት
አኗኗራችን እስከ ዘመናዊው ዓለም ያሉ ሁነቶች ተዳስሰውበታል። አቅርቦቱ
የውይይት በር እንደሚከፍት ተስፋ እናደርጋለን። ከአፍታ ንባብ የተሻገረ
አበርክቶ እንዲኖረውም ጥረናል።
በሌሎቹ የታዛ መጽሔት ገጾችም ትኩረታቸውን ኪነ-ጥበባዊ ጉዳዮች እና
የኪነ-ጥበብ ሰዎች ላይ ያደረጉ ጽሑፎች ይጠብቋችኋል። ታሪካዊ ሁነቶችን
ለመማማሪያ እና ለመታወሻ በሚሆን ልክ ያሚያስታውሱ፣ የሕትመት
ውጤቶችን እንድናነብ የሚገፋፉ፣ እምብዛም ካልተለመደ ጥበባዊ ካዋኔ ጋር
የሚያስተዋውቁ፣ ጽሑፎችም የሕትመቱ አንድ አካል ሆነዋል። አጠር አጠር
ያሉ ተዝናኖትን እና ቁምነገርን ያዘሉ ጽሑፎችም አልተዘነጉም።
እንደ ዘወትራዊ ጥሪያችን ሁሉ ዋና ግባቸውን የኅብረተሰብ ጠቀሜታ ላይ
ያደረጉ ስራዎች ልታደርሱን ለምትፈልጉ ልባችንም ቢሯችንም ክፍት ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top