ስርሆተ ገፅ

“በልጆቿ ላይ በምታየው ባህሪ የተከፋች አንድ እናት ትታየኛለች”

ከስነ ስዕል ውጭ የሚማርከውን የጥበብ ዘርፍ ሲጠየቅ ቲያትርን ያስቀድማል። ‹‹በትያትር እና ትወና ዘርፍ ላይ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እኔን ይማርኩኛል።›› የሚለው የዛሬው የስርሆተ ገጽ እንግዳችን ሰዓሊ ነው። በመቄዶንያ የአረጋዊያን እና የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማእከል ውስጥ በሚሰጠው የጥበብ ሕክምና ወይም አርት ቴራፒ ይታወቃል። በቅርቡ በሸራተን አዲስ ከሌሎች ሰዓሊያን ጋር በነበረው የስእል አውደ ርእይ ላይ የሚሸጡ ስእሎቹን ገቢ ለሜቄዶንያ ሰጥቷል። በመጽሐፍት ውይይቶች ላይ የማይጠፋው ዮናታን ሱራፌል በሴቶች መደፈር ላይ ባቀረባቸው ስእሎቹ በበርካቶች ዘንድ አድናቆትን አትርፏል። ከታዛ መጽሔት አዘጋጅ ጆኒ በሪሁ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንዲህ ተሰናድቷል። መልካም ንባብ!

አንተ እና ባልደረቦችህ መቄዶንያ ውስጥ የምታደርጉት እንቅስቃሴ ምንድነው?

 በሜቅዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ውስጥ እየሰራናቸው ካሉ ስራዎች ውስጥ አንዱ የአርት ቴራፒ ክፍላችን ነው። በዚህ ክፍላችን ውስጥ ልጆችን በየትኛው ጥበብ ልናክማቸው እንደምንችል እናያለን። መጀመሪያ ልጆቹ የሚወዱትን ነገር እንዲለዩ ምርጫ እናቀርብላቸዋለን። በጨዋታ መልክ ስንጠይቃቸው ፍላጎታቸውን በመጀመሪያው ቀን ወይም በሂደት ያሳውቃሉ። እኛም ምርጫቸውን ተከትለን፤ ስነጽሁፍ ስዕል ውዝዋዜ ትያትር ሊመርጡ ይችላሉ። ዋናው ትኩረታችን አርት ቴራፒ ውስጥ ብዙ ዘርፎች ስላሉ፤ የትኛው ላይ በተሰጥኦቸው ብቁ የሚሆኑት በሚለው በእድሜ አቻዎቻቸው እንዲቧደኑ አድርገን፤ እርስ በእርስ ጥበብን ወይም ስዕልን በመጠቀም እንዲተካከሙ ነው የምናደርገው። ጓደኞቻቸውን እያከሙ የሚታከሙበት አሰራር ነው ያለው ማለት ነው።

በአርት ቴራፒ ምን ያህል ተሰርቷል?

 በአርት ቴራፒ የመጨረሻው ደረጃ መሄድ  የሚቻለው ጤናማ እና ብቁ ዜጋን ማፍራት ነው። ነገር ግን አገራችን ላይ ስንመለከት ሃሳቡ አዲስ ይመስላል። በከተማ በሚገኙ ተቋማት ላይ እኛ ጀመርነው እንጂ፤ በትምህርት ቤት እና ሌሎች ተቋማት ማቋቋም ይቻላል። በትምህርት ቤቶች ውስጥ ትኩረት ተሰጥቶበት ል ን ሰ ራ ባ ቸ ው የምንችለው ነው። አሁን አሁን በጎ ጅምሮች አሉ። ተስፋ አለን እላለው።

 በቀንህ ውስጥ የት የት ቦታዎች ታሳልፋለህ?

 ብዙ የምንቀሳቀስባቸው ቦታዎች አሉ። ለምሳሌ ‹አጥፊ› አለመሆኔ በራሱ አንድ ጥሩ ነገር ነው። አጥፊ አይደለሁም፤ በተቻለኝ አቅም ሃገሬን ለመገንባት ነው የምጥረው። ዝዋይ አካባቢ እንደማደጌ እዛው ዝዋይ  አካባቢ ሃይቆቻችንን በማድረቅ ላይ ያለ ‹እንቦጭ› የሚባል አረም አለ። እሱን ለማጥፋት ከአካባቢው ወጣቶች ጋር አባል የሆንኩበት የበጎ-ፈቃደኞች ማኅበር አለ። በዛ ማኅበር እየተሳተፍኩኝ ነው። በተጨማሪም በአካባቢያችን ያሉ ገዳማትን በማስተዋወቅና የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ እየሰራሁኝ ነው።

 በመዲናችን በአዲስ አበባ ደግሞ ሱስ ውስጥ ያሉ እና ትምህርት ቤት የማይሄዱ ሕጻናትን ከብዙ ግብረ-ሰናይ ተቋማት ጋር በመተባበር እንደእግዚዘብሄር ፈቃድ ከችግራቸው በሚላቀቁበት ሁኔታ ላይ እየሰራሁ ነው።

 ለስእል ማሳያ የምትመኛቸው ቦታዎች አሉ?

እዚህ ቦታ ባሳይ ብለህ ታውቃለህ? ጥሩ ጥያቄ ነው። የመጀመሪያው የሰሜን ፓርክ ነው፤ ከቤት ውጭ ያለ የስዕል አውደ-ርዕይ ባሳይና፤ ከገቢውም ለብርቅዬ እንስሳዎቻችን ድጋፍ ባደርግ ደስ ይለኛል። ሁለተኛው ደግሞ የስዕል እና ቅርፃ-ቅርፅ ስራዎቼን በሶፍ-ኡመር ዋሻ ባቀርብ ደስ ይለኛል። ሶፍ-ኡመር በተፈጥሮ የተሳለ ነው፤ እኔ በሰው የተሳለ ስዕሌን አያስተያየሁ እዛ ባቀርብ ደስ ይለኛል።

ሰማያዊ ቀለም ላንተ ምንድን ነው?

ሰማየዊ ቀለም መጀመሪያ ስሙን የወሰደው ከሰማይ ነው። ሰማይ ስንል ደግሞ እጅግ ግዙፍ የሆኑ ነገሮች የሚከሰቱበት እና የተከሰቱበት ነው። አንድ ሰዓሊ ጓደኛዬ ከሰማይ ተሰደን ነው ወደምድር የመጣነው ይላል። በሃይማኖትም ትልቅ ትርጉም ያለው ነው። በሳይንስም ሰፊ ሽፋን ከሚሰጣቸው ቦታዎች ውስጥ ነው። እናም ሰማያዊ ቀለም ብዙ ጥልቅ ሚስጥር ያለው ነው። የቅዝቃዜ ስሜት ይሰጠናል። ከማንም ቀለም ጋር ሳይደባለቅ የሚገኝ ነው። ሌላው ደግሞ ቀለሙ በባህሪው ጠንካራ ከምንላቸው ቀለሞች ውስጥ ነው። በተጨማሪም ሰማያዊ ቀለም ምስጢራዊ እውቀትን ይገልጻል፣ ብሩህ ተስፋን ይገልጻል፣ እምነትን ይገልጻል፣ ስሜት ላይም በሳይንሱ ስናየው ቅዝቃዜን እርጋታን ይሰጠናል። የወንድ ቀለምም ነው ይባላል። ብዙ ትርጉሞች ያሉትና በስነስዕል ላይ ሰፊ ድርሻ ያለው ቀለም በመሆኑ ይስበኛል።

 ስለ ስእል ጅማሮህ ንገረኝ

 አዲስ አበባ ተወልጄ ከአራስነት ጊዜዬ ጀምሮ ያደኩት ዝዋይ ነው። ስእልን የተዋወኩት የመዋዕለ ህፃናት ተማሪ ሆኜ ነው። የስዕል ተሰጥኦ እንዳለኝ ያኔ በልጅ አእምሮዬ ነው ልገነዘብ ቻልኩ። ት/ቤቱ የሰጠኝ ድጋፍ መሠረት ሆኖኛል።

የስዕል ትምህርትን መጀመሪያ በሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ስር በተቋቋመው የ‹ኢንላይትመንት አርት አካዳሚ› ተቀላቅዬ ነው የጥበብ ጥናቴን ያካሄድኩት። በዛ የስዕል ተቋም ውስጥ ነው የስዕልና የቅርፃቅርፅ ሞያ ቀሰምኩ። ቀጥሎ ደብረዘይት በሚገኘው የአፍሪካ የስነጥበብ አካዳሚ ውስጥ፤ በሰዓሊ ሻምበል ለማ ጉያ ድጋፍ ኢትዮጵያዊ የሆነ የአሳሳል ስልቶችን፣ የቆዳ ላይ አሳሳል አጠናሁ። ለስዕል ሞያዬ የበለጠ እውቀትን በማዳበር፤ በተቋሙ ውስጥ ለአንድ ዓመት ከአራት ወር አካባቢ ትምህርታዊ ጥናቶችን አካሂጃለሁ።

 ስእልን ከቤተሰብ የወረስከው ነው ማለት ይቻላል? አያትህ ሰዓሊ ነበሩ?

ወንድ አያቴ ሰዓሊ አሸብር ጀምበሬ ይባላል። በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጊዜ፤ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ሲማር ባሳየው የስእል ችሎታ እንዳለው በመታወቁ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በስዊድን፣ በእንግሊዝ፣ እንዲሁም በአሜሪካ የነፃ ትምህርት እንዲያገኝ አደረጉ።

 አያቴ በርካታ የጥበብ ጥናቶቻችውን በመላው ዓለም ካደረጉ በኋላ ወደሃገራቸው ሲመለሱ ለሃገራችን ልዩ ልዩ ስራዎችን አበርክተዋል። በጊዜው ለሃገራችን የመጀመሪያ የሆነውን የሲልክ ስክሪን ህትመት ለሃገራችን አስተዋውቀዋል። ከዚህ ስራ በኋላም ለተለያዩ የመንግሥት እና የግል ተቋማት፤ የንግድ ምልክት (ሎጎ) የሚለውን ሃሳብ አስተዋውቀዋል። በዚህ ስራቸው ለሜታ ቢራ፣ ለደብረብርሃን፣ ለኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት፣…  የንግድ ምልክቶችን ሰርተዋል።

ልዩ ልዩ የአሜሪካ ኤምባሲ በሚያካሂዳቸው አርትን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ በንቃት ተሳትፈዋል። በወቅቱ አጠራር የሳይንስና ትምህርት ሚኒስቴር የሚባል ይመስለኛል … እዛ መስሪያ ቤት ውስጥ ከ28 ዓመታት በላይ አገልግለዋል።

ለወጣቶች መልእክት የማስተላለፍ እድል ብሰጥህ ምን ትላቸዋለህ?

የመጀመሪያውና ትልቁ ነገር ሰዎች በምድር ላይ ስንኖር ሁሉም ነገሮች ስርዓት  እና ስርዓተ-ምት አላቸው። ያንን ስርዓተ- ምት ተከትለን ስንሄድ ምድርን አንረብሻትም፤  እሷም አትረብሸንም። በዛ ስርዓተ-ምት ውስጥ  ሆነን የእለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችንን በተቀናጀ መንገድ በምናካሂድበት ጊዜ ውስጥ፤ ህይወታችንን ወይም ማህበረሰባችንን  እናደራጃለን እንጂ አናፈርስም። ይህን ስርዓተ- ምት እንዴት አድርገን እናመጣለን የሚለው  ላይ ነው እንግዲህ ትኩረት እንድናደርግ ሃሳቤ የሚሆነው። ሁሉም ነገር ህግ አለው፤ ምድራዊም እንዳለ ሁሉ ሰማያዊም ህግ አለን። ይብዛም ይነስም እነዚህን ነገሮችን ተከትለን ብንሄድ ጥሩ ነው። እኛ በዚህ ምድር ስንኖር ትልቅ ምክንያት አለን። ይሄ ነጥብ ለሁሉም ነገራችን ቁልፍ ነው። በምክንያት እንኑር፤ የምናስቀድመው ነገር ይኑረን፤ ወጣቶቻችን አንዳንድ የሚታዩ ባህሪዎችን ትተውና ከክፉ ድርጊት ተመልሰው፤ ራሳቸው ከብረው ሃገራቸውን ከፍ አድርገው እንዲያስከብሩ ትልቅ ፍላጎት አለኝ። ይህንን እንደሚያደርጉም ትልቅ ተስፋ አለኝ፡፡

 ኢትዮጵያ ማለት ታዘወትራለህ። ምሳሌዎችህም ኢትዮጵያዊ ብቻ ናቸው። ከኢትዮጵያ ውጪ ሌላ ዓለም አይታይህም?

ከኢትዮጵያ ውጪ ዓለም እንዳለ እርግጥ ነው። ኢትዮጵያን በጥበብ ዓይን ስመለከታት ላቅ ትልብኛለች። ከውጪው ዓለም ጋር ሳስተያያትም፤ ከዓለም ከተቀበለችው ለዓለም ያበረከተችው ይበልጣል ብዬ አስባለሁ።

ወቅታዊው የኢትዮጵያን ሁኔታ እንደሰአሊ ግለጽ ብትባል ምን ይታይሃል?

በልጆቿ ላይ በምታየው ባህሪ የተከፋች አንድ እናት ትታየኛለች። ግን ደግሞ ልጆቿ ታርቀው ብሩህ ተስፋ የሚያዩባት ኢትዮጵያ ትታየኛለች።

 በዚህ ዓመት መጨረሻ ስላሰብከው የስእል አውደ ርዕይ ጥቂት ንገረኝ?

 የተወለድኩት በጥምቀት በዓል ሰሞን ጥር 14 ነው። በዛ ቀን 30 ዓመቴን እደፍናለሁ። በእለቱ 30 የስዕል ስራዎችን ለማሳየት አስቤያለሁ። የአውደ-ርዕዩ ርዕስ ‹እርቁስ› ይባላል። ቅዱስ እና እርኩስ ከሚሉ ቃላት የተዳቀለ ነው። ቅዱስም እርኩስም ለማለት ነው። በሌላ በኩል ‹እርቁስ/ መታረቁስ› ማለትም ይሆናል። ‹የታል እርቁ?› ብሎ የሚጠይቅ ርዕስ ነው ያለው።

 ሰኔ ላይ በጋራ ሊደረግ የታሰበ የሚክስድ- አርት አውደርዕይ አለ። ያለፉትን ሦስት  ዓመታት ኢትዮጵያ ያሳለፈችውን ጊዜ፤ የተለያዩ ጥበባትን በመጠቀም በሚክስድ ሚድያ ለማቅረብ እቅድ ይዘናል።

ስለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ!

 በመጀመሪያ ታዛ መጽሔትን አመሰግናለሁ። በመቀጠል ልዩ ልዩ የህይወት ጉዞዬ ላይ በከፍታም በዝቅታም በነበርኩበት ከጎኔ ላልተለየችኝ እናቴ ሲ/ር ፍሬህይወት አሸብር። እንዲሁም ኢንጅነር ሱራፌል ሽፈራው አባቴን እጅግ በጣም አመሰግናለሁ። እዚህ ደረጃ እንድደረስ ለረዳኝ ለፈጣሪዬ ለእግዚአብሄርም ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top