የታዛ ድምፆች

፫ቱ ጠቃሚ ጥያቄዎች

አንድ ሠው ሶቅራጠስ ወዳረፈበት እልፍኝ ሄዶ እንዲህ አለው፡፡

‹‹ሶቅራጠስ ወዳጄ፣ እገሌ ስለተባለው ወዳጅህ ዛሬ የሠማሁት ነገር ምንም ደስ አይልም›› አለው፡፡

ሶቅራጦስ መከዳው ላይ እንደተደገፈ መልስ ሳይሰጠው ዝም አለ፡፡

ሠውየውም እንደገና ‹‹ይገርማል ከእርሱ አይጠበቅም፤ በጣም ገርሞኛል›› ሲል ተናገረ፡፡

ሶቅራጦስ፣ ይህ ሠው በቀላሉ እንደማይፋታው ስለተረዳ አንድ መደራደሪያ አቀረበለት፡፡ ‹‹ስለ ወዳጄ ልትነግረኝ የፈለግከውን እንድሠማህ ከፈለግህ ሶስት ጥያቄዎች አሉኝ፤ እነርሱን በቅድሚያ ልትመልስልኝ ይገባል! ይህ ሲሆን ብቻ ነው የምሰማህ›› አለው፡፡

ሠውየው ለወሬው ቢቸኩልም አማራጭ ስላልነበረው በሶቅራጠስ ሀሳብ ተስማማ፡፡

‹‹የመጀመሪያው ጥያቄዬ የእውነት ጥያቄ ነው” አለ ሶቅራጠስ። “ስለወዳጄ የሠማኸው መቶ በመቶ እውነት ነው ወይ?›› ሲል ጠየቀ፡፡

ሠውየውም፡- ‹‹መቶ በመቶ እንኳን እርግጠኛ መሆን አልችልም›› ሲል እያመነታ መለሰለት፡፡

‹‹በጣም ጥሩ! ልትነግረኝ የፈለግከው እርግጠኛ ያልሆነ ነገር ነው ማለት ነው፡፡ እሺ ሁለተኛው ጥያቄዬ የመልካምነት ነው፡፡ የምትነግረኝ መልካም ነገር ነው ወይ?›› ሲል ሶቅራጠስ አቀረበ ጥያቄውን፡፡

ሠውየውም፡- ‹‹እርሱማ መልካም አይደለም›› አለ ቱግ ብሎ፡፡ የሶቅራጠስ ጥያቄዎች ለማውራት የቋመጠለትን ወሬ እንዳያወራ እንቅፋት መስለው ታዩት።

ሶቅራጦስም ‹‹እውነትነቱ ያልተረጋገጠና መልካም ያልሆነ ነገር ልትነግረኝ ፈልገሃል፡፡ እሺ ሶስተኛውና የመጨረሻው ጥያቄዬን ልጠይቅህ?›› አለው፡፡

ሠውየውም ጥያቄውን ለመስማት ፈጥኖ ‹‹እሺ›› አለ፡፡

ሶቅራጦስ ጠየቀ፤ ‹‹የምትነግረኝ ነገር ለእኔ የሚጠቅመኝ ነገር አለው ወይ?››

‹‹የለም! የለም! መጥቀም እንኳን አይጠቅምህም። ብቻ ብትሰማኝ…›› ብሎ ሰውዬው መቅለስለስ ጀመረ።

ይሄን ጊዜ ሶቅራጦስ ‹‹ታዲያ እንደምን አድርጌ እውነትነቱ ያልተረጋገጠ፤ መልካም ያልሆነ እና ለእኔ ምንም ጥቅም የሌለው ነገር ልንገርህ ስትለኝ እንዴት እሰማሃለሁ። ዞር በል ካጠገቤ አልሰማህም!!›› አለው ይባላል፡፡

ስንቶቻችን ነን ሰው የሚነግረን ነገር እውነት፣ መልካምና ጠቃሚ መሆኑን አጣርተን የምንሰማው? ስንቶቻችን ነን ለሰው ቁምነገር ብለን ልንናገር ስንል ከሶስቱ አንዱን ማሟላቱን የምናረጋገጠው? አሁን እኮ ሰው ዝም ብሎ የተነገረውን ስለሚሰማ በቀላሉ እንደ እንስሳ የሚነዳ ሆኗል፡፡ በየሶሻል ሚዲያው ላይ ፖስት የሚደረጉት ብዙዎቹ መረጃዎች እውነት ያልሆኑ፣ መልካምነት የሌላቸው እና ለእኛ ምንም ጥቅም የማይሰጡ ናቸው፡፡ በተቃራኒው የውሸት መረጃዎች ሆነው ስንቱን ያጭበረበሩ፣ ሰይጣናዊ ርምጃ ለመውሰድ የሚገፋፉ ሆነው ሳለ ያለማቅማማት እንሰማቸዋለን፡፡

አሁን አሁን እውነት ከሚናገሩት ሰዎች በላይ በመርዝ የተለወሰ ውሸት የሚናገሩ ሰዎች የተሻለ ብዙ ተከታይ አላቸው፡፡ መልካም መልካሙን ከሚሰብኩ ሰዎች ይልቅ የጥፋት ሰባኪዎች ብዙ ደጋፊ አላቸው፡፡ ፍለጠው/ቁረጠው ባዮች ናቸው የጀገኑት፡፡ እነሱን ማስቆም አይቻል ይሆናል፤ ነገር ግን እነሱን አለመስማት/አለመከተል ቀላል ነው፡፡ እነዚህን የሶቅራጠስ 3ቱ ጥያቄዎችን እንደ ወንፊት ተጠቅመን ማጣራት ብቻ በቂ ነው፡፡

ጂም ቶርፔ

ፓፒ ፓፒ


ፎቶ ግራፉን በደንብ ተመልከቱ… ያደረጋቸው ጫማዎች የተለያዩ ናቸው። ፋሽን እንዳይመስላችሁ ፋሽን አይደለም ችግር ነው! በፈረንጆቹ አቆጣጠር 1912 የኦሎምፒክ ተወዳዳሪ ነበር ውድድሩን ምያደርገው አሜሪካንን ወክሎ ነው።

ጧት ወደ ውድድሩ ለመሄድ ከእንቅልፉ ተነስቶ ጫማውን ለማድረግ ሲሄድ ጫማው ተሰርቋል ሌላ ጫማ የለውም!


ጫማው ስለተሰረቀ ውድድሩን ለመቅረት አልወሰነም ሰፈሩ ወደሚገኘው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳ ሄዶ የተለያዩ ጫማዎችን ያገኘል።

አንደኛው እግር ጫማ ልኩ ሲሆን ሌላኛው እግር ጫማ ግን ከእግሩ መጠን በጣም ት…ልቅ ነበር…
የትልቁ ጫማ እግር ላይ ጨርቅ ጠቅልሎ ካልሲ ደርቦ ወደ ውድድሩ ሄደ…ተወዳደረ ፪የወርቅ ሜዳሊያዎችን ለሀገሩም ለራሱም አሸነፈ

ምድር ለማሸነፍ ምንም እንኳን አመቺ ባትሆንም የተፈጠረውን እንቅፋት ምክንያት አድርገን ለማሸነፍ መወዳደር ማቆም የለብንም ለማለት ያህል ነው።

ለማሸነፍ ፈተናዎቹን እያለፉ መወዳደር ግድ ነው!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top