ጣዕሞት

ጥምቀት በዩኔስኮ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ጥር 11 ቀን የሚከበረው የጥምቀት በዓል በዓለም አቀፍ የማይዳሰስ ቅርስነት ተመዘገበ። በቤተክርስቲያኒቱ ከሚከበሩ በዓላት መካከል በዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ላይ ሲሰፍር ከመስቀል በዓል ቀጥሎ ጥምቀት ሁለተኛው ነው። የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በኮሎምቢያ፣ ቦጎታ ባካሄደው ስብሰባው ነው።  

የኢትዮጵያ ባህል እና ቱሪዝም ሚንስተር የጥምቀት በዓልን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ማመልከቻ በማስገባት ሲከታተል የቆየ ሲሆን ኢትዮጵያ ካሏት ሌሎች የማይዳሰሱ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ክብረ-በዓላት መካከል እንደ አሸንዳ፣ ኢሬቻ እና ፊቼ ጨምባላላ ያሉትን የአደባባይ ክብረ-በዓላት በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርስነት ለማስመዝገብ በሂደት ላይ እንደሚገኝ ማሳወቁ ይታወሳል።

ጥምቀት በኢትዮጵያ በተለየ መልኩ የሚከበር መንፈሳዊ፣ ባሕላዊ እና ታሪካዊ እሴት በመሆኑ በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ ለመላው ኢትዮጵያውያን ትልቅ ድል ሲሆን የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን እንደሚያነቃቃ የብዙዎች እምነት ነው፡፡ በሌላ በኩል ጥምቀት የዓለም ቅርስ ሆኖ በመዝገብ ላይ ሲሰፍር ነባር ይዘቱን ጠብቆ ለትውልድ እንዲሻገር በመላው ኢትዮጵያውያን ላይ የተጣለ ዓለም አቀፍ አደራ መሆኑን የተናገረው የቱሪዝም ጋዜጠኛው ሔኖክ ስዩም ነው፡፡ ተጓዡ ጋዜጠኛ ለታዛ መጽሔት በሰጠው የስልክ ቃለ መጠይቅ እንደተናገረው

‹‹ቅርሱን በዩኔስኮ ማስመዝገብ ብቻውን ግብ አይደለም፤ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በሰጠው ዕውቅናና ክብር ልክ መሥራት፣ ማስተዋወቅ፣ ማልማት እና ወደ ሀገር የሚገባውን ቱሪስት በተገቢው መንገድ መንከባከብ እንደሚገባ፤ የጥምቀት በዓል በተለየ ድባብ በሚከበርባቸው አካባቢዎች አስተማማኝ ሠላም እንዲሰፍን፣ መሠረተ ልማት እንዲስፋፋ እንዲሁም በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ ላይ የበለጠ መጨነቅ እና ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል››

ጥምቀት በዩኔስኮ መዝገብ ላይ መስፈሩ በድርጅቱ የተመዘገቡ የኢትዮጵያ ቅርሶችን ቁጥር ከ11 ወደ 12 ከፍ ያደርገዋል፡፡

የራስ ወልደ ሥላሴ ዘውድ

የ18ኛው ክፍለ-ዘመን ሥሪት የሆነው የራስ ወልደ ሥላሴ ዘውድ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ።  ከመቐለ በ16 ኪሎ ሜትር በደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ የሚገኘው እና ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረው የሥላሴ ጨለቆት ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ከሚገኙ በርካታ ንዋየ ቅድሳት መካከል አንዱ የሆነው ይህ ዘውድ ከቤተክርስቲያኑ ወደ ኔዘርላንድስ ሮተርዳም ከተማ ተሰርቆ በአንድ ግለ-ሰብ እጅ መቆየቱ ታውቋል።  

ለአሥራ ስድስት ዓመታት በቤተ-ክርስቲያኗ በብህትውና የሚኖሩት የ82 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ አባ ገብረሥላሴ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ራስ ወልደሥላሴ ለቤተክርስቲያኗ ሦስት ዘውድ አበርክተዋል።  የሥላሴ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ፣ የድንግል ማርያም እንዲሁም ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር፣… የሚያሳይ ቅርጸ-ምስል የታተመበት ይህ ዘውድ በዓለማችን ካሉ 20 የዘውድ ዓይነቶች ውስጥ ተመሳሳይነት እንዳለው ታውቋል።  

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top