አድባራተ ጥበብ

‘ጅብ ነች’

የመጽሐፉ ርዕስ – መስከረም

ደራሲ – ታደሰ ሊበን

የገጽ ብዛት –

የታተመበት ዓመት – 1949 ዓ.ም.

ዐይን እንግዳ አዳሙ

(ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ)

የደራሲ ታደሰ ሊበን ስራዎች ለንባብ ከበቁ ድፍን ስልሳ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ መስከረም (1949ዓ.ም)  እና ሌላው መንገድ (1952 ዓ.ም.) በሚሉ አርዕስቶች ተሰይመዋል፡፡ በአንድ ጥራዝ የተጠቃለሉት ሁለት መጻሕፍት ስር በእያንዳንዳቸው 11 ልብ ወለዶች ተካተዋል፡፡ ልብ ወለዶቹ ደራሲው ሊያስተላልፈው የፈለገውን መልእክት ምስል ከሳች በሆነ መልኩ እንዲያስተላልፉ ተደርገው የተቀረጹ ናቸው፡፡ የገጸባህርያት ብዛት አንባቢን እንዲያምታታ አይፈልግም፡፡ በጥቂት ገጸ ባህርያት የተዋቀሩ አጫጭር ታሪኮች ናቸው፡፡ የልብ ወለዶቹ አጨራረስ ከአንባቢ ግምት የራቀ መሆኑ፣ የማኅበረሰቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በስነ-ምግባር መነጽር መዳሰሳቸው፣… ለንባብ የማይሰለቹ እና አስተማሪዎች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡

ይህንን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ምክንያት የሆነኝ መስከረም በሚለው በመጀመሪያው መጽሐፍ ስር ከተካተቱት አምስት ልብ ወለዶች ውስጥ የመጀመሪያ የሆነው ‘ጅብ ነች’ የሚለው ልብ ወለድ ነው፡፡ በእኔ አረዳድ የዚህ አጭር ልብ ወለድ ጭብጥ በማኅበረሰብ ሥዕለ ህሊና (Social Psychology) ታትሞ የተቀመጠን ልማድ መሰረት እንደሌለው ያመላክታል፡፡ ማኅበረሰቡ ‘ቡዳ’ በሚል ተጸውኦ በሚጠራቸው ወገኖች ላይ የነበረው ነባር እሳቤ በሳይንስም በሀይማኖትም ተቀባይነት እንደሌለው ለማሳየት ይሞክራል፡፡

ደራሲው ታደሰ ሊበን ተመሳሳይ ማኅበረሰባዊ ጉዳዮች እንዴት በተግባር ሊፈተሹ እና ሊረጋገጡ እንደሚችሉ ለማስረዳት የሄደበትን ርቀት ማርኮኛል፡፡ ጽሑፉን ሳነብ የተሰማኝን በዚህ መንገድ ለመግለጽ ሞክሬአለሁ፡፡

ይህች መጠነኛ ጽሁፌ ሂስ አይደለችም፤ ሙያዊ ማብራሪያም አይደለችም፡፡ በቃ… የተሰማኝን እና መልእክቱን የተረዳሁበትን መንገድ ለመግለጽ ብቻ ነው፡፡

መቼትን በተመለከተ

  • ኪሎ ሜትር

ዋናው የልብ ወለዱ ታሪክ የተፈጸመው ሸኖ የምትባል ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ደራሲው በልቦለዱ ውስጥ ሸኖ ከአዲስ አበባ በ75 ኪ.ሜ ርቀት ላይ እንደምትገኝ ይነግረናል፡፡ ለመሆኑ ደራሲው ድርጊቱ የተከናወነበት ቦታ ከመዲናዋ አዲስ አበባ የሚርቅበትን ሜትር መግለጽ ለምን አስፈለገው? ርቀቱ ለምን አሳሰበው? የሚል ጥያቄ ይፈጥራል፡፡

ርቀቱ ያስፈለገው በሀገራችን ከሚገኙ ከተሞች ሁሉ በላይ ስልጡን ከሆነችው አዲስ አበባ፣ የዘመናዊ ሰዎች መኖሪያ እና የዘመናዊ ሐሳቦች መፍለቂያ ከሆነችው አዲስ አበባ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መገኛ ከሆነችው ከተማ በቅርብ ርቀት ስልጣኔ አልገባም፣ ዝመና አልተሰራጨም፣… ሊለን ፈልጎ ይመስለኛል፡፡ የስልጣኔያችን እና የእውቀታችን የስርጭት አድማስ ጠባብ፣ ከራስ በላይ መትረፍ የተሳነው ደካማ፣.. እንደሆነ ለመግለጽ ሲል እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ አይሆንም ባይ ተከራካሪ ካጋጠመ ደግሞ ደራሲው በአጭር ልብ ወለዱ ላይ ኪሎሜትር ያለመጥቀስ መብቱን አልተጠቀመበትም? ከሞያሌ እስከ በራህሌ ያሉ የሐገሪቱ ጫፎች ለምን አልሳቡትም? በሚሉ ጥያቄዎች ጥያቄን በጥያቄ መመለስ ይቻላል፡፡

የአዲስ አበባ ስልጣኔ ላይ ለመሳለቅ አዲስ አበባ አፍንጫ ስር ያለን ሕጸጽ ከማንሳት የቀረበ ማሳያ የለም፡፡ የዋናው ገጸ ባህርይ እናት፣ እህቱ (አየለች)፣ እና ጎረቤታቸው ወይም ከሰፈራቸው ሰው መገርሳ አመለካከቶች በአሉታዊ ናቸው፡፡ የእናቱ አራሽ ሮባ እና ምናልባትም ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ያላቸው አመለካከት (ደራሲው ወደፊት በሚመጣ ትረካው በአሰፋ በኩል እንዳስረዳው) ካለመማር፣ ካለማወቅ፣ ካለመሰልጠን እና ካለመመርመር የሚመጣ ነውና የአዲስ አበባ ስልጣኔ ሸኖ አልደረሰም እንድንል ያስገድደናል፡፡

  • ሰዓት

በጅብ ናት ልብ ወለድ ውስጥ ከቦታው ርቀት በተጨማሪ የድርጊት ክንውን ሰዓቱም በምክንያት የተቀመጠ ነው፡፡

በዕለተ ቅዳሜ አሰፋ እናቱን ለመጠየቅ ከአዲስ አበባ ወደ ሸኖ ይሄዳል፡፡ ቀትር ላይ ሸኖ ደርሶ ከ6፡00 እስከ 9፡00 ከእናቱ እና ከእህቱ ጋር ይጨዋወታል፡፡ 9፡00 ላይ ውጭ ውጭ አሰኘው፣ ያደገበት አካባቢ ናፈቀው፣ ከቤት መውጣት ፈለገ፡፡ ከቤት ሊወጣ በር ላይ ቁሞ በጣም ከርቀት ካለው ጋራ እና ተራራ ጀምሮ ዕይታውን እያቀረበ እስከ በራቸው ድረስ አካባቢውን በተመስጦ ቃኘ (የዕናቱን ንግግር ሳይቀር በቅጡ ሳያዳምጥ አካባቢውን በተመስጦ ያስተውላል)፡፡

እናቱ ትጠይቃለች ‹‹የት ልትሔድ ነው አሰፋ›› 

9፡00 ላይ ከቤት መውጣቱ አልተመቻትም፡፡ ለምን ለሚለው ጥያቄው የሚላት መልሷ ቀትር ነው፤ የሚል ነው፡፡ በቀትር ከቤት መውጣት ጥሩ እንዳልሆነ ታምናለች፡፡ ለምን ባይ ጠያቂ ያፋጠጣት እንደሆን ደግሞ

‹‹በቀትር ከቤት መውጣት ለምኑም ለምኑም ደግ አይደለም፣ ስንት ነገር አለ›› ትላለች፡፡ (ለማለት የፈለገችው በአካባቢው የሚገኙት ቡዳዎች ይህንን ሰዓት ይመርጡታል ነው)፡፡ ስለዚህ ቀትር እስኪያልፍ፣ ቀዝቀዝ እስኪል እንዲቆይ ትመክረዋለች፡፡ ተጨማሪ ፍቺ ስናስስ ደግሞ መብሰልን እያመሰጠረች እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በዚህ ጊዜህ አንተ ወጣት ነህ (9፡00) ለመምከር አትበቃም፣ የተወሰነ ጊዜ በእድሜ እስክትደረጅ ድረስ (እስከ 11፡00) ቆይ ያለችውስ አይመስላችሁም?

  • በቤት ውስጥ መታጠር

አሰፋ ከቤት ሳይወጣ በር ላይ ሆኖ ውጭውን ከርቀት ይመለከታል፡፡ የዕይታ አድማሱን እያጠበበ እያሰፋ ከጎረቤት እስከ አድማስ ጥግ ዐይኑን ያማትራል፡፡ በቤት ውስጥ ብቻ መቀመጥን ግን አልመረጠም፡፡

ደራሲው በዚህ ገጸ-ባህርይ ድርጊት ማስተላለፍ የፈለገው ሁለት መልእክት ነው፡፡ የመጀመሪያው ከቤት ውጭ (እደጅ) መሆንን እንደናፈቀ ሲሆን ሁለተኛው ግን በተማረው ትምህርት አሻጋሪነት ካደገበት ማኅበረሰብ የተሻገረ ዕይታን አዳብሯል፣ ሩቅ ማየት፣ በጥልቀት ማሰብ፣ ከሳጥን የወጣ አመለካከት አዳብሯል የሚል ነው፡፡ ሩቅ አልሞ አይቀርም፤ ቅርብም ይመለከታል፡፡ አካባቢውን ያያል፡፡ በተማረው ትምህርት፣ በቀሰመው እውቀት የአካባቢውን ችግር ሊፈታ ይመኛል፡፡

ቤት ውስጥ ብቻ ተቀምጦ ማሳለፍ አለመፈለጉም በቤተሰቡ እና በአካባቢው የዘልማድ አስተሳሰብ ብቻ መታሰርን አለመፈለጉን ያሳያል፡፡ ቢያንስ 9፡00 ላይ (በአካልም በእውቀትም ሳይበስል) ከቤት መውጣት ቢከለከልም፣ 11፡00 ሲሆን (ሲበስል፣ የአዕምሮው ዝግጅት ሲፈቅድለት)፣ ሙቀቱ ሲቀንስ፣ (እናቱ ቁጣዋ ሲበርድላት) ግን ወጣ፡፡

  • የጎረቤት ቤት

የጎረቤቶቻቸውን ግቢ ማየት ማለትም ቤተሰቦቹ ያሉበትን አኗኗር፣ ከጎረቤቶቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነትና መቀራረብ (ፍቅር) መመርመር ነው፡፡ የጎረቤቶቻቸውን ግቢ ሲመረምር የተረዳው ነገር ቢኖር ከአካባቢው አኗኗር መለየታቸውን ነው፡፡ ቤታቸው ከአካባቢው ይለያል፡፡ ቤታቸው አሰራሩ እንደ አካባቢው ቤቶች አይደለም፡፡ ጎረቤቶቻቸው የተሰሩበት ስነልቦና (Psychology) በአካባቢው ተገፍተው፣ ቡዳ ናችሁ ተብለው፣ ተገልለው፣ በህዝብ መካከል እየኖሩ ግን ከአካባቢው ኅብረተሰብ ተለይተው ይኖራሉ የሚል መልእክት አለው፡፡ ለዚህም ማሳያ ይሆን ዘንድ ለጎረቤቶቻቸው ቤት ጣራውን የአካባቢውን ቤቶች (የሳር ክዳን) የማይመስል አሰራር (የቆርቆሮ ክዳን) ሰጥቶ ሲሰራው እንዲሁም ደግሞ ለወይኒቱ የራሷ ያልሆነ ማንነት (ቡዳነት) ኅብረተሰቡ እንደሰጣት ለማጠየቅ የራሷ ያልሆነ ጸጉር (በአሁኑ አጠራር ዊግ ልንለው እንችላለን) አልብሶ ቀረጻት፡፡

  • ከፍ ያለ ስፍራ

አሰፋ 11፡00 ላይ ከቤት ወጥቶ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ተቀምጦ ልጅቷን (ቡዳ ነች የተባለችውን ወይኒቱ) እንዴት እንደሚያገኛት እና እንደሚያናግራት መፍትሄ ይፈልጋል፡፡ ደግሞ ይሰጋል ግን መወሰን ነበረበት እና ወሰነ፡፡

ደራሲው በዚህ የድርሰቱ ክፍል ሰው አዕምሮው ሲበስል፣ ሲሰለጥን፣ ከስሜታዊነት ሲያልፍ (9፡00 ሲያልፍ) በእውቀት ሲደረጅ (11፡00 ሲሆን) ከቤቱ ወጥቶ (ከዘልማዳዊ አስተሳሰቦች ወጥቶ)፣ በተማረው ትምህርት እና በቀሰመው እውቀት (ከፍታ ቦታ ላይ ተቀምጦ) ለአካባቢው፣ ለጎረቤቶቹ፣  ለቤተሰቦቹ፣  በአጠቃላይ ለሀገርም ጠቃሚ የሚሆን መፍትሄ ሀሳብ ማፍለቅ እንዳለበት፣ ነገሮችን ሁሉ በጥበብ መመርመር እንደሚያስፈልገው ይመክራል፡፡ የመማርም ገቢራዊ ትርጉሙ ይኸው ነው፡፡

ልማዳዊ አስተሳሰባቸው ልክ እንዳልሆነ እና ይልቁንም ተፋቅረው በሰላም መኖርን ሊሞክሩት እንደሚገባ ሊያስረዳቸው ሲፈልግ ደግሞ አሰፋ ፍቅሯን በዐይኗ የነገረችውን ወይኒቱን ሊያገኛት ይወስናል በብዙ ጥረትም በመጨረሻ ያገኛታል፡፡ ለዚያውም ከእናቱ ትእዛዝ (ልታገኛት እንዳትሞክር ከሚለው ተግሳጽ) አፈንግጦ ያገኛታል፡፡ በእርግጥ ያፈነገጠው ከአስተሳሰቧ እንጅ ከትእዛዟ አይደለም፡፡ ዕያየችው መሄድ አልፈለገም (ትእዛዟን ሲያከብር) ነገር ግን ተደብቆ በሌሊት አገኛት (አስተሳሰቧን ሲቃወም)፡፡ የማኅበረሰብን መልካም የሆነውን ወግ፣ ልማድ አና ሕግ ሳይጥሱ ጎጅ የሆነን አስተሳሰብ እንዴት መመርመር እንደሚገባ ጥበባዊ በሆነ መንገድ ያስረዳናል፡፡

  • ሐኪሞቹ

የሚገርመው ደግሞ የእነዚያ ወይኒቱን ያከሟት ሐኪሞች ነገር ነው፡፡ የወይኒቱ እናት በየጤና ተቋማቱ እየተንከራተተች ስለወይኒቱ ያማከረቻቸው ሐኪሞች ሁሉ የጤናዋን ምርመራ ከማድረግ ውጭ የወይኒቱን በእሳት የተቃጠለ ጸጉር አይመለከተንም ያሉ ይመስላሉ፡፡ እናቷ እያለቀሰች ለምናቸዋለች ግን ምንም መፍትሔ ሲሰጧት አልተመለከትንም፡፡

ለእነዚህ ሐኪሞች መማር ማለት በአንድ በተወሰነ የሙያ ዘርፍ (ለእነሱ ሕክምና) መሰልጠን እና ያንኑ መተግበር እንጅ አጠቃላይ ለሆነ ማኅበረሰባዊ ችግር እንደተማረ ሰው መፍትሔ መፈለግ ማለት አይደለም፡፡ በዚህም ደራሲው እንደ ነብይ አሁን ላይ ዕያየነው ያለውን ነገር ቀድሞ የተነበየ ይመስላል፡፡ ልክ ዛሬ ላይ የተማረ ከሚባለው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ እንደምንታዘበው ከሰለጠነበት የሙያ መስክ ለየት ያለን ማኅበረሰባዊ ችግር ለመፍታት የሚሆን የመፍትሔ ሃሳብ ለማፍለቅ እንደማይሞክር እና የሚመለከተውም እንደማይመስለው ይልቁንም ለዚህ ችግር ተብሎ የሰለጠነ ሌላ ሙያተኛን እንደሚጠብቅ ደራሲው ቀድሞ የተረዳ ይመስላል፡፡ የወይኒቱ እናት መጨረሻ ላይ ያገኘችው ሐኪምም እንኳን ቢሆን ያመጣው መፍትሄ ለጊዜው ጥሩ ቢመስልም የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ስለሆነ ወይኒቱን ከጥቃት ያላዳነ ይልቁንም ለባሰ መሰደቢያ የሆናት እና ለመገለሏ አንዱ ምክንያት የሆነ (በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ) በእውቀት ላይ ያልተመሰረተ መፍትሄ ነው፡፡ እንደተማረ አካል ለማኅበረሰብ ችግሮች የምንነድፋቸው የመፍትሔ አማራጮች ነባራዊ ሁኔታዎችን ያገናዘቡ፣ በተጠቃሚው ዘንድ የሚያመጡት ጥቅምና ጉዳት በደንብ የተጠና፣ ከጉዳታቸውም ጥቅማቸው ያመዘነ፣ ከጊዜያዊነት ይልቅ ዘለቄታዊ መፍትሄነታቸው የታሰበበት ሊሆኑ እንደሚገባ ያስተምራል፡፡

  • ባህል እና እምነት

በእርግጥ እንደዚህ ያሉ ከማኅበረሰቡ ባህል እና እምነት ጋር በጥብቅ የተሳሰሩ ችግሮችን (culturally deep rooted problems) ለመፍታት ብዙ ጊዜ ፈታኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህም ይመስላል አሰፋ ወይኒቱን ቀርቦ ለማናገር እና ችግሩን ለመመርመር ሁኔታውን በደንብ አጢኖ፣ ነገሮችን አውጥቶ አውርዶ፣… ከወስነ በኋላ እንኳን ከወይኒቱ ጋር አድሮ በተመለከተው ነገር ሲጠራጠር እናገኘዋለን፡፡ እውቀት አንዳንዴ በእምነት እና በወሬ ይፈተናል፡፡ እናቱ ያለችው ትዝ ይለዋል፡፡ ለአፍታም ቢሆን ያየው ነገር እናቱ ከነገረችው ቃል ጋር ተገናኝቶ በአእምሮው እያቃጨለ ተጠራጣሪ ያደርገዋል፡፡ እውነቱን ጠይቆ እስከሚረዳም ለአፍታም ቢሆን እናቱ ያለችውን የተሳሳተውን አስተሳሰብ ወደመቀበል ማዘንበሉ ባህል፣ እምነት (Blief) እና ወሬ ምን ያክል የሰውን ልጅ ስነ-ልቡና ሊቆጣጠሩ እንደሚችሉ ያስረዳል (ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው እንዲሉ)፡፡

አሰፋ ተምሯል (ስለ ሳይንስም ሆነ ስለ ሃይማኖት በተወሰነ ደረጃ ያውቃል፣ ከሳይንስም ከሀይማኖት አስተምህሮም ለእናቱ ሲጠቅስ እናነባለንና)፤ ነገር ግን ያየው እና እውነት የመሰለው ነገር (የወይኒቱ በሌሊት ከቤት ውጭ ቆይቶ መግባት እና የጸጉሯን ‹ዊግ› ከራሷ ላይ አንስታ አስቀምጣው ማየቱ) የሚያውቀውን ሀቅ ጋረደበት፡፡ ቢሆንም ቀስ በቀስ ወይኒቱን እየጠየቀ እውነቱን ተረዳ፣ እውቀቱን ወደ ማረጋገጥ ደረሰ፣ የተረጋገጠ እና በተግባር የተፈተነ እውቀት (Experimentally tested and approved knowledge, if not wisdom [since the ways he followed to verify his assumptions are clearly visible and valid])  ይሉሻል ይሄ ነው፡፡ የደራሲው መጠራጠር እውነትን ለመመርመር መነሻ እንደሆነ የሚናገረውን ሳይንስ በአሰፋ ለመግለጽ የሞከረ ይመስላል፡፡ ነገር ግን እዚህ እውቀት ላይ ለመድረስ የምናጠፋው ነገር ብዙ ነው፡፡ አሰፋ መጠራጠሩ ብቻ ሳይሆን ወይኒቱን ልክ ሌሎች የአካባቢው ሰዎች እንደሚሰድቧት አግላይ ስድብ ሰድቧታል (ቡዳ ነሽ ብሏታል)፡፡ የወይኑ ልብ ምን ያክል ተጎድቶ ሊሆን እንደሚችል ማሰብ አይከብድም፡፡ ከሰዎች ያለማወቅ ማግለልና ስድብ የአሰፋ ከመጠራጠር የመጣ ስድብ ይከፋል፡፡ አፈቅርሻለሁ ብሎ ቀርቦ ማድማት፣ የእኔ በሚሉት ሰው መገፋት የበለጠ ያማልና፡፡

አሰፋ ወይኒቱን ጠይቆ የተረዳውን ነገር፣ ፈጥኖ ያወቀውን እውነታ ለሌሎች ሲያደርስ አንመለከትም፡፡ ለምን? ምክንያቱም አንድም የአጭር ልብ ወለድ ጸባዩ መስለኛል፣ አንድም ጸሐፊው ሰዎች የሰጡኝ አስተያየት ነው ብሎ በሁለተኛው መጽሐፉ መቅድም ላይ እንደገለጸው መልእከቱን ቆርጦታል (“አጠር-አይ! አይ ታደሰ፤-ምነው ትንሽ ቢያስረዝመው! ታደሰን ጠላሁት ታሪኩን ከመሀል ቆረጠው”)፡፡ ደራሲው ታደሰ ሊበን እያንዳንዱ ሰው (በተለይ የተማረ እና ሰለጠንኩ የሚለው ሰው ሁሉ) እንደነዚህ ያሉ እውነታዎችን በነፍስ ወከፍ መርምሮ እንዲያውቅ እንጅ አንዱ ያወቀውን እውነታ ለሌሎች በማካፈል የሚገኘው እውቀት ግድ የሰጠው አይመስልም፡፡ ምናልባት እንደዚህ ርእሰ ጉዳይ ያሉ በጣም ስስ እና አይነኬ የሚመስሉ የማኅበረሰብ ጉዳዮችን (socially or culturally very sensitive issues) በጠቀስነው ዐይነት እውቀትን የማካፈል ሁኔታ በቀላሉ መፍታት እንደማይቻል ተረድቶ ይሆን፣ ልክ አሰፋ ለእናቱ እና ለእህቱ ሊያስረዳቸው ሲሞክር እንዳልተቀበሉትና ለእነሱ እውነት በመሰላቸው ነገር (pseudo-facts) እንደሞገቱት፡፡ ወይም ደግሞ ታደሰን ትኩረቱን የሳበው ነገር ከምርምር ወይም እውቀት በኋላ ያለው የእውቀት ሽግግር (Knowledge dissemination) ሳይሆን (ተቀባይ ከተገኘ፣ ሰሚ ልቡናውን ከከፈተ ማስረዳቱ ባይከፋም) ልንመረምረው የሚገባን፣ ጥርጣሬ ውስጥ የሚከተን ርእሰ ጉዳይ መኖሩ ሊሆን ይችላል፡፡

ሰዎች ወይኒቱን ለመጠራጠራቸው እና ለማግለላቸው አስረጅ አድርገው ያቀረቡት እና ወደያዙት አቋም ያደረሳቸው የወይኒቱ ከአካባቢው ሰዎች የተለየ ጸጉር (ከእራሷ ላይ የሚነሳ ዊግ) እና ማታ ማታ ጅብ ትሆናለች (ለክፋቱ አንድ ቀን በምሽት ከቤቷ ውጭ አይተዋታል- በጨለማ ደግሞ ሁሉም ነገር ዛፉም ተራራውም እንኳን ሳይቀር አውሬ ይመስላልና) የሚለውን መከራከሪያ ነው፡፡ በሰዎቹ ቦታ ሆነን ስንመለከተው ያዩነት ነገር እና ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ትርክት ተደምሮ የያዙትን አቋም እውነት የሚያስመስል እና በየዋሃን ዘንድ ቅቡልነት ያለው ነው፡፡ አሰፋ ግን ይህን በዋዛ አላለፈውም (እውነት የሚመስልን ሀሰት ነገር መረጃን ተመርኩዞ ይመረምራል-ሀሰትን እውነት ለማስመሰል የቀረበን መረጃ መርምሮ ለተቃራኒ አቋም ማስረጃ አድርጎ ማቅረብ ይቻላልና- If the null hypothesis is rejected the alternative hypothesis will be accepted as true የምትለዋን እዚህ ላይ ልብ ይሏል)፡፡ ስለዚህ አሰፋ የጸጉሯንም ሆነ በሌሊት ከቤት የመውጣቷን ሚስጥር እስከ ስረ መሰረታቸው መረመረ፡፡

እውነታ የሚመስልን ነገር መርምሮ እውነታው ሌላ መሆኑን ማወቅ ገለባውን ከላይ አንስቶ ምርቱን እንደማጥራት ነው፡፡ ከላይ ሲታይ ገለባ ይመስላል ውስጡ ግን ምርት ነው፡፡ አሁን አሰፋ መርምሮ በደረሰበት እውነታ ማኅበረሰቡ እውነት ነው ብሎ ለያዘው አቋም አስረጅ አድርጎ የሚያቀርባቸው፣ በህዝቡ ዕይታ ከላይ ከላይ ሲታዩ እውነት የሚመስሉ ነገሮች በሚገባ ሲፈተሹ አውነት አለመሆናቸውን እና እውነታው ሌላ መሆኑን ነው፡፡ በመጠኑም ቢሆን ከዚህ በኋላ መሞገት እና ማስረዳት ከበፊቱ (ልክ አሰፋ እናቱን እና እህቱን ሲከራከር ያስረዳበት ከነበረው መንገድ… ሳይንስን ሳይንስ ለማያውቅ ሰው ከማስረዳት እና የሃይማኖት አስተምህሮን ስለሐይማኖት አስተመህሮ ከአንተ የተሻለ አውቃለሁ ሊለን ለሚችል ሰው መጥቀስ) የተሻለ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህም ይመስላል ደራሲው የማኅበረሰብን ንቃተ ህሊና ለመጨመር እና ከጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች ለማላቀቅ የበለጠ ወሳኙ ነገር የተረዳነው እውነት እና እውቀት ብቻ ሳይሆን እውነታው ላይ ለመድረስ የምንመርጠው መንገድ መሆኑን ለማሳየት ትኩረቱን የአሰፋ የምርምር ሂደት ላይ አድርጎ ከምርምሩ በኋላ አሰፋ እውነታው ላይ ሲደርስ ትረካውን የሚያቆመው፡፡

ማጠቃለያ

ይህ ድርሰት ብዙ ሊያስብል ቢችልም፤ ሐሳቤን ለማጠቃለል ያክል ታደሰ ቢያንስ በሁለት ነገር ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ የመጀመሪያው እና ዋናው ነገር በተለያዩ አጋጣሚወች እንዲሁ አልፎ አልፎ እየተነሱ የማኅበረሰቡ የመወያያ ርእሰ ጉዳይ ከመሆን የዘለለ በጽሁፍ ደረጃ ብዙም ትኩረት የማይሰጣቸው (ይህን ርእሰ ጉዳይ በተመለከተ በጥልቀትም ባይሆን እንዲሁ በተለያየ ደረጃ ያነሱ ከ2 እና 3 ያልበለጡ ጽሁፎችን የማንበብ ዕድል ገጥሞኛል -ወጥነት ባይኖራቸውም) ከሆኑ የማኅበረሰብ ጉዳዮች አንዱን ደፋር እና ጠንከር ብሎ በማንሳት ፈር ቀዳጅ ሊሆን ስለሚችል፡፡ ታደሰ ይህን ልብ ወለድ በጻፈበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ዘመንም ቢሆን የተማረ የሚባለው የማኅበረሰባችን ክፍል እንደዚህ ዓይነት ርዕሰ ጉዳዮችን አንስቶ በግልጽ የመወያየት፣ የመመራመር እና መልሶ ማኅበረሰብን የማንቃት ስራ ሲሰራ ብዙም አይታይምና፡፡

ሁለተኛው ደራሲው የሚመሰገንበት ጉዳይ ደግሞ እንደዚህ ያሉ ችግሮችን ለመመርመር እና ለመፍታት የሚያስብ ሰው ሁሉ በምን ዓይነት ብስለት እና ጥንቃቄ (በተለይም የስነ-ጽሑፍ እና ስነ-ሂስ እውቀቱ እና ልምዱ ያላቸው ባለሙያወች የበለጠ ሊያብራሩት ይችላሉ) መጓዝ እንዳለበት አጠር ባለ ግን በጣም ረቂቅ በሆነ መንገድ ስላስረዳ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ እንዲሁ ዝግጅት ሳይደረግ ያለጥንቃቄ ቢገባበት ምን ዓይነት ችግሮች እና መቋቋሞች ከማኅበረሰቡም ሆነ ከሚያየውና ከሚሰማው የተነሳ የሚከሰት የራሱ ውስጣዊ መታወክ ሊገጥመው እንደሚችል ለማስረዳት ሞክሯል፡፡ ይህ በጣም መልካም የሆነ የደራሲው አበርክቶት ልብ ወለድን እንዲሁ ማንበብ ለሚፈልጉ ብቻ ሳይሆን ለማኅበረሰብ ተመራማሪዎችም መንገድን አመላካች የሆነ ስራ ይመስለገኛል፡፡ ስለዚህ ያስመሰግነዋል፡፡

ይህ የእኔ ዕይታ ነው፡፡ በተረፈ ግን ይህች አጭር እይታዬ የሌሎችን ሃሳብ የመቀስቀስ ጉልበት አግኝታ ሌሎች የመጽሔቷ ደንበኞችም የበለጠ ሃሳባቸውን ቢገልጹ እና የውይይት መድረኮች ቢከፈቱ ለተሻለ የጋራ ግንዛቤ እና መነሳሳት በር ትከፍታለች የሚል እምነት አለኝ፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top